Monday, January 27, 2020

ከዓለመ መጻሕፍት


ሃይማኖተ አበው ቀደምት
ካለፈው የቀጠለ

ነገረ ክርስቶስን በምልአት አብራርተዋል
ክርስትና በፍሬምናጦስ አማካይነት በኢትዮጵያ ከተሰበከበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዐፄ ሱስንዮስ ዘመን ድረስ የነበረው የተዋሕዶ ባህለ ትምህርትቃልና ሥጋ በተዋሕዶ ወልድ ዋሕድ አካል ልጅ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው። በተዓቅቦ ባሕርያት ግብራት የባሕርይ ልደታት ወልደ አብ በመለኮቱ (በመለኮቱ የአብ ልጅ) ወልደ ማርያም በትስብእቱ (በሰውነቱ የማርያም ልጅ) አብ ቀባዒ (ቀቢ) ወልድ ተቀባዒ (ተቀቢ) መንፈስ ቅዱስ ቅብ (ቅብዐት) ሥግው ቃል (ሥጋ የኾነው ቃል) በተዋሕዶ ገንዘብ ባደረገው በሥጋ ርስት በሥጋ ባሕርይ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀበሎ ተቀብቶ፥ በቅባት መሲሕ ወበኵር (መሲሕና በኵር) በኵረ ልደት ለኵሉ ፍጥረት (ከምእመናን ኹሉ በጸጋ ልጅነት የመጀመሪያ ልጅ) ዳግማይ አዳም (ኋለኛው አዳም) ንጉሠ ነገሥት ሊቀ ካህናት፤ ነቢይ ሐዋርያ፣ ላእክ መልአክ (አገልጋይ መልእከተኛ) ኾነ ወይም ተባለ ማለት ነው።ይላሉ።ይህ ኹሉ በቅባት የሚሰጥ የሹመትና የግብር ስምሲኾን ከመቀባቱ ጋር ተያይዞ መሲሕነቱን አምልቶ አስፍቶ አጕልቶ የሚያሳይ ነው።

ባህለ ትምህርታቸው ተዋሕዶ ኾኖ ሳለ በካሮችና ቅብዐቶች ስማቸው ተቀምቶየጸጋ ልጆችአንዳንድ ጊዜምሦስት ልደትየተሰኙት ለክርስቶስ ኹለት የባሕርይ ልደታት፣ አንድ የግብር ልደት በድምሩ ሦስት ልደታት አሉት ብለው ስለሚያምኑና ስለሚያስተምሩ ነው። ኹለቱ የባሕርይ ልደታት የሚባሉትም ወልድ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው ልደትና ድኅረ ዓለም ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት የተወለደው ልደት ነው። ስለዚህ ወልድበአምላክነቱ የአብ የባሕርይ ልጅ፥ በሰውነቱ የማርያም የባሕርይ ልጅ፥ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰብእ፥ ወልድ ዋሕድነው። በመጀመሪያው ልደት ወልድ የአብ የባሕርይ ልጅ ነው፤ለአብ ወልድ ዘበአማን (የባሕርይ ልጅ) በሚባልበት በአባቱ ባሕርይ ለማርያም ወልድ ዘበአማን (የባሕርይ ልጅ) አይባልም፤ ጌታዋ ፈጣሪዋ እንጂ። እንደዚሁ ደግሞ ለማርያም ወልድ ዘበአማን በሚባልበት በናቱ ባሕርይ ለአብ ወልድ ዘበአማን አይባልም፤ ዘበጸጋ (የጸጋ ልጅ) እንጂ።ይላሉ።

ሦስተኛውና የግብር ወይም የጸጋ ልደት የሚባለው፣ ከማርያም በሥጋ የተወለደው (ሥግው ቃል) በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ተቀብቶ የእግዚአብሔር ልጅ የተባለበት ልደቱ ደግሞ የግብር ወይም የጸጋ ልደት ነው። ይህ ልደት በባሕርይ በመወለድ ሳይኾን በመስጠትና በመቀበል የሚገኝ ልደት ነው። በመኾኑም የግብር ልደት ለባሕርይ ልደት ምሳሌ እንጂ ዘበአማንነት (አማናዊነት) የለውም። ምሳሌ ከአማናዊ እንደሚያንስ፥ እንደማይተካከል የግብር ልደትም ከባሕርይ ልደት በስም (ልደት በመባል) ብቻ ይተካከላል። በግብር ልደት መወለድ የሚቻለው፥ትንሹም በታላቁ እንዲባረክ ክርክር የሌለበት ነገር ነው” (ዕብ. 77) እንደ ተባለው፥በወግ፥ በማዕርግ፥ በብዕል (በሀብት) በሥልጣን፥ በዕድሜ፥ በዘመን ከሚበልጠውና ከሚቀድመው ተባርኮ ተሹሞ፥ ሀብተ ወልድና (የልጅነት ሀብት) ስመ ወልድና (የልጅነት ስም) ተቀብሎ መውለዱና መወለዱ ሳይኖር በዚሁ በውሂቡና በነሢኡ (በመስጠቱና በመቀበሉ) ብቻ አባትና ልጅ መባባል ነውይላሉ። ሐተታውን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ሲያስደግፉትም፥ የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይጠቅሳሉ፦
·     እግዚአብሔር በነቢዩ በናታን በኩል ስለ ሰሎሞን የተናገረውንና፥እኔም አባት እኾነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይኾነኛልያለውን (2ሳሙ. 714) /ይህ ክፍል በዕብራውያን መልእክት ውስጥ ስለ ክርስቶስ የተጻፈ መኾኑ ተጠቅሷል (ዕብ. 15)/
·        ዳዊትም፥እርሱ፥ አባቴ አንተ ነህ፥ይላል። እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለሁያለውን (መዝ. 892627)
·         መልአኩ ገብርኤል ድንግል ማርያምን ሲያበሥራት፥ “… ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላልያላትን ይጠቅሳሉ (ሉቃ. 135)

