Monday, February 1, 2016

ኦርቶዶክስ ማነው? (ማኅበረ ቅዱሳን ኦርቶዶክሳዊ ነውን?)

(ከላእከ ወንጌል ዘኢየሱስ)

 ሳትሞት ሞተች ብለው ምንም ቢቀብሯት
አትሞትም፤ አትሞትም፤ አትሞትም እውነት፤
እውነት የግዜር ገንዘብ እንደግዜር ባሕርይ
ዘላለም ሕያው ናት በምድር በሰማይ፡፡[1]
የዚህ ጽሑፍ ዋና ዐላማ በትምህርተ ሃይማኖት ኦርቶዶክስ ሳይሆኑ ኦርቶዶክስ ነን በማለት በልዩ ልዩ መንገድ ቤተ ክርስቲያናችንን እያወኩ ያሉ ማኅበራት እነርሱ እንደሚሉት ኦርቶዶክሳውያን አለመሆናቸውን ለምእመናን ማሳወቅ ነው፤ በተለይ ወጣቱ በትምህርተ ሃይማኖት ዕጥረት ምክንያት ቤተ ክርስቲያኑን በተገቢው መንገድ ስለማያውቅ በየዩኒቨርሲቲው በግቢ ጉባኤያት ስም ላጠመደው ማኅበር ምርኮኛ ሆኖ ይታያል፡፡ ስለዚህ ወጣቶች ከማኅበር ፍቅር ይልቅ የአንዲት፣ ቅድስት፣ ከሁሉ በላይ የሆነችና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ፍቅር እንዲያድርባቸው በዚህ ተከታታይ ጽሑፍ ለመርዳት እንሞክራለን፤ የእውነት አምላክ ልባችንን ለእውነት ብቻ ማስገዛት እንድንችል ይርዳን፤ አሜን፡፡
በዚህ ዘመን ኦርቶዶክስ ነን ባዮች ኦርቶዶክስ ለመሆን ባይቻላቸውም ለመባል ብዙ አማራጮችን በመጠቀም ላይ ናቸው፤ እነዚህ አማራጮችም በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አጥር ግቢ ውስጥ መሰባሰብ፥ ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠ ሕግ እንመራለን ማለት፥ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የቊርጥ ቀን ልጆች ነን በማለት በየመጽሔቱ፣ በየጋዜጣውና በኢንተርኔት መስበክ፥ ከቅዱስ ሲኖዶስና ከአባላቱ ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በላይ ለኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተቈርቋሪዎች ለመምሰል መሞከር፥ የእነርሱ ማኅበር አባላት ለመሆን የማይፈልጉ ኦርቶዶክሳውያን አባቶች፣ አገልጋዮችንና ምእመናንን ተሐድሶ ናቸው በማለት መክሰስና ማሳደድ፥ ሁሉንም የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅሮች ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ ተሐድሶ እንደ ወረራቸውና ያልተወረረ የእነርሱ ማኅበር ብቻ ስለ ሆነ ሕዝቡ ቅዱስ ፓትርያርኩንም ሆነ ሌሎች አባቶችንና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን እንዲጠራጠር ማድረግና ብቸኛው የኦርቶዶክስ አለኝታ የማይጠረጠር ድርጅት የእነርሱ ማኅበር ብቻ መሆኑን መስበክ እንደ ሆነ ካደረግነው ክትትል ለመረዳት ችለናል፡፡

ኦርቶዶክስ ለመሆን የሚያስፈልጉ መሠረታውያን ነገሮች፥
(1) የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን ቅዱስ መጽሐፍን ሳይቀንሱና ሳይጨምሩ መቀበልና ትምህርትንና ሕይወትን በቅዱስ መጽሐፍ ላይ መመሥረት፥ ማለትም የእግዚአብሔርን ቃል ወደ ራስ ፍላጎት መጠምዘዝ ሳይሆን ፍላጎትንና አመለካከትን በእግዚአብሔር ቃል ማረም፥
(2) በአኃት ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን የሃይማኖት መግለጫዎች መቀበልና ማስተማር፥
