“የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም!” (ዮሐ. 2፥3)
ይህን ቃል የተናገረችው የጌታ እናት
ቅድስት ማርያም ናት። የተናገረችውም በቃና ዘገሊላ ሰርግ ቤት እርስዋ፣ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ ታድመው ባሉበት፣
ለሰርጉ የተዘጋጀው የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜ ነው። በብዙዎች ዘንድ ይህ የቅድስት ማርያም ቃል የእርሷ “ምልጃ” ተደርጎ እየታመነበትና
ስለ ምልጃዋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ተደርጎ እየተጠቀሰ ይገኛል።
በአንድ ወቅት ከነበሩ የቅዱስ ጳውሎስ
መንፈሳዊ ኮሌጅ የመጻሕፍት ተማሪዎች መካከል አንዱ ወደ መንደር ኼዶ ከወንጌላውያን አማኞች ጋር ስለ ማርያም ምልጃ ሲከራከር ቈይቶ
ወደ ኮሌጁ ይመለስና፣ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ባሉበት ለመምህሩ ስለ ክርክራቸው ይነግራቸዋል። መምህሩም “ምን ጠቅሰህ ተከራከርህ?”
ይሉታል። ደቀ መዝሙሩም “የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ኹለትን ጠቀስሁላቸው” ብሎ መለሰላቸው። እርሳቸውም “ሰው ሳይጣላ ማስታረቅ አለ
ወይ? ማንና ማን ተጣልቶ ነው ይህን ስለ ምልጃ ማስረጃ ብለህ ያቀረብኸው? ሰዎቹ ከጌታ ጋር አልተጣሉ፤ ጌታ እንዲያውም የተጠራው
ወዳጅ ኾኖ ነው እኮ! ስለዚህ ይህን ስለ ምልጃ መጥቀስህ ልክ አይደለም” አሉት።
ብዙዎች ግን ባለማወቅ አንዳንዶችም
“ማወቁን እናውቃለን፣ ብንናገር እናልቃለን” ብለው ይህን የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ኹለት ስለ ማርያም ምልጃ እንደሚናገር አድርገው
እንደሚጠቅሱት ይታወቃል። ባለማወቅ ሲደረግ የነበረውን ማረምና ማስተካከል ሲገባ፣ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ
ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በይፋ ይህ ክፍል ስለ ማርያም ምልጃ እንደሚናገር ለራሷ ባሳተመችው መጽሐፍ ቅዱሷ ውስጥ “ስለ እናቱ ምልጃ”
የሚል ርእስ በመስጠት አረጋግጣለች።
ለክፍሉ የተሰጠው ርእስ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኙ አንድ
አንቀጽ ወይም ከአንድ በላይ ለኾኑ አናቅጽ ወይም ምዕራፍ አርእስት መስጠት የተለመደ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በየምዕራፉ ላሉት
ምንባባት ልዩ ልዩ አርእስት የሚሰጠው የግእዙ ዐዲስ ኪዳን፣ ለዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 2 ከቍጥር 1 - 11 ድረስ ላለው የሰጠውና
እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ ሲሠራበት የቈየው ርእስ፣ “ዘከመ ተገብረ ከብካብ በቃና ዘገሊላ” “በቃና ዘገሊላ ሰርግ እንደ ተደረገ”
የሚል አንድ ርእስ ነበር። በአንድምታም በነጠላ ትርጓሜም በታተሙ የግእዝና ዐማርኛ ዐዲስ ኪዳን ውስጥ ይህ ክፍል በዚህ አንድ ርእስ
ሥር ተጠቃሎ ይታወቅ ነበር።[1] ይህን አከፋፈል ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ዕትሞችም ለምሳሌ፦ በ1980 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የታተመው ቀለል ባለ ዐማርኛ የተተረጐመው መጽሐፍ ቅዱስ እና በ1993 የታተመው ዐዲሱ መደበኛ
ትርጕም ይጋሩታል። የ1980ው “ኢየሱስ በገሊላ ቃና በሰርግ ግብዣ ላይ” ሲል፣ የ1993ቱ ደግሞ “ኢየሱስ ውሃን የወይን ጠጅ አደረገ”
የሚል ርእስ ሰጥቶታል። የ2000 ዓ.ም. ዕትም የኢኦተቤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ባልተለመደ፣ ምክንያታዊ ባልኾነና ለራስ አስተምህሮ
በሚመች መልኩ ክፍሉን በሦስት አርእስት ከፋፍሎታል። ይኸውም፦ ቍጥር 1 እና 2 የቀደመውን ዋና ርእስ (ዘከመ ተገብረ ከብካብ በቃና
ዘገሊላ የሚለውን) እንዲይዝ የተደረገ ሲኾን፣ ከቍጥር 3-5 ደግሞ “ስለ እናቱ ምልጃ” ተብሏል። ከቍጥር 6 – 11 ያለው ደግሞ
“ስለ መጀመሪያው ተኣምር” ተሰኝቷል። ይህ አከፋፈል ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ የተሰጠ
እንደ ኾነ ይታወቃል። ከዚያ ወዲህ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሚታተም የግእዝና ዐማርኛ ሐዲስ ኪዳንም ይህንኑ መንገድ የሚከተል ኾኗል።
እዚህ ላይ መነሣት ያለባቸው ኹለት
መሠረታውያን ጥያቄዎች አሉ፤ የመጀመሪያው፣ ክፍሉ የሚናገረው በቃና ዘገሊላ ስለ ተደረገው ሰርግ ነውና፣ የቀደመው ርእስ ለክፍሉ
በቂና ክፍሉን በሚገባ ገላጭ አልነበረምን? የሚል ሲኾን፣ ኹለተኛው ደግሞ ይህ በአንድ ርእስ የሚታወቀው ክፍል ከሦስት መከፋፈል
ለምን አስፈለገው? የሚል ነው።
በቅድሚያ መታወቅ ያለበት ለአንድ
የመጽሐፍ ቅዱስ አንቀጽ፣ አናቅጽ ወይም ምዕራፍ ርእስ የሚሰጠው ማእከላዊ ሐሳቡን ወይም ፍሬ ነገሩን መሠረት በማድረግ ነው። የዮሐንስ
ወንጌል ምዕራፍ ኹለት ከቍጥር 1 - 11 የሚናገረው በቃና ዘገሊላ ስለ ተደረገው ሰርግ ነው። በዚህ ታሪክ ውስጥ ዋናው ጉዳይ የኢየሱስ
በሰርጉ ላይ መገኘቱና ውሃውን የወይን ጠጅ ማድረጉ ነው። ሌላው ኹሉ የዚህ ዋና ታሪክ አጃቢ ነው እንጂ ዋና ጉዳይ አይደለም። ወንጌላዊው
ዮሐንስ ኢየሱስ ካደረጋቸው ምልክቶች መካከል ይህን የምልክቶች መጀመሪያ የጻፈው የኢየሱስን ክብር ለመግለጥና ሰዎች ኢየሱስ እርሱ
ክርስቶስ እና የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን እንዲያምኑ፣ አምነውም የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ለማድረግ ነው (ዮሐ. 2፥11፤
20፥30-31)። ከዚህ አንጻር ከ2000 ዓ.ም. በፊት የነበረው ግእዙም ሌሎቹም ዕትሞች ተመሳሳይነት ያለውን ርእስ የሰጡት በዚህ
ላይ ተመሥርተው ነው። የተሰጠው ርእስም ክፍሉን በሚገባ ገላጭ በመኾኑ፣ ርእሰ ጉዳዩን ከሦስት መከፋፈል ሳያስፈልግ በዚሁ አንድ
ርእስ መጠቀሙ ተገቢ ነው። ስለዚህ ክፍሉን ከሦስት መከፋፈል ያስፈለገው ርእስ ገላጭ ስላልነበረ ሳይኾን በሌላ ዐላማ ነው ማለት
ነው።
አንዱን ርእሰ ጉዳይ ከሦስት ወደ
መከፋፈል የተገባው ክፍሉን ይበልጥ ለማብራራት ታስቦ ነው ማለት አይቻልም። ከዚያ ይልቅ ስለ ማርያም ምልጃ ቤተ ክርስቲያኒቱ ያላት
አስተምህሮ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ እንዲኖረው ለማድረግ ዐስባ ያደረገችው ነው። አኹን ትልቁ ጥያቄ በዚህ ክፍል እንደ ተጻፈው ማርያም
“የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” በማለት የተናገረችውን “ምልጃ” ማቅረብ ብሎ መውሰድ ይቻላል ወይ? የሚለው ነው። እንደሚታወቀው ምልጃ
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ (1ዮሐ. 5፥16) ስለ ሌሎች በጸሎት የሚቀርብ ልመና እንጂ “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም!” የሚለው አነጋገር
ከምልጃ ሊቈጠር የሚችል አይደለም። ጉዳዩ ምልጃ ቢኾን ኖሮ ወንጌላዊው የዐደራ እናቱን (ዮሐ. 19፥26) “ምልጃ” ሳይመዘግበው
ባላለፈም ነበር። ነገር ግን ወንጌላዊው በማርያም አማላጅነት ሳይል፣ “ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤
ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።” ሲል ነው የጻፈው (ዮሐ. 2፥11)። ስለዚህ በአንድ ርእስ የሚታወቀውን ክፍል
ከሦስት መከፋፈል ያስፈለገው የራስን አስተምህሮ “ስለ እናቱ ምልጃ” የሚል ርእስ በመስጠት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ በሥርዋጽ ለማስገባት
እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም።
አንድምታው ምን ይላል?
ለዚህ ክፍል በሊቃውንቱ የተሰጠው
አንድምታዊ ትርጓሜ እንዲህ የሚል ነው፦
·
“ካንች ጋር ምን አለኝ? ማለት ውሃውን ጠጅ አድርግላቸው ብትዪኝ አይኾንም እልሽ ዘንድ ካንች ጋር
ምን ፀብ አለኝ?
· አንድም ውሃውን ጠጅ አድርግላቸው ብትዪኝ አይኾንም እልሽ ዘንድ ውሃውን ጠጅ ላላደርግላቸው ከሰርግ
ቤት ተጠርቼ መጥቻለሁን? ውሃውን ጠጅ ላላደርግላቸው ነውን? አላት።
·
“አንድም በአምላክነቱ አገብሮ (መገደድ) ተአዝዞ (መታዘዝ) እንደሌለበት ለማጠየቅ።
·
“አንድም ውሃውን ጠጅ አድርጌ የማጠጣቸው በኔ ፈቃድ ነው እንጂ ባንቺ ትእዛዝ ነውን አላት”
ከእነዚህ አንድምታዊ
ትርጕሞች የምልጃን ሐሳብ ሳይኾን፣ እርሷ በእናትነትዋ ላቀረበችው ጥያቄ ወይም ትእዛዝ ጌታ የሰጣትን መልስ ነው የምናነበው። በአንድምታው
መሠረት ለጌታ ምላሽ ሊቃውንቱ የሰጡት ትርጕም አዎንታዊም አሉታዊም አቀራረብ አለው። የመጀመሪያዎቹ ኹለቱ አንድምታዊ ትርጓሜዎች
አዎንታዊ ገጽታ ያላቸው ሲኾን፣ የመጨረሻዎቹ ኹለቱ ደግሞ በጌታ ምላሽ ውስጥ እርሱ ታዝዞ ወይም ተገድዶ የሚያደርገው ነገር እንደሌለና
እንደ ራሱ ፈቃድ እንጂ በማርያም ትእዛዝ ምንም ሊያደርግ እንደማይችል ነው የተገለጸው። ኹሉን በራሱ ፈቃድ እንጂ በእርስዋ ትእዛዝ
የማያደርግ መኾኑን የሚያመለክት ነው። ይልቁንም “ውሃውን ጠጅ አድርጌ የማጠጣቸው በኔ ፈቃድ ነው እንጂ ባንቺ ትእዛዝ ነውን? አላት”
የሚለው ለዚህ ግልጽ ማስረጃ ነው።
ዞሮ ዞሮ በዚህ
አንድምታዊ ትርጓሜ ውስጥ የምልጃን ነገር አናገኝም። ለዚህም ነው ከላይ የጠቀስናቸው የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የመጻሕፍት
መምህር የነበሩት ሊቅ፣ ክፍሉን ስለ ማርያም ምልጃ ለጠቀሰው ተማሪ “ሰው ሳይጣላ ማስታረቅ አለ ወይ? ማንና ማን ተጣልቶ ነው ይህን
ስለ ምልጃ ማስረጃ ብለህ ያቀረብኸው? ሰዎቹ ከጌታ ጋር አልተጣሉ፤ ጌታ እንዲያውም የተጠራው ወዳጅ ኾኖ ነው እኮ! ስለዚህ ይህን
ስለ ምልጃ መጥቀስህ ልክ አይደለም” ሲሉ የመለሱት።
የቅዱሳንን ምልጃ አስመልከቶ ያለውን
ልዩ ልዩ ዕሳቤ መመልከት ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ቅድስት ማርያምን ጨምሮ ቅዱሳን በዐጸደ ሥጋ
ሳሉ ብቻ ሳይኾን በዐጸደ ነፍስም እንደሚያማልዱ ታስተምራለች። ኾኖም ሊቃውንቷ በዐጸደ ነፍስ ያለውን ምልጃ በሚመለከት፣ በቀደመ
ልመናቸው የሚከናወን እንጂ በዐጸደ ነፍስ ልመና የሌለባቸው መኾኑን ጭምር የሚያስረዱበት ኹኔታ አለ። በውዳሴ ማርያም ትርጓሜ ላይ
“ሰአሊ ለነ ቅድስት” (ቅድስት ሆይ ለምኚልን) ለሚለውና በኋላ ለተጨመረው የዜማ መክፈያ የተሰጠው አንድምታዊ ትርጓሜ “ልመና እንኳን
በእርሷ በሌሎችም የለባቸውም፤ በቀደመ ልመናዋ ስለምታስምር እንዲህ አለ እንጂ” የሚል ነው።
ይህን የሊቃውንቱን ትርጓሜ ግን
ብዙዎች አያውቁትም፤ ቢያውቁትም አይቀበሉትም፤ ምክንያቱም ቅዱሳን በዐጸደ ነፍስ አኹንም በእግዚአብሔር ፊት ቆመው በማማለድ
ላይ እንደሚገኙና ከዚህ የተነሣ ከእነርሱ ጋር በጸሎት መነጋገር እንደሚችሉ ያስባሉና፤ ያምናሉም። ይህን የማይቀበሉ ሊቃውንት ደግሞ፣
‘በዐጸደ ነፍስ አኹን አያማልዱም፤ ነገር ግን የቀደመውና በሕይወተ ሥጋ ሳሉ የነበረው ልመናቸውና የተገባላቸው ቃል ኪዳን ሲያማልድ
ይኖራል ማለት ነው’ ይላሉ። “መርሐ ጽድቅ ባህለ ሃይማኖት” በዐጸደ ነፍስ ልመናና ምልጃ ያለባቸው የሚያስመስለውን አመለካከት ውድቅ
በማድረግ እንዲህ ይላል፦
ቅዱሳን ጻድቃን ያማልዳሉ ስለ ተባለ ግን ከላይ እንዳልነው በሕይወተ ሥጋ ሳሉ እግዚአብሔርን
አገልግለው የተቀበሉት ቃል ኪዳናቸው እስከ ዕለተ ምጽአት ሲያማልድ ይኖራል ማለት ነው እንጂ፥ እንደ ገና በአካለ ነፍስ መውጣት፥
መውረድ፥ መስገድ፥ መጸለይ፥ መለመን አለባቸው ማለት አይደለም። ... ሊቃውንትም፥ ‘ሰአሊ ለነ ቅድስት’ ያለውን ንባብ ሲተረጕሙ፥
በቀደመ ልመናዋ የምታስምር ስለ ኾነ ነው ይላሉ። ቃል ኪዳን ማለትም፥ ‘መሐልኩ በርእስየ ሕያው አነ (በራሴ ማልኹ፤ እኔ ሕያው
ነኝ)’ ያለው ቃሉ ሕያው ኾኖ ከእነርሱ በኋላ ለሚነሡ ትውልዶች የሚያደርገውን ይቅርታና ቸርነት በመሐላው እንዳጸናላቸው ይኖራል
ማለት ነው እንጂ፥ ከሞቱ በኋላ ሲያማልዱ ይኖራሉ ማለት አይደለም። (1988፣ ገጽ 125-126)።
እዚህ ላይ “ሰአሊ ለነ ቅድስት” ለሚለው
ንባብ የተሰጠውና ‘በቀደመው ልመናዋ የምታስምር ስለ ኾነ እንዲህ (ሰአሊ ለነ ቅድስት) አለ’ የሚለው ማብራሪያ፣ አንድ ጊዜ ለዘላለም
ከኾነው የመካከለኛችን የኢየሱስ ክርስቶስ የማስታረቅ አገልግሎት ተገልብጦ የተወሰደ ይመስላል። በዚህም ላይ ትምህርቱ “ለቅዱሳን
የተገባ ቃል ኪዳን አለ” በሚለው ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ላይ የተገነባ ስለ ኾነም መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለምና ተቀባይነት የለውም።
ምክንያቱም እግዚአብሔር በክርስቶስ ከገባው ዐዲስ ኪዳን በኋላ፣ የቀረው ነገር ኖሮ ያን ለማሟላት ሲል ለቅዱሳኑ የገባው ሌላ ወይም
ተጨማሪ ቃል ኪዳን ከቶ የለም። አለ ከተባለም ዐዲስ ኪዳንን መናቅ፣ የእግዚአብሔርን ልጅ መርገጥ፣ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ
ርኵስ ነገር መቍጠር፣ የጸጋውንም መንፈስ ማክፋፋት ሲኾን፣ ይህም እጅግ የሚብስ ቅጣት የሚያስከትል ኀጢአት ነው (ዕብ. 10፥29)። ከዐዲስ ኪዳን በኋላ እግዚአብሔር ሌላ
ቃል ኪዳን ገብቷል ብሎ ማስተማር ሌላ ስርየተ ኀጢአት የሚሰጥበት መንገድ አለ እንደ ማለት ነው። ይህ እንደማይኾን ግን መጽሐፍ
ቅዱስ ያረጋግጣል። መጽሐፍ “የእውነትን ዕውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኀጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኀጢአት መሥዋዕት
አይቀርልንም” ይላልና (ዕብ. 10፥26)።
ብዙ ጊዜ ለዐጸደ
ነፍስ ምልጃ ማስረጃ አድርገው የሚጠቅሱት ቅዱሳን በዐጸደ ሥጋ ሳሉ ስላቀረቧቸው ምልጃዎች የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ነው።
ስለ ቅድስት ማርያም ምልጃም ማስረጃ አድርገው የሚጠቅሱት ይህ የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 2 ቍጥር 3፣ ከላይ እንዳየነው የምልጃ
ነገር ባይኖረውም እንኳ፣ እርስዋ በሕይወተ ሥጋ ሳለች በቃና ዘገሊላ “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” ብላ ለልጇ የተናገረችው ቃል
ነው። እንግዲህ ቅድስት ማርያም በቃና ዘገሊላ ሰርግ ላይ የተናገረችውን ቃል በመጥቀስ ነው ዛሬ በዐጸደ ነፍስ ላለችው ቅድስት ማርያም
ምልጃ ማስረጃ አድርገው የሚጠቅሱት።
የማርያም ጥያቄና የጌታ ምላሽ ምን ነበር?
ማርያም ላቀረበችው
“የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” ለሚለው ጥያቄዋ ጌታ የሰጠው መልስ አስገራሚ ነው። “አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና
አልደረሰም” ነው ያላት። ምላሹ በተለይ “አንቺ ሴት” የሚለው አንዳንዶች እንደሚያስቡት እናቱን ዝቅ የማድረግ አነጋገር ሳይኾን፣
አክብሮት ያልተለየው፣ ነገር ግን የቅርብን ሳይኾን የሩቅን ሰው የሚያናግሩት ዐይነት አነጋገር ነው። እናቱን አቅርቦ “እናቴ” በማለት
ፈንታ አክብሮና አርቆ “አንቺ ሴት” ነው ያላት። በምላሹ ውስጥ፣ እናቱን አንቺ ላቀረብሽው ጥያቄ ምላሽ እንዳልሰጥ የሚያደርግ እንዳች
ነገር ከአንቺ ጋር የለኝም፤ ነገር ግን የእኔ ጊዜ ገና አልደረሰም ነው ያላት። በዚህም ጌታ የሰርግ ቤቱን ጕድለት የሚሞላው በራሱ
ፈቃድና ጊዜ እንጂ በማርያም ጥያቄና በእርሷ ጊዜ አለመኾኑን ግልጽ አድርጓል።
ጌታ እናቱን
“እናቴ” በማለት ፈንታ “አንቺ ሴት?” ለምን አለ? እርሱ ጌታችን ሰው ኾኖ የመጣው ዓለምን ለማዳን እንጂ በአንድ ቤተ ሰብ ውስጥ
ሥጋዊ ዝምድናን አጠናክሮ ለዚያ ቤተሰብ የተለየ አለኝታ ለመኾን እንዳይደለ ለማመልከት እንደ ኾነ ከዚህ ክፍልና ከሌሎችም ከእናቱ
ጋር በተገናኘ ከተናገራቸው ቃላት መረዳት ይቻላል። ጌታ በዐሥራ ኹለት ዓመቱ ለበዓል ከእናቱና ከዮሴፍ ጋር ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም
ወጥቶ ሳለ፣ ከበዓሉ ፍጻሜ በኋላ እርሱ እዚያው ቀርቶ ከመምህራኑ ጋር ይነጋገር ነበር። እናቱና ዮሴፍ ከመንገደኞች ጋር ያለ መስሏቸው
ነበር። ነገር ግን ባላገኙት ጊዜ ለሦስት ቀናት እየፈለጉት እንደ መጡና በመምህራኑ መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውና ሲጠይቃቸው በመቅደስ
እንዳገኙት በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ተመዝግቧል። ከዚያ እናቱ፦ “ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን
ስንፈልግህ ነበርን አለችው።” በዚህ ጊዜ ጌታ፦ “ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን? አላቸው።
እነርሱም የተናገራቸውን ነገር አላስተዋሉም።” (ሉቃ. 2፥42-50)።
በሌላም ጊዜ
ጌታ ሕዝቡን እያስተማረ ሳለ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት በውጭ ቆመው እንዳሉ በተነገረው ጊዜ፣ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ
እነማን ናቸው? አለው። እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ፦ እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ
ኹሉ፥ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና አለ።” (ማቴ 12፥46-50)።
እንደዚሁ ጌታ
ሲያስተምር በዚያ የነበረችና በትምህርቱ የተደነቀች የመሰለች አንዲት ሴት፣ “ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፦ የተሸከመችህ ማሕፀንና የጠባሃቸው
ጡቶች ብፁዓን ናቸው አለችው። እርሱ ግን፦ አዎን፥ ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው አለ።” (ሉቃ. 11፥27)።
በቃና ዘገሊላ
ሰርግ ላይም እናቱን አንቺ ሴት ብሎ በአክብሮት ነገር ግን የሩቅን ሰው እንደሚያናግር ዐይነት ማናገሩ ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ነው።
ትልቁ ነገር ጌታ ለምን እንዲህ አደረገ? የሚለው ነው። በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈው ጌታ ከዐሥራ ኹለት ዓመት ዕድሜው በኋላ ለእናቱና
ለዮሴፍ እየታዘዘ ነው ያደገው (ሉቃ. 2፥51)። በሠላሳ ዓመቱ ተጠምቆ ራሱን ከገለጠ በኋላ ግን በመሲሓዊ አገልግሎቱ ከእናቱ ጋር
ቤተ ሰባዊ ወይም ሥጋዊ ዝምድናን መሠረት አድርጎ የሠራው ነገር ስለ መኖሩ በመጽሐፍ ቅዱስ አልተመዘገበም። ጌታ እንዲህ ያደረገው
ሰው ኾኖ የመጣው ለዓለም ኹሉ መኾኑን መሠረት በማድረግ ነው። ከዚህ ሌላ ዛሬ ብዙዎች እንደሚያስቡትና እንደሚያደርጉት፣ ሰዎች በሥጋዊ
ዝምድና ላይ ተመሥርተው በአክብሮት ስም እናቱን ወደ ማምለክ እንዳይሸጋገሩ በሩን ለመዝጋትም ሊኾን እንደሚችል ይታመናል።
ቅድስት ማርያም በቃና ዘገሊላ ምን መልእክት አስተላለፈች?
በቃና ዘገሊላ
ሰርግ ላይ ጌታ ለቅድስት እናቱ የሰጣትን ምላሽ ተከትላ እርስዋ ለአገልጋዮቹ “የሚላችሁን ኹሉ አድርጉ” አለቻቸው። በዚህም ጌታ
ከሰጣት ምላሽ በመነሣት በጌታ ፈቃድና ጊዜ ሊኾን ያለ አንዳች ነገር እንዳለ አምናለች። ለአገልጋዮቹ በሰጠችው መምሪያ ውስጥም እርሱ
የሚላቸውን ኹሉ እንዲያደርጉ ስታሳስብ፣ ትኵረታቸው እርሱ በሚላቸው ነገር ኹሉ ላይ እንዲያርፍና ከዚያ የሚኾነውን እንዲጠብቁ የሚያሳስብ
ነው።
ይኹን እንጂ
ዛሬ ብዙዎች ይህን የማርያምን መልእክት ብዙም ቦታ አይሰጡትም። ከዚያ ይልቅ ያልተጻፈውን በማንበብ ላይ ተመሥርተው የቃና ዘገሊላ
ተኣምር ትኵረት ኢየሱስ ሳይኾን ማርያም እንድትኾን ይፈልጋሉ። ይህ ግን ከወንጌሉ ማእከላዊ ሐሳብ እጅግ የራቀና በክፍሉ ውስጥ የሌለ
ሐሳብ ነው።
[1]
(ኢኦተቤ፣ ወንጌል
ቅዱስ ከቀድሞ አባቶች ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ንባቡና ትርጓሜው (በአንድምታ)፣ (ዐዲስ አበባ፦ ብርሃንና ሰላም
ማተሚያ ቤት፣ 1988 ዓ.ም.)፣ 459፤ )።
ፖስት የምታረግትን ሁሉ አየሁ ስራቹ እንዳለ የሌብነት ነው ለምን የራሳችሁን ሃይማኖት ዪዛቹ አትኖሩም። መናፍቃን ናቹ በኦርቶዶክስ ስም መነገዱ ውሸታም ወይም አጭበርባሪነታችሁን ነው የሚያሳየው የራሳችሁን ኑሩ እኛን ተዉን እና እስቲ በ መልካም ኑሩ እሱኮ ይበልጥ ነበር ጊን ያለኛ አይሆንላችሁም እግዜር ልቦና ዪስጣቹ!!!
ReplyDelete