በእነዚህ ምስክርነቶች ውስጥ አባትነትና ልጅነት (አባት መባልና ልጅ መባል) የተገኙት በመስጠትና በመቀበል ነው እንጂ ባሕርያዊ በኾነ መንገድ በመውለድና በመወለድ አይደለም።

የተዋሕዶ ሊቃውንት እነዚህን የቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነቶች መሠረት አድርገው፥ ሊቃውንት የመሰከሩትንም አንድ ላይ ሰብስበው በግብር ልደት ላይ ያላቸውን ጽኑ ዐቋም እንደሚከተለው ይገልጣሉ፤ወንሰምዮ ወልደ፤ ናሁ ኮነ ለነ ወልደ በሀብት። ወተሠርዐ ወልደ እግዚአብሔር በኀይል ቅብዐ መንፈስ ቅዱስ። ወተወልደ ውእቱ ቀዳማየ እመንፈስ ቅዱስ ከመ ጸጋሁ ትዕዱ ላዕሌነ። እመሰ ኰሰይነ ልደቶ እንተ ከማነ በመኑ ተመሲለነ ንከውን ውሉደ እግዚአብሔር።”
ትርጕም፦ “ልጅ እንለዋለን፤ እነሆ ለእኛ በጸጋ ልጅ ኾኖልናል። በቅብዐ መንፈስ ቅዱስ በኀይል የእግዚአብሔር ልጅ ተባለ። ጸጋው ወደ እኛ ትሸጋገር ዘንድ እርሱ ከመንፈስ ቅዱስ የመጀመሪያ ልጅ ኾኖ ተወለደ፤ [ይህን] እንደኛ የኾነበትን ልደቱን ከካድነው በየትኛው ልደት መስለነው የእግዚአብሔር ልጆች እንባላለን?” ብለዋል።

ክርስቶስን በኵር እኛን ደግሞ ተከታይ ወንድሞች ያሰኘን ልደት፥ ወልድ እም ቅድመ ዓለም ከአብ የተወለደበት ልደት አይደለም፤ ድኅረ ዓለም ከቅድስት ማርያም የተወለደበት የሥጋ ልደትም አይደለም፤ እርሱ በኵር እኛ ደግሞ ተከታዮች ወንድሞች የኾንበት ልደት በመንፈስ ቅዱስ በመቀባት የተከናወነው የግብር ልደት ነው እንጂ (ሮሜ 829 ዕብ. 213)

ኪ.ወ.ክ. ይህን የግብር ልደት ይበልጥ ለማስረዳትም፥ ስለ ወልድ በብሉይ ኪዳን የተነገሩትን ትንቢቶች በሐዲስ ኪዳን መፈጸማቸው ከተጻፉባቸው ክፍሎች ጋር በማዛመድ ያትታሉ። በተለይም ከዘላለም የአብ የባሕርይ ልጅ የኾነው ወልድ፥ ሰው ከኾነ በኋላ መንፈስ ቅዱስን በአብ ተቀብቶ የእግዚአብሔር ልጅ መባሉን ለማስረዳት የሚጠቅሱት፥እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ ወአነ ዮም ወለድኩከ - እግዚአብሔር አለኝ፤ አንተ ልጄ ነህ፤ እኔም ዛሬ ወለድሁህየሚለውን ትንቢታዊ መዝሙር ነው (መዝ. 27) በዚህ መዝሙር ውስጥ፥አንተ ልጄ ነህየሚለው ከዘላለም የአብ ልጅ መኾኑን ሲያመለክት፥እኔ ዛሬ ወለድሁህየሚለው ደግሞ ሰው ከኾነ በኋላ፥ በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ መባሉን ያስረዳል ይላሉ። በእነዚህ ኹለት ዐረፍታተ ነገር ውስጥአንተ ልጄ ነህያለውም፥እኔ ዛሬ ወለድሁህያለውም ባለቤት (Subject) እግዚአብሔር ብቻ እንደ ኾነ ልብ ይሏል።

ይኹን እንጂ ይህን ባለማስተዋል፣ በተለይም ቅዱሳት መጻሕፍት የናዝሬቱ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስና በኀይል መቀባቱን የሚናገሩትን ክፍሎች (.. 427-28 1038 መዝ. 44(45)7 ዕብ. 18-9 ሉቃ. 226 417-19) ንባብ ጥሰው ምስጢር አፍርሰው ሥግው ቃል (ሥጋ የኾነው ቃል) በሰውነቱ በመንፈስ ቅዱስ አልተቀባም ጸጋንም አልተቀበለም የሚሉት ካሮች፣ በብሉይ ኪዳን የተነገረውን ይህን ቃል፥ የመጀመሪያውአንተ ልጄ ነህየሚለው ቀዳማዊ ልደቱን፥ ኹለተኛውእኔ ዛሬ ወለድሁህየሚለው ደግሞ ደኃራዊ ልደቱን (ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን) ያሳያል ይላሉ።[1]አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህበሚሉት በኹለቱም ዐረፍታተ ነገር ውስጥ፥ልጄ ነህእናወለድሁህያለው እግዚአብሔር ብቻ ስለ ኾነ፥ የኹለተኛውን ዐረፍተ ነገር ባለቤት ቅድስት ማርያምን ማድረግ ይመስላልና እንዲህ ከታሰበ ትልቅ ነገረ መለኮታዊ ችግር ውስጥ መውደቅን ያስከትላል። የዐረፍተ ነገሩ ባለቤት እግዚአብሔር መኾኑን እያወቁ አለማወቅም ይኾናል። መቀባቱን በመካድና ምስጢሩን በመለወጥ ወደ ሌላ ስሕተት ከማምራት ይልቅ፣ ከቅድስት ማርያም በሥጋ የተወለደውን ኢየሱስ ክርስቶስን እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስና በኀይል በመቀባቱ መሲሕና ወልደ እግዚአብሔር መባሉን የሚያመለከት መኾኑን ቢረዱ መልካም ነበር።

