Tuesday, January 2, 2018

ዕቅበተ እምነት

“መድሎተ ጽድቅ” በመድሎተ ጽድቅ ሲመዘን  ክፍል ዐምስት

READ PDF

ጮራ ቍጥር 49 ለንባብ በቅቷል። በመጽሔቱ ላይ ከወጡ ጽሑፎች መካከል አንዱ ለ"መድሎተ ጽድቅ" የተሰጠው ምላሽ ቀጣይ ክፍል ይገኝበታል። ጽሑፉ እነሆ፥ (ይህ ክፍል በመጽሔቱ ላይ ክፍል ሦስት ተብሎ ነው የተገለጸው ምክንያቱ ደግሞ የሚስተር ዳዊት ስቶክስ ታሪክ በዘመን ምስክር ዐምድ ላይ ስለወጣ ነው)

ባለፈው ዕትም “መድሎተ ጽድቅ”፣ እኛ በመሰለን እንደምናምን አድርጎ አንባቢን ለማሳሳት ያቀረባቸው ማስረጃዎች፣ በተሳሳተና በአሻጥር መንገድ ያቀናበራቸው መኾናቸውን በበቂ ማስረጃዎች አስደግፈን ማቅረባችንን ተከትሎ፣ በርካታ አንባብያን በምላሹ መደሰታቸውን ገልጸውልናል። ለዛሬው ደግሞ ይኸው “መድሎተ ጽድቅ” በገጽ 35-42 ላይ “1.1.2. በሐሰት መናገር” በሚለው ንኡስ ርእስ ሥር እኛ በሐሰት እንደምንናገር አድርጎ የጻፈውን እንመረምራለን።
በጽሑፉ መጀመሪያ ላይ “ሌላው የተሐድሶዎች መገለጫ በሐሰት መናገር (ውሸት) ነው። ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማታምነውንና የማትቀበለውን እንደምታምን እያስመሰሉ በሐሰት መጻፍና መናገር ዋና ጠባያቸው ነው። ለአብነት የሚከተሉትን እንመልከት፦” ብሎ ከተቀበረ መክሊት ላይ የሚከተለውን ጠቅሷል፦ በሌላ በኩል እግዚአብሔር በእርሷ ታላቅ ነገርን ሊያደርግ ከአንስተ ዓለም የመረጣትና ያከበራት የጌታችን እናት ቅድስት ማርያምን ልንመለከት እንችላለን። በመልአኩ ብሥራት እንደ ተገለጠው ጸጋ የሞላባት ናት። ይህ ማለት ግን እንደ እግዚአብሔር በኹሉ ስፍራ ትገኛለች፤ ኹሉን ታውቃለች ወደሚል ድምዳሜ አያደርሰንም። … በእርግጥ በፈጣሪና ፍጡራን መካከል ያለውን የባሕርይና የዕውቀት ልዩነት ካላወቅን ትልቅ ስሕተት ውስጥ እንወድቃለን። ፍጡራንን ከፈጣሪ ጋር አስተካክለው የሚያዩ ክፍሎች ችግርም ይኸው ነው። (ገጽ 164-5)።”  (መድሎተ ጽድቅ ገጽ 38)።
የተቀበረ መክሊት በሕዝቡ ዘንድ ያለውን አመለካከትና በዚያ ላይ የተመሠረተውን ሕይወት በተመለከተ ላሰፈረው ሐሳብ “መድሎተ ጽድቅ” ምላሽ ሲሰጥም፦
“… ከንቱ የሐሰት ውንጀላ ነው” ብሏል። አስከትሎም፣ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የምትሰጠው ክብር ግልጽና የታወቀ ነው። እርሱም መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ ማለትም ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች የሚል ነው። ከዚህ ውጭ ግን ‘እንደ እግዚአብሔር በኹሉ ስፍራ ትገኛለች ኹሉን ታውቃለች’ የሚል እምነትም ኾነ አስተምህሮ የለም። በኹሉ ስፍራ መገኘት (ምሉዕ በኵለሄነት) እና ኹሉን ዐዋቂነት (ማእምረ ኵሉ መኾን) የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቦች ብቻ መኾናቸው የታወቀ ነው። ስለዚህ ቅድስት ቤተ ርስቲያን ፈጣሪና ፍጡርን አሳምራ ለይታ የምታውቅ ናት እንጂ ‘ፍጡራንን ከፈጣሪ እኩል ማድረግና ማስተካከል’ የሚለው አይመለከታትም። … እኛ ይህን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን እምነት እየገለጽን ያለነው፣ ወደፊትም በየጉዳዩ የምንገልጸውና ምስክር የምንጠቅሰው ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቀደምት ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ትምህርት ስለ ኾነ እናንተም ከእነዚህ ምስክር አለን የምትሉ ከኾነ ማቅረብ እንጂ በስማ በለውና በይመስላል፣ እንዲሁም ደግሞ በግል ጸሎትና ለታሪክ፣ እንዲሁም ይህን ለመሳሰለው ተግባር ያሉትን ነገሮች በመጥቀስ አይደለም” ብሏል (ዝኒ ከማሁ)።

በቅድሚያ ኢኦተቤ ለቅድስት ማርያም ስለምትሰጠው “መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ” የተሰኘ ስፍራ የተሰጠው ማብራሪያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለው መኾኑን መግለጽ ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ እርስዋ ከሴቶች መካከል ተለይታ የተባረከችና የጌታ እናት ለመኾን የተመረጠች መኾኗን ይናገራል እንጂ፣ ይህን ክብር መንዝሮ ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ ወደሚል የተለየ ስፍራ አይለውጠውም። ጌታ በቅዱስ ወንጌል ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ሲመሰክር፣ “ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከኹሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።” (ሉቃ. 7፥28፤ ማቴ. 11፥11) ብሏል። ስለ ቅድስት እናቱ ግን “መልዕልተ ፈጣሪ መትሕተ ፍጡራን” ናት ሲል አልተናገረም። ይህ አገላለጽ የሰዎች እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ አይደለም ማለት ነው።
ይልቁንም ይህ “መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ” የተሰኘ ስፍራ ቀስ በቀስ እርሷን በፍጡራንና በፈጣሪ መካከል ያለች መካከለኛ እንዳደረጋት በተግባር የሚታይ እውነት ነው። በአዋልድ ውስጥም ይህን ሐሳብ የሚያንጸባርቅ ድርሰት እናገኛለን። ለምሳሌ ማሕሌተ ጽጌ፦
በከመ ይቤ መጽሐፍ ማእከለ ፈጣሪ ወፍጡራን
ለዕረፍት ዘኮንኪ ትእምርተ ኪዳን
ሰንበተ ሰንበታት ማርያም ዕለተ ብርሃን።
ብኪ ይትፌሥሑ ዘገነተ ጽጌ ጻድቃን።
ወብኪ ይወፅኡ ኃጥኣን እም ደይን።

ትርጕም፡-
መጽሐፍ እንዳለ በፈጣሪና በፍጡራን መካከል
ለዕረፍት የምልክት ኪዳን የኾንሽ
የሰንበታት ሰንበት ማርያም ሆይ!
