1ኛ ጥያቄ፥ ከእኅት ሐረገ ወይን፥ ጮራዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መልከ ጼዴቅ፥
“የስሙም ትርጓሜ በመጀመሪያ የጽድቅ ንጉሥ ነው፥ ኋላም ደግሞ የሳሌም ንጉሥ ማለት የሰላም ንጉሥ ነው። አባትና እናት
የትውልድም ቍጥር የሉትም፥ ለዘመኑም ጥንት ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ
ይኖራል” ይላል (ዕብ. 7፥2-3)። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ መልከ ጼዴቅ ኢትዮጵያዊ ነው የሚሉ ሰዎች ያጋጥማሉ። እውን
መልከ ጼዴቅ ኢትዮጵያዊ ነውን? ኢትዮጵያዊ ለመሆኑስ ምን ማስረጃ አለ?
መልስ፥ ከነቅዐ ጥበብ፥ ጠያቂአችን በቅድሚያ ስለ ጥያቄዎ
እናመሰግናለን። በመልከ ጼዴቅ ማንነትና ዜግነት ላይ የሚነሣው ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ ከተናገረው ወጣ ያለና ስለ እርሱ
ማንነት የተናገረበትን ዐላማ የሳተ ሆኖ ይታያል። እርስዎ እንዳሉት “መልከ ጼዴቅ ኢትዮጵያዊ ነው” ብለው በድፍረት የሚናገሩና
የጻፉም ሰዎች አሉ። ይህን ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት፥ በጽሑፍ ካሰፈሩ ሰዎች መካከል ሊቀ ጠበብት አያሌው ታምሩ አንዱና
ዋናው ናቸው ማለት ይቻላል። “የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ስለ ክህነት በተናገሩበት ክፍል፥
በኦሪት ክህነት ከመሰጠቱ በፊት “ከእግዚአብሔር ተመርጦ የተላከው በታማኝ ሽማግሌ በሴም አማካይነት ከእግዚአብሔር የተሾመው
ኢትዮጵያዊው መልከ ጼዴቅ ነው” ብለዋል። አክለውም “የመልከ ጼዴቅ ኢትዮጵያዊነቱ ከነገደ ካም በመወለዱ በስም አጠራሩ በኑሮ
ድርጅቱ ይታወቃል” ሲሉ ሦስት “ማስረጃዎችን” ጽፈዋል። አያይዘውም ሐዋርያው ጳውሎስ መልከ ጼዴቅ ከሰው መወለዱ እየታወቀ
አባትና እናት የሉትም፤ ዘመኑም አይቈጠርም፤ የተወለደበት፥ የሞተበት አይታወቅም ሲል የዘጋው የመልከ ጼዴቅን ሰውነት ረስቶ
ወይም ተሳስቶ ሳይሆን መልእክቱ የተጻፈላቸው ዕብራውያን አንቀበልም ብለው እልክ እንዳይጋቡና እንዳይሰናከሉ ነው ብለዋል። እርሱ
ስውር ቢያደርገውም “ደቀ መዝሙሩ ሐዋርያዊ ቀሌምንጦስ ዘእም ነገዱ ለካም ብሎ ገልጾታል” የሚልና ቀሌምንጦስ መልከ ጼዴቅ ከካም
ነገድ መሆኑን መናገሩን ጠቅሰዋል። ይህም የመልከ ጼዴቅ ኢትዮጵያዊነት የተገለጠባቸው ነገሮች ብለው ከዘረዘሯቸው ሦስት
“ማስረጃዎች” የመጀመሪያውና ትውልዱን የተመለከተው ነው።
ሁለተኛውና የመልከ ጼዴቅ ኢትዮጵያዊነት የተገለጠበት ነገር ደግሞ ስም አጠራሩ ነው ሲሉ ገልጠዋል፥
“በኢትዮጵያ መለከ ካለው ግስ የሚገኙት መልክ መለክ የሚባሉት ቃላት የክብር ስሞች ሆነው ይገኛሉ። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ
ነገሥታትና ገዥዎች መሊኩ መለክ ሰገድ እየተባሉ ይጠሩ ነበር። ትርጓሜውም ገዥ ገዥን የሚያሰግድ ማለት ሲሆን፥ መልከ ጼዴቅ
ማለት ንጉሠ ጽድቅ ንጉሠ ሰላም፥ የሰላም የጽድቅ ንጉሥ ማለት ነውና ከቋንቋው ከግእዝ የተመሠረተው ስሙ ሁለተኛ ምስክር ሊሆን
ችሏል” የሚል ነው።
“ሦስተኛውም የኑሮ ድርጅት በአዳምና በሔዋን ተመሥርቶ በኢትዮጵያውያን አበው ጸንቶ እንደሚኖረው ሥነ
ሥርዐት የላመ የጣመ አለመቅመስ፤ ዳባ መልበስ ጠጒርን አለመላጨት ጥፍርን አለመቊረጥ ከአንድ ቦታ በጸሎት ተወስኖ መኖር ከሱ
ተወርሶ እስከ ዘመናችን ደርሶ፥ በኢትዮጵያ አድባራትና ገዳማት ሲሠራበት ስናየው ሦስተኛው የዐይን ምስክር ሊሆነን ችሏል”
ብለዋል (ገጽ 66፡67፡68)።
እነዚህ ነጥቦች እውን በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጸውን መልከ ጼዴቅን የሚያሳዩ ናቸውን? ወይስ የኦርቶዶክስ
ተዋሕዶን ባህል እንዲላበስ አድርጎ መልከ ጼዴቅን መሣል? የሚለው በሚገባ ሊፈተሽ ይገባል። መልከ ጼዴቅ ሰው መሆኑ ግልጽ ነው።
የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን ተብሎ ስለ ተጠራም ንጉሥና ካህን መሆኑ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ነገዱ
አልተገለጸም። ወደ ፊት እንደምናስረዳው የመልከ ጼዴቅ ማንነት ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ይሆን ዘንድ ስለ ታቀደ በዚህ መንገድ
ብቻ እንዲገለጽ ያደረገው እግዚአብሔር ነው።
የመልከ ጼዴቅ ሹመቱ በሴም አማካይነት ነው የተከናወነው የሚለው አንድም ማስረጃ አይገኝለትም።
እንደሚታወቀው መልከ ጼዴቅ በአብርሃም ዘመን የነበረ የሳሌም ንጉሥ እና የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነው፡፡ አብርሃም ደግሞ
የሴም ዐሥረኛ ትውልድ እንደ መሆኑ መጠን በሴምና በእርሱ መካከል የብዙ ምእት ዓመታት ርቀት አለ (ዘፍ. 11፥10-26፤
1ዜና. 1፥24-27)። በሴምና በመልከ ጼዴቅ መካከልም ተመሳሳይ የዘመን ርቀት አለ ማለት ነውና ከብዙ ምእት ዓመታት በፊት
የሞተው ሴም፥ በአብርሃም ዘመን የነበረውንና የማያውቀውን መልከ ጼዴቅን ሾመው ማለት አያስኬድም። ይልቁንም ኢየሱስ ሊቀ ካህናት
ለመሆን ራሱን እንዳላከበረና በእግዚአብሔር እንደ ተሾመ ከሚናገረው የዕብራውያን መልእክት ተነሥተን ስናነጻጽረው፥ የመልከ ጼዴቅ
ሹመትም ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰው የተገኘ አለመሆኑን እንረዳለን (ዕብ. 5፥5-6)።
መልከ ጼዴቅ ከነዓናዊ ስም መሆኑ ባያጠራጥርም፥ ይህም ከካም ነገድ ይሆናል ለማለት የሚያስችል ፍንጭ
ቢሰጥም፥ “ኢትዮጵያዊ ነው” ወደሚል ድምዳሜ የሚያደርስ ግን አይደለም። ሌላው ቢቀር እንኳ መልከ ጼዴቅ የሳሌም ንጉሥ መሆኑ
ተነግሯልና መልከ ጼዴቅን ኢትዮጵያዊ ለማድረግ መሞከር፥ ኢየሩሳሌምን ኢትዮጵያ ወደ ማለት ይወስዳል። ነገር ግን ከመልክአ
ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ሳሌምንና ኢትዮጵያን የሚያገናኛቸው፥ መልከ ጼዴቅንም ኢትዮጵያዊ የሚያሰኘው አንዳች ምክንያት የለም።
“መልከ ጼዴቅ” የተሰኘው ባለ ዘርፍ ስም የግእዝ ስም ነው የሚለውም የሚያስኬድ አይደለም። በዐማርኛው እና
በግእዙ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናገኘው “መልከ ጼዴቅ” የሚለው ስም ምንጩ ግእዝ አይደለም። ግእዝ ከዕብራ ይስጥ የተዋሰውና
ተቀራራቢ የሆነ እጅግ መጠነኛ ሥነ ልሳናዊ ለውጥ በማድረግ የራሱ ያደረገው ስያሜ ነው። በውሰት አምጥቶ የራሱ ላደረገው “መልከ
ጼዴቅ” ለሚለው ስም ምንጩ ግእዝ ነው ማለት ትዝብት ላይ ከሚጥል በቀር ፍሬ የለውም። በግእዝ ሰዋስው መሠረት “መልክ” መለከ
ከሚለው ግስ ሊወጣ ይችላል (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ገጽ 593)። ይሁን እንጂ “ጼዴቅ” የሚለው ዘርፍ ግን
“ጸድቀ” ከሚለው የግእዝ ግስ ያልወጣ ዕብራይስጣዊ መሆኑ ግልጽ ነው። አለቃ ኪዳነ ወልድ በዕብራ ይስጥ “ጻዴ” የሚለው ቃል
ከስመ ፊደልነቱ በተጨማሪ “ጻድቅ” የሚል ፍቺ እንዳለው ጽፈዋል (ገጽ 744)። የግእዙ መዝሙረ ዳዊት ርእስም “ጻዴ ብሂል
ጻድቅ እግዚአብሔር” ማለት ነው ይላል (መዝ. 118/119፥137)። ስለዚህ ስሙ ግእዝ በተውሶ ያመጣው የዕብራይስጥ ስም ነውና
ኢትዮጵያዊ ስም ሊባል መልከ ጼዴቅንም ኢትዮጵያዊ ሊያሰኘው አይችልም።
ሊቀ ጠበብት አያሌው ሦስተኛ ማስረጃ ብለው ያቀረቡትና የመልከ ጼዴቅ “የኑሮ
ድርጅት” የተባለውም፥ በኢትዮጵያ አንዳንድ ገዳማት ሊታይ የሚችል አኗኗር እንጂ የመልከ ጼዴቅ አኗኗር ሊሆን አይችልም። መልከ
ጼዴቅ የልዑል እግዚአብሔር ካህን ብቻ ሳይሆን የሳሌምም ንጉሥ ስለ ነበረ፥ እርሱን ገዳማዊ አድርጎ ማቅረብ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ
ከተጻፈው ማንነቱ አንጻር የሚያስኬድ አይደለም። “የላመ የጣመ አለመቅመስ፤ ዳባ መልበስ ጠጒርን አለመላጨት ጥፍርን አለመቊረጥ
ከአንድ ቦታ በጸሎት ተወስኖ መኖር” ከእርሱ የተወረሰ ነው የሚለውም ምንም ማስረጃ የማይገኝለትና መልከ ጼዴቅን የግድ
ኢትዮጵያዊ ለማስመሰል ሲባል እርሱን ገዳማዊ አድርጎ ያቀረበ ገለጻ ነው። መልከ ጼዴቅ የሳሌም ንጉሥ መሆኑ ተገልጾአልና የልዑል
እግዚአብሔርም ካህን ነውና እነዚህ መግለጫዎች የሚስማሙት አይደሉም።
መጽሐፍ ቅዱስ ምስጢር አድርጎ የተወውን ነገር ለመግለጥ መሞከር አደገኛ አካሄድ ነው። እንደዚህ ላለ
ስሕተትም ይዳርጋል። ከዚህ ይልቅ “ምስጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ
ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው” (ዘዳ. 29፥29) ለሚለው መመሪያ ተገዢ መሆን ይገባል።
ከቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ስለ መልከ ጼዴቅ የሚነግሩን ኦሪት ዘፍጥረት፥ መዝሙረ ዳዊት እና የዕብራውያን
መልእክት ናቸው። ስለ መልከ ጼዴቅ መልስ መስጠት የምንችለው፥ ሙሴ በኦሪት ዘፍጥረት ስለ እርሱ የጻፈውን፥ ዳዊት ስለሚመጣው
መሲሕ ሊቀ ካህናትነት ከመልከ ጼዴቅ ጋር አያይዞ የተናገረውን ትንቢትና በእነዚህ ላይ ተመሥርቶ የዕብራውያኑ ጸሓፊ የሰጠውን
ማብራሪያ መሠረት በማድረግ ይሆናል። በእነዚህ ሦስት መጻሕፍት ውስጥ ግን መልከ ጼዴቅ ኢትዮጵያዊ ስለ መሆኑ አንድም ፍንጭ
አናገኝም። የመጻሕፍቶቹም ትኲረትና ዐላማ ይህ አይደለም።
በኦሪት ዘፍጥረት 14፥18-20 ላይ እንደ ተጻፈው በአብራም ዘመን የአሕዛብ ነገሥታት በየፊናቸው ተባብረው
ሲዋጉ፥ የአብራም የወንድሙ ልጅ ሎጥ የሚኖርባት የሰዶምና የገሞራ ነገሥታት ሸሹ። የተባበሩት አራት ነገሥታትም በሰዶምና በገሞራ
ያገኙትን ሁሉ ዘርፈው ሲሄዱ፥ ሎጥንም ማረኩት፤ ሀብትና ንብረቱንም ዘረፉ። ይህን የሰማው አብራም በቤቱ ተወልደው ያደጉ 318
ጦረኞችን አሰልፎ፥ ነገሥታቱን በማሳደድ ሎጥንና ዐብረው የተማረኩትን ወንዶችና ሴቶች፥ እንዲሁም ንብረቱን አስመለሰ። አብራም
ነገሥታቱን ድል አድርጎ ሲመለስ፥ የልዑል እግዚአብሔር ካህንና የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅ እንጀራና የወይን ጠጅ ይዞ በመውጣት
አብርሃምን እንዲህ ሲል ባረከው፤ “አብራም ሰማይንና ምድርን ለሚገዛ ለልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ነው፤ ጠላቶችህን በእጅህ
የጣለልህ ልዑል እግዚአብሔርም የተባረከ ነው አለውም” (ቊጥር 19-20)። አብራምም ይህን ቡራኬ ከእርሱ ከተቀበለ በኋላ
“ከሁሉ ዐሥራትን ሰጠው” (ቊጥር 20)። ከዚህ በኋላ መልከ ጼዴቅን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለአብርሃምም ሆነ ለሌላ ሰው ተገልጦ
አናገኘውም።
በዚህ ታሪክ ውስጥ መልከ ጼዴቅ የልዑል እግዚአብሔር ካህንና የሳሌም ንጉሥ መሆኑ ተነግሯል። ሳሌም ቀድሞ
ኢያቡስ ትባል የነበረችው ኢየሩሳሌም መሆኗ ግልጽ ሲሆን (1ዜና. 11፥4-7፤ መዝ. 75/76፥2)፥ መልከ ጼዴቅ የሚለው
ስምም በኢየሩሳሌም ሰፍረው ከነበሩት ከነገደ ካም ከሆኑት ከነዓናውያን
ወገን መሆኑን እንደሚያመለክት የመጽሐፍ ቅዱስ መተርጒማን ይናገራሉ፤ በዚሁ የስም ዘርፍ የሚጠራ ሌላውን የኢየሩሳሌም
ንጉሥ አዶኒ ጼዴቅንም እናገኛለን (ኢያ. 10፥1)።
መልከ ጼዴቅ የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነው። በካህንነቱ እንጀራና የወይን ጠጅ ይዞ በመውጣት አብርሃምን
ባረከው። ከአብርሃምም ዐሥራትን ተቀበለ። ዳዊትም በትንቢቱ ውስጥ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዐት አንተ ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ፥
እግዚአብሔር ማለ አይጸጸትም።” በማለት የመልከ ጼዴቅን ካህንነት ለኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናትነት ምሳሌ አድርጎ ጠቀሰ። የዕብራውያኑ
ጸሓፊም በዚሁ ላይ በመመሥረት የልዑል እግዚአብሔር ካህን መልከ ጼዴቅ ለሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ መሆኑን፥ ወይም
ኢየሱስ ሊቀ ካህናት የሆነው እንደ መልከ ጼዴቅ በሆነው ክህነት እንጂ፥ በአሮናውያን ክህነት መሠረት አለመሆኑን አብራርቷል።
በማብራሪያው የምንገነዘበው ስለ መልከ ጼዴቅ በቅዱሳት መጻሕፍት የሰፈረው ሁሉ፥ መልከ ጼዴቅ ለኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናትነት
ምሳሌ እንዲሆን አስቀድሞ በእግዚአብሔር የታቀደ መሆኑን ነው።
“የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን የሆነ ይህ መልከ ጼዴቅ አብርሃም ነገሥታትን ገድሎ ሲመለስ
ከእርሱ ጋር ተገናኝቶ ባረከው፤ ለእርሱም ደግሞ አብርሃም ከሁሉ ዐሥራትን አካፈለው። የስሙም ትርጓሜ በመጀመሪያ የጽድቅ ንጉሥ
ነው፥ ኋላም ደግሞ የሳሌም ንጉሥ ማለት የሰላም ንጉሥ ነው። አባትና እናት የትውልድም ቍጥር የሉትም፥ ለዘመኑም ጥንት
ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።” (ዕብ. 7፥1-3)።
በዚህ የሐዋርያው ገለጻ ውስጥ በአንድ ጊዜ ንጉሥም ካህንም የሆነው መልከ ጼዴቅ፥ ለኢየሱስ
ክርስቶስ ንጉሥነትና ሊቀ ካህናትነት ምሳሌ ይሆን ዘንድ አስቀድሞ መዘጋጀቱን እንገነዘባለን። የስሙ ትርጓሜ “የጽድቅ ንጉሥ”
እና “የሰላም ንጉሥ” መሆኑ የጽድቅና የሰላም ንጉሥ የሆነውን ክርስቶስን ያመለክታል (ኢሳ. 9፥6-7)።
ከአብርሃም ዐሥራትን በመቀበሉና ከአብርሃም በኋላ ብዙ ምእት ዓመታት ቈይቶ በኦሪት ሕግ መሠረት ካህን
የሆነው ሌዊ በአብርሃም ወገብ ውስጥ ሆኖ ዐሥራትን አውጥቷልና፥ ክህነቱ ከመልከ ጼዴቅ ክህነት የሚያንስ፥ የመልከ
ጼዴቅ ክህነት ደግሞ የሚበልጥ መሆኑን ያሳያል (ቊጥር 4-10)። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የልዑል እግዚአብሔር ካህን እና
“በእግዚአብሔርም ቤት ላይ የሆነ ታላቅ ካህን” ተብሏል (ዕብ. 5፥9-10፤ 1ዐ፥21)። ይህም ከነገደ ሌዊ እንደ ተወለዱት ሳይሆን በማያልፍ ሕይወት ኀይል በመሾሙ
ምክንያት ነው (ዘኊ. 8፥23-26፤ ዕብ. 7፥11-17)።
“አባትና እናት የትውልድም ቍጥር የሉትም፥ ለዘመኑም ጥንት ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም” መባሉ ይበልጥ
የክርስቶስን ማንነት እንዲገልጽ ተደርጎ የመልከ ጼዴቅ ማንነት መጻፉን እንረዳለን። እነዚህ መረጃዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ
እንዲሰፍሩ አለመደረጋቸው፥ የክርስቶስን ዘላለማዊነት ያሳዩ ዘንድ መሆኑ ግልጥ ነው (ሉቃ. 1፥32-33)። የመጨረሻው አረፍተ
ነገርም መልከ ጼዴቅ “በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል” ሲልም መልከ ጼዴቅ ለእግዚአብሔር ልጅ ለኢየሱስ
ክርስቶስ ክህነት ምሳሌ ሆኖ ከመጀመሪያው መታሰቡን ያረጋግጣል። ምስጢራዊነት ያለው ሰው መሆኑንም ያስረዳል።
ሌላው ተመሳስሎ፥ መልከ ጼዴቅ እንጀራና የወይን ጠጅ ይዞ በመውጣት አብርሃምን መቀበሉ ነው። እንጀራና
ወይን ጌታ ኢየሱስ ኀሙስ ማታ ለደቀ መዛሙርቱ እንካችሁ ብሉ፤ እንካችሁ ጠጡ ብሎ የእርሱን መታሰቢያ እንዲያደርጉበት ከሠራው
የቅዱስ ቊርባን ሥርዐት ጋር ሊመሳሰል ይችላል።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መልከ ጼዴቅ የሚናገረው ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ መሆኑን ነው እንጂ ማንነቱን ወይም
ዜግነቱን አይገልጥም። ምክንያቱ ደግሞ የመልከ ጼዴቅ የተሰወረ ማንነት ለኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊና ብልጫ ያለው ክህነት ምሳሌ
እንዲሆን ስለ ታቀደ ነው። በዚህ መልክ እንዲቀመጥ የተደረገውን የመልከ ጼዴቅን ማንነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፥ መልከ
ጼዴቅ ኢትዮጵያዊ ነው ማለት በሰው ወርቅ ለመድመቅ መሞከር ይሆናል።
2ኛ ጥያቄ፥ ከጎይትኦም “መጽሐፍ ቅዱስ አጋንንት ከሰዎች ውስጥ
በኢየሱስ ስም እንደሚወጡ በግልጽ ይናገራል። አንዳንድ አጋንንትን እናስወጣለን የሚሉ ሰዎች ግን በኢየሱስ ስም ብቻ ሳይሆን
በጻድቃንና በሰማዕታት ስም እናስወጣለን ይላሉ። በተጨማሪ አጋንንቱ ካደሩበት ሰው ጋር ትግል መግጠም፥ ሰውዮውን በመቊጠሪያ፥
በጧፍ፥ በመስቀል ወዘተ. መደብደብና የመሳሰሉ ድርጊቶችን ይፈጸማሉ። እነዚህንም ድርጊቶች በሲዲ እያሠራጩ ከክርስትና ትምህርት
ውጪ የሆኑ ልምምዶችን ያስፋፋሉ። እውን እነዚህ ነገሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ናቸውን?
መልስ ከመምህርት ሲያዴ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አጋንንት ከሰዎች
ሲወጡ የምናነበው በሐዲስ ኪዳን ክፍል ውስጥ ነው። አጋንንትን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያወጣ የምናገኘውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን
ነው። እርሱም አጋንንትን በሥልጣን ቃል እንዲወጡ ያዝዝ፥ አጋንንትም ከሰዎች ይወጡ፥ ሰዎቹም ነጻ ይሆኑ ነበር (ማቴ. 4፥24፤
8፥16-17፡28፤ 9፥33፤ 12፥22፤ ማር. 1፥34፡39፤ 5፥2፡8፤ 7፥29-30፤ 16፥9፤ ሉቃ. 4፥35፡41፤
8፥2፡33፤ 9፥42)። አጋንንትን የሚያወጣው በእግዚአብሔር መንፈስ፥ እንዲሁም በእግዚአብሔር ጣት መሆኑን ተናግሯል (ማቴ.
12፥28፤ ሉቃ. 11፥20)።
ጌታ ኢየሱስ በስሙ አጋንንትን ከሰዎች የማውጣትን ሥልጣን በመጀመሪያ ለተከታዮቹ ሐዋርያትና ቀጥሎም
ለኋለኞቹ ሰባው ተከታዮች (አርድእት) ሰጥቷል፤ እነርሱም አጋንንትን በስሙ አውጥተዋል (ማቴ. 10፥8፤ ማር. 3፥15፤
6፥12፤ ማር. 9፥38-40፤ ሉቃ. 9፥1፤ ሐ.ሥ. 16፥18)። ሐዋርያትና ሰባው አጋንንትን እንዲያወጡ የተሰጣቸው ስም
ኢየሱስ ብቻ ነው። “ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው። ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል”
ማለታቸው በወንጌለ ሉቃስ ተመዝግቧል (ሉቃ. 10፥7)።
በእርሱ የሚያምኑትን ከሚከተሏቸው ምልክቶች መካከል አንዱ በስሙ አጋንንትን ማውጣት ነው (ማር.
16፥17)። በትክክል የኢየሱስ ተከታዮች ያልሆኑ አንዳንዶች አጋንንትን በኢየሱስ ስም ማውጣታቸውና ለማውጣት ሙከራ ማድረጋቸው
ተጽፏል (ማቴ. 7፥22፤ ሐ.ሥ. 19፥13)። በተለይ “አጋንንትንም እያወጡ ይዞሩ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶች፥ ጳውሎስ
በሚሰብከው በኢየሱስ እናምላችኋለን እያሉ ክፉዎች መናፍስት ባሉባቸው ላይ የጌታን የኢየሱስን ስም ይጠሩባቸው ዘንድ ሞከሩ።
የካህናትም አለቃ ለሆነ አስቄዋ ለሚሉት ለአንድ አይሁዳዊ ይህን ያደረጉ ሰባት ልጆች ነበሩት። ክፉው መንፈስ ግን መልሶ፦
ኢየሱስንስ ዐውቀዋለሁ ጳውሎስንም ዐውቀዋለሁ፤ እናንተሳ እነማን ናችሁ? አላቸው። ክፉው መንፈስም ያለበት ሰው ዘለለባቸው፤
ቈስለውም ከዚያ ቤት ዕራቊታቸውን እስኪሸሹ ድረስ በረታባቸው፤ አሸነፋቸውም። ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት ሁሉ በአይሁድና በግሪክ
ሰዎች ዘንድ የታወቀ ሆነ፥ በሁላቸውም ላይ ፍርሀት ወደቀባቸው፥ የጌታም የኢየሱስ ስም ተከበረ፤ አምነውም ከነበሩት እጅግ ሰዎች
ያደረጉትን እየተናዘዙና እየተናገሩ ይመጡ ነበር። ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት፤
ዋጋውም ቢታሰብ ዐምሳ ሺህ ብር ሆኖ ተገኘ። እንዲህም የጌታ ቃል በኀይል ያድግና ያሸንፍ ነበር” (ሐ.ሥ. 19፥13-20)።
ይህ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የተመዘገበው ታሪክ ወደ ጎይትኦም የጥያቄ መልስ ያንደረድረናል። ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ በሥልጣኑ፥ እርሱ ሥልጣን የሰጣቸው ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው ደግሞ በኢየሱስ ስም አጋንንትን ሲያወጡና ሰዎችን ነጻ
ሲያደርጉ፥ ጌታ በሥጋ ከመገለጡ በፊትና በሥጋ ተገልጦ በተመላለሰበት ወቅትም ከአይሁድ አንዳንዶቹ አጋንንትን እያወጡ ይዞሩ
ነበር። አጋንንትን ያወጡ የነበረው ግን በኢየሱስ ስም አልነበረም። በኢየሱስ ስም ካልሆነ ታዲያ በማን ስም ነበር አጋንንትን
ያወጡ የነበረው? ቢባል በአስማት ነው። ይኸውም ሊታወቅ ሐዋርያት ሲያደርጉ አይተው በኢየሱስ ስም ክፉዎች መናፍስትን ለማውጣት
ሞከሩ። ክፉው መንፈስ ግን “ኢየሱስንስ ዐውቀዋለሁ ጳውሎስንም ዐውቀዋለሁ፤ እናንተሳ እነማን ናችሁ?” በማለት አባረራቸው፤
አሸነፋቸውም። ይህን ተከትሎ በሕዝቡ ላይ ፍርሀት ሲወድቅ፥ የጌታ የኢየሱስ ስም ተከበረ። ብዙዎችም ወደ መዳን ሲደርሱ፥
“ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት፤ ዋጋውም ቢታሰብ አምሳ ሺህ ብር ሆኖ ተገኘ።” እነዚህ
አስማተኞች አጋንንትን በኢየሱስ ስም ለማውጣት ከሞከሩትና ካልተሳካላቸው ወገን እንደ ነበሩ ምንም ጥርጥር የለውም። ለዚያ ነው
እስከዚያ ሰዓት ድረስ ይዘዋቸው የነበሩት የአስማት መጻሕፍት በሐሰት እንጂ በእውነት አጋንንትን ማስወጣት እንደማይችሉ
የተረዱትና በሰው ሁሉ ፊት ያቃጠሏቸው። ዛሬም በኢየሱስ ስም ሳይሆን በሌሎች ስሞችና በልዩ ልዩ ዘዴዎች አጋንንትን እናወጣለን
