READ PDF
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ
ካለፈው የቀጠለ
መዝገበ ቃላት
ኪ.ወ.ክ. ሲነሡ ከስማቸው ጋር ተያይዞ በዋናነት የሚነሣው ዕውቅ
ሥራቸው “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” ነው። የዚህ ንባቡ በግእዝ፣ ፍቺው በዐማርኛ የኾነ መዝገበ ቃላት ሥራ ጀማሪ
በእርሳቸው ብርዕ፣ “በሮማውያን ዘንድ የከበሩ ትምህርት ከጥፈት ያስተባበሩ፥ በትምርታቸውም የተደነቁና የታወቁ፥ በሀገራቸው ግን
እንደ ነቢያት የተናቁ እንደ ሐዋርያት የተጠቁ፥ እንደ ዮሴፍም ወንድሞቻቸው ጠልተው ተመቅኝተው ለማይረባ ዋጋ የሸጧቸው የአንኮበሩ
ሊቅ” በማለት የተገለጡት መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ወልደ አባ ተክሌ ሲኾኑ፣ ፈጻሚው ደግሞ ኪ.ወ.ክ. መኾናቸው በመጽሐፉ ላይ ተጠቅሷል።
“ሥራን መንቀፍ በሥራ ነው እንጂ በቃል ብቻ መንቀፍ አይበቃም”
የሚል ዐቋም የነበራቸው መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ይህን የግስ (የመዝገበ ቃላት) መጽሐፍ ለማዘጋጀት የተነሣሡት፣ ዲልማን የተባለው
የውጭ አገር ሊቅ ያዘጋጀውን የግእዝ ግስ ከተመለከቱ በኋላ፣ በተለይ በሞክሼ ፊደላት (ሀሐኀ፣ ዐአ፣ ሠሰ እና ጸፀ) አጠቃቀም ላይ
የታየውን ጕድለት በሥራቸው ለመንቀፍ (ትክክለኛውን ለማሳየት) ነው። ኾኖም ዲልማን የውጭ ዜጋ ኾኖ ግእዝን አጥንቶ መዝገበ ቃላት
በማዘጋጀቱ ከፍ ያለ አክብሮትና አድናቆት እንደ ቸሩትም በመዝገበ ቃላታቸው ውስጥ እናነባለን። ሞክሼዎቹ ፊደላት እንደ ቀድሞው የድምፅ
ልዩነት ባይኖራቸውም የመልክ ልዩነት ስላላቸውና ምስጢራቸውና ስማቸውም እንደ መልካቸው የተለያየ ስለ ኾነ ያ ተጠብቆ መጻፍ አለበት
ይላሉ።