ከነቅዐ ጥበብ
ባለፈው ዕትም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ
መካከለኛነት በቀረበው ጽሑፍ፦ አምላክ ሰው የሆነበትን ምክንያት፣ ቃል ሥጋ የመሆኑን አስፈላጊነት፣ የክርስቶስ አዳኝነትና
መካከለኛነት ተያያዥ መሆናቸውን በማብራራት፥ የኢየሱስ ክርስቶስን መካከለኛነት ለማስተባበል በዚህ ዘመን የሚነዙ የስሕተት
ትምህርቶችን ለመጠቈም ተሞክሯል፡፡ በዚሁ መሠረት ኢየሱስ አሁን ፈራጅ እንጂ አማላጅ አይደለም የሚለውንና ሮሜ 8፥34 ስለ
ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት የሚያስተምረውን በመጠኑ ተመልክተናል፡፡ በዚህ ዕትም ደግሞ ተከታዩ ክፍል ይቀርባል፡፡
ኢየሱስ
አሁን ጠበቃ ነው ወይስ ዳኛ?
ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለመድረስ ከራሱ ከመጽሐፍ
ቅዱስ መጀመር የግድ ነው፡፡ "ትንሽ ቆሎ ይዞ ወደ አሻሮ መጠጋት" እንደሚባለው ብሂል፥ የራስን አመለካከት
ወይም ሌላ ምድራዊ ተመክሮን ይዞ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መጠጋት፥ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመቀበል ሳይሆን፥ መጽሐፍ ቅዱስን
ለራስ ሐሳብ ደጋፊ አድርጎ ለማቅረብ ያለመ አካሄድ ነው፡፡