Friday, February 2, 2018

ወቅታዊ ጉዳይ

                           እውን ኢየሱስ (ሎቱ ስብሐት) “ሰይጥኗልን?”
ግቢያ
በየዘመኑ ኑፋቄንና ልዩ ወንጌልን የሚያስተምሩ ሰዎች በዋናነት ሐሳባቸው የሚያጠነጥነው የእውነተኛው ወንጌል ማእክል በኾነው በክርስቶስና በማዳን ሥራው ላይ ነው። ከክርስቶስና ከመስቀሉ ሥራ ላይ ዐይንን ማንሣት በቤተ ክርስቲያን፣ በአገር፣ በትውልድ፣ በቤተ ሰብ … ላይ የሚያመጣውን ድንዛዜ ዲያብሎስ በትክክል ያውቃል። ስለዚህ በየዘመናቱ ተመሳሳይ ክሕደቶችን ዘመን ቀመስ በማድረግና ከሰዎች ፍላጎት ጋር በማስተሳሰር፣ ይዘታቸውን በመለዋወጥና ሰፋ በማድረግ ሲያመጣ እናስተውላለን።

የስሕተቶቹ መልካቸውና ምንጫቸው ከኹለት አቅጣጫ ሊታይ ይችላል፤ የመጀመሪያው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን በትክክል ካለማጥናት ሲኾን፣ ኹለተኛው ደግሞ ሰውን ማእከል ያደረገውና የተዛባው የስሕተት ትምህርታቸው፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር ዝቅ የሚያደርግ ኾኖ ስለሚገኝ፣ ይህ እርሱን ያለመውደድ ውጤት ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። ስለዚህም ስሕተታቸውን ስንቃወምና ኹለተኛውን ሐሳብ ለማፍረስ ስንሠራ፣ የዋሃንንና ባለማስተዋል የሳቱትን በርኅራኄ ለመመለስና ለማቅናት ደግሞ የፊተኛውን ሐሳብ እንይዛለን።

ዛሬ በኢትዮጵያ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ከሚታመሱባቸው የስሕተት ትምህርቶች መካከል “የእምነት እንቅስቃሴ” አንዱ ነው። ይህ የስሕተት ትምህርት በ1980ዎቹ ብቅ ብሎ በጊዜው ብዙ ትርምስ ፈጥሮ፣ በኋላ ላይ ከስሞ እንደ ነበር የሚታወስ ነው። ከኹለት ዐሥርት ዓመታት በኋላ ግን እንደ ገና በማንሠራራት ወደ ቤተ ክርስቲያን መድረክ ተመልሶ ቤተ ክርስቲያንን እያወከ ይገኛል።  

በትምህርቱ የተዘፈቁበት እግዚአብሔርን ሳይፈሩና ሰውንም ሳያፍሩ የስሕተት ትምህርቱን ከጥግ እስከ ጥግ ሲያኼዱት፣ እንደ ጠበል የተረጩ የመሰሉት ደግሞ ፈራ ተባ እያሉና የሰውን ስሜት እየተከተሉ በጥቂት በጥቂቱ ብልጠት በተሞላበት አቀራረብ ይህን የስሕተት ትምህርት እያሠራጩና ብዙዎችን እያሳቱ ይገኛሉ። በተለይም የኹለተኛዎቹ ክፍሎች አካኼድ አደገኛና ብዙ ጥፋት የሚያደርስ በመኾኑ፣ ወገኖች ኹሉ ሊነቁና የዕቅበተ እምነትን ሥራ በማጠናከር የስሕተት ትምህርቱን በእግዚአብሔር ቃል እውነት ሊያፈርሱት ይገባል።

የትምህርቱን አደገኛነት ለማሳየት በስሕተት ትምህርቱ እስከ ዐንገታቸው የተዘፈቁበቱ በግልጽ የሚያውጁትንና ጅምሮቹ በስልታዊነት ቀስ በቀስ ሊገልጹት በይደር ያቈዩትን የስሕተቱን አንዱን ጥግ በማሳየት መጀመሩ መልካም መስሎ ታይቶናል። ምክንያቱም ሰዉ ቀስ በቀስ እየተወሰደበት ያለው የእምነት እንቅስቃሴ ትምህርት መዳረሻው የት እንደ ኾነ እንዲገነዘብ ዕድል ይፈጥርለታል ብለን እናምናለን። በቀጣይ ጊዜ ግን በርእሰ ጉዳዩ ላይ በተከታታይ እንደምንጽፍ ተስፋ እናደርጋለን።  

ክሕደቱ ሲገለጥ
አብዛኛዎቹ “የእምነት እንቅስቃሴ ፈጣሪዎች” የጌታ ኢየሱስን (ሎቱ ስብሐት) “መሰይጠን” የሚገልጹበት ትምህርት ተጠቃሎ ሲቀርብ ይህን ይመስላል፦ “… ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ የኾነው ማንነታችንን ሊያድን በመንፈሱ የሰይጣንን ባሕርይ ተካፈለ፤ ሰየጠነም፤ ሊያድነንም በመንፈሱ ሞተ፤” ሲያብራሩትም፣ “ሥጋዊ ሞት ኀጢአትን ማስወገድ አይችልም፤ ስለዚህ ኢየሱስ መንፈሳዊ ሞትን ስለ ኹሉ ሲል በደስታ ቀመሰ፤ …” ይላሉ። ይህንም ለሰይጣን ቤዛ ከፍሎ እኛን ከእርሱ እጅ እንደ ዋጀን አድርገው ነው የሚያቀርቡት።

መጽሐፍ ቅዱስን አማኞች ብቻ ሳይኾኑ መናፍቃንም ለኑፋቄያቸው ድጋፍ እንዲኾናቸው በተጻፈበት ዐውድ መሠረት ሳይኾን ለእነርሱ እንዲስማማቸው አድርገው ይጠቅሱታል። ከላይ ለተጠቀሰው የስሕተት ትምህርታቸው የእምነት እንቅስቃሴ ሰዎች ከሚጠቅሷቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ፦
1.      “ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም፦ አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ? ማለት ነው” (ማቴ. 27፥46)።
በእምነት እንቅስቃሴ መምህራን ዘንድ (ሎቱ ስብሐት) “ስለ ኢየሱስ መሰይጠን” ከሚቀርቡት ጥቅሶች አንዱ ይህ ሲኾን፣ “ኢየሱስ በመንፈሱ የሰይጣንን የኀጢአት ባሕርይ ተቀብሎ በሞተ ጊዜ” የተናገረው ቃል ነው ብለው ያምናሉ። ሌሎችም ይህን ቃል ለራሳቸው እንዲመች አድርገው ተርጕመውታል። ክርስቶስ በእግዚአብሔር ላይ አልተማመነም፤ በአብ ፈጽሞ መጣሉን ያመለክታል በማለት የተረጐሙትም አሉ።

ይህ ጥቅስ ከሰባቱ አጽርሐ መስቀል (ጌታ በመስቀል ላይ ኾኖ ከተናገራቸው ቃላት) አንዱ ነው። ቃሉን አስቀድሞ የተናገረው መዝሙረኛው ዳዊት ነው፤ በመዝ. 22፥1 ባቀረበው ጩኸቱ አምላኩ ለምን ዝም እንዳለው፣ ሊያድነውም እንዳልወደደ፣ ይህም መተዉንና የእግዚአብሔርን ዝምታ መቋቋም አለመቻሉን የሚያሳይ የዳዊት “የምልጃ ጸሎት” ነው። በእርግጥም ምንም መጠጊያ ታዛ ማጣቱ፣ መተዉና መረሳቱ የሥቃዩ ክፍሎች ኾነው መጠቀሳቸውን እናያለን። በኋላ ግን እግዚአብሔር የችግረኛውን ችግር እንዳልናቀና ፊቱንም ከእርሱ እንዳልሰወረ በማወጅ ለምስጋና ይነሣል፤ ሌሎችንም ይጋብዛል (ቍጥር 23-24)።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ “አምላኬ አምላኬ ስለ ምን ተውኸኝ?” ያለውም፣ በመስቀል ላይ ኀጢአታችንን በመሸከሙ፣ የኀጢአት ደመወዝ ሞት በመኾኑና በኀጢአት ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ በመምጣቱ እንደ ኾነ ከቃሉ ምስጢር መረዳት ይቻላል። በነቢዩ በኢሳይያስ የተነገረው ትንቢትም ለዚህ ምስክር ነው። “በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፥ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ፥ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ፥ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ኹላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የኹላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ።” (ኢሳ. 53፥4-6)። አስቀድሞም በአይሁድ እጅ ለመያዝ ጥቂት ሲቀረው በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ የሞት ጽዋው ከእርሱ እንዲያልፍ፣ ነገር ግን የእርሱ ፈቃድ ለአባቱ ፈቃድ እንዲገዛ ያቀረበው ጸሎትም ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደ ኾነ ማስተዋል አይከብድም።

ሰውን የማዳን ተግባር የተፈጸመው በእግዚአብሔር ሐሳብና ዕቅድ መሠረት ነው። አብ ዓለምን ወድዶ አንድያ ልጁን በመስጠት ፍቅሩን ሲያሳይና ወልድ ደግሞ በመታዘዝ የሰው ልጆችን ድኅነት ሲፈጽም፣ በመካከላቸው ምንም መለያየት አልነበረም። በእርግጥ፦ “አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ?” የሚለው የመድኀኒታችን የኢየሱስ ንግግር በመከራው ሰዓት በአብ መተዉን ያሳያል። መተዉም መከራ መስቀልን በመቀበል እስኪሞት ድረስ በመስቀል ላይ ሳለ የኾነ ትእምርታዊ እንጂ፣ በመንፈሱ (ሎቱ ስብሐት) የሰይጣንን የኀጢአት ባሕርይ መቀበል አይደለም። በመስቀል ላይ መተዉም በአብና በወልድ መካከል ያለውን ዘላለማዊ ፍቅር ፈጽሞ አልለወጠውም፤ በባሕርዩ እግዚአብሔር አይለወጥምና። ጌታችን ይህን ቃል ከተናገረ በኋላ በመቀጠል፦ “አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ ዐደራ እሰጣለሁ። ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ፤” (ሉቃ. 23፥46)። ከወንበዴዎቹ ለአንዱ የሰጠውም ተስፋ፦ “እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኾናለህ” (ሉቃ. 23፥43) የሚል ነው። እነዚህም የሚያሳዩን አብና ወልድ ባልተለወጠ ፍቅር መኖራቸውን ነው።

“አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ?” የሚለው ቃል ወደ መሰይጠን ይመራል ለማለት የሚያበቃ አንድም ፍንጭም ኾነ ምክንያት የማናገኝበት ከመኾኑም በላይ፣ በእኛ ላይ ያለውን የእግዚአብሔርን ዐላማ ፈጽሞ አለማስተዋልም ነው። በመስቀል ላይ የኾነውን ነገር ኹሉ ክርስቶስ አስቀድሞ ያውቃል። መዳናችንን የፈጸመውም ያለአንዳች እንከንና አባቱን ደስ በሚያሰኝ መንገድ ብቻ ነው። ክርስቶስ እኛን ለማዳን በመስቀል ላይ በፈጸመው ኹሉ፣ ኀጢአት ተገቢውን ቅጣት ያገኘ ሲኾን፣ እግዚአብሔርም ሰውን መውደዱንና ምሕረቱን አሳይቷል። ታዲያ መዳናችን እርሱ ራሱ ነውር የሌለበት ኾኖ ኀጢአታችንን በመሸከም በቅድስና በመቅረቡና እግዚአብሔርን በሚያረካ መሥዋዕታዊ ሞት በመፈጸሙ ነው ካልን፣ ያለአንዳች ማስረጃ ክርስቶስን (ሎቱ ስብሐት) ሰይጥኗል ማለት ፍጹም ክሕደት አይኾንምን? 

2.   “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኀጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኀጢአት አደረገው፤” (2ቆሮ. 5፥21)
ይህ ጥቅስ በግልጽ የሚናገረው ክርስቶስ ኀጢአት የሌለበት ንጹሐ ባሕርይ ኾኖ ሳለ፣ የሰው ኀጢአት በክርስቶስ ላይ መቈጠሩንና ከዚህ የተነሣ በኀጢአተኛው ሰው ፈንታ የሕግን ቅጣት መሸከሙን ነው እንጂ እርሱ ወደ ኀጢአትነት ወይም ወደ ሰይጣንነት መቀየሩን አያስረዳም። “የብልጽግና ወንጌል” የተሰኘው መጽሐፍ ላይ እንደ ተጠቀሰው ኮሊን ክሩዝ የተባሉ ሰው፣ በዚህ ጥቅስ ላይ ለመደገፍ የሚሞክረውን ይህን የስሕተት ትምህርት ማስረጃ አልቦነት ከገለጹ በኋላ፦ “ክርስቶስ የኀጢአት መሥዋዕት ኾኖ ነበር” እና ክርስቶስ የኀጢአታችንን ውጤቶች እንዲሸከም ተደርጎ ነበር” የሚሉ ፍቺዎችን ከሌሎች የክርስቶስን መሥዋዕታዊ ሞት ከሚያመለክቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር ለምሳሌ ከሮሜ 3፥25 እና 1ቆሮ. 5፥7 ጋር በማዛመድ ዐትተዋል። በተለይም በዘሌ. 4፥24 ይኸው ቃል “የኀጢአት መሥዋዕት” የሚል ፍቺ ይዞ የሚገኝና የእንስሳት መሥዋዕትነት ተምሳሌት (Symbolism) መኾኑን እንደሚያመለክት በማስረዳት፣ የክርስቶስም ሞት “እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኀጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በኀጢአትም ምክንያት ልኮ” ያደረገው መኾኑን በንጽጽር አመልክተዋል።

መጽሐፉ አክሎም፦ “በብሉይ ኪዳን ኀጢአት የሠራ ሰው ነውር በሌለበት እንስሳ ላይ እጁን ይጭንና ኀጢአቱ ወደ እንስሳው ይተላለፋል። ይህ ማለት ግን እንስሳው በቀጥታ ኀጢአተኛ ኾነ ማለት አይደለም። እንዲያውም ከዚያ የበላ ሰው ኹሉ ቅዱስ ይኾን ነበር (ዘሌ. 6፥25-27፡29)።” ይህም የሚያሳየው የሰውዬው ኀጢአት ወደ እንስሳው እንዲተላለፍ የሚደረገው በተምሳሌት መኾኑን ነው። የክርስቶስም ስለ እኛ ኀጢአት መኾን እንዲሁ ተምሳሌታዊ ነው እንጂ እርሱ ወደ ኀጢአትነት ተለወጠ የሚያሰኝ ፈጽሞ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስም እግዚአብሔር የኹላችንን በደል በእርሱ ላይ እንዳኖረ፣ እርሱም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኀጢአታችንን በዕንጨት ላይ እንደ ተሸከመ ነው የሚናገረው (ኢሳ. 53፥6፤ 1ጴጥ. 2፥24)። ለዚህም ነው ክርስቶስ ራሱን ያለ ነውር ለእግዚአብሔር አቀረበ ማለት የሚቻለው (ዕብ. 9፥14)። እርሱ ኀጢአት ኾኖ ቢኾን ኖሮ ግን እንደሌላው መሥዋዕት ተቀባይነት ባላገኘም ነበር።

ከጥንት የቤተ ክርስቲያን አባቶች አንዱ የኾነው ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት፥ ጌታ እኛን ለማዳን መከራን የተቀበለው በሥጋውና በነፍሱ መኾኑን ቅዱሳት መጻሕፍትን አብነት አድርጎ ገልጿል እንዲህ በማለት፦ “እርሱ እንደ ዐዘነ፥ እንደ ተከዘ በማርቆስ ወንጌል ተጽፏል፤ ሐዘን ትካዝ የነፍስ ሕማም ነው፤ መራብ፥ መጠማት፥ ጐዳና በመኼድ መድከም  በሐሰት ይደለ በእውነት የተቀበላቸው የቀሩት ሕማማት የሥጋ እንደ ኾኑ እንዲታወቅ የነፍስን ሕማም እንዲህ እናምናለን።” (ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 61 ቍጥር 11 ገጽ 197)። ከዚህ ውጪ በመንፈሱ ሞተ ተብሎ ስለ እርሱ አልተነገረም።  

“እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኀጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኀጢአት አደረገው” በሚለው አረፍተ ነገር ውስጥ ኹለት ተቃራኒ ክሥተቶችን እናገኛለን። የመጀመሪያው እኛ የእግዚአብሔር ጽድቅ መኾናችን ሲኾን፣ ኹለተኛው ደግሞ ክርስቶስ ስለ እኛ ኀጢአት መኾኑ ነው። እኛ ኀጢአተኞቹ በእርሱ (በክርስቶስ) የእግዚአብሔር ጽድቅ የኾንነው እግዚአብሔር የእኛን ኀጢአት በክርስቶስ ላይ አኑሮ እርሱን በእኛ ምትክ ሞታችንን እንዲሞትና የኀጢአታችንን ዕዳ እንዲከፍል በማድረጉ ነው። በዚህ አስደናቂ ልውውጥ ኀጢአትን በክርስቶስ በመቅጣቱ እግዚአብሔር ጻድቅነቱን ሲያሳይ፣ እኛን በክርስቶስ ሞት በማጽደቁ ደግሞ ፍቅሩን ገልጧል። ስለዚህ እነዚህን በተቃራኒ መንገድ የተገለጹትን ኹለት ክሥተቶች ነጣጥሎ ማየት አይቻልም። እኛ የእግዚአብሔር ጽድቅ የኾንነው በጸጋ እንደ ኾነ ኹሉ፣ ክርስቶስም ኀጢአት የኾነው በተምሳሌት ኀጢአታችንን ተሸክሞ በመሞት እንጂ ወደ ኀጢአትነት በመለወጥ ፈጽሞ አይደለም። ምን ጊዜም ክርስቶስ እኛን ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን ስለ ዐመፀኞች አንድ ጊዜ በኀጢአት ምክንያት ሞተው እርሱ ጻድቅ ኾኖ  ነው የሚለውን እውነት መዘንጋት የለብንም (1ጴጥ. 3፥18)።    

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የእምነት እንቅስቃሴ አራማጆች ሌላው የሚጠቅሱት ጥቅስ፣ “በዕንጨት የሚሰቀል ኹሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ ርግማን ዋጀን፤” (ገላ. 3፥13) የሚለውን ነው። በብሉይ ኪዳን ለሞት የሚያበቃ ኀጢአት የሠራ ሰው ሞት ቢፈረድበትና በዕንጨት ላይ ቢሰቀል በእግዚአብሔር ፊት የተረገመ ነው (ዘዳግ. 21፥22)። ሐዋርያው ይህን ቃል ጠቅሶ የክርስቶስን ሞት እኛን ከእርግማን ለመዋጀት ስለ እኛ እርግማን የኾነበት ሞት መኾኑን ተናግሯል። ይህ የኾነበትን ምክንያት ሲያስረዳም፦ “የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ” ነው ይላል። ይህም እርግማን ተምሳሌታዊ እንጂ እርሱ ወደ እርግማንነት ተለውጧል የሚል ትርጕም የለውም። እንዲያማ ቢኾን፣ ስለ እኛ እርግማን መኾኑ የአብርሃም በረከት በእርሱ በኩል ወደ አሕዛብ እንዲደርስ ባላደረገም ነበር።

3.  “እግዚአብሔርንም የመምሰል ምስጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥  ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ።” (1ጢሞ. 3፥16)።

ይህ ጥቅስ በግጥም መልክ የሰፈረ ሲኾን፣ የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን መዝሙር እንደ ኾነ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል። የእምነት እንቅስቃሴ አማኞች ከዚህ በግጥም መልክ ከቀረበው መልእክት ውስጥ ለስሕተት ትምህርታቸው ይደግፈናል መስሏቸው በማስረጃነት የሚጠቅሱት “በመንፈስ የጸደቀ” የሚለውን ስንኝ ነው። “በመንፈስ የጸደቀ” ከተባለ፦ “አንድ ነገር መጀመሪያ ርኩስ ካልኾነ በቀር በመንፈሱ ጻድቅ እንደማይኾን ግልጽ ነው።” ስለዚህ ክርስቶስ በመንፈስ “የሰየጠነበት” ጊዜ አለ በማለት ይተረጕማሉ። ነገር ግን እንዲህ ያለ አተረጓጐም ዐውዳዊ አለመኾኑን ማስተዋል ብዙም አዳጋች ስላልኾነ አንቀበለውም።

ቅዱስ ጳውሎስ ሥጋ ስለ ኾነው አምላክ ወይም ስለ ነገረ ትሥጉት ታላቅ ምስጢርነት አጕልቶ ይነግረናል። የእርሱ ሰው መኾንና እኛን ማዳን የቅድስናና የመንፈሳዊ ነገር ኹሉ መሠረት ነው። በመንፈስ የጸደቀ የሚለው ቃል ከተሠግዎቱ ጋር በመያያዝ የተነገረ ቃል ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከተሠግዎቱ ጋር በተገናኘ በተደጋጋሚ በአንድነት ተጠቅሰዋል። ጌታችን ኢየሱስ በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን አወጣ (ማቴ. 12፥28)። ለድኾች ወንጌልን እንዲሰብክ፣ ለታሰሩትም መፈታትን፣ ለዕውሮችም ማየትን ይሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ ያወጣ ዘንድ፣ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት ይሰብክ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቷል (ሉቃ. 4፥17-19)። ከሙታን መካከልም ያስነሣውና (ሐ.ሥ. 2፥32፤ ሮሜ 1፥4) አገልግሎቱን ያጸደቀውና ያረጋገጠው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው። ራሱ ጌታችን ኢየሱስም ወደ ሰማያት በኼደ ጊዜና መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ ክርስቶስ የተናገረውን ያንኑ ትምህርት ለደቀ መዛሙርቱ በማስተማርና በማስታወስ የእርሱን ሥራዎች ኹሉ እንደሚያጸና፤ እንደሚያረጋግጥ ተናገሯል (ዮሐ. 14፥25-27፤ 16፥13-15)። ዐውዱ የሚነግረንና የሚያስተምረን ይህን እንጂ፣ ኢየሱስ በሥጋው እንደ ሞተ ኹሉ በመንፈሱም ሞቷል፤ ወይም ሰይጥኗል የሚለውን አይደለም።

4. “ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዐመፀኞች አንድ ጊዜ በኀጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥ በእርሱም ደግሞ ኼዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤” (1ጴጥ. 3፥18-19)።
ይህ ጥቅስ በውስጡ ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሣና በበርካታ ምሁራን ብዙ መላምቶች የተሰነዘሩበት መኾኑን በቅድሚያ መግለጽ ያስፈልጋል። በመንፈስ ወደ ወኅኒ ኼዶ በዚያ ለነበሩት ነፍሳት ሰበከላቸው በሚለው ዐረፍተ ነገር ውስጥ መገለጽ ያለባቸው ብዙ ጉዳዮች ቢኖሩም፣ በዚህ ጽሑፍ ዋናው ትኵረታችን የምናደርገው ጌታ በመንፈስ ወደዚያ የኼደው ለምንድነው የሚለውን፣ የእምነት እንቅስቃሴ አራማጆች ጌታ ወደዚያ በመንፈሱ የኼደው በሰይጣን እጅ መከራን ለመቀበልና በሲኦል ለመሰይጠን ወይም “የሰይጣንን ባሕርይ ወርሶ ዳግም ለመወለድ” ነው በሚሉት ነጥብ ላይ ይኾናል።

መቼም ይህ የጴጥሮስ መልእክት ጌታ ወደ ወኅኒ በመንፈስ የኼደው፣ እነርሱ የሚሉትን ተግባር ለመፈጸም እንደ ኾነ ምንም የሚሰጠን ፍንጭ የለም። ክርስቶስ በመንፈስም ሞቶ ቢኾን ኖሮ፣ እንደ ሥጋው ሞት በግልጽ፣ በጕልሕና በተደጋጋሚ “በመንፈስ መሞቱ” በተጻፈ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን ግን ክርስቶስ በሥጋ እንደ ሞተና በሥጋ መሞቱም እኛን ለማዳን በቂ እንደ ኾነ ነው (ሮሜ 8፥3-4፤ ቈላ. 1፥21-22፤ 1ጴጥ. 2፥24፤ 3፥18፤ 4፥1-2)። ከእነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳውያን ማስረጃዎች መካከል እንኳ ጴጥሮስ ደጋግሞ የተናገረው ክርስቶስ በሥጋ መከራ መቀበሉንና በከበረ ደሙ የዋጀን መኾኑን እንጂ በመንፈስ መሞቱን ጭምር አይደለም። በዚህም እነርሱ በመንፈሱ ካልሞተ በቀር በሥጋ መሞቱና ደሙን ማፍሰሱ ብቻውን ለስርየት በቂ አይደለም የሚሉትን ክፉ ጥፉ ትምህርታቸውን ያፈርስባቸዋል።   

“ክርስቶስ በመንፈስ የሞተውን ሰው ለማጽደቅ፥ በሥጋ ብቻ ሳይኾን በመንፈስም መሞት ነበረበት፤ ማለትም ኹለት ጊዜ መሞት ነበረበት ቢባል እንኳ፥ ክርስቶስ ወደ ሲኦል መውረድ አለበት ወደሚል ድምዳሜ ሊወስደን አይገባም። ክርስቶስ ነፍሱን አሳልፎ ሊሰጥ በተቃረበ ጊዜ ‘አምላኬ አምላኬ ስለ ምን ተውኸኝ?’ ሲል እንደ ተጣራ ትዝ ይለናል። ይህም ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ተለይቶ እንደ ነበር ያመለክታል፤ ሞት ማለት ደግሞ ከእግዚአብሔር መለየት በመኾኑ [በመንፈሱ አልሞተም እንጂ] በመንፈሱ ሞቶ ነበር ቢባል እንኳ፥ ይኸው ክንውን በቂ እንደ ኾነ እንገነዘባለን። በሥጋ የሞተውና ከእግዚአብሔር ለዐጭር ጊዜ የተለየው እዚያው መስቀል ላይ እንጂ ሲኦል በመውረድ አይደለም።” (የብልጽግና ወንጌል ገጽ 44)።

ሌላው በቃሉ በትር መመታት ያለበት አጋንንታዊ ሐሳብ እግዚአብሔር እኛን ነጻ ለማውጣት ለሰይጣን ቤዛ ሰጥቷል የሚለው የእምነት እንቅስቃሴ አራማጆች የስሕተት ትምህርት ነው። እውን ኢየሱስ ቤዛ ኾኖ የተሰጠው ለሰይጣን ነው? በፍጹም!!! ይህ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ የተገኘ ትምህርት ሳይኾን ከውጪ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ በመሞከር የተፈበረከ ኑፋቄ ነው።

በቅድሚያ ሰይጣን ቤዛ ለመቀበል ምን ሕጋዊ መብት አለው? የሚለውን መመልከት አለብን። እንደሚታወቀው እግዚአብሔር ምድርን እንዲገዛ ሥልጣን የሰጠው ለሰው ነው። ይኹን እንጂ ሰው በሰይጣን ምክር ተታልሎ ትእዛዘ እግዚአብሔርን ሲያፈርስ እንዲገዛው የተሰጠውን ዓለም ይዞ በሰይጣን ሥር ወደቀ። ሰይጣንም ሠልጥኖበት የዚህ ዓለም ገዥ ተብሎ ተጠራበት፤ ቢኾንም በክርስቶስ ላይ አንዳች የለውም (ዮሐ. 12፥31፤ 14፥30፤ 16፥11፤ 2ቆሮ. 4፥4)። ይህ በማታለል የወሰደውና የተጠራበት እንጂ በሕጋዊ መንገድ ያገኘው መብቱ አይደለም። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን በያዘው ዘላለማዊ ዕቅድ ውስጥ፣ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ቤዛ የመቀበል መብት አልነበረውም፤ እግዚአብሔርም ለሰይጣን ቤዛ የመስጠት ግዴታ አልነበረበትም። እኛን ከጨለማው መንግሥት ሲያድነንም ጻድቅ ባሕርዩ የሚጠይቀውን ለማሟላት ነው እንጂ ለሰይጣን ዎጆ አልከፈለም። ይኸውም አስቀድሞ ሰውን፦ “… መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ” ብሎት ነበርና ስለ በላ ሰው መሞት አለበት። በፍቅሩ ሊያድነው ሲፈልግ ግን ሞትን ይሞት ዘንድ የተናገረውን ቃል ሳያጓድል መኾን ነበረበት። በእግዚአብሔር ፍቅር የታሰበው ሰው ግን እግዚአብሔር በጻድቅነቱ የሚጠይቀውን የሞት ፍርድ ከመቀበል ውጪ ለመዳን የሚሰጠው ቤዛ አልነበረውምና ቤዛ ይኾነው ዘንድ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ሰጠለት። በዚህም በእግዚአብሔር ጻድቅነት ላይ ምንም ጥያቄ ሳይነሣ ሰውን ከሞት የሚያድንበት ፍቅሩ ተገለጠ። “ምሕረትና እውነት ተገናኙ፤ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ።” ይሏል ይህ ነው (መዝ. 84/85፥10)። 

መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ስለ ብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት እንደ መጣ የተነገረው ኹሉ ከዚህ ጋር የተገናኘ ነው (ማቴ. 20፥28፤ ማር. 10፥45፤ 1ጢሞ. 2፥6)። ስለ ሕዝቡ ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበውም ለእግዚአብሔር እንደ ኾነ ግልጽ ነው (ኤፌ. 5፥2፤ ዕብ. 9፥14)። ቤዛ የሚሰጠው ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰይጣን  እንዳልኾነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይመሰክራል። በጥላው አገልግሎት ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ የማስተስረያ ስጦታ ይሰጥ የነበረው ለእግዚአብሔር ነው (ዘፀ. 30፥12)። “ወንድም ወንድሙን አያድንም፥ ሰውም አያድንም፤ ቤዛውን ለእግዚአብሔር አይሰጥም፥” ተብሎም ተጽፏል። (መዝ. 48/49፥7፤ እንዲሁም ኢዮ. 33፥24ን ይመለከቷል)። 

ታዲያ ከሰይጣን እጅ ያዳነን እንዴት ነው? በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን እርሱን በሞቱ በመሻር ነው (ዕብ. 2፥14፡15)። “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል፤ አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው።” (ቈላ. 2፥14-15) ይላል። መቼም ቤዛ ሰጥቶ ማስለቀቅና ቤዛ ተቀብሏል ያሉትን እርሱን (ዲያብሎስን) መሻር ፍጹም የተለያዩ ነገሮች ናቸው።

የዚህ ትምህርት አደገኛነት ክርስቶስን (ሎቱ ስብሐት) “ሰይጥኗል” ማለት ብቻ ሳይኾን የእኛ ስርየት የተከናወነው በሥጋ በመሞቱና በደሙ መፍሰስ አይደለም የሚል መኾኑም ጭምር ነው። ለመኾኑ ሳይጻፍ በራሳቸው መንገድ ለክርስቶስ ሊያላብሱት የፈለጉት የሰይጣን ባሕርይ ምን ይኾን?    

የሰይጣን ባሕርይ ምንድር ነው?
የሰይጣን ባሕርይ መብራራት ሳያስፈልገው “ለብዙዎች” የተገለጠ ነው፤ የመገለጡን ያኽል ግን በቅድስና ለመኖር ፈጽመን አልጨከንንም። ሰይጣን ኹል ጊዜ የእግዚአብሔርን የቅድስና ባሕርይ የሚቃረንና የሚጻረር፣ የመልካም ነገር ኹሉ ጠላት (ማቴ. 25፥41) ነው። ይህን መሠረት በማድረግም ስሙ አብዶን [ዐጥፊ] (ራእ. 9፥11)፣ ዲያብሎስ [ከሳሽ (የወንድሞች)] (ራእ. 12፥10)፣ ተንኰለኛ (2ቆሮ. 11፥3)፣ ባላጋራ (1ጴጥ. 5፥8)፣ የወደቀው እባብ ወይም ዘንዶ (ራእ. 12፥9)፣ ሰይጣን [አሳች ወይም አሰናካይ]፣ የክፋት አባት (ዮሐ. 8፥44)፣ ፈታኝ (1ተሰ. 3፥5)፣ የኀጢአት አመንጪ … ተብሎ ተጠርቷል።

ከመጀመሪያው ኀጢአትን ከራሱ ያመነጨው እርሱ ነው። እግዚአብሔርን በመዳፈር በትዕቢቱ እጅግ አበጠ፤ (1ጢሞ. 3፥6)። እርሱና ተከታዮቹ ኀጢአትን ሠርተው ወደ ጥልቁ ወደቁ (2ጴጥ. 2፥4)፤ በፍጻሜውም የዘላለም ፍርድ ተጠብቆላቸዋል (ማቴ. 12፥29፤ ራእ. 20፥10)። የጽድቅ ኹሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም የማያርፍ (ሐዋ. 13፥10)፤ ከእግዚአብሔርም ኾነ ከቅዱስ ቃሉ ጋር አንዳችም ትስስርና ዝምድና የሌለው በኹለንተናው ክፋትን የተመላ ነው። ጌታችን ኢየሱስ በምድር በነበረው አገልግሎቱ በማናቸውም መንገድ የሰይጣንን ምስክርነትም ኾነ፣ ማናቸውንም ነገር ሲቃወም እንጂ ሲቀበል አናይም። በግልጽ ቃልም፣ “ሂድ፥ አንተ ሰይጣን … ” (ማቴ. 4፥10) በማለት አሳድዶታል። ደግሞም ሥራውን ሊያፈርስ የመጣ መኾኑ ተነግሮለታል (1ዮሐ. 3፥9)። ክርስቶስ የሰይጣን ምስክርነት እውነት ቢኾንም እንኳ ፈጽሞ አልተቀበለውም (ሉቃ. 4፥34)። ደቀ መዛሙርትም ይህን የጌታን መንገድ ተከትለዋል (ሐዋ. 16፥16-18)።

እንግዲህ ለእግዚአብሔር መንግሥት ፍጹም ተቃራኒና የእግዚአብሔርም ኾነ የሰው ልጆች ኹሉ ጠላት፣ ይህን የሰይጣንን ባሕርይ ክርስቶስ ተካፍሎአልን? ከሰይጣን ጋር እንዴት ይኾን የተዛመደውና የእርሱን አካል የነሣው?! … የእምነት እንቅስቃሴ አራማጆች ክርስቶስን እንዴት ቢጠሉት ይኾን ይህን ባሕርይ ተካፍሏል የሚሉት?!

ክርስቶስ በሥጋ ብቻ ስለ መሞቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነቶች
          “ክርስቶስ ሰይጥኗል” የሚለው ትምህርት መሠረቱ፣ “ሰው መንፈስ ነው” የሚለው ነው። የእንቅስቃሴው መምህራን የሰውን መንፈስነት እንድንረዳ በብዙ መንገድ ሊያሳምኑን የሚጥሩት፣ ክሕደታቸውን እዚህ ጫፍ ላይ በማድረስ፣ “መንፈሳችንን ሊያድን ክርስቶስ በመንፈሳዊው ዓለም ሰየጠነ” የሚለውን ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርታቸውን ሊግቱን በመሞከር ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ግን እግዚአብሔር ወልድ ገና ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ቤዛ ኾኖ ሊሰጥለት የመጣለትን የሰውን (የአብርሃምን) ዘር እንጂ የመላእክትን ዘር እንዳልያዘ ይመሰክራል። በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን ዲያብሎስን ለመሻርና በሕይወታቸው ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን በሙሉ ነጻ ለማውጣት በሥጋና በደም መካፈል ብቻ በቂ መኾኑንም ያስረዳል። “ስለዚህ የሕዝብን ኀጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በኾነው ነገር ኹሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲኾን፥ በነገር ኹሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው።” (ዕብ. 2፥14-17) ይላል እንጂ ከዚህ ውጪ የሚያስፈልግ የመንፈስ ሞት ኖሮ ወደ ሰይጣንነት ተለወጠ ፈጽሞ አይልም። ቀጥሎ የሰፈሩት ምስክርነቶችም ይህን ያስረዳሉ፦

·        “ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ፤” (1ጴጥ.1፥18)፣ “ለኀጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኀጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቍስል ተፈወሳችሁ” (1ጴጥ. 2፥24)፤ ቅዱስ ጴጥሮስ በጻፈው መልእክቱ ኹለቱም ምንባባት ላይ፣  “በክቡር የክርስቶስ ደም” እና “እርሱ [ክርስቶስ] ራሱ በሥጋው ኀጢአታችንን በዕንጨት ላይ ተሸከመ” የሚሉት ክርስቶስ በፍጹም ሰውነቱ መሞቱንና ሰውነቱም [ደሙም] ቅዱስ መኾኑን ያስረዳል።

·        “በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን፥ እርሱም የበደላችን ስርየት።” ፣ “እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ኹለቱን ያዋሐደ በዐዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከኹለታቸው አንድን ዐዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ...” (ኤፌ. 1፥7፤ 2፥14)፤ “በመረቀልን በዐዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል ...” ፣ “ ... በገዛ ደሙ ሕዝቡን እንዲቀድስ”፣ “በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ የኾነውን ጌታችንን ኢየሱስ ...” (ዕብ. 10፥19 ፤ 13፥12፡20) በደሙ፣ በሥጋው፣ በኪዳን ደም የሚሉት ቃላት እርሱ በሥጋ ቤዛችን መኾኑንና ያዳነውም በሥጋው በኩል ባደረገው ሞቱ መኾኑን ያመለክታል።

·        “የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ኹሉ ከእግዚአብሔር ነው፥ ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ኹሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አኹንም እንኳ በዓለም አለ፤” (1ዮሐ.4፥2-3) ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በዘመኑ አምላክን በምንታዌነት ለሚያምኑ፣ ሥጋን በማንኳሰስና በመጥላት ያስተምሩ ለነበሩ ቀደምት መናፍቃን የክርስቶስን በሥጋ መምጣት በግልጽ ይቃወሙ ነበርና፣ እንዲህ ያሉት ከእግዚአብሔር አለመኾናቸውን በድፍረት ይናገራል።

የሕይወት ቃል ክርስቶስ ከመጀመሪያው [ከጥንት] የነበረ አምላክ ነው፤ ደግሞም ሰው ኾኖ በመጣ ጊዜ ሐዋርያቱ ሰምተውታል፣ በዐይኖቻቸውም አይተውታል፤ ያዩትን የተመለከቱትንም እጆቻቸውም የዳሰሱትን መስክረዋል (ዮሐ. 20፥20፡27፤ 1ዮሐ. 1፥1)። ሰው በመኾኑ ሥጋና ደምን ገንዘብ በማድረጉ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ ነው እንጂ መሰይጠኑን ያስተማረን አንድም ሐዋርያ የለም። ደግሞም ክርስቶስ በሥጋው ብቻ መሞቱን ካመንን በመንፈሱ ስለ መሞቱና ስለ መሰይጠኑ ያልተጻፈውን ለማውራት ዐቅምና ጕልበት አይኖረንም። በመንፈስ ሞቷል ለማለት ከላይ የሚጠቅሷቸው ጥቅሶች የእምነት እንቅስቃሴ አራማጆችን የተሳሳተ ሐሳብ ፈጽሞ እንደማይደግፉ ግልጽ ነው።

ማጠቃለያ
     በሥጋ የሞተልንና በቅድስና ያዳነን ጌታችን ኢየሱስ የኀጢአትን ኀይል፣ ሲኦልንና ዲያብሎስን በሕይወቱና በሥጋ በኾነው መሥዋዕታዊ ሞቱ ድል ነሥቷቸዋል፤ አሸንፏቸውማል። በዘመን ፍጻሜም በዲያብሎስ ላይ እንደሚፈርድበት በግልጽ ተጽፏል (ዮሐ. 12፥31 ፤ ቈላ. 2፥15 ፤ 1ዮሐ. 3፥8)። ስለዚህ በማናቸውም መንገድ የሰይጣንን ባሕርይ አልተካፈለም (አልሰየጠነም)። “ጌታችን ኢየሱስ ኀጢአትን አልሠራም፣ ዝንባሌውም የለውም፤ ኀጢአትን መሥራትም አይቻለውም” የምንለው፣ በሰይጣን ቢፈተንም እንኳ ኹሉንም ፈተናዎቹን ድል መንሣቱን ጭምር በማንሣት እንከን አልባ ጻድቅ መኾኑን በመመስከር ጭምር ነው።

በመንፈሱ አልሞተም ስንል፣ ባሕርዩን አይለውጥም ማለታችንም ነው። ሞትን ገንዘቡ ያደረገው በፍጹም ሰውነቱ፤ በሥጋው ብቻ ነው። ፍጹም ሰውነቱ እንከን አልባ ነውና፣ ሊያድነን ብቃት አለው! እንዲህ ያለውን ትምህርት የማያስተምርና ክርስቶስን ከሰይጣን ጋር የሚያዛምድ የትኛውም ትምህርት አጋንንታዊና ክርስቶስን የማያከብር ነው። እንዲህ ያለውን ትምህርት የሚያመጣ ኹሉ ጽኑ መርገም አለበት፤ እንዲህ የሚል፦ “ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይኹን፤” (1ቆሮ. 16፥22)።

ዋቢ መጻሕፍት
ኢኦተቤ። የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ንባብና ትርጓሜ - የኢትዮጵያ ሊቃውንት እንደ ተረጐሙት። ዐዲስ አበባ፦ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅት፣ 1988።
ኮሊን ማንሰል (ቄስ)። ትምህርት ክርስቶስ 2ኛ ዕትም። ዐዲስ አበባ፦ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፣  1999 ዓ.ም.።
የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር። የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት - 9ኛ ዕትም። ዐዲስ አበባ፦ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፣ 2002 ዓ.ም.።
ግርማዊ። የብልጽግና ወንጌል - “የዘመኑ የእምነት እንቅስቃሴ መሠረቶችና መዘዞች”። ዐዲስ አበባ፦ኤስ.አይ.ኤም ፕሬስ፣ 2008 ዓ.ም.።

No comments:

Post a Comment