Friday, March 8, 2013

መጽሐፍ ቅዱስ


የመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅላላ ዕውቀት
ከሁሉን መርምር
በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝ በብሉይ ኪዳን መጨረሻ ከገጽ 721-1037 በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች የማይገኙ መጻሕፍት በመጨመራቸው፥ ተጨንቀውና ግራ ተጋብተው ያውቃሉን? “ተጨማሪ (ዲዮትሮካኖኒካል) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት” በሚል የክፍል መጠሪያ የተጨመሩት መጻሕፍት 18 ናቸው፡፡

በውሳኔ የተጨመሩት መጻሕፍት የሚገኙበት ጥራዝ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ እንደሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ሲቈጠር እነርሱ የሌሉበት ጥራዝ ግን “ጐደሎ መጽሐፍ ቅዱስ” ተብሎ ሲጠራ ተሰምቷል፡፡

መጠሪያቸው እንደሚያስረዳው እነዚህ ተጨማሪ መጻሕፍት ቀደም ሲል ከቅዱሳት መጻሕፍት ቍጥር ውጪ እንዲሆኑና በአዋልድነት እንዲጠሩ ያደረጋቸው አያሌ ታዋቂ ምክንያቶች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቶቹ ከአዋልድ መጻሕፍቱ ጋር ታትመው ቢሆኑ ኑሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ባላደናገሩ ነበር፡፡

የብሉይ ኪዳን መምህራን ስለ እያንዳንዱ ዲዮትሮካኖኒካል መጽሐፍ በማስረጃ የተደገፈ ማብራሪያ ይሰጡናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይስማሙባቸውን ነጥቦች በመጠቈም ማቅረባችንን እንቀጥላለን፡፡

ተረፈ ዳንኤል
1.  “ተረፈ” ለሚለው ግስ ዘር የሆነው “ተረፍ” በዐማርኛ ትርፍ፥ ትራፊ ማለት ሲሆን፤ የምግብ ተረፍ ፍርፋሪ፥ የመጠጥ ተረፍ ጭላጭ ወይም አተላ፥ የምርት ተረፍ ግርድ ይባላል፡፡ የሌላ የሌላውም ተረፍ ወይም ትራፊ እንደዚሁ በተለያየ ስያሜ ይጠራል፡፡

ተረፈ ዳንኤል ለተባለው መጽሐፍ ትራፊ የሚለው ትርጉም የተሰጠው ከዋናው ከትንቢተ ዳንኤል ጥራዝ ስለ ተረፈ፥ በዳንኤል ስም የተደረሰ ቢሆንም የነቢዩ ዳንኤል መሆኑ አጠራጣሪ ስለ ሆነ፤ ከትንቢተ ዳንኤል ጋር በሐሳብ፥ በቃላት አሰካክ፥ በሐረግ አሳሳብ፥ በዐረፍተ ነገር አቀራረጽ … ስለማይመሳሰል፤ ትራፊ ወይም ተረፍ እንበለው ተብሎ ይሆን?

2.  ተረፈ ዳንኤል ተብሎ የተለየ ርእስ ከተሰጠው በኋላ ለትንቢተ ዳንኤል 13ኛ ምዕራፍ ሆኖ መቅረቡ ያስገርማል፡፡ ተረፍነቱ ለትንቢተ ዳንኤል መሆኑ ከታመነበት “ተረፈ ትንቢተ ዳንኤል” ተብሎ መሰየም ነበረበት፡፡

3. ሕዝብና መንግሥታት፥ ሀገርና ሰዎች የሚነቀሉበትና የሚፈርሱበትን፥ የሚጠፉበትንና የሚገለበጡበትን፥ እንደ ገናም የሚቆሙበትንና የሚተከሉበትን የትንቢት ቃል ይናገሩ ዘንድ እግዚአብሔር በነቢያት ላይ የሚያስቀምጠው ኀላፊነት በትርጉም ተወስዶ ሸክም ይባላል፡፡ እንዲያደርሱ ኀላፊነት ለተሰጣቸውም ሆነ ለሰሚዎቹ ሸክም ነው (ኢሳ. 13፥1፤ 15፥1፤ 17፥1፤ 19፥1፤ 21፥1፡13፤ 22፥1፤ 23፥1)፡፡  ይህም ሸክም የሚለው የዐማርኛ ቃል በግእዙ ብሉይ ኪዳን በተለይ በዕንባቆም 1፥1 እና በሚልክያስ 1፥1 ላይ “ራእይ ወይም ጾር” መባል ሲገባው፥ ተረፍ እየተባለ ተተርጉሟል፡፡ ዳሩ ግን በዚህ መመዘኛም ቢሆን ተረፈ ዳንኤል ታሪክን እንጂ ትንቢትን ወይም ራእይን አልያዘምና “ሸክም” ተብሎ የመነገር ብቃት የለውም፡፡

