ከነቅዐ ጥበብ
ካለፈው የቀጠለ
ማስገንዘቢያ፡- ሥላሴን በመካድ ከሰባልዮሳውያን ቀጥሎ የሚታወቁት አርዮሳውያን፣
እግዚአብሔር በማለት በግእዝና በዐማርኛ የሚጠራው መለኮታዊ ስም እንደ ዕብራይስጡ፣ “ይሆዋ ወይም ያህዌ” መባል አለበት የሚል
አቋም በመያዝ ስለ ተነሡ በዚህ ስም አንተርሰውና አስታክከው የሚነዙትን ሐሰተኛ ትምህርት ከመሠረቱ ጀምሮ ለማፈራረስ ሲባል
በዚህ ርእስ በሚቀርበው መሠረታዊ የክርስትና ትምህርት “ይሆዋ ወይም ያህዌ” የሚለውን ቃል መጠቀም የቃላት መደናገርን
ያስወግዳል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
“ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናና ዛሬ፥ ለዘላለምም ያው ነው፡፡ እስመ ኢየሱስ ክርስቶስ
ውእቱ ዘትማልም፥ ወዮም ውእቱ፥ ወእስከ ለዓለም፡፡” ሲል የሚያስተምረው መጽሐፍ ቅዱስ ነው ዕብ. 13፥8፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ
መተርጉማንም “ትናንት” የሚለው ቃል በሁለት ክፍል ሊታዩ የሚገባቸውን የወቅት ምዕራፎችን ያሳስበናል ይላሉ፡፡ ሲተነትኑትም፡-
አንደኛ፥ ዓለም ከመፈጠሩ፣ ዘመንም ከመቈጠሩ አስቀድሞ የነበረውንና የጊዜ መነሻ ያልነበረውን
የወልድን የአኗኗር ብሉየ መዋዕልነት፥ (የዕድሜ ባለጸጋነቱን) ያመለክታል ይላሉ፡፡
“ትናንት” በሁለተኛ ደረጃ ሲታይም ዓለም ከተፈጠረ፣ ዘመንም ከተቈጠረ ጀምሮ ያለውንና
ወልድ በሥጋ ከመገለጹ በፊት የነበረውን ጊዜ ያሳስባል በማለት ያክሉበታል፡፡ አያይዘውም እነዚሁ መተርጉማን “ዛሬ” ማለት
ከሥጋዌው (ሰው ከሆነበት ጊዜ) ጀምሮ እስከ ዳግም ምጽአቱ ድረስ ያለውን ጊዜ፣ “ለዘላለም” በማለቱም ከዳግም ምጽአቱ በመነሣት
ዳርቻ የሌለውንና ለዓለመ ዓለም በመባል ብቻ የሚገለጸውን የአኗኗሩን ዘላለማዊነት ማስረዳቱ ነው እያሉ አፍታተው ይተረጉሙታል፡፡
ከቤተ አርዮስና ከቤተ አውጣኪ የበቀለው ትምህርተ መለኮት ግን የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን መገለጽ “ትናንት” በመባል ከተነገረው
አኗኗር መደብ አውጥቶ በብሉይ ኪዳን ዘመን እንኳ አልተገለጸም፣ እያለ “ዛሬ” በሚለው የጊዜ ክልል ማለት በዘመነ ሥጋዌ
ወስኖታል፡፡
ወልደ እግዚአብሔር ቃል በሥጋ ከመገለጹ በፊት በዘመነ አበው በብሉይ ኪዳን በአርኣያ
መልአክ ተገልጾ እንደነበር ከሚያስተምሩት ጥቅሶች ጥቂቶችን ባለፈው ዕትም ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በእነዚህ ጥቅሶች
በመልእክተኛነት ተገልጾ የነበረውም ፍጡር መልአክ አለመሆኑን፣ ነገር ግን ለማይገሠሥ ሥልጣነ መለኮት በባለቤትነት የሚታወቅና
ስግደትን፣ አምልኮትን፣ መሥዋዕትንና ቍርባንን … የመቀበል መብት ያለው ይሆዋ አምላክ እንደ ሆነ ራእዩን የተቀበሉት አባቶች
አረጋግጠው ማስተማራቸውና ለእኛም ማስተላለፋቸውን ጠቍመን ነበር፡፡
በማከታተልም አርዮሳውያን ወልደ እግዚአብሔር ቃል “ትናንት” በሚለው በብሉይ ኪዳን
ዘመን አልተገለጸም ለማለት የሚገፋፉት፣ በዘመነ ብሉይ ኪዳን ለአበው ምእመናን በአርኣያ መልአክ የተገለጸውን ማንነት ጥቅሶቹ ሲያብራሩ
እርሱ ፍጡር መልአክ ያይደለ፣ ነገር ግን “ይሆዋ” እንደ ሆነ አጣምረው በአጽንዖት ስለሚያስረዱባቸውና የወልድን ይሆዋነት
በመካድ የቈለሉትን የእንቧይ ካብ ትምህርታቸውን ስለሚንዱባቸው፣ የይሆዋነት ሥልጣነ መለኮትን ለኢየሱስ ክርስቶስ በመስጠት ሊሆን
የሚገባውን ከመፈጸም ይልቅ ለፍጡራን መላእክት እንዲሰጡና የአማልክትን ብዛት እንዲያስተምሩ የሚገፋፋቸው ስውር መንፈስ ለመኖሩ
ጠቋሚ እንደ ሆነ አመልክተን ነበር፡፡
እንደዚሁም ከቤተ አውጣኪ ተወልዶ እያደገ የመጣው የሃይማኖት ቡድንም፣ ወልድ በብሉይ
ኪዳን መገለጹን የሚክድበት ምክንያት በአርኣያ መልአክ ለተገለጸው ይሆዋ የተሰጠውን ስግደትና አምልኮት፣ የቀረበውን መሥዋዕትና ቍርባን
ከባለ መብቱ ከወልደ እግዚአብሔር በመንጠቅ ለማይገባውና ይህ ቡድን አጠናክሮ ለሚሰብከው የመላእክት አምልኮ (ሕርመተ መላእክት)
ለመሸለም መንገድ የሚከፍትለት እየመሰለው መሆኑን ጨምረን አስገንዝበን ነበር፡፡
ዳሩ ግን ራሱ ይሆዋ ሆኖ ሳለ በአርኣያ መልአከ እግዚአብሔር (በይሆዋ መልእክተኛነት)
ከዘመነ አበው ጀምሮ የተገለጸው ለአብርሃም ዕለቱን በማሳየት ሐሴትን የሰጠው ራሱን የአብርሃም፣ የይሥሐቅና የያዕቆብ አምላክ
ይሆዋ ነኝ ብሎ ያስተዋወቀ፣ የባርነትን ቀንበር በመስበር ለእስራኤል ልጆች ነጻነትን ያጐናጸፈ፣ በመንገድ ላይ የብርሃን ዐምድና
የደመና መጋረጃ የሆነላቸው፣ የመገባቸው፣ ተቃዋሚዎቻቸውን በመዋጋት ድል እያቀዳጃቸው መሪዎቻቸውን እያበረታታና ምሪትን እየሰጠ
ቃል የገባላቸውን ርስት ያወረሳቸው እርሱ ወልደ እግዚአብሔር ቃል እንደ ነበረ አንባብያን ካለፈው ዕትም ጥቅሶች በሚገባ
ማረጋገጥ ችለዋል ብለን እናምናለን (ዘኍ. 23፥7-10፤ 18፥24፤ 24፥3-9)፡፡
አዎን ወልደ እግዚአብሔር ቃል የመሪዎቻቸው መሪ ሆኖ በየቀየሰላቸው መንገድ የተጓዙት
እስራኤላውያን አበው ማንነቱን ዐውቀው ሰገዱለት፤ ለይሆዋ በሚገባ ክብር አከበሩት፤ መሥዋዕትን ሠዉለት፤ ቍርባንንም አቀረቡለት፡፡
የእግዚአብሔር ስም ቡሩክ ይሁን፡፡
2. በአርአያ
ኰኵሕ (በአለት ምስያ) ተገልጾ ነበር
ወልደ እግዚአብሔር ቃል በዘመነ ብሉይ ኪዳን በአርኣያ ኰኵሕ (በአለት ምስያ)
የተገለጸበት ታሪክ ከፍተኛ ቦታ የተሰጠውና አስደናቂም ነው፡፡ ሆኖም ለተወሰኑ ጕዳዮች አርኣያ መልአክን (የመልአክን ምስያ)
ገንዘብ አድርጎ ተገለጠ ሲባል፣ ፍጡር መልአክ ነበር ማለት እንዳልሆነ ሁሉ፣ በዚህ ጊዜ ደግሞ በአለት ምስያ መገለጡ ለዚህ
ለተወሰነ ጕዳይ ገንዘብ ያደረገውን ተምሳሊት ዐይነት ለመናገር እንጂ፣ ከተፈጥሮ አለት ጋር ግንኙነት ነበረው እንዳልተባለ
መቼውንም ባለ አእምሮ የሆነ ሰው አይስተውም፡፡
ደቂቀ እስራኤል በይሆዋ ነጻ አውጪነት ከግብጽ ባርነት ከተላቀቁ በኋላ በሙሴ
አገልግሎት ቀይ ባሕርን የብስ ባደረገላቸው መለኮታዊ ተኣምራት እየተመሩ ራፊዲም በሚባል ቦታ እንደ ሰፈሩ የእግዚአብሔር ቃል
ይናገራል፡፡ በረሓ አቋራጩ ሕዝብ በዚህ ስፍራ ስለ ተጠማ በሙሴ ላይ አጕረመረሙ፡፡ በሕዝቡ ቍጣ የተጨነቀው ሙሴ ችግሩን ለይሆዋ
አመለከተ፡፡ ይሆዋም የሕዝቡን ሽማግሌዎች አስከትለህ ወደዚያ አለት ሂድ፡፡ ቀይ ባሕርን በመታህበት በትር እኔ በላዩ
የምቆምበትን በኮሬብ ያለውን አለት ምታው፤ ውሃ ይወጣል፤ ሕዝቡም ይጠጣል አለው፡፡ በሙሴ ልብ ውስጥ እንዲገባና እንዲመራበት
የተሰጠው የምስጢር መፍቻ ቃል “እኔ በላዩ የምገኝበትን አለት ምታ” የሚለው ነው፡፡
በአለቱ ላይ ይሆዋ ሲታይ ሙሴ ይህን ዐይነቱን አለት ብቻ መምታት ነበረበት፡፡
እባክህን፣ አለት ያው አለት ነው ብሎ ማንኛውንም አለት ቢመታ ውሃ ሊያወጣ ይችል ነበርን? ከጥማት ለመዳን ከተፈለገ ይሆዋ
እገኝበታለሁ ያለው፣ የተጠማውን ያረካ ዘንድ ነፍስ አድን ፈሳሽን ማፍለቅ የሚችለው አለት ብቻ በሙሴ በትር መመታት ነበረበት፡፡
ሙሴም ይህን ቃል ማሰላሰል ነበረበት፡፡ ሙሴም ይህን ቃል ማሰላሰል ነበረበት (ዘፀ. 17፥1-7)፡፡ ስለዚህም እንደ ታዘዘው ይሆዋ
ለእርሱ ተገልጾ የታየበትን አለት በበትሩ መታው፤ ውሃው ፈሰሰ፤ ሕዝቡም ጠጡ (መዝ. (78)፥15-16፤ (105)፥41፤ ነህ.
9፥15)፡፡
ያ ሕዝብ ጕዞውን በመቀጠል በምድረ በዳ ሲቅበዘበዝ ለዓመታት ኖረ፡፡ ተኣምራቱን ሁሉ
አይቶ መታዘዝ ያቃተው ትውልድ በበረከት ሙላት እንዲኖርበት ወደ ተዘጋጀለት ምድረ ርስት ሳይደርስ በምድር በዳ ወድቆ ቀረ፡፡
ተተኪውም ትውልድ ጕዞውን ቀጥሎ በቃዴስ ምድረ በዳ ሰፍሮ ነበር፡፡ በዚህም ቦታ ውሃ አልነበረምና በውሃ ጥም ያረረው ዐዲሱ
ትውልድ በመሪዎቹ ላይ አጕረመረመ፡፡ መሪዎቹም ችግሩን አመለከቱ፡፡ ይሆዋም ማኅበሩ እያዩ አለቱን ውሃ እንዲያፈልቅ እዘዘው ብሎ
ለሙሴ ነገረው፡፡ ነገር ግን ሙሴ በይሆዋ ቃል ሊያዘው ሲገባው፣ የበፊቱን የአሠራር ልምድ በመከተል አለቱን በበትሩ ሁለት ጊዜ
መታው፡፡ ይሆዋ ግን ያልታዘዘውን ሙሴን እንጂ በዚህ ጕዳይ ያልበደለውን ሕዝብ ላለመቅጣት በመወሰን አለቱ ውሃ እንዲያፈልቅ
አደረገ፡፡ የማኅበሩ አባላትና እንስሶቻቸውም ከዚያ ውሃ ጠጡ (ዘኁ. 20፥1-13)፡፡
የመጀመሪያው ከአለት ውሃ የፈለቀበት ተኣምር ከታየበት ከራፊዲም (በኮሬብ) ጀምሮ
እስከ ቃዴስ በርኔ ድረስ በተንጣለለው ሰፊ በረሓ ውስጥ ውሃ የሚያፈሱ የተፈጥሮ አለቶች ቆመው መገኘታቸውን የጠቈሙ የታሪክ
ቅርስ ዐሳሾች እስከ አሁን የሉም፡፡ አለቱ ተፈጥሮኣዊ አልነበረምና በሙሴ በትር ውሃ ያፈለቁ አለቶች ዛሬ በግኡዝነታቸው
አለመገኘታቸው አያስደንቅም፡፡ የእግዚአብሔር ቃልም እንደሚያስተምረው በበረሓ ውስጥ ያን የውሃ መጠጥ የሰጣቸው፣ በበረሓ ጕዟቸው
ሲከተላቸው የነበረው አለት ክርስቶስ ነበር፡፡ “ወኵሎሙ ሰትዩ ስቴ መንፈሳዊ ዘውእቱ ዘሰትዩ እምኰኵሕ መንፈሳዊት እንተ ተሐውር
ድኅሬሆሙ፤ ወኰኵሑሰ ክርስቶስ ውእቱ፡፡ - ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ አለት ጠጥተዋልና ያም አለት ክርስቶስ ነበረ” (1ቆሮ. 10፥4)፡፡
የእስራኤል ልጆችም በበረሓው ጕዞአቸው የተከተላቸውንና የመገባቸውን፣ በሙሴ በትር
እየተመታ፣ እየቈሰለና እየደማ ለጥማታቸው ርካታ ሰጪ ውሃ ያፈለቀላቸውን አለት ማንነት በዚያ ጊዜ የተረዱ ነበሩ ማለት ይቻላል፤
እንዲህ ሲሉ ዘምረዋልና፣ “ይሆዋ አለቴ አምባዬና መታመኛዬ ነው፡፡” (2ሳሙ. 22፥2፤ መዝ. 17/18፥2፤ በተጨማሪ ዘዳ.
32፥13፤ መዝ. 80/81፥16)፡፡
በእስራኤላዊነቱ የመኵራት መብት እያለው ያልተጠቀመበት፣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጥሪ
ለሐዋርያነት የተመረጠው ቅዱስ ጳውሎስ፣ አባቶቹን ቀን በደመና መጋረጃ፣ ሌሊትም በብርሃን ዐምድ ያገለገለ፣ ሲርባቸው መና፣
ሲጠማቸውም ውሃ የሚያፈልቅ አለት ሆኖ የመገባቸው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ መግለጹ፣ ወገኖቹ ለአባቶቻቸው የተደረገውን
ውለታውን እንዳይዘነጉ ለማስታወስ ነው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እስራኤላውያን አበው የምድር በዳው ጕዟቸውና በጕዟቸው
የተደረገላቸው የእግዚአብሔር ውለታ ይታሰብ በነበረበት የዳስ ክብረ በዓል ላይ ተገኘና፣ “የተጠማ ቢኖር ወደኔ ይምጣና ይጠጣ”
በማለት፣ አባቶቻቸው የምድረ በዳውን በረሓ ሲያቋርጡ እየተከተላቸው ውሃ በማፍለቅ ያጠጣቸው አለት ታሪክ፣ እርሱን ራሱን
እንደሚያመለክት የሚያስገነዝብና ልባቸውን ወደ እርሱ እንዲያዘነብሉ የሚያደርግ ትምህርት ሰበከ፡፡ ያን ጊዜ አባቶቻቸው በአርአያ
ኰኵሕ (በአለት ምስያ) ወደተገለጠው እርሱነቱ ቀርበው ሥጋዊ ርካታን እንደተቀበሉ ሁሉ፣ አሁንም በዚያ በዓል መታሰቢያ ክብረ በዓል
ላይ የተገኙት ሁሉ የሕይወት ውሃ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን ከእርሱ እንዲጠጡና መንፈሳዊ ርካታን እንዲያገኙ ጋበዛቸው (ዮሐ. 7፥37-39)፡፡
3. ወልድ
የሕዝብ እሰራኤል መሪ መሆኑ ስለመታወቁ
ሕዝበ እስራኤል፣ ቃል በሥጋ ይገለጽበት ዘንድ የተዘጋጀ ዘር ሊሆን የተጠራ፣
የተመረጠና የተመደበ ነበር (ዘፍ. 12፥1-3፤ ዘዳ. 10፥15፤ ዮሐ. 1፥11፤ ሮሜ 9፥5)፡፡ ስለዚህ ዓለም ሳይፈጠር እንኳ
ታቅዶ በነበረው መለኮታዊ ውሳኔ መሠረት (1ጴጥ. 1፥20-21፤ ሮሜ 16፥25-27) ወልደ እግዚአብሔር ቃል የእባብን ራስ ይቀጠቅጥ
ዘንድ የሴቲቱ ዘር ሆኖ እንደሚመጣ የተነገረው ተስፋ የተሰጠው ለዚያ ለእስራኤል ሕዝብ ነበር (ዘፍ. 3፥15፤ ገላ. 4፥4)፡፡
በኀጢአት ምክንያት የመጣውን መርገም ተሸክሞና ራሱ መርገም ሆኖ፣ በርግማን ምትክ በረከትን ለምድር አሕዛብ የሚያመጣ የአብርሃም
ዘር በመሆን ይገለጥ ዘንድ፣ ቃል ኪዳን የተገባውም ለዚያው ሕዝብ ነበር (ዘፍ. 22፥18፤ ገላ. 3፥13-16)፡፡
ፍጥረትንና ሥርዐተ ተፈጥሮን ያበጣበጠውን ኀጢአት በማስወገድ፣ ሰላምን ለምድር ሊያመጣ
የሰላም አለቃና ገዥ ሆኖ ከነገደ ይሁዳ እንደሚወለድም ለዚያው ለሕዝበ እስራኤል የተስፋው ቃል ተሰጠ (ዘፍ. 49፥8-12፤ ዘኍ.
24፥17-19፤ ኢሳ. 9፥6፤ ዕብ. 7፥14)፡፡ ከዚያ በማያያዝም የይሁዳን ዘር ተከትሎ በመውርድና ከቤተ ዳዊት በመወለድ
ዘላለማዊውን ንግሥ የሚቀዳጅ ጻድቅ ቊጥቋጥ እንደሚሆንም ለዚያው ሕዝብ ተነግሮት ነበር (2ሳሙ. 7፥12-17፤ 1ዜና. 17፥11-14፤
ሉቃ. 1፥32-33)፡፡ ወልደ እግዚአብሔር ቃል በቤተ ልሔም ከድንግል እንደሚወለድ ተብራርቶ የተነገረው ለባለ ተስፋው የእስራኤል
ሕዝብ ነበር (ኢሳ. 7፥14፤ 9፥6፤ ሚክ. 5፥2)፡፡ እነዚህ ጥቅሶች ሁሉ የሚያስጨብጡን ዐበይት ቁም ነገሮች፣ አንደኛ፣ ተስፋው
የተሰጠው ለዚያ ሕዝብ መሆኑና ወደ አሕዛብ የሚተላለፈው በዚያ ሕዝብ በኩል እንዲሆን መታቀዱን፤ ሁለተኛ፣ ተስፋው የሚፈጸምበት
ዘር ከዚህ ሕዝብ መገኘት ያለበት እንዲሆን መወሰኑን ነው፡፡
በዚህ ተስፋን በተሞላ ትንቢት መሠረት ሰው ሆኖ የሚገለጽበትን ሕዝብ፣ ነገድ፣ ቤት፣
ስፍራ፣ የጠቈመ፤ ሕዝቡንም ወደዚህ ግብ ለማድረስ የመራና የተንከባከበ እርሱ ማን ነው? ቢባል እርሱማ ይሆዋ ሆኖ ሳለ በይሆዋ መልእክተኛነት
(በአርኣያ መልአከ እግዚአብሔር) ራሱን የገለጸ ወልደ እግዚአብሔር ነው ይላል የእግዚአብሔር ቃል (ዘዳ. 32፥11-14፤ መሳ.
6፥7-24፤ ዮሐ. 8፥25-26)፡፡
ለተነገረው የተስፋ ቃል፣ ለተገባውም ኪዳን መፈጸሚያ ይሆን ዘንድ የታጨው ሕዝበ
እስራኤል እንደ ሆነ ሁሉ፣ እንደ ሙሴ እንደ ኢያሱ፣ … መጋቢ ሆኖ ይህን ሕዝብ ማገልገል ማለት ሕዝቡን ለሚመራቸው ራሱ ይሆዋ
ለሆነውና በይሆዋ መልእክተኛነት (በአርኣያ መልአከ እግዚአብሔር) ለተገለጸው ወልደ እግዚአብሔር ቃል አገልጋይ፣ ሎሌ መሆን
ማለት ነው፡፡ ለሕዝበ እስራኤል ዋና ገዥና የበላይ መሪ በሆነው ወልደ እግዚአብሔር ቃል ሥር መሆንና ያን ሕዝብ ለማገልገል
መወሰን ለዋናው መሪና ገዥ ለመታዘዝ ራስን መስጠት ማለት ነው፡፡ የዚያ ሕዝበ እስራኤል ዋና መሪና ገዥ በዕብራይስጥ መሲሕ፣
በግሪክ ክርስቶስ ይባል ዘንድ ያለው ወልደ እግዚአብሔር ቃል ነበረ (ዮሐ. 1፥42)፡፡ ስለዚህም ነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ
ከመጀመሪያው አንሥቶ ለእናንተ የተናገርሁት እኔ ስለ ሆንኩ፤ ስለ እናንተ የምናገረውም፣ የምፈርደውም ብዙ አለኝ ያለው፡፡
በበላይ መሪነቱ፣ የዚያ ሕዝብ ርእስ በመሆኑ ከጥንቱ ከጧቱ መመሪያ በመስጠት፣ ሕግ በማውጣት፣ የትእዛዝ ቃል በመናገር እንደ ተናገረውም
በፈጸመውና ባልፈጸመው ዜጋ ላይ የመፍርድ ሥልጣን ያለው እርሱ ጌታ ኢየሱስ ነው (ዮሐ. 8፥25-26)፡፡
በሀገራችን ከነበረው ትምህርተ መለኮት አንዳንዱ በጊዜ ብዛት ወይቦ የቀድሞውን
መልኩንና ውበቱን ቢለውጥም፣ ለዛውንና ወዘናውን ቢያጣም፣ አንዳንዱም ቢሞት፤ ቅርጹ ወይም ዐፅሙ ከላይ ለተነገረው ሐተታ
እውነትነት ይመሰክራል፡፡ ለምሳሌ፣ “ቃለ አብ ሕያው ዘወረደ ውስተ ደብረ ሲና፤ ወወሀበ ሕገ ለሙሴ … ውእቱኬ ዘወረደ ኀቤኪ ኦ
ደብር ነባቢት፤ - በደብረ ሲና የወረደው፣ ለሙሴም ሕግን የሰጠው የሕያው እግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ደብር ነባቢት ሆይ (ድንግል
ማርምን ነው) ወዳንቺ የወረደውም ያው በደብረ ሲና የወረደው ለሙሴም ሕግን የሰጠው የአብ ሕያው ቃል ነው” (ውዳሴ ማርያም)፡፡
4. ሙሴ የክርስቶስ ሌሌ መሆኑን ስለ ማወቁ
ሙሴ የሕዝበ እስራኤል ዋና መሪና ገዥ ክርስቶስ ይባል ዘንድ ያለው ወልደ እግዚአብሔር ቃል እንደ ሆነ ያውቅ
ነበርን? ሙሴ ለማን እየታዘዘ እንደ ነበር ለይቶና አረጋግጦ ነበርን? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ ሁሉን ቻይ (ኤልሻዳይ) በሚል ስም ተዋውቋቸውና
ቃል ኪዳን ገብቶላቸው የነበረው ወልደ እግዚአብሔር ቃል፣ ለእነዚሁ አባቶች በአርኣያ መልአክ (በመልእክተኛነት) ተገልጾ ስለ ነበረ፤
የዚህ የቃል ኪዳን ታሪክ ከተሰጣቸው ተስፋ ጋር ተያይዞ በውርስ ከአባት ወደ ልጅ ከተላለፈው የቅብብሎሽ ትምህርተ እምነት ድርሻው
ለሙሴም ተላልፎለት ነበር፡፡ ሙሴም የፈርዖን ልጅ ይባል ዘንድ በሚበቃ አስተዳደግ በፈርዖን ቤት ያደገ ቢሆንም፣ በእስራኤላዊ ዜግነቱ
ለሚጠብቀው ኀላፊነት ዕጩ የሚሆንበትን ተገቢ አስተዳደግና እስራኤላዊነትን የሚያጠናበትን ትምህርት ቤት ይሆዋ
አዘጋጅቶለት ነበር፡፡ የገዛ እናቱ በሞግዚትነት እንድታሳድገው አደረገ፡፡ ስለዚህ ሙሴ ሲጐለምስ ወደ ወገኖቹ ሰፈር እንዲሄድ ያነሣሣው፣
ያ በይሆዋ ጥበብ፣ በእናቱ አስተማሪነት በልቡ ውስጥ በጥልቀት ሥር የሰደደው የዜግነት ትምህርት ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ አጥቂውን
ግብጻዊ ሙሴ ተበቀለው፡፡ ባለታላቅ ተስፋም ሆኖ ሳለ፣ ጊዜያዊ መከራ እየተቀበለ የነበረውን ወገኑን ላለመካድ
ሲል በፈርዖን ቤተ መንግሥት መቀማጠልን ባፍንጫዬ ይውጣ ከሚል ውሳኔ ደረሰና ኰበለለ (ዘፀ. 2፥1-15)፡፡
ሙሴን የፈርዖን ልጅ መባል ይቅርብኝ ለሚል ውሳኔ ያበቃውና ቤተ መንግሥቱን ወደ ኋላ
በመተው ወደ ምድር በዳ እንዲኰበልል ያደረገው ምን እንደ ሆነ የእግዚአብሔር ቃል ያብራራል፡፡ “ሙሴ ከግብጽ ብዙ ገንዘብ ይልቅ
ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን ዐስቦአልና ለጊዜው በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር
ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፡፡ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና፡፡ - እስመ አእመረ ከመ የዐቢ ትዕይርቶ ለክርስቶስ
እምኵሉ መዛግብቲሆሙ ለግብጽ፡፡” ይላል (ዕብ. 11፥24-26)፡፡ ሙሴ ይህን ውሳኔ ያደረገው ይሆዋ በኮሬብ ተራራ ገና ሳይገለጽለት፤
ገናም በፈርዖን ቤተ መንግሥት በነበረበት ጊዜ ሲሆን፤ ስለ ክርስቶስ መነቀፍን የመረጠው የክርስቶስን ተስፋ ከእናቱ በትምህርት
ስለ ተቀበለ እንደ ነበረ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
ቀጥሎም በምድያም እረኛ በነበረበት ጊዜ በምድረ በዳ በቍጥቋጦ ውስጥ የተገለጸለት
የይሆዋ መልአክ፣ “እኔ የአባቶችህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይሥሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤ ያለና የሚኖር
እኔ ነኝ” በሚል ስም በተዋወቀው ጊዜ፣ አንተ የይሆዋ መልአክ ነህ፣ እንደ ገና የአባቶችህ አምላክ ይሆዋ ነኝ ትለኛለህን?
እንዴት እንደዚህ ሊሆን ይችላል? ለሚል ጥያቄ የሙሴ ልብ አልተነሣሣም፡፡ በይሆዋ መልአክ አምሳያ የተገለጠለት ራሱ ይሆዋ
መሆኑንና እርሱም ወልደ እግዚአብሔር ቃል እንደ ሆነ ተረድቶ ነበር (ዮሐ. 5፥45-46)፡፡ ስለዚህ “አንተና የእስራኤል
ሽማግሌዎች ወደ ፈርዖን ግቡ፤ የዕብራውያን አምላክ ይሆዋ ተገልጦልናልና ለአምላካችን ለይሆዋ እንሠዋ ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ
እንድንሄድ ልቀቀን በሉት” ሲባል ታዘዘ (ዘፀ. 3፥18)፡፡
ወልደ እግዚአብሔር ቃል፣ ክርስቶስ ሊሆን በሥጋ እንዲገለጽበት የተመረጠው፣ የተጠራውና
በምርጫም በጥሪም የእግዚአብሔር ሕዝብ የተደረገው ሕዝበ እስራኤል እንደ ነበረ ተመልክተናል፡፡ እንግዲህ ይህን ሕዝብ ማገልገል
ማለት ሕዝቡን በበላይነት ለመምራት በይሆዋ መልእክተኛ አምሳያ ለተገለጸው ወልደ እግዚአብሔር በሎሌነት ማደር ማለት እንደ ሆነ
ሙሴ ዐውቆ የይሆዋ ባሪያ ሙሴ መባልን መረጠ (ዘኍ. 12፥7 ኢያ. 1፥1)፡፡ ለዚህ የሥራ ቦታ የከፈለው ዋጋ የፈርዖን ልጅ
መባልን መተው ነበር፡፡
ስለ ክርስቶስ መነቀፍን በራሱ የውዴታ ውሳኔ የተቀበለው ሙሴ ስለ እርሱ ብሎ ከሕዝቡ
ጋር መከራ ሊቀበልለት የመረጠውን ክርስቶስን አያውቀውም፤ አልተገለጸለትም ማለት እንዴት ይቻላል? የእግዚአብሔር ቃል ሙሴ ስለ
ክርስቶስ መነቀፍን መረጠ ይላልና! ሙሴስ ስለ ተማረው አመነው፤ መረጠው፡፡ ስለ ተገለጠለትም ዐወቀው፤ ስላወቀውም ታዘዘው፡፡
ሙሴ ከእርሱ በፊት የነበረው ወልደ እግዚአብሔር ቃል ከእርሱ በኋላ እንደርሱ ያለ ሰው
ሆኖ በመሲሕነት እንደሚገለጥ ለሚመራው ሕዝበ እስራኤል በግልጽ በዐዋጅ አሳውቆ ነበር (ዘዳ. 18፥15-19)፡፡ ጌታ ኢየሱስ
ክርስቶስም ሙሴ እንደ ሰበከለት ሆኖ በመጣ ጊዜ በነቢይነቱ የምታምኑት ሙሴ የጻፈው ስለኔ ነው አለ (ዮሐ. 5፥46)፡፡
በቅዱሱ ተራራ ላይ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብሩን ሲገልጽም ይኸው ሙሴ ከኤልያስ ጋራ
በሥነ ሥርዐቱ ላይ እንዲገኝ ተደረገ፡፡ ያ ከእርሱ ጋር የሠራውና የእርሱ አለቃ የነበረው፣ ከእኔ በኋላም እንደኔ ያለ ሰው ሆኖ
ይመጣል ያለው ታላቁ መሪ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሆነ እንዲያረጋግጥና የሚገባውን ክብር እንዲሰጠው በሐዋርያት ተወካዮች
መካከል ተገኘ (ሉቃ. 9፥30-36)፡፡ ሙሴ የሚሰጠው ምስክርነት ዐብሮት ከሠራ ጭፍራ የሚነገር ምስክርነት ጭምር ስለ ሆነ
ምስክርነቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ ነበረው (1ዮሐ. 1፥1-3)፡፡
ከብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን በመሸጋገር ላይ የነበሩ ሰዎች ሙሴና ነቢያት
የጻፉለትን ክርስቶስን (መሲሕን) አገኘነው እኮ! እያሉ በሙሴና በነቢያት ቅስቀሳ ክርስቶስን ለማግኘት በምን ያህል ናፍቆት
ሲጠባበቁ ቈይተው እንደ ነበረ አያመለክተንምን? (ዮሐ. 1፥46)፡፡ ሙሴ ለወልደ እግዚአብሔር ቃል ጭፍራው ሆኖ አገልግሎአልና
አለቃና ጭፍራም ሆነው ሕዝበ እስራኤልን መርተዋልና፤ የዚህ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ቅኔና የበጉ ቅኔ በሰማይ እንኳ በአንድነት
ይዘመራሉ (ራእ. 15፥3-4) ጌታ ይክበር!!
5. የእስራኤል ሕዝብ በክርስቶስ ስለመመራቱ
ሕዝበ እሰራኤል በአንድ በኩል ወልደ እግዚአብሔር ቃል፣ ክርስቶስ ሊሆን በሥጋ ይገለጽበት ዘንድ የተጠራ፣
የተመረጠና የተዘጋጀ ሕዝብ ሲሆን፣ በሌላ መልኩ ራሱ ወልደ እግዚአብሔር ቃል ለዚህ ታለቅ ተልእኮ የተመረጠውን ሕዝብ ከእርሱ
በሥጋ ወደሚገለጽበት ስፍራና ጊዜ እስኪያመጣው ድረስ፣ እንደ ይሆዋ መልአክ ሆኖ ይመራውና ይንከባከበው ነበረ ማለት ነው፡፡
ክርስቶስ በሥጋ ከእርሱ ይወለድ ዘንድ የተመረጠውና የተጠራው ሕዝብም በዘመናት መካከል፣ በረጅም የታሪክ ጐዳና ውስጥ እየተጓዘ ያለፈው
በወልደ እግዚአብሔር ቃል ምሪትና በሥጋ ከእርሱ እንደሚወለድ ከተሰጠው ተስፋ ጋር በመጓዝ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ለዘመናት
ከክርስቶስ ጋር የተጓዘ ሕዝብ፣ ወይም ክርስቶስን ይዞ የተጓዘ የክርስቶስ ሕዝብ ተብሎ ይታወቅ ዘንድ ተገቢው ሆነ፡፡
ክርስቶስ ሆኖ ለመገለጥ በሥጋ ከእርሱ ወደሚወለድበት ውሱን ጊዜና ውሱን ስፍራ
ለማድረስ ያን ሕዝብ በአርኣያ መልአክ የመራው ማን ነበር? እንዳይባል ክርስቶስ የሚሆነው ራሱ ወልደ እግዚአብሔር ቃል እንደ ነበር
አይተናል፡፡ ይህም የታመነ እውነት ሕዝበ እስራኤልን የክርስቶስ ሕዝብ አሰኘው፡፡ በዚህ በታመነ እውነት ላይ ከተመሠረተው ተስፋ
ውጪ የነበሩት ሌሎች ሕዝቦች ያለ ክርስቶስ የኖሩ አሕዛብ ተብለው ታወቁ፡፡ ስለዚህም ጕዳይ መጽሐፍ የሚለውን እናንብብ፡፡
… ስለዚህ እናንተ
አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ዘንድ ያልተገረዙ የተባላችሁ ይህን አስቡ፡፡ በዚያ ዘመን
ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ፥ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ፥ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ፥ ከእግዚአብሔርም
ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ፡፡ አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም
ቀርባችኋል፡፡ … መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፤ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምሥራች ብሎ ሰበከ፡፡ - ወተዘከሩ
እንትሙ አሕዛብ ወኢተአምርዎ ለክርስቶስ ውእተ አሚረ፤ ወነኪራን አንትሙ እም ሕገ እስራኤል፤ ወነግዳን እምሥርዐተ ተስፋ፥ ወኢተአምርዎ
ለእግዚአብሔር በውስተ ዓለም፡፡ ወይእዜሰ ባሕቱ አንትሙ እም ትካት ርሑቃን ቀረብክሙ በደሙ ለክርስቶስ … መጽአ ወወሀበነ ሰላመ
ለርሑቃን፤ ወሰላመ ለቅሩባን፡፡ (ኤፌ. 2፥11-19)፡፡
ሕዝበ እስራኤል፣ ወልደ እግዚአብሔር ቃል በሥጋ የሚወለድበትና ክርስቶስ (መሲሕ) ሆኖ
የሚገለጽበት ሕዝብ እንዲሆን በእግዚአብሔር ምርጫ መመደቡን በመመልከት ከዘመነ ሥጋዌ በፊት ከክርስቶስ ጋር የነበረ የክርስቶስ
ሕዝብ ተባለ፡፡ ሕዝብ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሰጠውን የተስፋ ሰንደቅ ዐላማ እያውለበለበ፣ ዘመናትንና ታሪክን እየቈራረጠና
እየተመመ የተጓዘ፤ በዚያውም ላይ በአርኣያ መልአከ እግዚአብሔር (በይሆዋ መልእክተኛነት አምሳያ) ራሱ ወልደ እግዚአብሔር እየመራው
ክርስቶስ ሆኖ ወደሚገለጽበት ውሱን ጊዜና ውሱን ስፍራ አደረሰው፡፡ ስለዚህም በመልእክተኛነት የመራው ራሱ ክርስቶስ ሆኖ
እንደሚገለጽ በእምነት የተቀበለው - ጫፉን የጨበጠውና ፍጻሜውን እስኪደርስበት የናፈቀው የተስፋ ግብ፣ “የክርስቶስ ሕዝብ -
ከክርስቶስ ጋር በክርስቶስ መሪነት የተጓዘ ሕዝብ” የመባሉን ተገቢነት አጕልቶ አሳየለት፡፡ ለእርሱ ከተሰጠው ተስፋ በስተ ማዶ
የነበረው ሕዝብ ደግሞ፣ “ያለ ክርስቶስ፣ ያለ እግዚአብሔር፣ ያለ ተስፋ በሩቅ የኖረ ሕዝብ ነበረ” ማለት ነው፡፡
ሆኖም ወልደ እግዚአብሔር በአርኣያ መልአከ እግዚአብሔር የሚገለጽበት ጊዜ አብቅቶና
የሚታይ፣ የሚዳሰስ ሆኖ በሥጋ የሚገለጽበት ጊዜ ሲደርስ፣ ሕዝብና አሕዛብን የዋጀበትን ደሙን ካፈሰሰና የዕርቅና የደኅንነት
ወንጌል ለሁሉም ከተሰበከ በኋላ፣ በወንጌል የስብከት ሞኝነት ያመኑትን ሁሉ ከሥጋ በሥጋ በመወለድ የሚወረሰውን ተፈጥሮኣዊ ባሕርያቸውን
ለወጠ፡፡ በትውልዳቸው ከአረማውያን ወገን የሆኑት የኤፌሶን ሰዎችም እንደ ሌሎቹ አሕዛብ፣ ከአይሁድ ጋር በአንድ ጥላ ስር ሆነው
እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ የክርስቶስ ኢየሱስ ሕዝብ ናቸው የሚያሰኝ ማኅተም ታተመባቸው፡፡ ጳውሎስ ያብራራው ይህን ነበር (ሐ.ሥ.
19፥10፤ 17፥18፤ ኤፌ. 1፥13፤ 3፥1-6)፡፡
6. የብሉይ ኪዳን
ምእመናን ለወልድ የሰጡት ስፍራ - ይሆዋ ብለውታል
የብሉይ ኪዳን ምእመናን መሪዎች በአርኣያ መልአከ እግዚአብሔር የተገለጠላቸውን ወልደ
እግዚአብሔርን ምን ያህል ተረድተዉት እንደ ነበረና ለምእመናንስ እንዴት እንዳስረዱ ለማረጋገጥ የሚቻለው፣ ከእግዚአብሔር ቃል
ብቻ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ነውና (ሮሜ 15፥4፤ 2ጴጥ. 1፥20-21)፡፡
እያንዳንዳችን በየነበርንበት ሃይማኖታዊ ማኅበረ ስብእ በተለምዶ ይባል የነበረውን፣
ምንም ይሁን ምን፣ ወርሰን እናድጋለን፡፡ ውርሱ ትውፊት ይባላል፡፡ የወረስነውም ትውፊት ሁለንተናችንን ይዋሐድና ይወርሰናል፡፡
አንዳንዴ ወይም ብዙ ጊዜ በአመዛዛኝ አእምሮ ትውፊትን የምንወርስ መሆናችን ይቀራል፡፡ በትውፊት የምንወረስ የትውፊት ርስት
እንሆንናም ወደ ግኡዝነት የተለወጥን እንመስላለን፡፡ በዚህ ምክንያት የእግዚአብሔርን ቃል ስናጠና፣ የቃሉን ትርጕም ከወረስነው
ትውፊት ጋር ለማስማማት እንሞክራለን፡፡ እንዲያውም ትውፊቱ የበላይነቱን እንዲይዝ፣ የእግዚአብሔርም ቃል ለትውፊቱ እንዲገዛ
እናደርጋለን፡፡ ለወረስነው ትውፊት አልገዛ ያለውን የእግዚአብሔርን ቃል በልባችን ስፍራ አንሰጠውም፤ እናሳድደዋለን፤
እግዚአብሔር ይቅር ይበለን፡፡ በብሉይ ኪዳን ወልድ አልተገለጸም የሚባለውም የትውፊት እንቧይ ካብ እንዳይናድብን ለማድረግ
ካልሆነ በቀር የእግዚአብሔር ቃል ድጋፍ የለውም፡፡ እናስተውል!!
የብሉይ ኪዳን ምእመናን በዘመሩት ዝማሬ፣ በተቀኙት ቅኔ፣ ባቀረቡት መሥዋዕትና ቍርባን፣
ባደረሱት አምልኮ በጸለዩት ጸሎት እግዚአብሔር አብን ብቻ ሳይሆን ወልደ እግዚአብሔር ቃልን በተለየ ህላዌውና አካላዊ ግብሩ ምን
ያህል ከፍ ከፍ እንዳደረጉት ለመረዳት የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት ማስመስከር አለብን፡፡ አንባቢ ወደ ብዙ መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች
ሳይዘዋወር በአንድ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍና በአንድ የዐዲስ ኪዳን መጽሐፍ ላይ ዐይኑን አሳርፎ ማገናዘብ ይችል ዘንድ፣
ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ከተጻፈ መልእክት ከምዕራፍ አንድ ከ ቍጥር 6 - 13 ያሉትን ቍጥሮች ከመዝሙር መጽሐፍ ጋር
በማመሳከር ግንዛቤ እንዲወስድ ይጋበዛል፡፡
ዕብ. 1፥6 “ወይሰግዱ ሎቱ ኵሎሙ መላእክተ እግዚአብሔር - ሁሉም የእግዚአብሔር
መላእክት ለእርሱ ይስግዱለታል” ተብሎ በመዝ. 96/97፥7 የተጻፈው ቅኔ፣ ወልደ እግዚአብሔር ቃልን የሚያመለክት መሆኑን ገልጾ
የዕብራውያን መልእክት ጸሓፊ ትምህርት ሰጥቶበታል፡፡ በዚሁ መዝሙር በቍጥር 1 እና 2 “ይሆዋ ነገሠ፤ ምድር ሐሤትን ታድርግ፤
ብዙ ደሴቶችም ደስ ይበላቸው፡፡ ደመና ጭጋግም በዙሪያው ናቸው፤ ጽድቅና ፍርድ የዙፋኑ መሠረት ናቸው፡፡” በማለት ይጀምርና ዝቅ
ብሎ በቍ. 7 ላይ እንዲህ ይላል፡-“ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ ሁሉ፥ በጣዖቶቻቸውም የሚመኩ ይፈሩ፥ መላእክቱም ሁሉ ስገዱለት
(ይሰግዱላታል)” ካለ በኋላ፣ እንደገና በቍ. 9 ላይ፣ “አንተ ይሆዋ በምድር ላይ ሁሉ ልዑል ነህና፤ በአምልኮትም ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ብለሃልና”
እያሉ እስራኤላውያን መዘምራን ስለ ይሆዋ ክብር፣ መንግሥት፣ ሥልጣን፣ ፍርድ፣ ታላቅነት፣ ፍጹምነትና ዘላለማዊነት በመናገር፣
በመንፈስ ሆነው የመዝሙር ስንኝ እንደ ቋጠሩ እናገኛለን፡፡
እስራኤላውያን መዘምራን በዚህ ዝማሬ ማንን እንደ ወደሱ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ
በዕብራውያን መልእክት ጸሓፊ በኩል ተርጉሞ ሲያስተምር፣ “ወአመ ካዕበ ፈነዎ ለበኵር ውስተ ዓለም፥ ይቤ ይሰግዱ ሎቱ ኵሎሙ መላእክተ እግዚአብሔር - ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ የእግዚአብሔር መላእክት ሀሉም ለእርሱ
ይሰግዱለታል” ብሏል፡፡
ያለ እናት፣ ያለ ጊዜ በተወለደበት ቀዳማይ ልደት የአብ በኵርና አንድያ ልጅ የሆነው
ወልደ እግዚአብሔር ቃል፣ ያለ አባት በቍጥር በሚታወቁ ዘመናት ውስጥ ከድንግል በሚወለድበት ደኃራዊ ልደቱ ወደ ዓለም ሲገባ፣
ወይም በዳግማይ ምጽአቱ ለዘላለማዊ ንግሥ ሲገለጥ ለሚሆነው ክብሩ የቀረበ ዝማሬ ነው፡፡ በዚህ የዝማሬ ቃል ውስጥ “ይሆዋ”
እየተባለ የተወደሰውና “መላእክት ይሰግዱለታል” የተባለው ወልደ እግዚአብሔር ቃል መሆኑ አልተብራራምን?
ዕብ. 1፥7 “ዘይሬስዮሙ ለመላእክቲሁ መንፈሰ፤ ወለእለ ይትለአክዎ ነደ እሳት -
መላእክቱን መንፈስ፣ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ” ሲል በመዝ. 103/104፥4 ዘማሪው ከፍ፣ ከፍ ያደረገው፣
ወልደ እግዚአብሔር ቃልን እንደ ሆነ አሁንም የዕብራውያን መልእክት ጸሓፊ ይተረጉምልናል፡፡
በዚህ መዝሙር በቍጥር 1 ላይ “ነፍሴ ሆይ ይሆዋን ባርኪ፤ ይሆዋ አምላኬ አንተ እጅግ
ታላቅ ነህ!” በማለት ይጀምርና፥ ይሆዋ መላእክቱን መንፈስና የእሳት ነበልባል አድርጎ እንደ ፈጠራቸው፤ ወይም እነርሱን
ለሚያሰማራበት ተልእኮ ተስማሚ ይሆኑ ዘንድ ባሕርያዊ ተፈጥሮኣቸውን ከነፋስና ከእሳት እንደ ሠራላቸው ዘማሪው በመንፈስ ቃኘ፡፡ ዘማሪው
ነፍሱ ልታመሰግነው እንደሚገባ በመገንዘብና ራሱን ለውዳሴ በማነቃቃት እንዲህ በማለት ሲዘምር የዝማሬውና የውዳሴው ተቀባይ
ያደረገው፣ የመላእክት ፈጣሪ ይሆዋ እያለ የተቀኘለት ወልደ እግዚአብሔር ቃል መሆኑን የዕብራውን መላእክት ጸሐፊ አረጋገጠልን፡፡
ከፍ ብሎ እንደ ተገለጸው “መላእክት ይሰግዱለት ወይም ይሰግዱለታል” ሲባል፣
የሚሰግዱለት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ እነርሱ ሊሰግዱለት ተገቢያቸው የሆነው፣ እርሱም ስግደትን ሊቀበል ተገቢው የሆነው፣
መላእክት እንደ ሌሎቹ ፍጥረታት ሁሉ በቃልነቱ ከዊን (የአብ አካላዊ ቃል በመሆኑ) በትእዛዙ ስለ ተፈጠሩ እንደ ሆነ በመግለጽ የምስጢሩን
መክፈቻ ይነግረናል፡፡
ዕብ. 1፥10 “… ጌታ ሆይ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፣ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ
ናቸው” ተብሎ በመዝ. 101/102፥25-27 የተዘመረው ስለ ወልደ እግዚአብሔር ቃል ነው የሚለን አሁንም የዕብራውያን መልእክት
ጸሓፊ ነው፡፡ ይህ ጸሓፊ ከፍ ብሎ በቍጥር 8 እና 9 ላይ - ሥግው ቃል (ሰው የሆነው ቃል) ክርስቶስ ይሆን ዘንድ
በእግዚአብሔር ተቀብቶ መሾሙን ሲያብራራ፣ “እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ” ብሎ ነበርና በሰውና
በእግዚአብሔር መካከል መኖር ለሚገባው ለመሲሕነት የሥራ መደብ ሰው ከሆነ በኋላ ተቀባ፣ ተሾመ ቢባልም በመለኮት ሙላት፣ በይሆዋነት
ደረጃ ያለ (የሚገኝ) መሆኑን ለማስረዳት ከጥንት ምድርን የመሠረተ ሰማይንም ያጸና፣ በሰማይና በምድር
ያሉትን ሁሉ መላእክትን ጨምሮ ሁሉን የፈጠረ እርሱ እንደ ሆነ በብሉይ ኪዳን ታውቆ ተዘመረለት ይለናል፡፡
በተጠቀሰው መዝሙር 101/102 በቍጥር 1 ላይ “ይሆዋ ጸሎቴን ሰማ” በቍጥር 15
እና 16 ላይ “ይሆዋ አሕዛብ ስምህን፣ ነገሥታትም ሁሉ ክብርህን ይፈራሉ፡፡ ይሆዋ ጽዮንን ይሠራታልና በክብሩም ይገለጣልና፡፡”
በቍጥር 25-27 ላይ፣ “አቤቱ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፡፡ … አንተ ግን ያው አንተ
ነህ፡፡” በማለት ክብር፣ ውዳሴና ዝማሬ ያቀረበው ልዑል ለሆነው ይሆዋ ነው፡፡ እንደዚህ የተዘመረለት ይሆዋም ወልደ እግዚአብሔር
ቃል ነው፡፡
በዘመናት መካከል ያለፉት የብሉይ ኪዳን ምእመናን ሁሉ በጅምላ መዘምራኑን ተከትለው
ዝማሬውን ቢያስተዛዝሉና ቢያስተጋቡም፣ በመንፈስ የሆኑት ብቻ የሥጋ መጋረጃን ዐልፈው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በመግባት የዝማሬውን፣
የምስጋናውንና የክብሩን ባለቤት ጌታ እግዚአብሔር ወልድን አይተውታል፤ አስተውለውታል ብለን እናምናለን፡፡ በሥጋ የሆኑት ግን ዝማሬውን
እያዜሙ የውዳሴያቸው አድራሻ ለማን እንደ ሆነ ሳያዩ ከመቅደሱ ውጪ በአደባባይ ቀሩ (1ቆሮ. 2፥8)፡፡ ዛሬም በዐዲስ ኪዳን
ዘመን ቢሆን ማለት በመንፈስ ቅዱስ የተጻፈው የዕብራውያን መልእክት ለንባብ፣ ለትምህርት፣ ልብንም ለማቅናት ከበቃ በኋላ፣ በሥጋ
የሆኑት ሁሉ ወልደ እግዚአብሔር ቃል በብሉይ ኪዳን ዘመን ልዩ ልዩ የተምሳሊት መልክን (አርኣያን) ገንዘብ አድርጎ በራሱ ይሆዋ
የመባል ክብሩን እንደ ያዘ ተገልጾ የነበረ መሆኑን መቼ ተገንዘቡት?
ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠ ወልደ እግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ እርሱም በመጽሐፍ ቅዱስ
ውስጥ በሙሉ ክብሩ የተገለጠ ይሆዋ ነው!! በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህን ማየት ያልቻሉ ወገኖች የሚያዩበት ብርሃን እስኪያገኙ
ድረስ ይጸልዩ (ማቴ. 20፥29-34፤ ዮሐ. 9፥25)፡፡
በጮራ ቍጥር 7 ላይ የቀረበ
No comments:
Post a Comment