Saturday, July 27, 2013

መሠረተ እምነት

ከነቅዐ ጥበብ

ካለፈው የቀጠለ

ማስገንዘቢያ፡- ሥላሴን በመካድ ከሰባልዮሳውያን ቀጥሎ የሚታወቁት አርዮሳውያን፣ እግዚአብሔር በማለት በግእዝና በዐማርኛ የሚጠራው መለኮታዊ ስም እንደ ዕብራይስጡ፣ “ይሆዋ ወይም ያህዌ” መባል አለበት የሚል አቋም በመያዝ ስለ ተነሡ በዚህ ስም አንተርሰውና አስታክከው የሚነዙትን ሐሰተኛ ትምህርት ከመሠረቱ ጀምሮ ለማፈራረስ ሲባል በዚህ ርእስ በሚቀርበው መሠረታዊ የክርስትና ትምህርት “ይሆዋ ወይም ያህዌ” የሚለውን ቃል መጠቀም የቃላት መደናገርን ያስወግዳል ተብሎ ታምኖበታል፡፡

“ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናና ዛሬ፥ ለዘላለምም ያው ነው፡፡ እስመ ኢየሱስ ክርስቶስ ውእቱ ዘትማልም፥ ወዮም ውእቱ፥ ወእስከ ለዓለም፡፡” ሲል የሚያስተምረው መጽሐፍ ቅዱስ ነው ዕብ. 13፥8፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መተርጉማንም “ትናንት” የሚለው ቃል በሁለት ክፍል ሊታዩ የሚገባቸውን የወቅት ምዕራፎችን ያሳስበናል ይላሉ፡፡ ሲተነትኑትም፡-
አንደኛ፥ ዓለም ከመፈጠሩ፣ ዘመንም ከመቈጠሩ አስቀድሞ የነበረውንና የጊዜ መነሻ ያልነበረውን የወልድን የአኗኗር ብሉየ መዋዕልነት፥ (የዕድሜ ባለጸጋነቱን) ያመለክታል ይላሉ፡፡

Thursday, July 11, 2013

ክርስትና በኢትዮጵያየእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

ካለፈው የቀጠለ

ሦስተኛ፥ የመሰብሰቢያ ሕንጻ ማሠራቱ

ታላቁ ሐዋርያችን ፍሬምናጦስ በእርሱ ስብከት መነሻ በጌታ ያመኑትን በአንድ መንፈሳዊ ጉባኤ (ቤተ ክርስቲያን) አሰባሰበ፡፡ ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት ተብላ ለተሠየመችው ማኅበረ ምእመናን አመራር ሰጪ አካል የሆነ ድርጅት አቋቋመ፡፡ ለድርጅቱ ሥራ መንፈሳውያን አገልጋዮችን መርጦ በመሾም ማኅበሩን አጠናከረ፡፡ ይህን ሁሉ እያሟላ ካደራጀ በኋላ ፊቱን የመለሰው ለመሰብሰቢያና ለጽሕፈት ቤት የሚሆን ሕንጻ ወደ ማሠራት ነበር፡፡ ክርስትና ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ከተሰበከባት ከግሪክ የመጣ እንደ መሆኑ መጠን፣ ሕንጻው የት ይሠራ ለሚለው ጥያቄ ፍሬምናጦስ መልስ ነበረው፡፡ ቀደም ብሎ ይሠራበት የነበረውን ትውፊት መሠረት በማድረግ የማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት አስተዳደር ማእከልን በአክሱም መመሥረት ነበረበት፡፡

ስለዚህ ለሚጠፉት ሞኝነት፣ ለሚድኑት ግን የእግዚአብሔር ኀይል የሆነው የክርስቶስ የመስቀሉ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰበከባትና ፍሬ ባፈራባት በመዲናዋ በአክሱም ለማኅበሩ በማእከልነት የሚያገለግለው ሕንጻ እንዲሠራ ተወሰነ፡፡ እንደዚህ ላለው ጕዳይ በምርጫው ብቸኛ ሆኖ የሚቀርበው በአንድ ሀገር ወይም አውራጃ ለመጀመሪያ ጊዜ “መስቀል የተተከለበት ነው” ተብሎ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ታሪካዊ ስፍራ ለወንጌል ሥርጭትና ለምእመናን መንፈሳዊ አስተዳደር ማእከል በመሆን እንዲያገለግል ይደረጋል ማለት ነው፡፡