በማስተዋል ዐብራችሁ ኑሩ
የይሥሐቅን የጋብቻ ሁኔታ ለማየትና ከዚህ ጋብቻ ልንማረው የሚገባንን ትምህርት ለመገንዘብ በቅድሚያ ይሥሐቅ
ጠንካራ ሥነ ምግባርና እምነት ከነበረው ከአብርሃም የተወለደ ልጅ መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ይሥሐቅ የተወለደው አብራሃም በሸመገለበት
ጊዜና እምነቱ በከፍተኛ ደረጃ ከተፈተነ በኋላ ነው፡፡ “የምትወደውን አንድ ልጅህን ይሥሐቅን ይዘህ … ሂድ” ይህ ቃል አብርሃም
አንድ ልጁን ይሥሐቅን በመሥዋዕትነት እንዲያቀርብ እግዚአብሔር ለአብርሃም የተናገረው እጅግ ፈታኝ የሆነ ቃል ነው፡፡
ይኸውም አብርሃም ለይሥሐቅ የነበረውን የተለየ ፍቅር እግዚአብሔር ራሱ ያውቀው ስለ ነበረ የመሥዋዕትነቱ ጥሪ
የቀረበው አባትና ልጅ የነበራቸው ጥልቅ ፍቅር ከግምት ውስጥ ገብቶ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ የይሥሐቅን ሕይወት በሚመለከት ከተመዘገቡት
ሁለት ጠቃሚ ታሪካዊ ድርጊቶች ውስጥ በተለይ በእግዚአብሔር ፈቃድና በአብርሃም አነሣሽነት መሥዋዕት ለመሆን ወደ መሠዊያው ቦታ ያለምንም
ተቃውሞ መሄድ መቻሉና የሚያገባትን ሚስት ፍልጎ በማግኘቱ ረገድ የታየው ሁኔታ ይሥሐቅም በበኩሉ ለአባቱ ለአብርሃም እጅግ ታማኝና
ታዛዥ እንደ ነበረ ያሳያል፡፡
የአብርሃም ወንድም የናኮር ልጅ ከሆነችው ከርብቃ ጋር ይሥሐቅ መጋባት መቻሉ በእግዚአብሔር አጋዥነት እንደ
ሆነ የአብርሃም ሎሌ ኤሊዔዘር የጌታውን የአብርሃምን ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ካራን በሚጓዝበት ጊዜ ትክክለኛዋን ሚስት ፈልጎ ለማግኘት
እግዚአብሔር በአስደናቂ ሁኔታ ከሰጠው ምሪት አኳያ በግልጽ ይታያል፡፡ ይህ ታሪክ በዘፍጥረት 24 ላይ በሚገባ ተጠቅሷል፡፡ የአብርሃም
“ዘር” በመባል የሚታወቀው የተስፋ ልጁ ከአሕዛብ ሚስት ከማግባት መቈጠብ ይኖርበታል የሚለው መመሪያ የአብርሃምን ከፍተኛ ምኞትና
ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት እግዚአብሔር ከራሱ ከአብርሃም ቤተ ሰብ ውስጥ ለይሥሐቅ ሚስት በመስጠት የአብርሃምን
ምኞት እውን አደረገ፡፡ ይህ አጋጣሚ በአሁኑ ጊዜ የራሱ ተሳትፎ ሳይታከልበት በሌሎች ሰዎች ጥረት ብቻ የሚቀናጅ ጋብቻ ሊሠምር እንደማይችል
ለሚያስቡት ሁሉ ትልቅ መደፋፈርን የሚሰጥ ነው፡፡ እግዚአብሔር እያንዳንዱን ሁኔታ መቈጣጠርና ማስተካከል የሚችል አምላክ ነው፡፡
ለአማኞች ደግሞ በተለይ ለሚወዱትና እንደ ሐሳቡም ለተጠሩት ሕይወት ስኬታማነት እግዚአብሔር መልካም ሥራ ከሚሠራበት “ነገር ሁሉ”
ከተባለው ውስጥ ይህ ሁኔታ እንደሚያጋጥም ሊያውቁ ይችላሉ (ሮሜ 8፥28)፡፡
በዚህ ብኩን ዓለም ውስጥ እስከ ኖርን ድረስ በማንኛውም የጋብቻ ሕይወት ውስጥ ሁል ጊዜ ድክመትም ሆነ ጥንካሬ
ይኖራል፡፡ ጥንካሬዎቹ ለእግዚአብሔር ታላቅ ምስጋና ከማቅረብ የሚመነጩ ናቸው፡፡ ጋብቻ ከብስለት ደረጃ ላይ እንዲደርስና ጠንካራ
መሠረት እንዲይዝ ከተፈለገ ድክመቶች በፍጥነት ታውቀው ሊወገዱ ይገባል፡፡
የይሥሐቅና የርብቃ ታላቅ የጥንካሬ ምንጭ የአብርሃምና የሣራ የጽኑ እምነት ጸሎት መልስ በመሆኑ እነርሱን አንድ
ለማድረግ የሠራች ንጽሕት የእግዚአብሔር እጅ ናት፡፡ ይሁን እንጂ ክርስቲያን ተጋቢዎች ሁሉ የጋብቻቸውን ሁኔታ በመመርመር በኩል
ትኵረት ሊያደርጉባቸው የሚገባ ሁለት ድክመቶች እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡
ዕድገት እንዲሁ ብቻውን አይገኝም
1.
በአንድ በኩል ለይሥሐቅ ትክክለኛውን ሚስት ለመምረጥ አብርሃምንና ሎሌውን
ኤሊኤዘርን በመምራት እግዚአብሔር የሰጠውን አስደናቂ አመራር በግልጽ ስናይ በሌላ በኩል ይሥሐቅ በኑሮው ውስጥ ርብቃን “አሸንፎ
የማያውቅ” መሆኑን እንዲሁ ሳንጠቅሰው የሚታለፍ ጕዳይ አይደለም፡፡ በዚህ የተነሣ ይሥሐቅ በቤተ ሰቡ ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን የአመራር
ሚና ለመያዝ ችግር ያጋጠመው ይመስላል፡፡ ይህንኑ ችግር በወቅቱ ከመገንዘብና ከማስወገድ ርቆ ይሥሐቅ በዚህ ዋነኛ ድክመቱ በመቀጠል
በሕይወቱ ውስጥ እጅግ ጕልሕ ከሆኑት ሁኔታዎች መካከል ማለትም በሚስቱ በርብቃ ሙሉ ቍጥጥር ሥር እስኪሆንና በትንሹ ልጅ በያዕቆብ
ለመታለል እስኪበቃ ድረስ ሁኔታዎች ሁሉ እየተባባሱ እንዲሄዱ አደረገ፡፡ የዚህ አሳዛኝ ታሪክ ውጤት በዘፍጥረት 27 ላይ ተጠቅሶ
ይገኛል፡፡ ይሥሐቅ አባቱ አብርሃም በቤተ ሰቡ ውስጥ የነበረውን የመሪነት ስፍራ ለመያዝ ባልቻለበት ወቅት በጋብቻ ሕይወቱ ውስጥ
ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ለተወሰኑ ዓመታት ዐብሮት ያደገው የእስማኤል ሁኔታ ሊያስታውሰው በተገባ ነበር፡፡ አብርሃምን በተመለከተ
ይህ የአመራር ድክመት ለተወሰነ ጊዜ የታየ ድክመት ነበረ፡፡ ከይሥሐቅ ጋር ግን ይህ ዐይነቱ ድክመት ቋሚ ባሕርይ ለመሆን እስኪበቃ
ድረስ ለረዥም ጊዜ ዐብሮት ቈይቷል፡፡ በይሥሐቅ በኩል በእግዚአብሔር የተሰጠውን አመራር መለማመድ ያለመቻል ርብቃ ከእርሱ ቍጥጥርና
ትእዛዝ ውጭ መሆንን በበለጠ እየተለማመደች ቈይታ በመጨረሻ ሁኔውን በቤተ ሰቡ ውስጥ ግጭት እንዲፈጠርና ሰላም እንዲጠፋ አድርጓል፡፡
ለአንድ ክርስቲያን መሪ ዐይነተኛ ባሕርያት ከሆኑት መካከል አንደኛው በሐዋርያው
ጳውሎስ እንደ ተጠቀሰው “ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፥ ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር
ባያውቅ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃል?” (1ጢሞ. 3፥4-5)፡፡ በዚህ መሠረት ቤተ ሰብን እንደ እግዚአብሔር
ፈቃድ በመልካም ሁኔታ መምራት መሠረታዊ ትምህርትና የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል የሚያስችል ብቃት የሚገኝበት ታላቅ መሰናዶ
ነው፡፡
ከመመካከርና
ከመግባባት ውጭ ጥሩ የጋብቻ ቅንጅት መኖር አይችልም
2.
የይሥሐቅና የርብቃ የውስጥ ችግሮች በሕይወታቸው ወስጥ እያደር ግልጽ እየሆኑ
የመጡት የሁለተኛው ድክመት ማለትም መግባባት ያለመቻላቸው ውጤት ሊሆን ይችላል፡፡ በመጀመሪያ የጋብቻ ሕይወታቸው ወቅት የታዩ ሁኔታዎች
ጤናማዎችና የሚያደፋፍሩ ይመስሉ ነበር፡፡ ርብቃ ለይሥሐቅ ሚስቱ ስትሆን ይሥሐቅ እንደ ወደዳትና (ዘፍ. 24፥66) በተለይ ከእናቱ
ከሣራ ሞት በኋላ በታላቅ ምቾት ላይ እንደ ነበረ እንረዳለን፡፡ ጊዜ እያለፈ ሲሄድና ርብቃም ያለ ልጅ ስትቈይ ይሥሐቅ ስለ እርሷ
ጸለየ፤ ጌታም ለጸሎቱ ምላሽ ሰጠ (25፥21)፡፡ ነገር ግን በእርግዝናዋ ወቅት በማሕፀኗ ውስጥ የመታወክ ስሜት እየተሰማት ስትሄድ
የገጠማትን ችግር ከይሥሐቅ ጋር በመመካከርና ለመፍትሔው ወደ ጌታ በአንድነት በመቅረብ ፈንታ በራሷ ፍላጎት ስለ ገጠማት ችግር እግዚአብሔርን
ለመጠየቅ ብቻዋን ሄደች፤ ከዚያ ሁለት ልጆች ከእርሷ እንደሚወለዱና ታላቁ ታናሹን አንድ ቀን እንደሚያገለግለው የተገነዘበችበትን
ጠቃሚ መረጃ አገኘች፡፡ ርብቃ በእንደዚህ ዐይነቱ ትንቢት ላይ ምናልባት ከባሏ ጋር ተወያይታበት ይሆናል ብሎ ያለ መገመት አስቸጋሪ
ነው፡፡ ነገር ግን ይህን በርግጥ ስለ ማድረጓ የምናቀው የለም፡፡ የእርሷ ምርጫ ታናሹን የእርሱ ደግሞ ታላቁን ልጅ የሚመለከት ስለ ነበረ በይሥሐቅና በእርሷ
መካከል ጤናማ ያልሆነ የውድድር መንፈስ ሰፍኖ ታይቷል፡፡ ስለዚህ በግንኙነታቸው ተቀራርበውና ተፋቅረው መኖር የሚገባቸው ልጆቻቸው
ቤተ ሰቡን መለያየት ጀመሩ፡፡ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን በረከት ለተከታዩ ትውልድ የማስተላለፊያው ጊዜ ሲደርስ ይሥሐቅንና ርብቃን
ማግባባት ያላስቻላቸው ድክመት የመጨረሻ ውጤት በይበልጥ ገሃድ ሆነ፡፡ ይሥሐቅና ርብቃ በዚህ ጠቃሚ ጕዳይ ላይ ለምን በጋራ አልተወያዩበትም?
ለምንስ ዐብረው አልጸለዩበትም? ይህን በሚመለከት ከብዙ ዓመታት በፊት ስለ ተሰጠውስ የእግዚአብሔር ቃል አንዱ ለአንዱ ለምን አላስታወሰም?
ከዚህ በላይ በጥያቄ መልክ የቀረቡትን ሐሳቦች በተግባር ፈጽመው ይሥሐቅና ርብቃ ለእግዚአብሔር ፈቃድ በአንድነት በመታዘዝ እውነተኛ
ቅንጅት ያላቸው ባልና ሚስት መሆን ይችሉ ነበር፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ተቀብለው እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ መፈጸም እንዲችሉ
ልጆቻቸውንም ለመርዳት ይበቁ ነበር፡፡
ለክርስቲያን ባሎችና ሚስቶች እርስ በእርስ ተግባብቶ መኖርን መማር እጅግ
አስፈላጊ ነው፡፡ እርስ በእርስ ለመደማመጥ በተለይም የጓደኛን ሐሳብ ተስፋ፥ ፍርሀትና ጭንቀት መካፈል ጊዜን የሚጠይቅ ጕዳይ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ አንድ የትዳር ጓደኛ ከእግዚአብሔር ጠቃሚ የሆነ ነገር እንደ ተነገረው ሲረዳና ሲያምን ስለዚህ ሁኔታ ከኑሮ
ጓደኛው ጋር ሐሳብ ለሐሳብ መለዋወጥ ይኖርበታል፡፡ ክርስቲያን ሚስቶች በጸሎት ሕይወታቸው ከባሎቻቸው የተለዩ እንዳይሆኑ ከርብቃ
ሁኔታ ይማሩ፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ ዐይነቱ አዝማሚያ በሌሎች የሕይወት ክፍሎች ውስጥም አድጎ በመጨረሻ ወደ አለመታዘዝ ስሜት ሊያመራ
የሚችል ነውና፡፡ ክርስቲያን ባሎችም ቤተ ሰባዊ አመራርን ስለ መቀበልና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ቤተ ሰብን ስለ መምራት አስፈላጊነት
ከይሥሐቅ ይማሩ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ምሪትና መልካም አስተዳደር ያለው ቤተ ሰብ እግዚአብሔር የሚከብርበት ታላቅ ቤተ
ሰብ ነው፡፡ ይህ ዐይነቱ ቤተ ሰብ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎቱና በአካባቢው ለሚኖሩ ጎረቤቶቹ በሚሰጠው ምስክርነት ውጤታማ ነው፡፡
“በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፡፡” (ፊል. 2፥15)፡፡
(በጮራ ቊጥር 6 ላይ የቀረበ)
No comments:
Post a Comment