Monday, September 28, 2015

የክርስቶስ ተከታዮችና መለያቸው

መስበኪያ ቦታ የሚል ፈቺ ባለው በዚህ ዐምድ ወንጌል ይሰበካል፡፡
መምሬ ባሮክ
ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ለሚያምኑበት ነገር መለያ ወይም መታወቂያ ማበጀታቸው የተለመደ ነው፡፡ የጥንት ክርስቲያኖች በግሪኩ መስቀልና “ክቱስ” (የዓሳ ምስል) የክርስቲያንነታቸው መታወቂያ ነበር፡፡ በቅርቡ ኮሚኒስቶች ማጭድና መዶሻ የሚያምኑበት ነገር መገለጫ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በእናት ቤተ ክርስቲያንም አንድ ሰው ክርስቲያን መሆኑን ለመግለጽ በአንገቱ ላይ ማተብ (ክር) ማሰሩ የተለመደ ትውፊት ነው፡፡

ከጌታ ዕርገት በኋላ ስለ ሐዋርያት÷ የሐዋርያት ሥራ 4÷13 የክህናት አለቆች በድርጊታቸው ከኢየሱስ ጋር እንደ ነበሩ ዐወቋቸው ሲለን÷ ምዕራፍ 11÷26 ደግሞ እነዚህ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለመጀመሪያ ጊዜ በአንጾኪያ “ክርስቲያን” እንደ ተባሉ ይነግረናል፡፡ ለመሆኑ አንድ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ወይም ደቀ መዝሙር መታወቂያው ምንድን ነው? ብንል÷ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ዐሥራ ዐምስት ላይ ያስተማረው ይህን እውነት የሚገልጥ ነው፡፡ እንደምናውቀው የዮሐንስ ወንጌል ከምዕራፍ 13 እስከ ምዕራፍ 17 ጌታ በሕማማቱ ሳምንት ያስተማረው ትምህርት ሲሆን÷ እንደሚሰናበት ሰው ለደቀ መዛሙርቱ አደራና መመሪያ የሰጠባቸው ምዕራፎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ምዕራፎች ተለይቶአቸው የሚሄድ በመሆኑ ደቀ መዛሙርቱ ማዘናቸውንና ጌታም እነርሱን ማጽናናቱን÷ ተልእኮውንም አስረግጦ መግለጡንና ሊያደርጉ የሚገባቸውንም ማሳሰቡን እናነባለን፡፡ ከእነዚህ ዐምስት ምዕራፎች በተለይ ምዕራፍ ዐሥራ ዐምስት ላይ አጽንኦት የሰጠው የእርሱ ተከታዮች (ደቀ መዛሙርት) በሌሎች ሊታወቁ ወይም ሊገለጡ ስለሚችሉባቸው ሦስት መሠረታውያን መለያዎች ነው፡፡ 

1.    የኢየሱስ ተከታዮች የሚለዩት በእርሱ ውስጥ በመኖራቸው ነው ዮሐ.15÷1-12
በዚህ ዐሥራ ዐምስተኛው ምዕራፍ ዐሥራ ሁለት ቁጥሮች ውስጥ ጌታ በአጽንኦት “በእኔ ኑሩ” ሲል ተናግሯል፡፡ ይህን ለማስረዳት የወይን ግንድንና የቅርንጫፎቹን ምሳሌ ጠቀሷል፡፡ የኢየሱስ ተከታዮች የሚታወቁበት የመጀመሪያው መለያቸው በኢየሱስ መኖራቸው ነው፡፡ ለመሆኑ በኢየሱስ መኖር ማለት ምን ማለት ነው?

