በዚህ ዓምድ ለአንባብያን ጥያቄዎች ምላሾች ይሰጣሉ
ጥያቄ፡- ከቀሲስ ወልዱ አስተርአየ
1ኛ.
ጮራዎች ሐመር የተባለው የማኅበረ ቅዱሳን ልሳን የሆነው መጽሔት በጥርና በየካቲት 2003 ዓ.ም. ዕትሞቹ ላይ፥ “ቅዱስ ዮሐንስ
አፈ ወርቅና የ‘ተሐድሶዎች’ ቅሰጣ” በሚል ርእስ ተከታታይ ጽሑፎችን አስነብቧል።
በጽሑፎቹም እናንተ የዮሐንስ አፈ ወርቅን ትምህርት መጥቀሳችሁን ኰንኖ፥ እናንተና እርሱ በትምህርት አለመመሳሰላችሁን፥ እርሱን አባታችን
እያላችሁ የምትጠቅሱትም ለማደናገር እንጂ በትክክል ልጆቹ አለመሆናችሁን በስፋት ዐትቷል። ለዚህም ያሳይልኛል ያለውን ማሰረጃ ከድርሳኑ
ጠቅሶ ትንታኔ ሰጥቷል። በዚህ ጕዳይ ላይ ምን ምላሽ አላችሁ?
2ኛ.
ይኸው ማኅበር “የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ” በሚል ርእስ ባሳተመው መጽሐፍ ገጽ 67 ላይ ታላቁንና
በብዙ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ዘንድ አንቱ የተባሉትን ስመ ጥር ሊቅ አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብን “አንተ” እያለ በማንኳሰስ
ጽፏል። በዚህ ላይ አንድ ነገር ብትሉ መልካም ነው።
1ኛ መልስ፡- በመምህርት
ሲያዴ
በቅድሚያ ቀሲስ ወልዱን ስለ ጥያቄዎ ከልብ እናመሰግናለን።
እርስዎ የጠቀሷቸውን መጽሔቶች ተመልክተናቸዋል። ከጥንት ጀምሮ ሐሰተኞች እውነተኞች ነን በሚል፥ የእውነተኞችን ጩኸት እየቀሙ እውነተኞችን
ሐሰተኞች ሲሉና ሲያሰኙ ኖረዋል፤ ዛሬም ይኸው አካሄድ እንደ ቀጠለ ነው።
የክርስትና መመሪያ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚመሰክረው፥
ሁላችንም አንድ አባት አለን፤ እርሱም የሁላችን ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው (ሚል. 2፥10)። ከእርሱ በቀር ሌላ አባት ስለሌለም ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ ሲል አስተምሮናል (ማቴ. 23፥9)። ለእኛ የእግዚአብሔር አባትነት
ከበቂ በላይ ነው። ይሁን እንጂ የእግዚአብሔርን አባትነት በማይጋፋ መንገድ በሥጋ የወለዱንን፣ ትምህርት ያስተማሩንን፣ በዕድሜ የሸመገሉትን፣
በማዕርግ የላቁትን ወዘተ. ሁሉ አባት ብለን እንጠራለን። ዮሐንስ አፈ ወርቅን አባታችን ብለን የምንጠራውም በዚሁ መንገድ እንጂ፥
የእግዚአብሔርን አባትነት በሚጋፋ፥ ወይም ከዮሐንስ አፈ ወርቅ የምንካፈለው ርስት ኖሮ፥ ወይም ሌላ ትርፍ ለማግኘት አይደለም።
ማኅበረ ቅዱሳን ዮሐንስ አፈ ወርቅን አባታችን የሚልበት
