Thursday, November 21, 2013

ርእሰ አንቀጽ

ይህን ዓመት ደግሞ ተዋት!

የእያንዳንዱ ቅጽበት፥ ሰኮንድ፥ ደቂቃ ትዝታ ይህን ያህል ጐልቶ በተናጠል በአእምሮኣችን ባይመዘገብም፤ በሰዓት፥ በቀን፥ ከዚያም በወርና በዓመት እየተጠቃለለና የራሱን ድምር ትዝታ እየተወ ሲያልፍ ኖሮአል፡፡ ያለፈው ሁሉ ታሪክ ሆኖአል፤ ተጽፎአል፤ ተነቦም መዝገብ ቤት ይቀመጥ ተብሏል፡፡ አብዛኛው ሰው ባለፈው ቀን ትዝታ ላይ ሙሉ ጊዜውን ከሚያሳልፍ ይልቅ በሚመጣው ቀን ምን እንደሚያጋጥመው ዐውቆ ለመዘጋጀት በእጅጉ ይጥራል፡፡ ብርቱ ፍላጎትም ያለው ስለ ወደ ፊቱ ዕቅድ መሳካት ነው፡፡ ይህንም የሰው ልጅ ፍላጎት የተረዱ ብልጣብልጥ የኅብረተሰብ አባላት መጪውን ዕድልህን ልንነግርህ እንችላለን እያሉ የዋሁን ሕዝብ ለዘመናት ገንዘቡንና ጊዜውን በዘበዙት፤ ሥነ ልቡናውንም ሰለቡት፡፡

እንደዚህ የመሳሰለው አካባቢያዊ ተጽዕኖ ከሚቀሰቅሰው ውስጣዊ ግፊት የተነሣ ሰዎች ከአሮጌው ዓመት ትዝታ ይልቅ ለመጪው ጊዜ ምን ይሁንታ ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ ስለዚህም ለመጪው ዓመት ብሩህ ተስፋ እውን መሆን ሲሉ ጠንክሮ ለመሥራት በሙሉ ዕውቀታቸውና ኀይላቸው ይዘጋጃሉ፡፡ ስለዚህም በየዓመቱ መጀመሪያ ለዐዲሱ ዓመት እንኳን አደረሰህ! አደረሰሽ! በመባበል የመልካም ምኞት መግለጫ ይለዋወጣሉ፡፡ ስለ ዐዲሱ ዓመት እንጂ ስላለፈው ግድ የሚኖረው ያለ አይመስልም፡፡ ላለፈው ክረምት ቤት አይሠራለትምና፡፡


በሀገራችን ሴቶችም፥ ወንዶችም፥ አረጋውያንም አሮጌ ልብሳቸውን አጥበውና ተኩሰው ለአዲሱ ዓመት አቀባበል ይዘጋጃሉ፡፡ ሴቶች የመገልገያ ዕቃዎችን አንድ በአንድ እያጠቡ በመልክ በመልኩ ያስቀምጡታል፡፡ በዐዲስ ዓመት ሁሉን ዐዲስ የማድረግ ፍላጎት በሁሉም ዘንድ አለ ማለት ይቻላል፡፡ የተቻለውማ በዐዲስ ዓመት አብዛኛውን ዕቃ ዐዲስ ያደርጋል፡፡ በተለይም በሀገር ቤት በአሮጌው ዓመት የመጨረሻ ቀን ሌሊት ወንዱ ወደ ወንዝ ወርዶ የአሮጌውን ዓመት እድፍና ጠረን በሕጽበት ያስወግዳል፡፡ አካሉ ላይ የተለጠፈውን ቆሻሻ ሁሉ እየጠራረገ ወደ ጅረት ለሚወስደው ውሃ አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ራሱን ያድሳል፤ ዐዲስ ሰው በዐዲስ ዓመት - ለዐዲስ ሥራ- ለዐዲስ ኑሮ፡፡

ከወደ ፊደሉ ገፋ ያደረገ ከሆነ ደግሞ፥ ባለፈው ዓመት ምን ዐቅዶ እንደ ነበረ፥ ከታቀደው ምን ሠርቶ የቱ እንደ ቀረ፥ ለቀሪው ዕቅድ ግብ አለመምታት ምክንያት የነበረው ችግር ምን እንደ ሆነ ይመረምራል፤ ይገመግማል፡፡ ዐዲሱን ዓመት በዐዲስ ዕቅድ ሊጋተረው ቃል ገብቶ ይነሣል፡፡ ከችግሮቹ ባገኘው ተመክሮ ዐዳዲስ መፍትሒዎችን እያጠና ሊከተለው የሚገባውን መሥመር ወስኖ ይነሣል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሌላ ዐይነት የኅብረተሰብ አባሎች ይታያሉ፡፡ አምናን እንደካቻምና፤ ዘንድሮንም እንደ አምና በማሰብና በመሥራት “ባለህበት ሂድ” የተባሉ ይመስል፥ እዚያው የቆሙበት የሚረግጡ አሉ፡፡ እልፍ ማለት ካልቻሉ እግራቸውን በማንቀሳቀስ ባይደክሙስ? ያሰኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜማ የጥቂቶቹ የጊዜ መቍጠሪያ የቆመ ሲመስል፤ የጥቂቶቹ የጊዜ መቍጠሪያ ደግሞ ወደ ኋላ የሚሽከረከር ይመስላል፡፡ ያለ ዐላማና ግብ፥ ያለ ዕቅድና ፕሮግራም የሚሠሩ ያንኑ የድሮውን ስሕተት ዛሬም ለብዙ ሺሕኛ ጊዜ የሚደግሙ ናቸው፡፡ በእነርሱ ዘንድ በ1987 እና በ1988 (መጽሔቱ የወጣው በዚህ ጊዜ ነበር) ዓመተ ምሕረቶች መካከል ልዩነት የለም፡፡ ዕድሜኣቸው በየዓመቱ ያንድ ዓመት እመርታ እየጨመረ እዚህ መድረሱን እንኳ አይረዱትም፡፡

አብዛኞቻችን በቀን መቍጠሪያ ሰሌዳ ላይ የቀን፥ የወርና የበዓላት ስሞችን ስናነብ፥ ያው እንደ አምናውና እንደ ካቻምናው የነበሩና ያሉ፥ ወደ ፊትም ሲመላለሱ የሚኖሩ ይመስለናል፡፡ ከዚህ የተነሣ ሁሉ እንደ ነበረ ነው፤ የተለወጠና ዐዲስ ነገር የለም እንል ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን ካለፉት ቀን መቍጠሪያ ሰሌዳዎች አንዳች ተምረን ከሆነ ማክሰኞ መስከረም 1 ቀን  1998 ዓ.ም. የሚከበረው የዐዲስ ዓመት መጀመሪያ በዓል ባለፈው ጊዜ አልነበረም፤ ወደ ፊትም አይኖርም፡፡ እንዳለፈው ሁሉ መጪው ሌላ ነው፤ ዐዲስ ነው፡፡ ይህን እውነታ እንዘነጋ ይሆን?

ሁላችንም ልናስተውለው የሚገባ ሌላ ታላቅ ቁም ነገር ደግሞ አለ፡፡ በእያንዳንዱ ቀን ለኛ ብዙ የእግዚአብሔር ጸጋ ፈሶልናል፡፡ ያላየነውንና ያየነውን የጠላት ወጥመድ ሁሉ አክሽፎ፥ መረቡን በጣጥሶ፥ ቀስቱን ሰባብሮ፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን ሰውሮ፥ … ኧረ ስንቱ ተቈጥሮ እዚህ አደረሰን (መዝ. (91)፥1-16)፡፡ አዎን እንደ ገና ዐዲስ የንስሓ፥ የምሕረት፥ የጸጋ ዓመት ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ ሰጠን፡፡ ለዚህ ውለታውም የፍቅር ምላሽ ይፈልጋል፡- የንስሓ ፍሬ፡፡ ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስለ እኛ ቃተተ፡፡ በዚህ ምክንያት ሌላ ዐዲስ ዓመት ተሰጠን፡- ለፍሬ፡፡ “እንዳለፈው ዓመት ዘንድሮም፥ እኰተኵትላትና ማደበሪያ አደርግላት ዘንድ ሌላ የአንድ ዓመት ዕድሜ ለበለስህ ጨምራለት፡፡ ሁሉ ተደርጎላት ካላፈራች በሚቀጥለው ዓመት ትነቅላታለህና ይህን ዓመት ደግሞ ተዋት፡፡” እያለ ቃተተልን፤ ሆነም (ሉቃ. 13፥6-9፤ ሮሜ 8፥26-27)፡፡

አምላካችን ተቈጥሮ ከሚያልቀው፥ ለዓለማችን ከመደበላት የፀሓይ ጊዜ አንድ ዐዲስ ዐውደ ዓመት (የዓመት ዙር) በመስጠት አይወሰንም፡፡ ፍጹም ወደ ሆነ ዘላለማዊ ተሐድሶ እንደ ተስፋው ያስገባናል፡፡ በዐዲስ ሰማይና በዐዲስ ምድር የታቀፈች ዐዲስ ዓለም ሊያወርሰን ተስፋ ሰጥቶናል (ኢሳ. 65፥17፤ 2ጴጥ. 3፥13፤ ራእ. 21፥1-5)፡፡ በዐዲስ ስሙ ሊገለጥልን ቃል ገብቷል (ራእ. 3፥12)፡፡ ለእኛም ዐዲስ ስም አዘጋጅቶልናል (ኢሳ. 62፥2፤ ራእ. 2፥17)፡፡

የዚህ የተሐድሶ ዓለም የዜግነት መብት በኢየሱስ ክርስቶስ ዐዲስ ፍጥረት ለሆኑ ክርስቲያኖች ነው (ዮሐ. 3፥3-7፤ 2ቆሮ. 5፥17)፡፡ ስለሆነም በልባችን መታደስ ዕለት በዕለት እየተለወጥን፥ ያለፈውን በመርሳት ወደ ተቀመጠልን የዐላማ ምልክት ለመድረስና ለመያዝ ያለማቋረጥ ወደ ፊት እንሳብ፡፡ “ይህን ዓመት ደግሞ ተዋት” ተብሎልናልና (ሮሜ 12፥2፤ ፊል. 3፥12-14)፡፡

በጮራ ቍጥር 8 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment