የጮራ መንፈሳዊ መጽሔት 25ኛ ዓመት የምሥረታ ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ የቀረበ ጽሑፍ
“አቀድም አእኵቶቶ ለእግዚአብሔር በእንተ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ” (ሮሜ 1፥8)። በእንዲህ መሰሉ ክርስቲያናዊ ክብረ በዓል ላይ ቃለ አኰቴት መቅደሙ አያስገርምም። ደግሞስ እንደ ክርስቲያን በኹሉና ስለ ኹሉ ማመስገን ይገባን የለምን? ስለ ኾነም ከኹሉ አስቀድመን በነገር ኹሉ የረዳንን ልዑል እግዚአብሔርን በኢየሱስ ክርስቶስ እናመሰግነዋለን።
ቀጥሎስ? እንኳን
ደስ አላችሁ። የማኅበረ በኵር አባላትና አገልጋዮች፥ የጮራ መንፈሳዊ መጽሔት መሥራቾች፥ አዘጋጆች፥ ዐምደኞች፥ የራእዩ ደጋፊዎችና በዚች መጽሔት አገልግሎት የተጠቀማችሁ ኹሉ እንኳን ለዚህ ቀን አደረሳችሁ።
መግቢያ
አገራችን ኢትዮጵያ የሚታዩና የሚዳሰሱ ቀደምት የሥልጣኔ አሻራዎች ባለቤት
መኾኗ የታወቀ ነው። በአስገራሚ ኪናዊ ጥበብና ውበት የተገነቡ ዘመን ተሻጋሪ የሥነ ሕንጻ ባለቤት ናት። በሥነ ጽሑፋዊ ቅርሶችም
ረገድ የራሷ ፊደል ያላት ብቻ ሳይኾን ቀደምት ጽሑፎችን አበርክታለች። ለጽሑፍ ሥራ እንግዳ ኾናም አልኖረችም። በጥንታዊውም፥
በመካከለኛውም ኾነ በዘመናዊው ታሪካችን ወቅት በተከሠቱ ኹነቶችና ባጋጠሙን ውስጣዊም ኾነ ውጫዊ ፈተናዎች የወደሙትን ሳንቈጥር፥
በርካታ የሥነ ጽሑፍ ውጤቶች አካብተናል። እግዚአብሔር ይመስገን።