Sunday, April 21, 2013

የመዳን ትምህርትካለፈው የቀጠለ
የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመፀነስና በመወለድ ኀጢአተኛ ባሕርይን ስላልወረሰ ከሰይጣን ቍራኛነት ነጻ ነበረ፡፡ ሁሉን እንዲገዙ ሥልጣን ተሰጥቷቸው የነበሩት አዳምና ሔዋን ሁሉን ከሚያስገዛው ሥልጣናቸው ጋር ለሰይጣን በማደራቸው ምክንያት ሰይጣን የእነርሱን የገዥነት ሥልጣን እንዲወርስና የዚህ ዓለም ገዥ፥ የዚህ ዓለም አምላክ እንዲሆንና እንዲባል አበቁት (ዮሐ. 12፥31፤ 16፥11፤ 2ቆሮ. 4፥4)፡፡ ምድርንና ከእርሷ ሥርዐተ ተፈጥሮ ጋር የተያያዘውን ሁሉ ለመግዛት ከተሰጣቸው ሥልጣን ጋር በሰይጣን ገዥነት ሥር በወደቁት በእነዚህ ወላጆቻችን ምክንያት ሰይጣን ምንም የዚህ ዓለም ገዥ ወይም አምላክ ቢባልም በዚህ ዓለም ውስጥ ከአዳምና ከሔዋን ዘር ተወልዶ ሳለ፥ ኀጢአተኛ ባሕርይን በመንፈስ ቅዱስ አሠራሩ ለይቶ በመተውና ባለመውረሱ ምክንያት ብቻ ሰይጣን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ አለኝ የሚለው የሥልጣን ጥያቄ አልነበረም (ዮሐ. 14፥30)

ኀጢአተኛ ባሕርይን ሳይወርስ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ፍጹም ሰው የሆነው ቃል (ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ) በልደት ፍጹም ቅዱስ እንደ ሆነ ሁሉ በኑሮውም ሁሉ በሰውና በአባቱ ፊት ፍጹም ቅዱስ ነበረ (ሉቃ. 2፥40-52)፡፡ በጠላትነት የተነሡበት ሁሉ እንኳ እርሱን የሚከሱበት ምክንያት ስሕተት አላገኙበትም (ሉቃ. 23፥13-17፤ ዮሐ. 8፥46፤ 18፥38፤ 19፥4-6)፡፡ በቃሉም ፍጹም ቅዱስ እንደ ነበረ የእግዚአብሔር ቃል ይመሰክራል (ኢሳ. 53፥9፤ 1ጴጥ. 2፥22-23)፡፡ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰው ዘር አንድ ሰው እንኳ ሊፈጽመው ያልቻለውን ሕግ አንድ ነጥብ እንኳ ሳያጓድል፥ አድርግ የሚለውን በማድረግ፥ አታድርግ የሚለውን ባለማድረግ አጠቃሎ ሁሉን ሕጉ እንደሚያዘው ፈጸመው (ማቴ. 5፥17-18፤ ሉቃ. 2፥21-27፤ ሮሜ 10፥4)፡፡ ተመጻዳቂው የሰው ልጅ ሊያደርገው የሚፈልገው የኀጢአት ዐይነት ብዙ ሆኖ ሳለ በአቅም ማነስ፥ በይሉኝታ፥ በጊዜ አለመግጠም፥ በቦታ አለመመቸት፥ ምክንያት ያሰበውንና የተመኘውን ባለማድረጉ ብቻ ራሱን እንደ ሕግ ጠባቂና ፈጻሚ በመቍጠር ቅዱስ የሆነ ይመስለውና በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ይመጻደቅበታል፡፡ ዐሥረኛው የሕግ አንቀጽ አትመኝ የሚለው ነውና ገና ድሮ ሕጉ በሐሳብ በምኞትና በዕቅድ ማውጣት በተመጻዳቂው ሰው ተጥሷል፤ ኀጢአትም ተቈጥሮበታል፡፡ ለምሳሌ፦ በምኞት ያመነዘረው ሰው እኔ እኮ ድንግል ነኝ! ይላል፡፡ ሕጉ ግን ፈጽሞ አመንዝረሃል፤ ድንግልናህ ከፈረሰ ዓመታት ዐልፈዋል፡፡

