Monday, January 21, 2013

ጋብቻ

የአብርሃምና የሣራ ጋብቻ
“የምድር ነገዶች ሁሉ በአንተ ይባረካሉ፡፡”
ዘፍ. 12፥3

እግዚአብሔር የደኅንነትን ዕቅድ ሲያዘጋጅ አንድ ቤተ ሰብ መረጠ። አብርሃምን ከዑር እንዲወጣ ሲጠራው እግዚአብሔር “የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” ብሎ ተስፋ ሰጠው፡፡ እንግዲህ ቤተ ሰብ በእግዚአብሔር ሐሳብ ከፍ ያለ ዋጋ እንዳለው በዚህ እናያለን፡፡

የእግዚአብሔር ባሕርይ፥ የሰውም ሁኔታና የእምነት እውነታዎች ስላልተለወጡ፥ እኛም ምንም እንኳ በሌላው ዘመንና በተለየ ባህል ብንኖር ከአብርሃም ቤተ ሰብ የሚጠቅመንን ትምህርት ልንማር እንችላለን፡፡


የተባረከ ጋብቻ የቅንጅትን ሕይወት መኖር ይጠይቃል
ከሁሉ አስቀድሞ አብራምና ሚስቱ ሦራ (መጀመሪያ እንደ ተጠሩበት) ለእምነት ጒዞ በአንድነት ተነሡ፡፡ “ታራም ልጁን አብራምንና የልጁንም የአብራምን ሚስት ምራቱን ሦራን ወሰደ፤ ከእርሱም ጋር ወደ ከነዓን ምድር ይሄዱ ዘንድ ከከለዳውያን ዑር ወጡ” (ዘፍ. 11፥31)፡፡

በአሞጽ 3፥3 “ሁለት ሰዎች ሳይስማሙ ዐብረው መጓዝ ይችላሉን? ባልና ሚስት በእምነት መንገድ ጐን ለጐን እንዲሄዱ አስፈላጊ መሆኑን ከአባታችን ከአብራምና ከእናታችን ከሦራ ምሳሌ እንማራለን፡፡

“አሁን ግን የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ፡፡” የአብራምና የሦራ የመጨረሻ መድረሻ ሰማያዊ አገር መሆኑ በዕብራውያን 11፥16 ተጽፏል፡፡ እንግዶችና መጻተኞች ሆነው በምድር ላይ ሳሉም እንኳ እግዚአብሔር በምድራዊ ሕይወታቸው ይፈጽምላቸው የነበረውን የተስፋ ቃል ሁሉ በቅንጅት ሕይወታቸው ዐብረው ይካፈሉ ነበር፡፡ ይኸውም ለምሳሌ ወደ ተስፋው አገር ወደ ከነዓን ዐብረው ደረሱ፡፡ እዚያም ብዙ ዓመት ከቈዩ በኋላ የተስፋው ልጅ ይስሐቅ ተወለደላቸው፡፡ እንደዚሁም የክርስቲያን ባልና ሚስት ዐላማ ወደ ሰማያዊ አገር መድረስ ሲሆን፣ በዚህ ምድር እንደ መጻተኞች ሆነው በአንድነት ሲጓዙ በእግዚአብሔር የተዘጋጀላቸውን መልካም ዕቅድ እንዲካፈሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን በዚህ እናስተውላለን፡፡

የተባረከ ጋብቻ የግል ግንኙነትን ከእግዚአብሔር ጋር መመሥረትን ይጠይቃል
አብራምና ሦራ በእምነት ቅንጅት ሲሄዱ፥ ሁለቱም  በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ውስጥ ስለ ነበሩ፥ ከእግዚአብሔር ጋር የግል ግንኙነት ነበራቸው፡፡ ይህም በመሆኑ እግዚአብሔር የአብራምን ስም ሲለውጥ የሦራንም ስም ደግሞ ለወጠ፡፡ ከአብራም (“ታላቅ አባት”) ወደ አብርሃም (“የብዙዎች አባት”) ሲለወጥ፥ ከሦራ (“ልዕልቴ”) ወደ ሣራ (“ልዕልት”) ተለወጠ፡፡ የሁለቱም ስም መለወጥ በእግዚአብሔር ታላቅ ዕቅድ ውስጥ እንደ ተያዙ ያሳስባል፡፡

እንደዚሁም የይስሐቅ መፀነስ ጊዜ መድረሱን እግዚአብሔር ለአብርሃም ከነገረው በኋላ በሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ አብርሃም ድንኳን መጣ፡፡ በምን ምክንያት መጣ? ሣራ ራሷ ከእግዚአብሔር ይህን አስደሳች ዜና ሰምታ እንድታምንበት ነው፡፡ በርግጥ ይህ ታላቅ የእምነት ሥራ እንዲፈጸም የሁለቱም እምነት አስፈላጊ ነበረ፡፡ ስለዚህ በመጨረሻ በዐዲስ ኪዳን ስለ ተስፋው ልጅ መወለድ ሲጻፍ በእምነት የሚለው ስለ አብርሃም ብቻ ሳይሆን፣ “ሣራ ራስዋ ደግሞ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኀይልን በእምነት አገኘች” ተብሎ ተጽፎአል (ዕብ. 11፥11)፡፡

ማናቸውም ጋብቻ ለእግዚአብሔር ክብር ቢሆንም እያንዳንዱ ቅንጅት ልዩ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳለበት ባልና ሚስቱ ማስተዋል አለባቸው፡፡ የእግዚአብሔርን ጥሪ ባልየው ብቻ ሳይሆን ሚስቲቱም ጭምር ከእግዚአብሔር ብትሰማ በይበልጥ በእምነት ዐብረው መራመድ ይችላሉ፡፡ ጋብቻቸውም የተባረከና ለብዙ ሌሎች ሰዎች በረከት ይሆናል፡፡

የተባረከ ጋብቻ ያለፈውን የኑሮ ሁኔታ መተው ይጠይቃል
አብርሃምና ሣራ የሚኖሩበትን ሀገር ዘመዶቻቸውንና የወላጆቻቸውን ሀብት በመተው ጌታ ወደሚያሳያቸው አገር እንዲሄዱ ተነግሯቸው ነበር፡፡ ይህ ጒዞ እጅግ ከሚቀራረብ ቤተ ሰባዊ ትስስር ተላቅቆ መሄድን የሚጠይቅ በመሆኑ ቀላል ጒዞ አልነበረም፡፡

ይሁን እንጂ አብርሃምና ሣራ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ሲነሡ፣ ከቤተ ሰቦቻቸው ውስጥ የአብርሃምን አባት ታራንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን አስከትለው ወጡ፡፡ የአብርሃም አባት ታራ ዐሥራ ዐምስት ዓመት በኖሩበት በካራን ውስጥ ሞተ፡፡ አብርሃምና ሣራ ጒዞአቸውን በቀጠሉ ጊዜ ሎጥ ከእነርሱ ጋር ነበር፡፡ ሎጥ ከአብርሃምና ከሣራ እንዲለይ ያደረጉት ሁኔታዎች እስከ ተፈጠሩ ድረስ ከእነርሱ ጋር በጒዞ ላይ ቈየ፡፡ በኋላ ግን የሁለቱ ሰዎች ማለትም የአብርሃምና የሎጥ የከብትና የበግ መንጋ በእረኞቻቸው መካከል ጠብ እስኪፈጠርና በመጨረሻም በአንድነት ለመኖር እስከማይችሉበት ደረጃ እየጨመረ ሄደ፡፡ በርግጥ አብርሃምና ሣራ ጌታ ለእነርሱ ሕይወት ያቀደውን ዕቀድ ለመከተል ነጻነት የነበራቸው በመጀመሪያ ከታራ፥ ቀጥሎ ከሎጥ ጋር የመጨረሻ መለያየት ከተፈጠረ በኋላ ነበር፡፡ ይህ ታሪክ በዘፍጥረት ም. 12 እና 13 ላይ ይገኛል፡፡ በዘፍጥረት 2፥24 ላይ “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡”

መጽሐፍ ቅዱስ የሚያዝዘው የጋብቻ ዐይነት የነበረንን ነገር “መተው” ይታይበታል፡፡ ይኸውም እውነተኛ መሥዋዕት መክፈል ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ወደ ጋብቻ ሕይወት ሲገባ በሕይወት ውስጥ የሚያውቀውን የደኅንነት እንክብካቤ ያደረጉለትንና ከእርሱ ጋር እጅግ በጣም የተቀራረበ ግንኙነት የነበራቸውን አባቱንና እናቱን መተው ግድ ነው፡፡ ራሱን ሙሉ በሙሉ ለማስረከብ ከሚፈልጋት ሴት ጋር በእምነት ጒዞ ዐዲስ ቤት ለመሥራት መውጣት ይኖርበታል፡፡ ስለ ሆነም ተጋቢዎች ለጋብቻቸው ጌታ ያቀደላቸውን የተለየ ዐላማ ከግብ ለማድረስ የሚችሉት በአብርሃምና በሣራ የጋብቻ መንገድ በመጓዝ ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ሴቲቱም በበኩሏ አባትና እናቷን በመተው ከባሏ ጋር በእምነት ፈጥና መጣመር እንድትችል ተመሳሳይ የእምነት መሥዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት ይኖርባታል፡፡

የተባረከ ጋብቻ የሥርዐትን ቅደም ተከተል ማክበር ይጠይቃል
አብርሃምና ሣራ ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸው ግንኙነት ማደጉን ብቻ ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አንድ ለአንድ እንዴት መኖር እንደሚገባቸው የበለጠ እያወቁ መሄዳቸውንም ጭምር በጋብቻ ሕይወታቸው ከታየው ልምድ እንረዳለን፡፡ ለአብርሃምና ለሣራ እግዚአብሔር በነበረው ዕቅድ በእያንዳንዷ ርምጃ እግዚአብሔር በመጀመሪያ የሚናገረው አብርሃምን ነበር፡፡ ምክንያቱም ከመጀመሪያ ጊዜ ጀምሮ በቤተ ሰብ ውስጥ የመሪነቱን ሥልጣንና ኀላፊነቱን ለወንድ ሰጥቶ ስለ ነበረ ነው፡፡ ይኸውም ምንም እንኳ ሣራ ከአብርሃም ጋር የማትስማማበት ሁኔታ ቢያጋጥማትም ውሳኔውን ለመከተል መታዘዝና የፈቃደኝነት መንፈስ ማሳየት እንዳለባት የሚያመለክት ነው፡፡ ሣራ እግዚአብሔርን ስትታዘዝና ሁሉን ነገር በእምነት በእርሱ ላይ እየጣለች ስትሄድ ራሷን በይበልጥ በታማኝነት ለእግዚአብሔር ማቅረብ ያለባት መሆኗን በሚገባ ተገነዘበች፡፡

አብርሃም የተስፋውን ሀገር ከነዓንን ትቶ ምግብ ለማግኘት ወደ ግብጽ ለመሄድ የወሰነበት ጊዜ ነበር፡፡ በተለየ ሁኔታ ወደ ደቡብ ማለትም ወደ ጌራራ ንጉሥ ወደ አቤሜሌክ በሄደም ወቅት እንደ ገና ይህ ተመሳሳይ ሁኔታ ተከሥቷል፡፡ እነዚህ አጋጣሚዎች በዘፍጥረት ምዕራፍ 13 እና 20 ላይ ተጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ጊዜ አብርሃም ለሕይወቱ ስለ ሠጋ ሣራን እኅቴ ናት ሲል ቈየ፡፡ ከዚህ የተነሣም ሣራ ከፍተኛ አደጋ ላይ ወደቀች፡፡ ሣራ ይህ ችግር ቢያጋጥማትም በባሏ በአብርሃም ላይ አላመፀችም፡፡ በእያንዳንዱ የሕይወት ጒዞ ወቅት እግዚአብሔር ከእርሷ ጋር ይራመድ ስለ ነበረ ሊደርስባት ከሚችል አደጋ አድኗታል፡፡ ሣራ አብርሃም በዋሸው ግማሽ ውሸት መስማማት አልነበረባትም የሚል ስሜት ሊኖረን ይችላል፡፡ ዐዲስ  ኪዳን በዚህ ጒዳይ ላይ የሚሰጠው ሐሳብ የለም፤ ነገር ግን ሣራ ለአብርሃም ባሳየችው ሥርዐታዊ ዝንባሌና በፈቃደኛነት ስሜቷ ላይ የሚሰጠው አስተያየት አለ፡፡ ይኸውም ክርስቲያን ሚስቶች ሁሉ እርሷን በምሳሌነት በመውሰድ አርኣያነቷን መከተል እንዳለባቸው ነው፡፡ “ነገር ግን በእግዚብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ” (1ጴጥ. 3፥4)፡፡ ሣራ በእግዚአብሔር ፊት የነበራት ውስጣዊ ቊንጅና የተፈጥሮ ውበቷን በለጠው፡፡

በአብርሃምና በሣራ መካከል የነበሩ ሁኔታዎች እየተዛቡ መሄድ ሲጀምሩ በመጽሐፍ ቅዱስ በተለይም በዘፍጥረት ምዕራፍ 16 ላይ አንድ የተመዘገበ ጒዳይ አለ፡፡ ዓመታት በዓመታት እየተተኩ ዐለፉ፤ ለአብርሃምና ለሣራ ተስፋ የተገባላቸው ልጅ ግን ገና አልተወለደም፡፡ ስለዚህ ሣራ በነገሮች ሁሉ ራሷ ወሳኝ የምትሆንበት ወቅት እንደ ደረሰ ተሰማት፡፡ ወዲያውም በአካባቢያቸው ይኖሩ የነበሩ የአሕዛብን ሥርዐት መከተል እንደሚገባውና ከባሪያዋ ከአጋር ልጅ መውለድ እንዳለበት ለአብርሃም ነገረችው፡፡ ይህን በመፈጸም ባደረባት ጥርጥር የተነሣ ከነበራት የኀላፊነት ክልል ወጥታ የቤተ ሰቡ መሪ ለመሆን ሞከረች፡፡ በዚህ አሳዛኝ አጋጣሚ ምክንያት አብርሃምም ከነበረው ቤተ ሰባዊ ኀላፊነት በመውጣት የሣራን ሐሳብ ተቀበለ፡፡ የዚህ ስሕተት አሳዛኝ ውጤቶች ዛሬም ቢሆን ከእኛ ጋር አሉ፡፡ ምክንያቱም የእስራኤል ሕዝብ ከአብርሃም ጋር ያለውን የዘር ግንኙነት በይስሐቅ፥ አረቦች ደግሞ ከአጋር በተወለደ በእስማኤል በኩል እንደ ሆነ ስለሚያምኑ ነው፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ በጋብቻ ሕይወት ውስጥ የማዘዝንና የመታዘዝን ዐበይት መርሖች ኤፌሶን 5፥21-23 ላይ ጠቅሷቸዋል፡፡ “ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ፥ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ፥ ባል የሚስት ራስ ነውና ዳሩ ግን ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ፡፡ ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ወደዱ” (ቊጥር 22-25)፡፡

ባሎች ቤተ ሰባቸውን እንዴት መምራት እንደሚችሉ መማርና በክርስቶስ ፍቅርም መሞላት አላበቸው፡፡ ሚስቶችም ደግሞ መታዘዝን ማወቅና የክርስቶስን ትሕትና መላበስ ይኖርባቸዋል፡፡ ባል ወይም ሚስት በቤተ ሰብ ውስጥ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን የኀላፊነት ድርሻ በትክክል ለመወጣት ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ በእነርሱና በሌሎች ሰዎች የጋብቻ ሕይወት ውስጥ በረከትን ማስገኘት ለሚችለው ለታላቁ የእግዚአብሔር ዐላማ መኖርና መሥራት እንዳለባቸው ከዚህ በላይ የተመለከትነው የአብርሃምና የሣራ ጋብቻ ሁኔታ በሚገባ ያስረዳናል፡፡

መደምደሚያ
ነቢዩ ኢሳይያስ “ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሣራ ተመልከቱ፤ አንድ ብቻውን በሆነ ጊዜ ጠራሁት፤ ባረክሁትም፤ አበዛሁትም” (ኢሳ. 51፥2) በማለት እግዚአብሔር የባረከውንና የሠራበትን የአብርሃምንና የሣራን የጋብቻ ሕይወት በሚገባ እንድናየው ያነቃቃናል፡፡ አብርሃም ከእግዚአብሔር በረከትን እንዲቀበል ተጠርቶ ነበር፡፡ ከሣራ ጋር የነበረው ጋብቻም በእግዚአብሔር የተባረከና በመጨረሻ በክርስቶስ በኩል የተከናወነውን የእግዚአብሔርን ዐላማ ለመፈጸም ያስቻለ ነበር፡፡ ክርስቲያኖች ሰዎች በክርስቶስ አማካይነት የአብርሃምን በረከት ዐብረው ይካፈላሉ፡፡ የምሥራቹን ወንጌል በቃልና በኑሮ በማወጅ ለሌሎች በረከት እንዲሆኑ ተጠርተዋል፡፡ ክርስቲያኖችን እግዚአብሔር ወደ ጋብቻ የሚጠራበትን ምክንያት የቅንጅት ሕይወታቸው ይህንኑ ታላቅ የእግዚአብሔር ዐላማ በብቸኛነት ሕይወታቸው ከሚያከናወኑት በበለጠ እንዲፈጽሙ ነው፡፡ በዚህ የድካም ዓለም ፍጹም የሆነ ጋብቻ የለም፡፡ እንደ ተመለከትነው የአብርሃምና የሣራ ጋብቻም ፍጹም አልነበረም፡፡ ነገር ግን ሁለት የትዳር ጓደኛሞች ምንም ዐይነት ዋጋ ቢያስከፍል፥ እግዚአብሔርን ለማገልገል ራሳቸውን ለእርሱ ሲሰጡና ተስማምተው ዐብረው ሲጓዙ እግዚአብሔር በሕይወታቸው ለሚያደርገው ሁሉ የአብርሃምና የሣራ ጋብቻ ሕያውና ቋሚ ሐውልት ነው፡፡

No comments:

Post a Comment