Monday, April 1, 2013

ክርስትና በኢትዮጵያ


የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ
 ከነቅዐ ጥበብ
ካለፈው የቀጠለ

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የተገኘውን ድኅነትና በትንሣኤው የተጨበጠውን ጽድቅ የሚያበሥረውን ወንጌል በኢየሩሳሌም በይሁዳ በሰማርያ በዓለሙ ሁሉም እንዲያሠራጩ ኀላፊነት የተሰጣቸውና ራሳቸውንም ለዚሁ ሥራ የለዩ ዐሥራ አንድ ሐዋርያትና (ይሁዳ ተቀንሶ) ጥቂት ተባባሪዎች ነበሩ (ሉቃ. 24፥33-34) ከሐዋርያት ጋር የተባበሩ ናቸው ከሚባሉትም መካከል 70 ደቀ መዛሙርት ከፍተኛውን ቍጥር ሳይዙ አይቀሩም (ሉቃ. 10፥1)፡፡ እንደዚሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከርኩሳን መናፍስት አገዛዝ ነጻ ያወጣቸው የኀጢአትን ስርየት የሰጣቸው፥ ያደረጋቸውን ተኣምራትና መንክራት በማሳየትና በነቢያት ትንቢት መሠረት ዓለምን ሊያድን የመጣ መሲሕ (ክርስቶስ) እንደ ሆነ ከስብከቱ፥ ከሥራውና ከአኗኗሩ በመረዳት እያገለገሉት ከገሊላ ጀምሮ ይከተሉት የነበሩት ሴቶች ታክለውበት (ማቴ. 27፥55-56፤ ማር. 16፥9-11፤ ሉቃ. 7፥36-50፤ 24፥22-24) የጌታ የኢየሱስ እናትም ተጨምራ የሐዋርያቱንና የተባባሪዎቹን ቍጥር ወደ 120 አድርሰውት ነበር (ሐ.ሥ. 1፥8-15)፡፡
  
“ከኢየሱስ ጋር የነበሩ” በመባል ለሚታወቁት ተከታዮቹ በሥጋና በደም ሊሠራ የማይቻለውን የታላቁን ተልእኮ ኀላፊነት ይወጡ ዘንድ የሚመራቸውን፥ የሚያጽናናቸውን፥ በውስጣቸውና ከእነርሱ ጋር ሆኖ እውነትን ሁሉ በማሳወቅ የሚያሳድጋቸውን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ጌታ በኀምሳኛው ቀን አፈሰሰላቸው (ዮሐ. 14፥16፤ 17፥26 ሐ.ሥ. 2፥1-4)፡፡ ከዚህ በኋላ በሕይወትና በቃል የሰጡት ምስክርነት የጌታን ቃልም በማስተዋልና ለሰሚዎች በማስተላለፍ የታየባቸው ለውጥ ራሱ ተአምር እንደ ነበረ በሐዋርያት ሥራ በግልጥ የሚነበብ ታሪክ ነው (ሐ.ሥ 4፥13)፡፡


ከበዓለ ኀምሳ ጀምሮም በኢየሩሳሌም ውስጥ በሐዋርያት ዙሪያ ተከማችተው የነበሩትን ምእመናን የዕለት ተዕለት አስተዳደራዊ አገልግሎት እንዲከታተሉ ከተመረጡት ሰባት ዲያቆናት መካከል አንደኛው ፊልጰስ ነበረ (ሐ.ሥ. 6፥1-6)፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ሰው ከተመረጠበት አገልግሎት በተጨማሪ ከቤተ ሰቡ ጋር ወንጌል በማዳረስ የታወቀ አገልጋይ ነበረ (ሐ.ሥ. 21፥8-9)፡፡ በዚህም አገልግሎቱ በሰማርያ፥ ወንጌል በመስበክ ባከናወነው አገልግሎቱ ሳምራውያን የናዝሬቱ ኢየሱስ እየተባለ የተጠራው ራሱ ክርስቶስ (በነቢያት ትንቢት መሠረት የተጠበቀው መሲሕ) እንደ ሆነ አምነው ስለ ነበረ፥ ወሬውም በኢየሩሳሌም ወደ ነበሩት ሐዋርያት ዘንድ ደርሶ ስለ ነበረ፥ ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ሰማርያ ሄደው ሁኔታውን እንዲከታተሉት ተልከው ነበር፡፡ እነርሱም የሰማርያውን አገልግሎት አጠናቀው ከፊልጶስ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፡፡ ፊልጶስ ግን ለተለየ አገልግሎት ወደ ጋዛ እንዲወርድ የጌታ መልአክ ነገረው፡፡ ይህ በሆነበት ጊዜ ሕንደኬ ለተባለችው የኢትዮጵያ ንግሥት ባለሙሉ ሥልጣን ሚኒስትር የሆነ ሰው በኢየሩሳሌም ሥርዐተ አምልኮ አድርሶ በጋዛ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ  ላይ ነበረ፤ ኢትዮጵያዊው ባለሥልጣን በዘሩ ይሁዳዊ የነበረ ወይም በዘሩ ኢትዮጵያዊ ሆኖ በትምህርት ይሁዳዊነትን የተቀበለ መሆኑ አይታወቅም፡፡ እንዲሁም እስራኤላውያን ሁሉ በኢየሩሳሌም እየተገኙ እንዲያከብሯቸው በብሉይ ኪዳን ከታዘዙት 3 ዐበይት በዓላት በየትኛው በዓል ኢትዮጵያዊው ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ መመለሱ አልተገለጸም (ዘዳ. 16፥1-16)፡፡ ነገር ግን በመንገድ ላይ በሠረገላ እየተጓዘ ሳለ ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 53ን ያነብ እንደ ነበረ ተተርኳል፡፡

ፊልጶስም ኢትዮጵያዊው ዘንድ እንደ ደረሰ እንዲያነጋግረው በመንፈስ ቅዱስ ታዘዘ፡፡ ስለዚህም ይህን የምታነበውን ልታስተውለው ችለሃልን? አለና ፊልጶስ ንግግሩን ከፈተ፡፡ ኢትዮጵያዊው ግን ያለ አስተማሪ ሊረዳው እንደማይችል ገልጾ ወደ ሠረገላው እንዲወጣና እንዲያብራራለት ጋበዘው፡፡ ፊልጶስም የተነበበውን  የትንቢተ ኢሳይያስን ክፍል እንዳብራራለትና ውሃ ዘንድ ሲደርሱ ኢትዮጵያዊው “እነሆ ውሃ ከዚህ አለ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር ይኖራል” ብሎ እንደ ጠየቀ፥ ፊልጶስም ካመንህ ልትጠመቅ ተፈቅዷል ሲል እንደ መለሰለትና እንዳጠመቀው ከተተረከ በኋላ፥ ፊልጶስ በመነጠቅ ወደ ሌላ ስፍራ ሲሄድ ኢትዮጵያዊውም እየተደሰተ ወደ ሀገሩ እንደ ተጓዘ በመጻፍ የታሪኩ ክፍል ይደመደማል (ሐ.ሥ. 8፥5-40)፡፡ ከዚህ ታሪክ ባለፈው ዕትም ቀንጨብ አድርገን ሳናብራራ ያለፍናቸውን ጥቂት ነጥቦች አከል ማድረግ አስፈላጊ መስሎ ታይቶናል፡፡

በምሕረቱ ባለጠጋ የሆነ እግዚአብሔር ያሰበንና የጐበኘን፥ ወንጌል በምድረ እስራኤል ገና በሙሉ ባልተዳረሰበት ጊዜ መሆኑን አውስተን ነበር፡፡ በሰማርያ ወንጌልን ሲሰብክ የቈየው ፊልጶስ ከጴጥሮስና ከዮሐንስ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ተመለሰ ወደ ጋዛ ሄዶ ኢትዮጵያዊውን እንዲገናኘው ታዘዘ፡፡ ሰማርያ በይሁዳና በገሊላ መካከል ያለ የተደባለቀና የተካለሰ ሕዝብ ይኖርበት የነበረ አገር ሲሆን፥ እግዚአብሔር ባቀደው ጊዜ ከብዙ የዓለም ሕዝቦች በፊት ይህ ዕድል ስለ ተሰጠን የእግዚአብሔርን ውለታ መዘንጋት እንደማይገባን በማስታወስ የዚህን የኑብያን ኢትዮጵያ ክርስትና ታሪክ ዘግተን ዐልፈን ነበር፡፡

ፊልጶስ ወደ ኢትዮጵያዊው ሠረገላ ከወጣ በኋላ ከትንቢተ ኢሳይያስ 53 በመነሣት፥ ለምን ያህል ጊዜ ኢትዮጵያዊውን ሲያስተምረው እንደ ቈየ ባናውቅም በሰዓታት፥ ምናልባትም በቀናት ለሚቈጠር ጊዜ እያስተማረው አብሮት ሳይቈይ እንዳልቀረ እንድንገምት የሚያሳስቡን ነጥቦች በታሪኩ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ያነበው ከነበረው መጽሐፍ ጀምሮ ወንጌልን ሰበከለት የሚለውና (ቍ. 35) ኢትዮጵያዊውም “ውሃ ከዚህ አለ ብጠመቅስ” በማለት ራሱ እንደ ጠየቀ የሚናገረው መግለጫ (ቍ. 36) ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊው ይህ ቀረው የማይባል ሙሉ የወንጌል ትምህርትን እንዳስተማረው ያመለክተናል በዚህም መሠረት፡-

1.     እግዚአብሔር ኀጢአተኛውን ሰው ያድን ዘንድ ልጁን መሲሕ አድርጎ ለመላክ የነበረውን ዕቅዱን ከነ ምክንያቱ (መዝ. 39/40፥5-7)
2.    በመደጋገምና በማብራራት በተለያየ መንገድና ስልት በነቢያት በኩል እግዚአብሔር ስለ መሲሕ መገለጥ ሲያስተላልፍ የነበረውን ትንቢታዊ መልእክት (ሐ.ሥ. 3፥17-26)
3.    ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ወልድ ከድንግል በመፀነስና በመወለድ ሰው ሆኖ እንደ ተገለጸ፥ በ30ኛው ዓመት እንደ ተጠመቀ የመረጣቸውን ሐዋርያትና ደቀ መዛሙርት አስከትሎ በመዘዋወር እያስተማረ፥ ድንቅ ሥራዎችንም እያደረገ ለ3 ዓመታት ያህል የእግዚአብሔር ልጅነቱንና የሚጠበቀው መሲሕነቱን እንደ ገለጠ (ሐ.ሥ 2፥22)
4.    ጊዜውም ሲደርስ የሰውን ኀጢአት ተሸክሞ መሞቱን መነሣቱንና ማረጉን የዳግም ምጽአቱንም ተስፋ መስበኩን (ሐ.ሥ. 1፥1-5፡11)
5.    ተግተው ይጠብቁ ለነበሩ መቶ ሃያ የማኅበር አባላትና ቀጥሎም በእነዚህ ምስክርነት ላመኑት ሁሉ በኢዩኤል ትንቢት መሠረት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን በልግስና ማፍሰሱን (ሐ.ሥ. 2፥1-4፡39)፡፡
6.    ዛሬም የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ የተሠዋለት መሆኑን ለሚያምን ሁሉ የኀጢአት ስርየት ይሰጥ ዘንድ የወንጌል የአገልግሎት መስፋፋት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን (ሐ.ሥ. 5፥30-32)
7.    ሰማይንና ምድርን እንዲያገናኝ እግዚአብሔር በመለኮታዊ ጥበቡ የዘረጋው መሰላል (ሰዋሰው ዘይብጽሕ እምድር እስከ ሰማይ ዘፍ. 28፥10-17፤ ዮሐ. 1፥52) እግዚአብሔር ሰው (እግዚአብሔርና ሰው የሆነው) ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፥ እርሱ በኀጢአት ምክንያት የተለያዩትን እግዚአብሔርንና ሰውን በፍጹምነትና ለዘላለም ለማስታረቅና ለማነጋናኘት የቻለ ብቸኛ ሊቀ ካህናት (አስታራቂ) መሆኑን (ኤፌ. 2፥14-18፤ ዕብ. 10፥11-14) በእርሱ በኩልም ካልሆነ በቀር ሰው ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብበት የስርቆሽ በር አለመኖሩን (ዮሐ. 14፥6፤ 10፥9)፡፡
8.    ያመነ ሰው ሁሉ ወደ ምእመናን ኅብረት ለመጨመርና ለመተባበር ሕያው ቃሉ የሚያበሥረውን በረከትም ሁሉ በእምነት ለመቀበልና ለመታዘዝ በአብ፥ በወልድና በመንፈስ ቅደስ ስም መጠመቅ እንዳለበት (ማቴ. 28፥19-20፤ ዮሐ. 3፥5) ይህንና የመሳሰለውን ለክርስትና መሠረት የሆነውን ትምህርት ወንጌላዊ ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊው ሳያስተምረው እንዳልቀረ ይታመናል፡፡ ከዚህ የተነሣ ሁለቱም በሠረገላ እየተጓዙ በውይይት ላይ እንደ ነበሩ ውሃ ዘንድ ሲደርሱ ውሃ ከዚህ አለና ብጠመቅስ? የሚለውን ጥያቄ ኢትዮጵያዊው አነሣ፡፡ ይህንም ለማለት ያበቃው ፊልጶስ ስለ ጥምቀት አስፈላጊነት ጭምር አስተምሮት ከነበረውና በእምነት ከተቀበለው ትምህርት በመገፋፋት ነው ብሎ ለማሰብና ለመቀበል አመቺነት አለው፡፡

እንግዲህ በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ በሚል ስም የሚጠሩት ኑብያና ሳባ መሆናቸውን ጠቍመን፥ በዚህ በሐዋርያት ሥራ 8 እንደ ተገጸው ክርስትናን ተቀብሎ ወደ ሀገሩ የተመለሰው ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን የኑብያ ኢትዮጵያዊ እንጂ የሳባ ኢትዮጵያ ዜጋ እንዳልነበረ የኢትዮጵያን ታሪክ ተመራምረውና አበጥረው ከጻፉት የታሪክ ሊቃውንት የቀረበውን መሠረት በማድረግ በኑብያ ኢትዮጵያ በ56 ዓ.ም. በወንጌላዊ ፊልጶስ በመንገድ ላይ የተሰበከው ክርስትናና የፊልጶስ ደቀ መዝሙር በሆነው ኢትዮጵያዊ ተቋቋመ ተብሎ የሚታሰበው የኑብያ ማኅበረ ምእመናን (ቤተ ክርስቲያን) እስከ 1100 ዓ.ም. ድረስ ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ጋር እየተገናኙ ጸንተው መቈየታቸውን ባለፈው ዕትም ተርከን ነበር፡፡

በሳባ ኢትዮጵያም ቢሆን በእግዚአብሔር የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ ሰላማና ከሣቴ ብርሃን በሚል የግብር መግለጫ በስሙ ላይ ተጨምሮበት በሚጠራው በፍሬምናጦስ ስብከት የበራው የወንጌል ብርሃን በሳባ ኢትዮጵያ በጣዖታትና በመናፍስት አምልኮ ሰፍኖ የነበረውን ጨለማ አስወግዶታል፡፡ የወንጌል ብርሃን በፍሬምናጦስ ስብከት ወደ ሳባ ኢትዮጵያ ስለ መግባቱ ባለፈው ዕትም የቀረበውን መግቢያ አንባቢ ያስታውሰዋል፡፡

ፍሬምናጦስ ማነው
ወንጌል በኢትዮጵያ የተሰበከበትና ሕዝቧ ክርስቲያን የሆኑበት ታሪክ ሲወሳ፥ የሰላማ ወይም የከሣቴ ብርሃን ስም ሁሉ ጊዜ ዐብሮ መነሣቱ አይቀርም፡፡ የምክንያቱንም መነሻ አብዛኛው ክርስቲያን ይረዳዋል፡፡ የዚህ ሰው መጠሪያ ፍሬምናጦስ እንደ ነበረና ከአባቱና ከወንድሙ ጋር እንዴት ወደ ኢትዮጵያ እንደ ገቡ ታሪከ ኢትዮጵያን የጻፉ ሁሉ አብራርተውታልና፡፡

በ300 ዓ.ም. አካባቢ ሜሮጵዮስ በሚል ስም የተጠራ ግሪካዊ ነጋዴ ቀደም ብሎም ሆነ በዘመኑ በግሪካዊያንና በሳባ ኢትዮጵያውያን መካከል ተፈጥሮና ጸንቶ በቈየው ግንኙነት መሠረት ለንግድ ሥራ ወደ ኢትዮጵያ የባሕር ዳርቻ እንደ ደረሰ ይተረካል፡፡ ግሪካዊውን ነጋዴ ሽፍቶች ሲገድሉት እርሱን ተከትለው የመጡትን ልጆቹን ወይም የዘመዱን ልጆች የጠረፍ ጠባቂዎች ደርሰው ከመገደል አተረፏቸውና ለአካባቢው አስተዳዳሪ አቀረቡአቸው፡፡ አስተዳዳሪውም በበኩሉ ወደ አክሱም አምጥቶ ለንጉሡ ለአልዓሜዳ አስረከባቸው፡፡ የልጆቹ ስም የታላቁ ኤዲስዩስ ወይም ሲድራኮስ የሁለተኛው ፍሬምናጦስ ነበረ፡፡

ኤዲስዩስና ፍሬምናጦስ ወጣቶች ቢሆኑም የተወለዱባትና ያደጉባት አገር ግሪክ እንደ መሆኗ መጠን ግሪክ በዘመኑ የደረሰችበትን ዓለማዊ ዕውቀት የተማሩና ለክርስትና መሠረት የሆኑትን ቅዱሳት መጻሕፍትን በጥልቀት ያጠኑ ሆነው በመገኘታቸው በአክሱም ቤተ መንግሥት እንደ ደረሱ ወዲያው በሥራ ላይ ተመደቡ፡፡ እነዚህ ግሪካውያን ወጣቶች  በአክሱም ቤተ መንግሥት በሥራ ላይ መመደባቸው ሲታይ፥ የአክሱም ሥልጣኔ ቀድሞውንም ከግሪካዊው ሥልጣኔ ጋር ዝምድና የነበረው ለመሆኑ ፍንጭ ይሰጣል፡፡ በዚህ ጊዜም ሆነ ቀደም ብሎ በሐውልቶችና በገንዘቦች ላይ ተቀርጾ የነበረ ነው የሚባለው ምስልና ፊደልም የዚህኑ እውነተኛነት የሚረጋግጥ ነው የሚሉ አሉ፡፡