4.  በ1፥1-2 “ንጉሡ ዳርዮስ ሞቶ በባቶቹ መቃብር ከተቀበረ በኋላ፥ የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ መንግሥቱን ይዞ ዳንኤልም የንጉሡ የቂሮስ እልፍኝ አሽከር ነበር፡፡ ከባለሟሎቹም ሁሉ እሱ ይከብር ነበር” ተብሏል፡፡ ሆኖም ኢዮአቄም በነገሠ በ3ኛው ዓመት ናቡከደነጾር ወደ ይሁዳ ዘምቶ ከእግዚአብሔር ቤት ከፊል ዕቃዎችን ሲወስድ ወጣቱን ዳንኤልንና ሌሎችን እንደርሱ ያሉ የመሳፍንት ልጆችን ወደ ባቢሎን ይዞ መሄዱ ተረጋግጧል (ዳን. 1፥1-7)፡፡ የወጣቶቹ የእነ ዳንኤል እድሜ በተማረኩበት ጊዜ ስንት እንደ ነበረ ባይታወቅም፥ ዳንኤል በራሱና በጓደኞቹ ስም ሆኖ የተናገረውን አስተያየት (ዳን. 1፥8-16) ለማፍለቅና በእምነቱ ለመጽናት ያደረገውን ውሳኔ ስንመለከት የዚያን ጊዜ ዕድሜውን ለመገመት መንገድ ይከፍትልናል፡፡

አረማውያን እንስሳም ሆነ አውሬ ባረዱ ቍጥር ደሙን በመርጨትና የሥጋን ቅንጥብጣቢ በመወርወር አምልኮ ባዕድን ስለሚፈጽሙበት በዚህ ሁኔታ ከተዘጋጀ ሥጋ በመብላት በታረደው እንስሳ ሥጋና ደም በኩል ከሚመለኩ መናፍስት ጋራ ላለመቈራኘት እነ ዳንኤል ቍርጥ ውሳኔ አሳለፉ፡፡ በተጨማሪ በእስራኤላውያን ዘንድ የማይበሉ እንስሳትና አራዊት የሞቱትም ሳይቀሩ በአረማውያን ዘንድ እንደሚበሉ ያውቁ ነበርና ተዘጋጅቶ በሚሰጣቸው ምግብ የእነዚህ የማይበሉ እንስሳትና አራዊት ሥጋ ስለሚኖር በሕግ የተከለከለውን በመብላት ላለመርከስ ወሰኑ፡፡ ውሳኔአቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው ወጣቶቹ ፍጹም እምነት ነበራቸው፡፡ ሥጋ ባለመብላትና ጥራጥሬ ብቻ በመብላት በሰውነታቸው ሊደርስ ይችል የነበረውን ክሳት አምላካቸው እንደሚከላከልላቸው ያምኑ ነበር፡፡ ውሳኔያቸውን በግድ ለማስለወጥ ቢሞከር ኖሮ እስከ ሞት ድረስ ይጸኑ ነበር ማለትም ይቻላል፡፡

እስከዚህ ደረጃ የዳበረው የቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀታቸውና ሚዛኑን ለመጠበቅ የጐለመሰው አእምሮዋቸው፥ እንዲሁም በመጻሕፍት ቃል በመታመን የመጽናት ችሎታቸው ሲታይ በዚያ ጊዜ ዳንኤል ከ15-18 ዓመት እድሜ ሳይኖረው አይቀርም ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ስለሆነም
ሀ. ይህ አነስተኛ የዕድሜ ግምት ለዳንኤል ቢያዝ 15 ዓመት፣
ለ. የኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት 11 ዓመት ስለ ሆነ እነ ዳንኤል የተማረኩበት 3 ዓመት ሲቀነስ ከዚያ በኋላ ኢዮአቄም የገዛበት ዘመን (2ዜና. 36፥5) 8 ዓመት፣
ሐ. ከኢዮአቄም ቀጥሎ የነገሠውን የዮአኪንን የግዛት ጊዜ 3 ወርን (2ዜና. 36፥9) በመተው ቀጥሎ የነገሠው የሴዴቅያስ የግዛት ዘመን (2ዜና. 36፥11) 11 ዓመት፣
መ. የይሁዳ መንግሥት ከተደመሰሰ በኋላ ምድሪቱ ለሰባ ዓመታት እንድታርፍ በነቢዩ በኤርምያስ እንዲመለሱ እስከ ታወጀበት እስከ ፋርሳዊ ቂሮስ 1ኛ ዓመት ድረስ (2ዜና. 36፥17-23) 70 ዓመት ሲደመር በዚህ ጊዜ የዳንኤል ዕድሜ 104 ዓመት ሆኖ ነበር ማለት ነው፡፡ ዳንኤል በዚህ ዕድሜ ላይ በሚገኝበት ጊዜ ከባዱን የእልፍኝ አሽከርነት ሥራ ይሠራ ነበር ማለት ከእውነት የራቀ ነው፡፡
እንዲያውም ፋርሳዊ ቂሮስ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት ምርኮኞቹ አይሁድ ወደ ሀገራቸው ገብተውና ቤተ መቅደሳቸውን ሠርተው እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ የሚፈቅድ ዐዋጅ ባወጣላቸው ጊዜ የተወሰኑ አይሁድ ወደ ሀገራቸው ተጕዘው ኢየሩሳሌም እንደ ደረሱ፥ በሁለተኛው ዓመት የቤተ መቅደሱን ሥራ ሲጀምሩ (ዕዝራ 2፥8) ስለዚህ ጕዳይ ከፍተኛ ናፍቆት የነበረው ዳንኤል (ዳን. 9፥1-9) እስከ ፋርሳዊ ቂሮስ 3ኛ ዓመት ድረስ ወደ ሀገሩ ሳይመለስ እዚያው ከከለዳውያን ምድር መቈየቱ (ዳን. 10፥1) በእርጅናው ምክንያት ለመጓዝ ባለመቻሉ እንደ ሆነ ይገመታል፡፡

ምናልባት የተረፈ ዳንኤል ደራሲ ነቢዩ ዳንኤል ባይሆንስ? እንደዚህ ከሆነ ለትንቢተ ዳንኤል 13ኛ ምዕራፍ ሆኖ ተለጣፊ ከሚያደርግ ራሱን የቻለ ሌላ መጽሐፍ መሆን ነበረበት፡፡

የትንቢተ ዳንኤል ተረፍ ነው ቢባልም በጥንቃቄና በማስተዋል ሁለቱን እያነጻጻረ የሚያነብ ሰው ከታሪኩ ዘመንና ዕድሜ መፋለስ ሌላ፥ በቃላት አጠቃቀም፥ በቃላት አሰካክ፥ በሐረግ አስተሳሰር፥ በዐረፍተ ነገር አቈጫጨት በሐሳብ አቀነባበር ሁለቱ እንደማይገናኙ ሊረዳ ይችላል፡፡

5. ከቍ. 28 - 42 ዳንኤል ወደ አንበሶች ጕድጓድ እንደ ተጣለና እግዚአብሔር ከጕዳት እንደ ጠበቀው በዚህም ምክንያት ንጉሡ እግዚአብሔርን እንዳከበረ ይናገራል፡፡

አረማውያን ነገሥታት ከተዋሐዳቸው የመናፍስት አምልኮ አይነጹምና፥ ሊሆን ይችላል ተብሎ ከሚታለፍ በቀር፥ ከሚዶናዊው ዳርዮስ ቀጥሎ የነገሠው ፋርሳዊው ቂሮስ፥
ሀ. በኢሳ. 44፥28 “እርሱ እረኛዬ ነው፤ ኢየሩሳሌም ትታነጺያለሽ፤ ቤተ መቅደስም ይመሠረታል ብሎ ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል” ተብሎ ከ200 ዓመታት በፊት በተነገረው ትንቢት መሠረት በዚህ የታሪክ ዘመን የተነሣ፥
ለ. በነገሠ ጊዜም “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፤ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፡፡ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፥ በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፥ በኢየሩሳሌም ለሚኖረው አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሥራ” በማለት ያወጀ ንጉሥ ነውና የባቢሎናውያንን አማልክት ከልቡ ባያወጣ እንኳ የእግዚአብሔርን ታላቅነት የተረዳ ነበርና በእግዚአብሔር ተኣምር በተገደለው ዘንዶ ምክንያት ዳንኤልን ወደ አንበሳ ጉድጓድ ጣለው የተባለውን ታሪከ መቀበል ያስቸግራል፡፡

ከዚህ ቀደም ብሎ የከለዳውያንን መንግሥት ሜዶናውያንና ፋርሳውያን በመተባባር በጣሉትና ብልጦሶርን ገድለው ሥልጣነ መንግሥቱን በያዙ ጊዜ፥ ሜዶናዊው ዳርዮስና ፋርሳዊው ቂሮስ የከለዳውያንን የግዛት ይዞታ ለሁለት ተከፋፍለው ይገዙ እንደ ነበርና ዳንኤል የነበረበት ባቢሎንና ምዕራቡ ክፍል በሜዶናዊው ዳርዮስ ሲገዛ ቈይቶ ዳርዮስ ሲሞት ግን ፋርሳዊው ቂሮስ ሁሉንም በማጠቃለል እንደ ገዛው በታሪክ ይታወቃል፡፡ ሜዶናዊው ዳርዮስ በምዕራቡ ክፍል ሲገዛ በነበረበት ጊዜ ፋርሳዊው ቂሮስም በሌላው ክፍል ሲገዛ ነበርና፥ ነቢዩ ዳንኤል በዳርዮስ ዘመን በአንበሶች ጕድጓድ ተጥሎ የነበረበትንና የአንበሶችን አፍ በመዝጋት እግዚአብሔር ዳንኤልን ያዳነበትን ታሪክ፥ የተረፈ ዳንኤል ደራሲ በቂሮስ ዘመን እንደ ተደረገ አስመስሎ በድጋሚ ጽፎት ይሆናል፡፡ በዚያው ዘመን የከለዳውያንን መንግሥት ግዛት ተካፍለው ሁለቱም ሲገዙ ስለ ነበረ ስሕተቱ በቀላሉ ሊደርስ የሚችል ነው ብሎ ማለፍ ይቻላል፡፡

6. በቍ. 32-38 ዳንኤል በታሰረበት በአንበሳ ጕድጓድ እንዳለ በይሁዳ የነበረው ነቢዩ ዕንባቆም በዕርሻው ለሚሠሩ ሠራተኞቹ ምግብ ይዞ ሲሄድ በመልአክ ተወስዶ (በመነጠቅ) የያዘውን ምግብ በአንበሳ ጕድጓድ ለነበረው ለዳንኤል መስጠቱንና መመለሱን ይተርካል፡፡

“ነቢዩ ዕንባቆም” ሲል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትንቢተ ዕንባቆም በመባል የሚታወቀውን ትንቢት የተነበየውን ዕንባቆምን ማለቱ ይሆን? ወይስ በታሪካዊ ልብ ወለድ የተፈጠረ ሌላ ዕንባቆም ይሆን? የመጽሐፍ ቅዱስን ነቢዩ ዕንባቆምን ማለቱ ከሆነ ተሳስቷል፡፡

ነቢዩ ዕንባቆም በትንቢት መጽሐፉ 1፥1-4 በሀገሩ ውስጥ የነበረውን የአስተዳደር ማዛባትን፥ የፍርድ መጣመምን፥ ወንጀለኛ አጥቂ ንጹሕ ግን ተጠቂ ሆኖ በተገኙበት ጊዜ የሕግ አስከባሪውን አካል ቸልተኛነት በመመልከቱ የተበደሉትን ለመታደግ እግዚአብሔር ችላ ያለ ስለ መሰለው ማዘኑ ይነበባል፡፡

ከቍ. 5-11 ባሉት ጥቅሶች ግን ሁሉን የተመለከተ እግዚአብሔር ችላ እንዳላለ፥ ዐመፀኞችን ለመቅጣት ከለዳውያንን እንደሚያመጣና የሀገሪቱ ሀብትና ንብረት በከለዳውያን እንደሚወረስ ተናገረ፡፡ የነቢዩ ዕንባቆም ትንቢት በወንድሞቹ በኤርምያስ (5፥14-19፤ 25፥1-13፤ 27፥6-11) እና በአሞጽ (3፥11) በኩል እግዚአብሔር ከተናገረው ጋር ይስማማል፡፡ እግዚአብሔር ይሁዳን በከለዳውያን ሊቀጣ መወሰኑን የሚገልጽ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህና ሌሎች ነቢያት ሁሉ ካህናቱንም ነገሥታቱንም ተራውንም ሕዝብ ቢመክሩና ቢገሥጹም ቢያስጠነቅቁም አልተቀበሏቸውም (2ዜና. 36፥14-16)፡፡

ዕንባቆምም እንደነዚሁ ነቢያት ከለዳውያን ገና ከመምጣታቸው በፊት ይህን የከለዳውያንን መምጣት የተነበየ ነቢይ እንደ ሆነ ግልጽ ነው፡፡ የነበረበት ዘመን በትክክል አይታወቅም፤ እርሱ በነበረበት ዘመን ይገዛ የነበረው የንጉሡ ስም አልተጠቀሰምና፡፡ ሆኖም ነገሥታት፥ መሳፍንት፥ ካህናት፥ የሕዝብ አለቆች፥ ተራውም ሕዝብ ሁሉ ማንኛውም ነገር እንደ ነበረ የሚቀጥል መስሎአቸው በኀጢአት ላይ ኀጢአትን በመጨመር ድኾችንና ንጹሓንን በበደሉበት፥ አስተዳዳሪዎችና ዳኞች ኀላፊነታቸውን በዘነጉበት ዘመን በትንቢት አገልግሎት የተሰማራ ስለ ሆነ፥ “ቢነገራችሁ እንኳ እውነት ነው የማትሉትን ነገር አደርጋለሁ፤ ይደረጋል ብላችሁ ያማትጠብቁትንም ሥራ እሠራለሁ” ብሏል እያለ ነቢዩ ዕንባቆም ተናገረ፡፡ ይህ ትንቢት እየተነገረ በነበረበት ዘመን የጦርነት ወሬ እንኳ እንዳልነበረ ይጠቍማል፡፡

ለምሳሌ በኢዮስያስ ንጉሠ ይሁዳ ዘመን ግብጻውያንና አሦራውያን መካከለኛውን ምሥራቅ ለመቈጣጠርና አንዱ ሌላውን ለመግዛት ይፎካከሩ እንደ ነበረ ይታወቃል፡፡ የግብጹ ንጉሥ ኒካዑም ወደ አሦር ግዛት ዘልቆ ለመግባት እየገሠገሠ ነበር፡፡ ኤፍራጥስንም በማቋረጥ ይተምም የነበረውን ሠራዊቱን አግዶ ለማቆምና አሦር በግብጻውያን እንዳትወረር ለመርዳት ኢዮስያሰ በነገሠ በ31ኛው ዓመተ መንግሥቱ ወደ ሰሜን ዘመተ፡፡ በሚግዶልም ከግብጻውያን ጋር ተዋጉና ኢዮስያስ በጦርነቱ ተገደለ፡፡ የይሁዳ ሕዝብ የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን ቢያነግሡትም ኒካዑ ለበቀል ፊቱን ወደ ደቡብ በመመለስ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ መጣና ኢዮአክስን በነገሠ በ3ኛው ወር ከሥልጣን አወረደና በእስረኛነት ወደ ግብጽ ላከው፡፡ በእርሱ ፋንታም ወንድሙን ኤልያቄምን አንግሦ ስሙን ኢዮአቄም አለው፡፡ ይሁዳን የግብጽ ገባር አደረጋት ማለት ነው (2ነገ. 23፥28-35፤ 2ዜና. 36፥1-4)፡፡

ከዚህ ቀደም ብሎ ኀይል እየተሰማው የመጣው የባቢሎን መንግሥት ሠራዊትም ኢዮአቄም በነገሠ በ3ኛው ዓመት እስከ ኢየሩሳሌም በመዝለቅ ይሁዳን ከግብጻውያን አገዛዝ አስለቀቀና የባቢሎን ቅኝ ግዛት አደረጋት (2ነገ. 24፥1-2፤ ዳን. 1፥1)፡፡

ከኢዮስያስ ዘመን ጀምሮ የጦርነት ወሬ ከሰሜንም ከደቡብም በኋላም ከምሥራቅ ይነፍስ ስለ ነበረ፥ “ቢተረክላችሁ የማታምኑትን የከለዳውያኑን ጦር አመጣባችኋለሁ” ሲል ዕንባቆም ትንቢት ባልተናገረ ነበር፡፡ ከኢዮስያስ ጀምሮ ያለው ዘመን ቢታሰብ የኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት 31 ዓመት የኢዮአክስንና የዮአኪንን የግዛት ዘመን (6 ወራት በመተው) የኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት ቢቈጠር 11 ዓመት፥ የሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት 11 ዓመት በኤርምያስ ትንቢት መሠረት ሰባው የምርኮ ጊዜ ዐልቆ አይሁድ ወዳገራቸው እንዲገቡ በታወጀበት በቂሮስ 1ኛ ዓመት ነቢዩ ዳንኤል ወደ አንበሳ ጕድጓድ መጣሉ በተረፈ ዳንኤል ስለ ተነገረ 70 ዓመት፥ ድምር 123 ዓመት፡፡

በዚህ ጊዜ ዕንባቆም በዕርሻ ውስጥ ለሚሠሩ ሙያተኞች ምግብ ይዞ ወደ ምድረ በዳ ለመሄድ ቻለን? እውነትም መጽሐፉ ተረፍ፤ ከተረፍም ተረፍ እንደ ሆነ ተረጋግጧል፡፡ ትራፊውንም ለሌሎች ትተን ዋናውን አጥብቀን እንያዝ፡፡

በጮራ ቍጥር 6 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment