Sunday, November 3, 2013

የዘመን ምስክር


በዚህ ዐምድ ለቤተ ክርስቲያን መሻሻልና መለወጥ የተጋደሉ፥ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም መልካም ሥራን የሠሩ አበውን ሕይወትና የተጋድሎ ታሪክ አሁን ላለውና ለቀጣዩ ትውልድ አርኣያ እንዲሆን እናስተዋውቃለን፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ (1902-1971 ዓ.ም.)
ያለ መንፈስ ቅዱስ አብርሆት የእግዚአብሔርን ቃል ማስተዋልና መለወጥ እንደማይቻል የታወቀ ነው። እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ሲናገር፥ ሰው ሊሰማ ይችላል፤ ነገር ግን ያ ሰው ቃሉን የሚያስተውለውና በቃሉ ተለውጦ ዐዲስ ፍጥረት የሚሆነው፥ የተዘጋው የልቡናው በር በእግዚአብሔር ቃል ሲንኳኳና በመንፈስ ቅዱስ አብርሆት መከፈት ሲችል ብቻ ነው። ልድያ የተባለችው የትያጥሮን ሴት፥ ጳውሎስ የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልቧን ከፍቶላት ነበርና በሰማችው ቃል ሕይወቷ ተለወጠ (ሐ.ሥ. 16፥14-15)። የቅዱስ ጳውሎስ ድርሻ ቃሉን መናገር እንጂ እርሷን ማሳመን አልነበረም፤ ልቧን ከፍቶ ቃሉን እንድታደምጥና በቃሉ እንድታምን ያደረገው ጌታ ነው። ይህ ትናንትም ሆነ ዛሬ እግዚአብሔር ሰዎችን ለመለወጥና ዐዲስ ፍጥረት ለማድረግ የሚጠቀምበት ድንቅ አሠራሩ ነው።

መማርና ማወቅ ለሰው መልካም ነገሮች ቢሆኑም፥ የእግዚአብሔርን እውነት ለማስተዋል ግን ከላይ እንደ ተገለጸው የመንፈስ ቅዱስ አብርሆት ያስፈልገዋል። የፍጥረታዊ ሰው ልብ ብርሃን እግዚአብሔር እስኪበራበት ድረስ ጨለማ ነው (ሮሜ 1፥21፤ ኤፌ. 5፥8)። በዚህ ጨለማ ልብ ውስጥ እግዚአብሔር ካልበራ (መዝ. 118፥27) በቀር ፍጥረታዊው ሰው እግዚአብሔርንም ሆነ የእግዚአብሔርን ፈቃድና ሐሳብ ሊገነዘብ አይችልም (1ቆሮ. 2፥14)። ስለዚህ ሰው ያስተውል ዘንድ እግዚአብሔር በጨለመው የሰው ልብ ውስጥ ብርሃኑን ያበራል (መዝ. 18፥28፤ 2ቆሮ. 4፥4-6)። ሰውም በልቡ በበራው ብርሃን እየተመራ የእግዚአብሔርን እውነት ያስተውላል (መዝ. 36፥9)።


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በዘመናቸው ያስተላለፉአቸውን መጽሐፍ ቅዱሳውያን መልእክቶች ምን ያህሉ ሰው አስተውሏቸው ይሆን? ምን ያህሉስ የሕይወት ለውጥ አምጥቶባቸው ይሆን? እጅግ ከሚማርኩት ስብከቶቻቸውና ንግግሮቻቸው መካከል በብዙው ሰው አእምሮ ውስጥ ሠርጸው የቀሩትስ የትኞቹ ይሆኑ? ሥጋና ደም ሊያመሰጥራቸው የሚችላቸው ዕውቀቶች፥ ወይስ መንፈስ ቅዱስ ገልጦት ኀጢአተኛውን ሰው ወደ ንስሓና ወደ መታደስ የሚያመጣው የመዳን ዕውቀት? (ሉቃ. 1፥77-79) የሚሉት ጥያቄዎች በሕይወት ላለው ለእርሳቸው ዘመን ትውልድና አሁን ላለውም ትውልድ መነሣት ያለባቸው ወሳኝ ጥያቄዎች ናቸው።  

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ማናቸው?
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የተወለዱት ሚያዝያ 16 ቀን 1902 ዓ.ም. በምሥራቅ ጎጃም በማቻክል ወረዳ በደብረ ገነት ኤልያስ ነው። አባታቸው አቶ ወልደ ማርያም ውቤ፥ እናታቸው ወይዘሮ ዘርትሁን አደላሁ ይባላሉ። ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስም መልእክቱ ሲሆን፥ በጵጵስና እስኪሾሙ ድረስ በዚህ ስም ተጠርተዋል።

ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በተወለዱበት ደብር ንባብ፣ ዜማ፣ ቅኔ፣ የውዳሴ ማርያምና የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣ እንዲሁም የወንጌል ትርጓሜ ቀጽለዋል፤ በቅኔ መምህርነትም ተመርቀዋል። በ1920 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከታላቁ ሊቅ ከመምህር ሐዲስ ተክሌ (በኋላ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ) መጻሕፍተ ሐዲሳትን፣ ፍትሐ ነገሥትንና አቡሻህርን ጠንቅቀው በመማር ለመምህርነት በቅተዋል። ወንበር ዘርግተው በማስተማርም አያሌ ሊቃውንትን አፍርተዋል። ዕድሜያቸው 27 ዓመት ሲሆን በደብረ ሊባኖስ ገዳም ምንኩስናን ተቀብለዋል።

ቅዱስነታቸው ከአብነታዊው የቤተ ክህነት ትምህርት ባሻገር ዘመናዊውን ትምህርት ለመቅሰም ጽኑ ፍላጎት ነበራቸው። በ1934 ዓ.ም. በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ፈቃድ ዘመናዊ ትምህርት፥ በተለይም እንግሊዝኛ እንዲማሩ ከተመረጡት 20 ሊቃውንት መካከል አባ መልእክቱ አንዱ ነበሩ። በዚያ ጊዜ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት፥ ዛሬ የዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሆነው ጊቢ የተዘጋጀውን ትምህርት ተከታትለዋል። ከእንግሊዝኛ ሌላ ዐረብኛና ጣሊያንኛም ይችላሉ። ትምህርት ቤቱም “የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት” በሚል ስያሜ በ1935 ዓ.ም. መንፈሳዊውንና ሥጋዊውን ትምህርቶች በጥምረት እንዲሰጥ ተደርጎ ወደ አሁኑ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሲዛወርና በትምህርት ሚኒስቴር ሥር ሲሆን፥ በአባ መልእክቱ የበላይ አስተዳዳሪነት እንዲመራ ተደርጓል።

አባ መልእክቱ በመቀጠል የመካነ ሥላሴን ገዳም እንዲያስተዳድሩ በመምህርነት ማዕርግ የተሾሙ ሲሆን፥ በዚያ ለሦስት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት ተብለው በመሾም ካቴድራሉን አስተዳድረዋል። በ1938 ዓ.ም. ለኢትዮጵያውያን አበው ማዕርገ ጵጵስና እንዲሰጥ፥ በኢትዮጵያና በእስክንድርያ አብያተ ክርስቲያን መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት፥ ከተመረጡት 5 አበው አንዱ ሊቀ ሥልጣናት መልእክቱ ነበሩ። ሆኖም በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን በኩል በተፈጠረው እክል ምክንያት ሹመቱ ለ2 ዓመታት ከዘገየ በኋላ፥ በ1940 ዓ.ም. በግብጹ ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሳብ ተቀብተው ቴዎፍሎስ በመሰኘት የሐረርጌ ጳጳስ ሆነዋል።

ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ባላቸው የመንፈሳዊና የዘመናዊ ትምህርት ችሎታ በ1942 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ ምርጫ የብፁዕ አቡነ ባስልዮስ እንደ ራሴ ሆነው ተሾመዋል። ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ጋር በተደረገ ሌላ ስምምነትም ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ በ1943 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳት ሲሆኑ፥ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ለግብጹ ፓትርያርክ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሳብ በኢትዮጵያ ወኪል እንዲሆኑ ተደረገ። በ1951 ዓ.ም. ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ሆነው ሲሾሙ፥ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ በያዙት የሐረርጌ ሀገረ ስብከት በሊቀ ጵጵስና ማዕርግ ተሾመዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ፥ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ተጠባባቂ ፓትርያርክ ሆነው ለተወሰኑ ወራት ከቆዩ በኋላ፥ መጋቢት 29 ቀን 1963 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ 1ኛ ሆነው በመመረጥና 2ኛው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ በመሆን በኢትዮጵያውያን ጳጳሳት፣ ካህናትና ምእመናን ጸሎት በኢትዮጵያ ምድር ተሾመዋል። በፓትርያርክነትም እስከ የካቲት 9 ቀን 1968 ዓ.ም. ድረስ ቈይተዋል (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ 1987፣ 19)።
   
ለቤተ ክርስቲያንና ለአገር ምን አበረከቱ?
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ከ1935 ዓ.ም. - 1968 ዓ.ም. ድረስ በተለያዩ የሥልጣን ደረጃዎች በቈዩባቸው 33 ዓመታት ለአገርና ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ በርካታ ሥራዎችን በትምህርት፣ በስብከተ ወንጌል፣ በውጭ ግንኙነት፣ በቅርስ አጠባበቅ፣ በልማት፣ በምግባረ ሠናይ መስኮችና በመሳሰሉት ዘላቂ፣ እጅግ ጠቃሚና ውጤታማ የሆኑ በርካታ ሥራዎችን እንደ ሠሩ የሕይወት ታሪካቸውና ሥራዎቻቸው ይመሰክራሉ። ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል፡-

·     ትምህርት
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ትምህርት ለሁሉ ነገር መሠረት፥ ለመንፈሳዊም ሆነ ለሥጋዊ ኑሮ አቻ የሌለው መሣሪያ መሆኑን የተረዱ አባት ነበሩ። በመሆኑም በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት፥ “የሀገሪቱ የትምህርት ቦርድ ሲቋቋም ቤተ ክርስቲያንን እንዲወክሉ በንጉሡ ተመርጠው የቦርድ አባል በመሆን ለትምህርት መስፋፋት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው አስተዋፅኦ አበርክተዋል።” (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ 1987፣ 19)።