ኤዲስዩስ በአክሱም ቤተ መንግሥት የግቢው አዛዥ ሲሆን፥ ፍሬምናጦስ ግን ለንጉሡ ልጆች የሞግዚትነትና አስተማሪነት ሥራ ተሰጠው፡፡ ንጉሡ አልዓሜዳ በሞተ ጊዜም ልጆቹ አድገው በትረ ሥልጣኑን ለመረከብ እስኪበቁ ድረስ ንግሥት አሕየዋ (ሶፍያ) መንግሥቱን ስታስተዳድር ቈየች፡፡ በዚህ ጊዜ የኤዴስዩስና የፍሬምናጦስ ታላቁ ተልእኮ ለንጉሡ ልጆች ዒዛናና ሳይዘናስ ለቤተ መንግሥቱ ባለሥጣኖች፥ ለአክሱምና አካባቢውም ሕዝብ ወንጌልን በመስበክ ሰዎችን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መመለስ ነበር፡፡ ለንግሥት አሕየዋም ከወንጌል ትምህርት ሌላ በመንግሥት አስተዳደር ምክር ሳይለግሱዋት እንዳልቀረ ይታሰባል፡፡ ኤዲስዩስና ፍሬምናጦስ በምስክርነታቸው አይሁድንና አረማውያንን ባንድነት ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን ወደሚገኘው ድኅነትና ዘላለማዊ ሕይወት፥ ከሰይጣን ባርነት ወደ እግዚአብሔር የነጻነት መንግሥት አፈለሷቸው፡፡ እንኳ ከባዕድ ሀገር ለመጣ ስደተኛ ቀርቶ ለሀገር ተወላጅም ቢሆን አስቸጋሪና ከባድ የሆነውን ሥራ በማከናወናቸው በኢትዮጵያ ለተቋቋመው የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ ባለውለታዎች ናቸው፡፡

ዒዛናና ሳይዘናስ ሥልጣነ መንግሥቱን ለመረከብ ከሚያስችለው ዕድሜ ሲደርሱ ዙፋኑን ተረከቡ፡፡ ኤዲስዩስና ፍሬምናጦስም ስንብት ጠይቀው ስለ ተፈቀደላቸው ወደ ሀገራቸው ሊገቡ ጕዞ ጀመሩ፡፡ ኤዲስዩስ በቀጥታ ወደ ሀገሩ ለመመለስ ሲወስን ፍሬምናጦስ ግን በኢትዮጵያ የጀመረውን የወንጌል አገልግሎት ያለ ተተኪ ትቶ መሄዱ ስለ ከበደው ለኢትዮጵያ ቅርብ የሆነችው የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን እንድትከታተለው ወይም ወንጌላዊ እንድትልክ ለማሳሰብ ወስኖ ከወንድሙ ከኤዲስዩስ ተለየ፡፡ እስክንድርያ በደረሰ ጊዜም ሊቀ ጳጳሱን ማለት እለእስክንድሮስን የተካው አትናቴዎስን አገኘው፡፡ ሊቀ ጳጳሳት አትናቴዎስም ከፍሬምናጦስ የቀረበለትን ሪፖርት አዳምጦና መርምሮ የሕዝበ ኢትዮጵያን ቋንቋ የሚያውቀውን ፍሬምናጦስን አጰጵሶ የጀመረውን የስብከተ ወንጌል ሥራ እንዲቀጥል መልሶ ላከው፡፡ ፍሬምናጦስም ወደ ሀገሩ ገብቶ በሥጋ ዘመዶቹ መካከል በመኖር ከሚያገኘው ደስታ ይልቅ በኢትዮጵያ ከሚገኙ በእግዚአብሔር ቃል ከወለዳቸው ልጆቹ ጋር መኖርንና ክርስትናን ማስፋፋትን መርጦ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡ የአክሱም ቤተ መንግሥትም በክብር ተቀበለው፡፡

ለሳባ ኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሐዋርያ የሆነው ፍሬምናጦስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወንጌል በተሰበከባትና የመጀመሪያ አማኞች በተገኙባት በአክሱም ማኅበረ ምእመናንን (ቤተ ክርስቲያንን) ለማቋቋምና ድርጅታዊ ሥራውን ለማካሄድ የሚያስችለውን ሁሉ እግዚአብሔር በሰጠው ጥበብ አደራጀ፡፡

በዘመኑ ያከናወናቸው ተግባራት
ፍሬምናጦስ በአክሱምና በአካባቢው የዘራው የእግዚአብሔር ቃል ለፍሬ በደረሰበት ጊዜ አዝመራውን ትቶ ወደ ሀገሩ ከመሄድ ይልቅ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ በአትናቴዎስ በተሰጠው ምክርና በተጣለበት ኀላፊነት መሠረት ለኢትዮጵያ ያበረከተው ጥቅም እጅግ ብዙ ነው፡፡ አዝመራውን የመሰብሰብ መልሶም የመዝራትና የመሰብሰብ ዑደት ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ለማድረግ አስችሏል፡፡ ለዚህም ለማያቋርጠው በእግዚአብሔር መንግሥት ሲከናወን ለሚኖረው የቃሉን መዝራትና መሰብሰብ ዑደት አንቀሳቃሽ ኀይሎችን፥ ዕቅዶችንና መርሐ ግብሮችን ዘርግቷል፡፡

አንደኛ ማኅበረ ምእመናን (ቤተ ክርስቲያን) ማቋቋሙ

በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ሁሉ እርስ በርሳቸውና ከመድኅናቸው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በአንድ አካል የሚያዋሕዳቸው የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ መሆኑ መጠን ባይተዋወቁም እንኳ አንዱ ምእመን ለሌላው ምእመን በኢየሱስ ክርስቶስ አካል ውስጥ እንደሚገኝ የአካል ክፍል ነውና ውሕደቱ ፍጹምና መንፈሳዊ ነው (ሮሜ 12፥4-5፤ 1ቆሮ. 12፥12-13)፡፡ ይህም መንፈሳዊ አንድነት በኢየሱስ አምነው ያንቀላፉትንና በሥጋ ሕይወት ያሉትን፥ ወደ ፊትም ገና የሚያምኑትን ሁሉ፥ (የሚተዋወቁና የማይተዋወቁትን ሁሉ) ያጠቃለለ ስለ ሆነ፥ ሰማይና ምድርን የሞላች፥ ዛሬ በማያቋርጥ እድገት ላይ ያለች የኢየሱስ ክርስቶስ አካል የሆነች አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዳለች የእግዚአብሔር ቃል ያስተምራል (ኤፌ. 1፥10፤ 2፥20-21፤ 4፥11-16)፡፡

