“ወይመጽኡ ኀቤኪ እንዘ ይፈርሑ ወያመጽኡ አምኀ ደቂቆሙ እልኩ እለ አምዕዑኪ ወይሰግዱ ቅድመ መከየደ እግርኪ ወትሰመዪ
ሀገረ እግዚአብሔር ቅዱሰ እስራኤል ጽዮን - የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፥ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእግዚአብሔርም ከተማ፥ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል” (ኢሳ. 60፥14)።?
‘ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል’ የሚል ፍልስፍና ያላቸው ወገኖች አሉ። እንዲህ ለማለት ያበቃቸው
በተደጋጋሚ የሚያቀርቡትን ውሸት፥ ሰዎች እውነት ነው ብለው የተቀበሏቸው ስለ መሰላቸው ነው። ውሸት፥ ውሸት ነው፤ እውነት ደግሞ እውነት ነው። ዐሥር ወንፊት ቢደራረብ አንድ
ብልቃጥ ውሃ መያዝ እንደማይችል ሁሉ፥ ውሸት የቱንም ያህል የእውነት ጠብታ ቢጨመርበት ድምር ውጤቱ ውሸት ነው። ውሸት በምንም ተኣምር ወደ እውነትነት የሚለወጥበት ዕድል ከቶ የለም፤
አለ ከተባለ ግን እውነትን አለማወቅ፣ እውነትን ማራከስና ዋጋ ማሳጣት ይሆናል። ስለዚህ ውሸት ሲደጋግም እውነት ይመስላል እንጂ
እውነት ሊሆን በፍጹም አይችልም።
ኢሳ. 60፥14 ስለ ማን ይናገራል?
ስድሳ ስድስት ምዕራፎች ያሉት ትንቢተ ኢሳይያስ በሦስት ዐበይት ክፍሎች ሊከፈል እንደሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት
ይናገራል (1972፣ ገጽ 149)። የመጀመሪያው ክፍል ከምዕራፍ 1-39 ድረስ ያለው ሲሆን፥ ነቢዩ ኢሳይያስ በነበረበት ዘመን የተከናወኑትን
ድርጊቶች መሠረት በማድረግ የተጻፈ ነው። ሁለተኛው ክፍል ደግሞ፥ ከምዕራፍ 40-55 ድረስ ያለውና ከኢሳይያስ ዘመን በኋላ ስለ
ተፈጸመው ስለ ባቢሎን ምርኮ የተነገረ ትንቢት ነው። የመጨረሻው ክፍልም ከምዕራፍ 55-66 ደግሞ ወደ ፊት ማለትም ከባቢሎን ምርኮ
ፍጻሜ በኋላ ስለሚሆነው የጽዮን ክብር ይናገራል። በመነሻው ላይ የተጠቀሰው ጥቅስ የተወሰደውም በዚህ በሦስተኛው ክፍል ከሚገኘው
ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 60 ቊጥር 14 ላይ ነው።