ምክንያት በትምህርት እወለደዋለሁ ብሎ ይሆናል። እኛም እርሱን አባታችን የምንለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነው ትምህርቱ ከእርሱ ጋር
ስለምንስማማ እንጂ በሌላ አይደለም። እንዲህ ከሆነ እውን ዮሐንስ አፈ ወርቅ አባት ሊሆን የሚችለው ለማን ነው? የሚለውን ጥያቄ
እኛም ደግመን መጠየቅ እንወዳለን።
ሐመር መጽሔት ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለእናንተ አባታችሁ አይደለም
ሲል የጠቀሰው ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ የተባለውን የትርጕም ትርጕም ትርጕም መጽሐፍ ነው። በዚህ ከውጭ ቋንቋ ወደ ግእዝ በተመለሰው
ድርሳን፥ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የዕብራውያንን መልእክት ተርጕሟል። ይህን የእርሱን ትርጕም እንዳለ ወደ ግእዝ መመለስ አንድ ነገር
ነው፤ ነገር ግን የአገራችን ሊቃውንት ግእዙን በአንድምታ የትርጓሜ ስልት እንደ ገና የትርጕም ትርጕም ሠርተዉለታል። እንዲህ ሲያደርጉ
ዐላማቸው፥ የዮሐንስ አፈ ወርቅን ትርጓሜ ይበልጥ ለማብራራት ይሁን፥ ወይም የዕብራውያንን መልእክት ለማደብዘዝ ጕዳዩ መፈተሽ አለበት።
የማኅበረ ቅዱሳን ልሳን የሆነው ሐመር መጽሔት ዮሐንስ
አፈ ወርቅን እኛ ነን እንጂ እናንተ አትወለዱትም ሲል ማስረጃ አድርጎ ያቀረበው፥ በተለይ ‘ሊቀ ካህናት ሲል ብትሰማው ዘወትር የሚያገለግል
አይምሰልህ፤ ባገለገለ ጊዜ በማገልገል ሥራ ጸንቶ አልቆመም’ የሚለውን ክፍል ነው (13ኛ ድርሳን ገጽ 260)። መጽሔቱ ይህን ሲያብራራ፥
“ለጌታችን ምልጃ ሰው በመሆኑ በትሕትና ለሰው ተገብቶ የሠራው ‘የተዋርዶ’ /ራስን ዝቅ የማድረግ ሥራ ነበርና ከትንሣኤው በኋላ
ግን ይህንን የምልጃና የመሳሰሉትን ሰው በመሆኑ የሠራቸውን ሥራዎች እንደማይቀጥልበት” ያስረዳል የሚል የራሱን ትርጓሜ ይሰጣል (ሐመር
የካቲት 2003፣ 18)። ለክርስቶስ አምላክነት የቀና በመምሰልም “ሲያገለግል መኖር ከባሕርይ አምላክነት ያሳንሳል” ይላል። እንደ
ገናም “ጌታችን ‘አንድ ጊዜ’ አስታረቀን[፤] በእርሱም ሥራ /አንዴ በሠራልን/ ወደ አብ መግባት አለን እንላለን” ካለ በኋላ፥
ይህን አፍርሶ ኢየሱስ በማስታረቅ ሥራው እንዳልቀጠለና የዕርቅ ሥራውን ለቅዱሳን እንዳስተላለፈ ጽፏል (ገጽ 20)። ይህም ገለጻ
በክርስቶስ ሥራ ወደ አብ መግባት ከተቻለ ሌላ አስታራቂ ለምን አስፈለገ? የሚል ጥያቄን ያስነሣል።
ይህ ሁሉ ድካም የዕብራውያንን መልእክት ይበልጥ ለማስተዋል