በእኔ ኑሩ የሚለው በእርሱ ማመን የሚጀምር ሕይወትን ማሳያ ነው፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ መሲሕና የዐዲሱ ሕይወት ጅማሬ እንደ መሆኑ÷ ተከታዮቹም በእርሱ ያመኑ ትምህርቱንና ዓላማውን የተቀበሉ መሆን አለባቸው፡፡ እርሱ የሕይወት ምንጭ እንደ መሆኑ በእርሱ ማመን በስሙና በሥልጣኑ ሥር መሆንን÷ ለእርሱ መገዛትን÷ አዳኝነቱንና ቤዛነቱን መቀበልን ያመለክታል፡፡ በዚህ በዐሥራ ዐምስተኛ ምዕራፍ አስተምህሮ መሠረት÷ አንድ ሰው በእርሱ ሲያምን በእርሱ ውስጥ መኖር ይጀምራል፡፡ ይህን እውነት የገለጠው በወይን ግንድና ቅርንጫፍ ምሳሌ ነው፡፡ “በእኔ ኑሩ” የሚለውን የክርስቶስን ትምህርት ለመረዳት÷ ሐዋርያት ጳውሎስና ዮሐንስ ያቀረቡበትን ሁኔታ ማጤን የተሻለ ግንዛቤ ይሰጠናል፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ በመልእክታቱ ውስጥ “በክርስቶስ” የሚለውን ሐሳብ ብዙ ጊዜ ተጠቅሟል፡፡ ለምሳሌ በቈላስይስ 3÷1-3 ያለውን መመልከት ይቻላል፡፡ “ሞታችኋልና ሕይወታችሁም በክርስቶስ ውስጥ በሰማያዊ ስፍራ ተሰውሯል” ይላል፡፡ ጳውሎስ በዚህም ሆነ በሌሎች መልእክታቱ ውስጥ ደጋግሞ የሚያነሣው “በክርስቶስ መሆን”÷ ምእመን በክርስቶስ በማመኑ ስለሚያገኘው ወይም ስለ ተጠናቀቀው ድነቱ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በጳውሎስ የነገረ መለኮት እይታ በክርስቶስ መሆን ማለት አማኝ ያገኘውን የስፍራ ወይም የቦታ ለውጥ ያሳያል፡፡ ይህም አገላለጽ ፈጽሞ በአማኙ ማንነት ወይም በመልካም ሥራው ላይ ያልተመሠረተ÷ በክርስቶስ በተሠራለት የጽድቅ ሥራ የተገኘ ነው፡፡ 

የዮሐንስ ነገረ መለኮታዊ እይታ “በክርስቶስ መሆን” ከጳውሎስ የተለየ ነው፡፡ ለምሳሌ 1ዮሐ. 2÷6ን ብንወስድ÷ በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል ይላል፡፡ ይህ ማለት ለዮሐንስ በክርስቶስ መሆን ሂደታዊ ነው፡፡ አማኝ በየዕለቱ ከክርስቶስ ጋር ያለውን የማያቋርጥ ግንኙነት ሲያመለክት÷ ዕሳቤው በምድራዊ ሕይወቱ በማያቋርጥ ኅብረት በዕለታዊ ኑሮው የሚገልጸው ነው፡፡ ዮሐንስ ደጋግሞ የዘላለም ሕይወትን የአሁንና የወደ ፊት አድርጎ ያቀርባል፡፡ የዘላለም ድነት የወደ ፊት ቢሆንም አሁን መጀመር አለበት፡፡ 

እንግዲህ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ በዮሐንስ 15 ላይ የእርሱ ተከታዮች አንደኛው መታወቂያቸው (መለያቸው) በርሱ መኖራቸው መሆኑን ሲያስተምር በእኔ ኑሩ ብሏቸዋል፡፡ መኖር የሚለው ቃል ቢያንስ ዐሥር ጊዜ ያህል ተጠቅሷል፡፡ መኖር በጳውሎስ እይታ በእርሱ ውስጥ መግባትን፤ ማመንን ሲያመለክት÷ በዮሐንስ እይታ ደግሞ የማያቋርጠውን ከክርስቶስ ጋር ያለውን ኅብረት ያሳያል፡፡ በተግባራዊው ሕይወት በክርስቶስ መኖር ማለት ቃሎቹን ወይም ትእዛዙን መጠበቅ÷ ደግሞም እርሱ ባሳያቸው ፍቅር ውስጥ መመላለስ እንደ ሆነ አስተምሯል፡፡

2.   የኢየሱስ ተከታዮች የሚለዩት እርስ በእርስ በሚያሳዩት የማያቋርጥ ፍቅር ነው ዮሐ. 15÷12-17
የኢየሱስ ተከታዮች የሚታወቁበት ሁለተኛው መለያቸው እርስ በእርስ ያላቸው ፍቅር ነው፡፡ ይህን ጌታችን ከቊጥር 12-17 ደጋግሞ አጽንኦት ሲስጠው እናያለን፡፡ የደቀ መዛሙርቱ የእርስ በእርስ ፍቅር መነሻው ደግሞ እርሱ የሰጣቸው (ያሳያቸው) ፍቅር ነው፡፡ የእርሱ ስለ ኀጢአተኞች ቤዛ ሆኖ መሰጠት የፍቅር መግለጫው ጣሪያ ነው፡፡ ከዚህ የበለጠና የተሻለ ፍቅር የሚገለጥበት መንገድ የለም፡፡ ስለዚህ ጌታ ፍቅሩን ለተከታዮች የሚገልጥበትን የመጨረሻውን መንገድ ተጠቀመ፤ ነፍሱን ለእነርሱ በመስጠት፡፡ ስለዚህ ባሪያ የሚባሉትን ተከታዮቹን ወደ ወዳጅነት ደረጃ አቀረባቸው፤ ከፍ አደረጋቸው፡፡ ወዳጆች ስለ ሆኑ የአብን ፈቃድ ዐውቀዋል፡፡ ወዳጆች ስለ ሆኑ በመልእክተኛነት ተሾመዋል፡፡ ወዳጆች ስለ ሆኑ ከአብ ዘንድ በስሙ የሚለምኑትን ይቀበላሉ፡፡ ይህ ሁሉ ስለ ተደረገላቸው የተጠየቁት አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ እርስ በእርስ እንዲዋደዱ፡፡

የክርስቶስ ተከታዮች እርስ በእርስ የሚኖራቸው ፍቅር ትእዛዝ ሲሆን÷ ጌታ ለጕዳዩ አጽንኦት መስጠቱን የምናየው ሁለት ጊዜ በማንሣቱ ነው (ቁጥር 12 እና 17)፡፡ ለዚህ መነሻው የእርሱ ፍቅር ነው፤ “እኔ እንደ ወደድኋችሁ” ብሏል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ተከታዮቹ ለጌታቸው ያላቸውን ፍቅር የሚያሳዩበት ነው፡፡ በዚህ ክፍል ሦስት ጊዜ “እኔ” ማለቱን ልብ ይሏል፡፡ “እኔ እንደ ወደድኋችሁ”፣ “እኔ ያዘዝኋችሁን”፣ “እኔ መረጥኳችሁ እንጂ”፡፡ ስለዚህ ለጌታ ያላቸውን ፍቅር የሚገልጹት ለዚህ ትእዛዝ በሚሰጡት ምላሽ ነው፡፡ በዚህ ሌላው ዓለም እነርሱ የኢየሱስ ተከታዮች መሆናቸውን ይለያል፡፡ በዮሐንስ ወንጌል 13÷35 ላይ ይህን ሐሳብ በማስረገጥ “እርስ በእርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል፡፡

“እኔነት” በሞላበት ዓለም ስለ እርስ በርስ ማውራት አስቸጋሪ ነው፤ ምክንያቱም ከራስ መውጣትና ለሌላው መሰጠትን ይጠይቃልና፡፡ እነዚህ የተነገረላቸው ተከታዮች ይህን እውነት እንዲኖሩት የሚነገር የታሪክ ምስክር መኖሩ ደስ የሚል ነው፡፡ አንድ ጥንታዊ ጸሓፊ እንዳለው÷ “እዩአቸው እነዚህ ክርስቲያኖች በጣም ይዋደዳሉ፤ አንዱ ለሌላው ራሱን አሳልፎ ይሰጣል፡፡” ዛሬ እኛ ከወንድሞችና ከእኅቶች ጋር ያለን ፍቅር በተግባራዊው ሕይወታችን እንዴት ይገለጣል? በክርስትና ሕይወታችን ውስጥ ፍቅር ዋነኛ የሚሆነው እግዚአብሔርን ያወቅንበት መንገድ ስለ ሆነ ነው፡፡

3.   የኢየሱስ ተከታዮች መለያቸው ከዓለም ጋር ያላቸው አለ መግባባት ነው (ዮሐ. 15÷18-25)
የኢየሱስ ተከታዮች ምንም እንኳ መለያቸው ከዓለም ጋር ያላቸው አለ መግባባት ነው ሲባል ቃሉ አሉታዊ ቢሆንም÷ ጌታ እንዳስተማረው ተከታዮቹ የሚለዩበት ሦስተኛው መንገድ ከዓለም ጋር ባላቸው ግንኙነት የሚወሰን ነው፡፡ ዓለም የሚለው ሐሳብ የተለያየ ዐውዳዊ ትርጉም ቢኖረውም÷ በአብዛኛው የሰው ልጆችና ሥርዐታቸውን ያመለክታል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአጠቃላይ ዓለም በመጥፎ ገጽታዋ የቀረበች ሲሆን÷ ለእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ነገር ተቃዋሚ ተደርጋ ተወስዳለች፡፡ ምናልባት ዓለም በመልካምነት የተነሣችበት ቦታ ዮሐ. 3÷16 ያለውና እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለምን የወደደበት ክፍል ሲሆን÷ ይህም ከእግዚአብሔር ከራሱ የመነጨ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ዓለም ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን ስትቃወም ኖራለች፡፡ ቢሆንም በጥላቻ ለተሞላችው ዓለም እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ጽኑ ፍቅሩን ገልጿል፡፡

