Sunday, June 1, 2014

አለቃ ነቅዐ ጥበብ

የጥያቄና መልስ ጊዜ

ሥርዐተ አምልኮው እንደ ተፈጸመ፥ ለጥያቄዎች መልስ የሚሰጥበት ጊዜ መሆኑን ዲያቆን ምስግና እንዳስታወቀ፥ አለቃ ነቅዐ ጥበብ የተመደበላቸውን ስፍራ ያዙ፡፡ የዛሬው ጥያቄና መልስ በምን ርእስ ላይ እንደሚያተኵር አለቃ ሲጠይቁ፥ ከሳምንታት በፊት ስለ ምልጃ ከተማርን በኋላ ቀሪውን በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን ተብሎ እንደ ነበረ ዲያቆን ምስግና አስታወሳቸው፡፡ አለቃም መነጽራቸውን ካስተካከሉና መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ካመቻቹ በኋላ “መልካም” አሉ፡፡ “መልካም ባለፈው ጊዜ በሐዲስ ኪዳን ተገቢ ሊቀ ካህናት፥ ነቢይ፥ ንጉሥ፥ መካከለኛ ሆኖ የተሾመው፤ ሰውም እግዚአብሔርም የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ እንደ ሆነ የሚናገሩትን ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ እያወጣን ተመልክተን ነበር፡፡ በጥቅሶቹም አስረጅነት በመሐላ የተሾመው፥ ክህነቱ የማይሻረው ዘላለማዊው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ የመሥዋዕት ማቅረቡን ሥራ ጨርሶ በአብ ቀኝ ተቀምጦ ባለበት ጊዜም እያማለደን መሆኑን የሚያስጨብጥ ግንዛቤ አግኝተን እንደ ነበረ ይታወሳል” በማለት ጀመሩ (ጮራ ቍ. 4 እና 5)፡፡

ለሚቀጥለው ሐሳብ መግቢያ የሚሆነውን ሲያብራሩም እንዲህ አሉ፤ “የእስራኤል ልጆች ለእግዚአብሔር የተለየ ሕዝብ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የቃል ኪዳን ማኅተም ይሆን ዘንድ የእንስሳ ደም ተረጭቶባቸው ነበር (ዘፀ. 24፥6-8)፡፡ ደም ሕዝቡ የእግዚአብሔር፥ እግዚአብሔርም የሕዝቡ ለመሆናቸው ጽኑዕ የትስስርና የውርርስ ቃል ኪዳን ማረጋገጫ ነው፡፡ ሆኖም ሕዝቡ በተለያዩ መንገዶች ቢበድሉ በመቅሠፍት እንዳይቀጡና የእግዚአብሔር ሕዝብነታቸውን ዐድሰው እንዲኖሩ የመሥዋዕት ሕግ ተደነገገላቸው፡፡ እስራኤላዊው የእግዚአብሔርን ሕግ ቢተላለፍ የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና ሞት የሚያስፈርድበትን ኀጢአቱን የሚሸከምለትንና በምትኩ ይሞትለት ዘንድ የሚሠዋለትን እንስሳ ወደ መገናኛው ድንኳን መውሰድ ነበረበት፡፡ ሊቀ ካህናቱ ቢበድል (ዘሌ. 4፥1-12)፥ ማኅበሩ ቢበድል (ዘሌ. 4፥13-21)፥ የማኅበሩ መሪ ቢበድል (ዘሌ. 4፥22-26)፥ የማኅበሩ አባል ቢበድል (ዘሌ. 4፥27-35) እንደ ታዘዘው መፈጸም ነበረባቸው፡፡