Friday, December 21, 2012

ፍካሬ መጻሕፍት

Read IN PDF
(በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 44 ላይ የቀረበ)

“ወትቀውም ንግሥት በየማንከ
በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት
ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአፅምኢ እዝነኪ”
“በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።
ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ” (መዝ. 44/45፥9-10)

ይህን የመዝሙረ ዳዊት ጥቅስ በሚያነብብ በአብዛኛው ሰው አእምሮ ውስጥ በቶሎ የምትከሠተው ድንግል ማርያም ናት። ይህ የሆነው ጥቅሱ ስለ እርሷ የተነገረ ስለ ሆነ ግን አይደለም። ስለ እርሷ የተነገረ ነው ተብሎ ስለ ተወሰደ፥ በተደጋጋሚ ከእርሷ ጋር ተያይዞ ስለ ተነገረ፥ በየወሩ በ21 ለበዓለ ማርያም የሚዜም ምስባክ ስለ ሆነ ነው ስለ እርሷ የተነገረ ያህል እየተሰማን የመጣው። ቅድስት ድንግል ማርያምን ንግሥተ ሰማይ ወምድር ብለው የሚያምኑ ክፍሎች፥ ሐሳባቸውን በዚህ ጥቅስ ለማስደገፍ ይሞክራሉ። እርሷን በንጉሥ እግዚአብሔር ቀኝ እንደ ተቀመጠች ንግሥትም ይቈጥሯታል።

ቃሉ ስለ ማን እንደ ተነገረ ከመጽሐፉ ተነሥተን እንመልክት። ጥቅሱ ለሚገኝበት ለዚህ የመዝሙረ ዳዊት ክፍል የዐማርኛው የ1953ቱ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስ “ለመዘምራን አለቃ፤ በመለከቶች፤ የቆሬ ልጆች ትምህርት፤ የፍቅር መዝሙር” የሚል ርእስ ተሰጥቶታል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለራሷ ባሳተመችው የ2 ሺሁ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስም “ለመዘምራን አለቃ በመለከቶች የቆሬ ልጆች ትምህርት የፍቅር መዝሙር” በማለት ይህንኑ ርእስ ነው ያስቀመጠው።
ይህ የቆሬ ልጆች መዝሙር በቊጥር 1 ላይ “ልቤ መልካም ነገርን አፈለቀ፥ እኔ ሥራዬን ለንጉሥ እነግራለሁ፤ አንደበቴ እንደ ፈጣን ጸሓፊ ብርዕ ነው።” ተብሎ እንደ ተመለከተው፥ የዚህ መዝሙር ዐላማ ስለ ንጉሡ መልካም ቅኔን መቀኘት ነው። ከቊጥር 2 አንሥቶም እስከ ቊጥር 9 ድረስ ስለ ንጉሡ ይቀኛል። ቀጥሎም ከቊጥር 10 እስከ 15 ድረስ ንግሥቲቱን ያመጣታል።

የንጉሡ ማንነት በግልጽ የተቀመጠ ስለ ሆነ ጥያቄ አያስነሣም። ጥያቄው ያለው ንግሥቲቱ ማናት? በሚለው ሐሳብ ላይ ነው። ከላይ እንደ ጠቀስነው ብዙዎች “ንግሥቲቱ” የሚለውን ለቅድስት ድንግል ማርያም ሰጥተው ይተረጒማሉ፤ እውን በዚህ ዐውድም ይሁን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የጌታ እናት በመሆኗ “ንግሥት” የሚለውን ለእርሷ መቀጸል ተገቢ ነው ወይ? የንጉሥ እናትስ ንግሥት ተብላ ትጠራለች ወይ?

ንግሥት የንጉሥ ሚስት እንጂ እናት አይደለችም። መዛግብተ ቃላትም ይህንኑ ነው የሚያረጋግጡት።
& የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ንግሥት የሚለውን ቃል፥ “በቁሙ፤ በአባቷ ፈንታ የነገሠች፤ እንደ ማክዳና እንደ ህንደኬ እንደ ዘውዲቱና እንደ ቢክቶሪያ ያለች ባለሙሉ ሥልጣን። … የንጉሥ ሚስት እተጌ፥ ባሏ ከርሱ ጋር ያነገሣት” ብሎ ነው የሚፈታው (1948፣ ገጽ 624)።
& የደስታ ተክለ ወልድ “ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት”ም በተመሳሳይ "ዐልጋው [ዙፋኑ] ያባቷ ኹኖ ባሏ ሳይነግሥ ብቻዋን የነገሠች እንደ ማክዳ ያለች፤ ወይም ዐልጋው የባሏ ኹኖ ከባሏ ጋር የነገሠች ይተጌ።” በማለት ይተረጒማል (1962፣ ገጽ 840)።
& በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማእከል ያሳተመው ዐማርኛ መዝገበ ቃላትም ንግሥት የሚለውን ስም “በዘውዳዊ አስተዳደር ዙፋን ላይ የተቀመጠች የሀገር መሪ። የንጉሥ ሚስት” ሲል ይፈታዋል (1993፣ ገጽ 286)። ቃሉ የንጉሥ ሚስትን እንጂ እናትን አያመለክትም ማለት ነው። ሌሎችም መዛግብተ ቃላት ቢኖሩ ከዚህ ውጪ ሊናገሩ አይችሉም።

በዚህ የመዝሙር ክፍል ከቊጥር 9-17 ስለ ንግሥቲቱ የተነገሩት ሐሳቦች ንግሥቲቱ የንጉሡ ሚስት እንጂ እናት መሆኗን አያሳዩም። ንግሥት የተባለችው ለጊዜው የሐሴቦን ንጉሥ ልጅ መሆኗን እንረዳለን (ቊ. 13)። ንጉሡ ውበቷን ወድዷል። የእርሱ ሚስት ስላደረጋትም እርሱን በመከተል ትታቸው የወጣችውን ወገኖቿንና የአባቷን ቤት እንድትረሳ ይነግራታል። እርሷ የንጉሡ ሚስት በመሆን የምታገኘው ልዩ ልዩ ክብርም በዚህ ክፍል ውስጥ ተዘርዝሯል፤ - የምድር ባለጠጎች አሕዛብ በፊቷ ይማለላሉ፤ ልብሷ ለንግሥትነቷ የሚመጥን የወርቅ መጐናጸፊያ ነው፤ ሚዜዎቿ የሚሆኑ ደናግልም በእርሷ መሪነት ወደ ንጉሡ ይቀርባሉ፤ በአባቶቿ ፈንታ ስሟን ለልጅ ልጅ የሚያሳስቡ ልጆች ተወልደዉላታል፤ ንግሥት እንደ መሆኗም በአባቶቿ ፈንታ የተወለዱላትን ልጆች በምድር ላይ ገዥዎች አድርጋ ትሾማቸዋለች። እነዚህ ሁሉ በክፍሉ የተዘረዘሩት የንግሥቷ መገለጫዎች፥ ንግሥቲቱ የንጉሡ ሚስት እንጂ እናት አለመሆኗን ያሳያሉ።

ወደ መዝሙሩ ፍጻሜ ስንሄድ የዕብራውያኑ ጸሓፊ ከመዝሙር 44/45 ውስጥ ጠቅሶ ስለ ክርስቶስ የተናገረውን ቃል እናገኛለን። “ስለ ልጁ ግን፥ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው ይላል” የሚለው ከተጠቀሰው መዝሙር ቊጥር 6-7 ላይ የተወሰደ ነው። ስለዚህ የቆሬ ልጆች በዚህ ክፍል የዘመሩት ስለ ክርስቶስ ነው ማለት ነው። ንጉሥ የተባለው ክርስቶስ ከሆነ፥ ንግሥቲቱ ታዲያ ማናት? ክፍሉ የተነገረው ስለ መሲሑ (ክርስቶስ) ነውና፥ “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።” ተብሎ የተነገረላት ንግሥት ቤተ ክርስቲያን እንጂ ሌላ ልትሆን አትችልም።

በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ እግዚአብሔር የሕዝቡ የእስራኤል ባል እንደ ሆነ፥ እስራኤልም ሚስቱ እንደ ሆነች ተጽፏል (ኢሳ. 54፥5-6፤ ኤር. 3፥14፤ ሆሴ. 2፥4)። የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ደግሞ፥ ክርስቶስን በሙሽራ ቤተ ክርስቲያንን በሙሽሪት ገልጸዋቸዋል (ዮሐ. 3፥29፤ 2ቆሮ. 11፥2፤ ራእ. 19፥7-8፤ 21፥9፤ 22፥17)።

“ወትቀውም ንግሥት በየማንከ - ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” ለሚለው ንባብ በግእዙ መዝሙረ ዳዊት አንድምታ ላይ ከተሰጡት ትርጉሞች መካከል የመጀመሪያው ምእመንን (ቤተ ክርስቲያንን) የተመለከተ ነው። አንድም ብሎ ግን ለቤተ ክርስቲያን ሰጥቶት የነበረውን ትርጒም ለማርያም በግል በመስጠት ጥቅሱን አለንባቡ አለምስጢሩም ይፈታዋል (1982፣ ገጽ 240)።

በግብረ ሐዋርያት ተጽፎ እንደምናነበው ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት በኋላ፥ በኢየሩሳሌም ተሰብስበው የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ በመጠባበቅ በጸሎት ይተጉ ከነበሩት 120 ሰዎች መካከል አንዷ ቅድስት ድንግል ማርያም ነበረች (ሐ.ሥ. 1፥12-15)። ይህች ጉባኤ፥ ቤተ ክርስቲያን እንደ ሆነችና የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችውም በእነርሱ አማካይነት እንደ ሆነ ግልጽ ነው። በዚህ ውስጥ የጌታ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም የቤተ ክርስቲያን የአካል ክፍል ወይም ከምእመናን አንዷ በመሆኗ፥ ንግሥት ከተባሉት የቤተ ክርስቲያን አባላት መካከል ናት እንጂ፥ ከዚህች አንዲት የክርስቶስ አካል ውጪ በተለየ ሁኔታ ልትቈጠርና ንግሥት ልትባል የምትችልበት አግባብ ግን የለም። እንዲህ ስንል ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሚመሰክረውን እውነት ሳንሸራርፍና ሳንጨምርበት ማስቀመጣችን ነው እንጂ እርሷን ዝቅ ማድረጋችን እንዳልሆነ በትሕትና እንገልጻለን።  

ጥቅሱን ለማርያም መስጠት ለምን አስፈለገ?
በአገራችን “የእናት አማላጅ ፊት አያስመልስ አንገት አያስቀልስ” የሚል ብሂል አለ። ብዙ ጊዜ ብሂሉ የሚነገረው ከቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ ጋር ተያይዞ ነው። ብሂሉን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ትረካዎችም በአዋልድ መጻሕፍት ውስጥ በብዛት ይገኛሉ። “ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” የሚለው ጥቅስ አለንባቡና አለምሥጢሩ ለቅድስት ድንግል ማርያም የተሰጠውም ለብሂሉ ማጠናከሪያ ይሆን ዘንድ ይመስላል። እርሷ በንጉሥ ክርስቶስ ቀኝ የቆመች ንግሥት ተደርጋ ተወስዳለች፤ በቀኙ የቆመችውም ለምልጃ ነው ተብሎ ታምኗል። ይሁን እንጂ በዚህ ምድር ያሉ ቅዱሳን ካንቀላፉ ቅዱሳን ጋር የማይታይ መንፈሳዊ ኅብረት እንጂ በቀጥታ የሚገናኙበት መሥመር የላቸውም። በዚህ ዓለም ያሉትም ከጥቂቶችና በአካል ከሚተዋወቁት በቀር በዐይን የማይታይ መንፈሳዊ ኅብረት እንጂ ቀጥተኛ ግንኙነትም ሆነ ኅብረት የላቸውም። ስለዚህ ወዳንቀላፉ ቅዱሳን የአማልዱን ጥያቄ የምናቀርብበት እድል የለም። አዋልድ መጻሕፍት ግን ይህ ይቻላል ነው የሚሉት። እነርሱ በሚሉት መንገድ ቢታሰብ እንኳ፥ ተገቢነት የሌለውና ምልጃ ሊጠየቅበት የማይገባ ጒዳይ ሁሉ፥ የእናት ምልጃም ቢሆን እንኳ፥ በተማላጁ በኩል ተቀባይነት ያገኛል፥ ምላሽም ያሰጣል ማለት አይደለም።