ከተመኘህበት ጊዜ ጀምሮ ስምህ በአመንዝራዎች የስም ዝርዝር ውስጥ ተመዝግቦ በሕግ ከሳሽነት ኀጢአተኛነትህ ተረጋግጦ የኀጢአት ደመ ወዝ ሞት ነው በሚለው መለኮታዊ የሥነ ሥርዐት አፈጻጸም ደንብ መሠረት ሞት ተፈርዶብሃል፡፡ አሁን እኮ ለኀጢአትህ በሥጋ ሕያው ብትሆንም መንፈሳዊ ምዉት ነህ ይለዋል (ሮሜ 7፥7-12)፡፡

እንዲህ ያለ ሕይወትን የሚኖሩ ሰዎች ብዙዎች ቢሆኑም አንዳንዶቹ የሚስቱት የእግዚአብሔርን ቃል ባለማስተዋል ሲሆን (ማቴ. 22፥29፤ ማር. 12፥24)፣ የሚበልጡት ግን ሕግ ሰጪውንና ፈራጁን እግዚአብሔርን ልክ ሰውን በሚያታልሉበት ዘዴ ሊያታልሉት የሚሞክሩ ናቸው (ሮሜ 2፥12-24)፡፡

አንዳንዶችማ ቢያታልሉ ቢዘርፉ ቢገድሉ … እንኳ ይህን ኀጢአት ያደረግነው ለእግዚአብሔር ብለን ነው በማለት ወንጀልን ለእግዚአብሔር አምልኮት መፈጸሚያ መሣሪያ ያደርጉታል፡፡ እግዚአብሔርንም የወንጀላቸው ተባባሪ በማድረግና ቅድስናውን በሰው ዘንድ በማርከስ ያዋርዱታል፡፡ እንዲህ እንዲህ በሚፈጸምበት አምልኮት ውስጥ ሰይጣን እንጂ እግዚአብሔር እንደሌለ የሚረዱበት ጊዜ ይኖራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ሁሉንም በሚችለውና ሁሉን በሚያስችለው በአምላካችን ያልተወሰነ ኀይልና ሥልጣንም እንተማመናለን (1ቆሮ. 6፥9-11፤ ራእ. 22፥14-15)፡፡

ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ስንመለስ ሕግ መፈጸም ያለበት በድርጊት ብቻ ሳይሆን በሐሳብና በቃል ጭምር እንደ ሆነ ያስተማረው ጌታ ኢየሱስ፥ ያው የራሱን ሕይወት ወይም በሕይወቱ እየተፈጸመ ያለውን እንደ ሆነ ሕይወቱን የተከታተሉ ሁሉ ሊያረጋግጡ ይችላሉ (ማቴ. 5፥17-48፤ ዮሐ. 9፥24-33)፡፡ እግዚአብሔር ቅዱሳን ሁኑ ሲል የቅድስና መለኪያ ያደረገው ራሱን ነውና (ዘሌ. 19፥1-2)፡፡

ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ስንመሰክር በሕግ የተደነገገውን ሁሉ እንደ ታዘዘው ፈጸመ፥ ጠበቀ ማለት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ከዚህ በላይ የሆነ ኀይለ ቃል መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የሕግን መስፈሪያ በመሙላት ብቻ አልተወሰነምና፡፡ ሕግ ከሚፈልገው በላይ አትርፎና አትረፍረፎ ተገኝቷል፡፡ ይህን ኀይለ ቃል ከሕግ አንዲቱን ነቍጥ እንዳልፈጸሙ ኅሊናቸው እያወቀ፥ ሰውም እያወቀባቸው “ትሩፋት ሠራን” ለሚሉ ዋሾና ተመጻዳቂዎች ሕይወት መግለጫ እንዳንጠቀምበት እንጠንቀቅ፡፡ ከሰው ዘር መካከል ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ ሕግ ከሚጠይቀው በላይ ትሩፋት የሠራ አለ ሊባል ይቅርና የሚፈለግበትን የሕግ ግዴታም ቢሆን የተወጣ እንደሌለ እንወቅ፡፡ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ከተፈጸሙት ትሩፋት የሚከተሉትን በምሳሌ እንያቸው፡፡

1.     ኀጢአተኛ ባሕርይን በመወለድ ያልወረሰ ቅዱስ እንደ ሆነ ሁሉ በሐሳቡ፥ በቃሉ በሥራውም ቅዱስ ሆኖ ሳለ፥ የሰውን ዘር ኀጢአት ሁሉ፥ ምንም የሚያጸይፍና የሚቀፍ ርኩሰት ቢሆንም ሰው ይድን ዘንድ ብቸኛው መንገድ ይኸው ሆኖ በማግኘቱ በኀጢአተኞች የሰው ልጆች ቦታ ሆኖ ተሸከመው፡፡

በጌቴሴማኒ ነፍሴ እስክትሞት ድረስ ተከዘች እንዲል ያበቃውና የደም ላብ እስኪፈሰው ድረስ ያስጨነቀው በሥጋው ላይ ሊደርስ የተዘጋጀው ሥቃይ ምን እንደ ሆነ ማወቁ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁን ከዚያ በላይ እጅግ ከዚያ በላይ ያስጨነቀው ነውረ ኀጢአት ከቶ ነክቶት በማያውቀው እኔነቱ ላይ ካረፈውና ብንዘረዝር ከማንዘልቀው የርኩሰቱን አስጸያፊነት ለመግለጽ ቃል ከማናገኝለት የኛ ኀጢአት ቀፋፊነትና ከባዳነት የተነሣ እንደ ሆነ ሊሰማን ይገባል፡፡ ጌታም በዚህ ጊዜ ውስጥ ከአባቱ ጋር ያደረገው ውይይት እጅግ የሚያባባ ቃል ነበረ (ማቴ. 26፥37-44፤ ማር. 14፥32-39፤ ሉቃ. 22፥39-44፤ ዮሐ. 12፥27፤ 2ቆሮ. 5፥21)፡፡

ይህ ተግባር የሕግ ግዴታ አልነበረም፡፡ ጌታ ሕግ ከሚጠይቀው በላይ በትርፍነት የፈጸመው ነበር፡፡

2.    በጲላጦስ ፊት ተከሶ በነበረበት ጊዜ የቀረበበትን ክስ ገዢው ጲላጦስ ከመረመረ በኋላ ሊያስከስሰው እንደማይገባ ተናገረና ተከሳሽ ሆኖ የቀረበውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲከላከል ደጋግሞ በመጠየቅ መብት ጠብቆለት ነበር፡፡ በዚህ መብቱ ግን አልተጠቀመም፤ በመብቱ እንዳይጠቀም ባሕርዩ የሆነ ፍቅር እንጂ ሕግ አልከለከለውም፡፡

በሕግ የተሰጠውን መብቱን እንኳ ስላልተጠቀመበት ሕግ ከሚጠይቀው በላይ (ሕግ ያልጠየቀውን) ፈጸመ ለማለት ተቻለ (ማቴ. 27፥12-14፤ ማር. 15፥1-4)፡፡

3.    በመስቀል ላይ ተቸንክሮና በሞት አፋፍ ላይ ሆኖ በነበረበት ወቅት ይህን ሁሉ ግፍ የዋሉበትን ሰዎች ዐዘነላቸው፤ ራራላቸው፡፡ በእርሱ ላይ ያደረሱበትን ግፍ በአሜንታ መቀበሉ ከሚገባ በላይ ሆኖ ሳለ ከዚያ በላይ ርቆና ጠልቆ በመሄድ በእርሱ ላይ ላደረሷቸው የግፍ ሥራዎች የሚገባቸው ፍዳ እንዳይከፈላቸው አባቱን ማለደላቸው (ኢሳ. 53፥12፤ ሉቃ. 23፥34)፡፡ ይህን እንዲያደርግ የሚያስገድደው ሕግ አልነበረም፡፡ ግፍ አድራጊዎቹ የሰው ቅጣት ቢቀርላቸው እንኳ የእግዚአብሔር ፍርድ ስለሚጠብቃቸው “አባት ሆይ ይህን በእኔ ላይ የሚያደርጉትን ሁሉ እንደ ኀጢአት አትቍጠርባቸው” አለ፡፡ አንባቢ ሆይ! ሰይጣን ግን ዛሬ በአረማውያን አፍ ሳይሆን ክርስቲያን ነን በሚሉት አፍ “ግፍዖሙ እግዚኦ ለእለ ይገፍዑኒ ጽብኦሙ እግዚኦ ለእለ ይጸብኡኒ” እያለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግፍ የዋሉበትን ከሷቸው ነበር ብሎ ያውም ስቅለቱ በሚታሰብበት ዕለት ስሙን እያጠፋው ነው (ጮራ ቍ. 5 ገጽ 14 ተመልከት)፡፡

ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሕይወት አባቱ የሰጠው ምስክርነት ከሁሉ በላይ ሊደመጥ ይገባዋል፡፡ “ነፍሴ የወደደችው፥ እጅግ ደስ የተሰኘሁበት” ብሎታልና (ኢሳ. 42፥1-4፤ ሉቃ. 3፥22)፡፡

ጌታ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በመልኩ እንደ ምሳሌው ከፈጠረና ሁሉን ካስገዛለት በኋላ ተመልክቶ “እነሆ ሁሉ እጅግ መልካም ሆነ” ሲል በፍጥረት መጨረሻ ግምገማ ላይ በፈጠረው ሰውና ለእርሱ በሰጠው ሥልጣን ልቡ መርካቱንና ሁሉም እንዳቀደው ሆኖለት ሐሤት ማድረጉን ያመለክተናል (ዘፍ. 1፥26-31)፡፡ ይህ የመጀመሪያ ሰውና ሚስቱ እግዚአብሔርን ከመታዘዝ ይልቅ ሰይጣንን መታዘዝ መርጠው ራሳቸውን በኀጢአት ውስጥ ከጣሉ በኋላ በእነርሱ ወደ ዓለም የገባው ኀጢአት በዝርያዎቻቸውም እየቀጠለና እየተሰፋፋ ሲሄድ አይቶ እግዚአብሔር ዐዘነ፡፡ ሐዘኑም “ሰውን በመፍጠሩ ተጸጸተ” በሚል ከባድ ቃል ተገለጠ (ዘፍ. 6፥5-6)፡፡ በዘመናት ውስጥም ከሰው ዝርዎች መካከል አንድ እንኳ የእግዚአብሔርን ሥምረት ለመፈጸም ባሕርያዊ ለውጥ የታየበት ፍጡር ባለመኖሩም የእግዚአብሔር ሐዘን እንደቀጠለ ነበር (መዝ. 13/14፥2-3፤ 52/53፥2-3)፡፡

አሁን ግን በዚህ በመጨረሻ ዘመን ከሰው መካከል ከብዙ የሰው አእላፋት መካከል አንድ ምርጥ (ውሉድ እምአእላፍ) ተገኘ (ማሕ. 5፥10) እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በቀዳማዊ አዳም የተበደለና ያዘነ እግዚአብሔር ዳግማዊ አዳም በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ዕጥፍ ድርብ የሆነ ደስታንና ርካታን በማግኘቱ ልቡን የሞላው የደስታውና የርካታው ውቅያኖስ የሐዘኑንና የጸጸቱን ተራራዎችና ኰረብታዎች የሚውጥና የሚያሟሟ ሆነ ማለት ነው፡፡

የጌታ ምድራዊ አገልግሎት ማብቂያ
የእግዚአብሔር አካላዊ ቃል ኀጢአተኛ ባሕርይን ሳይወርስ ሰው መሆኑ በኀጢአት በተሸፈነ የሰይጣን ግዛት በሆነ ምድር ላይ ኀጢአት ሳይነካው በቅድስና መመላለሱ፣ ለሰዎች መልካም የሆነውን ሁሉ እያደረገ ለ33 ዓመታት ያህል መኖሩ በወንጌላውያን ተመዝግቦ ደርሶናል (ሉቃ. 3፥23)፡፡ ሦስቱ የአገልግሎቱን ዓመታት በፋሲካ በዓላት ማስላት ይቻላል፤ 1) ዮሐ. 2፥13  2) ዮሐ. 5፥1 እና ዮሐ. 7፥2   3) ዮሐ. 13፥1 እና ዮሐ. 18፥28፡፡

