Friday, February 22, 2013

ርእሰ አንቀጽ



የቀደመችው መንገድ

ከአንድ ጓደኛችን ቤት ተሰብስበን ስንጨዋወት፥ አንዳንዶቻችን መጽሔቶችንና አልበሞችን እናገላብጥ ነበር፡፡ ከመካከላችንም አንዱ ወንድም የተለያየ ጌጠኛ ቅርጽ የተሰጣቸው 50 የመስቀል ምስሎች የተሣሉበትን አንድ ገጽ ወረቀት አገኘና በአድናቆት አሳየን፡፡ የኪነ ጥበብ ሰዎች የተራቀቀ ሙያቸውን የገለጹባቸው ውበቶች ይታዩባቸው ነበር፡፡ የምስሎቹ ብዛት በአንድ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ ካየናቸው የመስቀል ምስሎች በ30 ቍጥር ብልጫ ነበረው፡፡ አንዱ ጓደኛችን “ከእነዚህ መካከል ትክክለኛው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የትኛው ነው?” አለና ጠየቀ፡፡ እርስ በርስ ተያየንና ተሣሣቅን፡፡ ሌላውም ሌላ ጥያቄ አከለበት፡፡ “ከዕንጨት፥ ከድንጋይ፥ ከብረታ ብረት፥ ከከበሩ ማዕድናት ከተፈበረኩት መካከል ክብር ያለው መስቀል የትኛው ነው?” ማንም መልስ አልሰጠም፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሲባል ወደ ሰው አእምሮ ፈጥኖ የሚመጣው ትውስታ እንደ “ተ” ያለ ቅርጽና እርሱን ለማስዋብ በባለሙያዎች የሚጨመርበት ሐረግ (ጠልሰም) ነው፡፡ ግን ይህም ሆነ ያ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባዋል፡፡ ለምን፥ እንዴት፥ ቢባል በዓለም ላይ መስቀል በሚል ስም የምናየው ምስል ሁሉ ሌላ ባለቤት አለው፡፡ አንጥረኞች፥ ጠራቢዎች፥ ቀራጺዎች፥ ዐናጺዎች፥ አምራች ድርጅቶች፥ ላመረቷቸው መስቀሎች የመጀመሪያ ባለቤቶች ሲሆኑ፥ ከእነዚህ ላይ የገዙ ሰዎችም ገንዘብ ያወጡበት ነውና የኔ የሚሉት የግል ንብረታቸው ነው፡፡ እነርሱም ሊሸጡት፥ ሊለውጡት፥ ሊያጌጡበትም መብት አላቸው፡፡ የጌታ መስቀል ግን አይሸጥም አይለወጥም፡፡ ሸጠው ለወጠው የሚለው ማስረጃ የለም፡፡ ያ መስቀል አሁንም የራሱ ነው፡፡



ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ ምእመናን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ካልሆነ በቀር በሌላ እንደማይመካ አስገነዘበ፡፡ ገላ. 6፥14 የሚመካበትንም ምክንያት ሲያብራራ፡-

አንደኛ፡- በእርሱ ላይ የተሰቀለው የመስቀሉ ባለቤት ማን እንደ ሆነ ስለሚያውቅ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ብሎታል፤ የጌታ በመሆኑ በቂ መመኪያ ነውና፡፡

ሁለተኛ፡- ዓለም በሚል አጠቃላይ ስም የሚታወቀው ጠላት (1ዮሐ. 2፥15-16) ለእኔ የተሰቀለበት ነው ብሎታል፡፡

ሦስተኛ፡- እኔም ለዓለም (ለጠላቴ) የተሰቀልሁበት ነው (ገላ. 2፥19-20) ሲል አጠቃሎታል፡፡
እንደ ሐዋርያው ማብራሪያ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የሚባለው ጌታ ኢየሱስ በኀጢአት የተሞላችዋን ዓለም ወይም ዓለምን ከነሙሊቷ (ኀጢአት) ተሸክሞ የኀጢአትን ዋጋ ለመክፈል ሲል እኔን ሆኖ የተቀጣበት፥ የተሰቀለበት፥ ተቸንክሮ እየቈሰለ እየደማ ነፍሱን የሰጠበት፥ በጠቅላላው ሥጋውንና ነፍሱን መሥዋዕትና ቍርባን አድርጎ ያቀረበበት (ኤፌ. 5፥2) በቀራንዮ ተራራ ላይ አንድ ጊዜ ተተክሎ የነበረ ዕንጨት ነው፡፡ ይህን መስቀል ዛሬ ወደ ቀራንዮ ብንሄድ እንኳ እዚያ አናገኘውም፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው ከገነዙና ከከፈኑት በኋላ ቀበሩት፤ (ዮሐ. 19፥38-42)፡፡ እርሱ ግን በሦስተኛው ቀን ተነሣ፤ በዐርባኛው ቀን ዐረገ፡፡ ዛሬም በአባቱ ቀኝ ይገኛል (ሐ.ሥ. 1፥1-9፤ 1ጴጥ. 3፥22)፡፡ ታዲያ ዛሬ ዓለም ለኔ የተሰቀለበትን እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበትን የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል የት ነው የማገኘው? ለመፈለግ ወደ ቍፋሮ ልሰማራን? አስመስዬ ልሥራን?

የገላትያ ምእመናን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቱ ቀኝ ባለበት ጊዜ እንደ ተሰቀለ ሆኖ በመንፈስ ዐይን ያዩት ነበር፡፡ ለእውነት መታዘዛቸው ሲቋረጥ ግን የተሰቀለውን ኢየሱስን ማየታቸው ተቋረጠ፡፡ ከዚህ የተነሣ ሐዋርያው የገላትያ ምእመናን ወደዚያ ደረጃ ተመልሰው ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ተሰቀለ ሆኖ እስኪያዩት ድረስ ይጠባበቅ ነበር (ገላ. 3፥1፤ 4፥19)፡፡

ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያንም ይህን በተመለከተ ጥልቅ ትምህርት አስተላልፋልናለች
“ተሰቅለ በእንቲአነ፤ ወበመስቀሉ ኮነ ሕይወትነ ጽንዕነ ቤዛነ፤ ዘውእቱ ምስጢር ኅቡእ ፍሥሓ ዘኢይትዌዳእ … ዘእምትካት ኅቡአ ኮነ ይእዜሰ ክሡተ ምስጢረ ኮነ ለምእመናን አኮ ከመ ይትረኣይ አላ ከመ ይትኀለይ ውእቱ ዝንቱ መስቀል … በዝንቱ እለ ትጸንዑሂ ምእመናን! ሕቱ ርእሰክሙ አጽምሙ አእዛኒክሙ ወእለ ይትረአያ አዑሩ አእይንቲክሙ እለ በገሃድ ከመ ታእምሩ ፈቃዶ ለኢየሱስ ክርስቶስ ወኵሎ ምስጢረ መድኀኒትክሙ”

ትርጉም፥ “[ኢየሱስ ክርስቶስ] ስለ እኛ ተሰቀለ፤ በመስቀሉም ደኅንነታችን፥ በጠላት ላይ ድል አድራጊነታችን፥ ከኀጢአትም መዋጀታችን ተገኘ፡፡ ይህም መዳንን ያገኘንበት መስቀል በዐይነ መንፈስ ካልሆነ በቀር በዐይነ ሥጋ የማይታይ፥ በእደ መንፈስ ካልሆነ በቀር በእደ ሥጋ የማይዳሰስ፥ ረቂቅ ምስጢር ነው፤ ተተርኮ የማያልቅም ደስታ ነው … አስቀድሞ ረቂቅ የነበረው ዛሬ ግን ለምእመናን ግልጥ ምስጢር የሆነው ይህ መስቀል የተገለጠ ሆኖአል ቢባልም በዐይነ መንፈስ የሚያዩት በኅሊና የሚያስቡት የሚያሰላስሉት በኀልዮ ገንዘብ የሚያርጉት ነው እንጂ በዐይነ ሥጋማ አይታይም … ይህን ትምህርት በመቀበል የጸናችሁ ምእመናን ሆይ! ራሳችሁን መርምሩ፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ የደኅንነታችሁ ምስጢር እንዴትና ምን ያህል ጥልቅ መሆኑን ታስታውሉ ዘንድ ዓለማዊ ሹክሹክታዎችን የሚሰሙ የሥጋ ጆሮቻችሁን ዝጉ፡፡ በዓለማዊ ክበብ የሚንቀሳቀሱትን ለማየት የሚጕረጠረጡትን የሥጋ ዐይኖቻችሁን ጨፍኑ፤ የደኅንነት ምስጢር የተፈጸመበት የኢየሱስ መስቀል የሚታየው በዚህ መንገድ ነውና፡፡”
በማለት ቤተ ክርስቲያን አስተምራ ነበር፡፡

ስለ ሆነም መስቀለ ኢየሱስ የሚመረት፥ ለገበያ የሚቀርብ፥ የሚሸጥና የሚለወጥ፥ ከከበሩ ማዕድናት የተሠራ የሀብት ክምችት ወይም ኪነ- ጥበብ አይደለም፡፡ የታሪክ ቅርስም አይደለም፡፡ የመስቀል ምስል በምልክትነት አያገለግልም አንልም፡፡ የምንለው ግልጽ ነው፡፡ በመስቀል ላይ ስለ ተቸነከረ ለመስቀልና ለምስማር ምስሎች፥ ስለ ተገረፈ ለጅራፍ ምስል፥ ራሱን በእሾኽ አክሊል ስለ ተወጋ ለእሾኽ ምስል፥ ስለ ተገነዘ ለመግነዝና ለከፈን ምስሎች፥ ጐኑን በጦር ስለ ተወጋ ለጦር ምስል እንስገድ ማለትን ቤተ ክርስቲያን አላስተማረችም፡፡ እንኳ ምስሎቻቸው ታሪክ የተፈጸመባቸው መሣሪያዎች ቢገኙ እንኳ ከታሪካዊ ቅርስነት አያልፉም፡፡

ከአባቶቻችን የወረስናት የጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ይህቺ ናት፡፡ ይቺን የቀደመችውን መንገድ እንፈልጋት፥ እናግኛት፥ እንራመድባት፥ እንቢም አንበል (ኤር. 6፥16)፡፡

(በጮራ ቍጥር 6 ላይ የቀረበ)

No comments:

Post a Comment