አይደለም፤ የዮሐንስ አፈ ወርቅን ትርጓሜ ለመቀበልም አይደለም፤ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ጥብቅና የቆመ መስሎ የእርሱን
የመካከለኛት ስፍራ ለቅዱሳን ለመስጠት ነው እንጂ።
ይህ የማኅበረ ቅዱሳን ትርጕም ነው፤ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
ከላይ የተጠቀሰውን ቃል የተናገረው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት ዘወትር የሚያገለግል አለመሆኑንና አንድ
ጊዜ ባቀረበው ምልጃና መሥዋዕት ዘወትር የሚያድን ስለ ሆነ በሁሉ ነገር ብልጫ ያለው ሊቀ ካህናት መሆኑን ለመግለጽ ነው። የሐሳቡ
መነሻም ሐመር መዝዞ ያወጣው ሐረግ ሳይሆን የሚከተለው ነው፤
“አኮ ውእቱሰ ዘይፈቅድ በኵሉ ዕለት ከመ ሊቀ ካህናት
ዘያበውእ መሥዋዕተ በእንተ ኀጢአቱ፤ ወእምዝ በእንተ ኀጢአተ ሕዝብ። ውእቱሰ ከመዝ ገብረ በምዕር ሦዐ ርእሶ። ናሁኬ ተዐውቀ በዝየ
ክብረ መሥዋዕት መንፈሳዊት፣ ወፍልጠተ ካህን፣ ወሃይማኖት፣ ወፍልጠተ ሕግ።
ትርጓሜ፡-
እርሱ እንደ ብሉዩ ሊቀ ካህናት ስለ ኀጢአቱ፥ ከዚያ ስለ ሕዝቡ ኀጢአት በየዕለቱ መሥዋዕት ማቅረብ የሚፈልግ አይደለም፤ አንድ ጊዜ
ራሱን [ስለ ሕዝቡ ኀጢአት] በመሠዋት ይህን አከናውኗል። እነሆ በዚህም የመንፈሳዊት
መሥዋዕቱ ክብር፣ የሊቀ ካህናቱ ብልጫ፣ የእምነትና የሕጉ መለየትም ታውቋል” (13ኛ ድርሳን ቊጥር 178-183)።
በእነዚህ ቊጥሮች ውስጥ ዋናው ማነጻጸሪያ የብሉይ ኪዳን
ሊቀ ካህናት ዘወትር ያገለግል ነበር። የሐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እንደርሱ ዘወትር መሥዋዕት በመሠዋትና ምልጃ
በማቅረብ አያገለግልም፤ አንድ ጊዜ ባቀረበው ምልጃና መሥዋዕት ለሁል ጊዜም ያስታርቃል፤ ያድናል፤ በሁሉ ነገርም ይበልጣል የሚል
ነው።
ዮሐንስ አፈ ወርቅ የተረጐመው የዕብራውያንን መልእክት
እንደ መሆኑ በትርጓሜው ሊያስረዳ የሚችለው የኢየሱስ ክርስቶስን የዐዲስ ኪዳን መካከለኛነት ነው። እርሱም በዚሁ ላይ ነው ያተኰረው።
የማኅበረ ቅዱሳኑ ሐመር መጽሔት ግን ሊቁ በስፋት የተናገረበትን የክርስቶስን መካከለኛነት ወደ ገደል ጨምሮ፥ ለራሱ የሚስማማ የመሰለውን
ሐረግ መዝዞ በማውጣት መልእክቱን የማዛባት ሥራ ነው የሠራው። ደርሶ አባቴ ነው በማለት ልጅነት ይገኝ ይመስል ማኅበረ ቅዱሳን ተሸቀዳድሞ
ዮሐንስ አፈ ወርቅን አባቴ ነው ይበል እንጂ፥ እንኳ በትምህርት ሊወለደው እንዳልተጐራበተውም ገልጧል። ይህን በማስረጃ አስደግፈን
ከዚህ ቀጥሎ እናሳያለን፤
·
“ወዘይቤሂ ጳውሎስ ይተነብል በእንቲኣነ ዝኒ እስመ ሊቀ ካህናት ይተነብል። … ይቤ እስመ ይክል አድኅኖቶሙ
ለዝሉፉ እስመ ሕያው ውእቱ ለዓለም ወአልቦ ተውላጥ እምድኅሬሁ ወእመሰ ኮነ ዘአልቦ ተውላጥ ናሁኬ ይትከሀሎ ይስፍን ላዕለ ኵሉ።
ወበዝየሰ ለእመ ኮነ ሊቀ ካህናት ዐቢይ ውእቱኬ እስከ ጊዜሁ ዘአመኮነ ሳሙኤል ወእለ ከማሁ በደኃሪሰ አልቦ እስመ እሙንቱ ሞቱ።
ወበዝየሰ አኮ ከማሁ፤ አላ ዘልፈ ያድኅን በኵሉ ጊዜ። … ወከማሁ ውእቱ አኮ ዘያድኅኖሙ ለእለ ይቀርቡ ኀበ እግዚአብሔር ባሕቲቱ
እመንገሌሁ በዝየ አላ ወበከሃከኒ።
ትርጓሜ፥
“ስለ እኛ ይማልዳል በማለት ጳውሎስ የተናገረው ይህ ነገር፥ ሊቀ ካህናት ስለሚማልድ ነው፤ … ለዘወትር ያድናቸው ዘንድ ይችላል
አለ፤ እርሱ ሕያው ነውና፤ ከእርሱ በኋላ የሚተካ የለም። ተኪ የሌለው ከሆነም በሁሉ ላይ ገዥ ሊሆን ይችላል። በዚህኛው (በብሉይ
ኪዳን) ታላቅ ሊቀ ካህናት ቢኖር ታላቅ መባሉ እስከ ጊዜው ድረስ ነው። ሳሙኤል እስከ ጊዜው ድረስ እንደ ኖረ እንደርሱ ያሉትም
ካህናት እስከ ጊዜው ድረስ እንደ ኖሩ፥ በኋላ ግን ታላቅ ሊቀ ካህናት መባላቸው የለም፤ ቀርቷል። በዚህኛው በዐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት
(በኢየሱስ ክርስቶስ) ግን እንደዚሁ አይደለም። ሁል ጊዜ ለዘላለም ያድናል እንጂ፤ በእርሱ አስታራቂነት በኩል ወደ እግዚአብሔር
የሚቀርቡትን የሚያድናቸውም በዕለተ አርብ ብቻ አይደለም፤ ከዚያም በኋላ ባለው ጊዜ ለዘላለምም ነው እንጂ” (ድርሳን 13 ቊጥር
138-144፡ 147-148)።
በዚህ ትምህርቱ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ
ሊቀ ካህናት በመሆኑ እንደሚማልድና የሚተካው የሌለ ብቸኛ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ እንደ ሆነ፥ መካከለኛነቱም አንድ ጊዜ ለዘለዓለም
ባቀረበው ምልጃና መሥዋዕት አማካይነት በዕለተ አርብ ብቻ ሳይሆን፥ ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ እስከ ዘላለም ድረስ የሚቀጥል በመሆኑ
ዛሬም መካከለኛችን እርሱ ብቻ መሆኑን አብራርቷል። ታዲያ ዮሐንስ አፈ ወርቅ አባት ሊሆን የሚችለው በተዛባ አተረጓጐም ላይ ተመሥርቶ፥
ዛሬ እርሱ አስታራቂ አይደለም፤ የአስታራቂነቱን ስፍራ ለቅዱሳን አስረክቧል ላለው ለማኅበረ ቅዱሳን፥ በተጨማሪም ዮሐንስ አፈ ወርቅ
“ይተነብል - ይማልዳል” ያለውን ቀጥተኛ ንባብ “ተንበለ - ማለደ” ተብሎ ለራስ አስተምህሮ በሚስማማ መንገድ ተዛብቶ የተተረጐመውን
ትርጓሜ ይዞ ለነጐደውና የኢየሱስ ክርስቶስን መካከለኛነት ያለፈ ድርጊት አድርጎ ለሚያቀርበው ለማኅበረ ቅዱሳን ነው ወይስ ለእኛ?
በሌላውም ትምህርት ቢሆን ዮሐንስ አፈ ወርቅ አባት ሊሆን
የሚችለው ለእኛ እንጂ ለማኅበረ ቅዱሳን አለመሆኑን የሚከተሉት ትምህርቶቹ ምስክሮች ናቸው።
·
“ሶበሰ ኢሀሎ ብሉይ ሕግ እምኢይቤ እሠርዕ ሎሙ ሕገ ሐዲሰ አጠየቀ ከመ ተአተተ አሐዱ ወተርፈ ካልኡ ህየንተ
ዘተአተተ በከመ ቤት ብሉይ ሶበ ይወድቅ ይገድፍ ብእሲ ኵሎ ዘወድቀ ወይትመየጥ ይሕንጽ መሠረተ ወንሕነኒ ንብል ይእዜ ከመ ውእቱ
ሐደሶ ወቦ ዘገደፈ እምኔሁ ወቦ ዘኀደገ።
ትርጓሜ፡-
“አሮጌው ሕግ (ብሉይ ኪዳን) ያለፈ ባይሆን ኖሮ ዐዲስ ሕግ (ሐዲስ ኪዳንን) እሠራላቸዋለሁ ባላለም ነበር። እንግዲህ እንዲህ በማለቱ፥
ብሉይ ኪዳን እንደ ተወገደና በተወገደው ምትክ ዐዲስ ኪዳን እንደ ጸና አስረዳ። ያረጀ ቤት በፈረሰ ጊዜ የወደቀውን ሁሉ በመተው
መሠረቱን እንደሚያድስ እኛም ሕጉን ዐደሰው እንላለን። ከሕጉ የጣለው አለ። የተወውም አለ” (ድርሳን 14 ቊጥር 150-153)።
·
“ብፁዕ ጳውሎስ ናሁ ከሠተ ይእዜ ከመ ሐዳስ ሕግ ትኄይስ እምሕግ ብሊት … እስመ አልቦ ውስተ ሐዳስ ሕግ ምንትኒ
ሥርዐተ ሥጋ ወኢግብረ ትእዛዝ፣ ኢምኵራብ፣ ወኢቅድስተ ቅዱሳን፣ ኢካህን ዘከመዝ ሥርዐተ ክህነቱ፣ ወኢትእዛዘ ኦሪት ዘይትዐቀብ በከርሠ
ታቦት አላ ኵሉ ትእዛዛቲሁ ሉዓላዊ ወአልቦ ውስቴቱ ምንትኒ ሕገ ሥጋ አላ መንፈሳዊ ኵለንታሁ።
ትርጓሜ፡-
“ብፁዕ ጳውሎስ እነሆ አሁን ዐዲሲቱ ሕግ ከዐሮጌዋ ሕግ እንደምትሻል አስረዳ። በወንጌል ምንም ምን የሥጋ ሥርዐት የለምና፤ የትእዛዝ
ሥራ የለም፤ ምኵራብ የለም፤ ቅድስተ ቅዱሳን የለም፤ የክህነቱ ሥርዐት እንደ ኦሪቱ የሆነ ካህንም የለም፤ በድንጋይ ጽላት ተጽፎ
በታቦቱ ውስጥ ተቀምጦ የሚጠበቅ የኦሪት ትእዛዝም የለም፤ ሥርዐቱ ሁሉ ሰማያዊና ፍጹም ነው እንጂ። በውስጡም የሥጋ ሕግ ምንም ምን
የለም፤ ሁለንተናው መንፈሳዊ የሆነ ሕግ ነው እንጂ” (ድርሳን 8 ቊጥር 2፡5-12)።
·
“ወሐዋርያትሰ ኢነሥኡ ምንተኒ ወኢተወፈዩ ዘተጽሕፈ በረቅ አላ ተወክፉ በሰሌዳ ልቦሙ ሀብተ መንፈስ ቅዱስ
-
ትርጓሜ፡-
“ሐዋርያት ግን በብራና የተጻፈ ሕግ አልተቀበሉም፤ የመንፈስ ቅዱስን ሀብት በልቡናቸው ሰሌዳነት ተቀበሉ እንጂ” (ድርሳን 14 ቊጥር
140-141)።
ዮሐንስ አፈ ወርቅ ብሉይ ኪዳን በሐዲስ ኪዳን መተካቱን፣
ከጸኑት ዐሥሩ ትእዛዛት በቀር ከብሉይ ኪዳን ወደ ዐዲስ ኪዳን የተሻገረና ‘ክርስቲያናዊ ትርጕም ተሰጥቶት’ አገልግሎቱ የቀጠለ አንድም
ነገር አለመኖሩን ተናግሯል። ብሉይን ከሐዲስ ደባልቆና “በክርስትና መንፈስ ተርጕሞ” የሚመራበት ማኅበረ ቅዱሳን ዮሐንስ አፈ ወርቅን
አባቴ ለማለት የደፈረው ይህን ትምህርቱን አምኖበትና ተቀብሎት ነው ወይስ በስሙ ለመነገድ ብቻ ፈልጎ?
·
“ወበከመ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞተ በተሰቅሎ ከማሁ ንሕነኒ በጥምቀት ወአኮ በሥጋ አላ እምገቢረ ኀጢአት።
ነጽር ኦ! ፍቁር ኀበ ሥርዐተ ሞት ውእቱሰ ሞተ በሥጋነ ዘብእሲ ብሉይ ወተንሥአ በሐዲስ አርኣያ ዘኢይደሉ ለሞቱ እንከሰኬ ይትፈቀድ
በግብር ከመ ይጠመቁ በማየ ጥምቀት ውእቱ ዘያኤምር ኀበ ሞቱ እስመ ተጠምቆ ኢኮነ ካልኣ ግብሩ አላ ያኤምር ኀበ አሚኖቱ ለዘተጠምቀ
ወኀበ ሞቱ ወተንሥኦቱ።”
ትርጓሜ፡-
“ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል እንደ ሞተ እንዲሁ እኛ በጥምቀት ሞትን፤ ሞትን ስንል ግን በሥጋ ሳይሆን ኀጢአትን ከመሥራት
ነው። ወዳጅ ሆይ! ወደ ሞቱ ሥርዐት ተመልከት፤ እርሱ ግን ሥጋችን በሚሆን በአሮጌው ሰውነት ሞቶ፥ ለሞት ተገቢ በማይሆን በዐዲስ
አርኣያ ተነሣ፤ እንኪያስ መሞቱን አመልካች በሚሆን በውሃ ጥምቀት ይጠመቁ ዘንድ ይገባል፤ የመጠመቅ ተግባርም የሚጠመቀው ሰው እምነቱን
ወደ ሞቱና መነሣቱ እንዲያደርግ አመልካች ነው እንጂ ከዚህ ሌላ አይደለምና” (ድርሳን 9 ቊጥር 203-212)።
·
“እመቦ ዘይብል አኮኑ ንሕነ ናዐርግ መሥዋዕተ ኵሎ ዕለተ ንብሎ ንሠውዕ ለተዝካረ ሞቱ ለልዑል መሥዋዕት አሐተ
ወአኮ ብዙኀ።
ትርጓሜ፡-
እኛስ በየዕለቱ ሁሉ መሥዋዕት እንሠዋ የለምን የሚል ሰው ቢኖር እኛስ ለልዑል ጌታ ለሞቱ መታሰቢያ እንሠዋለን እንለዋለን” (ድርሳን
17 ቊጥር 121-122)።
በእነዚህ ጥቅሶች መሠረት ዮሐንስ አፈ ወርቅ የጥምቀትንና
የቅዱስ ቊርባንን አስፈላጊነትና ዐላማ አብራርቷል። ጥምቀት ተጠማቂው እምነቱን ወደ ጌታ ሞትና ትንሣኤ እንዲያደርግ የሚያመለክት
ሲሆን፥ ቅዱስ ቊርባን ደግሞ ለጌታ ሞት መታሰቢያ መሆኑን ተናግሯል። ማኅበረ ቅዱሳን ዮሐንስ አፈ ወርቅን አባቴ ሲል ይህን ትምህርቱን
አስተባብሎት ነው ወይስ ተቀብሎት?
ሌላም ብዙ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል፤ ለጊዜው ግን የማኅበረ
ቅዱሳን አስተምህሮ ከጥንታውያን አበው ትምህርት ጋር በፍጹም የማይመሳሰል፥ ኢኦርቶዶክሳዊ ትምህርት መሆኑን እስካሁን የቀረቡት ማስረጃዎች
ይመስክራሉ። ውላጅ የቤት ውልድ ሁሉ ተነሥቶ ልጅ ነኝ ቢል፥ ሰሚም ተቀባይም አያገኝም፤ እንደ እውነተኛ ልጅ አፉን ሞልቶ የመናገር
መብትም የለውም። ዮሐንስ አፈ ወርቅን መጠየቅ ቢቻልና እውን ማኅበረ ቅዱሳን ከሚያስተላልፈው ትምህርት አንጻር ትምህርትህን የሚከተል፥
ከትምህርትህ የተወለደ ስብስብ ነውን ተብሎ ቢጠየቅ፥ “ያልወለድሁት ልጅ አባ አባ ቢለኝ አፌን ዳባ ዳባ አለኝ” በሚለው ብሂል ምላሽ
እንደሚሰጥ አያጠራጥርም።
2ኛ. መልስ
የጮራ መጽሔት ዋና አዘጋጅ የነበሩትን አለቃ መሠረትን
የሚያውቅ ያውቃቸዋል፤ እርሳቸውን “አንተ” ማለት የሚያዋርደው እርሳቸውን ሳይሆን አንተ ባዩን ክፍል ነው። እንዲህ ላለው አባት
አዋራጅ ስብስብ ምላሽ መስጠት ራስን ያስገምታልና፥ የምሕረት አምላክ እግዚአብሔር ማስተዋልን እንዲሰጣቸው በመለመን ምላሹን በዚሁ
ዐልፈነዋል።
በጮራ ቍጥር 41 ለይ የቀረበ
No comments:
Post a Comment