Sunday, April 21, 2013

የመዳን ትምህርትካለፈው የቀጠለ
የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመፀነስና በመወለድ ኀጢአተኛ ባሕርይን ስላልወረሰ ከሰይጣን ቍራኛነት ነጻ ነበረ፡፡ ሁሉን እንዲገዙ ሥልጣን ተሰጥቷቸው የነበሩት አዳምና ሔዋን ሁሉን ከሚያስገዛው ሥልጣናቸው ጋር ለሰይጣን በማደራቸው ምክንያት ሰይጣን የእነርሱን የገዥነት ሥልጣን እንዲወርስና የዚህ ዓለም ገዥ፥ የዚህ ዓለም አምላክ እንዲሆንና እንዲባል አበቁት (ዮሐ. 12፥31፤ 16፥11፤ 2ቆሮ. 4፥4)፡፡ ምድርንና ከእርሷ ሥርዐተ ተፈጥሮ ጋር የተያያዘውን ሁሉ ለመግዛት ከተሰጣቸው ሥልጣን ጋር በሰይጣን ገዥነት ሥር በወደቁት በእነዚህ ወላጆቻችን ምክንያት ሰይጣን ምንም የዚህ ዓለም ገዥ ወይም አምላክ ቢባልም በዚህ ዓለም ውስጥ ከአዳምና ከሔዋን ዘር ተወልዶ ሳለ፥ ኀጢአተኛ ባሕርይን በመንፈስ ቅዱስ አሠራሩ ለይቶ በመተውና ባለመውረሱ ምክንያት ብቻ ሰይጣን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ አለኝ የሚለው የሥልጣን ጥያቄ አልነበረም (ዮሐ. 14፥30)

ኀጢአተኛ ባሕርይን ሳይወርስ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ፍጹም ሰው የሆነው ቃል (ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ) በልደት ፍጹም ቅዱስ እንደ ሆነ ሁሉ በኑሮውም ሁሉ በሰውና በአባቱ ፊት ፍጹም ቅዱስ ነበረ (ሉቃ. 2፥40-52)፡፡ በጠላትነት የተነሡበት ሁሉ እንኳ እርሱን የሚከሱበት ምክንያት ስሕተት አላገኙበትም (ሉቃ. 23፥13-17፤ ዮሐ. 8፥46፤ 18፥38፤ 19፥4-6)፡፡ በቃሉም ፍጹም ቅዱስ እንደ ነበረ የእግዚአብሔር ቃል ይመሰክራል (ኢሳ. 53፥9፤ 1ጴጥ. 2፥22-23)፡፡

Thursday, April 11, 2013

የመዳን ትምህርትከናሁ ሠናይ
ካለፈው የቀጠለ

በኀጢአት ውስጥ የተዘፈቀውን የሰውን ዝርያ ከኀጢአቱና ኀጢአቱ ካመጣበት ፍርድ ለማዳን፥ ለመቀደስና ዓለም ሳይፈጠር ታቅዶለት ወደ ነበረው የክብር ስፍራ ለመመለስ (ማቴ. 25፥34) እግዚአብሔር የተጠቀመበት መንገድ

1.     ጻድቅና ቅዱስ አፍቃሪም በሆነው በአምላካችን ዙፋናዊ ችሎት ኀጢአትን ለመቅጣት ተገቢ የሆነው ፍርድ እንዲፈጸም፡፡
2.    ከምድር ዐፈር ለተሠራው ሰው ለሥጋና ለደሙ ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔር እስትንፋስ ለመጣች ሕያዊት ነፍሱ በዕሴት የተመጣጠነ ልዋጭ (ቤዛ) መስጠት ተገቢ ሆኖ እንደ ተገኘ ባለፈው ጮራ ቍጥር 5 በዚሁ ርእስ ስር ገልጠን የነበረ መሆኑን አንባቢ ያስታውሳል፡፡

ከዚህ በማያያዝም ከእግዚአብሔር በታደለው የመዓርገ ተፈጥሮ ከፍተኛነት የተነሣ
ሀ. ከዓለምና በውስጡ ካሉት የሀብት ክምችቶች ሁሉ፥
ለ. በሥጋና በደም ከሚንቀሳቀሱ እንስሳት፥ አራዊት፥ አዕዋፍ፤ በባሕርም ከሚርመሰመሱ ፍጥረታት ሁሉ፥
ሐ. መናፍስት ሆነው ከተፈጠሩት ሠራዊተ መላእክት ሁሉ ለሰው በዕሴት የተመጣጠነ ተውላጥ (ቤዛ) እንዳልተገኘለት፤ ነገር ግን ሰው ለሆነው ወልደ እግዚአብሔር (ሥግው ቃል) ብቻ ይህ ጕዳይ የሚቻልና የሚገባም ሆኖ እንደ ተገኘ (ራእ. 5፥1-14) በዚያው ክፍል መቅረቡ ይታወቃል፡፡

Monday, April 1, 2013

ክርስትና በኢትዮጵያ


የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ
 ከነቅዐ ጥበብ
ካለፈው የቀጠለ

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የተገኘውን ድኅነትና በትንሣኤው የተጨበጠውን ጽድቅ የሚያበሥረውን ወንጌል በኢየሩሳሌም በይሁዳ በሰማርያ በዓለሙ ሁሉም እንዲያሠራጩ ኀላፊነት የተሰጣቸውና ራሳቸውንም ለዚሁ ሥራ የለዩ ዐሥራ አንድ ሐዋርያትና (ይሁዳ ተቀንሶ) ጥቂት ተባባሪዎች ነበሩ (ሉቃ. 24፥33-34) ከሐዋርያት ጋር የተባበሩ ናቸው ከሚባሉትም መካከል 70 ደቀ መዛሙርት ከፍተኛውን ቍጥር ሳይዙ አይቀሩም (ሉቃ. 10፥1)፡፡ እንደዚሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከርኩሳን መናፍስት አገዛዝ ነጻ ያወጣቸው የኀጢአትን ስርየት የሰጣቸው፥ ያደረጋቸውን ተኣምራትና መንክራት በማሳየትና በነቢያት ትንቢት መሠረት ዓለምን ሊያድን የመጣ መሲሕ (ክርስቶስ) እንደ ሆነ ከስብከቱ፥ ከሥራውና ከአኗኗሩ በመረዳት እያገለገሉት ከገሊላ ጀምሮ ይከተሉት የነበሩት ሴቶች ታክለውበት (ማቴ. 27፥55-56፤ ማር. 16፥9-11፤ ሉቃ. 7፥36-50፤ 24፥22-24) የጌታ የኢየሱስ እናትም ተጨምራ የሐዋርያቱንና የተባባሪዎቹን ቍጥር ወደ 120 አድርሰውት ነበር (ሐ.ሥ. 1፥8-15)፡፡
  
“ከኢየሱስ ጋር የነበሩ” በመባል ለሚታወቁት ተከታዮቹ በሥጋና በደም ሊሠራ የማይቻለውን የታላቁን ተልእኮ ኀላፊነት ይወጡ ዘንድ የሚመራቸውን፥ የሚያጽናናቸውን፥ በውስጣቸውና ከእነርሱ ጋር ሆኖ እውነትን ሁሉ በማሳወቅ የሚያሳድጋቸውን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ጌታ በኀምሳኛው ቀን አፈሰሰላቸው (ዮሐ. 14፥16፤ 17፥26 ሐ.ሥ. 2፥1-4)፡፡ ከዚህ በኋላ በሕይወትና በቃል የሰጡት ምስክርነት የጌታን ቃልም በማስተዋልና ለሰሚዎች በማስተላለፍ የታየባቸው ለውጥ ራሱ ተአምር እንደ ነበረ በሐዋርያት ሥራ በግልጥ የሚነበብ ታሪክ ነው (ሐ.ሥ 4፥13)፡፡