ይህ የመዝሙር ክፍል (መዝሙር 2) የተነገረው ስለ ክርስቶስ በመኾኑ፥ በሐዲስ ኪዳን በክርስቶስ ተፈጽሞ እናነባለን (.. 1333 ዕብ. 15 55) በሐዋርያት ሥራ የተጠቀሰው ከትንሣኤ ክርስቶስ ጋር ታያይዞ ነው የቀረበው፤ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በኹለተኛው መዝሙር ደግሞ፥ አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና።” (1333) የተዋሕዶ ሊቃውንት፥ ሥግው ቃል የተቀባው በዕለተ ፅንስ (በተፀነሰበት ዕለት) ወይም ሰው በኾነ ጊዜ ነው ይላሉ።የግብር ልደት የሚፈጸመው ኋላ በትንሣኤ ነው። እስከዚያ የልደት መያዣ ወይም ዐረቦን ይባላል፤ ውጥን፥ ጅምር፥ ወይም ፅንስ ሽል እንደ ማለት ነው (ሮሜ 63-9 2ቆሮ. 122 55)የሐዋርያት ሥራን መሠረት በማድረግ በሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ላይ፥ወውእቱ ቅድመ ዘተወልደ እሙታን - እርሱ ከሙታን አስቀድሞ የተወለደ ነውተብሎ ተጽፏል። ይኹን እንጂ የዐረቦኑና የትንሣኤው ልደት፥እኔ ዛሬ ወለድሁህበሚለው የታሰረ አንድ ነው እንጂ ኹለት አይደለም፤ ዐረቦን እንደ ፅንስ፥ ትንሣኤ ደግሞ እንደ ልደት ነውና ይላሉ።

በዕብራውያን ክፍል የተጠቀሱት ደግሞ ከንጉሥነቱና ከሊቀ ካህናትነቱ ጋር ተያይዘዋል። በምዕራፍ አንድ ውስጥ የተጠቀሰው ስለ ንጉሥነቱ እንደ ተነገረ በዐውዱ ውስጥ ይታያል (ዕብ. 1568)እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊኾን ራሱን አላከበረም፤ ነገር ግን፥ አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ ነው፤የሚለውም ከሊቀ ካህናትነቱ ጋር ተያይዟል (ዕብ. 55)

ኢየሱስ፥ የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን በኾነው በመልከ ጼዴቅ አምሳል (ዕብ. 71) ንጉሥም ሊቀ ካህናትም ኾኗል። ነገር ግን ክህነታቸውና መንግሥታቸው ኀላፊና ሥጋዊ እንደ ነበረው የብሉይ ኪዳን ካህናትና ነገሥት የሚያልፍ ግዙፍ ቅባት አልተቀባም።ክህነቱም መንግሥቱም መንፈሳዊና ዘለዓለማዊ ስለ ኾነ በማያልፍና በማይጠፋ በረቂቁ ዘይት በመንፈስ ቅዱስ ቅብነት ተሹሟል (ኢሳ. 111-2 421 611 .. 1038) ሲሾምም ካባቱ ጋር አንድ የሚኾንበት ሥልጣንና ችሎት እያለው፥ ይቻለኛልና በገዛ እጄ ልሾም አላለም፤ አባቱ ቀብቶ ሾመው እንጂ” (.. 427 ዕብ. 54-6 ሉቃ. 132) ከዚህ የተነሣ መሲሕ፥ በኵር፥ ኹለተኛው አዳም፥ ክርስቶስ፥ ቀዳሜ ጸጋ (ጸጋን በመቀበል የመጀመሪያ) ወዘተ. በሚሉ ስሞች ተጠርቷል። እኛንም በመሲሕነቱ መሲሓውያን፥ በቅቡዕነቱ ቅቡዓን፥ በወልደ እግዚአብሔርነቱ ውሉደ እግዚአብሔር፥ በክርስቶስነቱ ክርስቲያን አሰኝቶናል ይላሉ።

ስለ ክርስቶስ ምልጃ
በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ ሊቀ ካህናት የኾነው ሥግው ቃል በሰውነቱ አስታራቂ መኾኑን ኪ.ወ.ክ. በግጥም ሲመሰክሩ፦
አምላክና ሰው መካከለኛ - የሰማይ የምድር ምሰሶ ዳኛ
ከማኽል ቁሞ እንዳምደ ወርቅ - አባቱን ከኛ የሚያስታርቅ
ስለኛም በደል ሲያቀርብ ካሳ - ወድቆ የሚሰግድ እጅ የሚነሣ
ሲሉ፣
በሌላም ክፍል፦
ካህንም ኹኖ ስለ ሕዝቡ - መሧዕት ጸሎት በማቅረቡ
አስታራቂና አማላጅ - ወይም ነገረ ፈጅ
ለሰማይ ርስት የሚያበቃ - አለቃና ጠበቃ።በማለት የክርስቶስን መካከለኛነት መስክረዋል።

ክርስቶስ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛና አስታራቂ መኾኑን የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተነሡ ክፍሎች እየለወጧቸውና እርሱን መካከለኛ ሳይኾን ፈራጅ ብቻ አድርገው ለማቅረብ እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ። እነርሱ ትርጕማቸውን የለወጧቸውን ክፍሎች አለቃ በመዝገበ ቃላታቸው ውስጥ ቍልፍ ቃላቱን በተገቢው መንገድ ተርጕመዋቸው እናነባለን። ለምሳሌ ሮሜ 834 ላይ ስለ ክርስቶስ ምልጃይትዋቀሥ በእንቲኣነስለ እኛ ይከራከራል ተብሎ የተነገረውንና ግእዙ ስለ እኛ ይከራከራል የሚል ፍቺ የሚሰጠውን ንባብ፣ አስተምህሮአቸውን ለቃሉ ማስገዛት ሲገባቸው፣ ቃሉን ለአስተምህሮአቸው ተገዢ እያደረጉ ያሉ ክፍሎችስለ እኛ ይፈርዳል” የሚል ትርጕም ሰጥተውታል። አለቃ ግንተዋቀሠለሚለው ቃል የሰጡት ትርጕምበቁሙ (ተዋቀሠ) ተሟገተ፣ ተከራከረየሚል ነው። ለአስረጂነት ከቀረቡት ጥቅሶች መካከልም ሮሜ 833 ላይመኑ ይትዋቀሦሙበዐማርኛውማን ይከሳቸዋል” የሚለውን ጠቅሰዋል። በዚህ ምዕራፍ (ሮሜ 8) ላይ በግእዙ ቃሉ ሦስት ቦታ ላይ እንደ ተጠቀሰ ልብ ይሏል፤ ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ ቍጥር 26 ላይወባሕቱ መንፈስ ይትዋቀሥ ለነ” የዐማርኛው መጽሐፍ ቅዱስመንፈስ ራሱ በማይናገር መቃተት ይማልድልናልይላል።

1 ዮሐንስ መልእክት ምዕራፍ 2 ቍጥር 1 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ዘንድ ጠበቃችን መኾኑን ይናገራል። ጠበቃ ተብሎ ወደ ዐማርኛ የተመለሰው የግሪኩ ቃል ፓራክሊቶስ ወይም ጰራቅሊጦስ ነው። ቃሉ ኹለት ዐይነት ፍቺ እንደሚሰጥ የኪ.ወ.ክ. መዝገበ ቃላት ያስረዳል። የመጀመሪያውአማላጅ አስታራቂ፤ አፍ ጠበቃ፤ ትርጁማን አምጃር፤ እያጣፈጠ የሚናገር፤ ስብቅል ካፉ ማር ጠብ የሚልሲኾን፣ አማላጅ አስታራቂ ለሚለው አስረጂ ኾኖ የተጠቀሰው 1ዮሐ. 21 ነው። የቃሉ ትክክለኛ ፍቺ ይህ ኾኖ እያለአማላጅ አስታራቂ፤ አፍ ጠበቃየሚለውን ትተውና ቃሉን ሳይተረጕሙ በቁሙጰራቅሊጦስ” አለን በማለትና ጰራቅሊጦስን ለኢየሱስ ቅጽል በማድረግ ፈንታ የሌላ ዐረፍተ ነገር ባለቤት ሲያደርጉት፣ አብን ደግሞ ለኢየሱስ በመቀጸል የግሪኩን ብቻ ሳይኾን የግእዙን ንባብ ጥሰው የመጽሐፉን ሳይኾን የሚፈልጉትን ጽፈዋል። በእግርጌ ማስታወሻ ላይ ግን ግሪኩ ማንም ኀጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጰራቅሊጦስ አለን እርሱም ጻድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይላል (የ2000 ዕትም መጽሐፍ ቅዱስ)። እዚህ ላይ ጰራቅሊጦስን ሳይተረጕሙ ያለፉት ጠበቃ እንዳይልባቸው ሠግተው መኾኑ ይታወቃል። ይህን ኹሉ ያደረጉት ደግሞ ኢየሱስን ከመካከለኛነቱ ስፍራ በማንሣት እነርሱ ላቆሟቸው መካከለኞች ስፍራ ለማግኘት ሲሉ ነው።      

ለጰራቅሊጦስ የተሰጠው ኹለተኛው ፍቺ ደግሞናዛዚ (የሚያረጋጋ) መጽንዒ (የሚያጸና) መስተፍሥሒ (የሚያስደስት) መንፈስ ቅዱስ የሚል ነው። ይህም ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ተያያዞ የሚነገር ነው። ለምሳሌ በዮሐ. 14፥15-16፡26 ላይ ዐማርኛው “አጽናኝ” ያለውን ግሪኩ ጰራቅሊጦስ ነው የሚለው።    

ስለ መንፈስ ቅዱስ
መንፈስ ቅዱስ ከአብ የሚሠርጽ (የሚወጣ) (ዮሐ. 1526) ከወልድ የሚነሣ (የሚወስድ) መኾኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ነው (ዮሐ. 1614) ኾኖም መውጣትና መውሰድ የተለያዩ ሐሳቦችን የተሸከሙ ቃላት ናቸው እንጂ ተመሳስሎ የላቸውም። ወይም መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ይሠርጻል የሚል ፍቺ የላቸውም። ስለዚህ የሚወስድ የሚለውን የሚወጣ (ዘሠረጸ) ብለን እንፍታው ብንል አያስኼድም ብለው መንፈስ ቅዱስ ከአብ የሠረጸ ከወልድ የሚነሣ መኾኑን ይናገራሉ። በመጽሐፈ ቅዳሴ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል “መንፈስ ቅዱስም ከአብ እንደ ሠረጸ (እንደ ወጣ) ከወልድም እንደ ነሣ (እንደ ወሰደ) ይናገራል።”[2]

ምሥራቃውያን ኦርቶዶክሶች ይህን ክፍል በዚህ መልኩ ሲተረጕሙት፥ ምዕራባውያን ካቶሊኮችም ኾኑ ፕሮቴስታንቶች መንፈስ ቅዱስን ከአብና ከወልድ የሠረጸ ብለው ነው የሚተረጕሙት። ይህም በ900 ዓ.ም. ውስጥ ዘጠነኛው ምእት ዓመት ሊፈጸም አቅራቢያ የተወሰነ መኾኑን ገልጠዋል።   

ቅዱሳት መጻሕፍት መንፈስ ቅዱስን ስለ አንጻሒነቱ (የሚያነጻ ስለ መኾኑ) ውሃ (ዮሐ. 7፥38-39)፣ ስለ ሀብትነቱ ቅብዕ ይሉታል (ሐ.ሥ. 10፥38፤ 1ዮሐ. 2፥20፡27፤ ኢሳ. 61፥1)። እግዚአብሔር አብ ሥግው ቃልን በሰውነቱ የቀባበት ረቂቁ ቅባት መንፈስ ቅዱስ መኾኑን ቅዱሳት መጻሕፍትን አብነት አድርገው ያብራራሉ (.. 427-28 1038 መዝ. 44(45)7 ዕብ. 18-9 ሉቃ. 226 417-19)
ስለ መንፈስ ቅዱስ የገጠሙት፦
የአብ ጠበቃ ነገረ ፈጅ - የልጁም የወልድ ቤት አሰናጅ
ልሳነ ዓለም ጰራቅሊጦስ - እኔንም እርዳኝ ቃልህን ላፍስ
በተማሪ ቤት በጽርሐ ጽዮን - ደጅ ለሚጠኑህ ምእመናን
አንተ ነህና አልፋ ኦሜጋ - የተማሮች ሀብት የፊደል ጸጋ
ከልብ ሠርጸህ ከቃል ስትነሣ - መንፈስነትህ ቃል የሚያስገሣ
እንደነዕዝራም አብነት ያጡ - ጽዋዐ እሳት አንተን ሲጠጡ
በሳትነትህ ስታቃጥል - በቅብዕነትህ የምታጠል።
እንዳይማሩ ከሚያስገድድ - እየተዋጋህ በቀለም ቀንድ
ነጩን ብጫውን ጥቍሩን ቀለም - የምታዋሕድ ከቀዩ ደም  

የቦሩ ሜዳ ጉባኤ
1878 .. የተደረገውን የቦሩ ሜዳን ጉባኤ አስመልክቶ ካሮች እንደ ረቱ ጸጎች (ተዋሕዶዎች) ደግሞ እንደ ተረቱ ሲተረክ ኖሯል። በተዋሕዶዎች በኩል የሚተረከው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ኪ.ወ.ክ. ለዚያ ጉባኤ መካኼድ መነሻው በዝብዝ ካሳ ነው ይላሉ። እርሱ በሽፍትነት ሳለ፣ አንድ ሕልመ ዮሴፍ የሚደግም የዕዳባ ኀደራ መነኵሴ ካሳ መንገሡን የሚያሳይ ሕልም እንዳየ ትርጓሜው ወደፊት መንገሡን እንደሚያሳይ ተናገረ። ከዚያ የገዳሙ መምህርና ማኅበሩ ምግብ አዘጋጅተው እርሱ ወደሚገኝበት በረኻ በመኼድ ካነጋገሩት በኋላ፣ ሲነግሥ ከገዳማቸው ዕጨጌ እንዲያወጣላቸው (እንዲሰይምላቸው) ለመኑት። እርሱም ልንገሥ ቢላቸው፣ እንዲነግሡ እኛ እንጸልያለን አሉት። በጸሎታችሁ እግዚአብሔር ቢያነግሠኝ ዕሺ ብሎ ሄሮድሳዊ ማላ (ማቴ. 14፥7፡9) ማለላቸው።

በዝብዝ ካሳ ዐማቹን ተክለ ጊዮርጊስን ድል ነስቶ ዮሐንስ ተብሎ በነገሠ ጊዜም እኒያ መነኮሳት ቀርበው ቃል ኪዳንዎን አይርሱብን አሉ። እርሱም በመሐላው መሠረት ዕጨጌ አወጣላቸው፤ ወልድ ቅብ የተባለውን ባህለ ትምህርታቸውን አጸናላቸው፤ የቦሩ ሜዳን ጉባኤም አቁሞ እነርሱን ከሳሽ አድርጎ በቀኙ አቆማቸው። ተዋሕዶዎቹን ግን ተከሳሾች አደረጋቸው። በዚህ ጊዜ ደብረ ሊባኖሶችክሱና ቀኙ የእኛ ነው፤ ነገሩም ቀድሞ ያለቀ ነው፤ ለዚሁም ታሪክ ይታይልንሲሉ አመልክተው ነበር። እርሱ ግን ለእነዚያ የማለው ማላ እንዳይፈርስ ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ በግራ አቆማቸው።

ከዚያ በመንበረ ማርቆስ ከተቀመጠው ከአባ ቄርሎስ በዐረብኛ ተጽፎ የመጣና ትክክለኛውን የተዋሕዶ ትምህርት የያዘ የተባለ የሃይማኖት ደብዳቤ ተነበበ፤ በውስጡም “ወልድ በተለየ አካሉ ቅብዕ (ቅባት) ነው፤ በሰውነቱ የባሕርይ አምላክ በሰውነቱ እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ ያውቃል፤ ማወቂያም ነው የማይል ሦስት ልደት የጸጋ ልጅ በቅብዐት የባሕሪ ልጅ የሚል የአርዮስ የንስጥሮስ የዩህዳ [የይሁዳ] መርገም ይድረስበት። ከምእመናን የተለየ ይኹን” የሚል ይዟል። “ይህም በፊታቸው በተነበበ ጊዜ የጸጋ ልጆች እንዲህ አሉ፦ ትግሮች ጳጳስ ሲያመጡ ከመንገድ ቈይተው የሰውነት ባሕሪ አምላክ (በሰውነቱ የባሕርይ አምላክ) ያሰኟቸዋል እንጂ ጳጳሳቱ እንዲህ አይሉም አሉ።”[3]

እንዲህ ያለው ነገር ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደ ተፈጸመ ኪ.ወ.ክ. ጽፈዋል። ለምሳሌ በ1777 የጎንደሮች መንግሥት ዘውዱ (ስሙ) ብቻ ቀርቶ ሥልጣኑ ወደ መሳፍንት ከተሸጋገረ በኋላ ራስ ወልደ ሥላሴ ትግራይን ለብቻቸው በሚገዙበት ዘመን፦ የተንቤኑ አባ ኪኑ፣ የደብረ ዳሞው ደብተራ በትሩና የአባ ገሪማው አለቃ ዐምደ መንሱት ከ44ቱ የጎንደር አድባራት የተላከ አስመስለው፣ 12 ክሕደት ፈጥረውና ጽፈው በኢትዮጵያ እንደዚህ የሚባሉ መናፍቃን አስቸግረውናል፤ እነርሱ ሊረቱ የሚችሉትና አፋቸውን የሚዘጉት “ወልድ ቅብዕ ነው” በሚለው እምነት ነውና ይህን እምነት አጽኑልን ብለው ላኩ። “ይህም ክታብ (ደብዳቤ) እስከ ዛሬ በግብጦች እጅ አለ።”

ከዚህ በኋላ ኢዮሳብ የሚባል ጳጳስ ተሹሞ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ “ወልድ ቅብ” በሉ ብሎ ሲናገር የጎንደር ሊቃውንት ግን እንዲህ ማለት ስሕተት ነውና ወልድ ቅብ አንልም አሉ። በዚህ ጊዜ ምነው እንዲህ ማለት መልካም ነው ብላችሁ ወደ እኛ ጽፋችሁልን አልነበረም ወይ? ሲላቸው፣ እኛ እንዲህ ብለን አልጻፍንም ምናልባት ካሮች ባህላቸው ወልድ ቅብ የሚል ስለ ኾነ ኃጥእነቱ እንዲጸድቅላቸው በእኛ ስም ጽፈውት ይኾናል ሲሉ መለሱ። በዚህ ጊዜ አባ ኢዮሳብ “እንኪያስ የኔ ሃይማኖት መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ፣ በተዋሕዶ ወልድ ዋሕድ፣ በቅባት መሲሕ ወበኵር ነው” አለ። እንደ ቀደሙት ጳጳሳት እውነተኛውን ባህለ ትምህርት ስላስተማረ ጎንደሮች እውነተኛ ጳጳስ ብለው ተቀበሉት። ከዚያ አያይዞም ሃይማኖታችሁ ተዋሕዶ ኾኖ ሳለ ታዲያ ለምንድነው ሦስት ልደት፣ በሰውነቱ የጸጋ ልጅ የምትሉት? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም ሲመልሱ ስለ ሦስተኛው የግብር ልደት ጉዳይ ከብሉያት ከሐዲሳትና ከሊቃውንት ምስክር እያመጡ ባስረዱት ጊዜ እርሱም የግብር ልደትስ እንዲህ ከኾነ የሚነቀፍ አይደለም፤ ትንሣኤንም ልደት ይለዋል ብሎ የሐዋርያት ሥራ 13፥33ን ጠቀሰላቸው።

በሌላም ጊዜ ተመሳሳይ ድርጊቶች እንደ ተፈጸሙ ሃይማኖተ አበው ቀደምት ይተርካል።
“ወልድ በተለየ አካሉ ቅብዕ ነው፤ በሰውነቱ የባሕርይ አምላክ በሰውነቱ እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ ያውቃል፤” የሚለው የካሮች ባህለ ትምህርት ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለውና በተዋሕዶ ሊቃውንት ዘንድም ትልቅ የስሕተት ትምህርት ተደርጎ የሚወሰድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ቅብዕ ብሎ የሚገልጠው መንፈስ ቅዱስን ብቻ ነው እንጂ አብን ወይም ወልድን ቅብዕ አይልም። ሊቃውንቱም እነ ቄርሎስ እነ ዮሐንስ አፈወርቅ በዚሁ መሠረት መንፈስ ቅዱስን ብቻ ነው ቅብዕ የሚሉት። ኪ.ወ.ክ.ም ትክክለኛው ትምህርት “ወልድ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ልጅ፥ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው ኹኖ [በአምላክነቱ] በቀባዒነት (በቀቢነት) ከአብ ጋራ [በሰውነቱ] በተቀባዒነት (በተቀቢነት) ከእኛ ጋራ አንድነት ስላለው፤ ቀባዒና ተቀባዒ (ቀቢና ተቀቢ) ቢባል እንጂ እንደ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” አይባልም። ነገር ግን “ወልድ ቅብዕ የሚል ሰው ቅብዕ (ቅባት)ና ቅቡዕ (የተቀባ) ለማለት አንድ ወልድ ብቻ አይበቃውም፤ በግድ ኹለት ወልድ እንደሚያስፈልገው ይወቅ ይላሉ በማለት ወልድ ቅብ የሚለውን ባህለ ትምህርት ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ይጥሉታል።

ካሮች ግን “መንፈስ ቅዱስ ቅብ (ቅባት ነው) ማለትን ነቅፈው፥ መለኮቱ ቀብዖ ለትስብእቱ (መለኮቱ ትስብእቱን ቀባው) ወልድ ቅብ፤ ተዋሕዶተ መለኮት ኮኖ ህየንተ ቅብዐት ለትስብእት (ከመለኮት ጋር መዋሐድ ለትስብእት የቅባት ምትክ ኾነው)” ብለዋል። ኪ.ወ.ክ. የዚህንም ስሕተትነት ሲያሳዩ፦ “መለኮት ቅባት ነው ማለት ወልድ ቅባት ነው ከማለት የተለየ መኾኑን ይናገራሉ። ምክንያቱም መለኮት የሦስቱ አካላት ባሕርይ ነው። ወልድ የተባለው ግን አንዱ አካል ብቻ ነው። ስለዚህ መለኮት ቅብ ማለት ሥላሴን ክርስቶስ ብሎ እንደ መጥራት ነው። ወልድ ቅብዕ ማለትም ቃልን ሳይጨምር ሥጋን ብቻ ክርስቶስ ያሰኛልና ይህ ከንስጥሮስ ባህል ጋር የተስማማ ነው።

በሰውነቱ የባሕርይ አምላክ የአብ የባሕርይ ልጅ የሚለው ባህለ ትምህርትም ወልድ ቅብዕ ከሚለው ባህለ ትምህርት ስሕተት የሚበልጥ እንጂ የሚያንስ አለመኾኑን በመግለጥ የጎንደር ሊቃውንት ከካሮች አባት ከሰላማ ሣልስ ጋር ባደረጉት ክርክር “በሰውነቱ አምላክ ከኾነ በምን ሞተ? ሞተ በሥጋ እንዳይባል [ሥጋውን] አምላክ ኹኖበታል። ባንድ ባሕርይ ኹለት ሥራ መሥራት አይቻልም፤ ባምላክነቱም እንዳይሞት አይስማማውም። ኹለተኛም በሰውነቱ የአብ የባሕርይ ልጅ ከኾነ ከማርያም በምን ተወለደ? አምላክ እንደ ዕሩቅ ብእሲ (ተራ ሰው) ባንድ ባሕርይ ካባትና ከናት መወለድ አይችልም። በመለኮቱ እንዳቶልደው አምላክነት ገንዘቧ አይደለም። የእስክንድርያም ሃይማኖት እኛ እንደምንለው፥ ወልደ አብ በመለኮቱ፥ ወልደ ማርያም በትስብእቱ ማለት ነው” እያሉ ሞግተዋቸው ነበር። 

ወደ ቦሩ ሜዳው ጉባኤ እንመለስና በክርክሩ ላይ ከተነሡት ነጥቦች አንዱ ልደትን የተመለከተ ነው። የካሮቹ አፈ ጉባኤ ወልደ ዮሐንስ በመጀመሪያ “ነአምን ክልኤተ ልደታተ” ይላል ብሎ ሦስተኛውን ከየት አመጣችሁት የሚል ጥያቄ ሲሰነዝር፣ ተዋሕዶዎቹ “ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ ብሎ ያመጣልሃል” አሉ።
ወልደ ዮሐንስም “ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ” ሲል አኃዝ (ሦስት የሚል ቍጥር) የለም ብሎ በመከራከር አኃዝ ከሌለ ተረታችኋል አለ።

(እዚህ ላይ ኪ.ወ.ክ. በቅንፍ እንዲህ የሚል ትችት አቅርበዋል “በመንፈስ ቅዱስ ቅብዕነት ዮም ወለድኩከን (ዛሬ ወለድሁህን) ተከትሎ ቃልን በሰውነቱ ዳግማይ አዳም ቀዳሜ ጸጋ መሲሕ ወበኵር በማለት ፈንታ ወልድ ቅብ ብሎ በሰውነቱ አምላክ የአብ ልጅ ፩ ባሕርይ ፩ ግብር እያሉ የክልኤቱን አኃዝ (የኹለቱን ልደት ቍጥር) መፈለግ የሞኝ ያላዋቂ የዘባራቂ ወይም የተሣላቂ ቃል ነው እንጂ ያዋቂ ጥያቄ አይደለም።”)

በዚህ ጊዜ ተረኛው የዋልድቤ እንግዳ ተማሪ ወልደ ሐና ተጠየቅ ብሎ ዐሥርቱ ቃላት አኃዝ (ዐሥር የሚል ቍጥር) የላቸውም ሲል ወልደ ዮሐንስ አዎን የላቸውም አለ። እናንተ እንደምትሉት ከኾነ ዐሥር መባል አይገባቸውም ማለት ነዋ! በማለት የእነርሱን የመጀመሪያ መከራከሪያ ካስጣለ በኋላ፣ የልደትንና ሥግው ቃል በሰውነቱ ጸጋ መቀበሉን በየስልቱ መጠየቅ ሲጀምር፣ “የወልደ ሐናን አጠያየቅና አመራመር፥ አያያዙን አተላለሙን፤ የአፉን መሞቅ የጥቅሱና የምላሹን መድመቅ የወልደ ዮሐንስን መጨነቅ አይተው” እውነት እንዳይወጣና መረታት እንዳይመጣ ፈርተው በኀይል ማስፈራራትና ያዘው ያዘው ማለትና ማሳደድ ጀመሩ።

በዚህ ጊዜ ወልደ ሐና በሕይወት ሲያመልጥ ሊቃውንቱን ኹሉ በእኛ ሃይማኖት ለማመን ማሉ ተገዘቱ ብለው በግድ ያዟቸው። “መከራና ሞት የፈሩ ወልድ ቅብ (ቅባት ነው) በሰውነቱ አምላክ፥ የአብ የባሕርይ ልጅ በለበሰው ሥጋ ዓለምን ያሳልፋል እያሉ ይምሉ ይገዘቱ ጀምር።” ብዙዎቹ ሸሽተው ተደብቀው ሲያመልጡ ፈርተው ያልሸሹና ኪ.ወ.ክ. “የሠለስቱ ደቂቅ ወንድሞች” የሚሏቸው ዋልድቤ እንግዳ፣ ዙራምቤ እንግዳና አባ ተክለ አልፋ ናቸው። እነርሱም በአንድ ቃል አላግባብ መከሰሳቸውንና ዳኝነት ማጣታቸውን ገልጠው ትክክለኛው ሃይማኖት የእነርሱ እንጂ የእነዚያ እንዳልኾነ ሰበኩ፤ መሰከሩ። ከዚያ “እንደ እስጢፋኖስ ለመምህራን በሚገባ ቃል ስለ ዘለፏቸው ዐፍረው ምላሳቸውን ቈረጧቸው። … ካራ ሃይማኖታቸውን በሊቃውንት ደም አጠመቁት።” ሲሉ ጽፈዋል።   

በካሮች በኩል ሲተረክ የኖረው ግን ልዩ ልዩ ጥያቄና መልስ እየተካኼደ ሳለ በመካከል ዐፄ ዮሐንስ አለቃ ሥነ ጊዮርጊስን[4] “ወልደ ዮሐንስ ኹለት ልደት የሚል ምስክር ከመጽሐፍ እንዳመጣ አንተም ሦስት ልደት የሚል ደረቅ ንባብ አምጣ አሏቸው። አለቃ ሥነ ጊዮርጊስም በደብረ ብርሃን ተኣምረ ማርያም ተጽፏል አሉ። [ዐፄ ዮሐንስም] ከምታስተምረው ከአራቱ ጉባኤ ዐጣህና ስለ ሃይማኖት ተኣምረ ማርያምን ትጠቅሳለህን? ቢሏቸው ከጉባኤው መጽሐፍስ የለም አሉ።”[5] የሚል ነው። 

ይህ ግን የፈጠራ ታሪክ መኾኑ ከአያያዙ ይታወቃል። ምክንያቱም ከላይ የልደት ቍጥር ተጠይቆ በተዋሕዶዎች በኩል የተሰጠውን ምላሽ ስንመለከት፣ እንዲሁም የተዋሕዶ ሊቃውንት በቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀት የበለጸጉ፣ ትምህርታቸውን በተመለከተ ከቅዱስ መጽሐፍና ከሊቃውንት መጻሕፍት ብዙ ማስረጃ ጥቅሶችን ስለሚያቀርቡ የጦጣን ልጅ በዛፍ የጸጋን ልጅ በመጣፍ የሚችል የለም[6] የተባለላቸው መኾኑን ስናስተውል፣ ሦስት ልደት ለሚለው አስረጂ የደብረ ብርሃንን ተኣምረ ማርያም ይጠቅሳሉ ማለት ዘበት ነው።
ጥንታዊው የኦርቶዶክስ ባህለ ትምህርት ሦስት ልደት መኾኑንና በቦሩ ሜዳው ጉባኤ በጸጋ ሊቃውንት ላይ ስደትና ቅጣት ደርሶ ባህለ ትምህርታቸው እንደ ሞተና እንደ ተቀበረ ቢነገርም፣ እርሳቸው ግን፦
“ስለ ተዘጋበት የተማሪ ቤቱ
ተዳፍኖ ይኖራል ኦርቶዶክስ እሳቱ
የጠፋ ይመስላል እሳት ቢዳፈን
ገላልጦ እስኪያነደው ጊዜና ዘመን”
ይላሉ። አዎን “እንደ ማታ እሳት ተዳፍኖ ተቀብሮ ቈይቷል። ሌሊቱ ዐልፎ መዐልት ሲመጣ መገለጡና መነሣቱ አይቀርም ለኹሉ ጊዜ አለውና።”
“ሳትሞት ሞተች ብለው ምንም ቢቀብሯት
አትሞትም አትሞትም አትሞትም እውነት”
እንዳሉትም በጕልበት ተዳፍኖ የቈየው እውነት እየተገለጠ መሄዱ አይቀርም።


[1] አባ ጎርጎርዮስ 1974፣ ገጽ 70።
[2] መጽሐፈ ቅዳሴ 1984፣ ገጽ 99።
[3] ጸሓፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ 2008 ዓ.ም.፣ ገጽ 64። 
[4] በካሮች በኩል የተዘጋጀው ታሪክ አለቃ ሥነ ጊዮርጊስ የጸጎች አፈ ጉባኤ ናቸው ይላል።
[5] አባ ጎርጎርዮስ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ 1974፣ ገጽ 71፡72።
[6] ቄስ ኮሊን ማንሰል፣ ትምህርተ ክርስቶስ፣ 1998፣ ገጽ 276።

No comments:

Post a Comment