የሚሉ ምድባቸው ከእነዚህ ወገን ነው።
ጠያቂአችን እንዳሉት፥ እነዚህ ወገኖች አጋንንትን ለማውጣት የኢየሱስን ስም ብቻ ሳይሆን የሌሎች ፍጡራንን
አስማት ይጠራሉ። አጋንንትም እየጮሁ “ወጣን” ሲሉ ይታያል። ይህ ከአይሁድ አንዳንዶች አጋንንትን እያወጡ ይዞሩ ነበር ካለው
ጋር ሊገናዘብ የሚችል ነው። የአጋንንቱ መውጣት ሰዎች ወደ ክርስቶስ እንዳይመጡ ለማዘናጋት ካልሆነ በቀር እውነተኛ አይደለም።
ዛሬ በዚህ መንገድ ከአጋንንት እስራት ነጻ ወጡ የተባሉቱ ብዙ ጊዜ ጌታን ሲከተሉት አይታይም። እንዲያውም
እርሱንና የእርሱን ወገኖች፥ የመንግሥቱንም ሥራ ሁሉ የሚቃወሙ ናቸው። ጌታ ከአጋንንት ነጻ ያወጣው ሰው ግን ጌታን ይወዳል፤
እርሱንም ለመከተልም አያንገራግርም፤ ለወንጌልና ለመንግሥቱ ሥራ መስፋት ደጋፊ እንጂ ተቃዋሚ አይሆንም (ማር. 5፥18)።
ስለዚህ ሁሉም በፍሬው ይታወቃል።
ሌላው ጠያቂአችን ያነሡት ነጥብ፥ አጋንንትን ከሰዎች ውስጥ በኢየሱስ ስም ብቻ ከማስወጣት ይልቅ አጋንንቱ
ካደሩበት ሰው ጋር ትግል መግጠም፥ በመቊጠሪያ፥ በጧፍ፥ በመስቀል መደብደብና የመሳሰሉ ድርጊቶችን መፈጸም አጋንንትን የማስወጫ
መንገዶች ተደርገው እየተወሰዱ ነው። ነገር ግን ስሕተት ነው። አጋንንት የሚወጡት ከኢየሱስ ስም ኀያልነት እንጂ እኛ ሰዎች
ከምንጠቀመው ኀይልና ልዩ ልዩ ዘዴ የተነሣ አይደለም። ስለዚህ አጋንንትን ለማስወጣት የኢየሱስን ስም በእምነት መጥራት ብቻ በቂ
ነው። ርኩሳን መናፍስትም በእውነት ከሰው የሚወጡት በዚህ ኀያል ስም ሲታዘዙ ብቻ ነው። ሐዋርያትም ሆኑ ሰባው አርድእት
አጋንንትን እንዲያወጡ የታዘዙትና ያስወጡት በኢየሱስ ስም ብቻ ነው እንጂ ሌላ ስም አልጠሩም፤ ሌላ ዘዴም አልተጠቀሙም። ደግሞስ
የተዘረዘሩትንና ሌሎችን የኀይል ርምጃዎች መውሰድ ሥጋና ደም የሆነውንና ርኩሳን መናፍስት ያደሩበትን ሰው አካል ከመጐዳትና
ሲከፋም ለሞት ከመዳረግ ውጪ መንፈስ በሆነው ጠላት ላይ እንዴት ማሳረፍ ይቻላል?
ጌታችን
አስቀድሞ እንደ ተናገረው ኀይለኛውን ሳያስሩ የኀይለኛውን ቤት መበዝበዝ አይቻልም (ማቴ. 12፥29)። ኀይለኛው ሊታሰርና
በቊጥጥሩ ሥር ያዋላቸው ሰዎች ነጻ ሊወጡ የሚችሉት ደግሞ በኢየሱስ ስም ብቻ ነው፤ ስለዚህ ሌላ ምንም ዐይነት ሰዋዊ ዘዴ ወይም
ስልት መጠቀም ሳያስፈልግ፥ ኢየሱስ የሚለውን ነጻ አውጪና ፈዋሽ ስም በእምነት መጥራት ከአጋንንት እስራት ነጻ ያወጣል።
Yes JESUS's name is unique ,as the bible tells us in Phill 2:9-11"therefor God exalted him to the highest place and gave him the name that is above all names,that at the name of JESUS every knee should bow , in heaven and on earth and under the earth,end every tongue shall confess that JESUS CHRIST is lord ,to the glory of GOD the Father" so no name need to be added.GOD bless you all.
ReplyDelete