ይህን ዓመት ደግሞ
ተዋት!
የእያንዳንዱ ቅጽበት፥
ሰኮንድ፥ ደቂቃ ትዝታ ይህን ያህል ጐልቶ በተናጠል በአእምሮኣችን ባይመዘገብም፤ በሰዓት፥ በቀን፥ ከዚያም በወርና በዓመት እየተጠቃለለና
የራሱን ድምር ትዝታ እየተወ ሲያልፍ ኖሮአል፡፡ ያለፈው ሁሉ ታሪክ ሆኖአል፤ ተጽፎአል፤ ተነቦም መዝገብ ቤት ይቀመጥ ተብሏል፡፡
አብዛኛው ሰው ባለፈው ቀን ትዝታ ላይ ሙሉ ጊዜውን ከሚያሳልፍ ይልቅ በሚመጣው ቀን ምን እንደሚያጋጥመው ዐውቆ ለመዘጋጀት በእጅጉ
ይጥራል፡፡ ብርቱ ፍላጎትም ያለው ስለ ወደ ፊቱ ዕቅድ መሳካት ነው፡፡ ይህንም የሰው ልጅ ፍላጎት የተረዱ ብልጣብልጥ የኅብረተሰብ
አባላት መጪውን ዕድልህን ልንነግርህ እንችላለን እያሉ የዋሁን ሕዝብ ለዘመናት ገንዘቡንና ጊዜውን በዘበዙት፤ ሥነ ልቡናውንም ሰለቡት፡፡
እንደዚህ የመሳሰለው
አካባቢያዊ ተጽዕኖ ከሚቀሰቅሰው ውስጣዊ ግፊት የተነሣ ሰዎች ከአሮጌው ዓመት ትዝታ ይልቅ ለመጪው ጊዜ ምን ይሁንታ ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡
ስለዚህም ለመጪው ዓመት ብሩህ ተስፋ እውን መሆን ሲሉ ጠንክሮ ለመሥራት በሙሉ ዕውቀታቸውና ኀይላቸው ይዘጋጃሉ፡፡ ስለዚህም በየዓመቱ
መጀመሪያ ለዐዲሱ ዓመት እንኳን አደረሰህ! አደረሰሽ! በመባበል የመልካም ምኞት መግለጫ ይለዋወጣሉ፡፡ ስለ ዐዲሱ ዓመት እንጂ ስላለፈው
ግድ የሚኖረው ያለ አይመስልም፡፡ ላለፈው ክረምት ቤት አይሠራለትምና፡፡