ምእመናን ወንዶችና ሴቶች የተለያየ የዕድሜና የዕውቀት ደረጃ የተለያየ የሥራ ዐይነት፥ የተለያየ ቋንቋ፥ የተለያየ ሥነ ልቡናዊ አመለካከትና ግንዛቤ ቢኖራቸውም፥ በምድር ላይ ማናቸውንም የልዩነት መለኪያና መለያ ዐጥር ሁሉ ወደሚደመስስ መንፈሳዊ አንድነት አምጥቶ ክርስቲያኖችን ሁሉ አንዲት ቤተ ክርስቲያን (አቅሌስያ) በመባል ወደምትታወቅ አንዲት የክርስቶስ አካል አጠቃሎአቸዋል ማለት ነው፡፡

ይህ አንድነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሁለትና ከዚያ በላይ ብዛት ያላቸው ምዕመናን ለአምልኮት ለጸሎት የእግዚአብሔርን ቃል ለማጥናት፥ የጋራ መንፈሳዊ ሕይወትን ለማነጽ ስለሚያስችሉ ጕዳዮች ተወያይቶ የእግዚአብሔር ቃል የሚሰጠውን መመሪያ ለመቀበል የሚያደርጉት ስብሰባ የትም ሆነ የት ቤተ ክርስቲያን ይባላል፡፡ እንግዲህ ከዚህ ተጀምሮ በዚህ ሁኔታ ከተቋቋሙ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ኅብረት ያለው የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ይመሠረታል (ማቴ. 18፥15-20)፡፡

ሰዎች በልማድ የመሰብሰቢያውን ቤት “ቤተ ክርስቲያን” በሚል ስም መጥራታቸው በእግዚአብሔር ቃል ተጽፎ አልተገኘም፡፡ የተለምዶ አባባሉም ሰዎች ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን ግንዛቤ አዛብቶታል፡፡ የግሪኩ ቃል አቅሌስያና የዕብራይስጡ ኳሃል “ለአንድነት የተጠሩና የተመረጡ ሰዎች ጉባኤ”  የመሆንን ምስጢር ከመያዛቸው በቀር ጉባኤው ከሚሰበሰብበት ሕንጻ፥ ወይም አደባባይ፥ ወይም ሜዳ ጋር የሚዛመድ ትርጉም የለበትም፡፡ ሆኖም በግእዝ “ቤት” የሚለው ቃል “ክርስቲያን” ከሚለው ጋር ተያይዞ መነገሩ አንዳንዶችን አደናግሮአል፡፡ ቤት የሚለው ቃል ቤተ እስራኤል (ሕዝ. 18፥25)፡፡ ቤተ ያዕቆብ (ሉቃ. 1፥33) ቤተ ይሁዳ (1ነገ. 12፥21-27) ቤተ ዳዊት፥ ቤተ ሳዖል (2ሳሙ. 3፥1) በሚለው ዐይነት “ወገን” በሚል ትርጉሙ እንዲያገልግል ገባ እንጂ ሕንጻን ወይም ጐጆን ለማመልከት አልነበረም፡፡ እንደዚህ በፊደላዊ ትርጉም እንቀበለው ከተባለም እግዚአብሔርን ማምለኪያ የሆነውን ቤት (ሕንጻ) ብቻ ሳይሆን የክርስቲያን ቤት የሆነውን ሁሉ ማለት ክርስቲያን የሚኖርበትን፥ የሚሠራበትን የሚበላበትንና የሚጠጣበትን … ቤት ሁሉ ጭምር በመግለጽ ማለት የክርስቲያን ንብረት የሆነውን ቤት ሁሉ የክርስቲያን ካልሆኑት ቤቶች በመለየት የሚያገለግል ተራ ትርጉም ያለው ቃል በሆነ ነበር፡፡

እንግዲህ ቤተ እስራኤል በሚለው አንጻር ቤተ ክርስቲያን መባሉ ለአንድነት የተጠራውንና የተመረጠውን የክርስቲያን ጉባኤ (ወገንን) ማለቱ ነው፡፡ ቤተ እስራኤል ሲባልም የእስራኤልን ምርጥ ጉባኤ እንጂ በተለይ ቤተ መቅደሳቸውን አያመለክት እንደ ነበረ ሁሉ፥ ቤተ ክርስቲያን ሲባልም በዚያው ንጽጽር የአምልኮት ስፍራን አያመለክትም፡፡ ጉባኤው የትም ይሁን የት ቢሰበሰብ፥ ስሙን ይዞ ይኖራል፡፡ ይህም ከታወቀ ሕያውንና ግዑዝን ወይም የሕያዋንን ስብስብና የግዑዛንን ስብስብ በማደባለቅ ራስን ግራ ከማጋባት ሌሎችንም ከማደናገር ይጠብቃል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምእመናን ጉባኤ ናትና የክርስቶስ አካል ናት፤ ሕንጻ ግን በምንም ዐይነት የከበረ ነገር ብትሠራ የክርስቶስ አካል አትሆንም፡፡

በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የታቀፉ የአጥቢያና የክልል አብያተ ክርስቲያናት (ማኅበረ ምእመናን) ከጥንቱም የየራሳቸው መጠሪያ ነበራቸው፡፡ አጥቢያው ወይም ክልሉ ከሚጠራባት ስም ጋር ተያይዘውም ይጠሩ ነበር፡፡ ለምሳሌ የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት (ሮሜ 16፥4)፣ የገላትያ አብያተ ክርስቲያናት (1ቆሮ. 16፥1)፣ በአቂላና ጵርስቅላ ቤት ያለች ቤተ ክርስቲያን (ሮሜ 16፥5)፣ የኤፌሶን የሰርምኔስ ቤተ ክርስቲያን (ራእ. 1፥1)1፡፡

ወደ ፍሬምናጦስ ታሪክ ስንመለስ በአክሱም ያቋቋማት ማኅበረ ምእመናን (ቤተ ክርስቲያን) ስም “ጽዮን” ወይም “ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት” የሰማያቷ ጽዮን ማኅበር ተብላ እንድትሰየም መደረጉን እናያለን፡፡ የማኅበሩ ስም ምርጫ በፍሬምናጦስ ቀርቦ ምእመናኑ ተቀብለውት እንደ ሆነ፤ ወይም አንዱ ምእመን ሐሳቡን አቅርቦ ፍሬምናጦስና ምእመናኑ አጽድቀውት እንደ ሆነ አልታወቀም፡፡ በማናቸውም መንገድ ቢሆን በአክሱምና አካባቢው በፍሬምናጦስ ስብከት ክርስትናን የተቀበሉ ምእመናን ለአንድነታቸው ጉባኤ የመሠረቱት ድርጅታዊ ስም የሰማያዊት ጽዮን ማኅበር ለምን ተባለ? ይህን ጥያቄ ለመመለስ ጽዮን የሚለው መጠሪያ ከየት ወደ የት እንደ ሆነ በቅድሚያ ማመልከት ይገባል፡፡

1.     ጽዮን የምትባለው ቀድሞ ኢያቡሳውያን በምሽግነት (አምባነት) የተገለገሉባት ተራራማ ክፍል ስትሆን፥ በኢያቡሳውያን ኢያቤስ ትባል ነበረ፡፡ የዳዊት የጦር ሠራዊት አምባዋን ከማረከ በኋላ የራሱ ከተማ አደረጋት፥ (1ዜና. 11፥4-8)፡፡
2.    አምባው ያለባት ተራራማዋ ክፍል ጽዮን ብትባልም፥ ከተማዋ ኢየሩሳሌም (ሀገረ ሰላም) ተብላ ትጠራለች፡፡ በዚህች የሰላም ከተማ ጼዴቅ ከሚል ቃል በፊት ተናባቢ ሆነ ቃል እየታከለበት መልከ ጼዴቅ (የጽድቅ ገዥ)፤ አዶኒ ጼዴቅ (የጽድቅ ጌታ) የተባሉ ነገሥታት ነግሠውባት ነበር (ዕብ. 7፥1-2፤ ዘፍ. 14፥18-20፤ ኢያ. 10፥1)፡፡
3.    በኢያሱ ጦር መሪነት የዘመተው ሠራዊትም ሆነ በኋላ የነገደ ይሁዳና የነገደ ስምዖን ጣምራ ጦር በኢየሩሳሌምና በአካባቢው ወረራ ቢያደርጉም ኢያቡሳውያንን ጠራርገው አላስወጡም፡፡ በዚህ ምክንያት የዕጣ ባለርስቶቹ ነገደ ብንያም ከኢያቡሳውያን ጋር ተቀላቅለው ይኖሩባት ነበር (መሳ. 1፥1-9፡21)፡፡ ከዚህ የተነሣም ዳዊት ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይገባ ተከላከሉት፡፡ ሆኖም ድል አድርጎ ከተማዪቱንና አምባዋን ያዘ (2ሳሙ. 5፥6-10)፡፡
4.    ዳዊት ሌሎች ጠላቶቹን ሁሉ ድል ካደረገና የውስጥ አስተዳደሩን ካደላደለ በኋላ በአቢዳራ ቤት ይቀመጥ የነበረውን የእግዚአብሔር ስም የተጠራበትን ታቦት በጽዮን አምባ ላይ በተከለው ድንኳን ውስጥ በታላቅ ሥነ ሥርዐት አስገባው (1ዜና. 15 እና 16)፡፡
5.    የኢየሩሳሌም አምባ ሲማረክ የኢያቡሳውያን ተዋጊ ሠራዊት በጦርነቱ ቢያልቁም ተራው ኢያቡሳዊ በየቤቱና በየርስቱ ኑሮውን መምራት የቀጠለ ይመስላል፡፡ ዳዊት በእግዚአብሔር ቍጣ የመጣው መቅሠፍት ይቆም ዘንድ መሥዋዕት የሚያቀርብበትን መሠዊያ ለመሥራት የመረጠው ስፍራ የኢያቡሳዊው የኦርና ርስት ነበረ፡፡ ቀድሞም ያ አካባቢ የሞሪያ ተራራ ይባል እንደ ነበረና በዚያ አብርሃም ልጁን እንዲሠዋ ከታዘዘ በኋላ ልጁ ቀርቶ ከእግዚአብሔር የተላከለትን በግ ሠውቶበት እንደ ነበረ ይታወቃል፡፡ ዳዊት ያን ቦታ ከኦርና ገዛውና መሥዋዕት አቀረበበት፡፡ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ በዚህ ላይ እንዲሠራ ለልጁ ለሰሎሞን ነገረው ሰሎሞንም እንደ ታዘዘው ፈጸመ (1ዜና. 21፥18-28፤ 2ዜና. 3፥1)፡፡
6.    ጽዮን የሚለው ስም የዳዊት ቤተ መንግሥት ያለበትን ክፍልና ከእርሱ በግንብ የተለየውን ቤተ መቅደሱ ያለበትን ቦታ የሚያመለክት ተወራራሽ ስም ነው (መዝ. 121/122፤ 131/132፥12-18)፡፡ ጽዮን አንዳንድ ጊዜም ለከተማዋ ለኢየሩሳሌም መጠሪያ ሆኗል (መዝ. 86/87፥1-3)፡፡ አንዳንድ ጊዜም ለቤተ እስራኤል አጠቃላይ መጠሪያ ሆኖ አገልግሏል (መዝ. 125/126፥1-6፤ ኢሳ. 49፥14-15)፡፡
7.    ጽዮንና ኢየሩሳሌም ጌታ በዳግም ምጽአቱ የሚገለጥበት ስፍራም ሆኖ ተነግሮአል (አብ. 17፤ ሚክ. 4፥1)፡፡

ስለ ምድራዊት ጽዮን ወይም ኢየሩሳሌም ይህን ያህል ከተመለከትን ሐዋርያው ጳውሎስ ስለሚናገርላት ስለ ሰማያዊቷ ጽዮን ከተጻፈው ጥቂት እንይ፡፡ በሐዋርያው በጳውሎስ ዘመን የነበረች ምድራዊት ጽዮን (ኢየሩሳሌም) ከሕግ ባርነት (ገላ. 4፥4-7) ከኀጢአት ባርነት (ዮሐ. 8፥34-36) በሞት ፍርሀት ሰዎችን ከሚገዛ ከዲያብሎስ ባርነት (ሮሜ 8፥2፤ ዕብ. 2፥14-15) ነጻ የሚያወጣትን መንፈሳዊ መሪ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመቀበሏ በሥጋ እስራኤላዊነት የሚመኩ ሰዎች የሚኖሩባት የባርነት ሁሉ እናት መሆኗን ሐዋርያው በድፍረት ይጽፋል፡፡ ያች ጽዮን (ኢየሩሳሌም) ያን ጊዜ ትተዳደረበት የነበረው የባርነት ሕግ የታወጀው በዐረብ አገር በነበረችው በደብረ ሲና እንደ ነበረ አውስቶ የሳራ ባሪያ አጋርም ዐረባዊት (ግብጻዊት) የነበረች መሆኗን ጠቅሶ፥ እርሷ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ያልሆነ፥ በሥጋ ፈቃድ ብቻ ከአብርሃም ልጅን ለባርነት ብትወልድም፥ ሳራ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከወለደችው ከባለተስፋው ልጅ ከይሥሐቅ ጋር አይወርስምና የአጋርን ልጅ ከቤት አስወጣ ተብሎ አብርሃም መታዘዙን ሐዋርያው አብራራ (ሮሜ 9፥8)፡፡

የብሉይ ኪዳኑን ታሪክ ለሐዲስ ኪዳኑ ተስፋ በንጽጽር በማምጣት ሐዋርያው እኛ (ነጻ ያወጣንን ክርስቶስን የተቀበልንና በእርሱ የምንመራ ክርስቲያኖች) እንደ ሥጋ የተወለድንበትን ልደት በሚሽር ዳግም ልደት ለሰማያዊት ጽዮን ወራሽነት በተስፋ ተወልደናልና ነጻዎች ነን የሚልበትን ምስጢር ካጐላ በኋላ፥ እነዚያ እንደ ሥጋ የተወለዱት ግን ከአብርሃምና ከሣራ የተወለዱ ቢሆንም፥ ከባርነት ሕግ ነጻ የሚያወጣውን ኢየሱስ ክርስቶስን ስላልተቀበሉ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት የሚለውን የነጻነት አዋጅ አልተቀበሉም፡፡ አብርሃምንም አልመሰሉትምና በሕግ ባርነት ያሉ ናቸው፡፡ በእምነት የሚገኘውን መንፈሳዊውን ርስትም አይወርሱም በማለት ሐዋርያው ምስጢራዊ ትንታኔ አቀረበ፡፡ (ገላ. 3 እና 4፥21-31፤ 5፥1)፡፡

ይኸው ሐዋርያ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የጻፈው ነው ተብሎ በሚታመነው መልእክቱም ሕግ የታወጀበትን ደብረ ሲናንና ሰማያዊት ጽዮንን በማነጻጸር የእስራኤል ልጆች የእግዚአብሔር ክብር በሚያስፈራ ግርማ ወደ ተገለጠበት ጭጋግ አውሎ ነፋስ የሚያቃጥል እሳት ወደ ነበረበት ተራራ ደርሰው እንደ ነበረ አውስቶ፥ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ግን የዚህ ሁሉ ተቃራኒ ሁኔታ ወደ ተገለጠባት ወደ ጽዮን፥ ወደ እግዚአብሔር ከተማ ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም መድረሳቸውን ተርኮ ይኽም መድረሻቸው በእግዚአብሔር የታቀደው ሉዓላዊና የፍጻሜ ሁሉ ፍጻሜ መሆኑን ያበሥራቸዋል (ዕብ. 12፥18-24)፡፡

እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ንጽጽራዊና ምስጢራዊ ትንታኔ ጽዮን ኳሃል በመባል የምትታወቀውን ለእግዚአብሔር የተጠራችውንና የተለየችውን ቤተ እስራኤልን (ጉባኤ እስራኤልን) በማመልከቷ ትይዩ በሐዲስ ኪዳን “አቅሌስያ” በመባል የምትጠራውን ተመርጣ የተለየችውን ጉባኤ ምእመናን (ቤተ ክርስቲያንን) ትገልጻለች፡፡ ስለሆነም፥

1.     የክርስቲያን እናት ሟችና በስባሽ ሥጋዊት ሴት አይደለችም፤ ሰማያዊትና የማታልፍ ናት እንጂ፡፡ ከእርሷ በእርሷ ለእርሷ በዳግም ልደት ተወልደናልና ወደ ኋላ የተውነውን በሥጋዊ ልደት የተቈራኘነውን ሁሉ ረስተነዋል፤ ትተነዋልም፡፡ ከሰማያዊት ጽዮን ጋር ተሳስረናል፤ አንድነታችንም እንደ ሥጋዊ ልደት እንኳ የማይሽረው ዘላለማዊ ነው ማለቱ ነው (መዝ. 44/45፥9-10፤ 86/87፥1-7፤ ኢሳ. 60፥1-22)፡፡
2.    ጽዮን ለመላው የእስራኤል ሕዝብ መንግሥትና ሀገር መግለጫ በምትሆንበት ትይዩ እኛ ክርስቲያኖች የምንወርሳት ርስት ሰማይና ምድር ሲያልፍ ዐብራ የምታልፍ አይደለችም፤ የእኛ ጽዮን (ኢየሩሳሌም) መንፈሳዊት ሰማያዊት ዘላለማዊት ሀገራችን መንግሥታችን የአንድነታችን መጠሪያ ናት፡፡ በዚህ በሚያልፍ ምድር እንኳ እየኖርን የሰማያዊት ጽዮን ማኅበርተኛነታችን (አባልነታችን) የተረጋገጠ ነው ማለቱ ነው (ዮሐ. 5፥29፤ ኤፌ. 2፥4-7፤ ቈላ. 1፥13-14)፡፡
3.    የአሁኑ በምድር መኖራችን የሰማያዊት ጽዮን ዜግነታችንን ይዘን ለሰማያዊት ጽዮን ስለምንሠራው ነው፤ በምድራውያንና በሥጋውያን የሚደርስብንን መነቀፍ የምንታገሠውም በመንፈሳዊ ዜግነት የተቈራኘናትንና የተመዘገብንባትን ሰማያዊት ጽዮንን አሻግረን እያየንና እየናፈቅን የዛሬውንና የምድሩን ስለማናስታውሰው ነው ማለቱ ነው (2ቆሮ. 5፥1-9፤ ፊል. 3፥20፤ ዕብ. 13፥13)፡፡

ፍሬምናጦስና ኢትዮጵያውያን ምእመናን ከዚህ በላይ ባጭሩ እንደ ተገለጸው ከእግዚአብሔር ቃል ከጨበጡት ከፍተኛ ግንዛቤ የተነሣ፥ በአክሱም የመሠረቷትን ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት የሰማያዊት ጽዮን ማኅበር በሚል መጠሪያ ሰየሟት፡፡

በዛጉዬ ዘመነ መንግሥት መዳረሻ ይኩኖ አምላክን ሥልጣነ መንግሥት ላይ ለማውጣት በተሸረበው ሴራና  በተደረገው ግልጽና ስውር ዘመቻ ይኩኖ አምላክን ከሰሎሞን ለማዛመድ በፈጠራ የተዘረጋውን ሐረገ ትውልድ ያጠናክረዋል ወይም እውነት ያስመስለዋል በሚል ምስጢራዊ ሸር የማኅበረ ጽዮን ሰማያዊትን ትውፊታዊ ትርጉም ለማበላሸት ተሞክሯል፡፡ በጽዮን አምባ መቅደስ ተሠርቶላት የነበረችው ታቦት ከቀዳማዊ ምኒልክ ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጥታ በፍሬምናጦስ ዘመን በአክሱም ነበረች፤ ፍሬምናጦስ ማኅበረ ምእመናኑን ጽዮን እንዲል ያበቃው በአክሱም በነበረችው ከጽዮን አምባ በመጣችው በታቦተ ጽዮን ስም ለመሰየም ነበረ ለማሰኘት ተሞክሯል፡፡ የዚህ ታሪክ ይዘትና አቀራረጽ ሰው ሠራሽ እንጂ፥ በቅዱሳት መጻሕፍት በብሉይ ኪዳን አዋልድ መጻሕፍት፥ በታመኑ ታሪኮች፥ በዘመኑ በተሠሩ ሐውልቶች፥ ገንዘቦችና ልዩ ልዩ ቅርሳ ቅርሶች ያልተደገፈ መሆኑን በጮራ ቍ. 4 ገጽ 12-17 የተጻፈውን አንባቢ ያስታውሰው፡፡

ሆኖም ፍሬምናጦስ ስለ መሠረታት ማኅበር ስያሜ ምንነት የሚያወሱትን ከፍሬምናጦስ ዘመን በኋላ ሁለት መቶ ዓመታት ያህል ቈይቶ በዜማ የተደረሱትን የያሬድ ድርሰቶችን ብሩሃን ገጾች የዐይናችንን መጋረጃ አስወግደን እስኪ እንያቸው፡፡

1.     “እንተ ተሐንጸት በስሙ፥ ወተቀደስት በደሙ፥ ወተዐትበት በዕፀ መስቀሉ ጽዮን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መዓዛሆሙ ለቅዱሳን ጽርሕ ንጽሕት አግዓዚት እንተ የዓውዳ ስብሐት፡፡
“በስሙ የታነጸችው (በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለማለት ነው) በደሙ የተቀደሰች፥ በመስቀሉም የተባረከች ጽዮን የምታባል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን መዓዛቸው ምስጋና የሚታወጅባት ጥራት ጥምቀትና ጥልቀት ያላት አዳራሽ ራሷ እመቤት ሆና ሌሎችን ነጻ የምታወጣ ናት፡፡ (ስለ ጽርሕ ትርጉም መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ዘአለቃ ኪዳነ ወልድ ገጽ 769 ይመልከቱ)፡፡

2.    “በደሙ ቤዘዋ ወበማይ ዘውኅዘ እም ገቦሁ አጥመቃ፥ በዕፀ መስቀሉ ዐተባ ከመ ትኩን ምስትስራየ ኀጢአት ጽዮን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መዓዛሆሙ ለቅዱሳን እንተ ኮነት ምክሐ ለኵሉ ዓለም አግዓዚት ኢየሩሳሌም ቅድስት፡፡

3.    “ይቤላ ልዑል ለቅድስት ጽዮን አንሰ በደምየ ክቡር ቀደስኩኪ ይሴባሕ ስምየ በላዕሌኪ፥ ማኅደረ መለኮት ረሰይኩኪ ወካዕበ ትብል ቤተ ክርስቲያን ወልድ እኁየ ቃልከ አዳም ጥቀ ሥሙር እም ወይን፡፡

ተመሳሳይ የምስጢር ሐሳብ የሚገልጹ በመሆናቸው በአማርኛ ሁሉም ባይተረጐሙም በእነዚህና በሌሎች የያሬድ የዜማ ድርሰቶች ጽዮን አግዓዚት (እመቤቲቱ ጽዮን) ሲል በደሙ የዋጃትን (ሐ.ሥ. 20፥28) የምእመናን ጉባኤ (ቤተ ክርስቲያንን) ማለቱ እንደ ሆነ ራሱ ደራሲው ግልጽ ማብራሪያ ሰጥቶበታል፡፡ ፍሬምናጦስ በሰማያዊት ጽዮን ስም የመሠረታት ማኅበር እስከ ዘመናችን ድረስ ትውፊቱን ይዛ ማኅበራኒሃ ለጽዮን የሰማያዊት ጽዮን ማኅበርተኞች የሚለው የማንነቷ መግለጫ የአንበሳ አርማ ባለው ማኅተም ዙሪያ ተቀርጾ መገኘቱ እጅጉን አስደናቂ ነው፡፡

በጮራ ቍጥር 6 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment