Sunday, October 25, 2015

" ... የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ ..." (ኢሳ. 60፥14)

“ወይመጽኡ ኀቤኪ እንዘ ይፈርሑ ወያመጽኡ አምኀ ደቂቆሙ እልኩ እለ አምዕዑኪ ወይሰግዱ ቅድመ መከየደ እግርኪ ወትሰመዪ ሀገረ እግዚአብሔር ቅዱሰ እስራኤል ጽዮን - የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፥ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእግዚአብሔርም ከተማ፥ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል” (ኢሳ. 60፥14)።?
ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል የሚል ፍልስፍና ያላቸው ወገኖች አሉ። እንዲህ ለማለት ያበቃቸው በተደጋጋሚ የሚያቀርቡትን ውሸት፥ ሰዎች እውነት ነው ብለው የተቀበሏቸው ስለ መሰላቸው ነው።  ውሸት፥ ውሸት ነው፤ እውነት ደግሞ እውነት ነው። ዐሥር ወንፊት ቢደራረብ አንድ ብልቃጥ ውሃ መያዝ እንደማይችል ሁሉ፥ ውሸት የቱንም ያህል የእውነት ጠብታ ቢጨመርበት ድምር ውጤቱ ውሸት ነው ውሸት በምንም ተኣምር ወደ እውነትነት የሚለወጥበት ዕድል ከቶ የለም፤ አለ ከተባለ ግን እውነትን አለማወቅ፣ እውነትን ማራከስና ዋጋ ማሳጣት ይሆናል። ስለዚህ ውሸት ሲደጋግም እውነት ይመስላል እንጂ እውነት ሊሆን በፍጹም አይችልም።
ኢሳ. 60፥14 ስለ ማን ይናገራል?
ስድሳ ስድስት ምዕራፎች ያሉት ትንቢተ ኢሳይያስ በሦስት ዐበይት ክፍሎች ሊከፈል እንደሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ይናገራል (1972፣ ገጽ 149)። የመጀመሪያው ክፍል ከምዕራፍ 1-39 ድረስ ያለው ሲሆን፥ ነቢዩ ኢሳይያስ በነበረበት ዘመን የተከናወኑትን ድርጊቶች መሠረት በማድረግ የተጻፈ ነው። ሁለተኛው ክፍል ደግሞ፥ ከምዕራፍ 40-55 ድረስ ያለውና ከኢሳይያስ ዘመን በኋላ ስለ ተፈጸመው ስለ ባቢሎን ምርኮ የተነገረ ትንቢት ነው። የመጨረሻው ክፍልም ከምዕራፍ 55-66 ደግሞ ወደ ፊት ማለትም ከባቢሎን ምርኮ ፍጻሜ በኋላ ስለሚሆነው የጽዮን ክብር ይናገራል። በመነሻው ላይ የተጠቀሰው ጥቅስ የተወሰደውም በዚህ በሦስተኛው ክፍል ከሚገኘው ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 60 ቊጥር 14 ላይ ነው።

ከላይ በቀረበው አከፋፈል መሠረት በሁለተኛው ክፍል፥ ማለትም ስለ ባቢሎን ምርኮ በተነገረው ትንቢት ውስጥ እንደ ተጠቀሰው፥ ሰባው የምርኮ ዘመን ሲያበቃ (ኤር. 29፥10) እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደ አገራቸው እንደሚመልሳቸው ተናግሮ ነበር። ለዚህም የመረጠው የፋርስን ንጉሥ ቂሮስን ነበር (ኢሳ. 45፥1-13፤ ዕዝ. 1፥1-4)። እርሱ ያወጣውን ዐዋጅ ተከትሎም ምርኮኞቹ የይሁዳ ሰዎች ወደ አገራቸው ተመልሰው ቤተ መቅደሳቸውን ሠርተዋል፤ የፈራረሰውን ቅጥርም ዐድሰዋል (መጽሐፈ ነህምያ እና መጽሐፈ ዕዝራ)።
ይህ ሁሉ በሚከናወንበት ጊዜና ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ለኢየሩሳሌም ወይም ለጽዮን ስለሚመጣው ብሩህ ጊዜ ደግሞ፥ በሦስተኛው ክፍል ውስጥ በስፋት ተጽፏል። በስፋት የተጻፈው በአገሪቱ ወይም በከተማዪቱ ስም ቢሆንም፥ ስለ ነዋሪዎቿ እየተናገረ እንደ ሆነ ማስተዋል አይከብድም። ኢሳ. 60፥14ም ስለዚሁ ሁኔታ ነው የሚናገረው። ጥቅሱ የተመዘዘበት አንቀጽ የሚጀምረው “በቊጣዬ ቀሥፌ በፍቅሬ ምሬሻለሁና መጻተኞች ቅጥርሽን ይሠራሉ፥ ነገሥታቶቻቸውም ያገለግሉሻል” (ኢሳ. 60፥10) በማለት ሲሆን፥ ይህም ቃሉ የተነገረው አስቀድሞ በእግዚአብሔር ቊጣ ስለ ተቀሠፈችውና በኋላ በእግዚአብሔር ፍቅር ስለምትማረው (ምሕረት ስለምታገኘው) ስለ ኢየሩሳሌም (ስለ ነዋሪዎቿ) ለመሆኑ በቂ ምስክር ነው። በርግጥም ኢየሩሳሌም (ጽዮን) ከእግዚአብሔር የሆነ ምሕረትን ስላገኘች እንደ ገና እንድትታደስና የቀደመ ክብሯ፣ ተሰሚነቷና ብልጥግናዋ እንዲመለስ እግዚአብሔር ማቀዱ በትንቢታዊ ቃሉ ውስጥ በግልጽ ቃላት ሰፍሯል።
ጽዮን በኀጢአቷ ምክንያት ለባቢሎናውያን ተላልፋ በመሰጠት የተጨነቀችባቸውና የተናቀችባቸው ዓመታት ነበሩ። እነዚህ ዓመታት ሲያበቁ የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፥ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእግዚአብሔርም ከተማ፥ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል (ኢሳ. 6014) ተባለላት። በመሆኑም አስቀድሞ ሲማርኳት አስጨንቀዋትና ንቀዋት የነበሩት ወገኖች ልጆች፥ እርሷን እንደ ገና ለመሥራትና የቀደመ ክብሯን ለመመለስ በእግዚአብሔር ሲታዘዙና የታዘዙትን ሲፈጽሙ እናነባለን። ከአስጨናቂዎቿ ልጆች መካከል አንዱ ንጉሥ ቂሮስ ነው። እግዚአብሔርም እርሱን ቀብቼዋለሁ ብሏል። እኔ በጽድቅ አስነሥቼዋለሁ፤ መንገዱንም ሁሉ አቀናለሁ፤ እርሱ ከተማዬን ይሠራል፥ በዋጋም ወይም በደመወዝ ሳይሆን ምርኮኞቼን ያወጣል”(ኢሳ. 45፥1፡13) ሲልም ተናግሮ ነበር። “… ወደ አንቺ ይመጣሉ … ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእግዚአብሔርም ከተማ፥ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል የተባለውም ከዚህ የተነሣ ነው። ስግደት የመገዛት ምልክት ነው። የናቋትና ያስጨነቋት ልጆች ለጽዮን እንደሚሰግዱ መነገሩም ክብሯ ሲመለስ ለእርሷ ተገዢ መሆናቸውን ያመለክታል።
ነገር ግን “የናቁሽ ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ” የሚለውና በነቢዩ ኢሳይያስ የተነገረው ትንቢታዊ ቃል፥ ከተነገረበት ከዚህ ዐውድና ከተነገረላቸው ወገኖች ውጪ ለሌላ አካል ተሰጥቶ ሲተረጐም በተደጋጋሚ እንሰማለን፤ በየታክሲው ላይም ተለጥፎ እናነባለን። ጥቅሱን በተደጋጋሚ ስንሰማና ተለጥፎም ስናነብ ብዙዎቻችን ጥቅሱ በዐውደ ምንባቡ መሠረት ስለ ተነገረላት ስለ ጽዮን ሳይሆን ስለ ቅድስት ማርያም የተነገረ ያህል እየተሰማን መጥቷል። ነገር ግን ይህ የአብዬን ለእምዬ የመስጠት ያህል ነው። ጥቅሱ ስለ ጌታ እናት ስለ ቅድስት ማርያም ይናገራል ብለው በእርሷ ስም የሚጠቅሱት ወገኖች፥ ቃሉ ስለ እርሷ የተነገረ ተሻጋሪ ትንቢት እንዳለው አድርገው መጥቀስ ለምን አስፈለጋቸው ይሆን? ከጥቅሱስ የትኛው ሐሳብ ይሆን ለእርሷ የሚስማማው?
ጥቅሱን ስለ ቅድስት ማርያም መጥቀስ ለምን አስፈለገ?
ይህ ጥቅስ ስለ ጽዮን ከተነገረው ዐልፎ ለሌላ አካል ወይም ለኢየሱስ እናት ለቅድስት ማርያም የሚተርፍና የሚስማማ ተሻጋሪ ትንቢት አለው ብሎ ማመን ያስቸግራል። አንዳንዶች ግን ጽዮን የሚለው ስም ከተማዋን ወይም ነዋሪዎቿን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ነገሮችንም እንደሚወክልና ከሚወክላቸው ነገሮች መካከልም ቅድስት ማርያም አንዷ እንደ ሆነች ያስተምራሉ። (ስለ ጽዮን ማንነት በጮራ ቊጥር 12 ገጽ 27-29 ላይ በስፋት የተጻፈውን ይመለከቷል)። በተለይ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ስለ ጽዮን ከተጻፈው መካከል በሴት አንቀጽና (ጾታ) አዎንታዊ ገለጻ ያላቸውን ቃላት ያሰፈሩትን ጥቅሶች ለቅድስት ማርያም ሰጥቶ መጥቀስና መተርጐም እየተለመደ መጥቷል። ነገር ግን በብሉይ ኪዳን ስለ ጽዮን ከተነገረው መካከል አንዱ እንኳ በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ከቅድስት ማርያም ጋር ተያይዞ ሲጠቀስና ተፈጻሚ ሲሆን አናነብም። የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጽዮን ማርያም ናት ብለው ባላረጋገጡበት ሁኔታ ታዲያ ስለ ጽዮን የተጻፈው ቅድስት ማርያምን ያሳያል ማለት ይቻላልን?
ስለ ቅድስት ማርያም እንደ ተነገሩ ትንቢቶች ተቈጥረው ከሚጠቀሱት መካከል በዐውዱ መሠረት እየተመለከትነው ያለው ኢሳ. 60፥14 አንዱ ነው። ይሁን እንጂ ከፍ ብሎ እንደ ተገለጸው፥ ይህ ጥቅስ የተጠቀሰበት አንቀጽ የሚጀምረው “በቊጣዬ ቀሥፌ በፍቅሬ ምሬሻለሁ” (ኢሳ. 60፥10) በማለት ነው። እንዲህ የተባለችዋ ጽዮን በአንቀጹ መጨረሻ ላይ ደግሞ፥ “የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፥ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእግዚአብሔርም ከተማ፥ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል” (ኢሳ. 6014) ተብላለች። ከአንድ አንቀጽ ውስጥ የተመዘዙት ሁለቱም ጥቅሶች የሚናገሩት ስለ አንድ አካል ነው። ስለዚህ በአዎንታዊ መንገድ የተነገሩትን ብቻ ወስዶ አሉታዊ አገላለጽ ያላቸውን መተው አይቻልም። መልካሙን ለጠቀስንለት አካል ሳንወድ በግድ ክፉውንም ጭምር ለእርሱው መጥቀሳችን አይቀርም። በዚሁ መሠረት የመጨረሻውን ጥቅስ ለቅድስት ማርያም የምንጠቅስ ሰዎች፥ የመጀመሪያው “ይለፈኝ” ማለት አንችልም። ታዲያ፥ “በቊጣዬ ቀሥፌ በፍቅሬ ምሬሻለሁ” የሚለውና አሉታዊ ቃላት ያሉበት አረፍተ ነገር፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሰው የቅድስት ማርያም ማንነት ጋር ይስማማልን? በፍጹም!!
ጥቅሱ ጽዮንን የናቋትና ያስጨነቋት ወገኖች አንገታቸውን ደፍተው ወደ እርሷ እንደሚመጡና ወደ እግሮቿ ጫማ እንደሚሰግዱ፥ የእግዚአብሔር ከተማ፣ የእስራኤል ቅዱስ የሆነሽ ጽዮን እንደሚሏትም ይናገራል። ጥቅሱ ስለ ጽዮን ብቻ የተነገረ መሆኑ ቀርቶ ለቅድስት ማርያም ከተሰጠና ጽዮን ማርያም ናት ከተባለ፥ እርሷን የናቀና ያስጨነቀ ወገን ነበረ ወደሚል አስተሳሰብ ይመራል። ለጠቃሾቹም መነሻ የሆናቸው ይህ ነው ተብሎ ይገመታል። ነገር ግን ይህ ወገን ማን ይሆን?
ንቀት አንድን አካል አቃሎና ዝቅ አድርጎ ማየት፥ እንዲሁም ለዚያው አካል ተገቢውን ክብርና ስፍራ አለመስጠት ነው። በአንጻሩ ክብር ለሚገባው ክብርን መስጠት ማለትም፥ ለክብር ተቀባዩ ማንነት የሚመጥን ከበሬታን ማሳየት ማለት ነው እንጂ፥ ገደብ የለሽ፣ ሽርደዳን የመሰለ፣ የተጋነነና በአክብሮት ስም አምልኮት የሆነ ክብር ሊሆን አይገባውም። አሊያ ይህ ክብርን መስጠት ሳይሆን መሸርደድ አሊያም ማምለክ ይሆናል። ሁለቱም አመለካከቶች ኢመጽሐፍ ቅዱሳውያን ናቸውና ሊወገዱ ይገባል።
ክርስቲያን የጌታን እናት ቀርቶ ማንንም ሰው መናቅ እንደማይገባው ያውቃል፤ ተገቢውንም ክብር ለሚገባው አካል ይሰጣል። ክብር በመስጠት ስም ግን አምልኮት አያቀርብም። ኢሳ. 60፥14ን ለጌታ እናት የሚጠቅሱት ወገኖች እርሷን የናቋትና ያስጨነቋት ወገኖች አሉ እያሉ ነው። እንዲህ ለማለት ግን ምን አነሣሣቸው? ቢሉ፥ ቅድስት ማርያምን በማክበር ስም በስሟ የሚቀርበውን አምልኮት ሌሎች ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም ብለው መተቸታቸውን በመቃወም ነው እንዲህ ለማለት የበቁት ማለት ይቻላል። ትችቱን አጢኖ በአክብሮት ስም እየቀረበ ያለውን አምልኮት በመጽሐፍ ቅዱስ በመመርመር ዐቋምን ማስተካከል ይገባል። ካፈርሁ አይመልሰኝ በሚል ዐቋም ጸንቶ፥ ትችቱ የተሳሳተ አተረጓጐምን ማስተካከል ሳይሆን፥ ቅድስት ማርያምን መናቅና ማቃለል ነው ማለት ግን ብዙ አያስኬድም።
በመሠረቱ ትችቱ አስተምህሮአችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይሁን የሚል ነው እንጂ የጌታን እናት መናቅና ማቃለል ሊሆን በፍጹም አይችልም። እርሷን የሚንቁና የሚያቃልሉ ክርስቲያኖች አሉ ለማለትም አያስደፍርም እንጂ፥ አሉ ቢባል እንኳ፥ ይህን ሁኔታ በኢሳ. 60፥14 ማስደገፍ የሚቻልበት አንዳችም ምክንያት የለም።
ኧረ ለመሆኑ፥ የራስን ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ ሳያስደግፉ ማቅረብ አይቻልም ወይ? ርግጥ ይህ የሚነግረን አንድ እውነት አለ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ባለሥልጣንና የክርስትና ትምህርቶችን ሁሉ አረጋጋጭ መሆኑን። ለዚህም ነው ሰዉ ሁሉ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት እንኳ ይዞ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ጠጋ ማለትን የሚመርጠው። ታዲያ ሥልጣን ላለው ለዚህ ቅዱስ መጽሐፍ ቃል መታዘዝ ይሻላል ወይስ እርሱን ለስሕተት መሸፈኛ አድርጎ መጥቀስ?
ጥቅሱ ስለ ቅድስት ማርያም የተጻፈ ነው የሚሉት ወገኖች የሚያቀርቡት ሌላው መከራከሪያ፥ በጥቅሱ ውስጥ የምናገኘውና “… ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ” የሚለው ሐረግ፥ ከተማን ሳይሆን ሰውን ነው የሚወክለው፤ ስለዚህ ጥቅሱ ስለ እርሷ የተነገረ ነው የሚል ነው። ነገር ግን ይህ በሥነ ጽሑፍ ውስጥ የዘይቤ አጠቃቀምን ሕግ ካለማስተዋል የሚሰጥ አስተያየት ነው። በጽሑፍ ውስጥ የተለያዩ ዘይቤዎችን መጠቀም የተለመደ ነው። ጸሐፍት ከሚጠቀሙባቸው ዘይቤዎች መካከልም አንዱ ሰውኛ ዘይቤ ነው። ይህ የዘይቤ ዐይነት የሰውን ጠባይና ተግባር ሰው ላልሆኑ ሕያዋንና ግዑዛን ፍጥረታት  አላብሶና ሰጥቶ፥ ሰው የሚያከናውናቸውን ተግባራት ሲያከናውኑ የሚያሳይ የዘይቤ ዐይነት ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከምናያቸው የዘይቤ ዐይነቶችም አንዱ ሰውኛ ዘይቤ ነው። ለምሳሌ፡- “የምድር ዳርቻዎች ሁሉ የአምላካችንን ማዳን አዩ። ምድር ሁሉ ሆይ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፤ አመስግኑ፥ ደስ ይበላችሁ፥ ዘምሩ” (መዝ. 97/98፥3፡4) በሚለው ጥቅስ ውስጥ ምድርንና የምድር ዳርቻዎችን ሁሉ በሰውኛ ዘይቤ ነው ያቀረባቸው። ዐይን እንዳላቸው ሁሉ “አዩ” ተብሏል። አንደበት እንዳላቸውም ሁሉ፥ “እልል በሉ፥ አመስግኑ፥ ደስ ይበላችሁ፥ ዘምሩ” ተብለው ታዘዋል።
“ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” (መዝ. 67/68፥31) በሚለው አረፍተ ነገር ውስጥም በተመሳሳይ ሁኔታ ኢትዮጵያን በሰውኛ ዘይቤ እጆቿን እንደምትዘረጋ ይናገራል። መቼም ኢትዮጵያ አገር እንደ መሆኗ እጆች የላትም። ስለ ጽዮን የተነገረውም በሰውኛ ዘይቤ የቀረበ ነው። ጽዮን ከተማ እንደ መሆኗ እግር እና ጫማ የላትም። ይህ በሰውኛ ዘይቤ የቀረበ አገላለጽ መሆኑን ሳያስተውሉ ጥሬ ንባቡን ብቻ ይዘው፥ እንዲህ የሚለው ስለ ከተማዋ ሳይሆን ስለ ቅድስት ማርያም ነው ማለትም ፈጽሞ አይቻልም። ቃሉን በግድ ለእርሷ ሰጥተን ብንተረጕመው እንኳ ቅድስት ማርያምን ማን ናቃት? ማንስ አስጨነቃት? እርሷንስ የት አግኝቶ ነው ወደ እግሮቿ ጫማ መስገድ የሚቻለው? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ አይገኝላቸውም። ስለዚህ ቃሉ ስለ ጽዮን እንጂ ስለ ቅድስት ማርያም የተነገረ አይደለም። 

ይቀጥላል
በጮራ ቍጥር 41 ላይ የቀረበ

1 comment:

  1. engdiawse selmen lketmaytu setsegdu atetayume

    ReplyDelete