Monday, April 23, 2012

በኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

 Read PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበና ካለፈው የቀጠለ

የፊደልና ሥነ ጽሑፍ ልደትና እድገት

ቀደምት ነዋሪዎች የነበሩት የነገደ ኩሽ ዝርያዎች በደቡብና በምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍሎች ለረጅም ጊዜ የኖሩ መሆኑ ሲረጋገጥ፥ ለሰው ዝርያ መኖሪያ በመሆን ሀገሪቱን የቀዳሚነት ደረጃ እንድትይዝ ያደረጓት መሆኑም ሲታወቅ፥ ተመራማሪዎች የእነዚህን ነገዶች ነባር ሥልጣኔ ፈልፍሎ በማውጣት ወደ ብርሃን አላመጡትም፡፡ ስለ ሆነም ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሳባዊ ሥልጣኔ ይቀድማል ተብሎ የሚታመነው የነገደ ኩሽ ኢትዮጵያውያን ፊደልና ሥነ ጽሑፍ ተገኝቶ ለንባብ አለ መብቃቱ ያሳዝናል፡፡ ወደ ፊት ዋሻዎች የኰረብታዎችና ሸለቆዎች ከርሠ ምድር ሲመረመሩ የሚገኘውን ውጤት በተስፋ እንጠባበቃለን፡፡

አሁን ግን በኢትዮጵያ የሳባዊውን ፊደል ታሪክ እንመለከታለን፡፡ ከዚህም ተያይዞ ከሳባውያን ፊደል የተወረሰውንና የተሻሻለውን የግእዝን ፊደል ልደትን እድገት እናነባለን፡፡