ታሪኩ በዚህ ብቻ ቢያበቃ ኖሮ በዚህ ታሪክ ብቻ ሰው ምን ሊጠቀም ይችል ነበር? ሰው ሁሉ ለአባቶች በተሰጠው ተስፋ በሕግ በተገለጠው ሥዕላዊ መግለጫና በነቢያት ቅስቀሳ መሠረት ለነፍሱ ቤዛ የሚሆን ነገርን ለማግኘት ሲጓጓ ኖረ፤ ናፍቆቱንም ለተተኪ ትውልድ እያስተላለፈ እስከ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ደረሰ፡፡ የናፍቆቱ ግብ ምን ሊሆን ይገባው ነበረ?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርቱ ሰው፥ ዓለምን ሁሉ (ምናልባትም እኛ የማናውቃቸውን ዓለማት ሁሉ አጠቃሎ ዓለመ መላእክትን ጭምር) ገንዘብ ቢያደርግ ምን ይጠቅመዋል ካለ በኋላ ከዚህ ሁሉ መካከል በከፊል ወይም በሙሉ ሰው ለነፍሱ ተለዋጭ የሚሆን ሊያገኝና ሊሰጥ እንደማይችል ሲያስገነዝብ ዓለምን ሁሉ አጠቃሎ የገዛው ሰውስ ለነፍሱ ቤዛ ምንን ይሰጣል? አለ፡፡ ለነፍሱ ቤዛ የመስጠት ግዴታ አለበት ማለት ነው፡፡ ቤዛ ካልሰጠ በኀጢአቱ ምክንያት መጥፋቱ ገሃነመ እሳት ውስጥ መግባቱ የማይቀር ነውና ቤዛው ሊሆን የሚችል ነገርን ሊያገኝ የማይችልበት ዓለም ሁሉ የእርሱ ቢሆን ምን ይጠቅመዋል? ማለቱ ነበር (ማቴ. 16፥26፤ ማር. 8፥35-37)፡፡

የተለዋጭ አስፈላጊነትም ሰውን የሚያስኰንነውን ኀጢአቱን ሁሉ ለሰው ተሸክሞለት÷ ሊሞተው የሚገባውን ሞት እንዲሞትለትና መሞት የሚገባው ሰው በኀጢአቱ መጠየቅና መሞት እንዲቀርለት ማድረግ ስለሆነ የመሢሕን መገለጥ የናፈቀው የሰው ዘር ጥማት ሊረካ የሚችለው ኢየሱስ ክርስቶስ በምትኩ ሲሞትለት ነው፡፡ ታዲያ የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት ከሰይጣን በስተቀር ያልናፈቀው የሰው ልጅ የለም ቢባል ውብ ኀይለ ቃል ሆኖ ሳለ፤ ከሰይጣን ጋር ያበሩት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የተገኘው ጥቅም ተካፋዮች አይደሉምና ለእነርሱ ሞቱ ከታሪካዊነቱ የተለየ ምስጢር የለበትም (ማቴ. 16፥21-23)፡፡

የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ካፈረሰበት ዕለት ጀምሮ የሞተውንና መንፈሳዊ ምዉት ሆኖ (ኤፌ. 2፥1-2) ወደ ዐፈር የሚመለስበትን ሰዓት ይጠባበቅ የነበረውን ሰው ዘር ሁሉ ከኀጢአትና ከሞት ለማዳን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ኀጢአተኛ ተቈጥሮ መሞትና መነሣት ነበረበት (ማቴ. 16፥21፤ 17፥22-23፤ ዮሐ. 3፥14)፡፡ ይህን አጸያፊና አሠቃቂ የሆነና ለኀጢአተኛ ብቻ ተገቢ የሆነውን ሞት ይቀበል ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድራዊ አገልግሎቱ ማብቂያ ላይ ወደሚሞትበት ወደ ኢየሩሳሌም ለመጓዝ ደቀ መዛሙርቱን አስከትሎ ተነሣ (ማቴ. 10፥17-19፤ ሉቃ. 18፥31-34)፡፡

ሞቱ ሰውን ከሞት የሚያድን ስለሆነ ወደሚሞትበት ሲሔድ ደቀ መዛሙርቱን ይቀድማቸው ስለነበር እርሱም ለመሞት ምን ያህል ፈቃደኛ እንደነበረ ያስረዳል (ማር. 10፥32-34፤ ሉቃ. 19፥28)፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት ሆኖ ለነቢዩ ለኢሳይያስ አስቀድሞ ታይቶት ነበር (ኢሳ. 53፥7)፡፡

ትንሣኤን በሚያህል ድል አድራጊነት አጀብ የታጀበውን ሞት ስለሚሞትም ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ድል አድራጊ የጦር መሪ የጠላትን መሸነፍ በሚያበሥርና ለርግጠኛ ሰላም መገኘት ዋስትና በሚሰጥ ንጉሣዊ ጕዞና ሰልፍ ታጅቦ ወደ መናገሻው እንደሚገባ ሆኖ ገባ እንጂ በድብቅ አልገባም (ዘካ. 9፥9፤ ማቴ. 21፥1-11፤ ማር. 11፥1-11፤ ሉቃ. 19፥28-40፤ ዮሐ. 12፥12-16)፡፡

የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ለኀጢአተኛ ሞት እንዴት ተቈጠረ?

