Tuesday, June 25, 2013

ክርስትና በኢትዮጵያ



 የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

ከነቅዐ ጥበብ
ካለፈው ቀጠለ

በፍሬምናጦስ አገልግሎት ክርስትና በኢትዮጵያ ፍሬ ማፍራት ጀምሮ እንደ ነበረ ባለፈው ዕትም አንብበን ነበር፡፡ በአዳኝነቱ ኢየሱስ፥ ሰውንና እግዚአብሔርን በአንድ አካል በማገናኘቱና ለፍጹምና ዘላቂ ኅብረት በማብቃቱ ዐማኑኤል፤ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል በተመሠረተ ኅብረት ላይ ለሚከናወነው የንጉሥነት፣ የነቢይነትና የክህነት አገልግሎት በመሠየሙ ክርስቶስ የተባለው፥ የእግዚአብሔርና የሰው ልጅ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል በተሰበከባት በሳባ ኢትዮጵያ መዲና በአክሱም ከተማ “ጽዮን” ወይም “ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት” የተባለችው ቤተ ክርስቲያን (ማኅበረ ምእመናን) ተቋቁማ እንደ ነበረ ተመልክቶ የነበረውን እናስታውሳለን፡፡

ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃልም በዕብራ ይስጡ ኳሃል፥ በግሪክኛው አቅሌስያ ምስጢርና ዘይቤ ሲፈታ ጉባኤ ምእመናንን እንደሚያመለክት ተገልጾ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ከሁለት ቍጥር ጀምሮ ብዛት ያላቸውን ያቀፈ፥ ከዚያም በላይ በመላው ዓለም የነበሩትን፣ ያሉትንና ገናም የሚኖሩት በክርስቶስ ደም የተዋጁትን ምእመናን ሁሉ ያቀፈች ለክርስቶስ አካልነት፣ ለክርስቶስ ሙሽሪትነት፣ በእግዚአብሔር ጸጋ የበቃችውን የቦታ ክልል የማይጋርዳትን፣ ከጾታ፣ ከዕድሜ፣ ከወገን ሁሉ የተጠራችውንና የተመረጠችውን አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንደሚገልጽ አንብበን የነበረውን እናስታውሳለን፡፡

Sunday, June 16, 2013

የዘመን ምስክር

በዚህ ዐምድ ለቤተ ክርስቲያን መሻሻልና መለወጥ የተጋደሉ፥ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም መልካም ሥራን የሠሩ አበውን ሕይወትና የተጋድሎ ታሪክ አሁን ላለውና ለቀጣዩ ትውልድ አርኣያ እንዲሆን እናስተዋውቃለን፡፡


ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ቀዳማዊ የወንጌል እስረኛ (1888 - 1974 ዓ.ም.)
በዘመናት ውስጥ የተፈጸመና ታሪክ የመዘገበው መልካምም ሆነ ክፉ ሥራ ሊረሳ አይችልም፡፡ ለጊዜው እውነት እንደ ሐሰት ይቈጠር$ ሐሰት ደግሞ የእውነትን ስፍራ ይቀማ ይሆናል፡፡ በደካሞች ግምትም እውነት ርቆ ሊቀበርና የሐሰት ዐፈር ሊጫነው ይችላል፡፡ እውነት ግን ለጊዜው እንጂ ተቀብሮ ሊቀር፥ ፈጽሞ ሊሰወርና ሊረሳ አይችልም፡፡ እውነት ሲወጣ ቀድሞ ተሰጥቶት የነበረው ዝቀተኛ ግምት ይለወጣል፡፡ በተቃራኒው ሐሰትም ከተሰቀለበት የክብር ማማ ላይ ይወርዳል፡፡ የብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የተጋድሎ ታሪክ ከተቀበረበት መውጣቱና ተገቢውን ስፍራ ማግኘቱ እውነትና እውነተኞች ተቀብረው እንደማይቀሩ ያሳያል፡፡    

የባለ ታሪኩ ማንነት
የተወለደው በ1888 ዓ.ም. በቀድሞው የኤርትራ ጠቅላይ ግዛት በሐማሴን አውራጃ፣ በላምዛ ሠሓርቲ ወረዳ፣ ዓዲ ቀሺ በተባለው ስፍራ ነው፡፡ ገብረ አብ ይባላል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ የቤተ ክህነት ትምህርቱን ተምሮ ወደ ትግራይ በመሄድ፥ በዓድዋ አውራጃ ዓዲ አቡን ከነበሩት ግብጻዊ ጳጳስ ከአቡነ ቄርሎስ ዲቁና ተቀበለ፡፡ ከዚያ ኤርትራ ውስጥ በሚገኘው አቡነ እንድርያስ ሠፍኣ ገዳም ገብቶ የግእዝን ትምህርት፣ የአበውን ግብረ ገብና ሥርዐተ ገዳምን እየተማረና እያገለገለ ዐምስት ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ መነኰሰ፡፡

አባ ገብረ አብ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ምስጢር ለመረዳት ጽኑ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ወደዚያው ለመድረስም ቅኔን ከነአገባቡ ተምረዋል፡፡ ፀዋትወ ዜማንና መዝገብ ቅዳሴንም በሚገባ የተማሩ ሲሆን በቅዳሴ መምህርነት ተመርቀዋል፡፡ በ1911 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከግብጻዊው ሊቀ ጳጳስ ከአቡነ ማቴዎስ የቅስናን ማዕርግ ተቀበሉ፡፡ ወዲያው በቀድሞው የሐረር ጠቅላይ ግዛት የሚገኘውንና በግራኝ ጊዜ የጠፋውን የአሰቦት ደብረ ወገግ ገዳም እንዲያቀኑ ተላኩ፡፡

መጽሐፍ “በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል” (መዝ. 36(37)፥4) እንደሚል፥ ከእርሳቸው ስምንት ቀን ያህል ቀድመው ወደ ቦታው ከመጡና አለቃ ገብረ መድኅን ከተባሉ የሐዲሳትና የሃይማኖተ አበው መምህር ጋር ተገናኙ፡፡ ይህም ሐዲሳትን ለመማር የነበራቸውን ጽኑ ፋላጎት ለማርካት የተፈጠረ ትልቅ ዕድል በመሆኑ፥ ከእርሳቸው ጉባኤ ሐዲሳትን እየቀጸሉ ጥቂት እንደ ቈዩ፥ በእኒሁ መምህር ምክንያት ወደ ኢየሩሳሌም የሚሄዱበት በር ተከፈተላቸው፡፡

Thursday, June 6, 2013

ርእሰ አንቀጽ


እግዚአብሔር አይዘበትበትም

ገበሬ በመኸር ሊሰበስብ የሚችለው ያንኑ የዘራውን ዐይነት አትርፎና አትረፍርፎ እንደ ሆነ ለማስገንዘብ፥ ያልዘራነውን እንሰበስባለን ብላችሁ በእግዚአብሔር አትቀልዱ፤ እግዚአብሔር ሊዘበትበት አይገባም ሲል የእግዚአብሔር መንፈስ በሐዋርያ ጳውሎስ በኩል አስተማረ (ገላ. 6፥7-9)፡፡ እየበቀለና እያደገ ለአዝመራ ደርሶ የምናጭደውና በትርፍ የምንሰበስበው ያንኑ የዘራነውን የእህል ዐይነት ነው፡፡ ጓያ የዘራ የስንዴ ምርት፥ ባቄላ የዘራም የጤፍ ምርት እግዚአብሔር ይሰጠኛል ብሎ አይጠብቅ፡፡ ነገ እንዲያገኝ የሚፈልገውን የምርት ዐይነት ካወቀ ለዚያ አዝመራ የሚያበቃውን ዘር ዛሬ መዝራት አለበት፡፡ ሌሎች ሰዎችም ሊያገኙ የማይችሉትን እንደሚያገኙ አስመስሎ ኢ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እንዲደክሙ መምራት ለሁሉም እንደየሥራው የሚከፍል እግዚአብሔር ጻድቅ ፈራጅ የሆነበትን የቅድስናውን ባሕርይ የለወጠ አስመስሎ ማስተማር ነውና በእግዚአብሔር አንቀልድ፡፡ ይህ ዐይነቱ ተልእኮ መጥፎ ምርት ለመሰብሰብ የሚያበቃ መጥፎ ዘር መዝራት ነውና፡፡ ምድራዊ ዳኛ እንኳ ጸያፍና ነውር የሚለው፥ እንዲያውም የሚያፍርበት አድልዎኛነትና ፍርድን ማዛባት በእግዚአብሔር ዙፋናዊ ችሎት ይሠራበታል ከማለት የበለጠ ድፍረት ከቶ የለም፡፡ ስለዚህ በምኞታችንና በንግግራችን እውነቱን እውነት፥ ሐሰቱንም ሐሰት ነው እንበል፡፡ ይህን አለማለት በሰይጣን ጐራ መሰለፍ ነውና (ማቴ. 5፥37)፡፡

በአለቃ ስም ከሚነገሩ ቀልዶች መካከል አንዱን እዚህ ብንጠቅስ ተገቢ ስፍራው ይመስለናል፡፡ በርኩሳን መናፍስት አገልጋይነቱ ሰዎችን ሲያሳስት የኖረ ሰው ሞተ፡፡ ሥራውንና የደለበ ሀብቱን ቤተ ሰቡ ወረሰ፡፡ ወራሾቹም የኀጢአት ስርየት ይገዙለት ዘንድ ከዕለተ ሞቱ ጀምሮ በዐርባው፥ ከዚያም በኋላ በሰማኒያው፥ በመንፈቁና በየዓመቱ በከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ጸሎተ ፍትሐት አስደረጉለት፡፡ ከዐርባው ድግስ ተቋዳሾች መካከል አንዱ አለቃ ስለ ነበሩ፥ በአጠገባቸው ተቀምጦ ይመገብ የነበረ ሌላው አለቃን ጠየቃቸው፡፡ “ሟቹ ንስሓ አልገባም፤ ወራሾቹ ሀብቱን ወርሰዋል፤ ሥራውንም ቀጥለዋል፤ አሁን እኛ የጸሎታችን ዋጋ የሆነውን ድግስ የምንመገበው ለሟቹ ነፍስ ስርየት አሰጥተናል፤ ርግጠኞች ነን ብለን ነውን? ርግጠኛ ባልሆነ የስርየት ሽያጭስ አንጠየቅምን? ቢላቸው፤
“እኛ እንብላ እያልን ማራት ማራት፤
አምላክ ከፈለገ ገነት ይጨምራት፤
ካልፈለገም ደግሞ እንጦርጦስ(ሲዖል) ያውርዳት፡፡” በማለት መለሱለት ይባላል፡፡ በእውነት እንዲህ ተብሎ ከሆነ ኀላፊነት ከማይሰማው ኅሊና የመነጨ አነጋገር ነው፤ አያሥቅም፡፡