“መስበኪያ ቦታ” የሚል ፈቺ ባለው በዚህ ዐምድ ወንጌል ይሰበካል፡፡
መምሬ ባሮክ
ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ለሚያምኑበት ነገር መለያ ወይም
መታወቂያ ማበጀታቸው የተለመደ ነው፡፡ የጥንት ክርስቲያኖች በግሪኩ መስቀልና “ኢክቱስ” (የዓሳ ምስል) የክርስቲያንነታቸው መታወቂያ ነበር፡፡ በቅርቡ ኮሚኒስቶች ማጭድና መዶሻ የሚያምኑበት
ነገር መገለጫ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በእናት ቤተ ክርስቲያንም አንድ ሰው ክርስቲያን መሆኑን ለመግለጽ በአንገቱ ላይ ማተብ
(ክር) ማሰሩ የተለመደ ትውፊት ነው፡፡
ከጌታ ዕርገት በኋላ ስለ ሐዋርያት÷ የሐዋርያት ሥራ
4÷13 የክህናት አለቆች በድርጊታቸው ከኢየሱስ ጋር እንደ ነበሩ ዐወቋቸው ሲለን÷ ምዕራፍ 11÷26 ደግሞ እነዚህ የኢየሱስ
ደቀ መዛሙርት ለመጀመሪያ ጊዜ በአንጾኪያ “ክርስቲያን” እንደ ተባሉ ይነግረናል፡፡ ለመሆኑ አንድ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ
ወይም ደቀ መዝሙር መታወቂያው ምንድን ነው? ብንል÷ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ዐሥራ ዐምስት ላይ ያስተማረው ይህን እውነት የሚገልጥ
ነው፡፡ እንደምናውቀው የዮሐንስ ወንጌል ከምዕራፍ 13 እስከ ምዕራፍ 17 ጌታ በሕማማቱ ሳምንት ያስተማረው ትምህርት ሲሆን÷ እንደሚሰናበት ሰው ለደቀ መዛሙርቱ አደራና መመሪያ የሰጠባቸው
ምዕራፎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ምዕራፎች ተለይቶአቸው የሚሄድ በመሆኑ ደቀ መዛሙርቱ ማዘናቸውንና ጌታም እነርሱን ማጽናናቱን÷ ተልእኮውንም አስረግጦ መግለጡንና ሊያደርጉ የሚገባቸውንም
ማሳሰቡን እናነባለን፡፡ ከእነዚህ ዐምስት ምዕራፎች በተለይ ምዕራፍ ዐሥራ ዐምስት ላይ አጽንኦት የሰጠው የእርሱ ተከታዮች (ደቀ
መዛሙርት) በሌሎች ሊታወቁ ወይም ሊገለጡ ስለሚችሉባቸው ሦስት መሠረታውያን መለያዎች ነው፡፡