Sunday, December 30, 2012

መሠረተ እምነት

Read in PDF
(በጮራ ቊጥር 4 ላይ የቀረበ)
         ከናሁ አዳም
(ካለፈው የቀጠለ)

ባለፈው ዕትም (ጮራ ቍጥር 3 ገጽ 18-20) ይሆዋ በአካል ሦስት መሆኑን፥ እያንዳንዱም አካላዊ መንፈስ በራሱ “የሠራዊት ጌታ ይሆዋ” ተብሎ የመጠራትና የመመለክ ባለመብት እንደ ሆነ፥ የብሉይ ኪዳን አባቶች ተረድተው የነበረ መሆኑን ከእግዚአብሔር ቃል ማለት ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አንብበን ከሐዲስ ኪዳንም ጋር አመሳክረን እንደ ነበረ ይታወሳል፡፡ በዛሬው ዕትምም ከዚያው በመቀጠል የሚከተሉት ነጥቦች በሐዲስ ኪዳን ትምህርት እንመርምራቸው፡፡

ነጥብ (ጭብጥ) ሦስት
ከሥላሴ እያንዳንዱ አካል የባሕርይ ምሉዕነትና የህላዌ (አኗኗር) ፍጹምነት አለው፤ ለሥራውም በባለቤትነት ይታወቃል፡፡

Wednesday, December 26, 2012

ክርስትና በኢትዮጵያ

Read in PDF
(በጮራ ቊጥር 4 ላይ የቀረበ)

የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

 (ካለፈው የቀጠለ)

አምልኮት በኢትዮጵያ

ጥንታዊው የኢትዮጵያውያን አምልኮት በተመሳሳይ ጊዜ በሌላው የዓለም ክፍል ከነበረበት የአምልኮት ታሪክ መሠረታዊ ልዩነት የለውም፡፡ በተመሳሳይ ጊዜም በሌላው የዓለም ክፍል እንደ ነበረው ሁሉ ዐይነቱ ብዙ ቢሆንም አያስደንቅም፡፡ የአምልኮቱ ዐይነት መብዛትና መለያየት ከነገዶቹ ዝርያ ጐሣዎች መብዛት፥ ከገቡበትም አቅጣጫና ጊዜ መለያየት የተነሣ ነው ቢባል ለእውነት የቀረበ ይሆናል፡፡

በቤት እንስሳት፥ በአራዊት፥ በአዕዋፍ፥ በኰረብታ፥ በሐይቅ በወራጅ ውሃ፥ በሚሳቡ ፍጥረታት (የእባብ ዐይነቶች)፥ በዛፎች፥ በድንጋዮች… የማምለክ ልምድ የነገደ ካም ዝርያዎች ትውፊት ነበር ይባላል፡፡ የነገደ ካም ዝርያዎች በዚያን ጊዜ በምድር ላይ ያዩዋቸውን፥ ለኑሮአቸው ጠቃሚ ሆነው ያገኟቸውንና እንደ ብርቅ ድንቅም የቈጠሯቸውን፥ ማለት ወይ በጠቃሚነታቸው፥ ወይ በእንቅስቃሴአቸው፥ ወይ በአቋማቸው ወዘተ. ስሜታቸውን የማረኳቸውን ተንቀሳቃሽና ኢተንቀሳቃሽ ፍጥረታትን ያመልኩ ነበረ የሚለውን ትረካ ከተቀበልን፥ በዚያን ጊዜ ሐሳባቸው ገና በአካባቢያቸው ውሱንና ትኲረታቸውም ካፍንጫቸው ሥር ብዙ ያልራቀ እንደ ነበረ የግምት ፍንጭ ሊሰጥ ይችላል፡፡

Friday, December 21, 2012

ፍካሬ መጻሕፍት

Read IN PDF
(በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 44 ላይ የቀረበ)

“ወትቀውም ንግሥት በየማንከ
በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት
ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአፅምኢ እዝነኪ”
“በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።
ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ” (መዝ. 44/45፥9-10)

ይህን የመዝሙረ ዳዊት ጥቅስ በሚያነብብ በአብዛኛው ሰው አእምሮ ውስጥ በቶሎ የምትከሠተው ድንግል ማርያም ናት። ይህ የሆነው ጥቅሱ ስለ እርሷ የተነገረ ስለ ሆነ ግን አይደለም። ስለ እርሷ የተነገረ ነው ተብሎ ስለ ተወሰደ፥ በተደጋጋሚ ከእርሷ ጋር ተያይዞ ስለ ተነገረ፥ በየወሩ በ21 ለበዓለ ማርያም የሚዜም ምስባክ ስለ ሆነ ነው ስለ እርሷ የተነገረ ያህል እየተሰማን የመጣው። ቅድስት ድንግል ማርያምን ንግሥተ ሰማይ ወምድር ብለው የሚያምኑ ክፍሎች፥ ሐሳባቸውን በዚህ ጥቅስ ለማስደገፍ ይሞክራሉ። እርሷን በንጉሥ እግዚአብሔር ቀኝ እንደ ተቀመጠች ንግሥትም ይቈጥሯታል።

ቃሉ ስለ ማን እንደ ተነገረ ከመጽሐፉ ተነሥተን እንመልክት። ጥቅሱ ለሚገኝበት ለዚህ የመዝሙረ ዳዊት ክፍል የዐማርኛው የ1953ቱ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስ “ለመዘምራን አለቃ፤ በመለከቶች፤ የቆሬ ልጆች ትምህርት፤ የፍቅር መዝሙር” የሚል ርእስ ተሰጥቶታል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለራሷ ባሳተመችው የ2 ሺሁ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስም “ለመዘምራን አለቃ በመለከቶች የቆሬ ልጆች ትምህርት የፍቅር መዝሙር” በማለት ይህንኑ ርእስ ነው ያስቀመጠው።

Tuesday, December 18, 2012

ማስታወቂያ

Read in PDF
ጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 44 ለንባብ በቅቷል
*   መሠረተ እምነት
ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ በኋላ እርሱን ተክተው በክህነት እንዲያገለግሉ የሾማቸው ካህናት አሉን? በሚል ርእስ በተዘጋጀው ጽሑፍ አየሱስን ወክለው የተሾሙ ካህናት አሉ የሚሉ ወገኖችን በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ይሞግታል፡፡
*   የዘመን ምስክር
የዚህ ዕትም የዘመን ምስክር ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ናቸው፡፡ ለአገርና ለወገን ያፈለቋቸው ተራማጅ ሐሳቦች ተዳስሰዋል፡፡ ስለ ሃይማኖት ነጻነት ከተናገሩት መካከል የሚከተለው ይገኛል፥ “… ባገራችን አንድ የድንቊርና ነገር አለ፡፡ ሃይማኖቱ ተዋሕዶ ያልሆነ ሰው ሁሉ እንደ ርኩስ ይቈጠራል፡፡ ይህም እጅግ ያሥቃል፡፡ አእምሮ የሌለው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ሳያውቅ የእግዚአብሔር ጠበቃ ሊሆን ይወዳል፡፡”

*   ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
በዚህ ዐምድ ሥር ለሁለት ጥያቄዎች ምላሸ ተሰጥቷል፡፡ አንደኛው ጥያቄ መልከ ጼዴቅ ኢትዮጵያዊ ነወይ? የሚል ሲሆን፥ ሁለተኛው ደግሞ “አንዳንድ አጋንንትን እናስወጣለን የሚሉ ሰዎች ግን በኢየሱስ ስም ብቻ ሳይሆን በጻድቃንና በሰማዕታት ስም እናስወጣለን ይላሉ። በተጨማሪ አጋንንቱ ካደሩበት ሰው ጋር ትግል መግጠም፥ ሰውዮውን በመቊጠሪያ፥ በጧፍ፥ በመስቀል ወዘተ. መደብደብና የመሳሰሉ ድርጊቶችን ይፈጸማሉ። እነዚህንም ድርጊቶች በሲዲ እያሠራጩ ከክርስትና ትምህርት ውጪ የሆኑ ልምምዶችን ያስፋፋሉ። እውን እነዚህ ነገሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ናቸውን?”
*  ታላላቅ መንፈሳውያን ቃላት
ስለ ዐዲስ ልደት ምንነት ትምህርት ያገኛሉ፡፡
*  ፍካሬ መጻሕፍት
“ወትቀውም ንግሥት በየማንከ” ለሚለው ጥቅስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ ሌሎችም ጽሑፎች ተካተዋልና ጮራን ያንብቡ፡፡ ሌሎችም እንዲያነቡ በማድረግ መንፈሳዊ አደራዎን ይወጡ፡፡

Sunday, December 9, 2012

ጋብቻ

የጋብቻ መሥዋዕትነት
በዝግጅት ክፍሉ
(በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 4 ላይ የቀረበ)

መግቢያ

ጋብቻ እግዚአብሔር በባልና በሚስት መካከል የሚገኝበት ቅንጅት ሲሆን፥ በቅንጅቱም ባልና ሚስት ፊት ለፊት ተያይተው ልባዊ መግባባት እንደሚኖራቸው በመጀመሪያው ጹሑፋችን ገልጸናል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የጋብቻ ቅንጅት እንደ እግዚአብሔር ዕቅድ እንዲሆን፥ በጋብቻ ውስጥ ያለውን አባወራነትና የሁለቱንም የተለያየ ኀላፊነት እንዴት እንደሚያብራራ ተመልክተናል፡፡ ይኸውም “የሴት ራስ ወንድ እንደ ሆነ” በእግዚአብሔር አብና በክርስቶስ መካከል ባለው አባወራነት ላይ ማለትም “የክርስቶስ ራስ እግዚአብሔር ነው” በሚለው የተመሠረተ መሆኑን አይተናል፡፡ ይህም ለባልና ለሚስት ምን ማለት እንደ ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን በመጥቀስ ገልጸናል፡፡ በመጨረሻም ጋብቻችን እንደ እግዚአብሔር ዕቅድ እንዲሆንና በሕይወታችን እንዲገለጽ አንዳንድ ጥያቄዎችን ጠይቀናል፡፡

በዚህ በሦስተኛው ጽሑፋችን ጋብቻን በተመለከተ ስለ ሌላ መሠረታዊ ሐቅ እግዚአብሔር ወደሚያስተምረን ወደ ዔደን ገነት እንመለስ፥ “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡” በጋብቻ ውስጥ የእርስ በርስ መቈራኘት መኖሩ (ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ)፤ ጥቅሱም ቊርኝቱ መሥዋዕትነትን እንደሚጠይቅ (ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል) ያስተምረናል፡፡ ሁኔታው በሴት አፈጣጠር ይታያል፤ ይኸውም እግዚአብሔር ከአዳም ጐን አንድ አጥንት ወስዶ ሴቲቱን ፈጠረ፤ ሴት የተገኘችው በአዳም “መሥዋዕትነት” ነበረ፡፡ ከዚህም በኋላ አዳም ሙሉ ሰው ሊሆን የሚችለው ከሚስቱ ጋር አንድ ሲሆን ብቻ ነበር፡፡ አዳምም “ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሥጋም ከሥጋዬ ናት” በማለቱ በጋብቻ ውስጥ ያለውን የርክክብና የመሥዋዕትነት ሁኔታ እንደ ተረዳ እናስተውላለን፡፡ የጋብቻ ቅንጅት የተቀደሰ ነውና በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ቅዱስ ግንኙነት እንደሚያመለክት ሐዋርያው ጳውሎስ ያስረዳናል፡፡ ጋብቻ የትርፍ ወይም የፌዝ ነገር ሳይሆን መሥዋዕትነትን የሚጠይቅ የርስ በርስ ርክክብ ያለበት ሁኔታ ነው፡፡