Thursday, January 17, 2013

የመዳን ትምህርት



(በጮራ ቊጥር 5 ላይ የቀረበ)

ካለፈው የቀጠለ

አዳምና ሔዋን ኀጢአትን ከሠሩ በኋላ ከእግዚአብሔር ለመሰወር፥ ነውራቸውንም ለመሸፈን ሲሉ በቊጥቋጦ ውስጥ እንደ ታሸጉና የበለስንም ቅጠል በመስፋት እንደ ለበሱ ሁሉ፥ የእነርሱም ልጆችና የልጅ ልጆች እንደ እነርሱ የሚያደንቋቸውን የምድር ፍጥረታትንና የሰማይ ሰራዊትን ሲማጸኑ ረድኤትን ለማግኘት እንዳልተሳካላቸው ባለፈው ዕትም ያነበብነውን እናስታውሳለን (መዝ. 120/121፥1)፡፡

በዛሬው ዕትም ደግሞ በራሱም በአካባቢውም ከሚገኙ ግዙፋንና ረቂቃን ፍጥረታት ተስፋ ላላገኘ የሰው ዘር እግዚአብሔር በራሱ ዕቅድ የነደፈለትን የመዳን መንገድ ለማስነበብ የሚከተለው ቀርቧል፡፡


ሰውን ለማዳን በእግዚአብሔር የተዘጋጀ ዕቅድ
የሰው ዘር ሁሉ ክፉ ከመሆንና ክፋትን ከማድረግ ራሱን ለመቈጣጠርም ሆነ ባሕርዩን ለውጦ መልካም ሊሆን እንደማይችል ተረድቶታል፡፡ በሚታየውና በማይታየው አካሉ ኀጢአትን ወርሶ የተፀነሰና የተወለደ በሐሳብ፥ በቃልና በሥራ ኀጢአትንም በመለማመድ የረከሰ ሰው ዐልፎ ዐልፎ መልካም የሚመስል ሥራ ይታይበታል ቢባል እንኳ፥ በሰው መካከል ለመመጻደቂያ ካልሆነ በቀር ባሕርያዊ መልካምነት ስለሌለውና የተሠራበትም መሣሪያ ማለት ሰብኣዊ ባሕርይ፥ አእምሮና ጒልበት የረከሰ ስለ ሆነ እግዚአብሔርን ሊያስደስት አልቻለም፡፡ ስለዚህም ኢሳይያስ ‘ርኲሳን ሆነናል፤ ጽድቅ ነው በማለት የሠራነው እንኳ በእግዚአብሔር ፊት ሲታይ በወር አበባ እንደ ተነከረ ጨርቅ የሚያስጸይፍ ነው’ በማለት ልባዊ ጩኸቱን በምሬት አሰማ፡፡ ነቢዩ ስለሚታወቀው ስለ ኀጢአታችን አስጸያፊነት አልተናገረም፤ ጽድቅ ነው ብለን ስለ ሠራነው መልካም ሥራ መበላሸት እንጂ፡፡ ጩኸቱ የሁላችንም ነው (ኢሳ. 64፥6)፡፡ ይህም የኢሳይያስ አባባል ከመጽሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ 14፥4 እና 15፥14 ጋር ይስማማል፡፡

ለወደፊቱ ጠባዬን አሻሽላለሁ ራሴንም በመቈጣጠር ኀጢአትን ላለመሥራት እታገላለሁ የሚል ተመጻዳቂ ቢኖር እንኳ፥ ከቶ አይሆንለትም እንጂ እንደ ተነገረው ቢሳካለት ኖሮ በመወለድ ለወረሰው የሞት ልጅነቱና ከተወለደበትም ጊዜ ጀምሮ ኀጢአትን ለመተው ውሳኔ እስካደረገበት ጊዜ ድረስ ለሠራው ኀጢአቱ የሞት ዕዳን የመክፈል ግዴታ አለበት (ዘፍ. 2፥16-17፤ ሮሜ 6፥20-23)፡፡

ኀጢአተኛው ዕዳን ለመክፈል ሲል ቢሞት፥ ለኀጢአት ተገቢ የሆነውን ዘላለማዊውን ሞት መሞቱ ነውና ተመጻዳቂነቱ ምን ያተርፍለታል? ይልቁን ለኀጢአቱ ተገቢ የሆነውን ሞት የሚሞትለት ቅዱስ የሆነ ተለዋጭ ቢያገኝና ቅዱስነትንና ኀጢአተኛነትን ከነውጤቶቻቸው ቢለዋወጡ አማራጭ የሌለው ብቸኛ ዘዴ በሆነ ነበር፡፡ እንግዲያውስ ኀጢአተኛውን የሰው ዘር ለማዳን በእግዚአብሔር የወጣው ዕቅድና የተነገረው የተስፋ ቃል ይህንኑ የሚያመለክት ነበር፡፡

ቅጠላ ቅጠልን ለብሰው በቊጥቋጦ ውስጥ የተደበቁትን አዳምንና ሔዋንን የእግዚአብሔር ድምፅ ቀሰቀሳቸው፤ ከውድቀታቸው ለማንሣት በጸጋው ያቀደውን ምስጢራዊ የምሥራች ሹክ አላቸው፡፡ የተስፋውም ቃል የሚፈጸመው፡-
1.     ጥቃትን የሚወጣላቸው የሴቲቱ ዘር ሲወለድ፥
2.    የሴቲቱ ዘር በልማደኛው ጠላት በእባብ ሰኰናውን ሲነከስ፥
3.    የሴቲቱ ዘር በምላሽ የጠላትን ራስ ሲቀጠቅጥ እንደሚሆን ተጠቊሞ ነበር (ዘፍ. 3፥5) በሴቲቱ ዘር ድል አድራጊነት የሚደመደመው አጸፋዊ ፍልሚያ የሚካሄደው ጠላት የሴቲቱን ዘር ሰኰና ከነከሰና ጊዜያዊ ድል ካገኘ በኋላ እንደሚሆን ግልጽ ሆኖ ይነበባል፡፡

የተስፋውን ቃል ያዳመጠችው ሔዋን ጒዳዩን በቀላሉ አላለፈችውም፤ ምስጢሩ ገብቷታልና፡፡ ሆኖም ሔዋን የተስፋውን ቃል በመተርጐም ረገድ ትክክለኛነቷ ፍጹም አልነበረም፡፡

*    የእባብን ራስ ይቀጠቅጣል የተባለው የሴቲቱ ዘር ወንድ ልጅ እንደሚሆን ተረድታ ነበር፡፡
*    የሴቲቱ ዘር ሲባል ከሴቲቱ ብቻ የሚወለድ እንጂ ከአዳም አብራክ የምትቀበለው ዘር ሊሆን እንደማይችል አላስተዋለችም፡፡

በመሆኑም ተስፋው ይፈጸም ዘንድ ብድር መላሹን ወንድ ልጅ የምትወልድበትን ጊዜ እጅግ ናፈቀችው፡፡ የመጀመሪያ ልጇን ቃኤልንም ስትገላገል ባለተስፋው ዘር መሰላትና “ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር ተሰጠኝ” አለችና ተነፈሰች (ዘፍ. 4፥1)፡፡

የእግዚአብሔር ሐሳብና የሔዋን ምኞት የሰማይና የምድር ያህል ተራራቀ (ኢሳ. 55፥8-9) ቃኤል የጠላትን ራስ በመቀጥቀጥ ብድር መላሹ ልጅ አልሆነም፤ ይልቁን የጠላት አገልጋይ ሆኖ ለእግዚአብሔር አገልግሎት ያደረውን የአቤልን ራስ ቀጠቀጠ (ዘፍ. 4፥8)፡፡ አቤል ከሞተ ቃኤልም ተቅበዝባዥ ከሆነ በኋላ ሔዋን ለአዳም ሌላ ወንድ ልጅ ወለደች፤ በቃኤልም ላይ አሳርፋው የነበረውንና የከሸፈውን ምኞቷን የሚፈጽም መሰላትና “ምትኬ” ለማለት ስሙን ሴት አለችው (ዘፍ. 4፥25)፡፡

የጠላት ራስ መቀጥቀጥ ከመጀመሪያዎቹ ሰዎች ጀምሮ ሲናፈቅ እንደ ነበረ ከዚያው ከመነሻው ይታይ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ሴት የተስፋውን ዘር ለሚያፈራ ተክል በሥርወ ታሪክነት አገለገለ እንጂ ራሱ የተስፋው ዘር አልሆነም፡፡ ስለዚህ ተስፋው ወደ ተነገረለት ዘር ለመምጣት በሐረገ ትውልድ አወራረድ ከሴት ወደ ኖኅ፥ ከዚያ ወደ ሴም፥ በመቀጠልም ወደ አብርሃም ይደርሳል፡፡ ለአብርሃምም እግዚአብሔር የተስፋውን ቃል በማደስ፥ “በዘርህ የምድር አሕዛብ ይባረካሉ” አለና ያ የሴቲቱ ዘር የተባለው የአብርሃምን ትውልድ ተከትሎ የሚበቅል፥ በጠላት ተንኰል ምክንያት ወደ ሰው የመጣውንም ርግማን አስወግዶ በረከትን የሚያመጣ ዘር እንደሚሆን አመለከተ (ዘፍ. 3፥14-19፤ 5፥6-32፤ 10፥21፤ 11፥10-26፤ 22፥18፤ ገላ. 3፥16)፡፡

እንደ ገናም በዘር ቈጠራ አወራረድ ወደ ይሁዳ ወልደ ያዕቆብ ሲደረስ፥ ገዥ ለመሆን ከነገደ ይሁዳ የሚወጣው ዘር እጆቹን በጠላት ደንደስ ላይ እንደሚያነሳ ተስፋና ትንቢቱ ታድሶ ተነገረ (ዘፍ. 49፥8-12፤ ዘዳ. 32፥7)፡፡

የትውልድን ሐረግ እንዲሁ እያሳሳብን ወደ ዳዊት ስንመጣ፥ ፍጻሜ የሌለውን ሰላም የሚያመጣ ዘር ከዳዊት ቤት እንደሚነሣ የተነገረበትን እናገኛለን (2ሳሙ. 7፥12-13፤ ኢሳ. 9፥6-7፤ ኤር. 23፥5-6)፡፡ የጠላትን ራስ የሚቀጠቅጥ፥ በጠላት ደንደስ ላይ እጁን የሚያነሣ፥ በረከትን የሚያመጣ፥ ሰላምን የሚያሰፍን የሴቲቱ ዘር አንዳንድ ጊዜ ዘር ብቻ በማለት የተገለጸው ከድንግል እንደሚወለድ የልደቱም ስፍራ ቤተ ልሔም እንደ ሆነ በግልጽ አመለከተ፡፡ የተቋረጠው የሰውና የአምላክ ኅብረት በሴቲቱ ዘር ስለሚታደስ ስሙ ዐማኑኤል እንዲባል መወሰኑ ተነገረ (ኢሳ. 7፥14፤ ሚክ. 5፥2)፡፡

የተስፋው ቃል በምሳሌ ሲገለጽ
ለአባቶች የተነገራቸው ተስፋ ዛሬ ተፈጽሟል፤ የጠላት ራስ ተቀጥቅጧል፤ በረከት፥ ሰላም፥ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ተገኝቷል፤ በዚህም የጸጋ ሥራ ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች “ዲያብሎስ ወድቀ፤ አርዌ ተከይደ፤ ወከይሲ ተኀጉለ፤ - ዲያብሎስ ወደቀ፤ አውሬው ተረገጠ፥ ዘንዶው ተጐዳ (ተቀጠቀጠ)” በማለት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ናቸው፡፡ ታዲያ ተስፋው በተፈጸመበት ዘመን ለምንኖረው ለእኛ ግልጽ የሆነውን ያህል ተስፋው በቃል በተነገረበት ዘመን ለነበሩ አባቶች ሁሉ ግልጽ ነበረ ማለት ያስቸግራል፡፡ ስለ ሆነም በሚታይና በሚዳሰስ ምሳሌ ገላጭነት ሰዎች ይበልጥ እንዲረዱትና ፍጻሜውን ለመጠበቅ እንዲተጉ ማድረግ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነ፡፡ ከተስፋው ቃል ጐን ለጐን ሆኖ በሰዎች ፈቃድ ጒልበትና ሀብት እየተከናወነ የተስፋው ቃል እንዴት እንደሚፈጸም በማስረዳት የሰውን እምነት ያጠናክር ዘንድ ግዙፍ የድርጊት ሥርዐት በኦሪት ተሰጠ፡፡ በኦሪት የተሰጠው ሁሉ በድርጊት የሚከናወን ምሳሌያዊ መግለጫ ነበረ፡፡

አንደኛ፥ የእግዚአብሔር ቅድስናና የሰው ርኲሰት በኦሪት ተገለጠ።

ኦሪት ከያዘቻቸው ብዙ ስጦታዎች አንዱ ዐሥር አንቀጾችን የያዘው የሕግ ድንጋጌ ነው (ዘፀ. 20፥3-17፤ ዘዳ. 5፥6-22)

እያንዳንዱ የሕግ አንቀጽ ቅዱስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚተረጒመው ብቻ አልነበረም፡፡ ሰውን በርኲሰት የሚከስስ፥ የሚወቅሥና ከፍርድ በታች መሆኑን የሚያውጅ ሕግ ነበረ፡፡ ለምሳሌ፦

ሀ. የመጀመሪያው አንቀጽ “ከእኔ በቀር ሌላ አታምልክ” ይላል፡፡ ሰው ግን በገነት ዔደን ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰይጣንን በመታዘዝ አምልኮ ባዕድን የተለማመደ ነበር፡፡
ለ. ሌላው አንቀጽ “አትስረቅ” የሚል ነው፡፡ ዳሩ ግን ሰው ካልተፈቀደለት የሞት ዛፍ ከቀጠፈበት ጊዜ ጀምሮ በመስረቅ የተወነጀለ ፍጡር ነው፡፡
ሐ. የመጨረሻው አንቀጽ “አትመኝ” አለ፡፡ ሰው ግን በገነት ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ከተከለከለው ዛፍ ለመብላትና እንደ አምላክ ለመሆን የልብ ምኞትንና የዐይን አምሮትን ካስተናገደበት ጊዜ ጀምሮ አንቀጹን በመጣስ የተወነጀለ ሆኗል፡፡

ስለዚህ የሕጉ አናቅጽ ሁሉ የሰውን ርኲሰት እያጐሉ የእግዚአብሔርን ቅድስና ያብራራሉና በኀጢአት የረከሰው ሰው የእግዚአብሔር ባሕርይና ፈቃድ መግለጫ በሆነው ቅዱስ ሕግ መስተዋትነት ራሱን ሲመለከት ከኲነኔ በታች የመሆኑን ተገቢነት አምኖ እንዲቀበል ይገደዳል (ሮሜ 3፥19-20)፡፡

እንግዲህ የሕጉ ዐላማ የእግዚአብሔርን ቅድስና ባንድ በኩል፥ በሌላው ወገንም የሰውን መርከስና ከፍርድ በታች መሆኑን ለመግለጽና እንደዚሁም ከራሱ ውጪ የሆነ መለኮታዊ መድኅን እንደሚያስፈልገው ለማስገንዘብ እንደ መሆኑ (ሮሜ 7፥7) በሁለቱ መካከል ያለው ርቀትና የባሕርያት መቃረን ከመሠረተ ተፈጥሮ የመጣ ሳይሆን በጣልቃ ገቡ ኀጢአት ምክንያት በመሆኑ (ኢሳ. 59፥1-8)፡፡

1.     እግዚአብሔር ሕጉን ለመስጠት በሲና ተራራ ላይ በክብሩ ሲገለጽ ዓውሎ ነፋስ ጭጋግና ድቅድቅ ጨለማ አካባቢውን አለበሰው፤ ተራራው ነደደ፤ ጢሱም ተትጐልጒሎ ወጣ፤ የእንቢልታ ድምፅ አካባቢውን አናወጠው፡፡ ከዚህም የተነሣ የባሕርዩ ተቃራኒ የሆነውን ኀጢአተኛ ሰው አስፈራው፤ የእግዚአብሔር ግርማ አራደው (ዘፀ. 19፥16-18)፡፡

2.    ማንም ሰው ተራራውን እንዳይነካ የተራራው እግርጌ ተከለለ፤ አፈጻጸሙ ሰው ባለበት ሁኔታ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንዳልተፈቀደለት አመለከተ (ዘፀ. 19፥19-24)፡፡

3.    ከእግዚአብሔር አፍ የወጣው እያንዳንዱ ቃል ወደ ሰው ጆሮ ሲደርስ “እግዚአብሔር አይናገረን” እስኪሉ ድረስ ሰዎችን አስበረገገ (ዘፀ. 20፥18-21፤ ዕብ. 12፥18-21)፡፡

ሁለተኛ፥ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅና ኅብረትን ለማደስ የሕይወት ካሣ መክፈል እንዳለበት በኦሪት ተነገረ፡፡

እግዚአብሔር በቅድስናውና በጽድቁ የወሰነውን ቅን ፍርዱን በማጣመም ወይም በፍርደ ገምድልነት ኀጢአትን ይቅር እንደማይል፥ ነገር ግን በሕጉ የተወቀሠና ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ የፈለገ ኀጢአተኛ ኀጢአቱን የሚሸከምለትና የኀጢአት ብድራት ሆነውን ሞት የሚሞትለት ተለዋጭ (ቤዛ) ማቅረብ እንዳለበት በሕገ መሥዋዕት ተደነገገ (ዘሌዋውያን ምዕራፍ  4 ፥ 5 እና 6) በቤዛነት የሚቀርበው እንስሳ ለሰው ነፍስ የዕሤት ተመጣጣኝነት ባይኖረውም ለሰው ሁሉ ኀጢአት አንድ ጊዜ ሊሠዋ የሚመጣውን የእግዚአብሔርን በግ በማመልከት ረገድና በምሳሌያዊ ገላጭነቱ ለሚታመኑ ሁሉ ከፍተኛ ጥቅም ነበረው (ዮሐ. 3፥16)፡፡

ሦስተኛ፥ መካከለኛና አስታራቂ እንደሚያሻ በኦሪት ተገለጠ፡፡

ለኀጢአተኛ ሰው ቤዛ የሚሆነውን መሥዋዕት ከኀጢአተኛው ተረክቦ ለእግዚአብሔር በማቅረብ የሚያስታርቅ መካካለኛ ካህን በኦሪት ተመደበ (ዘፀ. 20፥18-19፤ 28፥1፤ ዘሌ. 9፥7፤ ዘዳ. 5፥5)፡፡ በቅድሚያ ስለ ራሱ መሥዋዕት አቅርቦ ስርየትን ከተቀበለ በኋላ ነሳሒው (ንስሓ ገቢው) ኀጢአተኛ በቤዛነት የሚያቀርበውን መሥዋዕት ተቀብሎ የሚሠዋለት ካህን እንዲመደብ ሲደረግ፥ ሰውና እግዚአብሔር በኀጢአት ምክንያት በመለያየታቸው በመካከላቸው የሚቆም አገናኝ እንዲያሻቸው ታወቀ፡፡ ይልቁንም በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሊቀ ካህናቱ የሚገባበት ቅድስተ ቅዱሳን፥ መቋቋሙ የእግዚአብሔር መኖሪያ ለሰው ዝግ ሆኖ እንዲቈይ መደረጉን አረዳ (ዕብ. 9፥6-8)፡፡

እንግዲህ እግዚአብሔር ለአባቶች በገባው ቃል መሠረት ሰኰናውን በእባብ በመነከስ የሕይወት ካሣ ከፍሎና በአጸፋው የተናዳፊውን እባብን ራስ ቀጥቅጦ ሰውን ከመረዘው ከእባብ መርዝ ካዳነ በኋላ፥ ቀድሞ ወደ ነበረበት ክብር፥ ሥልጣንና አምላካዊ ኅብረት የሚመልሰው የሴቲቱ ዘር እስኪመጣ ድረስ ባለው ረጅም ጊዜ ውስጥ፥ የዚያን የተስፋ ቃል አፈጻጸምና ጥቅሙን ለማስተዋል የሚረዱ ልዩ ልዩ ምሳሌዎችን በሥርዐተ ኦሪት እያሳየ በትንቢተ ነቢያትም እያብራራ ለተስፋው ቃል መፈጸም የሰዎችን ናፍቆት ሲያሳድግና ሲያጠነክር መቈየቱን እንገነዘባለን (መዝ. 41/421፥2)፡፡

በእግዚአብሔር የታቀደው ጊዜ ሲደርስም “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር” በማለት ከወሰኑት ሥላሴ አንዱ ወልድ (ቃል) ከድንግል ማርያም ተወለደ (ማቴ. 1፥1-23፤ ዮሐ. 1፥12፤ ገላ. 4፥4)፡፡

ሰውን የማዳን ሥራ እግዚአብሔርነት በሌለው ማለት በፍጡር ሊከናወን ለምን አልተቻለም?

ብዙ ሰዎች ሰውን የማዳን ሥራን ለመፈጸም ቃለ እግዚአብሔር ወልድ፥ ሰው ይሆን ዘንድ ለምን አስፈለገ? ከእግዚአብሔርነትስ ባነሰ ደረጃ ሰውን የማዳን ሥራን መተግበር ለምን አልተቻለም? በማለት ቢጠይቁና መልሱን ከእግዚአብሔር ቃል ቢቀበሉ ተገቢ ይሆናል፡፡

1.     መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ይለናል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ወዶአልና ለተወደደው የሰው ዘር የተፈጠረ ነገርን በመስጠት ባሕርያዊ ፍቅሩ ሊረካለት አይችልም (ማሕ. 8፥6-7)፡፡ ፍቅር ራስን በመስጠት ብቻ ግቡ የሆነውን ርካታ በማግኘት ስለሚፈጸም እግዚአብሔር የሆነ ቃል ራሱን ለሰው እንዲሰጥ ባሕርያዊ ፍቅሩ አስገደደው በማለት ይደመደማል (ዮሐ. 3፥16፤ 10፥11)፡፡

2.    በኀጢአት ምክንያት ሞት የተገባውን ሰው እግዚአብሔር ከወደደው፥ የቅድስና ባሕርዩ ሳይጐዳው፥ ፍርዱም ሳይጓደል ሊያደረግለት የሚችለው ብቸኛ መንገድ ቀጥሎ የተመለከተው መሆን ነበረበት፡፡

*   የሰውን ኹለንተና ገንዘብ አድርጎ የተገኘውን እርሱነቱን የሰው ተለዋጭ ይሆን ዘንድ በኀጢአተኛ ሰው ቦታ መሰየም፤
*    የሰውን ዘር ኀጢአተኛነትና በደል ሁሉ በራሱ መሸከም፤
*    ቅጣት ኀጢአትን ይከተላልና ለኀጢአተኛነትና ለበደል የተገባውን ቅጣት መቀበል፤
*    የራሱን ንጽሕናና ቅድስና ተለዋጭ ለሆነለት የሰው ዘር እንዲቈጠር ማድረግ፡፡

እንግዲህ ሰውን የማዳን ሥራ ይህን ያህል ዋጋ መክፈልን የሚጠይቅና የሚያስጠይቅ ከሆነ፥ በፍቅር ምክንያት እንደ ግዴታው በመቊጠር ከራሱ በቀር ይህን ማን ሊፈጽመው ይችላል (ችሎታን በሚመለከት) አሁንም ከራሱ በቀር ማን ሊያከናውነው ይገባል? (ተገቢነትን በሚመለከት)

3. ሰዎች ሁሉ የኀጢአተኞቹ የአዳምና የሔዋን ልጆች በመሆናቸው የሀገራችን ክቡራን አባቶች እንደሚያብራሩት ሰይጣን “የላሜ ልጅ፥ የአውራዬ ውላጅ” ብሎ የሚጠራቸውና አንድም ሳይቀር ሁሉም የኀጢአት ዕዳ የተመዘገባበቸው ስለ ሆኑ ከነርሱ መካከል አንዱ የሌላው ቤዛ መሆን አይችልም (መዝ. 49፥36-37)፡፡

4.  ዓለም ሁሉ (ከዓለመ ሰብእ ውጭ ያሉት ዓለማት ሁሉ በአንድነት) ተጠቃሎ የሰውን ያህል ዋጋ ሊያወጣና በዕሤቱ ተመጣጥኖና ለሰው ተለዋጭ ሆኖ ይሰጥ ዘንድ ብቃት የለውም፡፡ (ማር. 8፥36-37)፡፡

5.  በደመ ነፍስ ተንቀሳቃሽ ፍጥረታት ከመሬት ብቻ ለተፈጠረው ለሰው ሥጋና ደም ተመጣጣኝነት ያላቸው ናቸው ቢባል እንኳ፥ ከእግዚአብሔር አፍ በሰው አፍንጫ በኩል ገብቶ ሰውን ሕያው ነፍስ እንዲባል ላበቃው በሰው ውስጥ ላለ ረቂቅ (መንፈሳዊ) አካል ተለዋጭ (ቤዛ) ለመሆን ብቃት እንደሌላቸው ግልጽ ነው፡፡ ስለ ሆነም በኦሪት ሥርዐት ይቀርቡ የነበሩ እንስሳትም ስለ ሰው ሁሉ ቤዛ ሆኖ የሚሠዋውን አማናዊ መሥዋዕት በምሳሌነት በማመልከትና እስከ ጊዜው ለአንጽሖተ ሥጋ በማገልገል ረዱ እንጂ ዘላለማዊ የነፍስ መንጻትንና መቀደስን አላመጡም (ዕብ. 9፥8-14፤ 10፥1-10)፡፡

6.  የሰው ቤዛ ለመሆን ሥጋቸውና ደማዊት ነፍሳቸው ከመሬት ብቻ የተፈጠሩት ፍጥረታት ብቃት የሌላቸው ቢሆንም መናፍስት ሆነው የተፈጠሩት መላእክት ለምን የሰው ቤዛ መሆን አቃታቸው? የሚል ጥያቄ ቢነሣ ተገቢ ይሆናል፡፡ መላእክት መናፍስት ቢሆኑም ለሰው ቤዛ እንዳይሆኑ ሁለት ነገር ይጐድላቸዋል፡፡

ሀ) ሥጋና ደም ስለሌላቸው ለሰው ሥጋና ደም ተለዋጭ ሊሆኑ አይበቁም (ዕብ. 2፥14-16)፡፡
ለ) ሰው ሕያው ነፍስ የሆነበት እስትንፋስ ሕይወቱ (ሕያውነቱ) የተቀዳ ወይም የመጣ ሲሆን (ዘፍ. 2፥7) መላእክት ግን እግዚአብሔር እንዲሁ ካለመኖር ወደ መኖር (“እም ኀበ አልቦ ኀበ ቦ” ይሉታል አባቶች) ያመጣቸው የተፈጠሩ መናፍስት ናቸው፡፡ ይህም ማለት በመንፈስነታቸው ደረጃም ቢሆን ከእግዚአብሔር እስትንፋስ በእፍታ ከመጣው የሰው ሕያው ነፍስ ጋር ሲነጻጸሩ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው፤ የዕሤት ተመጣጣኝነት የላቸውም (መዝ. 103/104፥4)፡፡

ባለመዝሙሩ ከመላእክት ጥቂት አሳነስኸው (መዝ. 8) ቢልም፥ ይህ የሰውን ጥንተ ተፈጥሮ የሚያመለክት ሳይሆን የሰው ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው በተቀበለው መከራ ውርደትና ሞት ምክንያት ከመላእክት እንኳ ያነሰበትን ሁኔታ እንደሚያመለክት የዕብራውያን መልክት ጸሓፊ አስረድቷል (ዕብ. 2፥14-16)፡፡

ከሰው የተወለደ ሌላ ሰው ሊሆን ያልቻለውን ቤዛነት ሰው ሆኖ የተወለደው ቃለ እግዚአብሔር (ወልድ) ቤዛ ሊሆን የቻለበትን ምስጢር የሚያስረዳው ክፍል በሚቀጥለው ዕትም ይቀርባል፡፡

No comments:

Post a Comment