መጥምቁ ዮሐንስ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት መንገድ ጠራጊ፣ ዐዋጅ ነጋሪ እንደ መኾኑ፣
ሕዝቡ፣ ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፣ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ እንዲመለሱና ለንስሓ የሚገባ ፍሬ እንዲያፈሩ
“መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” በማለት በበረሓ እያወጀ ነበር የመጣው።
የሰሙትም ኀጢአታቸውን እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በእርሱ እጅ ይጠመቁ ነበር። ዮሐንስ እኔ ጐንበስ
ብዬ የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ ነኝ፤ ከእኔ የሚበልጠው ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ እርሱ
ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል አለ። ሕዝቡን ከጌታው ጋር ካገናኘ በኋላም ሕዝቡ የጌታ፣ ጌታም የሕዝቡ ብቻ መኾናቸውን ለመግለጽ
“ሙሽራዪቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው” ሲል ተናገረ። በዚሁ ዐውድ እርሱ እንደ ሚዜ የሚቈጠርና አገልግሎቱም እዚሁ ድረስ ብቻ መኾኑንና
መፈጸሙን ገለጸ።
ከመጥምቁ ዮሐንስ በኋላ የተነሡት የቃሉ አገልጋዮች ሐዋርያትም፣ በዮሐንስ መንገድ ጠራጊነት የመጣውንና
ስለ በጎቹ ራሱን አሳልፎ የሰጠውን ጌታ እርሱ ለሞተላቸው ኹሉ በማስተዋወቅ ሙሽራውንና ሙሽራዪቱን የማገናኘት ተግባር ነው የፈጸሙት።
ቅዱስ ጳውሎስ “እስመ ፈኃርኩክሙ ለአሐዱ ምት ድንግል ወንጹሕ ክርስቶስ ከመ አቅርብክሙ ኀቤሁ - እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን
ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ ዐጭቻችኋለሁ” (2ቆሮ. 11፥2) ሲል የሰጠው ምስክርነትም ይህንኑ እውነት ያስረዳል።