Saturday, January 6, 2018

ርእሰ አንቀጽመድኀኒት፥ እርሱም ክርስቶስ ጌታ ተወልዶላችኋል! ! !
            “ወመ በጽሐ ዕድሜሁ ፈነወ እግዚአብሔር ወልዶ፤ ወተወልደ እምብእሲት…” ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ላከና እርሱም ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ ከሕግ በታች እንደ ተወለደ የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል (ገላ. 4፥4-5፤ ከዘፍ. 3፥15 እና ከኢሳ. 7፥14 ጋር ይነበባል)።
“ንጹሕ ይኾን ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ከሴትስ የተወለደ ጻድቅ ይኾን ዘንድ እንዴት ይቻላል? ከርኩስ ነገር ንጹሕን ሊያወጣ ማን ይችላል? አንድ እንኳ የሚችል የለም።” (ኢዮ. 14፥4፤ 15፥14-16) ተብሎ በተነገረው መሠረት ሳይኾን፥ ከድንግል በሥጋ የሚወለደው “ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ” ይባል ዘንድ ታቀደ። ስለዚህም መንፈስ ቅዱስና አብ በቅድሚያ ወደ እርሷ በመምጣት በእግዚአብሔራዊ እኔነት (የራሱ በኾነ ምልአተ አካል) የሚታወቀውን ቃል እንድትፀንስና እንድትወልድ ከተወረሰው አዳማዊ ባሕርይ የማንጻቱንና የመቀደሱን ሥራ እንደሚያከናውኑ የምሥራች ተነገራት። እርሷም ለመልእክተኛው እንዳልከው ይኹን፤ እኔ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የማገልገል ባሪያው ነኝ አለች። ዓለምን ለማዳን እግዚአብሔር ባወጣው ዕቅድ ተስማሚነቷን በእሺታ ንግግሯ ገለጸች። (ሉቃ. 1፥26-38)።

ከፀነሰችም በኋላ በማኅፀኗ የተሸከመችው ፅንስ ለእርሷ አምላኳም መድኀኒቷም እንደ ኾነ መሰከረች፤” ወትትሐሠይ መንፈስየ በአምላኪየ ወመድኀኒየ፤ እስመ ርእየ ሕማማ ለዓመቱ” አለች። ለእርሷም ኾነ ለሌላ ሰው ኹሉ በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ካልኾነ በቀር መዳን በሌላ በማንም በኩል እንደማይገኝ ያወቀችውን አሳወቀች (ሉቃ. 1፥46-48፤ ሐ.ሥ. 4፥12)።

ቅድስት ድንግል ማርያም የፀነሰችውን ለመውለድ በተቃረበችበት ጊዜ፥ ለሕዝብ ቈጠራ ክንውን ኹሉም በየትውልድ ከተማው ቀርቦ ይመዘገብ ዘንድ የተላለፈውን ቄሣራዊ ትእዛዝ ለመፈጸም ከምትኖርበት ከናዝሬት ከተማ ወደ ቤተልሔም መኼዷን ወንጌል ይናገራል። ማረፊያዎች ቀድሞው በደረሱ መንገደኞች በመያዛቸው ይኹን፥ ወይም ለማረፊያ የሚጠየቀውን ገንዘብ ለመክፈል ባለመቻላቸው ይኹን፥ ግልጽ ባልኾነ ምንያት ለማረፊያ የሚኾን ስፍራ ስላላገኙ፥ ማርያምና ዮሴፍ በከብቶች በረት ዐረፉ። ሕፃኑ ኢየሱስም በዚያ ተወለደና እናቱ በግርግም አስተኛችው (ሉቃ.2፥1-7)።
ምድራችን ያድናት ዘንድ የመጣላትን መሲሕ ለማስተናገድ ምንም መሰናዶ ባላደረገችበት፥  እንዲያውም ያለመቀበል ምልክት ይኾን ዘንድ ማደሪያ በከለከለችው ሰዓት፥ ሰማይ ደስታ በፈነቀላቸው መላእክት ዝማሬ ተናውጦ ነበር። መደባቸው ከተናቀው ኅብረተ ሰብ ክፍል ለኾኑት እረኞችም የምሥራቹ የተናገረቸው በእነዚሁ መላእክት አንደበት ነበረ። “እነሆ ለሕዝብ ኹሉ የሚኾን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኀኒት፥ እርሱም ክርስቶስ ጌታ የኾነ ተወልዶላችኋል” ተባሉ። እረኞቹም በተሰጣቸው ምልክት እየተመሩ ወደ ቤተልሔም ሲደርሱ ኹሉም ልክ እንደ ተነገራቸው ኾኖ አገኙት፤ ማርያምንና ዮሴፍን፥  በግርግም የተኛውን ሕፃኑን ኢየሱስንም አዩ (ሉቃ. 2፥8-20)።      
ባለራእዮቹ እረኞች ሕፃኑ የተገኘበትን ቤተ ሰቡንና ሌሎች ኹኔታዎችን ቢመለከቱም ትኵረታቸው አንድ ብቻ ነበረ፤ ያም ሕፃኑ ኢየሱስ ብቻ። የእግዚአብሔርም ቃል ስለ እረኞቹ ትኵረት ሲናገር፥ “አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገራቸውን ነገር ገለጡት” ይላል። የእረኞቹን ምስክርነት የሰሙ ኹሉ ተደነቁ። ከተደነቁትም መካከል ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ነበረችና የተባለውን ኹሉ በልቧ ሰሌዳ ላይ ትመዘግበው ነበር።”ወማርያምሰ ተዐቅብ ዘንተ ኵሎ ነገረ ውስተ ልባ” እንዲል (ሉቃ. 2፥19)።
መላእክት በዝማሬያቸው ባስተላለፉት መልእክት በሕፃኑ ኢየሱስ መወለድ ስለ ተገኙት ሦስት ታላላቅ ነገሮች በመጠቈም “ይኹንታዎችን” ዐውጀዋል (ሉቃ. 2፥14)።
አንደኛ ፡- “ለእግዚአብሔር በአርያም ክብር ይኹን” አሉ። በባሕርዩ ዘላለማዊ ክብር ጐድሎበት የማያውቀው እግዚአብሔር በጥንተ ፍጥረት የጥበቡን ርቀትና የመንግሥቱን ሉዓላዊ ክብር የገለጸበት የሰው ልጅ በኀጢአት በወደቀ ጊዜ፥ ሰይጣን ዘላለማዊውን መለኮታዊ ዕቅድ ለማበላሸት የተቻለው መስሎት ነበር። ነገር ግን በጥንተ ፍጥረት የተገለጸው ገና ወደ መኾን ከመምጣቱ አስቀድሞ እኛን የሰውን ልጆች “ቅዱሳንና ነውር አልቦ እንኾን ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ ሊመርጠን ዓለም ሳይፈጠር ዐቅዶና ወስኖ ነበር” ይላል ቃሉ። ለምን? ቢባል “እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ” በማለት ይመልሳል (ኤፌ. 1፥4-6)።
በመፍጠር ከሚገለጸው ክብሩ ይልቅ፥ በጸጋው ሰውን በማዳን ለሚከሠተው ክብሩ ብልጫንና የዕቅድ ቅድሚያን ስለ ሰጠ በኀጢአት የወደቅነው እኛ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ፥ ለበለጠው ክብሩ እንመረጥ ዘንድ አስቀድሞ ማለት ዓለም ሳይፈጠር አምላካችን ወስኖ ነበር። በተፈጥሮ በነበርንበት ኹኔታ ሳይኾን ተፈጥሮኣችንን ካበላሸብን ውድቀት በማንሣት ትርሲተ ወልዱ (ለልጁ የሚሰጥ ሽልማት) ሊያደርገን፥ በእርሱም በኩል ልጆቼ ብሎ የወራሽነት መብት ሊሰጠን ወድዶ፥ ዓለም ሳይፈጠር ባወጣው ዕቅዱ የመንግሥቱ ወራሾች አደረገን። ለምን? ቢባል “ለክብሩ ምስጋና እንኾን ዘንድ ነው” ይላል አኹንም ቃሉ (ኤፌ. 1፥12)።
በጸጋው የመዳናችንን ወንጌል በዘመናችን ሰምተን እናምንና እንድን ዘንድ፤ የልጅነታችንና የወራሽነታችንም መብት ለመንፈሳችን ይረጋገጥ ዘንድ፤ ለመንፈሳችን በሚመሰክረውና ዐረቦናችን በኾነው (መያዣ ኾኖ በተሰጠን) በመንፈስ ቅዱስ ማኅተም እንድንታተም የተወሰነው በዘመን ፍጻሜ አልነበረም (ሮሜ 8፥29-30)። ከውድቀት በኋላ በሚኖር ትንሣኤ በሰማይና በምድር ያለውን ኹሉ በልጁ ለመጠቅለል ዓለም ሳይፈጠር ያወጣው መለኮታዊ ዕቅድ ነበረ። ለምን? ቢባል “ለክብሩ ምስጋና ይኾን ዘንድ ነው።” በማለት የእግዚአብሔር ቃል ምላሹን ይሰጣል (ኤፌ.1፥10-14)።
ይጨመርለት ዘንድ ከባሕርዩ ውጪ ምንም የማይፈልግ፥ መለኮታዊ ባሕርዩ፥ ኹሉ በኹሉ ኾኖለትና ተትረፍርፎለት የሚኖር ልዑል፥ ቅዱስ እግዚአብሔር ሊፈጥረው ያለውንና እንደሚወድቅም አስቀድሞ ያወቀውን የሰው ልጅ ከውድቀቱ በማንሣት በተፈጥሮው ሊኖረው ከሚገባው ክብር ይልቅ እጅግ ለላቀ መለኮታዊ ክብር ተካፋይነት ማብቃትን የክብሩ ኹሉ መደምደሚያ አደረገው (ዮሐ. 17፥22-23፤ 2ጴጥ. 1፥4) ይህን በማድረጉ የሚጨመርለት ክብር ሳይኖር የእኛን መዳን የክብሩ መደምደሚያ ያደረገበትን መለኮታዊ ምስጢር ዐስበንና ተመራምረን የማንደርስበት፥ በስፋትም በጥልቀትም ዳር የለሽ ውቅያኖስ ነው። እንዲሁ ከሰማይ መላእክት ጋር በዝማሬ በመተባበር ላከበረን፥ ለክብሩ ምስጋና እንኾን ዘንድ ላበቃን ለእርሱ “ክብር ይኹን” እንላለን።
አስቀድሞ ከዘላለም በእግዚአብሔር ዘንድ በእግዚአብሔርነት ደረጃ እግዚአብሔር ኾኖ የኖረው “ቃል” ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ኾኖ በተወለደበት ዕለት ዜናው “ለሕዝብ ኹሉ የሚሆን ታላቅ የምሥራች (ዐቢይ ዜና ፍሥሓ ዘይከውን ለኵሉ ሕዝብ) መኾኑን መላእክት በዜማ አበሠሩ። ለመለኮታዊ የክብሩ ሙላት ወደምደሚያ (ጕልላት) ይኾን ዘንድ ዓለም ሳይፈጠር የወሰነው፥ ሰውን በጸጋው የማዳን ዕቅዱ ሊፈጸም በቃል ሥጋ መኾን ተጀመረ፤ ለዘመናት ሲናፈቅ የኖረው የእግዚአብሔር ክብር በምድር መገለጽ ጀመረ። ስለዚህ ሰማያት የሐሤቱ ተካፋዮች በመኾን ይህን ከክብር ኹሉ በላይ የላቀ ክብር ያስተጋቡ ዘንድ ተጋበዙ።
“ሰማያት ሆይ! ዘምሩ፤ አንተም የምድር ጥልቅ ሆይ! ጩኽ፤ እናንተም ተራሮች፥ አንተም ዱር፥ በዱርም ያለህ ዛፍ ኹሉ፥ እልል በሉ፥ እግዚአብሔር አድርጎታልና፤ ያዕቆብንም ተቤዥቶታልና። በእስራኤልም ዘንድ ይከበራልና (ኢሳ. 44፥23)።
ወገኖች! እግዚአብሔር የመለኮታዊ ክብሩ መደምደሚያ ላደረገው ዓለም ሳይፈጠር ላቀደው፤ ለዘመናት ሲናፈቅ ለቈየው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለተገኘው “መዳናችሁ” እናንተ በበኩላችሁ ምን ዐይነት ግምት ትስጡት ይኾን? የዋጋውንስ ክቡርነትና ውድነት በምን ደረጃ ትመዝኑት ይኾን? በእግዚአብሔር ጸጋ መዳናችሁ ለእግዚአብሔር የክብሩ ሙላት መደምደሚያ ነው በተባለው በእግዚአብሔር ሚዛን ትስማማላችሁን?
    ሁለተኛ፡- በመላእክት አንደበት የተነገረው ኹለተኛው ዐዋጅ “ሰላም በምድር ይኹን” የሚል ነበር።
እግዚአብሔር የመጀመሪያውን አባታችንን በውድቀቱ ጊዜ ለመጀመሪያ በርቀት፥ በድምፅ ብቻ ተገናኘው። በወቅቱ የእግዚአብሔርና የሰው መለያየት ጕልሕ ኾኖ ታየ። እንዲሁም አንድ አካል ናቸው የተባሉት ባልና ሚስት (አዳምና ሔዋን) እርስ በርስ ተካሰሱ። ሔዋንም ከምትገዛቸው አራዊት መካከል የኾነውን እባብ የጥፋታቸው ምንጭ አድርጋ አጋለጠች።
እግዚአብሔርም “ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍ በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትኹን።… እሾኽንና አሜከላን ታብቅልብህ፤ …” በሚል ርግማን ሰውን ተለየው (ዘፍ. 3፥10-19)። ከእንግዲህም መንፈሱ በሰው ላይ እንደማይኖር በመናገር የጸቡን መክረርና የቅያሜውን ትኵሳት አስታወቀ (ዘፍ. 6፥3)። የእግዚአብሔርና የሰው ቍርጠኛ መለያየትም “እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ከዔድን ገነት አስወጣው” በሚል ኀይለ ቃል ተነገረ (ዘፍ. 3፥22-24)።
አኹን ግን፥ በእግዚአብሔር ዘንድ በእግዚአብሔራዊ እኔነት ከዘላለም ታውቆ የኖረው ቃል፥ ሰው ኾኖ ሲወለድ፥ እግዚአብሔር - ሰው በተዋሕዶ በአንድ አካል አማኑኤል ኾነ። ድምፁን ከርቀት ሲሰማ ይርበደበድ፥ ይሸሽ፥ በቍጥቋጦ ውስጥ ይደበቅ፥ በዐይኑ ላለመታየትና ራቍትነትን ለመከለል ቅጠላ - ቅጠል ይለብስ የነበረው አዳማዊ ሰው ከእግዚአብሔር የተጣለበት ጥል ኹሉ ወደማይታሰብበት ደረጃ ይለወጥ ዘንድ፥ የኹለቱ ጠበኞች መዋሐድ የሰላም መሠረት ኾኖ በምድር ተጣለ። ኹለቱን በእኩል ዝምድና የሚያገናኝ የአንድ ብቸኛ ማእከል (ማእከላዊ) መኖር ለሚፈጠረው ዕርቅ ዋስትናው ስለ ኾነ ከእንግዲህ “ሰላም በምድር ይኹን” ተባለ። የምድር ጠበኞች ኹሉ በነገድ፥ በቋንቋ፥ በቀለም፥ በጾታ፥ በመደብ … መለያየታቸው ቀርቶ በክርስቶስ አንድ አካል ኾኑ (1ቆሮ. 12፥13፤ ገላ. 3፥26-28፤ ኤፌ. 2፥14-22)።

       ሦስተኛ፡- “ለሰውም በጎ ፈቃድ ይኹን አሉ” መላእክት።
አንድ ጊዜ አስደናቂ ታሪክ መፈጸሙ ተነገረ። በአንድ ሀገር ላይ ወራሪ ጠላት በመጣ ጊዜ ብዙዎች ዜጎች በዱር በገደል ኾነው ወራሪውን ጠላት ለመቋቋም ወስነው ሸፈቱ። ለጥቂት ወራት የከረረ ፍልሚያ በኹለቱም መካከል ሲካኼድ ከቈየ በኋላ በወራሪውና በተሸናፊው መንግሥታት መካከል ዕርቅ ተደረገና የሰላም ውል ተፈረመ። ዜጎቻቸውም ወደ የግል ተግባራቸው ተሰማሩ። ነገር ግን ሰላም ከተፈጠረ ከ25 ዓመታት ያኽል በኋላ ጥቂት ዐርበኞች የነበሩ ሰዎች ተሸናፊ በነበረው ሀገር ውስጥ፥ ገና በዱር (በሽፍትነት) መገኘታቸው በተደረሰበት ጊዜ ዓለም ጉድ! አለ። ዐርበኞቹ በነበሩበት ደን በኩል የሚያልፍ ጠላት ባለመኖሩ የሚዋጉት አልነበረም። ብቻ የጦር መሣሪያቸውን ይዘው በደን ውስጥ፥ ዐውሬ እያደኑ ፍራፍሬ እየለቀሙ ይመገቡ ነበር። እነዚህ ዐርበኞች ወይም የሰላሙን ቃል ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም፤ ወይም የዕርቁን የሰላሙን የምሥራች ገና አልሰሙም ነበር ማለት ነው።
በእግዚአብሔርና በፈጠረው ሰው መካከል፥ እግዚአብሔር-ሰው በኾነው ዐማኑኤል ዕርቅ ተመሥርቷል፤ የሰላምም ዐዋጅ ታውጇል። አኹን የሚጠበቀው ለዕርቁና ለሰላሙ ፈቃደኛ ኾኖ ምላሽ መስጠት ስለ ኾነ፥ መላእክት ከእንግዲህ የሰው በጎ ፈቃድ እንዲኖር ጠየቁ። በእውነትም ዕርቁን ለመቀበል፥ ሰላሙን ለመጐናጸፍ ዛሬም ዐማኑኤልን መቀበል ያስፈልጋል። ሰው በዐማኑኤል እግዚአብሔርም በዐማኑኤል እኩል ዝምድና ይኖራቸው ዘንድ አንድ ማእከላዊ ብቻ ተመድቧል (1ጢሞ. 2፥3-7)። እንዲህም መደረጉን ያለመረዳት ገና በሽፍትነት መኖርን ያሰከትላል። እግዚአብሔርንና ሰውን እኩል የማያገናኝ ማእከላዊ (መካከለኛ) መመደብም ሞኝነት ነው። ስለዚህ ለእኛና ለእግዚአብሔር እኩል ዘመድና ብቸኛ ማእከላዊ በኾነው በዐማኑኤል ላይ የቆመውን የዕርቅና የሰላም ውል ለመቀበል ኧረ! ለሰው ኹሉ በጎ ፈቃድ ይኹን። አሜን።
ጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቍጥር 11 ርእሰ አንቀጽ

No comments:

Post a Comment