ከፍሬአቸው ታውቁአቸዋላችሁ
ምሁር ነኝ የሚሉ አረጋዊ ከሰዎች ጋር ሲነጋገሩ፥ “የእኛን ሃይማኖት የሚያህል ፈጽሞ
የለም” ብለው የማውራት ልምድ ተጠናውቷቸዋል፡፡ እንዲህም ሲናገሩ ስመ ሃይማኖታቸውን እየጠሩ ነው፡፡ ቅያሬ የሌለውና የተጋነነው
ከቃል ንግግር በቀር የሕይወት ምስክርነት ያልነበረው ወሬአቸው ወዳጆቻቸውንና ቤተ ሰባቸውን ጭምር አሰልችቷቸው ኖሮአል፡፡
አንድ ቀን ከአንድ ወዳጃቸው ጋር ይጨዋወቱ ነበር፡፡ እንደ ተለመደው “የእኛን
ሃይማኖት የሚያህል የለም፤ ብቻ ምን ያደርጋል” ሲሉ፤ በተከታዮች ብዛት ከሆነ የ… እምነት ተከታዮች ይባልጣሉኮ! አለና
መለሰላቸው፡፡ ትልቋ ልጃቸው ግን “አባባ የእኛ ሃይማኖት ካለማመን የሚለይበትን አንድ ነጥብ ቢነግሩኝ” ብትላቸው ምን ለማለት
እንደ ፈለገች አልተረዱላትም፡፡ ልጅቷ የመደነጋገር ምልክት በአባቷ ፊት ላይ እንዳየች በሌላ የአገላለጽ ዘዬ ልታስረዳቸው
ሞከረች፡፡ አባቷም ሲረዱ በጣም ተቈጡ፡፡
የአረጋዊው ምሁር አስተሳሰብ እምነታችን ጥሩ ነው፤ የእምነታችን ፍሬ ግን መራራ ነው፤
ወይም እምነታችን ፍሬ አልባ (መካን) ነው እንደ ማለት ነው፡፡ ሊሆን ግን አይችልም፡፡ አንድ ሰው ወይም ቡድን የተቀበለውና
የሚመራበት የክርስትና እምነት ሕያው ከሆነ የቃል ምስክር ሳያስፈልገው ጣፋጭ ፍሬ አንዠርግጎ ይታያል፡፡ የሃይማኖትን እውነተኛነት
በሰውነት ላይ በሚታሠር፥ በሚንጠለጠል ወይም በሚለጠፍ ምልክት ወይም በድርጅት መለዮ ለመግለጥ መሞከር ከንቱ ድካም ነው፡፡
በንግግር ማሳመር የእምነታቸውን ጥራትና እውነተኛነት ለመግለጥ የሚሞክሩ ካሉም ብልጦች ሊያሰኛቸው ቢችል ነው፡፡ ከዚህ ግን
አያልፍም፡፡
የመጀመሪያው የእምነት ፍሬ ፍቅር ነው፡፡ ጌታችንም የእርሱ ለመሆናችን የሰጠን ምልክት
ይኸው ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱንና ደቀ መዛሙርቱን ለማስተናገድ ፈቃደኞች ያልሆኑትን የሰማርያ ነዋሪዎች፥ “እሳት
ከሰማይ ወርዶ እንዲበላቸው እናድርግ” የሚል ጥያቄ ያቀረቡትን የዘብዴዎስን ልጆች፥ “ከምን መንፈስ እንደ ሆናችሁ አታውቁምን?
የሰው ልጅ ሊያድን፥ ራሱንም ለሰዎች ቤዛ ሊሰጥ መጣ እንጂ ሰዎችን ለማጥፋት አልመጣም” ያለው ቃል ትዝ ሊለን ይገባል (ሉቃ.9፥51-56)፡፡
ክርስቲያኖች ስለ ሃይማኖታችን ጥራት በመመስከር አንድከም፤ መልካም ዛፍ ስለ ጣፋጭነቱ
ተናግሮ አያውቅም፤ ማስታወቂያ ተናገሩልኝ፥ ምልክትም እሠሩብኝ አይልም፡፡ አበባዬንና ፍሬዬን መስጠት ብቻ ይበቃኛል፡፡ ሰዎችም
አበባዬን አሽትተው ስለ መዓዛው፥ ፍሬዬንም ቀምሰው ስለ ጣፋጭነቱ ይናገሩ ባይ ይመስላል፡፡ ሕያው እምነትም የሚታወቀው እምነቱ
በሚሠራው መልካም ሥራ ነውና፡፡
“ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ፤ ከእሾኽ ወይን፥ ከኲርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ
መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፤ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል፡፡ መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት ወይም ክፉ ዛፍ
መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም” (ማቴ. 7፥16-18)፡፡
መልካም
ፍሬ ማፍራት የማንችለው እውነተኛ የወይን ግንድ በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ባለመብቀላችንና ባለማደጋችን፥ ከሥሩም ከግንዱም
የሚተላለፍልንን ሁሉ በብቃት ባለመቀበላችን ሊሆን ስለሚችል መጀመሪያ የበቀልንበትን ግንድ ማንነት እንመርምር፡፡ ተሳስተንም ሆነ
ዐውቀን በአሜኬላ ላይ የበቀልን ከሆነ የወይን ፍሬ በሚያፈሩት ስንቀና እንኖራለን፡፡ ቅናትም ወደ ምቀኝነት፥ ምቀኝነትም ወደ ቊጣና
በቀል ያሸጋግሩናል እንጂ ምን ጊዜም የወይን ፍሬ እንድናፈራ አይረዱንም (ማቴ. 12፥33-34)፡፡
God bless you again and again , I pray for our ETOC brothers so GOD opens their eyes and ears.
ReplyDelete