Friday, June 1, 2012

ጋብቻ

Read in PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ

የጋብቻ ቅንጅት

መግቢያ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክና ስለ ሰው ልጆች የቅርብ ግንኙነት ሰፋ ባለ ሁኔታ አብራርቶ ያሳየናል፡፡ በመጀመሪያ የነበረው ይህ ግንኙነት የሰው ልጅ ፈጣሪውን እስከ በደለበት ወቅት መልካም ነበር፡፡ ሆኖም ሰው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተላልፎ በኀጢአት በመውደቁ ግንኙነቱ ተበላሸ፡፡ ምንም እንኳ የሰው ልጅ በኀጢአት ቢወድቅም፥ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የነበረውን ግንኙነት እንደ ገና ዐድሶታል፡፡ በተጨማሪም ይህ የእግዚአብሔር ቃል በወንድና በሴት መካከል የነበረውን የቅርብ ግንኙነት የሚያስረዳ ሲሆን፥ ከሁሉም በላይ ደግሞ የጋብቻን ክቡርነትና የበላይነት በሰፊው ዘግቦ ይገኛል፡፡ ይህም ከዘላለም የነበረው የእግዚአብሔር አሠራርና ባሕርይ አሁንም ያልተለወጠ በመሆኑና ቀደም ሲልም በቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፎ የሚገኘው የሰው ልጆች የሕይወት ታሪክ በአሁኑ ወቅት ላለነው ለእኛ ለየት ያለ ቢሆንም መልካም ትምህርት ይሰጠናል፡፡


የመጀመሪያ ጋብቻ
ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ሲገለጥ ለተከታዮቹ መመሪያና ትምህርት የያዘ ስለ ሆነ በይበልጥ ልብ ልናደርገው ይገባናል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ለመጀመሪያው የጋብቻ ሁኔታ ትኲረት ሰጥተን ሰፋ ባለ ሁኔታ እንመለከተዋለን፡፡ እግዚአብሔር በወንድና በሴት መካከል ስላለው የጋብቻ ሁኔታና ዓላማ እንዴት እንዲሚያስብ በእግዚአብሔር ቃል በግልጥ ይታያል፡፡


በሦስት ጽሑፎች በመጀመሪያው ጋብቻ የተገኙትን ሦስት መሠረታዊ ደንቦች እናያለን፡፡ ይህን ስናደርግ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፈው ከሚገኙት የጋብቻ ምሳሌዎች እየጠቀስን በዘመናችንም ካለው የጋብቻ ሁኔታ ጋር እናነጻጽረዋለን፡፡

ጋብቻ እግዚአብሔር በመካከል የሚገኝበት ቅንጅት ነው፡፡
ዘፍ. 2፥18-25 ስናነብ ጋብቻ በሁለት ተፈላላጊ ጾታዎች መካከል እግዚአብሔር የሚገኝበት ቅንጅት እንደ ሆነ ማየት እንችላለን፡፡

“ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት፡፡” ብሎ ጋብቻን ለሰው ልጅ የሰጠው እግዚአብሔር ነበር፡፡

በአዳም እንቅልፍ ጥሎበት ከጐኑ የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጐ ከሠራት በኋላ ወደ እርሱ አምጥቶ ጋብቻን የቀደሰው እግዚአብሔር ነበር፡፡

የክርስቲያኖችን ጋብቻ በቤት ልንመስለው እንችላለን፤ ይኸውም ምሰሶው እግዚአብሔር ሲሆን ማእዘኖቹ ባልና ሚስት በመሆናቸው ነው፡፡ በዚህም ምሳሌ መሠረት ሁለቱም ወደ እግዚአብሔር እየቀረቡ በሄዱ መጠን ሲፋቀሩ፤ በአንጻሩ እያንዳንዳቸው ከከርስቶስ በራቁ ቊጥር እየተለያዩ ይሄዳሉ፡፡




እንግዲህ እውነተኛ የጋብቻ ቅንጅት እያንዳንዱ ተባባሪ ከእግዚአብሔር ጋር በጥሩ ግንኙት በመሆን ይጀምራል፡፡ ሁለት በሬዎች በአንድነት ተጠምደው በትክክትል ወደ ፊት ካልተጓዙ ለማረስ አይችሉም፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ” ያለው፡፡

አብርሃምና ሣራ በእምነት ለእግዚአብሔር ጥሪ መልስ ሰጥተው ዐብረው እንደ ሄዱና የመልካም ጋብቻ ምሳሌ እንደ ሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳየናል፡፡ እንዲሁም ቦኤዝና ሩትን እግዚአብሔር በሚያስገርም መንገድ መርጦ ስላጋባቸው ከእነርሱ ዘር መሲሕ እንዲወለድ ፈቅዶአል፡፡ እንዲሁም አቂላና ጵርስቅላ ቤታቸውን በመክፈት ሐዋርያው ጳውሎስን፥ ዐዲስ አማኝ የሆነውን አጵሎስንና በሮሜ ይሰበሰቡ የነበሩትን ምዕመናን ተቀብለዋቸዋል፡፡

አክዓብና ኤልዛቤል በቅንጅታቸው በኀጢአት እየተደጋገፉ ወደ መጥፎ መጨረሻ እንደ ደረሱ አሟሟታቸው ይመሰክራል፡፡ ሎጥ ምንም እንኳ ጻድቅ ቢሆንም ከሰዶም የመጣች ሴት በማግባቱ ለጥፋት ተዳርጓል፤ ነገር ግን በአብርሃም ጸሎት ከጥፋት ሊድን በቅቷል፡፡

በእኛስ ጋብቻ ውስጥ ለእግዚአብሔር ምን ቦታ ሰጥተነዋል? እግዚአብሔር እኛን ወደ ጋብቻ እንደሚመራን እናምናለን? ወደ ፊትስ ዐብረን እንጓዛለን? በእምነትም ዐብረን እንሄዳለን? ዐብረንስ የእግዚአብሔርን ቃል እናነባለን? ዐብረንስ በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር እንነጋገራለን? ቤታችንንስ ለእርሱ አስረክበናል?

እስካሁን ድረስ ካለገባንና ስለ ጋብቻ የምናስብ ከሆነ እግዚአብሔር የጋብቻችን መሪና ፈጻሚ እንዲሆን እንፈልጋለን?

ቅንጅቱ ፊት ለፊት ሆኖ የልብ መግባባትን ያመለክታል፡፡

በዘፍ. 2፥18-25 መሠረት የጋብቻ ቅነጅት በባልና ሚስት መካከል ያለውን የልብ መግባባት እንደሚያመለክት እንረዳለን፡፡ ይህንም እግዚአብሔር ሴትን በፈጠራት መንገድ ልንመለከት እንችላለን፡፡ እንዲህም ስንል ሴት የተፈጠረችው እንድትገዛው ከወንዱ ራስ፥ ወይም እንድትገዛ ከወንዱ እግር ሳይሆን እንዲወዳትና እንዲጠብቃት በልቡ አጠገብ ከጐኑ ማለት ነው፡፡ እርሷም ከእርሱ ጐን የተፈጠረችው በሕይወት ዘመንዋ እንድትረዳው ነው፡፡ በመጀመሪያ አዳምና ሚስቱ በነበራቸው ፍጹም ግንኙት ሳይተፋፈሩ ዐብረው ይኖሩ ነበር፡፡ በመካከላቸውም ምንም የሚያግዳቸው ነገር አልነበረም፡፡ በኋላ ግን ለእግዚአብሔር ያለመታዘዛቸውን የሚያመለክት አንዱ ውጤት በሰውነታቸው ላይ የበለስን ቅጠል እንደ ልብስ ሰፍተው ማገልደማቸው ነበር፡፡ በዚህም መንገድ ለእግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን እርስ በእርሳቸውም ለመደባበቅ ሞከሩ፡፡

የይስሓቅና የርብቃ ጋብቻ ዋና ስሕተት የቅርብ ግንኙነት አለ መኖሩ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ጋብቻቸውን በግልጽ መንገድ ይመራ እንደ ነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦአል፡፤ ምንም ቢሆን ጋብቻቸው በጥሩ መንገድ አላደገም፤ ርብቃም እግዚአብሔር ስለ ያዕቆብ የሰጠውን የተስፋ ቃል እስከሚፈጽም ድረስ ይስሓቅን አታለለችው፡፡ ስለ ጉዳዩ ለመነጋገር ለምን አልቻሉም ነበር? ይህንም ባለማድረጋቸው ብዙ ዓመታትን በሐዘን አሳለፉ፡፡ በርግጥ ያዕቆብ ከዔሳው ቢሸሽም፥ ርብቃ ግን እርሱን በምድር ላይ እንደ ገና አላየችውም፡፡

በእኛስ መካከል ያለው ግኙነት እንዴት ነው? እርስ በእርሳችንስ እንደማመጣለን? ደስታን፣ ተስፋን፣ መከራን፣ ችግርን ዐብረን እንካፈላለን ወይ? በመካከላችንስ የሚያግደን ነገር አለ ወይ? ሁል ጊዜ በቀን ውስጥ አንድ ችግር ቢነሣ ከመተኛታችን በፊት መታረቅ ብንሞክር ይህ ጥሩ ልምድ ሊሆነን ይችላል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚል “በቊጣችሁ ላይ ፀሓይ አይግባ፤ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት፡፡”

ማጠቃለያ፤

ይህም የመጨረሻ ጥያቄ ላላገቡት ነው፡፡ አንድ ቀን ጋብቻ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ብታምን ከእግዚአብሔር ለአንተ የተመረጠችውን ለመቀበልና ሕይወትህን በእውነተኛ የጋብቻ ቅንጅት ከእርሷ ጋር ለመካፈል ዝግጁ ነህን?

በመጨረሻም አንድ አሳብ ላገቡት እናቀርባለን፡፡ እስከ አሁን ድረስ ካላደረጋችሁ አንድ ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐብራችሁ መርጣችሁ ለጋብቻችሁ እንዲሆን ጽፋችሁ በመኝታ ቤታችሁ ውስጥ አስቀምጣችሁ ሁል ጊዜ አንብቡት፡፡ የተጻፈውንም በሕይወታችሁ እውን አድርጋችሁ በተግባር እንድታስታውሱትና ጌታ ጸጋውን እንዲያጐናጽፋችሁ ጸልዩ፡፡

ለዚህም የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች፡-
ዘፍ. 2፥18-25፤ 3፥7፤ 12፥4-5፤ 19፥23-29፤ 25፥21-23፤27፤ ሩት 4፥13-16፤ 1ኛነገ. 19፥1-2፤ 22፥34-36፤ 2ኛነገ. 9፥30-33፤ ማቴ. 1፥18-21፤ ሉቃ. 1፥38፤ ሐ.ሥ. 18፥1-3፤ 24-26፤ ሮሜ 16፥3-5፤ 2ኛቆሮ. 6፥14፤ ኤፌ. 4፥26፡፡

No comments:

Post a Comment