Monday, April 23, 2012

በኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

 Read PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበና ካለፈው የቀጠለ

የፊደልና ሥነ ጽሑፍ ልደትና እድገት

ቀደምት ነዋሪዎች የነበሩት የነገደ ኩሽ ዝርያዎች በደቡብና በምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍሎች ለረጅም ጊዜ የኖሩ መሆኑ ሲረጋገጥ፥ ለሰው ዝርያ መኖሪያ በመሆን ሀገሪቱን የቀዳሚነት ደረጃ እንድትይዝ ያደረጓት መሆኑም ሲታወቅ፥ ተመራማሪዎች የእነዚህን ነገዶች ነባር ሥልጣኔ ፈልፍሎ በማውጣት ወደ ብርሃን አላመጡትም፡፡ ስለ ሆነም ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሳባዊ ሥልጣኔ ይቀድማል ተብሎ የሚታመነው የነገደ ኩሽ ኢትዮጵያውያን ፊደልና ሥነ ጽሑፍ ተገኝቶ ለንባብ አለ መብቃቱ ያሳዝናል፡፡ ወደ ፊት ዋሻዎች የኰረብታዎችና ሸለቆዎች ከርሠ ምድር ሲመረመሩ የሚገኘውን ውጤት በተስፋ እንጠባበቃለን፡፡

አሁን ግን በኢትዮጵያ የሳባዊውን ፊደል ታሪክ እንመለከታለን፡፡ ከዚህም ተያይዞ ከሳባውያን ፊደል የተወረሰውንና የተሻሻለውን የግእዝን ፊደል ልደትን እድገት እናነባለን፡፡


ይህን ርእስ ከመነሻው ጀምሮ ለመከታተል የሚቻለው፥
1ኛ. የሰው ታሪክ መነሻና መድረሻ ተመዝግቦበት ከሚገኝ የዘመናት አሮጌ እየተባለ ከሚጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ ምንጭ፤

2ኛ. በሰው ላይ በየጊዜው የተፈጸመውንና የሚፈጸመውን በምድራችንም የደረሰውንና የሚደርሰውን የሆነውንና የሚሆነውን ሁሉ እያጣሩና በጥናት እየመዘገቡ ከተዉልን የሰዎች ታሪክ ምንጭ፤

እንደ ሆነ የተረጋገጠ ነው፡፡ ስለ ሆነም ስለ ግእዝና ስለ ፊደላችን አመጣጥ ከመነሻው በምንወስደው ጥናት እላይ ከጠቀስናቸው ምንጮች የተገኘውን ታሪክ ባጭሩ እነሆ እናቀርባለን፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ እንደሚታወቀው ሁሉ ከጥፋት ውሃ በኋላ ኖኅና ልጆቹ ከነሚስቶቻቸው ከመርከብ ወረዱ፡፡ ልጆችንና የልጅ ልጆችንም ወለዱና ተባዙ፡፡ ለመበታተንም ፈቃደኞች ባለ መሆናቸው በአንድ ሜዳ ላይ እስከ ሰማይ የሚደርስ ግንብን በተተኰሰ ጡብና ዝፍት መሥራት ጀመሩ፡፡ እግዚአብሔር ግን ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት ሲላቸው በምድር ሁሉ ተበታትነው እንዲኖሩ እንጂ ለሰው መኖሪያ የፈጠራት ምድር ባዶ እንድትሆን አልነበረምና ይግባቡበት የነበረውን አንዱን ቋንቋቸውን አደባለቀባቸውና አንዱ የሌላውን ቋንቋ እንዳይሰማ አደረገ፡፡ ከዚህም የተነሣ ጀምረዉት የነበረውን የግንብ ሥራ አቆሙ፡፡ የቋንቋቸው መደበላለቅ ምክንያት ሆኖ ለመግባባት ስላልተቻላቸው በየአቅጣጫው ተባታትኖ መስፈር ግዴታ ሆነባቸው፡፡

በየሰፈሩበት መሬት የትውልዳቸው ሐረግ ሲቈጠር የኖኅ ልጅ ካም ኩሽን፥ ከነአንንና ወንደሞቻቸውን ወለደ፡፡ የኩሽ ልጆችም ምጽራይም፥ ፉጥ፥ ሉድ ሌሎቹም ከግብጽ እስከ ኢትዮጵያ የዐባይን ወንዝ ተከትለው ሰፈሩ ዘፍ. 2፥13፤ 10፥6-9፡፡