በዮሐ. 15÷18-25 በጌታ ትምህርት መሠረት ዓለም ለጌታ ለራሱና ለተከታዮቹ ያላት ምላሽ በጥላቻ የተሞላ ነው፡፡ እግዚአብሔር በልጁ በኩል ለዓለም ያለውን ጥልቅ ፍቅሩን በገለጠ መጠን÷ ዓለም በእግዚአብሔር ያላትን ነገር የሰጠችው ምላሽ ጥላቻ ነው፡፡ ስለዚህ ዓለምና የኢየሱስ ተከታዮች ያላቸው ግንኙነት ባለመግባባት የተሞላ ነው፡፡ ምክንያቱም ዓለም እግዚአብሔርንም ሆነ ተከታዮቹን አትቀበልም፤ አትወድም፤ ታሳድዳቸዋለች፤ ምክንያቱም እነርሱ የኢየሱስ እንጂ የዓለም አይደሉም፡፡ ስለዚህ ተከታዮቹ በዓለም ይጠላሉ፤ ይሰደዳሉ፤ ይገደላሉ፡፡ ዓለም ለክርስቶስ ተከታዮች አትመችም፡፡ የዕብራውያን ጸሓፊ (11÷37) ስለ እምነት አባቶች “ዓለም አልተገባቸውምና” ሲል የሚነግረን÷ ዓለም እንዳልተመቻቸው ነው፡፡ ለእነርሱ ዓለም ኮምፈርት ዞን አልነበረችም፡፡

ምንም እንኳ የኢየሱስ ተከታዮች ለዓለም የመስቀሉን ሥራ በመንገር በኩል ፍቅራቸውን ቢያሳዩም÷ ከዓለም ርኵሰት ጋር እንዳይተባበሩና በተቃራኒው እንዲቆሙ መጽሐፍ ቅዱስ ያዛል (1ዮሐ. 2÷15-17)፡፡ ዓለምንና በዓለም ያለውን አትውደዱ ሲል÷ የሚያልፈውን የዓለም ምኞትና ከእግዚአብሔር ፈቃድ በተቃራኒ የሚቆመውን ነገር ሁሉ አለመውደድን ያመለክታል፡፡ ዓለምን አትውደዱ ሲል ለዓለም ሥርዐት አንገዛም ማለት አይደለም፤ ወይም ደግሞ በዓለም ያለውን ተፈጥሮኣዊ ሥርዓት መብላት፣ መጠጣት፣ መልበስ፣ ሌሎችንም አስፈላጊ ነገሮችን አታድርጉ ማለት አይደለም፡፡ ዳሩ ግን ለእግዚአብሔር እውነት ተቃራኒ የሆነውን በርኵሰትና በኀጢአት የተሞላውንና ከእግዚአብሔር ጽድቅ ተቃራኒ የሆነውን አታድርጉ ለማለት ነው፡፡ 

ምን እንማራለን?
በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 15 ውስጥ ጌታ ደቀ መዛሙርቱ የተለዩ እንዲሆኑ ያስተማረው ትምህርት÷ በእርሱ መኖር፣ እርስ በእርስ መዋደድና ዓለምን አለ መውደድ ዘመናትን ተሻግሮ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ላለን አማኞች ያለው አንድምታ ምንድን ነው? እንደሚታወቀው ዘመናችን ከሕይወት ይልቅ የአገልግሎት ሩጫ የበዛበት ነው:: የክርስቲያኖች መለያና መግለጫ የሆነውን “እኔ በክርስቶስ ነኝ” የሚለውን እውነት በክርስቶስ ከተሠራልን ሥራና ከተቀመጥንበት መንፈሳዊ ስፍራ አንጻር በዕለታዊ ሕይወታችን ልንተገብረውና ልናሰላስለው የሚገባ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም በክርስቶስ ውስጥ መሆን የነገር ሁሉ መጠቅለያና መቋጫ ነው፡፡ ልንጓጓለት የሚገባ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከክርስቶስ ውጭ የሚያበቃውና የሚቀበለው ነገር ስለሌለ በዕለታዊ ሕይወታችን ከእርሱ ጋር ያለንን ኅብረት ልንናፍቀውና ደስ ልንሰኝበት ይገባል፡፡

ስለ ክርስቲያኖች ፍቅር ስንነጋገር ጌታ እንዳዘዘን ማሰብ ያለብን÷ ዓለም ዐቀፉን የክርስቲያኖች ፍቅር ሳይሆን÷ ከአጠገባችን ካለው ጎረ ቤታችን ጋር ስላለን ፍቅር ነው ማሰብ ያለብን፡፡ በዮሐ. 15÷35 ላይ ጌታ እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ እንዳለ÷ ፍቅር እግዚአብሔርን ያወቅንበትና ያየንበት መንገድና የእግዚአብሔር የመሆናችን መታወቂያ ነው፡፡ ስለዚህ በዕለታዊው ሕይወታችን ይህን የእግዚአብሔርን ፍቅር እንዴት እንደምንገልጸው ልናስብ ይገባል፡፡


በጮራ ቍጥር 39 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment