Thursday, January 10, 2013

መጽሐፍ ቅዱስ


ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጠቅላላ ዕውቀት
(በጮራ ቊጥር 4 ላይ የቀረበ) 
ከሁሉን መርምር

በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝ በብሉይ ኪዳን መጨረሻ ከገጽ 721-1037 በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች የማይገኙ መጻሕፍት በመጨመራቸው ተጨንቀውና ግራ ተጋብተው ያውቃሉን? “ተጨማሪ (ዲዮትሮካኖኒካል) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት” በሚል የክፍል መጠሪያ የተጨመሩት መጻሕፍት 18 ናቸው፡፡ በውሳኔ የተጨመሩት መጻሕፍት የሚገኙበት ጥራዝ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ እንደ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ሲቈጠር፥ እነርሱ የሌሉበት ጥራዝ ግን “ጐደሎ መጽሐፍ ቅዱስ” ተብሎ ሲጠራ ተሰምቷል፡፡

መጠሪያቸው እንደሚያስረዳው እነዚህ ተጨማሪ መጻሕፍት ቀደም ሲል ከቅዱሳት መጻሕፍት ቊጥር ውጪ እንዲሆኑና በአዋልድነት እንዲጠሩ ያደረጓቸው አያሌ ታዋቂ ምክንያቶች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቶቹ ከአዋልድ መጻሕፍቱ ጋር ታትመው ቢሆኑ ኑሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ባላደናገሩ ነበር፡፡


የብሉይ ኪዳን መምህራን ስለ እያንዳንዱ ዲዮትሮካኖኒካል መጽሐፍ በማስረጃ የተደገፈ ማብራሪያ ይሰጡናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይስማሙባቸውን ነጥቦች በመጠቈም ማቅረባችንን እንቀጥላለን፡፡

መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል
ም. 1፥1 “አገራችን ኢየሩሳሌም በጠፋች በሠላሳ ዘመን ዕዝራ እባል የነበርኩ እኔ ሱቱኤል በባቢሎን ነበርኩ” ይላል፡፡ ሆኖም መጽሐፉ ኢየሩሳሌም በጠፋች በ30ኛ ዓመት የተጻፈ ሆኖ እንዳይታመን የሚያደርጉ አያሌ ጒዳዮች በመጽሐፉ ውስጥ አሉ፡፡ እነርሱንም በየምዕራፉ እናቀርባቸዋለን፡፡

ም. 3፥25 “ከሀገሮች ሁሉ አንድ የእስራኤልን ሀገር መረጥህ፤ በሀገሩ ሁሉ ከታነጹ ምኲራባት አንድ ቤተ መቅደስን መረጥህ” ይላል፡፡

በኢየሩሳሌም አንድ ቤተ መቅደስ እንዲኖር አስቀድሞ በእግዚአብሔር መመረጡ፥ መታዘዙ በዚህም መሠረት መታነጹ በእግዚአብሔር ቃል ተገልጿል (ዘዳ. 7፥14፡22-25፤ 16፥1-17፤ መዝ. 131/132፥13-14፤ 2ዜና. 3፥1፤ 6፥1-11)፡፡ ሆኖም ከቤተ መቅደስ መታነጽ በፊት ምኲራባት መታነጻቸውና ለምርጫ መቅረባቸው በእግዚአብሔር ቃል የተደገፈ ትረካ አይደለም፡፡ ቤተ መቅደስ ከተደመሰሰና ሕዝቡ በምርኮ ከተበታተኑ በኋላ ስለ ሃይማኖታቸውና ባህላቸው ሊወያዩባቸው የምኲራብ ማቋቋምን ሥርዐት እንደ ተለማመዱ ከታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡

የመጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል ደራሲ በ30ኛው የምርኮ ዓመት ሳይሆን ቤተ መቅደስ እንደ ገና ታንጾ ከምኲራባት ጋር አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ የጻፈው ቢሆን ነው እንዲህ ለማለት የበቃው ከሚሰኝባቸው ነጥቦች አንዱ ይህ ነው፡፡
ም. 4፥5፡6 “የሚመጣው ዓለም የመንግሥተ ሰማይ ምስጢር ሳይታወቅ፥ ሃይማኖትን የሚያጸኗት ሰዎች በልበ ሥላሴ ሳይቈጠሩ የዚያን ጊዜ ፍጡር ያይደለሁ እኔ ይህን ዓለም እጐበኝ ዘንድ ዐስቤአለሁና ... አለኝ” ይላል፡፡ ሥላሴ አማኞችን ያላወቁበት ጊዜ እንደ ነበረ ዕውቀታቸው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንደ መጣ አስመስሎ ሊነግረን ይሞክራል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ይህን አባባል አይደግፍም (ሮሜ 8፥29-30፤ ኤፌ 1፥4፤ 1ጴጥ. 1፥20-21)፡፡

