Sunday, December 30, 2012

መሠረተ እምነት

Read in PDF
(በጮራ ቊጥር 4 ላይ የቀረበ)
         ከናሁ አዳም
(ካለፈው የቀጠለ)

ባለፈው ዕትም (ጮራ ቍጥር 3 ገጽ 18-20) ይሆዋ በአካል ሦስት መሆኑን፥ እያንዳንዱም አካላዊ መንፈስ በራሱ “የሠራዊት ጌታ ይሆዋ” ተብሎ የመጠራትና የመመለክ ባለመብት እንደ ሆነ፥ የብሉይ ኪዳን አባቶች ተረድተው የነበረ መሆኑን ከእግዚአብሔር ቃል ማለት ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አንብበን ከሐዲስ ኪዳንም ጋር አመሳክረን እንደ ነበረ ይታወሳል፡፡ በዛሬው ዕትምም ከዚያው በመቀጠል የሚከተሉት ነጥቦች በሐዲስ ኪዳን ትምህርት እንመርምራቸው፡፡

ነጥብ (ጭብጥ) ሦስት
ከሥላሴ እያንዳንዱ አካል የባሕርይ ምሉዕነትና የህላዌ (አኗኗር) ፍጹምነት አለው፤ ለሥራውም በባለቤትነት ይታወቃል፡፡

ማስረጃ 1. ሉቃ. 1፥35
የምሥራች ነጋሪው ገብርኤል ወደ ድንግል ማርያም በተላከ ጊዜ እንዲህ አላት፤  “... መንፈስ ቅዱስ ወዳንቺ ይመጣል (1)፤ የልዑል (አብ) ኀይልም ይጸልልሻል (2)፤ ስለዚህ ደግሞ ካንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል (3)፡፡”

ሀ) ወደ ድንግል ማርያም ይመጣል የተባለው መንፈስ ቅዱስ በራሱ የባሕርይና የህላዌ ፍጹምነትና ምሉዕነት ያለው ለመሄድ፥ ለመምጣት… ለማናቸውም ለራሱ ግብር ባለቤት የሆነ አካላዊ መንፈስ ነው፡፡

በድንግል ማርያም ማሕፀን የነበረው ፅንስ በመንፈስ ቅዱስ አሠራር የተገኘ እንደ ሆነ ማቴዎስ ሲያብራራ፥ “ከእርሷ የተፀነሰው [በ] ከመንፈስ ቅዱስ ነው” ብሏል፡፡ ድንግል የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ አሠራር ነውና በሉቃስ የተነገረው የመንፈስ ቅዱስ ቀደም ብሎ ወደ ድንግል የመምጣት ምክንያት ከአዳምና ከሔዋን ንጽሐ ጠባይዕ መጒደፍ ጀምሮ ከአባትና እናት ወደ ልጅ እየተላለፈ የመጣውን የኀጢአት ባሕርይ ሳይወርስ ቃል በቅዱስ ሥጋ እንዲፀነስና እንዲወለድ ለማድረግ መሆኑን ይገነዘቧል፡፡ በሥጋ፥ በነፍስና በመንፈስ የተዋቀረውን የሰብኣዊነትና የሁለንተና (1ተሰ. 5፥23) ከድንግል አካል የመክፈልን፥ የማንጻትና የማዋሐድን ሥራ መንፈስ ቅዱስ አከናወነው፡፡ ማንጻት፥ መቀደስ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነውና (1ቆሮ. 6፥11)፡፡

ለ) “የልዑል ኀይል ይጸልልሻል፡፡” ጸለለ የሚለውን ግስ በመጋረድ ትርጒሙን የምንረዳው ከሆነ እንደ አቧራ የመሰለውን አላስፈላጊውን እየተከላከለ የሚፈለገውን ብርሃን እንደሚያሳልፍ መጋረጃ የአብ ኀይል ጸልሏታል፡፡ እንዲሁም “ጸለለ” ን በማጥለል ፍቺ የምንተረጒመው ቢሆን ግን ፈሳሽን እያጠለለ ንጹሑን ወደሚፈለገው ቃ ሲያሳልፍ የማይፈለገውን ከንጹሕ በመለየት ከውጪ የሚያስቀር ማጥለያ ሆኖ የአብ ኀይል እንደ ሠራ ያስገነዝባል፡፡ (ስለ ጸለለ ትርጒም መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ 1948፥ ገጽ 755-756 ይመልከቱ)፡፡

ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ቃል ሊዋሐድ ያለውን የሰብኣዊነትን ሁለንተና በመክፈል፥ በማንጻትና በማዋሐድ ድንግል እንድትፀንስ ስላደረገ፥ ጌታ እግዚአብሔር አብም በኀይሉ በመጸለል ፅንሱን ስለ ተንከባከበ፥ የሥራቸው ውጤት “ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፡፡” ማለትን አስከተለ፡፡

ሐ) ከአብ ጋር በተለየ አካል በእግዚአብሔርነት ደረጃ የነበረ ቃል የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ከድንግል ተፀነሰ፤ ተወለደም እንደ አብና መንፈስ ቅዱስ የህላዌ ፍጹምነት እንዳለው አስተዋልነው (ዮሐ. 1፥1-14፤ 14፥26)፡፡

የጥቅሱ ሐሳብ ሲጠቃለል አንዱ ሌሎቹን እንዳልሆነ፥ ሌሎቹ አንዱን እንዳልሆኑ እናስተውላለን፡፡ ከሥላሴ እያንዳንዱ አካላዊ መንፈስ በባሕርይ ምሉዕነትና በህላዌ ፍጹምነት ተገኝቶ ራሱን የገለጸበትን ሥራ ሲሠራ ያታያል፡፡

አንዱ አካላዊ መንፈስ የሁለቱ ግልባጭ አይደለም፤ ጊዜውን እየጠበቀ በሦስት ስሞችና ኹነታዎች የሚገለጽ አንድ አካልም አይደለም፡፡ በአንድ ጊዜ የሚከናወኑትን ሥራዎች በየድርሻቸው የሚሠሩ የህላዌ ፍጹምነት ያላቸው ሦስት አካላት በጥቅሱ ይታያሉ፤ “መንፈስ ቅዱስ ወደ አንቺ ይመጣል፤ የልዑል ኀይል ይጸልልሻል፤ ካንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፡፡”

ማስረጃ 2. ሉቃ. 2፥39
“ሕፃኑ አደገ፤ በመንፈስ ጠነከረ፤ የእግዚአብሔር ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ፡፡” የሕፃኑ ኢየሱስ እድገት ጥንካሬና በጸጋ መሞላት በተለያዩ ወቅቶች በአንድ የግብር ባለቤት የተሠራ ክንዋኔ አልነበረም፡፡ ሦስቱም (ሥላሴ) በተገለጹበት የሥራ ድርሻ በአንድ ወቅታዊ ጊዜ የተካፈሉበት ሂደት ክንዋኔ ነው፡፡

ማስረጃ 3
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ፥ “... መንፈስ ቅዱስ በርግብ መልክ ወርዶ ዐረፈበት የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ድምፅ መጣለት” እያሉ ወንጌላውያን ጽፈዋል (ማቴ. 3፥16-17፤ ማር. 1፥10-11፤ ሉቃ. 3፥21-22)፡፡

የኢየሱስን ማንነት ለማሳወቅ (ለማስተዋወቅ) ሆን ተብሎ በተዘጋጀው ክብረ በዓል ላይ፥
v ተጠማቂው ኢየሱስ ማለት ሰው የሆነው ወልደ እግዚአብሔር ይታያል፡፡
v መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ላይ ሲያርፍ ይታያል፡፡
v ይህ ልጄ ነው የሚለው የአብ ድምፅ ይሰማል (ዮሐ. 1፥32-34፤ 2ጴጥ. 1፥17)፡፡

ማስረጃ 4. ማቴ. 28፥19-20
እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፥ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ የሚለው ትእዛዝ ሥላሴን ለማወቅ በቂ ትምህርት ነው፡፡

ሐዋርያት ይሆዋ በሥሉስ አካላት የተገለጸ አንድ አምላክ ነው ብለው አያምኑም ነበር እያሉ አርዮሳውያንና ሰባልዮሳውያን ይናገራሉ፡፡ አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ ሦስት መሆናቸውን ቈጥረው አልደረሱበትም ለማለት፥ ወይስ በዚያ ጊዜ እስከ ሦስት የመቊጠር ዕውቀት አልነበረም ሊሉ ፈልገው ይሆን?

ትምህርተ እምነታቸው በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት ላይ አለመመሥረቱን እንዲረዱ፥ ሊያስተውሉ የሚችሉበትን ይነ ልቦና ሥላሴ እንዲያበሩላቸው ልንጸልይላቸው ይገባል፡፡

አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያትና በተከታዮቻቸው ዘመን በግልጽ የታወቀ የሥላሴ ስም እንደ ሆነና ይሆዋ ሥላሴ፤ ሥላሴም ይሆዋ መሆኑን በመጠቈም ለምእመናን ትምህርት የተሰጠበት መሠረተ እምነት እንደ ነበረ ከዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት የሚከተሉትን ጥቅሶች በማንበብ እናረጋግጥ፡፡ በእያንዳንዱ ጥቅስ አብን፥ ወልድን፥ መንፈስ ቅዱስን በሚወክሉት ስሞች ግርጌ እናሥምር፡፡

ዮሐ. 14፥15-16፡25፡26፤ 15፥26-27፤ 16፥7-10፤
ሐ.ሥ. 1፥4-5፤ 10፥38፤ 20፥27-28
ሮሜ 1፥1-4 ፤ 15፥16፤ 17፥30
1ቆሮ 2፥10-16፤ 6፥9-11፡14-20፤ 12፥3-6
ገላ. 4፥6
ኤፌ. 1፥13-14፤ 2፥18-20፤ 4፥30-32
ቲቶ 3፥4-7
ዕብ. 9፥13-14
1ጴጥ. 1፥1-2፤ 3፥18፤
1ዮሐ. 4፥2

አርዮሳውያን እንደሚሉት እነዚህ ጥቅሶች ከ300 ዓ.ም. በኋላ የተጻፉ ስላልሆኑ፥ ሐዋርያት ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በተላለፈላቸው ምስክርነት መነሻ ይሆዋ ሥላሴ፥ ሥላሴም ይሆዋ እንደ ሆነ እምነታቸውን የገለጹባቸው ያስተማሩባቸውና ጌታ በመንፈሱ በኩል የተወልን የቃሉ ማስረጃዎች ናቸው፡፡

ነጥብ (ጭብጥ) አራት
በእስራኤላውያን አካባቢ የነበሩ አረማውያን ይሆዋን በአንድም በብዛትም ይጠሩት ነበር፡፡
በእስራኤል ልጆች አካባቢ የነበሩ አረማውያን ስለ ይሆዋ መጠነኛ ግንዛቤ ነበራቸው፡፡ አረማውያንም በመካከላቸው ወይም በጉርብትናቸው ከነበሩት እስራኤላውያን ምስክርነት የተመጠነ ጠቅላላ ዕውቀትን ሊቀሥሙ ችለው እንደ ነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቊመናል፡፡

መቼም ዕብራውያን አማኞች በአንድ ይሆዋነት የሚታወቀው አምላካቸው ራሱን በሦስትነት መግለጹን ተረድተው እንደ ነበር ቀደም ሲል የጨበጥነውን የትምህርት ሐቅ በዚህ ስፍራ ባንደግመውም አንባቢ ያስታውሰዋል ብለን እናምናለን፡፡

ይህ እምነት የምሁራኑ ብቻ ሳይሆን የተራው ሕዝበ እስራኤል እምነት ጭምር ስለ ነበረ ዐብሮአቸው ወይም በጉርብትናቸው ለኖሩት አረማውያን በምስክርነታቸው የእስራኤል አምላክ ይሆዋ ኤሎሂም (ሥሉስ) ሆኖ በአንድነቱ የሚታወቅ መሆኑን የሰበኩላቸውና አረማውያኑም ሐሳቡን የተረዱላቸው መሆኑን የሚጠቊሙ ፍንጮች ይገኛሉ፡፡ 

1.    የይሆዋ ሥሉስነት በተራው ሕዝበ እስራኤል ልብ ጠልቆ ስለ መግባቱ
ሙሴ በሲና ተራራ ለ40 ቀናት ያህል ከእግዚአብሔር ሕግንና ሥርዐትን ሲቀበል በቈየ ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ ሙሴ ከነበረበት ተራራ እስኪመለስ ድረስ የነበረውን የዝምታ ጊዜ መታገሥ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ የሙሴ ወንድምና ወኪል የነበረው አሮንን በፊታችን የሚሄዱ አማልክት (ኤሎሂም) ሥራልን አሉት፡፡ ስንት አማልክት እንዲሠራላቸው የጠየቁት ይመስላችኋል? የሕዝቡን ጥያቄ የተረዳው አሮን ግን የወርቅ ጌጦቻቸውን አቅልጦ ያቆመላቸው 1 የጥጃ ምስል ብቻ ነበር፡፡ ለሕዝቡም “እስራኤል ሆይ አማልክትህ እነዚህ ናቸው” አላቸው፡፡

በብዙ ቊጥር በኤሎሂምነት የሚታወቀውን አንዱን ይሆዋ በአንድ ጥጃ ምስል ማቅረቡ ምንም ከአረማውያን የተወረሰ የጣዖት አምልኮ ቢሆንም፥ ይሆዋን አምላካቸውን በሚጠሩበት ስም በብዙ ቊጥር፥ “አማልክትህ እነዚህ ናቸው” ማለቱ ሕዝቡ ስለ ይሆዋ ስላላቸው አስተሳሰብ አንዳች ትርጒም አይሰጠንምን?

አሮን አንዱን ጥጃ “አማልክትህ እነዚህ ናቸው” ሲላቸው ሕዝቡ ይህ የአንድ ጥጃ ምስል ነው፥ ሌሎቹስ የታሉ? በማለት አልጠየቁትም፡፡ አንዱን የጥጃ ምስል እንደ አንዱ ይሆዋ በብዙ ቊጥር በአማልክትነት መቀበላቸውን አያስረዳንምን?

እግዚአብሔርም በተራራው ላይ ከእርሱ ጋር ይነጋገር የነበረውን ሙሴን ስለ ሕዝቡ ኀጢአት ሲወቅሠው ሕዝቡ የተናገረውን እንደዚያው እንደ ተነገረበት ቃል ጠቀሰው “ሕዝብህ ከግብጽ ያወጡኝ አማልክቴ እነዚህ ናቸው በማለት ቀልጦ ለተሠራው ጥጃ ምስል ሰገዱለት፥ ሰዉለት” ብሎታል፡፡

ይሆዋ እንዲህ ሲል ለሙሴ መናገሩ፥ ሕዝበ እስራኤል፥ ከግብጽ ምድር ያወጡን አማልክታችን የሚሏቸውን ሥላሴን በአንድ ይሆዋ እንደ ተረዱት፥ ወይም ከግብጽ ያወጣቸው አንዱ ይሆዋ በአማልክትነት (ሥሉስነት) እንደሚታወቅ አድርገው ተቀብለውት እንደ ነበረ የልባቸውን በሚያውቀው ይሆዋ ንግግር የተብራራ አልሆነምን? (ዘፀ. 32፥1-24)፡፡

2. ፍልስጤማውያን የእስራኤልን አምላክ ይሆዋን እንዴት እንደ ተረዱት
ፍልስጥኤማውያን በጉርብትናም ተደባልቆ በመኖርም ከሕዝበ እስራኤል ጋር የተቈራኘ ታሪክ እንዳላቸው የታወቀ ነው፡፡ አንዱ ሕዝብ ሌላውን ለመግዛት ወይም ራሱን ነጻ ለማድረግ በየጊዜው ተዋግተው ነበር፡፡

በዚሁ መሠረት በዔሊ ዘመን ከፍልስጥኤማውያን ጋር በመዋጋት ላይ የነበሩት እስራኤላውያን በጠላቶቻቸው ላይ ድልን ለመቀዳጀት ፈልገው የይሆዋን የቃል ኪዳን ታቦት ከሴሎ ወደ ጦር ሰፈራቸው ወደ አቤንኤዘር አመጡት፡፡ ታቦቱ ወደ ጦር ሰፈር በደረሰ ጊዜ ሕዝቡ ምድርን ባናወጠ እልልታ ተቀበሉት፡፡

የይሆዋ የቃል ኪዳን ታቦት ወደ እስራኤል የጦር ሰፈር ሲገባ ያስተዋሉና በፍርሀት የተሸበሩ ፍልስጥኤማውያን  “እግዚአብሔር ወደ ሰፈር መጥቷል፤ ወዮልን ከእነዚህ ኀያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? እነርሱ እኮ ግብጻውያንን በልዩ ልዩ መቅሠፍት የመቱ አማልክት ናቸው” በማለት ተወያዩ፡፡

ፍልስጥማውያን ወደ እስራኤል ጦር ሰፈር ሲገባ ያስተዋሉት አንዱን የይሆዋን ቃል ኪዳን ታቦት ስለ ነበረ፥ “እግዚአብሔር ወደ ሰፈራቸው ገብቷል” በማለት በአንድ ቊጥር ገለጹት፡፡

ከእስራኤላውያን ምስክርነት የሰሙትን የአንዱን ይሆዋ ኤሎሂምነት (ሥላሴን) ሲያስታውሱ ደግሞ እነዚህ ኀያላን አማልክት ናቸው፤ እስራኤላውያንን በተኣምራታቸው ከግብጽ ያወጧቸው እነዚህ አማልክት ናቸው እኮ አሉ (1ሳሙ. 4፥1-8)፡፡

3. ባቢሎናውያን ይሆዋን የእስራኤል አምላክ እንዴት ተረዱት?ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ አናንንያ፥ አዛርያና ሚሳኤል የነበሩት ቡድን ከኢዮአቄም 3ኛ ዓመተ መንግሥት ጀምሮ በምርኮኝነት በባቢሎን እንደኖረ ይታወቃል ዳን. 1፥1-7፡፡

ናቡከደነፆር በነገሠ በ8ኛው ዓመት ወደ ይሁዳ በዘመተ ጊዜ 10‚000 እስራኤላውያንን ወደ ባቢሎን እንደ ገና ማርኮ ነበር (2ነገ. 24፥10-14)፡፡

በናቡከደነፆር በ19ኛው ዓመተ ንግሥ የይሁዳ መንግሥት ሲደመሰስ ብዛት ያላቸው እስራኤላውያን ለ3ኛ ጊዜ ወደ ባቢሎን ፈልሰው እንደ ነበረ እናስታውሳለን (2ነገ. 25፥8-12)፡፡

እነ ዳንኤል ስለ አምላካቸው ለባቢሎናውያን መመስከራቸው፥ ይሆዋም በምስክሮቹ ሕይወት ማንነቱን ለባቢሎናውያን ማሳወቁ ግልጽ ነው፡፡ ባቢሎናውያን አረማውያን ቢሆኑ ስለ እስራኤል አምላክ ስለ ይሆዋ መጠነኛ እውቀት ቀሥመው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህም የተነሣ ይህን ታላቅና መንፈስ የሆነ የእስራኤል አምላክ በአንድም በብዙ ቁጥርም ይጠሩት እንደነበረ ከመጽሐፍ ቅዱስ መረዳት ተችሏል፡፡

ሀ) በአንድ ቊጥር ሲጠሩት
ዳን. 2፥47 “በእውነት አምላካችሁ የአማልክት አምላክ፥ የነገሥታትም ጌታ ነው፡፡”         
ዳን. 3፥28-29 “የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ፡፡”
ዳን. 4.34-37 “እኔ ናቡከደናፆር … የሰማይን አምላክ አመሰግናለሁ፤ ታላቅም አደርገዋለሁ፡፡ አከብረዋለሁ፡፡”
ዳን. 6፥16-27 “እርሱ ሕያው አምላክ ለዘላለም የሚኖር ነው”

ለ. በብዙ ቊጥር ሲጠሩት
ዳን. 3፥25 “እነሆ እኔ የተፈቱ በእሳትም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎችን አያለሁ፡፡ ... የአራተኛው መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል፡፡”

የናቡከደነዖር ምስክርነት
ዳን. 4፥8-9፤18 ዳንኤል የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት ሰው
የንግሥቲቱና የንጉሡ ብልጣሶር ምስክርነት
ዳን. 5፥11-14 “ዳንኤል የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት ሰው”

የአረማውያን አማልክት በአንድ አካባቢ እንዲያውም በአንድ ቤት ቢኖሩ እንኳ በተለያዩ ሰዎች ከተለያዩ ነገሮች፥ በተለያዩ ጊዜያት የተሠሩ አንድ፥ ሁለት፥ ሦስት፥ አራት በማለት የሚቈጠሩ ናቸው፡፡ ስለ አንዱ የተነገረው ሌሎቹን አያጠቃልልም፡፡ የየራሳቸው ድርሳንና ገድል ያላቸው ልዩ ልዩ ናቸው፡፡ የእስራኤል አምላክ ይሆዋ ግን ዳር ድንበር የማይከልለው፥ ሁሉን የሠራ እርሱ ግን በማንም ያልተሠራ ዘለዓለማዊነቱንና ራሱን በሦስትነት የገለጸ መንፈስ እንደ ሆነ ከአማኞች እስራኤላውያን አንደበት የሰሙት አረማውያን አንድነቱንና ሦስትነቱ (ኤሎሂምነቱን አማልክትነቱን) ሊረዱ ቻሉ ማለት ነው፡፡


የሚያስገርመው ግን አረማውያን ከአማኞች ጋር በጉርብትና በመኖራቸው ስለ ይሆዋ ይህን ያህል ሲረዱ፤ አርዮሳውያንና ሰባልዮሳውያን ስለ አምላካችን ስለ እግዚአብሔር ዕለት ዕለት እየመሰከርንላቸው፤ የምንሰብከውንም ቃሉን እያነበቡ፤ ስለ ይሆዋ አንድነትና ሦስትነት ሳይገባቸው ዓመታት ማለፋቸው ነው፡፡ እውነትም የኢሳይያስ ትንቢት ተፈጽሞባቸዋል (ጮራ ቊጥር 3 ገጽ 20፤ ኢሳ. 6፥1-10፤ ዮሐ. 12፥36-42፤ ሐ.ሥ. 28፥25-27)፡፡

No comments:

Post a Comment