አንቺ የብርሃን ዕለት ነሽ።
አበባ በሞላበት ገነት ውስጥ ያሉ ጻድቃን በአንቺ ደስ ይላቸዋል።
በአንቺም ኃጥኣን ከሥቃይ ስፍራ (ከሲኦል) ይወጣሉ።
በማለት እርስዋን ስለ ክርስቶስ በተነገረው ቃል (2ጢሞ. 2፥5) በፈጣሪና በፍጡራን መካከል ያለች ሰንበተ ሰንበታት (የዕረፍቶች ዕረፍት) ያደርጋታል። (መቼም የ “መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ ይህን የማሕሌተ ጽጌ ቃል “የግል ጸሎት” ነው ብሎ አትጥቀሷቸው ካላቸው አዋልድ ውጪ እንደማያደርገው ተስፋ አለን። በነገራችን ላይ ጸሓፊው “በግል ጸሎትና ለታሪክ፣ እንዲሁም ይህን ለመሳሰለው ተግባር ያሉትን ነገሮች” ሲል የጠቃቀሳቸው አዋልድ መጻሕፍት እንደ  )
    
የቅዱሳን ወይም የቤተ ክርስቲያን አንድነት በተገለጸባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ለማርያም “ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች” የሚል ስፍራ ተሰጥቷት በአንድም ስፍራ አናነብም። በአንድ አካል የተገለጸችው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አንድ ራስ አላት፤ እርሱም ክርስቶስ ብቻ ነው። የቤተ ክርስቲያን ራስ በኾነው በእርሱና አካሉ በኾነች ቤተ ክርስቲያን መካከልም ሌላ የለም (ኤፌ. 1፥22-23)። ቅድስት ማርያምም ከሴቶች መካከል ተለይታ የተባረከች ብትኾንም፣ የክርስቶስ አካል የኾነችው ቤተ ክርስቲያን አባል እንጂ ከአካሉ ውጭ የኾነች ሌላ አካል አይደለችም ማለት ነው።
ቅዱስ ገብርኤል ሲያበሥራት “ጸጋ የሞላብሽ ሆይ” ብሎአት ነበር (ሉቃ. 1፥28)። የመጀመሪያዎቹ የጌታ ደቀ መዛሙርት የአብን ተስፋ ርደተ መንፈስ ቅዱስን (የመንፈስ ቅዱስን መውረድ) እየተጠባበቁ ሳለ፣ በመካከላቸው የኢየሱስ እናት እንደ ነበረች ተጽፏል። በዚያ የነበረችውም “መልዕልተ ፈጣሪ መትሕተ ፍጡራን” ኾና አይደለም፤ ተስፋውን ከሚጠባበቁት አንዷ ኾና ነበር እንጂ። ሐዋርያቱ ኹሉ “ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ኾነው ለጸሎት ይተጉ ነበር።” የሚለው ቃል ምስክርነትም ይህን ነው የሚያረጋግጠው (ሐ.ሥ. 1፥14)።
በዕብራውያን መልእክት ውስጥ፣ “ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የኹሉም ዳኛ ወደሚኾን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ኾኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የዐዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚኾን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል።” (ዕብ. 12፥22-24) በሚለው ክፍል ውስጥ የጌታችን እናት ብፅዕት ማርያም በተለየ ኹኔታ “መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ” ኾና አልተጠቀሰችም። የእርስዋ ስፍራ ሊኾን የሚችለው እዚህ አንድነት ውስጥ ነው እንጂ፣ “ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ” ተብሎ አልተጠቀሰም። የዐዲስ ኪዳን መካከለኛው (ኅሩይ ማእከለ እግዚአብሔር ወሰብእ - በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው 2ጢሞ. 2፥5) ግን ኢየሱስ ክርስቶስ መኾኑ በግልጽ ተጠቅሷል።
ስለዚህ “መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ” የሚለው ገለጻ ለማርያም ተሰጥቶ የምናገኘው በአዋልድ መጻሕፍት እንጂ በቅዱሳት መጻሕፍትና እርሱን መሠረት አድርገው ባስተማሩ አበው ትምህርት ውስጥ አለመኾኑ እሙን ነው። ይህ አነጋገርና በውስጡ የያዘው ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ በተቃራኒ ቅድስት ማርያም የተለየ ስፍራ እንዲኖራት አድርጓል። ቀስ በቀስም “መትሕተ ፈጣሪ” መኾኗ ቀርቶ ከፈጣሪ ጋር በክብር እስከ መተካከል አድርሷት እናገኛለን። እርግጥ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ፣ “መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ” ለሚለው ገለጻ ከመጽሐፍ ቅዱስ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው አበው ከጻፉት ምስክር አላመጣም። ይህም የሚጠቍመው ይህ አመለካከትም ኾነ ትምህርት ምንጩ እስትንፋሰ እግዚአብሔር የኾኑት ቅዱሳት መጻሕፍት (መጽሐፍ ቅዱስ) አለመኾናቸውን ነው። “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ሥርዐተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት” የተሰኘው የቤተ ክርስቲያኒቱ መጽሐፍም ምንም ማስረጃ ሳያቀርብ “ድንግል ማርያም ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች ክብሯ ከፍ ያለ ነው” በማለት ይህን ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት አጽንቶታል (ገጽ 50)።
በመሠረቱ ቅድስት ማርያም ቃልን በሥጋ ለመውለድ ከሴቶች መካከል የተመረጠች በመኾኗና እግዚአብሔር በእርሷ ታላቅ ነገርን በማድረጉ “መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ” የሚል ደረጃ ሳይወጣለት ክብሯ ከፍ ያለ መኾኑን ክርስቲያን የኾነ ኹሉ ይገነዘበዋል። የወጣላት ደረጃ ግን እርስዋን በማክበር ስም ወደ ማምለክ እንዳሸጋገራት በተግባር እየኾነ ካለው በግልጽ መረዳት ይቻላል። ቤተ ክርስቲያኒቱ በዚህ ረገድ አላት የሚባለው ትምህርት እና በካህናቱም ኾነ በሕዝበ ክርስቲያኑ አመለካከት ውስጥ ያለው ግንዛቤና በዚያ ላይ ተመሥርቶ የሚታየው ልምምድም ከዚያ የተለየ ኾኖ እናገኘዋለን። ይህን ጉዳይ ለማስተንተን “መድሎተ ጽድቅ” ከመጽሐፍ ቅዱስ ወይም በዚያ ላይ ከተመሠረተው የአበው ትምህርት እንጂ አዋልድ መጻሕፍት የሚሉትን እንዳንጠቅስ፣ “በግል ጸሎትና ለታሪክ፣ እንዲሁም ይህን ለመሳሰለው ተግባር ያሉትን ነገሮች በመጥቀስ አይደለም” (ገጽ 38) በማለት በሩን ሊዘጋ ፈልጓል። ምክንያቱ ደግሞ “ከንቱ የሐሰት ውንጀላ ነው” ሲል አስቀድሞ የደመደመው ሐሳቡ የሚፈርስበት መኾኑ ቀድሞ ስለሚያውቅና እያልነው ያለው እውነት እንጂ ሐሰት አለመኾኑ ስለሚጋለጥበት ነው። ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ የሌለውን ከየት ማምጣት ይቻላል? ያው ትምህርቶቹ ከበቀሉበት ከአዋልድ መጻሕፍት ነው እንጂ።
በሌላም በኩል የጻፍነው ጉዳይ እውነትና መረጃውም በአዋልድ መጻሕፍትና በሕዝቡ አመለካከትና ልምምድ ውስጥ የሚገኝ መኾኑን ስለሚያውቅና በእነርሱ አስረጂነት እንዳንከራከረው ለማድረግ እንደ ኾነ ግልጽ ነው። በግል ደረጃ ያሉት ብቻ ሳይኾኑ በቤተ ክርስቲያኒቱ ደረጃ ተቀባይነት አግኝተው በአገልግሎት ላይ የዋሉት አንዳንድ የጸሎትና የአምልኮት መጻሕፍትም፣ ፍጡርን ከፈጣሪ ጋር የማስተካከል ነገር ይታይባቸዋል። ያም ቢኾን፣ በዚህም ኾነ በሌላው ስለ ማርያም በጻፈበት ክፍል ውስጥ ለአነጋገር ያኽል ብቻ፣ “እኛ ይህን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን እምነት እየገለጽን ያለነው፣ ወደፊትም በየጉዳዩ የምንገልጸውና ምስክር የምንጠቅሰው ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቀደምት ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ትምህርት” ነው ይበል እንጂ፣ ከላይ እንዳልነው “ማርያም መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ ናት” የሚለውን ይህን እንግዳ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ አስረጂነት ለማሳየት ያቀረበው ምስክር የለም።
“መድሎተ ጽድቅ” እንደሚለው፣ ይህ ምንጩ ያልታወቀ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስም ኾነ በአበው ትምህርት ውስጥ ስለሌለ፣ የግድ ወደ አዋልድ መጻሕፍት መኼድና የእነርሱ መልእክት፣ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ዕውቀት ማነስ የተነሣ የሕዝቡን አመለካከት እንዴት በተሳሳተ አቅጣጫ እንደ መራው መፈተሽ፣ ማርያም “መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ” ሳትኾን ከፈጣሪ ጋር ተስተካክላ ወደ መመለክ መሸጋገሯንም ማረጋገጥ እንችላለን። ምክንያቱም ከላይ እንደ ተገለጸው መጽሐፍ ቅዱስም ኾነ በዚያ ላይ የተመሠረተው የአበው ትምህርት፣ ማርያም “መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ” የሚል ደረጃ አላወጡምና።
በመጀመሪያ ማስረጃ አድርገን የምንጠቅሰው ደቂቀ እስጢፋኖስንና እምነታቸውን ለመቃወም እንደ ተደረሰ በሚነገርለት “መስተብቍዕ ዘመስቀል” (ደቂቀ እስጢፋኖስ በሕግ አምላክ 1996፣ ገጽ 36) የተሰኘውን ድርሰት ነው። ይህ ድርሰት በግል የሚጸለይ ሳይኾን በቤተ ክርስቲያን የማኅበር ጸሎት ላይ ዘወትር በተለይ ነገረ መስቀሉ በሚታሰብባቸው ዕለታት በረቡዕ፣ በዐርብ እና በቀዳሚት ሰንበት (ቅዳሜ)፣ እንዲሁም በበዓለ መስቀል ካህናቱና ሕዝቡ በመቀባበል በዜማ እና/ወይም በንባብ የሚያደርሱት ጸሎት ነው። መቼም በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዐተ አምልኮት ውስጥ ተካትቶ የሚገኘውንና ዘወትር በሥራ ላይ የሚውለውን ይህን ጸሎት፣ “የግል” ጸሎት ብቻ አድርጎ መመልከት፣ ወይም ድርሰቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ  ድርሰት አይደለም ማለት አይቻልም። ይህ ድርሰት “መድሎተ ጽድቅ” እንደሚለው ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ጋር ተቃርኖ ያለው ቢኾንም እንኳ፣ ፍጡርና ፈጣሪን እኩል ያደርጋል። ለእሉ ክልኤቱ ፍጡራን ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ። - ለእነዚህ ለኹለቱ ፍጡራን (ለማርያምና ለዕፀ መስቀል) የፈጣሪ ክብር ይገባቸዋል። በክብራቸው ከፈጣሪ ጋር ተካክለዋልና”  የሚለው ንባብ ለዚህ አስረጂ ነው።  
ይህ ድርሰት የሚለው “የፈጣሪ ክብር” ወይም “ለፈጣሪ ሊሰጥ የሚገባው ክብር” ለማርያምና ለዕፀ መስቀልም ይገባቸዋል ነው። ለምን? ቢባል “በክብራቸው [ከፈጣሪ ጋር] ተካክለዋልና” የሚል ምክንያት ቀርቧል። መቼም ይህ መተካከል አንዳንዶች እንደሚሉት በኹለቱ ፍጡራን (በማርያምና በመስቀል) መካከል የኾነ ሳይኾን፣ ከፈጣሪ ጋር መኾኑን ከግእዙ ገጸ ንባብ መረዳት ይቻላል። መስተብቍዕ ዘመስቀል ስሕተት ነው ከማለት ይልቅ ስሕተቱን ለመሸፈን ተብሎ ማርያምና መስቀልን እኩል ለማድረግ መሞከርም ሌላ ስሕተት መፍጠር ነው የሚኾነው።
“መድሎተ ጽድቅ”፣ ማርያም “… ‘እንደ እግዚአብሔር በኹሉ ስፍራ ትገኛለች ኹሉን ታውቃለች’ የሚል እምነትም ኾነ አስተምህሮ የለም። በኹሉ ስፍራ መገኘት (ምሉዕ በኵለሄነት) እና ኹሉን ዐዋቂነት (ማእምረ ኵሉ መኾን) የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቦች ብቻ መኾናቸው የታወቀ ነው። ስለዚህ ቅድስት ቤተ ርስቲያን ፈጣሪና ፍጡርን አሳምራ ለይታ የምታውቅ ናት እንጂ ‘ፍጡራንን ከፈጣሪ እኩል ማድረግና ማስተካከል’ የሚለው አይመለከታትም።” በማለት የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ይህ መኾኑን ገልጿል። ገለጻው ትክክለኛ ቢኾንም በተግባር የሚታየው ግን በተቀበረ መክሊት የተገለጸው መኾኑን ማስተባበል አይቻልም። ደግሞም “መድሎተ ጽድቅ” ለጽሑፎቻችን ምላሽ መስጠትን ተገን በማድረግ ስላቀረበው እንጂ ራሱን ችሎ፣ “ማርያም እንደ እግዚአብሔር በኹሉ ስፍራ አትገኝም፤ ኹሉንም አታውቅም” ብሎ ቢያስተምር ምን ይገጥመው ነበር? ብንል የሚገጥመውን መገመት አያስቸግርም።
እዚህ ላይ እውነተኛው ትምህርት “መድሎተ ጽድቅ” ያለው ነው። አስተምህሮው ብቻ በአንዳንዶች ዘንድ ይገኛል እንጂ፣ በብዙዎች የሚታመነው ግን ከአስተምህሮው በተቃራኒ እንደ ኾነ ለማንም ግልጽ ነው። ለምሳሌ በጥር 21 ቀን በሚከበረው የቅድስት ማርያም በዓለ ዕረፍት አብዛኛው ካህንና ምእመን በሚገኝበት፣ በማርያም ስም በታነጸ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በዕለቱ ማርያም እንዳለች፣ የሚቀርብላትን ውዳሴና ዝማሬም እንደምትሰማ አደርጎ ነው የሚያስበው። ማርያምን ምልዕት በኵለሄ አድርጎ ካላሰበ በቀር እንዴት በቍጥር እጅግ በርካታ በኾኑትና በአገር ውስጥ በከተማና በገጠር እና ከአገር ውጪም በስሟ በታነጹ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በአንድ ጊዜ እንደምትገኝ ሊያስብ ይችላል? ይህ ደግሞ በግልጽ የሚስተዋል ነው። ፕሮፌሰር ጌታቸው ኀይሌ ስለ አትሮንሰ ማርያም ታቦት ታሪክ በጻፉት ጽሑፍ መግቢያ ላይ ያሰፈሩት ጽሑፍ ይህን ይጠቍማል፤[1]
እያንዳንዱ ታቦት በጳጳስ ወይም በኤጲስ ቆጶስ ከተባረከ ወይም ከቅዱሳን (መላእክት፣ ሰማዕታት፣ ቅዱሳን መነኮሳት፣ ወዘተ.) ስሞች በአንዱ ስም ወይም ከእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ስሞች (እግዚአብሔር አብ፣ ዐማኑኤል፣ ኢየሱስ፣ መድኀኔ ዓለም፣ ወዘተ.) ከተሰየመ በኋላ መታሰቢያ ተደርጎ ይሰጣል። በዚህ ጊዜ ታቦት በቅዱሳን ስም የሚጠራ ብቻ ሳይኾን፥ የቅዱሳኑን፣ ወዘተ. የተጠራበትን ስም ባለቤት የሚያመለክት ወይም የሚወክለው ወደ መኾን ይሸጋገራል። በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን አስተሳሰብ፥ እግዚአብሔር ወይም አንዱ ቅዱስ ወይም ቅድስት ርሱ/ርሷ በታቦት ተመስሎ/ላ በዚያ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይኖራል/ትኖራለች። ለምሳሌ፦ ለማርያም መታሰቢያ በተደረገ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፥ ማለትም ለማርያም መታሰቢያ ተደርጎ የተሰጠ ታቦት በሚኖርበት ማርያም ራሷ ትኖራለች ማለት ነው፤ ምክንያቱም በዚያ የምትኖረው ማርያም፥ ማለት ታቦቷ እንዲሁ ለማርያም መታሰቢያ ተደርጋ የተሰጠች መታሰቢያ ብቻ አይደለችምና። ታቦት ቅዱሳኑን የሚወክል ስለሚኾን የቅዱሳኑን ጾታ ይወስዳል። ማርያም ታቦቷ ሴት ናት (በሴት አንቀጽ ነው የምትጠራው)። (Getatchew Haile “A HISTORY OF THE TABOT OF ATRONƎSÄ MARYAM IN AMHARA (ETHIOPIA)” Paideuma, Bd. 34, pp. 13-22.1988, 14.)  
            ፕሮፌሰር ጌታቸው በሕዝቡ ዘንድ ያለውንና የሚስተዋለውን እውነታ ነው በጽሑፍ ያሰፈሩት። ይህ አስተሳሰብና ልምምድ በጊዜ ብዛት በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የዳበረና በብዙዎች ዘንድ ስፍራ ያገኘ አመለካከት እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ግን የለውም። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የቆመውን ነገረ መለኮት የሚቃረን ኾኖ ይታያል። ይህን “መድሎተ ጽድቅ” ጭምር የተስማማበት እውነት ነው።
ከላይ የተገለጠው አስተሳሰብ ግን፥ ፍጡራን በኹሉ ስፍራ ይገኛሉ ወደሚል ስሕተት ይመራል። ለምሳሌ፦ በማርያም ስም የተሰየመች ታቦት ባለችበት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ “ማርያም አለች” ብሎ ማሰብ፣ ማርያም በኹሉ ስፍራ ትገኛለች እንደ ማለት ይቈጠራል። ምክንያቱም ይህ የሚኾነው በአንድ ስፍራ ብቻ ሳይኾን፣ ከላይ እንዳየነው በኹሉም በማርያም ስም የተሰየሙ ታቦታት ባሉባቸው ሕንጻተ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኹሉ ነውና። ይህን ለመገመት በኢኦተቤ ውስጥ በማርያም ስም የተሰየሙ ስንት ታቦታትና ሕንጻዎች አሉ? የሚለውን መጠየቅና ብዛቱን መረዳት፥ ከዚያ ማርያም በእነዚህ ኹሉ ስፍራዎች በአንድ ጊዜ እንደምትገኝ ማሰብ ነው። ነገር ግን ማርያም ፍጡር እንደ መኾኗ በስፍራ የተወሰነች ናት እንጂ፥ እንደ ፈጣሪ በኹሉ ስፍራ የምትገኝ አይደለችም።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ለ2008 ዓ.ም. ጾመ ፍልሰታ ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን ውስጥ ይህን ልምምድ ሊያጸና የሚችል ወይም ተመሳሳይነት ያለው መልእክት እንዲህ ሲሉ አስተላልፈው ነበር፤ “ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ‘እነኋት እናትህ’ ከተባለበት ሰዓት ጀምሮ እመቤታችንን ወስዶ በቤቱ አኑሮአታል፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እመቤታችን በእያንዳንዱ አማኝ ልጇ ቤት በመንፈስ እየገባች ትኖራለች።” (www. addisababa.eotc. org.et /site/en/news/343, 2008)።
ይህ የቅዱስነታቸው መልእክት፥ ከላይ በፕሮፌሰር ጌታቸው ከተጠቀሰው የማርያምን በአንድ በስሟ በታነጸ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መገኘት እጅግ ሰፋ አድርጎ ወደያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ ቤት ድረስ ያወርደዋል። ነገር ግን ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው የክርስትና ትምህርት ፈጽሞ የራቀና ከላይ በተጠቀሰው ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተሳሰብ ላይ የቆመ እንደ ኾነ መመልከት ይቻላል። ስለ ዮሐንስ “እነኋት እናትህ” ተብሎ የተነገረው ቃል፣ ለምእመናን ኹሉ እንደ ተነገረ ተደርጎ በልማድ ሲጠቀስ መስማት የተለመደ ቢኾንም፣ ቃሉ ከዮሐንስ ዐልፎ ግን ለምእመናን ኹሉ የተነገረ አይደለም። ዮሐንስ፣ “እነኋት እናትህ” የተባለው፣ ቅድስት ማርያም ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መከራ ሲቀበል ካየችው በላይ፣ የሞትን ጽዋ ሲጐነጭ ተመልክታ፣ የበለጠ ሐዘን እንዳይከብድባት ብሎ እንደ ኾነ ከዐውደ ምንባቡ እንገነዘባለን። የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ድርሰት በኾነው “ጸሎተ ሰብዓቱ ጊዜያት” ውስጥም ይህን የሚያረጋግጥ ምስክር እናገኛለን።
“ሐዘነ ማርያም እምከ ነጺረከ ለዘታፈቅሮ ሐዋርያ፣
ትቤሎ እምከ ነያ፣
ከመ ትናዝዝ ብዝኀ ብካያ …”
ትርጕም፦  “የእናትህን የማርያምን ሐዘን ተመልክተህ፣ ከልቅሶዋ ብዛት ታረጋጋ ዘንድ፣ ለምትወደው ሐዋርያ እነኋት እናትህ አልኸው።” (ጸሎተ ሰብዐቱ ጊዜያት)።
ቀደም ሲል ይህን፣ “እነሆ ልጅሽ … እነኋት እናትህ” የሚለውን ቃል፣ በዐውደ ምንባቡ መሠረት ሊቃውንት ይረዱት የነበረው በዚህ መልኩ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታዲያ ለዮሐንስ፣ ለዚያው ጊዜ ብቻ የተነገረው ይህ ቃል፣ ለምእመናን ኹሉ የተነገረ ነው የሚባለው በምን ምክንያትና በምን መሠረት ይኾን? እርሷ አኹን በዐጸደ ነፍስ ባለችበት ኹኔታ ዮሐንስ እንዳደረገው የማንም ርዳታ አያስፈልጋትምና፣ ያም ሐዘኗ በደስታ ተተክቷልና ምእመናን እርሷን ወደ ቤታቸው የሚወስዱበት ምክንያትም፣ አግባብም፣ መንገድም የለም፤ አይኖርምም። እርሷም ደግሞ በያንዳንዱ አማኝ ልጇ ቤት በመንፈስ እየገባች የምትኖርበት ምክንያትም፣ አግባብም፣ መንገድም ፈጽሞ የለም።
            ምናልባት ይህን እንግዳ ትምህርት፣ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “እኔ ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልኾን፣ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ” ካለው ቃል ጋር ለማጠጋጋት ይታሰብ ይኾናል። ነገር ግን ሐዋርያው ይህን ለቆሮንቶስ ሰዎች የተናገረው በዐጸደ ሥጋ ሳለ ነበር። እንዲህ ያለውም፣ በሥጋ ከእናንተ ርቄ ብኖርም፣ በመንፈስ በኹሉ ስፍራ እገኛለሁ ለማለት ግን አልነበረም። በሐሳብ ከእናንተ ጋር በመስማማት ዐብሬያችሁ እንዳለሁ ቍጠሩኝ ለማለት ነው እንጂ። ከዐውደ ምንባቡ የምንረዳው ይህንኑ ነው።
በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በነበረውና የአባቱን ሚስት ባገባው ሰው ላይ ስለሚወሰደው የሥነ ሥርዐት ርምጃ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፤ “ከእናንተም ጋር እንዳለሁ ኾኜ፣ ይህን እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አኹን ፈርጄበታለሁ፤ እናንተና መንፈሴም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ኀይል ጋር ተሰብስበን፣ መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው” ብሏል (1ቆሮ. 5፥3-6)። ይህም በአካል በመካከላቸው ሳይገኝ በሐሳብ ዐብሮ በመኾን፣ መወሰድ ባለበት ርምጃ መስማማቱን ለመግለጥ እንደ ኾነ ዐውደ ምንባቡም፣ በጥቅሱ ውስጥ የምናገኛቸው አንዳንድ ቃላትም ያረጋግጡልናል። ለምሳሌ፡- “ከእናንተ ጋር እንዳለሁ ሆኜ” ሲል፣ በአካል እዚያ እንደማይገኝ ግልጽ አድርጓል። “እናንተና መንፈሴም . . . ተሰብስበን” ሲልም፣ የጳውሎስ መንፈስ ከእርሱ ወጥቶ፣ እርሱ በአካል ባልተገኘበት ስፍራ ከቆሮንቶስ ቅዱሳን ጋር ይሰበሰባል ማለት እንዳልኾነ ግልጽ ነው። ነገር ግን ከእነርሱ ጋር እንዳለ ኾኖ በመልእክቱ የሰጠው ፍርድ በመፈጸሙ የሚስማማ መኾኑን ለማመልከት ነው።
ከዚህ አንጻር የጌታ እናት ቅድስት ማርያም አኹን በዐጸደ ነፍስ ባለችበት ኹኔታ “በያንዳንዱ አማኝ ልጇ ቤት በመንፈስ እየገባች ትኖራለች” መባሉ፣ ከክርስትና ትምህርት አንጻር ፍጹም ስሕተት ነው። እርሷ ከሴቶች መካከል ተለይታ የጌታ እናት እንድትኾን በእግዚአብሔር የተመረጠች ብትኾንም፣ ከሰውነት ደረጃ ወጥታ ወደ አምላክነት ደረጃ ከፍ ብላለች ማለት ግን አይደለም። በሌላ አነጋገር በስፍራ የተወሰነች ፍጡር መኾኗ ቀርቶ በኹሉ ስፍራ የምትገኝ ፈጣሪ ኾናለች ማለት አይደለም፤ በእያንዳንዱ አማኝ ቤት በመንፈስ ለመገኘት ፈጣሪ መኾንን ይጠይቃልና። ስለዚህ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት የሚቃረን ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ፣ ኢክርስቲያናዊም አስተሳሰብ በመኾኑ ሊታረም የሚገባው ነው። “መድሎተ ጽድቅ” ይህን በፓትርያርኩ ደረጃ እንኳ እየተነገረ ያለውን ወደ ጐን ብሎ ቤተ ክርስቲያኗ እንዲህ አታምንም እንዴት ይላል? እውነታው ይህ ስለ ኾነ መጀመሪያው ላይ “መድሎተ ጽድቅ” “ከንቱ የሐሰት ውንጀላ ነው ያለውን ሐሰት ወደ ቦታው (ወደ ራሱ) መልሰን ወደ ሌላው ነጥብ እናልፋለን።
“ሌላው ውሸታቸው” ብሎ “መድሎተ ጽድቅ” የጠቀሰው ደግሞ “በአራተኛው ምእት ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ላይ የሐዋርያትን ሲኖዶስ በመሻር አይሁድን የሚበቀል ውሳኔ ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች መነጨ። አይሁድ ክርስትናን የሚቀበሉ ከኾነ በቅድሚያ ወደ አሕዛብነት መፍለስ አለባቸው ተባለ። … አይሁድ ወደ ወንጌል ሲመጡ (ክርስቲያን ሲኾኑ) የግዝረትን ሕግ ሕገ ኦሪትን የመሥዋዕትና የመቅደስ ሥርዐታቸውን ከምድረ ግብጽ የወጡበትን የነጻነት በዓላቸውን ፋሲካን እነዚህን የመሳሰሉትን የማንነታቸውን መታወቂያዎች ማስቀመጥና የአሕዛብ ማንነት የተንጸባረቀባቸውን መታወቂያዎች መያዝ አለባቸው ተብሎ በኒቅያ ጉባኤ ሲወሰን ውሳኔው አይሁድን ከወንጌል ውጪ አደረጋቸው። አይሁዶች ግርማዊነትም የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ ዶክተር ዮራን ላርሰን ይህን ውሳኔ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ እንደ አንድ ትልቅ አሳዛኝ ጉዳይ አድርጌ እመለከተዋለሁ ይላሉ። (ጮራ ቍ 24፣ ገጽ 1-2)።” (መድሎተ ጽድቅ 39)።
“የሰው ዘር ኹሉ በራሱ ስፍራ ባህል ሃይማኖት ውስጥ እንዳለ ኾኖ በወንጌል የተገለጸውን የእግዚአብሔር ጽድቅ መቀበል መቻሉ መዘንጋት የለበትም (ጮራ ቍ. 24 ገጽ 1)።” (መድሎተ ጽድቅ 41)።
ከተጠቀሰው የጮራ መጽሔት ላይ የተወሰዱት እነዚህ ሐሳቦች፣ በመጽሔቱ ሊገለጽ የተፈለገውን ሳይኾን፣ ለራሱ እንዲመቹት አድርጎ “መድሎተ ጽድቅ” በተዛባ መንገድ ያቀረባቸው ናቸው። በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቍጥር 24 ላይ “ወንጌል ድብቅ ዐላማ የለውም” በሚል ርእስ የቀረበው ርእሰ አንቀጽ ፍሬ ነገር፣ ወደ ዓለም ኹሉ በመኼድ ለፍጥረት ኹሉ እንዲሰበክ የተላከው ወንጌል፣ ሰዎች በየሚገኙበት ኹኔታ እንዲሰበክላቸው እንጂ የእነርሱን ባህልና ሃይማኖት በማስተው የሌላውን የመጫን ተልእኮ የሌለው መኾኑን የሚናገር ነው።
በዚህ ውስጥ “መድሎተ ጽድቅ” እንደ መጫወቻ ካርታ ሊጠቀምበት የሞከረው ታዲያ “ሃይማኖት” የሚለውን ቃል ነው። “ሰው በራሱ ስፍራና ባህል ኾኖ ወንጌልን መቀበል መቻሉ እውነት ነው። ኾኖም ‘በራሱ ሃይማኖት ውስጥ እንዳለ ኾኖ በወንጌል የተገለጸውን የእግዚአብሔር ጽድቅ መቀበል መቻል መዝንጋት የለበትም’ የሚለው ግን የሚገርም ነው። እያንዳንዱ ሃይማኖት ስለ ሕይወት ስለ ሰው መዳን ስለ ጽድቅና ኵነኔ ወዘተ የሚለው የየራሱ ትምህርት አለው። በወንጌል የተገለጸው የእግዚአብሔር ጽድቅ ደግሞ በሌላ በማንኛውም ሃይማኖት ከተገለጸው የመዳን መንገድ የተለየ ነው። ለምሳሌ፦ ስለ ሕይወትና ስለ መዳን ምንነት እንዴትነት ስለ ሰው ሕይወት ግብና ፍጻሜ ወዘተ ቡድሂዝም የሚለው እስልምና ከሚለው፣ እነዚህ የሚሉት ፓንቴይዝም ከሚለው፣ ዞራስትሪያኒዝም የሚለው ሂንዱይዝም ከሚለው፣ … አንዱ የሚያምነውና የሚለው ሌላው ከሚያምነውና ከሚለው የተለየ ነው፤ ክርስትና የሚለው ደግሞ ከእነዚህ ኹሉ የተለየ ነው። እንዲያማ ባይኾን ኖሮ በክርስትና እና በሌሎቹ እምነቶች መካከል ልዩነት ባልኖረ ነበር።” እያለ ማደናገሩን ይቀጥላል።
የተሳሳተ ሐሳቡን በጥቅስ ለማስደገፍም፦ “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ ጽድቅ ከዐመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና ብርሃን ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው ከርስቶስ ከቢልሆር ጋር ምን መስማማት አለው ወይስ የሚያምን ከማያምን ምን ክፍል አለው ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው” (2ቆሮ. 6፥14-16)። የሚለውን ቃል እንደ ለመደው አለቦታውና አለዐውዱ ይጠቅሳል። ይህ ቃል ከማይመስሉን ጋር በማይመች አካኼድ ወይም በኀጢአት መንገድ ኅብረት ማድረግ እንደሌለብን የሚናገር እንጂ፣ በተለያየ ሃይማኖት ውስጥ ያሉ ሰዎች በሃይማኖታቸው ውስጥ ኾነው ወንጌል ሊሰበክላቸው አይገባም የሚል አይደለም።
ሃይማኖት የሚለው ቃል ሰፊና አሻሚ ትርጉም ያለው ቃል እየኾነ መምጣቱ ይታወቃል። በተለይ በዚህ ዘመን አንድን የሃይማኖት ተቋም የሚወክልና የሚገልጽ ቃል ወደ መኾን እየተሸጋገረ ነው። ቀደም ሲል ግን መጽሐፍ ቅዱስ “ሃይማኖት” የሚለው ትርጉሙ እንዲህ አልነበረም። ሰዎች የፈጠሩትን የሃይማኖት ተቋም ሳይኾን የእግዚአብሔርን እውነተኛነት ይልቁንም ለመዳን በክርስቶስ ላይ መደገፍን የሚያሳይ ቃል ነው። ስለዚህ የሰው ዘር በራሱ ሃይማኖት እንዳለ ኾኖ በወንጌል የተገለጸውን የእግዚአብሔርን ጽድቅ መቀበል ይችላል ማለት ስሕተት አይደለም። እንዲህ ሲባል ግን  የወንጌል እምነትና የግለሰቡ ሃይማኖት ተዳብለው ዐብረው ይኼዳሉ ማለት አይደለም። ሰው በወንጌል የተገለጸውን የእግዚአብሔርን ጽድቅ በእምነት ሲያገኝ ለእግዚአብሔር መኖር ይጀምራል።  
እዚህ ላይ የሚስተዋለው የ“መድሎተ ጽድቅ” ችግር የወንጌልንና የሃይማኖትን ልዩነት አለማወቁ ነው። የጮራ ርእሰ አንቀጽ ያተኰረው በአይሁድና በአሕዛብ መካከል የነበረውን የባህልና የሃይማኖት ልዩነትና ኹለቱም ወገኖች ባሉበት ሃይማኖትና ባህል ውስጥ ኾነው በወንጌል የተገለጸውን የእግዚአብሔር ጽድቅ መቀበል መቻላቸውን ነው። ይህን ለማሳየትም በሮሜ መልእክት 1፥29-30 የተጻፈውን ቃል ነው የመልእክቱ ማጠንጠኛ ያደረገው። “እግዚአብሔር የአይሁድ አምላክ ብቻ ነውን? የአሕዛብስ አምላክ አይደለምን? አዎን የአሕዛብም አምላክ ነው። የተገረዘውን በእምነትያልተገረዘውንም በዚያው እምነት የሚያጸድቅ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነውና” (ዐ.መ.ት)። ልብ እንበል ለወንጌል የቀረበ ሃይማኖት የአይሁድ ነው ተብሎ፣ አሕዛብ አስቀድመው ወደ አይሁድ እምነት እንዲገቡ፣ ከዚያ በኋላ በወንጌል እንዲያምኑ አልተደረገም። አሕዛብን በራሳቸው ማንነት ሳሉ መገረዝ ሳያስፈልጋቸው በእምነት እግዚአብሔር ያጽድቃቸዋል። አይሁድም በሥርዐተ ግዝረት እየኖሩ በእምነት የሚገኘውን ጽድቅ ሊወርሱ ይችላሉ፤ “የተገረዘውን በእምነት . . . የሚያጸድቅ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነውና።”
በመኾኑም በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15 ላይ አሕዛብን ወደ ይሁዲነት ለማፍለስ በአንዳንድ ሰባክያን ይደረግ የነበረውን ጥረት የሚከለክል ውሳኔ ሐዋርያት ማስተላለፍ ችለው ነበር። እንዲህ በማለት፦ “ ከአሕዛብ ወደ እግዚአብሔር የዞሩትን እንዳናስቸግራቸው፥ ነገር ግን ከጣዖት ርኵሰትና ከዝሙት ከታነቀም ከደምም ይርቁ ዘንድ እንድንጽፍላቸው እቈርጣለሁ። … ለጣዖት ከተሠዋ፥ ከደምም፥ ከታነቀም፥ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና፤ ከዚህም ኹሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ።” (ቍ. 19፡20፡28-29)። ይህ ለአሕዛብ አማኞች የተወሰነው ከአይሁድ አንጻርም ለአይሁድ ይሠራል። ይኹን እንጂ በአሕዛብ ዘመን የሐዋርያትን ሲኖዶስ በመሻር በሌላ ገጽ አይሁድን የሚበቀል ውሳኔ በኒቅያ ጉባኤ መተላለፉን መገንዘብ ይቻላል። የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ በኒቅያ ጉባኤ የተወሰኑ 20 ቀኖናዎች ብቻ መኾናቸውንና አንቀጸ ሃይማኖትን አርቅቀው መለያየታቸውን በጕልሕ በመጥቀስ፣ “ከዚሁ ጋር የትንሣኤ በዓል የሚውልበትን ዕለት አወሳሰን በተመለከተ የይትበሃል ልዩነቶች ስለ ነበሩ እነርሱን ወደ አንድነት የሚያመጡ ውሳኔዎችን ወሰኑ።” በማለት አድበስብሶ ያለፋቸው ሌሎች ውሳኔዎችም መኖራቸውን የሚጠቍም እንደ ኾነ መመልከት ይቻላል። ዝቅ ብሎም “የኒቅያ ጉባኤ የአርዮሳውያንና የአይሁዳውያን በእውነትም አከርካሪያቸው የተመታበት ጉባኤ ነበር፤ ምክንያቱም የእነርሱ ስሕተታቸው የተጋለጠበትና በዓለም ዐቀፋዊ መድረክ የተወገዘበት ውሳኔ ስለ ኾነ ነው።” (ገጽ 40) በማለቱ በኒቅያ ጉባኤ አይሁድን የተመለከተ ውሳኔ መተላለፉን በተዘዋዋሪ አምኗል።
ዮራን ላርሰን ግን፣ “በ325 በኒቅያ ጉባኤና በዚሁ ዘመን በተደረገ ሌላ ጉባኤ ለክርስቲያኖች ሰንበትን ማክበር፣ በፋሲካ ጊዜ እርሾ የሌለበት ቂጣ መብላት ወይም ማንኛውንም የአይሁድ ልማድ መከተል እንደሌለባቸው በይፋ ታወጀ። አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ይህንን ድንጋጌ ባይቀበሉ ከቤተ ክርስቲያን ይታገዱ ነበር። ከዚያ በኋላ አይሁዶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመምጣት የግድ አሕዛብ መኾን ነበረባቸው!” ካሉ በኋላ በዚህ ዘመን ክርስትና በታሪኩ ከመጀመሪያው የዐዲስ ኪዳን ዘመን አስተሳሰብ መራቁን በማስረጃ አስደግፈው ያቀርባሉ። ይኸውም የመጀመሪያዎቹ አይሁድ ክርስቲያኖች ‘አሕዛብን ወደ ኅብረተሰባቸው ለመቀበል ማንነታቸውን መለወጥ ሳያስፈልጋቸው ወይም ወደ ይሁዲነት ሳይገቡ እንዳሉ ኾነው ሊቀበሏቸው እንደ ወሰኑ፣ በዚህ ዘመን የነበረችው የአሕዛብ ቤተ ክርስቲያን ግን አይሁድ ክርስቲያን መኾን ካለባቸው ይሁዲነትን መተውና እንደ እኛ መኾን አለባቸው የሚል መንገድን እንደ ተከተሉ ጠቅሰዋል (ዮራን ላርሰን፣ አይሁዶች ግርማዊነትዎ፣ (ትርጉም፦ ጣልአርጌ የሺድንበር (ዶ/ር)፣ (ዐዲስ አበባ፦ ብራና ማተሚያ ድርጅት፣ 1993 ዓ.ም.፣) 38፡39።
በዐፄ ገላውዴዎስ የሃይማኖት ውሳኔ ላይ “የታሪክ መጽሐፋችን ‘ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በግዛት ዘመኑ የተጠመቁትን አይሁድ ኹሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ዕለት ያሳማ ሥጋ እንዲያበሏቸው አዘዘ’ የሚል ጽሑፍ አለ።” የሚል ሐሳብ ሰፍሯል (አባ ጎርጎርዮስ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ (ዐዲስ አበባ፦ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ 1974 ዓ.ም.፣ 178-179)። ይህም አይሁድን ከሃይማኖታቸው ሥርዐት የሚያወጣቸውና የሌላውን ባህል የሚጭንባቸው ድርጊት ኾኖ የሚታይ ሲኾን፣ በቈስጠንጢኖስ አማካይነት ከላይ የተባለው ነገር መወሰኑንና መፈጸሙን ያመለክታል። ኾኖም አይሁድም ኾኑ አሕዛብ በተለያዩ ዘመናት ከወንጌል ዐላማ በተቃራኒ በመኼድ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ብዙ ችግር ያደረሱና ከወንጌል ተልእኮ ውጪ የነበሩ ጥፋቶች የፈጸሙ መኾናቸው የእግዚአብሔር ሐሳብ እንዳልኾነ ግልጽ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚመሰክረው ቅዱስ ወንጌል የማይለወጥና ለዘላለም ድኅነት የሚኾን ነው (ማር. 16፥8)። ይህ መልእክቱ የማይለወጥ ወንጌል በተለያየ የዓለም ክፍል፣ በልዩ ልዩ ባህልና ሃይማኖት ውስጥ ለሚገኝ የሰው ዘር ኹሉ ይሰበካል። ወንጌል የተሰበከላቸው ሰዎች የወንጌልን መልእክት አንድም ሳያዛቡ፣ ሳይጨምሩበትና ሳይቀንሱለት በእምነት ሊቀበሉትና ሊድኑበት ይገባል። ወንጌልን ሲቀበሉ ግን እንዲኖሩ በተወሰነላቸው ቦታ የያዙትን ባህል፣ ሃይማኖትና ማንነታቸውን እንዲለውጡ አይጠበቅም። ክርስትና መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ሲኾን፣ የሚራመድበት ባህለ ሃይማኖት ግን እንደየሀገሩ ልዩ ልዩ ነው። ለምሳሌ ዐምስቱ ኦሬንታል የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት አስተምህሮ ተመሳሳይ መኾኑ ይነገራል። ባህለ ሃይማኖቱ ግን ልዩ ልዩ ነው። የባህለ ሃይማኖቱ መለያየት የተፈጠረው ግን የተለያየ ወንጌል ስላመኑ ሳይኾን፣ በአንዱ ወንጌል ያመኑ ቢኾንም ወንጌሉ የተዘራበትና የበቀለበት ባህለ ሃይማኖት ልዩ ልዩ ስለ ኾነ ነው። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከክርስትናው ዓለም ጋር አንድ የሚያደርጋት መሠረተ እምነት ያላት ቢኾንም፣ ኦሬንታሉን ጨምሮ ከሌላው ዓለመ ክርስትና የምትለይበት የራሷ ባህለ ሃይማኖት አላት። ከዚህ ልዩነት የተነሣ እንዲያውም አንዳንዶች “ከብዙ አንጻር ሲታይ ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖት በኢትዮጵያ የበቀለ እንጂ የተተከለ አይመስልም።” ከማለት ደርሰዋል (ተሾመ ዘሪሁን (መልአከ ታቦር)፣ ዝክረ ነገር፣ (ዐዲስ አበባ፣ ማተሚያ ቤቱ ያልተገለጸ፣ 2009 ዓ.ም.፣) 74)።
ይህን ያልተገነዘበው የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ ግን ወንጌልና ሃይማኖትን በማምታታት ነገሩን ወደማያስኼድና ወዳልተባለ ጽንፍ ይለጥጥና፣ “ይህ አስተሳሰብ አኹን እየተንፀባረቀ ያለው ኹሉም ሃይማኖት ትክክል ነው ወደ እግዚአብሔር ያደርሳል እየተባለ ያለው የዩኒቨርሳሊዝም አስተሳሰብ ነው” ይላል። በማንኛውም ሃይማኖት ውስጥ ላለ ሰው በሃይማኖቱ ውስጥ ሳለ ወንጌል ያስፈልገዋል፤ በክርስቶስ ካመነ በወንጌል የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ጽድቅ ማግኘት ይችላል ማለት፣ እንዴት ተብሎ ቢነበብ ነው “ኹሉም ሃይማኖት ወደ እግዚአብሔር ያደርሳል ማለት ነው” ተብሎ የሚተረጐመው? መቼም ቢኾን ኹሉም ሃይማኖት ትክክል ነው፤ ወደ እግዚአብሔር ያደርሳል ማለትና በኹሉም ሃይማኖት ውስጥ ያለ ሰው በወንጌል የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ጽድቅ አግኝቶ ወደ እግዚአብሔር ይደርሳል ማለት የተለያዩ ነገሮች መኾናቸውን ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው ኹሉ ይረዳል። ስለዚህ ከክርስትና ውጪ ላሉት ብቻ ሳይኾን በክርስትና ውስጥ ለሚገኙና ከተመሠረቱበት የወንጌል መሠረት ወደ ባህል ለተንሸራተቱ ኹሉ ወንጌል ሊሰበክላቸውና በክርስቶስ የቤዛነት ሥራ የተዘጋጀውን የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሊያገኙ ይገባል።
ጮራ ለማስተጋባት የፈለገችው ይህ ኾኖ ሳለ፣ “መድሎተ ጽድቅ” ግን ነገሩን አስረዝሞ አርዮሳውያንንና አይሁዳውያንን ደግፈን እንደ ቆምንና የ318ቱን ሊቃውንት የሃይማኖት ውሳኔ እንደ ተቃወምን አስመስሎ የራሱን እርስ በርሱ የተምታታ ሐሳብ ለመሸፋፈን ሞክሯል። ጮራ አርዮሳውያንን በተመለከተ ያላትን ግልጽ ዐቋም ገና በጥዋቱ ከቍጥር 2 ዕትሟ ጀምሮ ገልጻለችና ከ “መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ በቀር ማንም በዚህ ስሟን አላነሣም፤ አያነሣምም። አይሁድን በተመለከተ ከላይ የቀረበው ሐሳብም ከወንጌል ተልእኮ አንጻር የቀረበ መኾኑን በመካድ “እናንተ ከእነ ማን ወገን መኾናችሁን ነግሮናልና እንድናውቃችሁ ስለ ረዳችሁን እናመሰግናችኋለን” ሲል እኛን ኦሪታውያን አስመስሎ ጽፏል። ለኦሪታዊነቱ እንኳ እናንተ ናችሁ የምትቀርቡት። በንግግር ኦሪታዊ አይደለንም ብትሉ እንኳ፣ በሐዲስ ኪዳን፦
“ይሻር የነበረ” (2ቆሮ. 3፥11)፣
“ደካማና የሚናቅ” (ገላ. 4፥9)፣
“ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ” (ቈላ. 2፥17)፣
“የምትደክም፥ የማትጠቅምም” (ዕብ. 7፥18-19)፣
“ምሳሌና ጥላ” (ዕብ. 8፥5)፣
“ነቀፋ ያለበት” (ዕብ. 8፥6)፣ 
“አሮጌና ውራጅ” (ዕብ. 8፥13)፣ ወዘተ. እየተባለ የተገለጠውን ኦሪትን ጠቃሚ ነገር አለው በሚል ይዞ የሚጓዘውና በክርስትና መንፈስ እየተረጐምን እንጠቀምበታለን የሚለው ማን ኾነና?
ሌላው “መድሎተ ጽድቅ” ያነሣው ነጥብ የሚከተለው ነው፣ “ትልቁ ችግራቸውና የችግራቸው ኹሉ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ አለመቀበላቸውና አለማመናቸው ነው። ለዚህም ማሳያ የሚከተሉትን አባባሎች እንመልከት
·         ጌታ ኢየሱስ ግፍዖም እግዚኦ ለእለ ይግፍዑኒ ጽብዖሙ እግዚኦ ለእለ ይጸብኡኒ። አቤቱ በእኔ ላይ ግፍ የፈጸሙትን ሰዎች ፍዳ ግፍዕ ክፈላቸው። እየተጣሉኝ ያሉትን ተጣላቸው ሲል ለአባቱ ክስ አቀርቦ ነበር የሚሉ የሐሰት ምስክሮች ምንም ዛሬ ቢቆምበትም ቅንጣት ታኽል እውነትነት እንደሌለበት የታወቀ ነው (ጮራ ቍ. 3 ገጽ 25-26)
·         “ … አንባቢ ሆይ ሰይጣን ግን ዛሬ በአረማውያን አፍ ሳይኾን ክርስቲያን ነን በሚሉ አፍ ግፍዖሙ እግዚኦ ለእለ ይገፍዑኒ ጽብኦም እግዚኦ ለእለ ይጸብኡኒ እያለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግፍ የዋሉበትን ከሶአቸው ነበር ብሎ ያውም ስቅለቱ በሚታሰብበት ዕለት ስሙን እያጠፋ ነው።” (ጮራ ቍ. 6 ገጽ 25) (መድሎተ ጽድቅ 41)።
ይህ የመዝሙረ ዳዊት 34/35 ክፍል በስቅለት ዕለት በዜማና በውርድ ንባብ ይደርሳል። መድኅነ ዓለም ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ መከራን ላሳዩትና ለሰቀሉት የካህናት አለቆችና አይሁድ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ማለቱ በግልጽ እየታወቀ፣ ከዚህ በተቃራኒው፦ “አቤቱ፥ የሚበድሉኝን በድላቸው፥ የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው” ብሏል ብሎ ይህን ክፍል በስቅለት ዐውድ ውስጥ እርሱ እንደ ተናገረው አድርጎ ማቅረብ፣ እንደ ተባለው ለሰቃዮቹ ምሕረት የለመነላቸውን ጌታ፣ ለአባቱ ክስ አቅርቧል የሚያሰኝ ነው።
ምንም ይህ የዳዊት መዝሙር በዜማ ማሕዘኒ (በሚያራራ ዜማ) ቢደርስ (ቢባል)፣ ጌታ በመስቀል ላይ ኾኖ ያልተናገረው ቃል በመኾኑ በስቅለት ዐውድ መቅረብ የሌለበትና አለቦታው የተጠቀሰ ቃል ነው። ትልቅ ነገረ መለኮታዊ ስሕተትንም የሚያስከትል ነው። ምክንያቱም ክርስቶስ በግፍ መከራን ሲቀበል በመዛትና ወደ አባቱ ክስ በማቅረብ ፈንታ ለጠላቶቹ በመማለድ ያሳየው ትዕግሥትና ፍቅር፣ እኛም እርሱን አብነት አድርገን ፍለጋውን እንድንከተል የተወልን መልካም ምሳሌ ነው። ቃሉም ይህን ሲያረጋግጥ እንዲህ ይላል፤ “በግፍ መከራን የሚቀበል ሰው እግዚአብሔርን እያሰበ ሐዘንን ቢታገሥ ምስጋና ይገባዋልና። ኀጢአት አድርጋችሁ ስትጐሰሙ ብትታገሡ፥ ምን ክብር አለበት? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል። የተጠራችኹለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። እርሱም ኀጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ” (1ጴጥ. 2፥19-23)።