(3)አኃት የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የተቀበሏቸውን የኒቅያ፣ የቊስጥንጥንያና የኤፌሶን ጉባኤያትንና ውሳኔዎቻቸውን መቀበልና ማክበር፥
(4) በቅዱስ መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ መሆኑን እያረጋገጡ የቀደምት ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንትን ትምህርት መቀበል ናቸው፡፡
ከተራ ቊጥር (2)-(4) የተጠቀሱት እውነተኛነታቸው የሚረጋገጠው በቅዱስ መጽሐፍ የተመሠረቱ በመሆናቸው ይሆናል፤ የቅዱስ መጽሐፍን ትምህርት የሚቃረን ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ሥርዐት መስተካከል ይኖርበታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ማረም የማትችለው መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ሚዛንነት ማስተካከል ትችላለች፤ ይገባታልም፡፡  
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኦርቶዶክስም፣ ተዋሕዶም፣ ቤተ ክርስቲያንም የተባለችው በክርስቶስ ላይ ባላት እምነትና ትምህርት ነው፤ ያለ ክርስቶስ ያገኘችው ቅጽል የኢትዮጵያ የሚለው ቃል ብቻ ነው፤ ያለ ክርስቶስ ኦርቶዶክስም፣ ተዋሕዶም፣ ቤተ ክርስቲያንም መሆን አትችልም፤ ለመባል ግን የሚከለክላት አይኖርም ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው በማንኛውም መለኪያ ተለክተው ኦርቶዶክስ መሆን የማይችሉ ማኅበራት ኦርቶክስ ነን ከማለት አልፈው እውነተኞችን የኦርቶዶክስ አገልጋዮችና ምእመናን በማሳደድ ሥራ ተጠምደው ያሉት፡፡ ለእነርሱ ኦርቶዶክሳዊነት መከሰስ ሳይሆን መክሰስ፣ መሰደድ ሳይሆን ማሳደድ፣ መገፋት ሳይሆን መግፋት ነው፡፡ አብንና ልጁን ኢየሱስን ስለማያውቁ እውነተኞችን ሲገድሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ያቀረቡ ይመስላቸዋል፡፡[2]
የማኅበረ ቅዱሳንን ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነ ትምህርት ለማሳየት የተጠቀምንባቸው ምንጮች በራሱ በማኅበሩ ልሳናት በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣና በሐመር መጽሔት የሚወጡ ጽሑፎች፣ በማኅበሩ የሚዘጋጁ መጻሕፍት፣ በግለሰቦች ተዘጋጅተው በማኅበሩ ኤዲቶሪያል ቦርድ ታይተውና ተፈቅደው የሚታተሙና የሚሠራጩ መጻሕፍት፣ በኢንተርኔትና በልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች የሚሠራጩ የማኅበሩ ትምህርቶች ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የማኅበሩን ስሕተቶች ለማሳየት ማኅበሩ ኀላፊነት ያልወሰደባቸውን ጽሑፎች በማስረጃነት አንጠቀምም፡፡   
ለእውነት ባልተሰጠ ልብ ሲመዘን ማኅበረ ቅዱሳን መናፍቅ ነው ቢባል በራሱ አባላትም ሆነ በምእመናን ዘንድ ከዚያም ዐልፎ በጳጳሳት ሳይቀር ድንጋጤና አግራሞት እንደሚፈጥር እንገምታለን፤ ሆኖም ርግጠኞች የሆንንበት እውነት ቢኖር ማኅበረ ቅዱሳን የመናፍቃን ስብስብ እንጂ ኦርቶዶክሳዊ አለመሆኑ ነው፡፡ ይህንም እውነት ዐብረውን ለሚዘልቁ አንባቢዎቻችን በእግዚአብሔር ቃል መሠረት በተከታታይ በሚወጣው በዚህ ጽሑፍ እንደምናረጋግጥላቸው ርግጠኞች ነን፡፡  
በመሠረቱ ማኅበረ ቅዱሳን ከእውነት በመራቅ ገንዘብና ሥልጣን ላይ ብቻ ትኲረት ባደረጉ አንዳንድ ጳጳሳትና አገልጋዮች ዘንድ አይነቀፍ እንጂ የእግዚአብሔር ቃል ቢነቅፈው ጒዳዩ አይደለም፤ ምክንያቱም የተቋቋመበት ዋና ዐላማ ቤተ ክርስቲያንን በመንፈሳዊ ኀይል የሚያስታጥቀውን የእግዚአብሔርን ቃል ለመስበክና ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትንሣኤ እንድታደርግ መርዳት ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን ቃል በተረታ ተረት በማሰር ትንሣኤዋን ማዘግየት፥ እንዲሁም የተመሠረተበትንና የቆመለትን ሐሰተኛ ታሪክ ለመጠበቅ ነውና፡፡   
የማኅበሩን የስሕተት ትምህርቶች ምንጭ ለማወቅ ባደረግነው ጥናት ማኅበረ ቅዱሳን አሁን ከገባበት የክሕደት ገደል ውስጥ የገባውና ለመውጣትም የተቸገረው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ካለው የተሳሳተ እምነት የተነሣ እንደ ሆነ ተገንዝበናል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጸሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል አታውቁምና ትስታላችሁ[3] ሲል የሰዱቃውያንን የምንፍቅና ትምህርት ምንጭ እንደ ገለጠልን፥ ማኅበሩም በእግዚአብሔር ቃል ላይ ባለው የተሳሳተ እምነት ምክንያት ስሕተቱን የማረምና ንስሓ የመግባት ዕድል ያላገኘው ከዚህ መሠረታዊ ችግር የተነሣ ነው ማለት እንችላለን፡፡ በዚህ ጽሑፍም ማኅበሩ በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ከፈጸማቸው ስሕተቶች አንዱን እናያለን፡፡
1.    ማኅበረ ቅዱሳን በመጽሐፍ ቅዱስና በአዋልድ መጻሕፍት መካከል ያለውን መሠረታዊ ልዩነት አያምንም፡፡
በብሉይና በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፈውን የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ ልናምነውና ልንቀበለው ይገባል፤ ምስጢሩ ባይገባንና ባንረዳው እንኳን ግለጥልን ብለን ወደ እግዚአብሔር ልንጸልይ፥ በእግዚአብሔር ቃል ዕውቀት የበሰሉትን በመጠየቅና መጻሕፍትን በማንበብ ልንመረምር ይገባናል እንጂ ልንነቅፍ አይገባንም፡፡ ማንም ቢሆን ምንም ቢማርና ቢመራመር በመንፈሳዊ ነገር ቅዱስ መጽሐፍን የሚቃወምና የሚያፈርስ መጽሐፍ መጻፍ አይገባውም፤[4] አዋልድ መጻሕፍትንም እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሊቈጥራቸው አይገባም፡፡ ነገር ግን የቅዱሳንን ታሪክ ለማወቅ፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያዎችን ለመመልከት በፈለግን ጊዜ አዋልድ መጻሕፍትን ልናነባቸው እንችላለን እንጂ እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት ቈጥረን የግድ ልንቀበላቸው፥ የሃይማኖት ክርክር በተነሣ ጊዜ ጠቅሰን ልንከራከርባቸው፥ ሰዎችንም እነዚህን መጻሕፍት ካልተቀበላችሁ ክርስቲያኖች አይደላችሁም ብለን ልናወግዛቸው አንችልም፡፡
