(በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ)
“ጌታ ሆይ እንጸልይ ዘንድ
አስተምረን፡፡” (ሉቃ. 11፥1)
ከክርስትና ሕይወታችን አብዛኛው ክፍል የሚያዘው በጸሎት እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ያለመታከት መጸለይ እንዲገባን
የእግዚአብሔር ቃል ይመክረናል (ሉቃ. 18፥1-7)፡፡
ኑሮአችን በጥያቄና በችግር
የተሞላ ስለሆነና ሁል ጊዜ የምንቀበለው ስለሚበዛ፥ ያለ ጸሎት ልንኖር አንችልም፡፡ ትንሽ ልጅ ሲርበው፤ ቊርሱን፥ ምሳውን፥ እራቱን፤ ሲበርደው
ልብሱን፥ መጠለያውን ይጠይቃል፡፡ ሲታመም ይቅበጠበጣል፥ ያለቅሳል፡፡ እንቅፋት ቢመታው፥ እሾኽ ቢወጋው፥ የጎረቤት ልጅ ቢያጠቃውና በእድገቱ ሂደት የሚያጋጥሙትን ዐዳዲስ
ነገሮች ሁሉ የማወቅ ጥማቱን ለማርካት ጥያቄዎችን ይደረድራል፡፡ ትናንት ጠይቆ በተቀበለው ተጠቅሟል፥ አመስግኗልም፡፡ ሆኖም
ትናንት ዐልፎአልና ዛሬ ለዐዲስ ጥያቄ ዐዲስ ምላሽ ይጠብቃል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ክርስቲያንም በዚህ ተመሳሳይ
ምክንያት ጸሎትን ማቋረጥ አይችልም፤ አያስታጕልም፡፡