በሌላ በኩል የኖኅ ልጅ ዔቦር ሲሆን፤ የዔቦር ልጆች ፋሌቅና ዮቅጣን፥ የዮቅጣንም ልጆች ሳባ፥ አቤማኤል፥ አውፊር፥ ኤውላጥ፥ ዮባብ፥ መሆናቸው ተመዝግቧል፡፡ የሰፈሩትም ከማሴ አንሥቶ እስከ ስፋርና እስከ ምሥራቅ ተራራ ድረስ ነው (ዘፍ. 10፥25-31)፡፡

ሳባውያን በሰፈሩበት በዛፍ (የመን) መንግሥታቸውን መሥርተውና መንግሥተ ሳባ አሰኝተው፥ ለሴማዊ ቋንቋቸው ሳባዊ ፊደል ቀርጸው ሥልጣኔያቸውን ያስፋፉ ነበር፡፡ እነዚህ ሳባውያን ናቸው በከፊል ወደ አሁኒቷ ኢትዮጵያ ሲመጡ ሥልጣኔያቸውን ይዘው በመግባት ከኩሽያውያን ጋር የተደባለቁት፡፡

የዱሮ ሳባውያን የፊደል ፈጠራ ሥራ ቢደነቅም ተሻሽሎ ለግእዝ ቋንቋ አጠቃቀም በሚያመች ሁኔታ የበለጠ ጠቃሚ አገልግሎት እንዲሰጥ ያደረጉትን አባቶች ውለታ አያሳንስም፡፡ ይኸውም ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ በገባ ጊዜ በአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃንና በተከታዮቹ ሊቃውንት የተከናወነው ቀዋሚ የሆነ የፊደል ማሻሻል ሥራ ነው፡፡

ፍሬምናጦስ በ330 ዓ.ም. አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ተብሎ ለኢትዮጵያ መጣ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በፍሬምናጦስ ስብከት ስለ ሠራ በንጉሥ ዔዛና ዘመን ከነበሩ ኩሽያውያን፥ ሳባውያን እስራኤላውያን መካከል ብዙዎች አምነው ተጠመቁ፡፡

ወዲያውም ለክርስትና እምነት ትምህርት መሠረት የሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍት ወደ ቋንቋቸው እንዲተረጐምላቸው አስፈላጊና ተገቢ መሆኑን ተረዱና አነበቡት፡፡

ይሁን እንጂ ሳባዊ ሥነ ጽሑፋቸው በዛሬው አቀማመጡ ግእዝ የምንለው አንደኛውን ቦታ ይዞ የምናየው ብቻ አናጋሪነት የነበረው እንጂ ከካዕብ እስከ ሳብዕ (ከሁለተኛ እስከ ሰባተኛ) የሚያናግሩት ድምፀ ፊደላት አልነበሩምና በሳባውያን ሥነ ጽሑፍ እንደሚታይ ተዘነ አገበረ፤ (ታዜና አግበረ) ብሎ የመጸፍ መንገድ ብቻ ይጠቀሙ ነበር፡፡

ነገር ግን ቅዱሳት መጻሕፍትን በዚህ የአጻጻፍ መንገድ ለመጠቀም የሚፈልጉ ቢሆን ኖሮ አብርሃም የሚለውን ስም አበረሀመ፥ ኢየሱስ የሚለውንም አየሰሰ፥ ዳዊት የሚለውን ደወተ፥ ክርስቶስ የሚለውንም ከረሰተሰ እየተባለ ሊጻፍ ግድ በሆነ ነበር፡፡

እንዲዚህ ቢሆን ደግሞ በግሪክና በዕብራይስጥ ተለምደው ከቈዩት የሃይማኖት ቃላትና ስሞች መራቅን ሊያስከትል ነው፡፡ እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ቋንቋቸው እንዲተረጐምላቸው የወደዱ ክርስቲያኖች ሳባውያን ከከሣቴ ብርሃን ሰላማ ጋር በመመካከር ተዘነ አገበረ በሚል አካሄድ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመተርጐም ይልቅ፥ በፊደላቸው አተኰሩና ፊደላቸውን አሻሽለው መጻፍን መረጡ፡፡

ስለዚህ ጥንታዊና ባህላዊ ሰባዊ ፊደላቸው መልኩና የቅርጹ ይዘት ሳይለወጥ መደቡን እንደ ያዘ በዋየሎቹ (vowels) አ.ወ.የ. አናጋሪነት ከካዕብ እስከ ሳብዕ (ከሁለተኛ እስከ ሰባተኛ) የፊደላት ድምፆች እንዲነገር፤

አናጋሪ ዋየሎቹ (አ.ወ.የ.) ደግሞ ከውስጥ እንዳሉ በሚያሳዩት ምልክቶች ከካዕብ እስከ ሳብዕ (ከሁለተኛ እስከ ሰባተኛ) ድምፅ ሊያናግሩ እንዲዘጋጁ ወሰኑ፡፡