ይህን የመዝሙረ ዳዊት ክፍል አስመልክቶ የተባለው ይህ ኾኖ ሳለ፣ “መድሎተ ጽድቅ” ግን ይህ ግፍዖሙ እግዚኦ ለእለ ይገፍዑኒ ጽብኦሙ እግዚኦ ለእለ ይጸብኡኒ - አቤቱ የሚበድሉኝን በድላቸው የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመዝሙረ ዳዊት 34(35) ላይ የሚገኝ ቃል ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለን የእግዚአብሔር ቃል መናገር ኀጢአት ከኾነ ጽድቁ ምን ሊኾን ነው? በዚያውም ላይ ደግሞ ‘ጌታ ኢየሱስ ‘ግፍኦሙ እግዚኦ ለእለ ይገፍዑኒ ጽብኦሙ እግዚኦ ለእለ ይጸብኡኒ አቤቱ በእኔ ላይ ግፍ የፈጸሙትን ሰዎች ፍዳ ግፍዕ ክፈላቸው። እየተጣሉኝ ያሉትንም ተጣላቸው’ ሲል ለአባቱ ክስ አቀርቦ ነበር የሚሉ የሐሰት ምስክሮች ምንም ዛሬ ቢቆሙበትም’ የተባለው ያው የተለመደ ውሸት ነው። ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ለአባቱ ክስ አቀርቦ ነበር ብላ አታውቅም፡። ኾኖም ቃሉ የእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል ስለኾነ ይነባባል። ከአንዱ የእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል መካከል ይህ ይባላል ያ ግን አይባልም ይነባባል። ደግሞ ርኩስ ነው እያሉ ለመከፋፈል ማን ሥልጣን ሰጣቸው? ራሳቸውን ከቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል በላይ ያደርጉ ዘንድ እስከዚህ ድረስ ትዕቢትና ዕብሪትን ከየት አገኙት? የእነዚህ ምንጫቸው ይታወቃልና ያው ከአባታችሁ ካልኾነ በስተቀር ከየት ይኾናል።” ሲል ለማስተባበል ይሞክራል።
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ለአባቱ ክስ አቀርቦ ነበር ብላ አታውቅም። ኾኖም ቃሉ የእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል ስለኾነ ይነባባል።” ስለ ተባለው፣ ለመኾኑ ይህ ቃለ እግዚአብሔር በስቅለት ዕለት ሲባል ተናጋሪው ማነው? ወይም ማነው የተወከለበት? ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለምን? መቼም በዚያ ቀን ሌላ የሚታሰብ የለም። ቤተ ክርስቲያኒቱ ከቅዱሳት መጻሕፍት አውጣጥታና ዐውዱን ጠብቃ፣ እንደ “ግፍዖሙ” አንዳንዱ ዐብሮ ባይኼድም አንድን በዓል የሚመለከትና ዐውዱን የጠበቀ ነገር በማቅረብ የደረጀ ባህለ ሥርዐት ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት። ለምሳሌ በበዓለ ማርያም በቅዳሴ ላይ ከሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ኹለተኛዪት የዮሐንስ መልእክት አንዱ ነው። ይህ መልእክት ለተመረጠች እመቤትና ለልጆችዋ ተብሎ የቀረበ ሲኾን፣ መልእክቱ የተጻፈው ለማርያም አለመኾኑ ይታወቃል። ነገር ግን “የተመረጠች እመቤት” ስለሚል ብቻ በየወሩ በበዓለ ማርያም ማርያምን እንዲጠራ ወይም እንዲያመለክት ተደርጎ የሚነበብ ይመስላል፤ ለዚህም መስከረም 21፣ ጥቅምት 21፣ ጥር 21፣ የካቲት 21፣ የነሐሴ 16 እና 21 ንፍቅ ዲያቆኑ የሚያነብበውን ምንባብ ከመጽሐፈ ግጻዌ መመልከት ይቻላል። “ግፍዖሙ” የስቅለት ዕለት እንዲደርስ ሲደረግም ስለ እኛ መከራን የተቀበለው ጌታ እንደ ተናገረው የሚያሳስብ እንጂ ዝም ብሎ የቀረበ ነው ወይም “ቃሉ የእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል ስለኾነ ይነባባል።” በማለት አድበስብሶና አምታትቶ ለማለፍ መሞከር ስሕተትን አለመቀበልና ለመታረም አለመፈለግን ነው የሚያሳየው።
“ግፍዖሙ” ከስቅለቱ ጋር ተያይዞና ጌታ እንደ ተናገረው ተቈጥሮ ሊጠቀስ የሚገባው አይደለም ማለታችንን ሌላ መልክ ሰጥቶም “ከአንዱ የእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል መካከል ‘ይህ ይባላል፤ ያ ግን አይባልም። ይህ ቅዱስ ነው፤ ያ ደግሞ ርኩስ ነው’ እያሉ ለመከፋፈል ማን ሥልጣን ሰጣቸው? … መዝሙረ ዳዊት እንቀበለዋለን ከሚሉት ከስል[ድ]ሳ ስድስቱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለ ነው። እንቀበለዋለን ከሚሉት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዱ ከኾነው መጽሐፍ ከመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የማይቀበሉት ክፍል ካለ እንዲህ እያሉ መመዘኛቸው እነርሱን የመሰላቸው ብቻ ስለኾነ ባልመሰላቸው ቍጥር እየቀነሱ እያወጡት ይኼዳሉ ማለት ነው።” የሚለው ማደናገሪያ ግን ራስን የሚያስገምት እንጂ ሚዛን የሚደፋ አይደለም። ያልተቀበልነው “ግፍዖሙ”ን ጌታ በመከራው ውስጥ ኾኖ ወይም በመስቀል ላይ ሳለ የተናገረው የሚያስመስለውን አቀራረብ እንጂ ቃሉማ የቅዱስ መጽሐፍ ቃል መኾኑን እንደምናምን የ “መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊም አይጠፋውም።
እኛ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ “መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ ለእኛ አስተሳሰብ በሚመች መልኩ አንጠቀምበትም። ቃሉን እንደ “መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ ከባህለ ትምህርታችን አሳንሰን አናየውም፤ ወይም ለባህለ ትምህርታችን መጠበቅ ስንል አንሠዋውም፤ ባህለ ትምህርታችን በቃሉ መመሥረቱን እናረጋግጣለን እንጂ፣ ከቃሉ የምንቀንሰውም ኾነ በቃሉ ላይ የምንጨምረው የለም። በእግዚአብሔር ቃል ስሕተታችንን እናርማለን እንጂ፣ ስሕተታችንን ለማጽናት ስንል የማይለወጠውን የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ቃል እስከ መለወጥ ድረስ ደፍረን አንኼድም። ይህ ከእኛ ይራቅ!!!   
በመጨረሻም “ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ መዳን የምታስተምረውን ሸምጥጠው በመካድ የሚዳነው በዚህ መንገድ ነው ያለች ለማስመሰል የእነርሱን የስሕተት ትምህርት ተቀብሎ በእነርሱ የሞት መንገድ የማይኼደውን ሰው ኹሉ በሽታውን ቢያውቅም መድኀኒቱን መውሰድ ባልጀመረ በሽተኛ ይመስሉትና በመቀጠል እንዲህ ይላሉ፦ “የታዘዘለትን መድኀኒት በመውሰድ ፈንታ ከቤተ ክርቲያን ዐውድ ጕዝጓዝ ዕጣንና ሰንደል ወዘተ የሚታጀበውን የቡና መንፈስ ይማለላል። (ጮራ ቍ. 8፣ ገጽ 22)። እስኪ ኅሊና ላለው ሰው የቤተ ክርስቲያኒቷ የመዳን ትምህርት ይህ ነውን? ይህን ቤተ ክርስቲያን የምትደግፈውና አድርጉ የምትለው ነው ብሎ መጻፍ ምን ያህል ያውቁብኛል አለማለትና የክፋት ዳርቻ ነው!” ብሏል (ገጽ መድሎተ ጽድቅ፣ ገጽ 42)። እርሱ በጠቀሰው ጮራ ቍጥር 8 ገጽ 22 ላይ ግን እንዲህ የሚል ንባብ የለምና ለጊዜው በዚህ ላይ ምንም ማለት አይቻልም።
ይቀጥላል




[1] ከዚህ ቀጥሎ ያለው ጽሑፍ “አልተሳሳትንምን?” ከተሰኘው የዲ/ን አግዛቸው ተፈራ መጽሐፍ 2ኛ ዕትም ከገጽ 52 - 55 ላይ የተወሰደ ነው።

1 comment:

  1. እግዚአብሔር አገልግሎታችሁን ይባርክ !

    ReplyDelete