ቅዱስ አትናቴዎስ 40 የብሉይ ኪዳንና 27 የሐዲስ ኪዳን በአጠቃላይ 67 አምላካውያት መጻሕፍትን በተመለከተ ሲናገር፥ “እነዚህ የተጠማ በውስጣቸው በሚገኙ ቃላት ይረካ ዘንድ የእውነተኛ ድነት (መዳን) ምንጮች ናቸው፤ በእነዚህ ብቻ የቅድስና ትምህርት ይሰበካል፡፡ ከእነዚህም ማንም ምንም መጨመር ወይም መቀነስ አይችልም፡፡” ብሏል፡፡ ስለ ተነባቢዎቹ (ንባባውያት) መጻሕፍት ደግሞ፡- “... ከሚቀነኑት መጻሕፍት ጋር ያልሆኑ ነገር ግን ዐዲስ ለሚመጡትና ትምህርተ ክርስትናን ለመማር ለሚፈልጉ ይነበቡ ዘንድ በአባቶች የታዘዙ ሌሎች መጻሕፍት እንዳሉ አስፈላጊ መሆኑን እጨምራለሁ” ብሏል፡፡[5]
ማኅበሩ ግን ሚያዝያ 1999 .ም. ባሳተመው ሐመረ ተዋሕዶ የሐመር መጽሔት ልዩ መጽሐፍ በዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተዘጋጅቶ  ትምህርተ ሃይማኖትበሚል ርእስ የቀረበውን ጽሑፍ ፈቅዶ ማሳተሙንና ማሠራጨቱን ገልጾአል፡፡ እኛም በዚህ ጽሑፍ የተፈጸሙ ስሕተቶችን በአራት ነጥቦች አካተን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
1.1.  የአዋልድ መጻሕፍትን ምንነት ለማስረዳት የተጻፈውን ጽሑፍ ትምህርተ ሃይማኖት በሚል ርእስ ማቅረብ ተገቢ አይደለም
ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር በተያያዘ ትምህርተ ሃይማኖት በሚል ርእስ መቅረብ የሚገባው የአሥራው መጻሕፍትን ምንነት፣ ቀኖናና ተቀባይነት ለማስረዳት የሚጻፍ ጽሑፍ ነው፡፡ የዚህን ጽሑፍ መልእክት ግን የአዋልድ መጻሕፍት ጥቅምና በቤተ ክርስቲያን ያላቸው ተቀባይነትበሚል ወይም በሌላ ተመሳሳይ መልእክት በሚሰጥ ርእስ ሥር አቀናብሮ ማቅረብ ይቻል ነበር፡፡ ለማኅበረ ቅዱሳን ግን አዋልድ መጻሕፍትን አለመቀበል አሥራው (ቅዱሳት መጻሕፍት) መጻሕፍትን አለመቀበል እንደ ሆነ ስለሚቈጠርና ከሃይማኖት እንደ መውጣትም ስለሚታይ፥ ይህን የማኅበሩን የተሳሳተ ግንዛቤ ለማጒላትና በአባላቱም ሆነ በአንባብያን ምእመናን ላይ የስሕተት ትምህርቱን ለመጫን ትምህርቱ ትምህርተ ሃይማኖትበሚል ርእስ ሲቀርብ፥ የማኅበሩ የኤዲቶሪያል ቦርድ ለራሱ ርእዮት እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ደኅንነትና ለእውነት አልቆመምና ሳይስተካከል እንዲታተም ፈቀደ፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዐቋም ለመረዳት እንድንችል ለሚመለከተው አካል (ለሊቃውንት ጉባኤ) ለማስመርመርም ፈቃደኛ አልነበረም (ቢያንስ ትምህርተ ሃይማኖት ነክ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ጽሑፎች ቢያስመረምር ለራሱም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን የተሻለ ይሆን ነበርና)፡፡
 1.2. አዋልድ ያልሆኑትን አዋልድ ብሎ ጠቅሷል
በገጽ 61 አዋልድ የሚለው ቃል ትርጉም፥ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐሳብና እውነታ ሳይወጡ በእርሱ ላይ ተመሥርተው የመጽሐፍ ቅዱስን ኀይለ ቃልና ውስጠ ምስጢር ለመተርጎም፣ ለማብራራት፣ ለማተትና ለመተንተን፣የሚጻፉ መጻሕፍት አዋልድ መጻሕፍት ይባላሉ፤ … ይህን መሠረታዊ ወላጃቸውን (መጽሐፍ ቅዱስን) መስለው የተወለዱና የተገኙ መጻሕፍት ናቸው፤ አዋልድ መጻሕፍት የሚባሉት፡፡ሲል የሚያስማማ ትርጉም ከሰጠ በኋላ ብዙ ሳይርቅ በገጽ 62 ) የያሻር መጽሐፍ ) የእግዚአብሔር የጦርነት መጽሐፍ ) የእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ) የይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የብሉይ ኪዳን የአዋልድ መጻሕፍት ምሳሌዎች ሆነው ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በየትኛውም ጊዜ፣ በየትኛውም ቤተ ክርስቲያን (ምንም እንኳን በማኅበሩ እምነት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውጭ ቤተ ክርስቲያን ባይኖርም) አዋልድ አልተባሉም፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኙና (የተወለዱ) መጽሐፍ ቅዱስን ለማብራራት የተጻፉም አይደሉም፤ ስለዚህ እኒህን መጻሕፍት አዋልድ ብሎ ከመጥራት ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሰጣቸውን ስም፥ የጦርነት ወይም የታሪክ መጽሐፍ የሚለውን ስማቸውን ልናከብርላቸው ይገባል፡፡
1.2. የአሥራው መጻሕፍትንና የአዋልድ መጻሕፍትን ዝምድና ለመግለጥ የሚያሳስት ምሳሌ መጠቀም
የዚህን ምሳሌ አሳሳችነት ስንናገር፥ ማኅበረ ቅዱሳን ምሳሌ ዘየሐጽጽ” (ጒድለት ያለበት ምሳሌ) ነው ሊለን እንደሚችል እንገምታለን፡፡ ሆኖም የእኛ ዐላማ ምሳሌው የሚያስተምረውን የስሕተት ትምህርት ማጋለጥ እንጂ የምሳሌን ዘየሐጽጽነት ማስተባበል አይደለም፡፡ በገጽ 62 ጢሞቴዎስ አለን የተባለው ሕንዳዊ የሥነ መለኮት ሊቅ አንድን መጽሐፍ አዋልድ የሚያሰኙ መስፈርቶችን ካስቀመጠ በኋላ፥ የአዋልድ መጻሕፍትን ምንነት ለማስረዳት የተጠቀመውን ምሳሌ ስሕተቱን ሳይመረምር ተጠቅሞበታል፡፡ ምሳሌውም፥የሰው ዘር አባትና እናት አዳምና ሔዋን ናቸው፤ ልጆቻቸው ግን በዝተዋል፤ ሞልተዋል፤ ይበዛሉም፤ ይሞላሉም፤ አዋልድ መጻሕፍትም አባት እናታቸው አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ቢሆንም ልጆቻቸው ግን በዝተዋል፤ ሞልተዋል፤ ይበዛሉም፤ ይሞላሉም፡፡ይላል፡፡ በዚህ ምሳሌ ውስጥ ክፉ ሐሰተኛ ትምህርት ተሰውሮ አለ፡፡ ሰው ከሰው ሲወለድ አባቱንና እናቱን ፍጹም ሊያክል፣ ፍጹም ሊመስል ይችላል፤ በመጽሐፍ ቅዱስና በአዋልድ መጻሕፍት መካከል ያለውን ከፍተኛ ልዩነት ግን መቼም ቢሆን ማቀራረብ አንችልም፡፡ ምክንያቱም ከሰው የተወለደ ሰው ከወላጁ ጋር እኩል ቢሆንምከመጽሐፍ ቅዱስ የተወለደ መጽሐፍ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መቼም ቢሆን እኩል ሊሆን አይችልምና፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ግን ሊያሳስት በሚችል ምሳሌ ተጠቅሞ አዋልድ መጻሕፍትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እኩል ሊያደርግ ሲጣጣር ይታያልና ሃይ ሊባል ይገባል እንላለን፡፡ በእኛ በኩል ከቅንነት መጒደል እንጂ ከዕውቀት ማነስ አይመስለንምና ሥጋታችን ከፍተኛ ነው፡፡
 1.4. ለአሥራው መጻሕፍት (ለመጽሐፍ ቅዱስ) የተነገረን ጥቅስ ለአዋልድ መጻሕፍት ሰጥቶ መጥቀስ
በገጽ 62 የተጠቀሰውን 2ጢሞ. 314-17 (በመጽሔቱ 1ጢሞ. ተብሎ ነው የተጠቀሰው) እነርሱ እንደ ቈነጸሉት ሳይሆን ሞልተን ስንጠቅሰው እንደሚከተለው ይነበባል፡፡አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፤ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን[ት] መጻሕፍትን ዐውቀሃል፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ፣ ልብንም ለማቅናት፣ በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል፡፡ዳንኤል ስሕተቱን ለመደገፍ የጠቀሰው የተሠመረበትን አረፍተ ነገር ብቻ ነው፡፡ በዳንኤልና በመሰሎቹ የማኅበረ ቅዱሳን የኤዲቶሪያል ቦርድ አባላት ትምህርት መሠረት መዳን የምንችልበትን ጥበብ የሚሰጡን፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው መጻሕፍት ማለት በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ዐቢይ ክፍል በብሉይ ኪዳን የተካተቱ ቅዱሳት መጻሕፍት ሳይሆኑ ጢሞቴዎስ ያጠናቸው የነበሩ ገድላት፣ ድርሳናት፣ የተአምርና የትርጓሜ መጻሕፍት ናቸው፡፡ ለመሆኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ቅዱሳት መጻሕፍት የሚባሉት በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገብነት የተካተቱት፥ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉት ቅዱሳት መጻሕፍት (Inspired books) ሳይሆኑ ገድላትና ድርሳናት እንዲሆኑ የተወሰነው መቼና በየትኛው ቀኖና ይሆን?
ይህ ጥቅስ ስለ የትኞቹ መጻሕፍት እንደሚናገር እውነትን በተረዱና ቅን ልቡና ባላቸው ሰዎች ዘንድ የተገለጠ ነው፡፡ የአዋልድ መጻሐፍትን ተቀባይነትና ጠቃሚነት ለማስረዳት ማኅበረ ቅዱሳን ጥቅሱን ባልተነገረበት ዐውድ ከመተርጐም ይልቅ ጊዜ ወስዶ፥ ሌሎች መረጃዎችን ሰብስቦ ቢጽፍ የተሻለ ይሆን ነበር፤ ሆኖም ማኅበሩ የፈለገው እውነት መናገርን ሳይሆን  የያዘውን ሐሰት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲደግፍለት መጠምዘዝ ነበርና በዚሁ ቀጠለበት፡፡ መቼ ይሆን የእኛን አሳብ በእግዚአብሔር ቃል ለማረም ፈቃደኞች የምንሆነው? እግዚአብሔር ልባችንን ወደ እርሱ ይመልስ!
ለዛሬ ይህን ያህል ካየን፥ ማኅበረ ቅዱሳን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የያዘውን የተሳሳተ ዐቋም የምንዳስስበትን ቀጣይ ጽሑፍ እስከምናቀርብ ድረስ በዚህች ዐጭር ግጥም እንሰናበታችኋለን፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወድዱት ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን፡፡[6]
አይዟችሁ በጎች /ምእመናን/ አትደንግጡ
ይህን ሰርዶ ስትግጡ /የወንጌልን እውነት ስትማሩ፤
ከዚሁ አለና በመንፈስ
እረኛችሁ ኢየሱስ[7]
 በጮራ ቊጥር 42 ላይ የቀረበ 
[1] ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፡ ሃይማኖተ አበው ቀደምት ወፍልጠተ ውሉድ ደኃርት
[2]  ዮሐ. 16፥1
[3] ማቴ. 22፥29
[4] ኅሩይ ወልደ ሥላሴ(1919) ጽባሕ ገጽ 24-29
[5] ዶ/ር ዲበኵሉ ዘውዴ (1987)፡ 81 ቅዱሳት መጻሕፍትና ምነጮቻቸው ቀኖናት ገጽ 48-54
[6] ኤፌ. 6፥24
[7] ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፡ ሃይማኖተ አበው ቀደምት ወፍልጠተ ውሉድ ደኃርት

No comments:

Post a Comment