Monday, January 16, 2017

“ዘቦቱ መርዓት መርዓዊ ውእቱ - ሙሽራዪቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው” (ዮሐ. 3፥29)

መጥምቁ ዮሐንስ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት መንገድ ጠራጊ፣ ዐዋጅ ነጋሪ እንደ መኾኑ፣ ሕዝቡ፣ ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፣ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ እንዲመለሱና ለንስሓ የሚገባ ፍሬ እንዲያፈሩ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” በማለት በበረሓ እያወጀ ነበር የመጣው። 

የሰሙትም ኀጢአታቸውን እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በእርሱ እጅ ይጠመቁ ነበር። ዮሐንስ እኔ ጐንበስ ብዬ የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ ነኝ፤ ከእኔ የሚበልጠው ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል አለ። ሕዝቡን ከጌታው ጋር ካገናኘ በኋላም ሕዝቡ የጌታ፣ ጌታም የሕዝቡ ብቻ መኾናቸውን ለመግለጽ “ሙሽራዪቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው” ሲል ተናገረ። በዚሁ ዐውድ እርሱ እንደ ሚዜ የሚቈጠርና አገልግሎቱም እዚሁ ድረስ ብቻ መኾኑንና መፈጸሙን ገለጸ። 

ከመጥምቁ ዮሐንስ በኋላ የተነሡት የቃሉ አገልጋዮች ሐዋርያትም፣ በዮሐንስ መንገድ ጠራጊነት የመጣውንና ስለ በጎቹ ራሱን አሳልፎ የሰጠውን ጌታ እርሱ ለሞተላቸው ኹሉ በማስተዋወቅ ሙሽራውንና ሙሽራዪቱን የማገናኘት ተግባር ነው የፈጸሙት። ቅዱስ ጳውሎስ “እስመ ፈኃርኩክሙ ለአሐዱ ምት ድንግል ወንጹሕ ክርስቶስ ከመ አቅርብክሙ ኀቤሁ - እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ ዐጭቻችኋለሁ” (2ቆሮ. 11፥2) ሲል የሰጠው ምስክርነትም ይህንኑ እውነት ያስረዳል። 

የቃሉ እውነተኛ አገልጋዮች ሙሽሪት ቤተ ክርስቲያንን (ምእመናንን) ከሙሽራዋ ከክርስቶስ ጋር የማስተዋወቁን ተልእኮ ፈጽመው ያንቀላፉ ቢኾንም፣ ዛሬ ግን ሙሽሪት ቤተ ክርስቲያን ሙሽራዋን ከሚዜዎች ለይታ በማታይበትና ከእነርሱ ኹሉ ጋር አንድ አድርጋ በምትቈጥርበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ለዚህም አንዳንድ ሰባክያነ ወንጌልና አስተማሪዎች ቤተ ክርስቲያንን ወደ ክርስቶስ በማቅረብ ፈንታ እንደ ሚዜ ለሚቈጠሩት ቀደምት የቃሉ አገልጋዮች፣ ለቅዱሳን መላእክት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ለማይታወቁ ጻድቃን ሰማዕታት ለተባሉት ጭምር እያቀረቡ በመኾናቸው ነው። ወንጌል አንድ፣ መልእክቱም አንድ፣ እርሱም የተሰቀለው የናዝሬቱ ኢየሱስ ኾኖ ሳለ፣ አብዛኛውን ጊዜ ስብከታቸው እንደ ፌንጣ ከሃ ወዝየ (ወዲያና ወዲህ)፣ ለፌ ወለፌ/ (እዚህና እዚያ) የኾነ፣ ማገቻ /ልጓም/ እንደሌለው ፈረስ፣ ወይም ፍሬኑ እንደ ተበላሸ መኪና ከማይመለከተው ጋር ሲላተምና ሲጋጭ ይታያል።


እጅግ የሚያሳዝነው በዚህ መንገድ  ዐይናቸውን ከክርስቶስ ላይ እንዲያነሡና ፍጡራንን እንዲያመልኩ የተደረጉት ምእመናን፣ ዕረፍተ ነፍስ ወሥጋ ሳያገኙ ጽድቅን ፍለጋ ደጋ፣ ወይና አደጋ፣ ቈላና በረሓ፣ በማለት ዕድሜ ልካቸውን የሚንከራተቱ ኾነዋል። ሲሞቱም እዚህ ቦታ ቅበሩኝ እያሉ ይናዘዛሉ፤ ይህም የሚያሳየው ከሸክማቸው ሳያርፉ እንደሚሞቱ ነው። ምናለበት! ምእመናንን፣ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ኹሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ” (ማቴ 11፥28) ካለው ጌታ ጋር ቢያስተዋውቋቸውና ወደ ዕረፍቱ እንዲገቡ መንገዱን ቢያሳዩአቸው! 

ቤተ ክርስቲያንን ከታጨችለት ከአንዱ ሙሽራዋ ከክርስቶስ በተጨማሪ የሌሎችም እንድትኾን ያደረጉ ሰዎች ያላስተዋሏቸው ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ ቤተ ክርስቲያን ከፈጣሪ ባልተናነሰ ክብር እንድታመልካቸው የተደረጉትና በስማቸው የተነገደባቸው የእግዚአብሔር ባሪያዎች ቅዱሳን ሰዎችም ኾኑ መላእክት በዚህ ሐሳብ የማይስማሙ መኾናቸውን ነው።

ሐዋርያው ዮሐንስ ራእዩን ላሳየው መልአክ ኹለት ጊዜ ሊሰግድለት በእግሩ ፊት በተደፋ ጊዜ፣ መልአኩ “እንዳታደርገው ተጠንቀቅ” በማለት ከማስጠንቀቁም በላይ፣ እርሱ ከዮሐንስና የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞቹም ከነቢያትም ጋር ዐብሮ ባሪያ መኾኑን ጠቅሶ ለእግዚአብሔር ብቻ እንዲሰግድ ነግሮታል (ራእ. 19፥10፤ 22፥8-9)። ሐዋርያው ጴጥሮስም ሊሰግድለት ከእግሩ ሥር በወደቀ ጊዜ ለቆርኔሌዎስ የሰጠው ምላሽ ተመሳሳይ ነው (ሐ.ሥ. 10፥25-26)። ይህም መላእክት የእግዚአብሔር ባሪያዎች፣ ለእርሱ የሚሰግዱና እርሱን የሚባርኩ (መዝ. 96/97፥7፤ 102/103፥20)፣ ቅዱሳን ሰዎችም ጴጥሮስ እንዳለው “ሰው” እና በተመሳሳይ ኹኔታ የእግዚአብሔር ባሪያዎች እንጂ፣ እንደ እግዚአብሔር የሚመለኩ ተወራጅ አማልክት አለመኾናቸውን ያሳያል።


በኹለተኛ ደረጃ፣ እነዚህ በተለይም ቅዱሳን ሰዎች የቤተ ክርስቲያን አባላት እንጂ ከዚያ ውጪ ኾነው በቤተ ክርስቲያን የሚመለኩ አካላት አለመኾናቸውን አላስተዋሉም። በተሳሳተ መንገድ በስሟ ይህ ስፍራ የተሰጣት የጌታችን እናት ቅድስት ማርያም፣ ለመልአኩ ገብርኤል በሰጠችው ምላሽ ውስጥና በጸለየችው ጸሎት ውስጥ ደጋግማ የተናገረችው፣ የእግዚአብሔር ባሪያ መኾኗን ነው (ሉቃ. 1፥38፡48)። ጌታ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ፣ ሐዋርያቱ የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ እየጠበቁ በነበረበት ጉባኤ ውስጥ፣ ቅድስት ማርያም እየጸለዩ ተስፋውን ከሚጠባበቁት መካከል አንዲቱ ነበረች እንጂ፣ ከዚያ ውጪ ኾና ጸሎት የሚቀርብላት አምላክ አልነበረችም፤ አይደለችምም። ስለዚህ ክርስቲያን የማንም ሳይኾን በደሙ የዋጀው የጌታው ብቻ መኾኑ መታወቅ አለበት። አዎን! ሙሽራዪቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው።

No comments:

Post a Comment