እግዚአብሔር መጀመሪያና መጨረሻ፥ አልፋና ኦሜጋ ነው ሲባል መጨረሻና ኦሜጋነቱ፥ አልፋና መጀመሪያ ከሆነበት ጊዜ በኋላ የመጣለት ሳይሆን፥ አልፋና ኦሜጋነቱ ምን ጊዜም በባሕርዩ የነበረ፥ ያለና የሚኖር፥ የህላዌውና የዕውቀቱ ፍጹምነትና ሙሉነት ነው (ኢሳ. 44፥6፤ 48፥12፤ ዘፀ. 3፥14፤ መዝ. 138/139፥16)፡፡

ም. 6፥9-32 ጻድቃንም ሆኑ ኃጥአን ሲሞቱ ነፍሶቻቸው ወደ ሲዖል ወይም ወደ ገነት ወዲያው እንደማይወሰዱ፥ ነገር ግን በሥጋ ሕይወት በነበሩበት ጊዜ ስለ ሠሩት መልካም ሥራ እየተወደሱ ወይም ስለ ክፉ ሥራቸው እየተወቀሡ የሚያሳልፏቸው “ነጻ” ሰባት ቀናት እንዳሉ ይናገራል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ግን የማይቀበለው አባባል ነው፡፡ ገነትና ሲኦል እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ነፍሳት የሚቈዩባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ ስለ ሆነም
1) “ዛሬ ከኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ሉቃ. 23፥43
2) “ድኻውም ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም ዕቅፍ ወሰዱት፤ ባለጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ፤ በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ፡፡” (ሉቃ. 16፥23) ሲል ያስተምረናል፡፡

መጽሐፈ ጦቢት
ትውልዱ ከነገደ ንፍታሌም የሆነው የጦቢት ልጅ ጦቢያ በፋርስ ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን መማረኩን የመጽሐፉ ርእስ ይናገራል፡፡ ስልምናሶር የአሦር ንጉሥ እንጂ የፋርስ ንጉሥ አልነበረም፤ ግዛቱን በማስፋት የአሦርን ወሰንተኛ አገሮች ፋርስንም ጨምሮ ማስገበሩን ለመግለጽ ይሆናል፡፡

ም. 1፥1 “ወደ ነነዌና ወደ ፋርስ አገር ከኔ ጋር ለመጡ ለወገኖቼ ብዙ ምጽዋት መጸወትኩ” ይላል፡፡
አሦር ንጉሥ ስልምናሶር ምርኮኞቹን እስራኤላውያን በሚገዛቸው አገሮች ሁሉ ደልድሎአቸው ይሆናል፡፡

ማስገንዘቢያ፤ እንግሊዝኛው ስልምናሶርን ንጉሠ አሦር ሲለው ጦቢት በምርኮኛነት የሄደበትንም አገር በአሦር የምትገኝ ነነዌ መሆኗን ይናገራል፡፡

ም. 1፥2 “ሕፃን ሆኜ … አባቴና የንፍታሌም ወገኖች ሁሉ … በኢየሩሳሌም ከተሠራው ሕግ ወጥተው ካዱ” ይላል፡፡
ነገደ ንፍታሌም ከሌሎቹ 9 የእስራኤል ነገዶች ጋር በማበር ከዳዊት ቤት ተገንጥለውና አምልኮተ እግዚአብሔርን ትተው ሌላ መንግሥትንና ልዩ (ባዕድ) አምልኮትን ሲያቋቁሙ፥ ሕፃን እንደ ነበረ ጦቢት ይገልጻል፡፡ በዐማርኛው ትርጒም ግን በቊጥር 1 የተገለጸውን ሐሳብ በዚህ በቊጥር 2 በመድገም “ሕፃን ሆኜ እመጸውት ነበር” የሚል የሌለ ንባብ ታክሎበታል፡፡

ለማስረጃ
ሀ) ግእዙ “ወእንዘ ሀሎኩ ውስተ ኢየሩሳሌም ብሔርየ እንዘ ንኡስ አነ ኲሉ ሕዝበ ንፍታሌም አበውየ ክሕዱ እምነ ቤተ ኢየሩሳሌም” ሲል፤

ለ) እንግሊዝኛውም “In my young days when I was still at home in the land of Israel the whole tribe of Naphtali my ancesters broke away” ይላልና፡፡

ይህ ማለት ጦቢት ሕፃን የነበረበትን ጊዜ በዚህ ስፍራ ለመግለጽ የፈለገው በዚያ ጊዜ ዐሥሩ ነገደ እስራኤል ተለይተው የራሳቸውን መንግሥት ማቋቋማቸውን ለማስገንዘብ እንጂ፥ ይመጸውት እንደ ነበር ለማስረዳት አልነበረም፡፡ ይህንማ በቊጥር 1 ገልጾታል፡፡

እንዲህ ከሆነ ማለት ዐሥሩ ነገደ እስራኤል የራሳቸውን መንግሥት በለዩበት ጊዜ ጦቢት ሕፃን የነበረ ከሆነ፥ የሰሎሞን አገዛዝ ዘመን ከማክተሙ (930 ከክርስቶስ ልደት በፊት) አስቀድሞ ተወልዶ ነበር፡፡ የእስራኤል መንግሥት ከ241 እስከ 261 ዓመት ያህል ከቈየ በኋላ በአሦር መንግሥት ሲፈርስ ጦቢት ከተማረከው ሕዝብ ጋር ወደ ነነዌ ተወሰደ፡፡ ከዚያም አስራዶን እስከ ነገሠበት (680 ከክ.ል.በ.)  ጦቢት በነነዌ ነበር (ቊ. 48)፡፡

ለምን ያህል ጊዜ እንደ ኖረ ባይታወቅም፥ ከዚያ በኋላ ለብዙ ጊዜ በነነዌ እንደ ኖረ መጽሐፉ ይገልጻል፡፡ ከም. 2 እስከ ም. 14፥11 ያለው ረጅም ታሪክ ያለው ሥራ የተሠራው አስራዶን ከነገሠ በኋላ መሆኑን መጽሐፉ ያስነብበናልና፡፡ ታዲያ በዚህ ስሌት የጦቢት ዕድሜ ወደ 270 ዓመት ይጠጋል፡፡ ከሆነ በዘመኑ ትውልድ የዕድሜ ርዝማኔ ግምት 4 ትውልድን ወይም የ22 ነገሥታት የግዛት ዘመንን አሳልፎአል ማለት ነው፡፡

ም. 1፥15 “ስልምናስር በሞተ ጊዜ ሥራው ክፉ የሆነ ሰናክሬም በሱ ፋንታ ነገሠ” ይላል፡፡
ከስልምናሶር ቀጥሎ በአሦር የነገሠው ሳርጐን ነበር፡፡ ከዚያም ቀጥሎ ሰናክሬም ነገሠ፡፡ የመጽሐፈ ጦቢት ደራሲ ሳርጐንን ለምን ዘለለው? የሚለው ጥያቄ አልተመለሰም፡፡

ም. 5፥12-14 ጦቢት ልጁን ጦቢያን ወደ ሜዶን ሊልከው ወሰነና ዐብሮት የሚሄድ ተቀጣሪ እንዲፈልግ አዘዘው፡፡ ልጁ ጦቢያም አብሮት የሚሄድ ሰው በመለፈግ ላይ እያለ ሩፋኤል የተባለው መልአክ በሰው አምሳል አገኘውና ተነጋግረው ተስማሙ፤ ወደ አባቱ ወደ ጦቢት አመጣው፡፡ ጦቢት ስሙንና ነገዱን እንዲነግረው መልአኩን በጠየቀው ጊዜ የታላቅ ወንድምህ የአናንያ ልጅ አዛርያ ነኝ በማለት ዋሽቶ መለሰለት፡፡

መዋሸት ለቅዱሳን መላእክት ይፈቀዳልን? እስከምናወቀው ድረስ ያልሆነውን “ነኝ” ማለት መዋሸት ነው፤ ይህም የውሸት አባት የሰይጣን መታወቂያ ነው (ዮሐ. 8፥44-45)፡፡ አዎን ከሆነ “አዎን” በሉ፤ አይደለም ከሆነም “አይደለም” በሉ፤ ከዚህ ያለፈ ከክፉው ነውና (ማቴ. 5፥37፤ ዘፀ. 23)፡፡

ም. 14፥15 ጦቢት በቅድሚያ በነገረው መሠረት ጦቢያ የነነዌን ጥፋት ሰማ፤ ስልምናሶርና ናቡከደነፆርም የነነዌን ጥፋት ሰምተው ደስ አላቸው ይላል፡፡

ስልምናሶርንና ናቡከደነፆርን ምን አገናኛቸው? ስልምናሶር (726-722 ከክ.ል.በ.) በነነዌ የነገሠ የአሦር ንጉሥ ሲሆን፥ ናቡከደነፆር ግን (605-562 ከክ.ል.በ.) የባቢሎን ንጉሥ ነበር፡፡

ነነዌ የጠፋችው በናቡከደነፆር አባት በናቡፓላዘር የግዛት ዘመን ነበር፡፡ ስልምናሶርንና ናቡከደነፆርን ዘመን ቢያገናኛቸው ኖሮ ቢሆን እንኳ የነነዌ ጥፋት ለናቡከደነፆር ብቻ ደስታ፥ ለስልምናሶር ግን ልብን የሚሰባብር ሐዘን በሆነ ነበር፡፡

No comments:

Post a Comment