ይህም በመደረጉ እንቅፋት የሚሆነው ነገር ሁሉ ተወግዶ ስለ ተካከለ ቅዱሳት መጻሕፍት ያለ አንዳች ችግር ሊተረጐሙ ተቻለ፡፡ በዚህ ረገድ ልምድ እየተገኘለት የታወቀ ቋንቋ ሆነ፡፡ እንግዲህ የግእዝ ቋንቋ የሳባውያን የታደሰ ቋንቋ መሆኑ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ክርስትና ጋር ተያይዞ ዐብሮ በቀል መሆኑ ነው፡፡

የግዕዝ ቋንቋ ትምህርት ጥቅም

የግእዝ ቋንቋ ከጥንት ከሳባውያን ተሻሽሎ የመጣ ሴማዊ ቋንቋ ነው፡፡ እምነተ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ዘመን ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስና ልዩ ልዩ መጻሕፍት ከግሪክ፥ ከሶርያ፥ ከቅብጥ (የዱሮ የግብጽ ቋንቋ) ወደ ግዕዝ ተተጕመው ይገኛሉ፡፡

የሀገሪቱ ሊቃውንትም የደረሱዋቸው ልዩ መጻሕፍት የሚገኙት በግእዝ ቋንቋ ነው፡፡ ለምሳሌ፦ የታሪክ፥ የፍልስፍና  የመጽሐፍ ቅዱስ ባህላዊ አተረጓጐም የቤተ ክርስቲያን አባቶች መጻሕፍት እንዲሁም የዜማና የቅኔ ድርሰቶች በጠቅላላው ኢትዮጵያዊ የሆነ የሥነ ጽሑፍ ጓዝ ሁሉ በግእዝ መጻሕፍት ተጽፈው ይገኛሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ የተስፋፋው የአማርኛ ቋንቋም የተወለደው ከግዕዝ ስለ ሆነ፥ የቃላቱ መሠረት ከግእዝ ይፈለጋል፡፡

በጠቅላላው የተዘረዘሩትን ሁሉ ለማጥናትና ለማወቅ ሲያስፈልግ የግዕዝ ትምህርት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቶአል፡፡

“የማሽላ ዘር ከነአገዳው ቸር” ተብሎ በምሳሌ እንደሚነገር ሁሉ ግእዝና ፊደላቱ በሁሉም ረገድ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጠቃሚዎች ሆነው ተገኝተዋል፡፡

ስለ ግእዝ ቋንቋና ስለ ሥነ ጽሑፍ ጥቅም ከዚህ በላይ አስረድተን ገልጸናል፡፡ ይህ የግዕዝን ቋንቋ ለተማሩና ለሚያነቡ ሲሆን፤ የግዕዝ ፊደል ደግሞ ለኢትዮጵያ ብሔረሰብ አገልግሎቱን በማበርከት የማይቋረጥ ጥቅም እየሰጠ ነው፡፡

መጀመሪያ ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመተርጐም ሲባል በሰላማ ከሣቴ ብርሃንና በአክሱማውያን ሊቃውንት የግእዝ ፊደል አገልግሎት ለግእዝ ቋንቋ ዐዋቂዎች ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ላሉት ብሔረሰብ ሁሉ ሆኖ ይገኛል፡፡

የዐማርኛ ሥነ ጽሑፍ በግእዝ ፊደል ነው፡፡
የትግርኛ ሥነ ጽሑፍ በግእዝ ፊደል ነው፡፡
የኦሮምኛ ሥነ ጽሑፍ በግእዝ ፊደል ነው፡፡
የከምባትኛ ሥነ ጽሑፍ በግእዝ ፊደል ነው፡፡
የወላይትኛ ሥነ ጽሑፍ  በግእዝ ፊደል ነው፡፡
የጉራጌኛ ሥነ ጽሑፍ በግእዝ ፊደል ነው፡፡
የኮንሶኛ ሥነ ጽሑፍ በግእዝ ፊደል ነው፡፡
አኙዋክኛ የመሳሰሉት ብሔረሰቦች ሁሉ

በጠቅላላው በመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር እየተዘጋጁ ለተለያዩ ብሔረሰቦች የሚታደሉ ቅዱሳት መጻሕፍት በግእዝ ፊደላት የተጻፉ ናቸው፡፡

ስለዚህ ግእዝና በመጀመሪያዎቹ ዘመናት ፊደላቱን ያዘጋጁ ሰዎች ሥራቸው ተባርኮላቸዋል ለማለት እንችላለን፡፡
ይኸውም ግእዝና ፊደላቱ በሥጋዊና በመንፈሳዊ ብሔረሰብ ሁሉ ጋር ተካፋይነቱን የሚያሳይ ሆኖአል፡፡

No comments:

Post a Comment