የጋብቻ ትምህርት
“እግዚአብሔር መረጠ” (1ቆሮ. 1፥27)
“ነገር ግን የዘመኑ
ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ፡፡” (ገላ. 4፥4) በአብርሃምና በሣራ፥ በይሥሐቅና በርብቃ፥ እንዲሁም በያዕቆብና በሚስቶቹ
የጋብቻ ሕይወት ጥናታችን ውስጥ ግንኙታነቸው፥ ጥንካሬዎችና ድክመቶች እንደ ክርስቲያንነታችን ልንገነዘባቸው የቻልን የተለያዩ ትምህርቶች
እንደ ነበሩ እናስታውሳለን፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ውድ ልጁን በሕፃንነቱም ሆነ በወጣትነቱ ወቅት ሊያስተናግድ የሚችል ቤት ለመሥራት
ምን ዐይነት ቤተ ሰብ መረጠ? እግዚአብሔር ለዚህ ታላቅ ነገር በሚመርጣቸው በእነዚህ ሰዎች ሕይወት ውስጥ እርሱን የሚያስደስቱ መልካም
ባሕርያትን በርግጥ እናያለን፡፡ በዚህም የክርስቲያናዊ ጋብቻ ጥናታችንን መሆን በሚገባው መጠን ልናዳብረው እንችላለን፡፡
ፍሬ በአንድ ዕለት አይበስልም
ከጋብቻ ችግሮች ሁሉ
የገንዘብ ዕጦት ዋናው እንደ ሆነ የሚታመን ቢሆን እግዚአብሔር ለልጁ እናት እንድትሆንለት ሀብታም ሴትን ወይም ባለጸጋ አሳዳጊ አባትን
እንዳልመረጠ ልብ ማድረግ ይጠቅማል፡፡ ምክንያቱም ዮሴፍ፥ “ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልንን?” በማለት ናትናኤል “በእውነት
የእስራኤል ሰው” (ዮሐ. 1፥46) የተነገረላት የተናቀችዋ የናዝሬት ከተማ ኗሪ የሆነ ተራ ሠራተኛ ወይም ዕንጨት ጠራቢ ሰው ነበረና
ነው፡፡ ማርያምም እንደ ዮሴፍ ሁሉ በናዝሬት ከተማ ትኖር የነበረች የዓለምን ነገር ገና ያልተገነዘበች ድንግል ነበረች፡፡ ልጇ የሚወለድበት
ጊዜ ሲቀርብ ማርያምም ሆነች ዮሴፍ በራሱ ቅድመ አያቶች ከተማ በቤተ ልሔም በነበሩበት ጊዜም እንኳ ተመልሰው የሚገበቡት የራሳቸው
የሆነ ንብረት ወይም ሀብት የነበረው የታወቀ ዘመድ አልነበራቸውም፡፡ ሕፃኑ የተወለደው በግርግም ውስጥ ነው፡፡ ሕፃኑን በቤተ መቅደስ
ውስጥ ለጌታ ለመስጠት ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄዱ መሥዋዕት ይዘው የሄዱት “ሁለት የዋልያ ወይም ሁለት የዕርግብ ጫጩቶችን” ነበር፡፡
እንደዚህ ዐይነቱ ስጦታ የጠቦት መሥዋዕት ማቅረብ የማይችሉ እጅግ የደኸዩ ሰዎች የሚያቀርቡት መሥዋዕት እንደነበር በሕግ መጽሐፍ
ተጠቅሷል (ዘሌ. 12፥8)፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከሰብአ ሰገል ጕብኝት ቀጥሎ በዚያን ጊዜ የይሁዳ ንጉሥ ከነበረው ከሄሮድስ የጭካኔ
ሥራ ለማምለጥ ዮሴፍና ማርያም ወደ ግብጽ እንዲሄዱ ተነገራቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ምናልባት ለችግራቸው ይሆናቸው ዘንድ የወርቅ ስጦታዎችን፥
ዕጣንና ከርቤ በእግዚአብሔር ርዳታ ሳያገኙ አልቀሩም፡፡ ለዚህ በተለየ መንገድ ለተመረጠ የኑሮ ጉድኝት በገንዘብ ችግር ምክንያት
መጠለያ መጥፋቱ እግዚአብሔር፥ “የዚህን ዓለም ብልጽግና” አለመምረጡን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህን ያደረገው ምናልባት ሁለቱ ዮሴፍና
ማርያም ለሚያስፈልጋቸውና ለሚያጋጥማቸው ችግር ሁሉ በትሕትና መንፈስ በእርሱ ላይ ተደግፈው እንዲኖሩ በመፈለጉ ነው፡፡ “ገንዘብ
ስለሌለን በኑሮአችን ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር መታዘዝ አንችልም” በሚል ሐሳብ የሚፈተኑ ክርስቲያን ባለትዳሮች ካሉ ከዚህ
ቤተ ሰብ አኗኗር ይማሩ፡፡