የዳዊት ልጅ  ሰሎሞን ከነገሠ በኋላ፥ አጊት ከተባለች ሴት የተወለደው ሌላው የዳዊት ልጅ አዶንያስ መንገሥ ባይሆንለትና ዙፋኑ ለሰሎሞን ቢሰጥበት፥ ዳዊትን በእርጅናው ታገለግለውና ታሞቀው የነበረችውን ቆንጆዪቱን ሱነማዪቱን አቢሳን እንዲድርለት የሰሎሞንን እናት ቤርሳቤህን አማላጅ አድርጎ ወደ ሰሎሞን ልኳት ነበር። ቤርሳቤሕን የላከው “የእናት አማላጅ ፊት አያስመልስ አንገት አያስቀልስ” ብሎ ይሆናል። “አያሳፍርሽምና ሱነማዪቱን አቢሳን ይድርልኝ ዘንድ ለንጉሡ ለሰሎሞን እንድትነግሪው እለምንሻለሁ” ሲልም ተማጽኗት ነበር (1ነገ. 2፥17)። “ቤርሳቤሕም፥ መልካም ነው፥ ስለ አንተ ለንጉሡ እነግረዋለሁ አለች። ቤርሳቤሕም የአዶንያስን ነገር ትነግረው ዘንድ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ገባች። ንጉሡም ሊቀበላት ተነሣ፤ ሳማትም፤ በዙፋኑም ተቀመጠ። ለንጉሡም እናት ወንበር አስመጣላት፥ በቀኙም ተቀመጠች። እርስዋም፦ አንዲት ታናሽ ልመና እለምንሃለሁ አታሳፍረኝ አለች። ንጉሡም። እናቴ ሆይ፥ አላሳፍርሽምና ለምኚ አላት። እርስዋም፦ ሱነማዪቱ አቢሳ ለወንድምህ ለአዶንያስ ትዳርለት አለች። ንጉሡም ሰሎሞን ለእናቱ መልሶ፦ ሱነማዪቱን አቢሳን ለአዶንያስ ለምን ትለምኝለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ ነውና መንግሥትን ደግሞ ለምኚለት። ካህኑም አብያታርና የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ ደግሞ ከእርሱ ጋር ናቸው አላት። ንጉሡም ሰሎሞን፦ አዶንያስ ይህን ቃል በሕይወቱ ላይ አለመናገሩ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፥ ይህንም ይጨምርብኝ። አሁንም ያጸናኝ፥ በአባቴም በዳዊት ዙፋን ላይ ያስቀመጠኝ፥ እንደ ተናገረውም ቤትን የሠራልኝ ሕያው እግዚአብሔርን! ዛሬ አዶንያስ ፈጽሞ ይገደላል ብሎ በእግዚአብሔር ማለ። ንጉሡም ሰሎሞን የዮዳሄን ልጅ በናያስን ላከ፤ እርሱም ወደቀበት፥ ሞተም።” (ቊ. 18-25)።

ንጉሡ እናቱን ወንበር አስመጥቶ በቀኙ አስቀምጧት ነበር። “እናቴ ሆይ፥ አላሳፍርሽምና ለምኚ” ብሏትም ነበር። ይሁን እንጂ ልመናዋ በንጉሡ በልጇ ዘንድ ተገቢ ሆኖ ባለመገኘቱ፥ ምንም እናቱ ብትሆን የገባላትን ቃል ሊጠብቅ አልቻለም። አዶንያስ አቢሳን ሚስቱ ሊያደርጋት ካለመቻሉም በላይ ሕይወቱንም ዐጣ። እናትም ብትሆን እንኳ ልመናዋ ሁሉ ይሰማል ማለት እንዳይደለ ከዚህ ታሪክ እንማራለን። ከዚህ አንጻር “የእናት አማላጅ ፊት አያስመልስ ዐንገት አያስቀልስ” የሚለው ብሂልም በጥያቄ ውስጥ ይወድቃል። 

በአዋልድ መጻሕፍት ውስጥ ድንግል ማርያም ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን ምልጃ ጠየቀችባቸው የተባሉቱ አንዳንዶቹ ጒዳዮች የጌታን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን ጨምሮ የእግዚአብሔር ሰዎች ምልጃ ሊጠይቁባቸው የማይገቡና በእግዚአብሔር ቃል ከተገለጠው የእግዚአብሔር ፈቃድና ሐሳብ ጋር ፈጽሞ የማይስማሙ ናቸው። በተኣምረ ማርያም ውስጥ ስለ በላኤ ሰብእ በተጻፈው ትረካ ውስጥ፥ ደኻው ሰው በውሃ ጥም እጅግ ተቃጥሎ “ስለ እግዚአብሔር ብለህ ውሃ አጠጣኝ” ሲለው በላኤ ሰብእ እጅግ እንደ ተቈጣውና በማርያም ስም ሲለምነው ግን እንደ ሰጠው ተጽፏል። በዚሁ መነሻነት በላኤ ሰብእ ሲሞት ማርያም ተከራክራ ነፍሱን እንዳስማረች ተጽፏል (ተኣምረ ማርያም 1985፣ ገጽ 70)።

በቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ ላይ የምናገኘው የአንድ ባለጠጋ ታሪክም ተመሳሳይ ይዘት አለው። ባለጸጋው የነበረውን ሀብት “ላዝማሪ ለዘዋሪ እየሰጠ ዐለቀበት።” ከዚያም ሀገሩን ጥሎ ወደ ሌላ ወደማይታወቅበት ስፍራ ሲሄድ፥ ሰይጣን የጨዋ ልጅ መስሎ ወዴት ትሄዳለህ ይለዋል። ባለጠጋውም የደረሰበትን ይነግረዋል። ሰይጣንም ድንጋዩን በምትሐት ወርቅ አድርጎ በማሳየት ይህን ብሰጥህ አትመለስም ወይ? ሲለው እመለሳለሁ ይላል። እርሱም የምሰጥህ የምፈልገውን ስትፈጽምልኝ ነው በማለት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን እንዲክድ ይጠይቀዋል። እርሱም ይክዳል። መላእክት ጻድቃን ሰማዕታት አያማልዱም በል ይለዋል። እርሱም ይላል። በመጨረሻም የማርያምን ወላዲተ አምላክነት ካድ ይለዋል። ይሁን እንጂ ባለጠጋው እርሷንስ አልክድም በማለት ይመልሳል፤ በዚህ ጊዜ ሰይጣን ወርቅ አስመስሎ የሰጠውን ደንጊያ ተቀብሎ በእርሱ ይመታውና ይገድለዋል።

በምድር ላይ በኖሩት ሕይወት መሠረት የበላኤ ሰብእም ሆነ የባለጠጋው ነፍስ ዘላለማዊ መኖሪያ ሊሆን የሚችለው ሲኦልና ገሃነመ እሳት ነው። እግዚአብሔርን የካዱትን በላኤ ሰብእንና ባለጠጋውን ቅድስት ድንግል ማርያም በምልጃዋ አስታረቀች የሚለው ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም። በስሟ የተደረሰ ድርሰት ካልሆነ በቀርም የጌታ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔርን የካደውን ከእግዚአብሔር ጋር ልታስታርቅ አትችልም። እንኳ እንዲህ ያለው የከፋ በደል ቀርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ላልሰማውና እግዚአብሔር ለናቀው ለሳኦል በሕይወተ ሥጋ ሳለ ሲያለቅስ የነበረውን ሳሙኤልን፥ “በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው?” ብሎ ዳዊትን እንዲቀባው ነገረው። በዚህም የሳሙኤል ልቅሶ ለሳኦል እንዳልጠቀመው እናስተውላለን (1ሳሙ. 16፥1፡12-13)። በሕይወተ ሥጋ አንዱ ስለ ሌላው እንዲማልድ ሞገስን የሰጠ እግዚአብሔር፥ በአንዳንድ ሁኔታዎች ከዚህ ቀደም በፊቱ ለመቆም ሞገስ ያገኙና ያንቀላፉ ቅዱሳን መማለድ ቢችሉ እንኳ ልመናቸው ተቀባይ እንደማይኖረው እግዚአብሔር የተናገረበት ሁኔታ አለ። ነቢዩ ኤርምያስ “እግዚአብሔርም እንደዚህ አለኝ። ሙሴና ሳሙኤል በፊቴ ቢቆሙም፥ ልቤ ወደዚህ ሕዝብ አይዘነብልም ከፊቴ ጣላቸው ይውጡ” ሲል መስክሯል (ኤር. 15፥1)።
ቅድስት ድንግል ማርያምን ጨምሮ የእግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽሙ እንጂ ከእግዚአብሔር ፈቃድ በተቃራኒ የሚቆሙ አይደሉም። ሐዋርያው ዮሐንስ በመልእክቱ፥ “ማንም ወንድሙን ሞት የማይገባውን ኀጢአት ሲያደርግ ቢያየው ይለምን፥ ሞትም የማይገባውን ኀጢአት ላደረጉት ሕይወት ይሰጥለታል። ሞት የሚገባው ኀጢአት አለ፤ ስለዚያ እንዲጠይቅ አልልም” (1ዮሐ. 5፥16) በማለት፥ በሕይወተ ሥጋ ያለን ክርስቲያኖች ስለ ሌሎች ምልጃ የምናቀርብባቸው ኀጢአቶች እንዳሉ ሁሉ፥ ምልጃን ልናቀርብባቸው የማይገቡ ኀጢአቶች መኖራቸውንም ያስረዳል።

“ሞት የሚገባው ኀጢአት” በሚለው ሐሳብ ዙሪያ ሊቃውንት የተለያየ አመለካከት ያንጸባርቃሉ። በመልእክተ ዮሐንስ ውስጥ ሐዋርያው ያነሣውና ምልጃ እንዳይቀርብበት የከለከለው ኀጢአት ምን ይሆን? በመልእክቱ ውስጥ የተገለጸው አንዱና ዋናው ኀጢአት የክርስቶስ ተቃዋሚ መሆን ነው። “ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው” እንዲል (1ዮሐ. 2፥18፡22)። መቼም አግዚአብሔርን ከመካድ የበለጠና የሚከፋ ኀጢአት አይኖርም። “ሰውስ ሰውን ቢበድል እግዚአብሔር ይፈርድበታል፤ ሰው ግን እግዚአብሔርን ቢበድል ስለ እርሱ የሚለምን ማን ነው?” የሚለውም ቃል እግዚአብሔርን በቀጥታ የበደለን ሰው የሚያስታርቀው አማላጅ እንደማይኖር ያብራራል (1ሳሙ. 2፥25)። ይልቁንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለራሷ ያሳተመችው የ2ሺሁ ዓ.ም. መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጥቅስ፥ “ሰውስ ሰውን ቢበድል ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩለታል፤ ሰው ግን እግዚአብሔርን ቢበድል ወደ ማን ይጸልዩለታል?” ነው የሚለው።


ከላይ እንደ ተመለከትነው “ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” የሚለው ጥቅስ፥ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። በጥቅሱ ሽፋንነት እየተሠራጩ የሚገኙት ልዩ ልዩ ኢመጽሐፍ ቅዱሳውያን ትምህርቶች ሁሉ ግን ከእግዚአብሔር ሐሳብ ውጪ ስለ ሆኑና የድንግል ማርያምን “ርኅራኄ” በመግለጽ ስም ሰው እግዚአብሔርን እስከ መካድ ቢደርስ እንኳ በእርሷ ምልጃ ይድናል ወደሚል የክሕደት ትምህርት የሚወስዱና ኀጢአትን የሚያበረታቱ ናቸውና በክርስትና ትምህርት ውስጥ ተቀባይ የላቸውም።

1 comment:

  1. እግዚአብሔር ይባርካችሁ ጮራዎች።

    ReplyDelete