የጋብቻ ትምህርት
“እግዚአብሔር መረጠ” (1ቆሮ. 1፥27)
“ነገር ግን የዘመኑ
ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ፡፡” (ገላ. 4፥4) በአብርሃምና በሣራ፥ በይሥሐቅና በርብቃ፥ እንዲሁም በያዕቆብና በሚስቶቹ
የጋብቻ ሕይወት ጥናታችን ውስጥ ግንኙታነቸው፥ ጥንካሬዎችና ድክመቶች እንደ ክርስቲያንነታችን ልንገነዘባቸው የቻልን የተለያዩ ትምህርቶች
እንደ ነበሩ እናስታውሳለን፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ውድ ልጁን በሕፃንነቱም ሆነ በወጣትነቱ ወቅት ሊያስተናግድ የሚችል ቤት ለመሥራት
ምን ዐይነት ቤተ ሰብ መረጠ? እግዚአብሔር ለዚህ ታላቅ ነገር በሚመርጣቸው በእነዚህ ሰዎች ሕይወት ውስጥ እርሱን የሚያስደስቱ መልካም
ባሕርያትን በርግጥ እናያለን፡፡ በዚህም የክርስቲያናዊ ጋብቻ ጥናታችንን መሆን በሚገባው መጠን ልናዳብረው እንችላለን፡፡
ፍሬ በአንድ ዕለት አይበስልም
ከጋብቻ ችግሮች ሁሉ
የገንዘብ ዕጦት ዋናው እንደ ሆነ የሚታመን ቢሆን እግዚአብሔር ለልጁ እናት እንድትሆንለት ሀብታም ሴትን ወይም ባለጸጋ አሳዳጊ አባትን
እንዳልመረጠ ልብ ማድረግ ይጠቅማል፡፡ ምክንያቱም ዮሴፍ፥ “ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልንን?” በማለት ናትናኤል “በእውነት
የእስራኤል ሰው” (ዮሐ. 1፥46) የተነገረላት የተናቀችዋ የናዝሬት ከተማ ኗሪ የሆነ ተራ ሠራተኛ ወይም ዕንጨት ጠራቢ ሰው ነበረና
ነው፡፡ ማርያምም እንደ ዮሴፍ ሁሉ በናዝሬት ከተማ ትኖር የነበረች የዓለምን ነገር ገና ያልተገነዘበች ድንግል ነበረች፡፡ ልጇ የሚወለድበት
ጊዜ ሲቀርብ ማርያምም ሆነች ዮሴፍ በራሱ ቅድመ አያቶች ከተማ በቤተ ልሔም በነበሩበት ጊዜም እንኳ ተመልሰው የሚገበቡት የራሳቸው
የሆነ ንብረት ወይም ሀብት የነበረው የታወቀ ዘመድ አልነበራቸውም፡፡ ሕፃኑ የተወለደው በግርግም ውስጥ ነው፡፡ ሕፃኑን በቤተ መቅደስ
ውስጥ ለጌታ ለመስጠት ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄዱ መሥዋዕት ይዘው የሄዱት “ሁለት የዋልያ ወይም ሁለት የዕርግብ ጫጩቶችን” ነበር፡፡
እንደዚህ ዐይነቱ ስጦታ የጠቦት መሥዋዕት ማቅረብ የማይችሉ እጅግ የደኸዩ ሰዎች የሚያቀርቡት መሥዋዕት እንደነበር በሕግ መጽሐፍ
ተጠቅሷል (ዘሌ. 12፥8)፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከሰብአ ሰገል ጕብኝት ቀጥሎ በዚያን ጊዜ የይሁዳ ንጉሥ ከነበረው ከሄሮድስ የጭካኔ
ሥራ ለማምለጥ ዮሴፍና ማርያም ወደ ግብጽ እንዲሄዱ ተነገራቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ምናልባት ለችግራቸው ይሆናቸው ዘንድ የወርቅ ስጦታዎችን፥
ዕጣንና ከርቤ በእግዚአብሔር ርዳታ ሳያገኙ አልቀሩም፡፡ ለዚህ በተለየ መንገድ ለተመረጠ የኑሮ ጉድኝት በገንዘብ ችግር ምክንያት
መጠለያ መጥፋቱ እግዚአብሔር፥ “የዚህን ዓለም ብልጽግና” አለመምረጡን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህን ያደረገው ምናልባት ሁለቱ ዮሴፍና
ማርያም ለሚያስፈልጋቸውና ለሚያጋጥማቸው ችግር ሁሉ በትሕትና መንፈስ በእርሱ ላይ ተደግፈው እንዲኖሩ በመፈለጉ ነው፡፡ “ገንዘብ
ስለሌለን በኑሮአችን ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር መታዘዝ አንችልም” በሚል ሐሳብ የሚፈተኑ ክርስቲያን ባለትዳሮች ካሉ ከዚህ
ቤተ ሰብ አኗኗር ይማሩ፡፡
ዮሴፍና ማርያም የመጻሕፍት
ዕውቀት የነበራቸው ሰዎች እንደ ነበሩ በመጻሕፍት ውስጥ ስለነርሱ በሚገባ ተገልጿል፡፡ ሁለቱም በመታዘዝ ጥንቃቄ የሚያደርጉ
ሰዎች ነበሩ፤ ማቴዎስ ዮሴፍን “ጻድቅ” ሰው ብሎታል፡፡ እንደዚህ ዐይነቱ አገላለጽ ማቴዎስ በሚጽፍላቸው በተለይ በአይሁዳውያን ዘንድ
በብሉይ ኪዳን ውስጥ በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔር ሕግ በመጠበቅ ዮሴፍ የሚደነቅ ሰው እንደ ነበር ያሳያል (ማቴ.
1፥19)፡፡ ከዚህ ጥቅስ የቋንቋ ውሱንነት በስተ ጀርባ ማርያምን በሕዝብ ፊት እንዳትጋለጥ
ለመጠበቅ ከራሱ ፍላጎትና ለእንደዚህ ዐይነቱ አጋጣሚ መፈጸም ከሚገባው የሕግ ዕውቀቱ ጋር ሲታገል ዮሴፍ ምን ያኽል አስጨናቂ በሆነ
ምርጫ ውስጥ እንደ ነበረ መገመት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ዮሴፍ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ዘልቆ የሚመጣው የእግዚአብሔር ድምፅ
ጠልቆ የሚሰማው ሰውም እንደ ነበር እናያለን፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ ማድረግ የሚገባውን በመንገር በሕልም እንደ ተገለጸለት
ማቴዎስ አራት ጊዜ ጠቅሶታል (ማቴ. 1፥20-23፤ 2፥13፤ 2፥19-20፤ 2፥22)
ማርያም ስለ መጽሐፍ
ታውቅ እንደ ነበር ለመገንዘብ የመሲሑ እናት እንደምትሆን ከተበሠረላት በኋላ በልቧ ውስጥ የፈሰሰውን የውዳሴ መዝሙር አገላለጽ ብቻ
መመልከት ይኖርብናል፡፡ መላው መዝሙር ከሳሙኤል መወለድና ለጌታ መሰጠት በኋላ በቀረበው በሐና የውዳሴ መዝሙር ላይ ተመሥርቶ የቀረበ
መዝሙር ነው (1ሳሙኤል 2፥1-10)፡፡
ጌታ ለአብርሃም የገባው
ቃል ኪዳን በብሉይ ኪዳን እንደ ተገለጸ ሁሉ፥ ብዙዎቹን የአምላካውያት ባሕርያት ጸጋዎችንም ታላቅነት ያረጋግጣል፡፡ ከዚህ የውዳሴ
መዝሙር ይዘት አንጻር ማርያም የጸሎት ሰው ነበረች፤ እግዚአብሔር ለሷ ያደረጋቸውን አስደናቂ ነገሮች በማሰብ አሰላሰለች፡፡ “ይህን
ነገር ሁሉ በልቧ እያሰበች ትጠብቀው ነበር፡፡” (ሉቃ. 2፥19)፡፡
ዮሴፍና ማርያም ለእግዚአብሔር
የመታዘዝን ምስጢር በሚገባ አስተውለዉታል፡፡ ዮሴፍ በሕልሙ በተገለጸለት የእግዚአብሔር መልአክ አማካይነት ለተሰጠው መመሪያ ወዲያው
የገለጸውን የመታዘዝ ስሜት ማወቅ ችለናል (ማቴ. 1፥24፤ 2፥14-15፤ 2፥21፤ 2፥22-23)፡፡ ማርያምም በተነገራት ጕዳይ
ላይ የነበራት ያን ያኽል ጭንቀቷና ነገሩን በሚገባ ያለመረዳቷ ከተሰማት ታላቅ ደስታና ከበረከቱም ጋር የተቀላቀለባት መሆኑን እየተገነዘበች
እያለች “እነሆኝ የጌታ ባርያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ፡፡” (ሉቃ. 1፥38) በማለት ለመልአኩ ገብርኤል መልስ ሰጥታለች፡፡
ስለዚህ የዚህ
ዓለም ሀብት የሌላቸው፥ በመጻሕፍት ዕውቀታቸውና ለጌታ ባላቸው ታዛዥነት ግን እጅግ የበለጸጉ
ዮሴፍና ማርያም ዓለምን ለማዳን የመጣውን የእግዚአብሔርን እውነተኛ ልጅ በድኽነት ቤታቸው ውስጥ ለማሳደግ በእግዚአብሔር ተመረጡ፡፡
እኛም ከጋብቻ በፊት ሊኖረን በሚገባ ጠቃሚ የዝግጅት ጊዜ በእግዚአብሔር መንገዶች የመጓዝን አስፈላጊነት ከእዚህ ቤተ ሰብ ሕይወት
እንማራለን፡፡ በእግዚአብሔር መደገፍ፥ የመጻሕፍት ዕውቀት፥ ለጌታ መታዘዝና መገዛት በአንድ ዕለት ውስጥ አይታዩም፡፡ እነዚህ ተወዳጅ
ባሕርያት በያንዳንዳቸው ሕይወት ውስጥ አስቀድሞ በማደግ ላይ የነበሩ ፍሬዎች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር በሚመርጣቸው በሴቷና በወንዱ
ሕይወት ውስጥ እንዲንጸባረቁ የሚፈልጋቸው መልካም ባሕርያት ናቸው፡፡
ከፍሬው ዛፉ ይታወቃል
በእግዚአብሔር ዕቅድ
ውስጥ ማርያም ዐይነተኛ ጠቃሚ መሣሪያ እንደ ነበረች ጥርጥር የለውም፡፡ ምክንያቱም ሕፃኑ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ የተፀነሰው በእርሷ
ማሕፀን ውስጥ ነውና፡፡ ሆኖም እግዚአብሔር ከዚህ የተነሣ ለቤተ ሰባዊ ሕይወት ቀደም ሲል ያበጀውን ሥርዐት አሁንም አላጠፋውም፡፡
ከመጀመሪያው ጀምሮ ወንድን የቤተ ሰቡ መሥራችና መሪ እንዲሆን ወስኗል፡፡ ዮሴፍንም እግዚአብሔር የሚቈጥረው በዚህ ዐይነት መንገድ
የቤተ ሰብ መሪ እንደ ሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያ ከማርያም ጋር ኑሮአቸውን በመቀጠሉ ጕዳይ ላይ፥ በኋላም ወደ ግብጽ በተደረገው
ጕዞና በመጨረሻ ደግሞ ወደ እስራኤል በመመለስ ወቅት አመራር የመስጠቱ ኀላፊት ለዮሴፍ የተሰጠ የሥራ ድርሻ ነበረና ነው፡፡
የማርያም መንፈሳዊነት
ምን ያኽል ጥልቅ እንደ ሆነ በእንደዚህ ዐይነት ሁኔታዎች ውስጥ ለዮሴፍ በነበራት ቅንነት የተሞላበት ታዛዥነት በሚገባ ታይቷል፡፡
አኗኗራቸው አስቸጋሪ በሆነበት ጊዜ ዮሴፍ ማድረግ የማይፈልገውን ከፈቃዱ ውጪ እንዲፈጽም የማስገደድ ሙከራ አላደረገችም፤ ነገር ግን
እንደ ሣራ ነገሮችን ሁሉ ለጌታ በመተው በመጨረሻ እግዚአብሔር በእርሷ ውስጥ ታላቅ ነገር እንደሚፈጽም ተገነዘበች፡፡ ከቦታ ወደ
ቦታ በሚዘዋወሩበት ጊዜም የዮሴፍን አመራር አስቸጋሪ አላደረገችውም፡፡ የዚህ ምስጢርም ለዮሴፍ የነበራት መታዘዝ ለእግዚአብሔር ከነበራት
መታዘዝ የመነጨና ይኸውም ለመልአኩ “እነሆኝ የጌታ ባሪያ” (ሉቃ. 1፥38) በማለት እስከ ሰጠችው ልባዊና እውነተኛ ምላሽ ድረስ
በማደግ ቀጥሏል፡፡
12 ዓመት ሲሆነው
ኢየሱስን አስከትለው ዮሴፍና ማርያም የፋሲካን በዓል ለማክበር ባደረጉት የኢየሩሳሌም ጕብኝታቸው ወቅት የተፈጸመ ሉቃስ የጠቀሰው
የታወቀ ጕዳይ አለ፡፡ በአይሁድ ደንብና ሥርዐት መሠረት ይህ አጋጣሚ እንደ አንድ ሃይማኖታዊ ኅብረተ ሰብ ሙሉ አባል ማግኘት የሚገባውን
ተገቢ ስፍራ የሚይዝበት የኢየሱስ ዕድሜ መድረሱን የሚያስታውስ ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ጊዜ ኢየሱስን በዕውቀት ኰትኵቶ የማሳደግ ኀላፊነት
ከእናቱ ወደ አሳዳጊ አባቱ የተላለፈበት ጊዜ ነው፡፡ ሉቃስ ይህን
ሁኔታ፥ “እናትና አባቱ ባዩት ጊዜ ተገረሙ፤” ሆኖም፥ “ልጄ ሆይ ለምን እንዲህ አደርግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን
ስንፈልግህ ነበርን፡፡” (ሉቃስ 2፥48) በማለት የጠየቀችው ማርያም እንደ ሆነች በወንጌሉ ጽፏል፡፡ ይህም ምናልባት ማርያም በበለጠ
ቀድማ በመውጣት የሁለቱንም ድርሻ የምታከናውን ታዛዥ መሆኗን የሚያመለክት ነው፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ለቤተ ሰቡ መሪ እንዲሆን በእግዚአብሔር
ለተመረጠው ለዮሴፍ የነበራትን ታዛዥነት የጐላ ያደርገዋል፡፡
ልጁን ወደዚህ ዓለም
ለማምጣት ምንም እንኳ የእግዚአብሔር የድኅነት (Salvation) ዕቅድ በሥራ በመተርጐም ውስጥ ወሳኝነት ያለው ታላቅ ድርሻ የተሰጣት
ቢሆንም፥ እግዚአብሔር የቤተ ሰቡን አመራር በትሕትና ሊወስድ የሚችል ሰው በመፈለግ ላይ ነበረ፡፡ ትዕቢተኛ ሰው የበታችነትን ባሕርይ
የተላበሰና በሚስቱ ቍጥጥር ሥር ሊወድቅ የሚችል ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር በሰጣት ጥሪ ያገኘችውን እጅግ ከፍተኛ መብትና ክብር በምታረጋግጥበትም
ወቅት ለዕጮኛዋ ያላትን ታዛዥነት በመፈተን ታማኝ ሆና እንደትገኝ ለእግዚአብሔር ባሳየችው ታዛዥነት ብቃት የነበራትን እጅግ ትሑት
ሴት ይፈልግ ነበረ፡፡
ከዓመታት በኋላ በሕዝባዊ
አገልግሎቱ ወቅት ሲያስተምር ኢየሱስ ራሱን “ትሑት ልብ” በማለት ገልጾታል፡፡ በእናቱና በአሳዳጊ አባቱ ሕይወት ውስጥ እውነተኛ
በሆነ የቅድስና ልብ ውስጥ ያደረ መልካም ባሕርይን ተመልክቷል፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያን ባልና እያንዳንዷ ክርስቲያን ሚስት በትክክለኛ
ኀላፊነታቸው ላይ ለእግዚአብሔር ልጅ ምሳሌነት ያለውን ክብር በተግባር ለማሳየት ጥረት ያድርጉ፤ በዮሴፍና በዕጮኛው በማርያም ታሪክ
ላይ በተጨባጭ የታየው የእግዚአብሔር በረከትም በእኛ የትዳር ሕይወት ውስጥ ይንሰራራ፡፡
“የአብርሃምና የሣራ
ጋብቻ” በሚል ርእስ ባዘጋጀነው ጽሑፍ ላይ ወደ ቀረበልን ጥያቄ እናምራ፤ በብሉይ ኪዳን ስለ ተነሡ ግብረ ገብ ጕዳዮች ስናስብ እግዚአብሔር
ፈቃዱን የገለጸው በደረጃ እንደ ነበረ ማስታወስ አለብን፡፡ በሥነ ምግባር ሁኔታዎች ላይ የተሟላ
ዕውቀት የተገኘው ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መምጣት ጋር ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ታሪኮችን በብሉይ ኪዳን ጸሓፊዎች ዐይን
መመልከትና ከዚያም በነዚህ ታሪኮች ውስጥ ምንን ለመጥቀስ የዐዲስ ኪዳን ታሪክ ጸሓፊዎች በመንፈስ ቅዱስ ኀይል እንደ ተመሩ ማስተዋል
አለብን፡፡ ምክንያቱም የሚፈልጋቸው ትምህርቶች በምሳሌ መልክ በተለያዩ ሰዎች ታሪክ አማካይነት የተሰጡ ናቸውና ግልጽ ግብረ ገባዊ
ትምህርት ሳይኖር ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር የሰዎችን አካሄድ መቀበሉን ወይንም አለመቀበሉን ከአካሄዳቸው በሚገኘው ውጤት ያሳየናል፡፡
ይህም ማለት በአንድ በታወቀ ሰው ታሪክ አማካይነት እግዚአብሔር የሚያስተምረው ምን እንደሆነ ማጤንና በዚያ ሰው ታሪክ ማንኛውም
ግበረ ገባዊ ጕዳይ አካቶ ያስተምረናል ብለን መጠበቅ የለብንም፡፡
ሐዋርያው ጴጥሮስ ሣራን የጠቀሳት ለባሏ ላሳየቸው የመታዘዝ
መንፈስ ለማመስገንና በዚህም ክርስቲያን ሚስቶች ለሆኑት ሁሉ መልካም ምሳሌ መሆንዋን ለመጠቈም ነው፡፡ ሣራን ለመገምገም (1ጴጥ.
3፥5-6) ሐዋርያውን መንፈስ ቅዱስ የመራው በዚህ መንገድ ነበረ፡፡ እኛ በእውነተኛነቷ
ረገድ ሣራን እንድንከተላት አልተጠየቅንም፡፡ ለምሳሌ በዐዲስ ኪዳን ውስጥ በኤፌ. 4፥25 ላይ እውነትን ስለ መናገር ግልጽ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ በአብርሃምና
በሣራ ታሪክ ውስጥ እግዚአብሔር በርግጥ ከፊል እውነትን መናገራቸውን እንዳልተቀበለው አብርሃም ለፈጸመው ውጤት በመሆን በአብርሃም
በራሱ ላይ በተከሠተው ሁኔታ አሳይቷል፡፡ ይህን በተመለከተ ኀላፊነት የወደቀው የቤተ ሰቡ ራስ በሆነው በአብርሃም ላይ እንጂ በሣራ
ላይ አልነበረም፡፡ በዚህ ድርጊት ውስጥ ሣራ ከነበራት ድርሻ የተነሣ እግዚአብሔር የወቀሣት አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ለባሏ ለመታዘዝ
ልቧ ቀና በመሆኑና ይኸውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ከፍጹም እውነተኛነት ይልቅ ይህ በእርሱ ፊት እጅግ አስፈላጊ ነበርና ነው፡፡
ስለዚህ በዚህ ጕዳይ ላይ ሣራ ለአብርሃም ለመታዘዝ እንቢ
ማለት አልነበረባትምን? ብለህ አሁን ስትጠይቅ ቅዱሳት መጻሕፍት ለዚህ የሚሰጡት መልስ ሣራ ለአብርሃም መታዘዟና በዚህ መመስገኗ
ትክክል ነበረ የሚል ይመስላል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ምላሽ አንጻር እንደ ዐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች እውነትን መናገር ምንም ፋይዳ
የለውም ወደሚል ማጠቃለያ መድረስ እንደሌለብን መጠንቀቅ ይኖብናል፡፡ ይህን በተመለከተ በወንጌል ውስጥ የተሟላ ግንዛቤ አለን፡፡
ዛሬ አንድ ክርስቲያን ሴት በዚህ ዐይነት ሁኔታ ብትገኝ ምን ማድረግ አለባት? ጌታዋን እንድትክድ ወይንም ስለ እርሱ ሐሰት እንድትናገር
ብትደረግ በርግጥ ይህን ድርጊት ልትፈጽም አትችልም፡፡
በዚህ ረገድ ለጌታዋ ያላት ታዛዥነት ለባሏ በሚኖራት ላይ
የበላይነት ሊኖረው ይገባል፤ ሆኖም በአነስተኛ ነገሮች ሁሉ ለባሏ ታዛዥ ሆና መገኘት ከሌሎች ሁሉ ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት የበለጠ
ዋጋ እንዳለው ልብ ታድርግ (1ጴጥ. 3፥1-4)፡፡ አንዳንድ ጊዜ ማብራሪያ ከመስጠት ይልቅ ዝምታ የሚመረጥበት ጊዜ ሊኖር ይችላል፡፡
ከዚህም በላይ ሣራ ላሳየችው መልካም ጠባይ በሐዋርያው የተሰጣት ምስጋና በተጠቀሰው ክፍል እንደሚያመለክተው የሚያምኑ ባሎች ካሏቸው
ሚስቶች ሁኔታ አንጻር የቀረበ ነው፡፡
የማያምኑ ባሎች እንደ
ክርስቲያን ለማድረግ የማይፈልጉትን ብዙ ነገር ማለትም ወደ ቤተ ክርስቲያን ስብሰባዎች እንዳይሄዱና የመሳሰሉትን እንዳይፈጽሙ በሚስቶቻቸው
ላይ ጫና መፍጠር ይችላሉ፡፡ ይኸውም ለጌታና ባሎቻቸውን ወደ ጌታ ለማምጣት ሲባል ሴቶች የሚወስዱት ርምጃ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የክርስቲያን
ሴት ልብ ለባሏ የመታዘዝ ልብ በብርሃን በመመላለስ እግዚአብሔርን ለማስደሰት ከወሰነ በግል ሥራ ኀላፊነቷ እንዴት መራመድ እንዳለባት
የሚረዳትን መለኮታዊ ጥበብ እንዲሰጣት በጌታዋ መታመን ትችላለች፡፡
ከዚህ በላይ ያሰፈርነው
ሐሳብ ጥያቄህን በመጠኑ ለመመለስ እንደሚረዳ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እነዚህን ነጥቦች ስታሰላስልና በእነርሱ ላይ በምትጸልይ ጊዜ
ጌታ ማስተዋልን ይስጥህ፡፡
(በጮራ ቍጥር 8 ላይ የቀረበ)
No comments:
Post a Comment