Friday, February 22, 2013

ርእሰ አንቀጽ



የቀደመችው መንገድ

ከአንድ ጓደኛችን ቤት ተሰብስበን ስንጨዋወት፥ አንዳንዶቻችን መጽሔቶችንና አልበሞችን እናገላብጥ ነበር፡፡ ከመካከላችንም አንዱ ወንድም የተለያየ ጌጠኛ ቅርጽ የተሰጣቸው 50 የመስቀል ምስሎች የተሣሉበትን አንድ ገጽ ወረቀት አገኘና በአድናቆት አሳየን፡፡ የኪነ ጥበብ ሰዎች የተራቀቀ ሙያቸውን የገለጹባቸው ውበቶች ይታዩባቸው ነበር፡፡ የምስሎቹ ብዛት በአንድ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ ካየናቸው የመስቀል ምስሎች በ30 ቍጥር ብልጫ ነበረው፡፡ አንዱ ጓደኛችን “ከእነዚህ መካከል ትክክለኛው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የትኛው ነው?” አለና ጠየቀ፡፡ እርስ በርስ ተያየንና ተሣሣቅን፡፡ ሌላውም ሌላ ጥያቄ አከለበት፡፡ “ከዕንጨት፥ ከድንጋይ፥ ከብረታ ብረት፥ ከከበሩ ማዕድናት ከተፈበረኩት መካከል ክብር ያለው መስቀል የትኛው ነው?” ማንም መልስ አልሰጠም፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሲባል ወደ ሰው አእምሮ ፈጥኖ የሚመጣው ትውስታ እንደ “ተ” ያለ ቅርጽና እርሱን ለማስዋብ በባለሙያዎች የሚጨመርበት ሐረግ (ጠልሰም) ነው፡፡ ግን ይህም ሆነ ያ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባዋል፡፡ ለምን፥ እንዴት፥ ቢባል በዓለም ላይ መስቀል በሚል ስም የምናየው ምስል ሁሉ ሌላ ባለቤት አለው፡፡ አንጥረኞች፥ ጠራቢዎች፥ ቀራጺዎች፥ ዐናጺዎች፥ አምራች ድርጅቶች፥ ላመረቷቸው መስቀሎች የመጀመሪያ ባለቤቶች ሲሆኑ፥ ከእነዚህ ላይ የገዙ ሰዎችም ገንዘብ ያወጡበት ነውና የኔ የሚሉት የግል ንብረታቸው ነው፡፡ እነርሱም ሊሸጡት፥ ሊለውጡት፥ ሊያጌጡበትም መብት አላቸው፡፡ የጌታ መስቀል ግን አይሸጥም አይለወጥም፡፡ ሸጠው ለወጠው የሚለው ማስረጃ የለም፡፡ ያ መስቀል አሁንም የራሱ ነው፡፡

Sunday, February 17, 2013

መሠረተ እምነት



ካለፈው የቀጠለ
ነጥብ (ጭብጥ) ስድስት

በሦስት አካላትና በሦስት ኩነታት ራሱን የገለጸው አንዱ ይሆዋ በመሆኑ፥

የማይከፋፈል አንድ መለኮት (አምላክነት)
የማይበተን አንድ ሥልጣን
የማይለያይ አንድ ዘላለማዊ መንግሥት ብቻ እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡

1.     ስለ አምላክነት
አብ፥ ወልድና መንፈስ ቅዱስ (ሥላሴ) ያንዲት የማትከፋፈል መለኮት እኩል ባለቤቶች ናቸውና፥
1-ሀ. “አብ እውነተኛ አምላክ ነው” እንላለን “እውነተኛ አምላክ የሆንኽ አንተን ብቻ የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ የዘላለም ሕይወት ናት” ዮሐ. 17፥3፡፡

Monday, February 11, 2013

መሠረተ እምነት



ከናሁ አዳም
ነጥብ (ጭብጥ) ዐምስት

ካለፈው የቀጠለ

አብ፥ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በመባል የህላዌ ፍጹምነትን ለሚያረጋግጥ የየራሳቸው ግብር ባለቤት የሆነው በሦስት አካላትና ስሞች የተገለጹት ሥላሴ “በኩነትም” ሦስት መሆናቸውን የእግዚአብሔር ቃል ያስተምራል፡፡ ይህም ማለት አንዱ አካላዊ መንፈስ በሦስት “ኩነታት-ኹነታዎች” አልተገለጸም፡፡ ዳሩ ግን እያንዳንዱ አካላዊ መንፈስ በአንዱ መለኮተ ይሆዋ በተለየ አካሉ የራሱን ህላዌና ባሕርያዊ ግብር መግለጽ በሚችል “ኩነት- ኹነታ” ታውቋል፡፡

ኩነት (ኹነት-ኹነታ)

አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ (ሥላሴ) ሥሉስነታቸው እንደ ተጠበቀ በአሐዳዊው መለኮተ ይሆዋ እያንዳንዳቸው ምን ሆነው እንደሚገኙ በእግዚአብሔር ቃል የተገለጸው ባሕርያዊ ኹነታቸው በግእዝ “ኩነት” ይባላል፡፡ አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ ለሦስት ህልዋን ተገቢ በሆኑ ሦስት ስሞች እንደሚጠሩና እንደሚታወቁ ሁሉ እያንዳንዱ አካላዊ መንፈስ በራሱ ባሕርያዊ ኹነታ ስለ ታወቀ ለሥላሴ ሦስት ኹነታት አሏቸው ማለት ነው፡፡

Friday, February 8, 2013

ልዩ ልዩ


ከማኅበረ በኲር

1.    አመሠራረቱ

ወንጌል በሀገራችን እንደተሰበከ ከተቋቋሙት ቀደምት ማኅበራት አንዱ ማኅበረ በኵር ነበረ፡፡ አሁንም “በኲረ አኀው (የምእመናን ወንድሞች አለቃ)” በሆነው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ማኅበረ በኲር የቀድሞውን ስምና ትውፊት ወርሶ ተቋቁሟል፡፡

2.   የእምነት መግለጫ
የማኅበረ በኲር ትምህርተ እምነት መሠረቱ፥ ግድግዳው፥ ጣሪያውና ጒልላቱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጥንታውን ሊቃውንት ከመጽሐፍ ቅዱስ በማውጣጣትና አሰባስቦ በማዘጋጀት እምነታቸውን የገለጹባቸው፡-

ሀ. የሐዋርያት እምነት መግለጫ፥
ለ. የኒቅያ የእምነት መግለጫ (ጸሎተ ሃይማኖት)፥
ሐ. የሐዋርያት አመክንዮ እና
መ. የአትናቴዎስ የእምነት መግለጫ የተባሉትን ማኅበረ በኲር በእምነት መግለጫነታቸው ይቀበላቸዋል፡፡

3.  አስተምህሮት
የማኅበረ በኲር አስተምህሮት በጮራ መጽሔት በግልጽ ይተላለፋል፡፡ የምእመናንን ዐይን መግለጥ እንደ ጦር የሚፈሩት፥ ለራሳቸው የሚያምኑትን፥ የኔ የሚሉትን በማስተማር ፈንታ ባልተሰጣቸው ውክልና ስለሌላው መናገር የሚያዘወትሩት ትውልደ አውጣኪ ከሚነዙት መርዘኛ ወሬ የማኅበረ በኲር አስተምህሮት የተለየ ነው፡፡

4.   ግንኙነት
“በአብ የተጀመረች እምነት ወደ ወልድ ታደርሳለች፥ በመንፈስ ቅዱስም ትፈጸማለች፡፡ ሃይማኖት እንተ እም ኀበ አብ ተወጥነት ኀበ ወልድ ታበጽሕ፥ ወኀበ መንፈስ ቅዱስ ትትፌጸም፡፡” እያሉ በአብ፥ በወልድ፥ በመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ መሆን ከሚያምኑ ሁሉ ጋር የመንፈስ አንድነት እንዳለው ማኅበሩ ያምናል፡፡ ስለ ሆነም፥ ጒድለትና ጭማሪ የሌለበትን ሦስትነትና ፍጹምነት ያለውን የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት ይመሰክራል፡፡


(በጮራ ቊጥር 5 ላይ የቀረበ)

Wednesday, February 6, 2013

መጽሐፍ ቅዱስ


የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት
 በጮራ ቊጥር 5 ላይ የቀረበ
ኦሪት ዘፍጥረት 3፥14-25

የእግዚአብሔር ፍርድና የደኅንነት መንገድ

መግቢያ፤ ሰው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተላልፎና ማስጠንቀቂያውን ጥሶ በኀጢአት እንደ ወደቀ ባለፈው ጥናት ተመልክተናል፡፡ አማኞች ይህን አንቀጽ ሲያነቡ ብዙ ጊዜ በእግዚአብሔር ፍርድ ላይ ያተኲራሉ፡፡ እግዚአብሔር በፍርድ ሰውን መቅጣት ብቻ ሳይሆን ሰውን የማዳን ዐላማ ያለው በመሆኑ በዚህ አንቀጽ የደኅንነትን መንገድ እግዚአብሔር እንዴት እንደ ከፈተ እንመረምራለን፡፡ በርግጥ ይህ ምዕራፍ ስለ ክርስቶስ በግልጽ አይናገርም፡፡ ነገር ግን ወደ ዐዲስ ኪዳን ሐሳብ የሚመሩን ልዩ ልዩ ፍንጮች አሉ፡፡ ምክንያቱም በብሉይ ኪዳንም ሆነ በዐዲስ ኪዳን ዘመን ሰው የሚድንባቸው መሠረታውያን ነገሮች አንድ ዐይነት ስለ ሆኑ ነው፡፡

ለጥያቄዎቹ መልስ ለመስጠት ከመሞከርህ በፊት የሚከተሉት ማስታወሻዎች ሊረዱህ ይችላሉ፡፡

ቊ. 14 በሆድህም ትሄዳለህ፤ እባብ በፊት ቀጥ ብሎ በክብር የሄደ ይመስላል፡፡
ቊ. 15 በዘርህ፥ የእባብ ዘር የሰይጣንን ተከታዮች ያሳስባል፡፡
በዘርዋም፥ የሴቲቱን ዘር በሥጋዊና በመንፈሳዊ አቅጣጫ መተርጐም የሚቻል በመሆኑ ቃሉ ሰዎችን ሁሉ በእምነት የሚኖሩትን ብቻ ወይም ክርስቶስን ሊያመለክት ይችላል፤ ዘፍ. 17-18፤ ሮሜ 16፥20፤ ገላ. 3፥16፡፡

Sunday, February 3, 2013

አለቃ ነቅዐ ጥበብ


ጭውውት
አለቃ ነቅዐ ጥበብና ቤተ ሰባቸው
 (በጮራ ቊጥር 5 የቀረበ)
የአለቃ እልፍኝ እንደ ተለመደው በሰዎች ተሞልታለች፡፡ ልዕልት፥ አንተነህና ግሩም እንግዶቹን በማስተናበር ከቈዩ በኋላ፥ ወደ በሩ አጠገብ ተቀምጠዋል፡፡ የዐይን መነጽራቸውን እንደ ሰኩ፥ በፊታቸው ትልቅ መጽሐፍ በአትሮንስ ላይ ዘርግተው ከፍ ባለ በርጩማ ላይ በእንግዶቹ መሐል የተቀመጡት አለቃ ነቅዐ ጥበብ ጉባኤውን በጸሎት አሳልፈው ለእግዚአብሔር ሰጡ፡፡ ቀጥለውም ወደ ሰዎቹ ቀና ብለው አንድ በአንድ ተመለከቷቸውና “የዛሬው ውይይት በምን ርእስ እንዲሆን ወስናችኋል?” አሉና ጠየቁ፡፡

ዲያቆን ምስግና መስቀልኛ ያደገደገውን ኩታውን ከአመቻቸ በኋላ፥ “ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅነት ቢያስረዱን? አንብቡ የተባልነውን ኦሪት ዘሌዋውያን ከም. 4-6 ያለውንና ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የተጻፈውን መልእክት ደጋግመን አንብበናል፡፡ በዚህ ርእስ የሚሰጡንን ማብራሪያ ለመከታተል ተዘጋጅተናል፡፡” ሲል ሁሉም ዲያቆን ምስግና በተናገረው መስማማታቸውን ለመግለጽ ራሳቸውን ወደ ላይና ወደ ታች ነቀነቁ፡፡

Friday, February 1, 2013

መጽሐፍ ቅዱስ


የመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅላላ ዕውቀት

ከሁሉን መርምር
(በጮራ ቊጥር 5 ላይ የቀረበ)
በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝ በብሉይ ኪዳን መጨረሻ ከገጽ 721-1037 በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች የማይገኙ መጻሕፍት በመጨመራቸው ተጨንቀውና ግራ ተጋብተው ያውቃሉን? “ተጨማሪ (ዲዮትሮካኖኒካል) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት” በሚል የክፍል መጠሪያ የተጨመሩት መጻሕፍት 18 ናቸው፡፡

በውሳኔ የተጨመሩት መጻሕፍት የሚገኙበት ጥራዝ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ እንደ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ሲቈጠር እነርሱ የሌሉበት ጥራዝ ግን “ጐዶሎ መጽሐፍ ቅዱስ” ተብሎ ሲጠራ ተሰምቷል፡፡