Friday, June 1, 2012

ጋብቻ

Read in PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ

የጋብቻ ቅንጅት

መግቢያ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክና ስለ ሰው ልጆች የቅርብ ግንኙነት ሰፋ ባለ ሁኔታ አብራርቶ ያሳየናል፡፡ በመጀመሪያ የነበረው ይህ ግንኙነት የሰው ልጅ ፈጣሪውን እስከ በደለበት ወቅት መልካም ነበር፡፡ ሆኖም ሰው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተላልፎ በኀጢአት በመውደቁ ግንኙነቱ ተበላሸ፡፡ ምንም እንኳ የሰው ልጅ በኀጢአት ቢወድቅም፥ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የነበረውን ግንኙነት እንደ ገና ዐድሶታል፡፡ በተጨማሪም ይህ የእግዚአብሔር ቃል በወንድና በሴት መካከል የነበረውን የቅርብ ግንኙነት የሚያስረዳ ሲሆን፥ ከሁሉም በላይ ደግሞ የጋብቻን ክቡርነትና የበላይነት በሰፊው ዘግቦ ይገኛል፡፡ ይህም ከዘላለም የነበረው የእግዚአብሔር አሠራርና ባሕርይ አሁንም ያልተለወጠ በመሆኑና ቀደም ሲልም በቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፎ የሚገኘው የሰው ልጆች የሕይወት ታሪክ በአሁኑ ወቅት ላለነው ለእኛ ለየት ያለ ቢሆንም መልካም ትምህርት ይሰጠናል፡፡


የመጀመሪያ ጋብቻ
ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ሲገለጥ ለተከታዮቹ መመሪያና ትምህርት የያዘ ስለ ሆነ በይበልጥ ልብ ልናደርገው ይገባናል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ለመጀመሪያው የጋብቻ ሁኔታ ትኲረት ሰጥተን ሰፋ ባለ ሁኔታ እንመለከተዋለን፡፡ እግዚአብሔር በወንድና በሴት መካከል ስላለው የጋብቻ ሁኔታና ዓላማ እንዴት እንዲሚያስብ በእግዚአብሔር ቃል በግልጥ ይታያል፡፡