ቅዱስነታቸው ሥራ ይስጡኝ ከሚሏቸው ይልቅ ያስተምሩኝ የሚሏቸውን ሰዎች ይወዱ እንደ ነበር ይነገራል። ከመንግሥት ያገኙ በነበረው ድጋፍ በሀገረ ስብከታቸው ዋና ከተማ በሐረርና በቁልቢ ገዳም ሁለት ትምህርት ቤቶችን አቋቁመው፥ ከአካባቢውና ከሌላውም የኢትዮጵያ ክፍል እየተመለመሉ ብዙ ወጣቶች በመንፈሳዊና በሥጋዊ ዕውቀት እንዲሠለጥኑ በማድረግ፥ ለቤተ ክርስቲያንና ለአገር ጥቅም የሚሰጡ ዜጎችን በማፍራት በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

በውጭ ግንኙነት ዘርፍ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር በፈጠሩት ጠንካራ ወዳጅነት ነጻ የትምህርት ዕድል በመጠየቅ፥ ወደ ግብጽ፣ ግሪክ፣ ሩሲያ፣ አውሮፓ፣ አሜሪካና እስያ በርካታ ወጣቶችን በመላክ፥ በከፍተኛ ሥነ መለኮት፣ በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በማኅበራዊ ሳይንስ ወዘተ. የትምህርት ዐይነቶች በቢ.ኤ.፣ በማስትሬትና በዶክትሬት ዲግሪዎች እንዲመረቁና ቤተ ክርስቲያንንና አገርን በውጤታማነት እንዲያገለግሉ አድርገዋል። በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት መካከል ጥቂቶቹ፡- የአሁኑ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኀይሌ፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል፣ ረዳት ፕሮፌሰር ሉሌ መላኩ፣ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ ዶ/ር ጸጋዬ ሀብቴ እና ፕሮፌሰር በእደ ማርያም ጸጋ ይጠቀሳሉ (ራእየ ቴዎፍሎስ 2002፣ 26፡30)።

·     ስብከተ ወንጌል
ቅዱስነታቸው ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት ያበረከቱት አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ ነው። በሀገረ ስብከታቸውም ሆነ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል፥ በውጭ ሀገርም ጭምር እየተዘዋወሩ ምእመናንን በትምህርተ ወንጌል ያጽናኑ ነበር። በ1951 ዓ.ም. በሰሜን አሜሪካ፣ በዌስት ኢንዲስና በደቡብ አሜሪካ እየተዘዋወሩ ምእመናንን አስተምረዋል፤ አብያተ ክርስቲያናትንም መሥርተዋል። በተለያዩ ጊዜያት ተመላልሰው እየጎበኙም በእምነታቸው እንዲጸኑ ጥረዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ክርስቲያን ላልሆኑትም ወንጌልን በመስበክና በማሳመን ብዙዎችን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች አድርገዋቸዋል። በዚህ ረገድ በ1949 ዓ.ም. በባሌ ክፍለ ሀገር በገደብ አውራጃ በዶዶላ፣ በሲሮፍታ፣ በሄቤኖ፣ በኮኮስና በጋጫ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክ 24 ሺህ የአዋማና የልዩ ልዩ እምነት ተከታዮችን አሳምነው አጥምቀዋል።  

ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት በነበራቸው ጕጕት በ1958 ዓ.ም. የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ድርጅት በመንበረ ፓትርያርኩ ሥር ያቋቋሙ ሲሆን፥ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ቅርንጫፍ በመክፈትም የስብከተ ወንጌል ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አድርገዋል። በስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ድርጅት አማካይነትም ምእመናን በቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ ቀጥተኛ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ የተቻላቸውን ሥራ ሠርተዋል። ሰባክያን የሚሆኑ ቀሳውስትና ዲያቆናት የሚሠለጥኑባቸው የካህናት ማሠልጠኛዎች በየሀገረ ስብከቱ እንዲቋቋሙም መሠረት ጥለዋል።

ቅዱስነታቸው ወጣቶች በዘመናዊ አስተሳሰብና እየነፈሰ በነበረው የኮሚኒዝም ነፋስ ሊወሰዱ እንደሚችሉ ቀድመው በመገንዘብ ከቤተ ክርስቲያን እንዳይርቁ ለማድረግ የወጣቶች መምሪያ የተባለ ክፍል የመሠረቱ ሲሆን፥ በእርሱ አማካይነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፉና ወጣቶች በእምነትና በሥነ ምግባር ታንጸው ለአገርና ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ ዜጎች እንዲሆኑ ለማድረግ ከፍ ያለ ሚና ተጫውተዋል (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ 1987፣ 19)። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የሚታየው የወጣቶች እንቅስቃሴ ያን ጊዜ የተመሠረተና የተስፋፋ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

በዚያ ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የውጭ አገር መምህራኖቻቸው ወደ ራሳቸው እምነት ሊስቧቸው ጥረት ያደርጉ ስለ ነበር፥ ትምህርተ ሃይማኖት የሚያስተምር መምህር እንዲመደብላቸው ለቤተ ክህነት ጥያቄ ባቀረቡ ጊዜ፥ በዘመኑ ምስጉን ሰባኬ ወንጌል የነበሩት ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ተመድበው በየሳምንቱ አርብ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አዳራሽ እየተገኙ ተማሪዎቹን ያስተምሩ ነበር። ይኸው እንቅስቃሴ ቀጥሎ በግንቦት ወር 1951 ዓ.ም. ሃይማኖተ አበው የተሰኘውን አንጋፋ የተማሪዎች ማኅበር ወለደ (ራእየ ቴዎፍሎስ 2002፣ 27)።

·     የውጭ ግንኙነት
“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከውጭ አብያተ ክርስቲያናት ጋር የነበራትን ግንኙነት በማደስና በማጠናከር፥ እንዲሁም ዐዳዲስ ግንኙነቶችን በመመሥረት ረገድ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የፈጸሙት ተግባር አቻ የለውም” (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ 1987፣ 23)። ቅዱስነታቸው ሊቀ ሥልጣናት ተብለው ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኗ የራሷ ፓትርያርክ እንዲኖራት በሚደረገው ጥረት ልኡካንን በመምራት ግብጽ ድረስ እየሄዱ ተገቢውን ድርድር በማድረግ የላቀ ድርሻ አበርክተዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ መሥራች አባል ያደረጓትም ቅዱስነታቸው ናቸው። በ1940 ዓ.ም. በሆላንድ አምስተርዳም በተደረገው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት መሥራች ጉባኤና ከዚያም በኋላ በተለያዩ አገሮች በተደረጉ ተከታታይ ጉባኤዎች ላይ በመገኘት ንቁ ተሳትፎ አድርገዋል። በ1960 ዓ.ም. በስዊድን አብሳላ በተደረገው ጉባኤ ላይ የጉባኤው ማእከላዊ አባል ሆነው እንዲሠሩ ተመርጠው ነበር።

የመላው አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጉባኤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያላትን ታሪካዊ ሚና በመረዳትና የቅዱስነታቸውን በሳል አመራር በመገንዘብ፥ ለሁለት ተከታታይ ጊዜያት ከተመረጡት 3 ፕሬዝዳንቶች መካከል አንዱ እንዲሆኑ አድርጓል። በዚሁ መሠረት በ1961 ዓ.ም. በአቢጃን አይቮሪኮስት የተካሄደውን ጉባኤ ቅዱስነታቸው በሊቀ መንበርነት መርተዋል።

በ1956 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ በተደረገው የኦርየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን መልእክተኞች በመምራት ተሳትፈዋል። በ1963 የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር ማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አዲስ አበባ ላይ እንዲደረግ በመጋበዝ የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥንታዊነትና ታሪካዊነት ለማስተዋወቅ እድል እንዲፈጠር ሁኔታዎችን አመቻችተዋል።

በ1965 በአሜሪካ ባደረጉት ጕብኝት በተለያዩ ግዛቶች በመዘዋወር ታላላቅ ካቴድራሎችን፣ ታዋቂ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶችንና ሰፋፊ ዩኒቨርሲቲዎችን የጐበኙ ሲሆን፥ ከታላላቅ የሃይማኖትና የፖለቲካ መሪዎች፥ እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ጋር ተነጋግረዋል። “በታላላቅ ካቴድራሎች ቀድሰው አቊርበዋል፤ ዓለም ዐቀፋዊ የጸሎት ሥነ ሥርዐቶችን መርተዋል፤ ባሰሟቸው ስብከቶች በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ምእመናንን አጽናንተዋል። ከሁሉም በላይ በታላላቅ ጉባኤዎች ላይ በመገኘት ባደረጓቸው ንግግሮች፥ የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት በሚያምኑ አብያተ ክርስቲያናት መካከል መተባበር፣ መቀራረብና አንድነት እንዲጠናከር አስገንዝበዋል”(ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ 1987፣ 30-31)።

በአጠቃላይ “ከ1938 ዓ.ም. ጀምሮ በልዩ ልዩ አህጉራት አብያተ ክርስቲያናትን በመጐብኘት ከታላላቅ የሃይማኖት መሪዎች ጋር በመነጋገርና የውጭ ግንኙነትን በማስፋፋት ቤተ ክርስቲያኗ በኦርቶዶክስ፣ በካቶሊክና በፕሮቴስታንቶች ዘንድ በአግባቡ እንድትታወቅ አድርገዋል” (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ 1987፣ 24-25)።

·     የሰበካ ጉባኤ መቋቋም
ቅዱስነታቸው ለቤተ ክርስቲያን ከሠሯቸው ሥራዎች መካከል ሰበካ ጉባኤን ማቋቋማቸው ሳይጠቀስ መታለፍ የለበትም። ይህም ቤተ ክርስቲያኗ ከመንግሥት ታገኝ የነበረውን መተዳደሪያ የሚተካና የየአጥቢያው ምእመናን በሚያደርጉት አስተዋፅኦ ራሷን እንድትችል ያደረጉበት አሠራር ነው። እንደሚታወቀው ቤተ ክርስቲያኒቱ ቀድሞ ትተዳደር የነበረው ከመንግሥት ባገኘችው ርስት ነበር። ቅዱስነታቸው ግን ይህ ቀጣይ ሊሆን እንደማይችል ቀድመው በመገንዘብ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሰበካ ጉባኤ በመመሥረት ራሷን የምትችልበትን መንገድ ቀይሰዋል።