የጌታችን መሞት ለኀጢአተኛ ሰው ሞት ሆኖ እንዴት ተቈጠረና ሰውን በኀጢአት ከመጠየቅ እንዴት ነጻ አደረገው? የሚለውን ጥያቄ በተለያየ መንገድ መመለስ ይቻላል፡፡ በዐጭሩም በመሥዋዕት ምሳሌ እንደ ኦሪት ትእዛዝ ሲፈጸም የኖረውን ሥርዐት ጠቅሶ ማስረዳትም አንደኛው መንገድ ነው፡፡ ኀጢአት መሥራቱን ያስተዋለ እስራኤላዊ ነውር የሌለበትን ጠቦቱን እየነዳ በኢየሩሳሌም ወደ ቆመው ቤተ መቅደስ ከሄደ በኋላ እንስሳውን ለካህኑ ያቀርብ ነበር፡፡ ኀጢአተኛው እጁን ለመሥዋዕት ባቀረበው እንስሳ ላይ በመጫን ኀጢአቱን ያስተላልፋል፤ ከዚያ በኋላ ነውር ያልነበረው እንስሳ በነውረኛው ሰው ምትክ በመሠዊያ ላይ ይሠዋል፤ ደሙን ካህኑ ተቀብሎ ይረጫል፤ ሥጋውም ተቈራርጦ በሕግ እንደ ተደነገገው ይፈጸምበታል (ዘሌ. 4 እና 5 እንዲሁም 6)፡፡ በዚህ መንገድ ስርየት እንደሚገኝ በእግዚአብሔር የተነገረውን ቃል በመተማመን መሥዋዕት አቅራቢው ከኀጢአት ክስና ቅጣት ነጻነትን አግኝቶ በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ ነበር፡፡ ይህም የጌታን ሞት ጥቅም ለማስረዳት ምሳሌነቱ ጠቃሚ ነው (ዮሐ. 1፥29)፡፡

በዚህ ቦታ ግን ለየት ባለ ሁኔታና ምሳሌ ለማስረዳት ተሞክሯል፡፡ በእባብ ሰኰናን መቀጥቀጥ (መነከስ) እና የእባብን ራስ በመልሶ ማጥቃት መቀጥቀጥ የሚለውን መርጠናል፡፡

የእባብን ራስ የእባብ ልጅ የመቀጥቀጥ ችሎታ የለውም ማለት፥ አዳምንና ሔዋንን ለቃሉ እንዲታዘዙ በማድረግና የራሱን ባሕርይ በፈቃዳቸው በምርጫቸው በታዘዙለት ቃሉ አማካይነት ወደ ውስጣቸው በማስተላለፍ፥ የሰውን ዘር የበከለው ሰይጣን የእርሱ ውላጅ በሆነውና ራሱ በሚቈጣጠረው ሰው ጥቃት ሊደርስበት አይችልም፡፡ እግዚአብሔርም ቢሆን የወደደውን ሁሉ የማድረግ ችሎታውንና የበላይ የሌለበት ያልተገደበ ሥልጣኑን መሣሪያ በማድረግ የእባብን ራስ እንዲቀጠቅጥ ፍትሕና ርትዕን የሚያፈልቀው ቅዱስና ጻድቅ ባሕርዩ አይፈቅድለትም፡፡ ከባሕርዩ ውጪ ለመሆን ራሱን መለወጥ አይሆንለትምና (ሚል. 3፥6፤ 2ጢሞ. 2፥13)፡፡

አዳምና ሔዋን በወደቁበት ጊዜ ስለ እባብ በተነገረው ቃለ መርገም “በአንተና በሴቲቱ በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አቆማለሁ፤ እርሱ (የሴቲቱ ዘር) ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ” በተባለው መለኮታዊ ተስፋ መሠረት፥ የሴቲቱ ዘር ራሱን ሳይሆን ሰኰናውን በእባቡ እንዲነከስ በመልሶ ማጥቃቱ ግን ሰኰና ነካሹ እባብ በሴቲቱ ዘር ራሱን የሚቀጠቀጥበት ጥቃት እንዲደርስበት ተገቢ ሆኖ ታቅዶ ነበረ፡፡ ሁኔታዎቹ ለዚህ መለኮታዊ ዕቅድና ግብ እየተመቻቹ ወደ ፍጻሜው ማምራት ነበረባቸው፡፡ ስለዚህም፡-

1.   ቃል ኀጢአተኛ ባሕርይን ሳይወርስ ከድንግል ተፀነሰ (ገላ. 4፥4፤ ዕብ. 2፥17)፡፡
2.  ሥግው ቃል በዚህ ምድር ኀጢአትን ሳያደርግ በቅድስና የኖረ ብቸኛ ሰው ሆነ (ዕብ. 4፥15)፡፡
3.  ኀጢአተኛ ባሕርይን ሳይወርስ የኖረውን በኑሮውም በቃልም ቅዱስ የሆነውንና የሚከሰስበት አንዳች እንከን የሌለበትን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰይጣን ዝም ብሎ አልተመለከተም፡፡ ክርስቶስን የሚከስበት አንዳች ምክንያት አላገኘበትም (ዮሐ. 14፥30)፡፡ በአምላክ ነኝ ባይነት ባስተዳደረው ዓለም ውስጥ የእርሱ ቍራኛ ከሆነው የሰው ዝርያ መካከል ከእርሱ ቍራኛነት ነጻ ሆኖ ሰይጣን በስሑት አእምሮው ሊረዳ ባልቻለው መለኮታዊ ጥበብ ተወልዶአልና፤ የአዳምና የሔዋን ልጆችን ሁሉ በኀጢአት ምክንያት እያነቀ ወደ ሲኦል በሚወስድበት ሞት ባለሥልጣንነቱ (ዕብ. 2፥14-15) ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚደፋፈርበት አግባብ መንገድ አልነበረውም፡፡

4.  እብሪተኛው ሰይጣን ግን አንዳች እንከን የሌለበትን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የመንግሥትና የክህነት ባለሥልጣኖችና ጭፍሮቻቸው የእርሱ ሠራዊት በመሆናቸው ብቻ በእነርሱ ተጠቅሞ ኢየሱስ ክርስቶስን አስገደለው (ሉቃ. 23፥18-23)፡፡

5.  ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሚያደርገውን ያውቃልና እኔ ኀጢአትን ስላልሠራሁ ልሞት አይገባኝም ሳይል ኀጢአተኛ ብቻ ሊሞተው የሚገባውን ሞት በግፍ እንዲሞት ሲፈርዱበት የአባቱን ቅን ፍርድ እየተጠባበቀ ሰይጣን በተባባሪዎቹ አማካይነት እንዳሻው እስኪያደርግበት ድረስ ራሱን ተወ (ሉቃ. 23፥46፤ 1ጴጥ. 2፥23፤ ማቴ. 26፥62፤ ፊል. 2፥5-8)፡፡

6.  ግፈኛውና ዕብሪተኛው ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዥ ነኝ ባይነቱ ጌታ ኢየሱስን ካስገደለ በኋላ በማንኛውም ኀጢአተኛ እንደሚያደርገው ሥጋውን ወደ መቃብር ነፍሱንም ወደ ሲኦል በድፍረት አስገባው፡፡

7.  ምንም የኀጢአት ንክኪነት የሌለበትን ጻድቁን ኢየሱስ ክርስቶስን ጊዜያዊ ድል አድራጊ በሚያስመስለው ወይም የሴቲቱን ዘር ሰኰና እንደ መንከስ በሚቈጠረው የድፍረት ሥራው፥ ጭንቅላቱን እንደ መፈጥረቅ ለሚቈጥረው፥ ጽድቅና ርትዕ ለሚፈርደው የእግዚአብሔር ውሳኔ ሁኔታው እንዲዚህ ሆኖ ተመቻቸ (ሐ.ሥ. 2፥22-23)፡፡

8.  ሞት የመጣው ኀጢአትን ተከትሎ መሆኑ ይታወቃል፤ ታዲያ ኀጢአት የሌለበትን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመግደል የበቃበትን ምክንያት ሰይጣን ማስረዳት አይችልም፡፡ የዚህ ዓለም ገዥና የሞት ባለሥልጣን በመሆኑ ብቻ የፈጸመው የዕብሪት ሥራ ስለ ሆነ ጽድቅና ርትዕን በሚፈርደው በእግዚአብሔር ችሎት የተሰጠው ውሳኔ፡-
1.1.  ኀጢአት ሳይኖርበት ኀጢአትን ተከትሎ በመጣ ሞት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀጣው ያለ ሕግ ስለ ሆነ ሞት ይይዘው ዘንድ አይገባምና ነፍሱ ወደ ሥጋው ተመልሳ ከመቃብር እንዲወጣ (እንዲነሣ) (ሐ.ሥ. 2፥24-32)፣
1.2. ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ኀጢአት ሳይኖርበት ለኀጢአተኛ ብቻ በተገባ ሞት በግፍ ለደረሰበት ቅጣት ካሣው ይሆን ዘንድ ሞቱ ሞታችን ትንሣኤውም ትንሣኤያችን ነው ብለው ለሚታመኑ ኀጢአተኞች ያለ አግባብ የተቀበለው ሞቱ በአግባቡ ለሚቀበሉት ሞታቸው፤ በእግዚአብሔር ቅን ፍርድ የተገኘው ትንሣኤውም ትንሣኤ በሌለው ሞታቸው የማያገኙትን ትንሣኤን የሚያገኙበት ትንሣኤ ሆኖ እንዲቈጠር (ሮሜ 4፥22-25፤ 6፥9-11፤ 1ቆሮ. 15፥3፡16-22)፣

1.3.  ይህንም በእግዚአብሔር ጸጋ የእነርሱ እንዲሆን የተቈጠረላቸውን የኢየሱስ ክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ የሚያበሥረውን ወንጌል በመታመን የሚቀበሉ ሁሉ በቍራኛነት ምክንያት የሰይጣን መሆናቸው እንዲቀርና ለኢየሱስ ክርስቶስ የሚሆኑበት የመንፈስ ቅዱስ ማኅተም እንዲታተምባቸው (2ቆሮ. 1፥21-22፤ ኤፌ. 1፥13-14፤ ሮሜ 7፥2-6፤ 14፥7-9፤ 2ቆሮ. 5፥14-15)፣
1.4.  እብሪተኛው ሰይጣን የሞትና የሲኦል ሥልጣኑን ያለ አግባብና ከወሰን በላይ ስለ ተጠቀመበት ሥልጣኑን እንዲያጣና የሞትና የሲኦል አበጋዝነት ለኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሰጥ (ዮሐ. 12፥31-32፤ 16፥11፤ ራእ. 1፥18)፣
1.5.  ከእንግዲህ ወዲያ የሰው መኰነን በኢየሱስ ክርስቶስ የተፈጸመውን ሰውን የሚያድነውን ወንጌል ባለመቀበሉ እንዲሆን (ዮሐ. 3፥18፡35፡36፤ 5፥24)፣

በተላለፈው የፍርድ ውሳኔ ለአንዴና ለመጨረሻው ሰይጣን ራሱን ተቀጠቀጠ፡፡ በእባብ (በሰይጣን) ሰኰናውን የተነከሰው የሴቲቱ ዘር ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመልሶ ማጥቃት ርምጃ ጽድቅና ርትዕ በሆነ አምላካዊ ፍርድ የእባብን ራስ የቀጠቀጠበት መለኮታዊ ጥበብ ከጥበበ-ጥበባት ሁሉ በላይ የሆነ የጥበብ ራስ ነው (ኢዮ. 11፥2-9፤ 1ቆሮ. 1፥18-31፤ 2፥6-10)፡፡ ስለ ሆነም እግዚአብሔር አምላካችን ከዘላለም እኛን ሊያድን በማቀዱና ልጁን አሳልፎ በመስጠቱ፥ እግዚአብሔር ወልድም በእግዚአብሔርነቱ ደረጃ ከመኖርና ከመመለክ ባሕርያዊ መብቱ ራሱን በፈቃዱ አዋርዶ እስከ መስቀል ሞት በመስጠቱ፥ በዚህ ምክረ ትሥልስት የተስማማው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የተገኘውን ደኅንነት በማብሠሩ ምስጋና ይድረሰው፡፡ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ለእርሱ ይሁን፡፡ ለጠላቶቻችን ጥርስ ንክሻ ያላደረገን ጠላት ያጠመደውን ወጥመድ ሰባብሮ ነጻ ያወጣን፥ የአምላካችን ስም ይባረክ (መዝ. 123/124፥6-7)፡፡

በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ተሟልቶና እንከን አልባ ሆኖ የተገኘውን ደኅንነት ሰው እንዴት ሊጠቀምበት ይችላል? የሚለው ጥያቄ በሚቀጥለው ዕትም ይመለሳል፡፡


(በጮራ ቍጥር 6 ላይ የቀረበ)

No comments:

Post a Comment