ኢየሱስ
ክርስቶስ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ
ባለፈው ዕትም በዚህ ክፍል ውስጥ የዕብራውያንን መልእክት መሠረት በማድረግ የኢየሱስ ክርስቶስን
መካከለኛነት ለማሳየት ሞክረናል። በተከታታይ እያቀረብን ያለነው የክርስቶስን መካከለኛነት የተመለከተው ይህ ትምህርት ከክርስቶስ
ትምህርነት መጀመር እንደ ነበረበት አልዘነጋነውም፤ ሆኖም በክርስቶስ መካከለኛነት ዙሪያ ዋና መከራከሪያ ሆነው የሚገኙት መጽሐፍ
ቅዱሳውያን ክፍሎች መልእክታተ ሐዋርያት በመሆናቸው፥ በዚያ መጀመሩ መልካም መስሎ ስለ ታየን ከዚያ ጀመርን። እስካሁን ያየነውና
በሐዋርያት ምስክርነት ላይ የተመሠረተው የክርስቶስ የመካከለኛነቱ ትምህርት ምንጭ ራሱ ክርስቶስ መሆኑን በዚህ ዕትም ለማሳየት
እንሞክራለን። ከኢየሱስ መካከለኛነት ጋር ተያይዞ
መካከለኛነቱን ማስቀረት ላይቻል፥ በአንዳንድ
ወገኖች ለማምታታት ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ መከራከሪያዎችንም እንዳስሳለን።
የክርስቶስን መካከለኛነት ማስተዋል ከስሕተት የሚያድንና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያመጣ ዋና እና
መሠረታዊ የክርስትና ትምህርት ነው። ይህን የትምህርት መንገድ የሳተ ሰው ፍጻሜው ጥፋትና የዘላለም ሞት ይሆናል። ምክንያቱም ያ
ሰው ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰውን ብቸኛና ቀና መንገድ ስቶ ሌላ አቅጣጫን ተከትሏልና።