የፈሩት አልቀረም፤ በደርግ መንግሥት የቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብትና ንብረት ሲወረስ፥ በተቋቋመው የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር አማካይነት ምእመናን በሚያዋጡት ወርኃዊ መዋጮና ልዩ ልዩ ገቢ የአገልጋዮችና የሠራተኞች ደመወዝ እየተሸፈነ ቤተ ክርስቲያኗ በሁለት እግሯ እንድትቆም ተደርጓል (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ 1987፣ 24-25)። ከዚህ የተነሣ ዶ/ር  ሐዲስ የሻነህ የተባሉ ጸሓፊ ቅዱስነታቸውን “ነቢይ ነበሩ” ብለዋል፤ ምክንያቱንም ሲያስረዱ “ነቢይ ነበሩ ሲባል በመጪው ዘመን ቤተ ክርስቲያን ሊደርስባት ከሚችለው የለውጥ ማዕበል የምትድንበትን አስቀድመው በመረዳት የቤተ ክርስቲያን መድኅን የሆነውን የሰበካ አስተዳደር ጉባኤን በማዋቀራቸው ነው” ብለዋል (ዲያቆን ሰሎሞን 1999፣ 77)።  

ለቤተ ክርስቲያን መታደስ ምን ሠሩ?
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ሆነው ሲሾሙ በብዙዎች ዘንድ ተስፋ የተደረገው በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እየታየ የነበረው ተሐድሶ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ዘንድ እውን እንደሚሆን ነበር። ፓትርያርክ ሆነው በተሾሙ ጊዜ የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ የተሰኘው አንጋፋ ጋዜጣ እንዲህ ብሎ ነበር፤ “የሌሎች አገሮች አብያተ ክርስቲያኖች እንደ ታደሱ ሁሉ የእኛም እንደ ዘመኑ መራመድ ይኖርባታል። የዐሥራ ዐምስተኛው ክፍለ ዘመን ሰዎች አስተሳሰብና የኻያኛው ክፍለ ዘመን ፍልስፍና በጣም የተራራቀና የተለያየ ስለ ሆነ፥ ሊያሳምን በሚችል በዐዲስ ዘዴ መቅረቡ የተሻለ ውጤት ያስገኛል። ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ይህን ሁሉ በማመዛዘን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ፣ በአሠራር፣ በአስተሳሰብና በአፈጻጸም የታደሰችና የዘመኑን ሥርዐት የተከተለች እንደሚያደርጓት ከፍተኛ ኀላፊነት ይጠብቃቸዋል” (1963፣ 2)።

ይህ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ቀርቦ የነበረው የዚያን ወቅት ድምፅ፣ ቅዱስነታቸው በተለያዩ ጊዜያት ባስተላለፏቸው መልእክቶች ውስጥ ያንጸባረቋቸው ተሐድሶኣዊ ሐሳቦችና ከእርሳቸው ሞት በኋላ፥ አንዳንዶች እያንጸባረቁት ያለው የእርሳቸው የለውጥ ሐሳብ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መታደስ አስፈላጊዎች መሆናቸውን የጮራ መጽሔት ዝግጅት ክፍል ያምናል ቅዱስነታቸው በተለያዩ ጊዜያት ያስተላለፏቸውን ተሐድሶኣዊ መልእክቶች ከተለያዩ ምንጮች ሰብስቦ ከዚህ ቀጥሎ ሲያቀርብም፥ በቅዱስነታቸው መልእክት ላይ ተመሥርቶ ያቀረበው የዝግጅት ክፍሉ አስተያየት መሆኑን በቅድሚያ ለአንባብያን መግለጽ ይወዳል። 

“ተሐድሶ” የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ካላቸው ነገረ መለኮታውያን ቃላት መካከል አንዱ ቢሆንም፥ ይህን ባልተረዱና ሃይማኖትን ከባህል መለየት በተሣናቸው በአንዳንዶች ዘንድ ግን ቃሉ እንደ ስድብ ሆኗል። እነዚህ ወገኖች ቃሉን የዘመኑ ልጆች የፈለሰፉት እንግዳና አፍራሽ ሥራ የሚከናወንበት አሉታዊ ቃል ለማስመሰል ጥረት ያደርጋሉ። የኖረውን ሃይማኖት ለማበላሸትና ለማጥፋት የተነሣ ዐዲስ ወይም መጤ ሃይማኖት አስመስለው እስከ ማቅረብና ብዙዎችን እስከ ማሳሳትም ደርሰዋል። የቃሉን መንፈሳዊ ትርጕም ተረድተው የእግዚአብሔርን ሐሳብ ለማገልገል የተነሡ አንዳንዶችም ከተቃዋሚዎች በኩል በቃሉ ላይ ከተከፈተው ዘመቻ የተነሣ ቃሉ ስድብ እየመሰላቸው፥ እየሸሹት፣ እየጠሉትና ሌላ አቻ ቃል እየፈለጉለት ይገኛሉ።

ካለፉት ስድስት ዐሥርት ዓመታት በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን ሆኖ የሚያገለግለው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ፥ ከ1960ዎቹ መጨረሻ አንሥቶ እስከ መስከረም 1982 ዓ.ም. ድረስ የተሐድሶ ዐምድ ነበረው። የዐምዱ ስያሜ በመጀመሪያ “ለተሐድሶ ዓምድ ለውይይት” የሚል ነበር። በኋላ “ተሐድሶ ዐምድ ለውይይት” ሆኗል። በዚህ ስያሜ እስከ ነሐሴ 1979 ዓ.ም. ድረስ ቀጥሏል። ከዚያ እስከ መስከረም 30/1982 ዓ.ም. ድረስ “የተሐድሶ ዐምድ ለውይይትና ለትምህርት” ተብሎ ቀጥሎ የነበረ ሲሆን፥ ከዚያ ወዲህ ግን ዐምዱ ቀርቷል። የቀረበት ምክንያት የቤተ ክርስቲያቱ ተሐድሶ ተጠናቆ ነው በማለት ይሁን፥ ወይም ወቅቱ ከአስተዳራዊ ተሐድሶ በላይ፥ ወሳኙ መንፈሳዊ ተሐድሶ እየመጣ የነበረበት ወቅት ስለ ሆነ ያን በመፍራት ይሁን የታወቀ ነገር የለም። ከዚያ ወዲህ ግን ቀድሞ በበጎ ይታይና ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስፈላጊነቱ ታምኖበት ይሞካሽ የነበረው ተሐድሶ፥ ፀረ ተሐድሶ ዐቋም ባላቸው ወገኖች፥ መጥፎ ገጽታን እንዲላበስና እንዲጠላ ተደርጎ ብዙ ስለ ተነገረበትና በሌሎችም ምክንያቶች አንዳንዶች ዛሬም ተሐድሶ የሚለውን ስም በበጎ ጎኑ አይመለከቱትም።

በዐምዱ ላይ የሚቀርቡትን ጽሑፎች በተመለከተ ዐምዱ፥ “የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር የሚሻሻልበትን፣ የገቢ ምንጭዋ የሚስፋፋበትን፣ መሪዎችዋ የሚመረጡበትንና በተሐድሶ ጎዳና የምትመራበትን መንገድ በማብራራትና በማስረዳት በግለ ሰቦች የሚቀርቡ አስተያየቶች ናቸው” ይላል። ጋዜጣው በዘመኑ የነበረውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት ያደረገ ተሐድሶኣዊ መልእክት ያስተላለፈባቸው ርእሰ አንቀጾችም አሉት። ለምሳሌ፡- የጥር 20/1971 ዓ.ም. እና የመስከረም 5/1972 ዓ.ም. ርእሰ አንቀጾች፥ “ተግባራዊ ተሐድሶ” እና “ተሐድሶ በተግባር” በሚሉ አርእስት ተሐድሶኣዊ መልእክቶችን አስተላልፈዋል። በተለይ የመስከረም 5/1971 ዓ.ም. ርእሰ አንቀጽ “የኢትዮጵያ አብዮት ከፈነዳ ወዲህ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ ብዙ ጊዜ በቃህ[] ሲነገር ይሰማል፤ ይሁን እንጂ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ አንዳንድ የተሐድሶ ምልክቶች ሊታዩ አልቻሉም ብለን መናገር ባንደፍርም፥ ብዙ በቃል የሚነገረውን ያህል በተግባር ተተርጕሟል ብሎ መናገር ደግሞ አዳጋች ይሆናል” በማለት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሚነገረው በላይ ተሐድሶን በተግባር እንድታሳይ መልእክቱን አስተላልፋል።

“ተሐድሶ” የሚለው ቃል ለቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነ ለኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት እንግዳ ባለመሆኑ፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊነቱን ተገንዝበው ከጥንት ጀምሮ ሲጠቀሙበትና ሲሠሩበት እንደ ነበረ ይታወቃል። ቃሉን በግልጽ ከተጠቀሙ ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ አንዱ ናቸው። እኒህ ትጉሕና የለውጥ ሐዋርያ የነበሩት አባት፥ ለ1ኛ ዓመት የፓትርያርክነት በዓለ ሢመት ያቋቋሟትን መጽሔት ስም “ሐዲስ ሕይወት” ብለው ሰይመዋታል። ከሽፋኑ እግርጌው ላይም “ንሕነኒ ናንሶሱ ውስተ ሐዳስ ሕይወት” የሚል ቃል በግእዝ ተጽፏል፤ “እኛ ግን በሐዲስ ሕይወት እንመላለሳለን” ማለት ነው።

የመጽሔቱ መክፈቻ የሆነውና “ሐዲስ ሕይወት” የሚለው የቅዱስነታቸው መልእክት፥ “የሰው ልጅ ዳግም ልደት ያገኘበት መንፈሱ፣ ኅሊናው፣ ሁለንተናው የታደሰበት፥ ሁል ጊዜ በየቀኑ የሚታደስበት የዘለዓለም ፍሥሓ መገኛ የሚሆን የእግዚአብሔር ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን” በሚል ሰላምታ ይጀምራል። ሐተታውን በመቀጠልም፥ “ዐዲስ፣ አሮጌ፥ ዘመናዊ፣ ጥንታዊ የሚል የተለያየ ሐሳብ በየዘመኑ የነበረ ያለም ነው። ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው ሕይወት ዐዲስነት ከዚህ ጋር ግንኙነት የለውም። የማያረጅ፣ የማይለወጥ ሁል ጊዜ ዘላቂ፣ ጠባዩን እንደ ያዘ የሚኖር፥ መታደስን ለሚመኙና ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ትክክለኛ አቅጣጫ የሚያዩበት መለኮታዊ መርሕ ያለበት ትምህርት ነው” ይላል።

ቅዱስነታቸው፥ ተሐድሶ ሰው ሠራሽ ፍልስፍና ሳይሆን መለኮታዊ ሐሳብ ያለበት ቃል መሆኑን ለማስገንዘብ፥ ቃሉ የተነገረባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ዋቢ አድርገው በመጥቀስ የሚከተለውን ሐሳብ አስፍረዋል። “ሐዲስነት ያለማቋረጥ ሁል ጊዜ በክርስቶስ መታደስ (ወእንተ ውስጥነሰ ይትሐደስ ኵሎ አሚረ - ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፤ 2ቆሮ. 4፥16) መሆኑን ለማስገንዘብ ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመናት መካከል ያለማቋረጥ የሚያስተጋባ ብርቱ ድምፅ ደጋግሞ አስምቶአል።

“‘ወይእዜሰ በክርስቶስ ተሐደሰ ኵሉ ዘኮነ ወኀለፈ ዘትካት - ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን ዐዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም ዐዲስ ሆኖአል።’ (2ቆሮ. 5፥17)፤
“‘ሐደሰ ለነ ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት ግብተ በመንጦላዕተ ሥጋሁ - በሥጋው መጋረጃ በኩል የሕይወትንና የጽድቅን መንገድ ፈጽሞ ዐድሶልናል’ (ዕብ. 10፥20/ የ2000 ዓ.ም. ዕትም)፤
“‘እስመ ኀለፈ ዘቀዳሚ ሥርዐት ወናሁ ተሐደሱ ኵሎሙ - እነሆ፥ ሁሉን ዐዲስ አደርጋለሁ’ (ራእ. 21፥5)፤
“‘ንሕነኒ ናንሶሱ ውስተ ሐዳስ ሕይወት - እንዲሁ እኛም በዐዲስ ሕይወት እንድንመላለስ … (ሮሜ 6፥4)፤
“‘ሐድሱ መንፈሰ ልብክሙ ወልበስዎ ለሐዲስ ብእሲ ዘሐደሶ እግዚአብሔር በጽድቅ ወበርትዕ በንጽሕ - በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።’ (ኤፌ. 4፥24) በዚህ ትምህርተ ተሐድሶ፥ ጽድቅ፣ ርትዕ፣ ንጽሕ ለሰው ሁሉ የመንፈሳዊ ሕይወት ጕዞ (አቅጣጫ) መሪዎች ናቸው” (ሐዲስ ሕይወት 1964፣ 7)።

ቅዱስነታቸው አክለውም ቤተ ክርስቲያን የመታደስና የዳግም ልደት መገኛ ባለቤት መሆኗን ገልጸዋል። በርግጥም ተሐድሶ ከውጭ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚገባ እንቅስቃሴ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያን ዘወትር በእግዚአብሔር ቃል ራሷን እየመረመረች ልታነሣሣውና ልታከናውነው የሚገባ አምላካዊ የንስሓ ጥሪ ነው።

ቅዱስነታቸው ቤተ ክርስቲያንን ከልማድ ቊራኛነት በማላቀቅ፥ በትክክለኛው የወንጌል ጎዳና እንድትጓዝ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ አንዳንድ ሙከራዎችን ጀምረው ነበር። የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዋና ሥርዐተ አምልኮ መፈጸሚያ የሆነውን መጽሐፈ ቅዳሴን ከግእዝ ወደ ዐማርኛ በመተርጐምና በአገልግሎት ላይ በማዋል ሕዝቡ በሚሰማው ቋንቋ እግዚአብሔርን እንዲያመልክ ዕድል ፈጥረዋል፤ ከውጭ ቆሞ የሚያስቀድሰው ሕዝብም የአምልኮው ተካፋይ እንዲሆን ሥርዐተ ቅዳሴውን በድምፅ ማጉያ እንዲካሄድ አድርገዋል (ተኮናኙ ኮናኝ 2000፣ 35)። ‘ቀዳሾች ዐምስት ካልሞሉ ቅዳሴ ሊከናወን አይችልም’ የሚለውን ልማድም፥ ብዙ አገልጋይ በሌለበት ቦታ ምእመናን እንዳይጕላሉ ከ3 ባላነሱ አገልጋዮች  እንዲቀደስ ማሻሻያ አድርገዋል (ዝክረ ቴዎፍሎስ ሰማዕት 1989፣ 35)።  

በአጽዋማትና በበዓላት ላይም ማሻሻያ እንዲደረግ በቅዱስ ሲኖዶስ ተጠንቶ ሕዝቡ አስተያየት እንዲሰጥበት ተወስኖ የነበረ ሲሆን፥ ሲኖዶሱ የሚከበሩትን ዓመታውያን በዓላት ዝርዝር አቅርቧል። “ሕዝቡ ግን እንደ ልማድ አድርጎ ዛሬ በየወሩ የሚያከብራቸው በዓላት በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት የተሠሩ ናቸው እንጂ ሲኖዶስ ዐውቋቸው የምእመናን ግዴታ ሆነው የሚከበሩ አይደሉም” በማለትሕዝቡ የተዘረዘሩትን በዓላት ብቻ እንዲያከብርና በሌሎቹ ግን እንዲሠራ የሚል የማሻሻያ ሐሳብ በማቅረብ ሕዝብ አስተያየቱን እንዲሰጥበት ውሳኔ አስተላልፎ ነበር (ሐዲስ ሕይወት 1967፣ 32-33)።

አጽዋማትን በተመለከተም ሰባቱ አጽዋማት ተብለው ከሚታወቁት መካከል ጌታ የጾመው ፵ ጾም፣ ረቡዕና አርብ፣ የልደት ገሃድ፣ የጥምቀት ገሃድ፣ ጾመ ነነዌ፣ ጾመ ፍልሰታ የተለመዱ መሆናቸውን ጠቅሶ፥ ሕሙማን፣ ወታደሮች፣ መንገደኞች፣ የፋብሪካ ሠራተኞች፣ ከፍተኛ ጥናት ባለው በትምህርት ላይ የሚገኙና ከባድ ሥራ የሚሠሩ ከጥሉላት (የፍስክ ምግቦች) በቀር ቊርስ እንዲበሉ ተፈቅዷል። ጾመ ነቢያት (የገና ጾም) እና ጾመ ሐዋርያት (የሠኔ ጾም) ግን “እንደ ዐበይት አጽዋማት ስለማይቈጠሩ የጾሙ መታሰቢያነት እንዳይረሳ ያህል የነቢያትና የሐዋርያት ጾም ለሕዝቡ ሲባል፥ ካልጾሙ ፋሲካ ካላዘኑ ደስታ አይገኝምና ከየአጽዋማቱ መጨረሻ ዐምስት ዐምስት ቀናት በመጾም የክርስቶስ ልደትና የሐዋርያት ዓመት በዓል እንዲከበር” ሐሳብ ቀርቧል (ዝኒ ከማሁ ገጽ 33)።  ይህንኑ ተዳፍኖ የቈየውን የማሻሻያ ሐሳብ በ2000 ዓመተ ምሕረት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የታተመውና “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ.ም. ” የተሰኘው መጽሐፍ ቈስቊሶታል (ገጽ 37፡52)።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ወግ አጥባቂዎችና የልማድ ቊራኛዎች ትናንትም ሆነ ዛሬ ለሲኖዶስ ውሳኔ ተገዢ ባለመሆናቸው እነዚህን ውሳኔዎች አክብረዋቸዋል ማለት አይቻልም። እንዲያውም በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነውን ውሳኔ በመቀልበስና ያለ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከዚህ በፊት የማይታወቁ “ቅዱሳን”ን እያስተዋወቁ፣ “ገድላቸውን” እያጻፉ፣ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን እያሳነጹና የጕዞ መርሐ ግብሮችን እያዘጋጁ ብዙ በዓላትን በፈቃዳቸው ሠርተዋል።

በአጽዋማት ረገድ ከተለመዱት አጽዋማት ውጪ ማሻሻያ የተደረገባቸውን ማሻሻያቸውን ባለመቀበል የቀደመው አሠራር እንዲቀጥል ከማድረጋቸውም በላይ፥ ካሁን ቀደም በጾምነት የማይታወቀውን “የጽጌ ጾም” በሚል ያለ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተጨማሪ ጾም ሠርተዋል። ለምሳሌ፡- ማኅበረ ቅዱሳን የተባለው ማኅበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጽጌ ጾም የሚል አክሎ 8 አጽዋማት እንዳሏት በነሐሴ 1987 ሐመረ ተዋሕዶ ላይ ጽፎ ነበር፤ ይሁን እንጂ ይህን ከቤተ ክርስቲያን ቀኖና ውጭ ማኅበሩ በገዛ ፈቃዱ የጨመረውን 8ኛ ጾም፥ “ጾመ ጽጌ የፈቃድ እንጂ ከሰባቱ አጽዋማት የሚቈጠር ስላይደለ … አስቸኳይ እርማት እንዲደረግበትና” በቀጣይ ማኅበሩ የሚያሳትማቸው ጽሑፎች ሁሉ በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ አማካይነት እየታረሙ እንዲወጡ የኢኦተቤክ መንበረ ፓትርያርክ በቊጥር 6738/8513/87 በ2/13/87 ዓ.ም. ለማኅበረ ቅዱሳን ጽሕፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ ትእዛዝ አስተላልፎ እንደ ነበር የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ድረ ገጽ ላይ የወጣው መረጃ ይጠቊማል(http://www.eotcssd.org 6/13/2003 4:43 AM)። ነገር ግን ማኅበሩ ተሳስቼ ነበር ብሎ እርማቱን ያውጣ ወይም የተጻፈለትን ደብዳቤ ውጦ ዝም ይበል የታወቀ ነገር የለም። ሆኖም ከጊዜ ወደ ጊዜ የጽጌን ጾም እንደ 8ኛው ጾም ቈጥረው የሚጾሙ ወገኖች እየተበራከቱ መምጣታቸው፥ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ያስተላለፈው ትእዛዝ ውሃ እንደ በላው አስቈጥሯል ማለት ይቻላል ።             

በቅዱስነታቸው ዘመነ ፕትርክና በአጽዋማት ላይ የተደረገውን ማሻሻያ አልቀበል ያሉ ወገኖችን ሁኔታ የሚያሳይ ቀልድ ይነገር ነበረ፤ በገና ጾም ወቅት ሁለት ሰዎች ሥጋ ለመብላት ወደ ልኳንዳ ቤት ሞቅ ያለ ጨዋታ ይዘው ይሄዳሉ። ይጫወቱ የነበረው ሲኖዶሱ አሳለፈው በተባለው የጾም ማሻሻያ ጕዳይ ላይ ነበር። ጨዋታቸው ስላልተቋጨ ያዘዙት ሥጋ እስኪመጣ ድረስ እንደ ገና ቀጠሉበት። ከጎናቸው ተቀምጦ ቊርጥ ሥጋውን የሚበላው ሌላ ሰው ጨዋታቸው ጆሮውን ይስበውና ይቀላቀላቸዋል፤ “ለመሆኑ ይህ ጳጳስ ምንድን ነው የሚለው?” ይላል። ከሁለቱ አንደኛው፥ “የገናና የሠኔ ጾም ይቀነስ ነው የሚለው” ሲል ይመልስለታል። በዚህ ጊዜ ሥጋውን በጥርሱና በእጁ ይዞ እየቈረጠ “እንሞታታለን እንጂ የገናና የሠኔ ጾም አይቀነስም!!” አለ ይባላል። ለዚህ ሰው የገናና የሠኔ ጾም ከቶ ምኑ ነው?

ቅዱስነታቸው ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎቹንም ተሐድሶ ያወጁባቸውን ልማዶችና ወጎች በሥራ ላይ እንዳያውሉ “መሻሻልንና ለውጥን ከማይፈልጉ ወግ አጥባቂዎች” እና ከሌሎችም ፀረ-ቴዎፍሎስ ቡድኖች የነበረባቸው ተግዳሮት ቀላል አልነበረም (ዝክረ ቴዎፍሎስ ሰማዕት 1989፣ 35)። የእርሳቸውን ራእይ የሚደግፉ ወገኖች የቅዱስነታቸው ራእይ ቢፈጸም ኖሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ወደ ተሻለ መንፈሳዊ ደረጃ ትደርስ ነበረ ሲሉ፥ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሆነው ድምፃቸውን እያሰሙ ነው።

በጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል “ራእየ ቴዎፍሎስ” በሚል ስያሜ በተዘጋጀው መጽሔት ላይ፥ “በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ” በሚል ርእስ የቀረበው ጽሑፍ፥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በሕይወት ቢቈዩ ኖሮ ሊመጣ የሚችለውን ለውጥ ዘርዝሯል። ከሚጠቀሱትም መካከል፥ “ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ እስከ ዛሬ ድረስ ቢኖሩ ኖሮ፥ … እምነትን ከማይጠቅም ባህል፣ ልማድና ተረት በመለየት በነበራቸው ጥበብና ድፍረት፥ የቤተ ክርስቲያቱን አንድ ወጥ የእምነት ሥርዐት እንዲዳብር ያደርጉ ነበር” የሚለው ይገኝበታል (ራእየ ቴዎፍሎስ 2002፣ 16)።
     
ትምህርተ ቴዎፍሎስ
ቅዱስነታቸው፥ “በሊቅነታቸው ተርጕመው የሚያመሰጥሩ፣ በጣዕመ ስብከታቸው ተናገረው የሚያረኩ፣ በአመራራቸው የቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዐት ከልማድ ቊራኝነት ለይተው ለማስቀመጥና ክርስቲያኖች ትክክለኛውን መንገድ ተከትለው እንዲሄዱ ለማድረግ ችሎታ ያላቸው፣ ትክክለኛውን የቤተ ክርስቲያን ባህል ምርት ከወግ አጥባቂነት ገለባ ለማጥራት መንሽና ላይዳ የሆነ እውነትና ሥልጣኔ የነበራቸው፣ ይህንንም ለመፈጸም የወግ አጥባቂዎች ፈሪሳውያን አሉባልታ የማይፈታቸው፣ ፍርሀትና ማመንታት የማያውቁ ቈራጥና ጥቡዕ ሰማዕት” ናቸው (ዝክረ ቴዎፍሎስ ሰማዕት 1989፣ 35) ተብሎ የተመሰከረላቸው ሊቅ እንደ ነበሩና እምነታቸውና ትምህርታቸው በልማድ ላይ ሳይሆን በቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀት ላይ የተመሠረተ እንደ ነበረ፥ በተለያዩ ጊዜያት ከሰጧቸው ምስክርነቶች፣ ካስተማሯቸው ትምህርቶችና ካሰሟቸው ንግግሮች መገንዘብ ይቻላል። ሁለተኛው ፓትርያርክ ሆነው በተሾሙበት ዕለት የገለጡት ኦርቶዶክሳዊ እምነታቸው ከልማድ የተለየና በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ተመሥርቶ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ሲገልጡት የኖረና የቀና እምነት ነው።

በበዓለ ሢመቱ ላይ ለተሰበሰበው ሕዝብ ባሰሙት ቃለ ሃይማኖት፥ “ከሁላችሁ ጋር አብሬ ስለምካፈለው በእግዚአብሔር ጸጋ ልጠብቀውና ላስፋፋው ስለምፈልገው እምነት ምስክር መስጠት መልካም ሆኖ ታይቶኛል” በማለት ስለ እምነታቸው ምስክርነት ሰጥተዋል። በምስክርነታቸው የገለጡት እምነት፥ በሥላሴና በክርስቶስ ላይ ያተኰረ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነትና በተቀበለቻቸው የሃይማኖት ቀኖናዎች ላይ የተመሠረተ ነው። ስለ ሥላሴ፥ “አንድ አምላክ በሚሆን በቅድስት ሥላሴ ያለኝን እምነት እመሰክራለሁ። እግዚአብሔር አንድ ነው፤ እሱም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ይባላል። አብ ፍጹም አምላክ ነው። ወልድ ፍጹም አምላክ ነው። መንፈስ ቅዱስ ፍጹም አምላክ ነው። ግን አንድ አምላክ ይባላል እንጂ ሦስት አማልክት አይባልም” (ሐዲስ ሕይወት 1964፣ 39) በማለት ትምህርተ ሥላሴን አመስጥረዋል።

ስለ ክርስቶስ በሰጡት ምስክርነትም፥ ከሥላሴ አንዱ እግዚአብሔር ወልድ እኛን ለማዳን ከድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ የነሣውን ሥጋና ነፍስ ያለመለወጥ፣ ያለመቀላቀል፣ ያለመለያየት፣ ያለመከፋፈል በሆነ ተዋሕዶ ከራሱ ጋር በአንድ አካል ማዋሐዱንና ፍጹም ሰው ሆኖ መወለዱን ገልጠዋል። “አንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ነው፤ እሱም ፍጹም ሰው ነው። … በዚህም ተዋሕዶ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል በመሆን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለዘለዓለም ይኖራል”  ሲሉም ማንነቱንና ግብሩን አስረድተዋል። ስለ አዳኝነቱ ከሰጡት ምስክርነት መካከል የሚከተለው ይጠቀሳል፤ “በአዳኝነቱም ሰውን ከእግዚአብሔር አብ ጋር አስታርቆ ለሰው የእግዚአብሔርን ልጅነት እንደ ገና መለሰለት፤ … የሰይጣንን ኀይል ድል ለመንሣት ክርስቶስ ስለ እኛ በመስቀል ላይ ሞተ፤ በሦስተኛውም ቀን በአሸናፊነት ከሙታን ተለይቶ ተነሣ። ክርስቶስ በትንሣኤው ያስገኘው ድል በመላው ዓለም ለሚገኘው የሰው ልጅ ነው” (ሐዲስ ሕይወት 1964፣ 40)።

የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ሲያስገነዝቡም፥ “የተሰቀለውና ከሙታን የተነሣው ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተው በመስቀሉና በትንሣኤው ያስገኘው ድኅነት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለመላው ዓለም ይገለጥ ዘንድ ነው። ክርስቶስ ሁል ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ዐድሮ ይኖራል። መንፈስ ቅዱስም ሁሉ ጊዜ የቤተ ክርስቲያንን ሕይወትና ተግባር ይመራል። ቤተ ክርስቲያን የሁሉ ናት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም የዚህች የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ክፍል ናት” ብለዋል (ሐዲስ ሕይወት 1964፣ 40)። ክርስቲያናዊ አስተሳሰብ ይሏል ይህ ነው!!

ቤተ ክርስቲያንን ቤተ ክርስቲያን ያሰኟትን መሠረታውያን አስተምህሮዎች ጠንቅቀው የተረዱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ፥ ሌሎች ልዩነቶች ቢኖሯቸውም በትምህርተ ሥላሴና በትምህርተ ሥጋዌ አንድ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናት የአንዲቱ ቤተ ክርስቲያን ክፍሎች መሆናቸውን በመገንዘብ፥ ከመለያየት ይልቅ መቀራረብና አንድነትን መፍጠር እንደሚገባቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰብከዋል። ስለዚህ ሁኔታ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በጻፉት የቅዱስነታቸው ዐጭር የሕይወት ታሪክ ላይ የሚከተለውን አስፍረዋል፤ “ከሁሉም በላይ በታላላቅ ጉባኤዎች ላይ በመገኘት ባደረጓቸው ንግግሮች የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት በሚያምኑ አብያተ ክርስቲያናት መካከል መተባበር፣ መቀራረብና አንድነት እንዲጠናከር አስገንዝበዋል” (1987፣ 32)።

ቅዱስነታቸው ግንቦት 10/1965 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በዩ.ኤስ. አሜሪካ አብያተ ክርስቲያናት ብሔራዊ ጉባኤ ማእከል ተገኝተው በእርሳቸው መሪነት ዓለም ዐቀፋዊ የጸሎት ሥነ ሥርዐት ከተካሄደ በኋላ፥ ካስተላለፉት መልእክት መካከል የሚከተለውን መጥቀስ ይቻላል። “በዛሬው ጊዜ አብያተ ክርስቲያናትን የሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች በጣም ታላላቅና የተወሳሰቡ እንደ መሆናቸው መጠን፥ በዚህ ወቅት ሀብትንና ኀይልን ባልተቀናጀና ባልተያያዘ ሁኔታ እንዲያውም ተቃራኒ በሆኑ የተለያዩ አቅጣጫዎች ማባከን ብልኅነት የጐደለውና ቤተ ክርስቲያንን የሚጐዳ እንደ ሆነ ይሰማናል። ዛሬ በአፍሪካ ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን የገጠሟቸው ችግሮች አምልኮተ ባዕድና እግዚአብሔር የለም ባይነት፣ ቊስ አካላዊነትና ኮሚኒዝም፣ ድንቊርና፣ ድኽነት፣ በሽታ፣ የፍትሕ መጓደል መከራና ሥቃይ ናቸው። እነዚህን ችግሮች ዝም ብለን ልናያቸው አንችልም። ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም መድኀኒትና አዳኝ መሆኑን በጋራ የሚያምኑ አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን ችግሮች ለመቋቋምና የእግዚአብሔርን ቃል በፍቅር፣ በአጽንዖትና በንቃት ለመስበክ፣ በተግባርም ለመግለጽ እንዲችሉ በክርስቶስ ዐርማ ሥር በአንድነት መሰባሰብ ይገባቸዋል። …” (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ 1987፣ 38-40)።

በዚያ ዘመን የነበሩ ሚስዮናውያን በአፍሪካ ምድር ስላከናወኑት በጎ ተግባርና እያደረሱ ስላለው ጥፋት ሚዛናዊ የሆነ አመለካከታቸውን በጉባኤው ላይ አንጸባርቀዋል፤ “ወደ አፍሪካ የገቡ ሚስዮኖች የእግዚአብሔርን ቃል በመስበክ፣ ትምህርትን፣ ጤንነትን በማስፋፋት ታላላቅ ተግባራትን ቢፈጽሙም፥ ዋጋ ቢስ ከሆነ የጭቈና ሥርዐት ጋር ራሳቸውን ማሰለፋቸው በአሁኑ ጊዜ አሳሳቢ ችግር ፈጥሯል፤ ከአህጉሩ ውስጥና ውጭ ለሚነሡ የክርስትና እምነት ተቃራኒዎችም ተጨማሪ ኀይል ሰጥቷል” (ዝኒ ከማሁ 39)።

ቅዱስነታቸው ስብከተ ወንጌልን በተመለከተ የቤተ ክርስቲያናቸውን የወደ ፊት ራእይ ሲገልጹም እንዲህ ብለው ነበር፤ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም ሁላችንም የምንሰብከውን አንዱን ጌታ ለማገልገል ከእኅት አብያተ ክርስቲያናት ጋር በመተባበር በአፍሪካ ለዐዲስና ለተጠናከረ የስብከተ ወንጌል ተግባር ዋና መሣሪያ ልትሆን ትችላለች” (ዝኒ ከማሁ 38-39)።

ቅዱስነታቸው በጨዋታ እያዋዙ የሚያስተላልፏቸው መልእክቶች የሰውን አስተሳሰብ የሚያጐለምሱና በበጎ ሥነ ምግባር የሚቀርጹ እንደ ነበሩ ይነገርላቸዋል። እርሳቸው የተናገሯቸው የሚባሉና በቃል የሚነገሩ በርካታ ብሂሎች አሉ። ከእነዚያ መካከል አንዱ እነሆ! “አቡነ ቴዎፍሎስ የፓትርያርኩ የአቡነ ባስልዮስ እንደ ራሴ ሆነው ይሠሩ በነበሩበት ጊዜ አንድ ሰው ሊያነጋግቸው ወደ ቢሮአቸው ይመጣል፡፡ ሰውየው በአቡነ ባስልዮስ ላይ ቅሬታ ስለ ነበረውንኑ ቅሬታውን ለአቡነ ቴዎፍሎስ ሲገልጽ ኀይለ ቃል እየተጠቀመ ነበር፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ ግን በአነጋገሩ ስላልተደሰቱ ሰውየው ተናግሮ ሳይጨርስ፣ ተው እኮ፤ እንዴት እንዲህ ትናገራለህ? አንተ ጤና የለህም እንዴ? ቅዱስ አባታችንን ነው እንዲህ የምታላቸው? በማለት ይቈጡታል፡፡
ሰውየው ከአቡነ ቴዎፍሎስ የዚህ ይነቱን አነጋገር አልጠበቀ ኖሮ ደንግጦ፣ አባታችን ይቅርታ ያድርጉልኝ፡፡ እንዲህ ማለት እንኳ አልነበረብኝም፡፡ እንዲያው አድጦኝ ነው ይላቸዋል፡፡
እሳቸውም መልሰው፤ ታዲያ ሰው ባይሆን ወደ ታች ያድጠዋል እንጂ ወደ ላይ ያድጠዋል [እንዴ]? አሉት ይባላል፡፡
ቅዱስነታቸውን የገጠሟቸው ተቃውሞዎችና በደርግ ሥርዐት የተቀበሉት መከራ
ምንም ቢሆን ሰው ከትችት አያመልጥም፤ በአንድ በኩል የተመሰገነ ሰው በሌላ በኩል ሊወቀሥ ይችላል። ካሁን ቀደም በጮራ ቊጥር 39 በዚህ ዐምድ ላይ ታሪካቸው የቀረበው ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፥ ለደረሰባቸው ለዚያ ሁሉ እንግልት የዳረጓቸው በዋናነት ዐፄ ኀይለ ሥላሴ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፤ ንጉሠ ነገሥቱ ከጀርባ ሆነው ቅጣቱን ሲበይኑባቸው፥ ጕዳዩን ሃይማኖታዊ ሕጸጽ በማስመሰል ከፊት ለፊት የከሰሷቸውና የፈረዱባቸው ግን በዚያ ጊዜ የፓትርያርኩ እንደ ራሴ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ እንደ ነበሩ ተናግረዋል። ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ከጥቂት ጳጳሳት ጋር በመሆን ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የጻፉትን መጽሐፍ እንዲያርሙ ነግረው አላርምም በማለታቸው እንዳወገዟቸውና እንዳጋዟቸው መጻፋችን ይታወሳል።

በሌላም በኩል ቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመሰገኑበት ጥቂት ነገር ቢኖርም የሚወቀሡበት ነገር ይበዛል የሚሉት ደግሞ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ናቸው። “የቋሚ ምስክርነት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ፥ “በጠባይ በኩል ፓትረያርክ ቴዎፍሎስ ዝግ ያሉ ከሁሉ ጋር መግባባት የሚፈልጉ ታጋሽም ነበሩ። ይህም ዝግታቸው ግን ለሥራ ጎታች ለሐሳብ አድካሚ ነበር። አንድ ለመምራት ቈርጦ የተነሣ ሰው ማለትም የሥራ ወኔ ያለው ወደ እርሳቸው ሲቀርብ በርዶ ቀዝቅዞ ይመለሳል፤ ሐሳቡም ተቀይሮ ሥራውም ቀርቶ ወይም ተቋርጦ ይገኛል። በመሠረቱ የሥራ ሰው አልነበሩም፤ የሠራተኛ መምረጥም ዕድል አልነበራቸውም፤ ስለዚህ በሄዱበት ሁሉ ይህን ሠሩ አይባሉም። ይሁን እንጂ ለዘመኑ አስተሳሰብ የሚግባቡ የዘመኑ አስተሳሰብም የሚገባቸው እርሳቸው በመሆናቸው ንጉሠ ነገሥቱ ለከፍተኛ ማዕረግ ለፓትረያርክነት እርሳቸውን ይመኙ ነበር” ብለዋል (ገጽ 18)።

በደርግ አምባገነናዊ ሥርዐት ከሥልጣን ለመውረድ የበቁባቸውን ምክንያቶችም ሲያስረዱ፥ “በመጀመሪያ እርሳቸው በፓትርያርክነት ሥልጣናቸው ስላልሠሩበት፤ መብታቸውን ዝም ብለው ስላስወሰዱት፤ 2ኛ ቤተ ክርስቲያን ሀብቷ ሲወሰድ፤ መብቷ ሲረገጥ ዝም ብለው ስላዩ፤ 3ኛ ለቀ ኃ ሥ የማሉትን መሓላን ስላፈረሱ፤ 4ኛ ስድሳው ሰዎች ሲገደሉ፤ ቀ ኃ ሥ ሲገደሉ ባለመናገራቸው፤ እንደ ፓትርያርክ ያያቸው፤ የቈጠራቸውም የለም። ከካህናትም ከሕዝብም በኩል ቢሆን ለምን እንዲህ ሆኑ ያለ አንድስ እንኳን እንቅስቃሴ ያደረገ የለም” ይላሉ። የሚጠቅም መስሏቸው ከደርግ ጋር መሥራት ጀምረው እንደ ነበርና በኋላ ግን እንደ ራቁ፥ ይህም የሕዝቡን ጥላቻ እንዳበረታባቸውም ተናግረዋል። ይህን የተረዳው ደርግም ስማቸውን በማጥፋት ሥራ ተጠመደ፤ ከዚያ ደርግ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥልጣን ለመቈጣጠር ባቋቋመው “በተሐድሶ ጉባኤ አባላትና በጥቂት አድር ባይ ጳጳሳት ውሳኔ ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ አስደረገ” ሲሉም ጽፈዋል (ገጽ 56፡68)። ቀደም ብለው የደርግን ድርጊት በግልጽ ቢቃወሙና ቤተ ክርስቲያን ልትይዝ የሚገባትን ዐቋም ቢያሳዩ ኖሮ ደርግ ወደ በለጠ ጥፋት አይሄድም ነበር፤ እርሳቸውንም አያስራቸውም፤ አይገድላቸውም ነበር። እንዲህ አድርገው ቢታሰሩና ቢገደሉ ኖሮም የዘመኑ ሰማዕት መባል ይገባቸው ነበር። ይህ ሁሉ ሳይሆን የተሰጣቸው የሰማዕትነት ክብር ተገቢያቸው አይደለም በማለትም ይከራከራሉ (ገጽ 67)።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በጻፉት የቅዱስነታቸው ዐጭር የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ላይ እንደ ገለጹት ደግሞ፥ አቡነ ቴዎፍሎስን በዋናነት ደርግና እርሱ ያደራጀው ጊዜያዊ የተሐድሶ ጉባኤ አባላት አላሠራ እንዳሏቸው ጠቅሰዋል። ደርግ ቤተ ክርስቲያንን መተዳደሪያና ንብረት አልባ ለማድረግ የጀመረውን ሀብቷንና ንብረቷን የመውረስ እርምጃ እንደ ተቃወሙና ያለ ተመጣጣኝ ካሣ የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት ሊወረስ እንደማይገባ ማስታወሻ ጽፈው ለጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ማቅረባቸውን ጽፈዋል።
    
ቋሚ ምስክርነት ለተሰኘው የብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ መጽሐፍ ምላሽ የሚሆኑ መጻሕፍት በተለያዩ ግለ ሰቦች የተጻፉ ሲሆን፥ ከእነዚህም አንዱ ዓለማየሁ ዓለምነህ የጻፉት “ተኮናኙ ኮናኝ” ይጠቀሳል፤ እርሳቸው እንደሚሉት፥ ቅዱስነታቸው የቀደመው (የንጉሡ) ሥርዐት አባል መሆናቸው ቢታወቅም፥ ከውስጥ የተጠነሰሰው ሤራና የተነሣሣው አድማ ወደ ውጭ እንዲወጣና እርሳቸውን ለማጥፋት ተጨማሪ ኀይል ሆኖ በጨካኙ በደርግ እጅ ለ3 ዓመታት ታስረው እንዲሠቃዩና በግፍ እንዲገደሉ አድርጓል። ከውስጥ ለተነሣባቸው የጠነከረ ተቃውሞ ዋና መነሻው ጎጠኛነትን መሠረት ያደረገው የሥልጣን ትግል መሆኑን ያስረዳሉ። ከመጀመሪያው ፓትርያርክ ሞት በኋላ፥ በአንድ ወገን ሸዬዎች (ደብረ ሊባኖሶች) በሌላ በኩል ጎንደሮች ፓትርያርክነቱ የሚገባው ለእኛ ነው በሚል ቅዱስነታቸውን የማጥላላት ሰፊ ዘመቻ ከፍተውባቸው እንደ ነበር እኒሁ ጸሓፊ ያትታሉ። ቅዱስነታቸው ከእነርሱ መንደር ተወልደው ቢሆን ኖሮ፥ “የሠራ አካላቱን በዘጠና ዘጠኝ ክንፎች ያሸበርቁት እንደ ነበረ አይጠረጠርም” ሲሉም ያክላሉ (ተኮናኙ ኮናኝ 2000፣ 122)።

ጸሓፊው፥ “ደርግ ፈራ ተባ እያለ እያለ በተዘዋዋሪ መንገድ ይጎነትላቸው ነበር እንጂ በቀጥታ እጁን አላሳረፈባቸውም ነበር። ይህን የደርግ ጕንተላ የተመለከቱ እነዚያ ሰማያት ተከፍተው የብርሃን መስቀልና የብርሃን አክሊል ይወርድልናል፣ መቋሚያውና ጸናጽሉ ይላክልናል፣ ከ24 ካህናተ ሰማይ ጋር ትከሻ ለትከሻ እየተሻሸን መንበረ ጸባዖትን እናጥናለን፣ ዲያብሎስንና እግዚአብሔርን ለዕርቅ እናደራድራለን፣ … እያሉ ራሳቸውን በራሳቸው ሲያንቆለጳጵሱ የነበሩ ምድረ ጎጠኛ ተረት አናፋሽ ታሪካዊ ጠላቶቻቸው” እንደ ተነሡባቸውና ዐዲስ ጥቃት እንደ ከፈቱባው ጽፈዋል (ዝኒ ከማሁ ገጽ 126)።

ቅዱስነታቸው ሁለተኛው ፓትርያርክ ሆነው ከመመረጣቸው በፊት “ከወዲያኛው ዐባይ ማዶ መጥተው የተሰባሰቡት ጎጠኞች ፓትርያርክነት የሚገባው ለእኛ ነው በማለት በአቶ መኮንን ዘውዴ (በወቅቱ የቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩ) እና በሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ (የአሁኑ አቡነ መልከ ጼዴቅ፥ የቋሚ ምስክርነት ጸሓፊ)” በኩል ጥረት አድርገው እንደ ነበረና እንዳልተሳካላቸው እኒሁ ጸሓፊ ያወሳሉ (ዝኒ ከማሁ ገጽ 127)። ብፁዕ አቡነ መልክ ጼዴቅም የቋሚ ምስክርነት በተሰኘው መጽሐፋቸው የቅዱስነታቸውን ስም ያጠፉት ሲመኙት የነበረውን ፓትርያርክነት ባለማግኘታቸው መሆኑን ይናገራሉ (ዝኒ ከማሁ ገጽ 24)።  የሁለቱን ወገኖች ክርክር ለታሪክ ተመራማሪዎች ትተን ወደ ሌላው በቅዱስነታቸው ላይ ወደ ተነሣው ተቃውሞ እናልፋለን።

ወንጌል ያለ መከራና ያለ ተቃውሞ አይሰበክም። የለውጥ ሐዋርያ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ፥ የጀመሩትን በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ ተሐድሶኣዊ ጕዞ ለማደናቀፍ ከውስጥና ከውጭ የተለያዩ ተቃውሞዎች ገጥመዋቸዋል። ዋና ዋና ተቋዋሚዎቻቸው፥
·        የደርግ አባላት፣
·        የጊዜያዊ ጉባኤ አባላትና የቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች፣
·        ኮከብ ቈጣሪዎች መሰግላን (ጠንቋዮች)፣
·        ዐንካሴ የሚሸከሙ ባሕታውያን መሰሎች እና
·        መሻሻልንና ለውጥን የማይፈልጉ ወግ አጥባቂዎች
እንደ ነበሩ፥ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ገልጸዋል። “እነዚህ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ባያሰናክሏቸው ኖሮ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን አሁን ካለችበት ደረጃ በበለጠ ያሳድጓት ነበር” ሲሉም አክለዋል (ዝክረ ቴዎፍሎስ ሰማዕት 1989፣ 35)።

በዚያ ወቅት ቅዱስነታቸውን የሚቀናቀኑ ከተባሉት “የሁለት ወንዝ ተወላጆች” መካከል አንደኛው ዛሬ ማኅበረ ቅዱሳን የተባለው ማኅበር የቀድሞ መሥራቾች የአጠቃላይ ጉባኤ አባላት እንደ ነበሩና ዐላማቸውንም ጭምር ዜና ቤተ ክርስቲያን የተባለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን ጽፏል፤ እንዲህ በማለት፡- “ማኅበረ ቅዱሳን አሁን የሚጠራበትን የክርስትና ስም ወደ ዝዋይ ወርዶ ሳያገኝ ምን ዐይነት ስመ ተጸውዖ እንደ ነበረው አሁን ያሉት የማኅበሩ አባላት እንኳን ሊያውቁት አይችሉም፤ ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ግን የቀድሞ ስሙን ገና ከጅምሩ ያውቀዋል፤ በአንድ ወንዝ ላይ ተመሥርቶ የሁለተኛውን ፓትርያርክ (የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን) አባትነት ላለመቀበል፣ ዐላማቸውን ለማደናቀፍና ለመኰነን አጠቃላይ ጉባኤ በሚል ስያሜ የተቋቋመ ማኅበር ነበር” (ዜና ቤተ ክርስቲያን፣ መጋቢትና ሚያዝያ 1996፣ 5፡7)።

በቅርቡ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ደጀሰማይ የተሰኘ ድረገጽ “ማኅበረ ቅዱሳን ይዞታዎቹን እየተነጠቀ መሆኑ ተገለጸ” በሚል ርእስ በለቀቀው ጽሑፍ ውስጥም፥ ከዚህ ጋር ሊገናዘብ የሚችል ሐሳብ እናገኛለን። በጉጂ ቦረና ሊበን ዞኖች በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ምእመናን ተወካዮች፣ በሻኪሶ ወረዳ አስተዳደር ጸጥታ ጽሕፈት ቤትና በሻኪሶ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ዕውቅና የተሰጣቸው 21 ሰዎች ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ባቀረቡት 11 ገጽ  አቤቱታ ላይ፥ “ቅዱስነትዎ ሆይ! አጠገብዎ እንደ እባብ የሚለሳለሰውን በዳር አገር እንደ አንበሳ የሚፎክረውን እርስዎን ሌጣ አድርጎ እንደ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ለሰማዕትነት ሲከጅልዎ የሚኖረውን በሃይማኖት ካባ ሹመት ናፋቂ የሆነውን ቀንና ሌሊት የቤተ ክርስቲያን ልጆችን የሚከሰውን መውጫው እንደ ደረሰ ጋኔን እየጮኸ ያለውን ማኅበር እንዲያስታግሡልንና እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገው ይህን የቤተ ክርስቲያን ጠላት እንዲነቅሉልን ስንጠይቅ ዐብረንዎ መሥዋዕት ለመሆን በመጨከንም ነው” የሚል ጽሑፍ ሰፍሯል (http:/WWW.dejesemay.org 6/6/2003 2:38 AM)።

በዜና ቤተ ክርስቲያን ላይ የቀደሙት የማኅበረ ቅዱሳን መሥራቾች የተባሉት የአጠቃላይ ጉባኤ አባላት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን አባትነት ላለመቀበልና ዐላማቸውን ለማደናቀፍ የተቋቋሙ መሆናቸው ተጠቅሷል። አሁን ባለው ማኅበረ ቅዱሳን ላይ በቀረበው አቤቱታ ውስጥ ደግሞ፥ “እርስዎን (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን) ሌጣ አድርጎ እንደ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ለሰማዕትነት ሲከጅልዎ” የሚለው ሐረግ የቀደሙትና የአሁኖቹ የዐላማ መመሳሰል እንዳላቸው የሚጠቊም ፍንጭ ያለው ይመስላል።

ማኅበረ ቅዱሳን የልቡን የሚተነፍስበት ተብሎ በስፋት የሚታማው ደጀሰላም የተባለው ድረገጽም በተለያዩ ጊዜያት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ላይ የሚለቃቸው አንዳንድ መረጃዎች ይዘትም፥ በአቤቱታው ውስጥ የተጠቀሰውን ሐረግ የሚያጐላ ሆኖ ይታያል። ለምሳሌ፡- በማርች 11,2011 “ተሐድሶ - በወሊሶ” በሚል ርእስ በለቀቀው ጽሑፍ ላይ አስተያየት ከሰጡ ሰዎች መካከል አንዱ እንዲህ ብሎ ነበር፤ “ወሬ ማብዛት ብቻ!! ተሐድሶ፤ ካቶሊክ፤ ጴንጤ ምናምን ማለት ምን ዋጋ አለው? እስኪ ልብ ካላችሁ መበለት እጅጋየሁንና የዕውቀት መጢቃ []ጋሻውን ያሰማራውን ነጭ ለባሽ ግን ራው ጥቁሩን ሰውዬ አስወግዱ!! ግንዱን መጣል ሲያቅታችሁ ቅርንጫፉ ላይ ትንጫጫላችሁ። አንዱ ቅርንጫፍ ቢቈረጥ ግንዱ ካለ ሌላ ቅርንጫፍ የማይወጣ ይመስላችኋል?” (አጽንዖት የግል)።     

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በደርግ፣ በጊዜያዊ ጉባኤ አባላትና በአንዳንድ የቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች ትብብር የካቲት 9 ቀን 1968 ዓ.ም. ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ ከተደረገ በኋላ በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ውስጥ በሚገኝ ጠባብ ክፍል ውስጥ እጃቸውንና እግራቸውን ከዐልጋ ጋር ተጠፍረው ታሰሩ። ቊጥር 1 ወደሚባለው እስር ቤት ከተዛወሩ በኋላም በደርግ ጭፍሮችና ዘቦች ሞራላቸውን የሚነካ ንግግርና ሌላም ብዙ መከራ ተቀብለዋል። ግላዊ ነጻነታቸውና መብታቸው በተገፈፈበት ሁኔታ እስከ ሐምሌ 7 ቀን 1971 ዓ.ም. በዚህ ሁኔታ ከቈዩ በኋላ፥ ቅዱስነታቸው የት እንደ ደረሱ፥ ምን ዐይነት ግድያ እንደ ተፈጸመባቸው፥ የት እንደ ተቀበሩም ሳይታወቅ ለ13 ዓመታት ያህል ተዳፍኖ ቈየ። የደርግ መንግሥት ወድቆ ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቈጣጠረ በኋላ፥ ቅዱስነታቸው በአሠቃቂ ሁኔታ ተገድለው አስከሬናቸው የተጣለበት ቦታ በከፍተኛ 12 ቀበሌ 22 ከሚገኘው ልዑል ዐሥራተ ካሳ ቤት መሆኑ ስለ ታወቀ፥ ከዚያ ተቈፍሮ ወጥቶ ሐምሌ 4 ቀን 1984 ዓ.ም. ራሳቸው ባሠሩት በጐፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል በክብር ዐርፏል። በቅዱስ ሲኖዶስም ሰማዕት ተብለው ተሠይመዋል።

እናስተውል
·        ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ለቤተ ክርስቲያን መታደስና ወደ ፊት መራመድ ብዙ መሠረቶችን ጥለዋል። “ዘመን ተሻጋሪ የቤተ ክርስቲያን ባለውለታ አባት” ቢሆኑም፥ “ባሳደጓቸው፣ ባስተማሯቸውና ለሹመት ባበቋቸው ልጆቻቸው ቈስቋሽነት የመከራው ገፈት ቀማሽ እንዲሆኑ ተደረገ” (ራእየ ቴዎፍሎስ 2002፣ 5)። የቅዱስነታቸው አላግባብ ከሥልጣን መውረድና በግፍ መገደል የጐዳው እርሳቸውን ብቻ ሳይሆን፥ በተሐድሶ ጐዳና ላይ የነበረችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንንም ጭምር ነው። ለነገሩ አሳልፈው የሰጧቸው የቤተ ክህነት ባለሥልጣናትንም አሳልፎ ሰጪነታቸው አልጠቀማቸውም። የእርሳቸው መልካም ሥራዎች ግን ዛሬም ድረስ በበጎ ገጽታቸው ይነሣሉ፤ አሁን ላለው ትውልድም ትልቅ አርኣያነት አላቸው።

ዛሬም የቤተ ክርስቲያን አባቶች፥ ሕዝቡን ቅዱስነታቸው ከእግዚአብሔር ቃል ወዳመላከቱት ተሐድሶ መምራትና በሁለንተናዋ በወንጌል የታደሰችና የተለወጠች ቤተ ክርስቲያንን ለክርስቶስ ንጽሕት ሙሽራ አድርገው ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው እሙን ነው (2ቆሮ. 11፥2)። ለዚህም በብፁዕ አቡነ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የተጀመረውን ተሐድሶኣዊ ጕዞ አጠናክረው መቀጠል ያለባቸው መሆኑ አከራካሪ አይሆንም። ብዙ ዋጋም ያስከፍላል።

·        አንዱ ሌላውን ለመጣል በሚያደርገው የሥልጣን ትግል በርካታ የተሐድሶ ወርቃማ ዕድሎች በከንቱ ባክነዋል። አባቶች ለግል አጀንዳቸው እርስ በርስ ከመታገል ይልቅ ለቤተ ክርስቲያን ተሐድሶና እድገት በጋራ ቢሠሩ ቤተ ክርስቲያን ወደ ተሻለ ነገር ትደርስ ነበር። በቅዱስነታቸው ላይ የተደረገው ሁሉ ዛሬም እንዳይደገም አባቶች የመሪነት ሥራቸውንና ኀላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው። ከዚህ ውጭ አንዱ ሌላውን ለመጣል አባቶችን በማቧደንና በማጋጨት ሃይማኖት ለበስ ድብቅ አጀንዳውን በቤተ ክርስቲያን ስም ለማራመድ የሚያደርገው ጥረት፥ በእንጭጩ ካልተቀጨ፥ የቀድሞው “አጠቃላይ ጉባኤ” ርዝራዦች፥ እንዲሁም ልጆቻቸው የአባቶቻቸውን ሥራ ላለመድገማቸው ምንም ዋስትና የለም። ስለዚህ ዛሬ ያሉት አባቶች ካለፈው መማርና ከግላዊ አጀንዳቸው ይልቅ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት መታደስም መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

·        ቤተ ክርስቲያን በዘመናዊ አሠራር፣ በልማት፣ በበጎ አድራጎትና በመሳሰለው ሁኔታ ከዘመኑ ጋር መጓዝ እንዳለባት ሁሉም ይስማማል ማለት ይቻላል፤ በመንፈሳዊ ዐቋሟ በእግዚአብሔር ቃል ራሷን እየመረመረች በየጊዜው ተሐድሶ እንድታደርግና እግዚአብሔር ወዳቀደላት ግብ እንድትደርስ ደግሞ የእግዚአብሔር ዐላማ ነው። ይሁን እንጂ የእግዚአብሔርን አሠራር ከቅዱስ ቃሉ ያላስተዋሉና የተሐድሶን መንፈሳዊና ተፈጥሮኣዊ ባሕርያት ያልተረዱ ወግ አጥባቂዎችና የልማድ ቊራኛዎች፥ ተሐድሶን መቃወማቸው የነበረ፣ ያለና የሚኖር ሂደት ነው። እነዚህ ወገኖች የተሐድሶን መጽሐፍ ቅዱሳዊነት እያስተባበሉ ሌላ አፍራሽ ስም ይሰጡታል፤ የኖረውን ሃይማኖት ለማጥፋትና ዐዲስ ሃይማኖት ለመስበክ የተነሣ እንቅስቃሴ አስመስለው በማቅረብ፥ ሕዝብን ይቀሰቅሱበታል፤ ያሳድሙበታል፤ ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨትም ድብቅ አጀንዳቸውን ያስፈጽሙበታል። ነገር ግን የተሐድሶን እንቅስቃሴ መቃወም እግዚአብሔር ለሕዝቡ በየጊዜው ያለማቋረጥ የሚያውጀውን የንስሓና የመታደስ ጥሪ መቃወም መሆኑን አልተገነዘቡም።
እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያኑ ዕለት ዕለት እየታደሰች እርሱ ወዳቀደላት ግብ እንድትደርስ የለውጥ ሐዋርያ አድርጎ የሚያስነሣቸው ሰዎች አሉ። ተሐድሶን የሚቃወሙ ሰዎች አዳሾቹንም መቃወማቸው ግን አይቀርም። ተቃውሞው የሚነሣው በታማኝ አገልጋዮች ላይ ብቻ ሳይሆን በተሐድሶ ስም በሚነግዱትም ላይ ነው።
ታማኝ አገልጋዮች ተቃውሞ ቢገጥማቸው ዋጋቸው በሰማያት ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ሊላቸው ይገባል። በስመ ተሐድሶ የሚነግዱቱ ግን በሚገጥማቸው ተቃውሞ በሰማይም በምድርም ኪሳራ እንጂ ትርፍ የላቸውም። ያልተደረገውን ተደረገ፤ ያልተጀመረውን ተጠናቀቀ የሚሉ፥ መንፈሳዊውን ገድል ሳይጋደሉ በከንቱ ያባከኗቸውን ዓመታት እንደ ድል ዓመታት እየቈጠሩ ሥራውን ትተው በዓላቸውን ወደ ማክበር ፊታቸውን የሚያዞሩ፥ ከእኛ በላይ የለውጥ ሐዋርያ የለም፤ [እግዚአብሔር መሪ የሆነበትን] ተሐድሶን እኛ ካልመራነው ድራሹ ይጥፋ ብለው በወዳጅ-ጠላትነት የቆሙ፥ እንደ ጦረኛ እንዋጋበታለን ያሉትን ያረጀና ያፈጀ የጦርነት ስልታቸውን ለወንጌል ተቃዋሚዎች እያስጠኑ የእንዋጋ ጦር የሚሰብቁ፥ በጥፋታቸው እየቀሰቀሱ ያለውን ተቃውሞ ስለ እግዚአብሔር እንደ ተቀበሉት መከራ እንዲታይላቸው ላይ ታች የሚሉና የሚነግዱበት፥ ለወንጌል ተቃዋሚዎች ልቦለድ ሪፖርት እያቀበሉ ሽብር የሚነዙ፥ ውስጥ ውስጡን ከወንጌል ተቃዋሚዎች ጋር ተወዳጅተው የእግዚአብሔር ሐሳብ የሆነውን ተሐድሶን በእጅ አዙር የሚያደናቅፉ ሁሉ፥ ባለማወቅና ባለማስተዋል ከሚቃወሙት የበለጠ ተጠያቂዎች እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም።

ዋቢ ጽሑፎች
ሐዲስ ሕይወት 1964፣ ግንቦት።
                   1967፣ ግንቦት።
መልከ ጼዴቅ (ሊቀ ጳጳስ) (1995 ዓ.ም.) የቋሚ ምስክርነት። አሜሪካ፣ ዓለም ማተሚያ ቤት።
ራእየ ቴዎፍሎስ 2002፣ ሐምሌ።
ሰሎሞን (ዲያቆን) (1999) የፓትርያርክነቱ መንበር እንዴት ተገኘ? አዲስ አበባ፣ ካሉ ማተሚያ ቤት።
ዓለምነህ ዓለማየሁ (2000) ተኮናኙ ኮናኝ። አዲስ አበባ፣ ማተሚያ ቤቱ ያልተገለጸ።
ዜና ቤተ ክርስቲያን፣ 1996 መጋቢትና ሚያዝያ።
ዝክረ ቴዎፍሎስ ሰማዕት 1989፣ ሐምሌ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ.ም (2000) አዲስ አበባ፣ ሜጋ ማተሚያ ኀ.የተ. የግል ማኅበር።
የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ (1963) ሚያዝያ 2።
ጳውሎስ (ፓትርያርክ) (1987) የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ዐጭር የሕይወት ታሪክ። አዲስ አበባ፣ ማተሚያ ቤቱ ያልተገለጸ።
(http://WWWeotcssd.org 6/13/2003 4:43 AM)
      (http:/WWW.dejesemay.org 6/6/2003 2:38 AM)።
በጮራ ቍጥር 41 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment