የመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅላላ ዕውቀት
መጽሐፈ ባሮክ
ካለፈው የቀጠለ
መግቢያ
ባሮክ የነቢዩን የኤርምያስን ቃል እየሰማ ይጽፍ የነበረ ወይም በዐጭር ቃል ኤርምያስንና የቃሉን ባለቤት እግዚአብሔርን በጸሓፊነት ያገለገለ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ነበረ ይታወቃል (ኤር. 36፥1-8፤ 27፥32)፡፡
በኤርምያስ አንደበት እንደ ተነገረው የእግዚአብሔር ቃል፥ ናቡከደነፆር ያዘመተው የከለዳውያን ጦር ሠራዊት ምድረ ይሁዳን ከወረረ፥ የኢየሩሳሌምን ከተማ ከነቅጥሯ ከደመሰሰ፥ የቤተ መቅደሱን መገልገያ ዕቃዎች ከወሰደና ቤተ መቅደሱን ካቃጠለ በኋላ፥ የሕዝብ አለቆችንና ባለሙያዎችን ወደ ባቢሎን አፈለሰ፡፡ የደረሰውን ጥፋት አስቀድሞ በመተንበዩ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ ተግዞ የነበረውን ኤርምያስንም በነጻነት በፈለገው ስፍራ እንዲኖር ፈቀደለት (ኤር. 38፥17-18፤ 39፥11-14፤ 40፥1-6)፡፡
ነገር ግን ለባቢሎናውያን መገዛትን ያልተቀበለ፥ እስማኤል በተባለ ሰው የተመራ ቡድን የከለዳውያን ተሿሚ የነበረውን ጎዶልያስንና ተከታዮቹን ከገደለ በኋላ፥ ኤርምያስንና ጸሓፊውን ባሮክን በማስገደድ ወደ ግብጽ ይዞ ኮበለለ (ኤር. 40፥7-16፤ 41፤42፤ 43፥1-7)፡፡
ነቢዩ ኤርምያስም በምድረ ግብጽ በነበረበት ጊዜ በግብጽና በመንግሥቷ፥ በሕዝቧም ላይ ሊመጣ ያለውን ጥፋት ተነበየ፡፡ ወደ ግብጽ ተሰደው በመጡት ወገኖቹ ላይም የፈሩት ረኃብ፥ በሽታ፥ ጦርነትም እንደሚደርስ፤ እንዲያውም ናቡከነፆር ወረራውን በመቀጠል ወደ ግብጽ እንደሚዘልቅ በግልጽ ተናገረ፡፡ ከዚህም በቀር ስደተኞች ወገኖቹ “ንግሥተ ሰማይ” እያሉ በሴቴ መንፈስ ስም ጠበልና ጸሪቅ (ጠዲቅ) እያቀረቡ የሚዘክሯትን ምስለ ጣዖት ማምለክን እንዲተዉ እያስተማረ በግብጽ ቆይቶ ነበረ (ኤር. 43፥8-13፤ 44፥1-30)፡፡
በእግዚአብሔር ቃል ተመዝግቦ የደረሰን እውነተኛ ታሪክ ይህ ሆኖ ሳለ፥ በአዋልድ መጻሕፍት ግን ከዚህ የተለየ የፈጠራ ትረካ እንዳለ ታውቋል፡፡ ይህንም በሚመለከት በጮራ ቍ. 3 ገጽ 6 የወጣውን አንባቢ አይረሳውም፡፡ በተጨማሪ የመጽሐፈ ባሮክ ደራሲ የኤርምያስ ጸሓፊ የነበረ ሰው እንደ ሆነ ወይም ሌላ ባሮክ ቢሆን አይታወቅም፡፡
አሁንም በዚህ ዕትም በዐማርኛ መጽሐፈ ባሮክ የተጻፈውን በማስቀደም ተመሳሳይነት ያላቸውን የግእዙንና የእንግሊዝኛን መጽሐፈ ባሮክ በማስከተል በእግዚአብሐር ቃል እንመረምራቸዋለን፡፡
1. የዐማርኛው መጽሐፈ ባሮክ
1.1 አንደ መጽሐፉ ትረካ ደብዳቤ ተጻፈ የሚለው ወደ ባቢሎን ስለ ሆነ ጸሓፊው ባሮክ ኢየሩሳሌም ነበረ ማለት ነው (ም. 1፥1)፡፡ እንዲሁም ወደ ባቢሎን ተማርኮ የነበረው የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጅ ኢኮንያንና (ዮአኪን?) ሌሎች ምርኮኞች በኢየሩሳሌም ወዳሉ ካህናት የጻፉትን ይህን መጽሐፍ (ደብዳቤ) ባሮክ አነበበው ስለሚል፥ ባሮክ በኢየሩሳሌም ነበረ የሚለውን ሐሳብ ያጠናክራል (ም. 1፥3-4)፡፡
1.2 ትኵረት የሚያስፈልገው ሌላው ነጥብ በዐማርኛው መጽሐፈ ባሮክ ከም 1፥3 ጀምሮ እስከ መጽሐፉ መጨረሻ ድረስ የሚነበበው፥ ምርኮኛው አኮንያን (ዮኪን) በኢየሩሳሌም ወደ ነበሩ ካህናት ጻፈው የሚባለው ብቻ ነው እንጂ፥ ባሮክ ራሱ የጻፈው ነገር በመጽሐፉ ውስጥ ስፍራ አልተሰጠውምና የባሮክ ደብዳቤ ይዘት አልታወቀም፡፡ ይህንኑ የኢኮንያንን ደብዳቤ በመጽሐፍ መልክ በማዘጋጀቱ መጽሐፉ በስሙ እንዲሰየምለት ተደረገ ካልተባለ በቀር በውስጡ ባሮክን የመጽሐፉ ባለቤት ለመሆን የሚያበቃው ሥራ የለም፡፡ ምናልባት በም. 1፥1 እንደ ተነገረው ባሮክ ወደ ባቢሎን ለኢኮንያን ደብዳቤ ጽፎ ከቈየ በኋላ፥ ለዚያ መልስ ከኢኮንያን የተጻፈለት ደብዳቤ በመጽሐፈ ባሮክ ስፍራ ሲሰጠው የባሮክ ደብዳቤ ግን ባለ መገኘቱ ሊመዘገብለት ሳይችል ቀርቶ ይሆናል፡፡ መጽሐፉ መቼም በባሮክ ዘመን ቢጠረዝ ኖሮ የራሱ ደብዳቤ እንደ መጀመሪያ ገጽ፥ የደብዳቤው መልስ (የኢኮንያን ደብዳቤ) ከዚያ ተከታታይ ሆኖ በተጠረዘ ነበር፡፡ ደብዳቤዎች እየተሰበሰቡ በመጽሐፍ ቅጽ ሲጠረዙ፥ ከጊዜ መርዘም የተነሣ ባለ መታደል፥ የባሮክ ደብዳቤ አልተገኘ ይሆናል፡፡
1.3 በም. 1፥5 “ናቡከደነፆር ኢኮንያንን ከማረከው በኋላ፥ የኢየሩሳሌምን ወገኖች ከማረካቸው በኋላ፥ ወደ ባቢሎንም ከወሰዳቸው በኋላ፥ ሴዴቅያስ የብሩን ዕቃ አሠርቶ ከወርቁ ጋር ሰደደላቸው” ተብሏል፡፡
ነገር ግን የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን ኢኮንያን ከተማረከ በኋላ፥ ከለዳውያን በምትኩ ሴዴቅያስን አንግሠዉት እንደ ነበረ ዕውቅ ነው (2ነገ. 24፥8-17)፡፡ ሴዴቅያስም ስላመፀ ከለዳውያን እንደ ገና ወደ ይሁዳ ዘመቱ፤ በ11ኛው ዓመት ንጉሥ ሴዴቅያስን ማረኩት፤ ዐይኖቹን አውጥተውና በሰንሰለት አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት፤ እስከ ዕለተ ሞቱም በወኅኒ ቈየ (2ነገ. 25፥6-7፤ ኤር. 52፥8-11፤ ሕዝ. 12፥10-13)፡፡ ይህ ሴዴቅያስ ነው ንዋየ ቅዱሳት ወደ ኢየሩሳሌም ላከ የተባለው፡፡
ኢኮንያንም ቢሆን፥ (ዮአኪን ከሆነ) ከባቢሎን ወኅኒ ቤት የወጣውና የንጉሠ ባቢሎን ተቀላቢ የሆነው፥ ለ37 ዓመታት ከታሠረ በኋላ ነበረ (2ነገ. 25፥27-30፤ ኤር. 52፥31-34)፡፡ ከምርኮኞች ወገኖቹ ጋር እየተገናኘ ወደ ሀገሩ ደብዳቤ የመጻፍ ዕድል እውነት አግኝቶ ይሆን?
1.4 በ 1፥8 “ይቺን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ማደሪያ በቤተ መቅደስ አንብቧት አለ” ተብሏል፡፡ “የሞተውን አያ ይሉታል!” እየተባለ ይተረታል፡፡ ቤተ መቅደሱ ተቃጥሎ ስፍራው ወና እንደ ተደረገ የመጽሐፈ ባሮክ ደራሲ አላየም፤ አልሰማም ማለት ነውን?
2. የግእዙና የእንግሊዝኛው መጽሐፈ ባሮክ
2.1 መጽሐፉ የተጻፈው በባቢሎን ከነበረው ባሮክ ከተባለ ሰው ነው፡፡ ዐማርኛው መጽሐፈ ባሮክ፥ ጸሓፊውን ኢየሩሳሌም የነበረ ሲያስመስለው፥ ይህ ግን በባቢሎን የነበረ አድርጎታል፤ ምርኮኛው ንጉሥ ኢኮንያንና (ዮአኪን) ሌሎቹ ምርኮኞች በባቢሎን ሶዲ (ሱድ) በተባለ ወንዝ አጠገብ ሲሰበሰቡ ባሮክ ያዘጋጀውን ይህን መጽሐፍ አነበበላቸው፡፡ የሰሙት አለቀሱ፤ ጾሙ፤ ጸለዩ፤ ገንዘብም አዋጡ፤ ያዋጡትንም ገንዘብ እንዲሁም ቀደም ሲል ሴዴቅያስ፥ ያሠራውንና ናቡከደናፆር ከቤተ መቅደስ የወሰዳቸውን ንዋያተ ቅድሳት በይሁዳ ወደሚገኙት ካህናት ከደብዳቤ ጋር ላኩላቸው ይላል፡፡ በገንዘቡ ለመሥዋዕትና ለቍርባን የሚሆነውን እየገዙ፥ በተላከላቸው ንዋያተ ቅድሳት እንዲገለገሉበት፤ ስለ ንጉሥ ናቡደናፆርና ስለ ልጁ ብልጣሶር ዕድሜና ስለ ምርኮኞቹ ኑሮ መቃናት ምሕላ እንዲደረግ ማሳሰቢያው እንደ መግቢያ ሆኖ በመጽሐፉ ቀርቧል፡፡ መጽሐፉም በኢየሩሳሌም በቤተ እግዚአብሔር እንዲነበብ ያሳስባል (ም. 1፥1-14)፡፡
2.2 ደብዳቤው (መጽሐፉ) የያዘው
- ምርኮኞቹ ስለ ራሳቸውና ስለ መላው ሕዝባቸው ኀጢአት ያደረጉት ኑዛዜ፥
- የእግዚአብሔርን ምሕረትና ይቅርታ የጠየቁበት ጸሎት፥
- ስለ ጥበብ ታላቅነት
- የእስራኤል ሕዝብ ስለሚመሩበት መለኮታዊ ጥበቃ
- ስለ ወደ ፊቱ ተስፋ
ሲሆን ምናልባት ይህን ደብዳቤ ከባቢሎን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረሰው ባሮክ ይሆን?
2.3 መቼም ኢየሩሳሌም በጠፋች በዐምስተኛው ዓመት በናቡከደነፆር ዘመነ መንግሥት የቤተ መቅደስ ዕቃዎች ወደ ኢየሩሳሌም ስለ መመለሳቸውና ካህናቱ ሥርዓተ አምልኮ ስለ መፈጸማቸው በመጽሐፈ ባሮክ የተጻፈው ታሪክ በእጅጉ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ምክንያቱም፡-
አንደኛ፥ ኢየሩሳሌም ስትደመሰስ፥ ቤተ መቅደሱ ሲቃጠል፥ ታዋቂና ባለ ሙያ ሰዎች ወደ ባቢሎን እንዲማረኩ ሲደረግ፥ ምድሪቱ ለ70 ዓመታት እንድታርፍ በእግዚአብሔር ተወስኖ የነበረ በመሆኑ ነውና ፋርሳዊ ቂሮስ ከመንገሡ በፊት የቤተ መቅደስ ዕቃ አልተመለሰም (2ዜና. 36፥17-23፤ ዕዝ. 1፥1-11)፡፡
ሁለተኛ፥ በፋርሳዊ ቂሮስ ዐዋጅ መሠረት ኢያሱና ዘሩባቤል ከምርኮኞች ወገኖቻቸው መካከል የመጀመሪያውን ተጓዥ ቡድን እየመሩ በፈራረሰችው የኢየሩሳሌም ከተማ ሲደርሱ መሠዊያ አላጋጠማቸውም፡፡ ይልቁን ይህን ለማድረግ መሠዊያ መሥራት ነበረባቸው (ዕዝራ 3፥1-3)
አንባቢ ሆይ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጸ መለኮታዊ ራእይ ትምህርት፥ ተግሣጽ፥ ታሪክ እንዲናድ እየተደረገ ስለ ሆነ ምን መደረግ አለበት ብለው ያስባሉ? (2ጢሞ. 4፥3-5)፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ከተረቶችና ከወጋ-ወግ ታሪኮች ተለይቶና በቅዱስ መጽሐፍነቱ ተጠብቆ እንዲኖር የማድረጉ ኀላፊነት የማን ነው? (መዝ. (12)፥6፤ (18)፥30፤ (19)፥7፤ ምሳ. 30፥5)፡፡
(በጮራ ቍጥር 8 ላይ የቀረበ)
በዚህ ውሸትና የዲያቢሎስ ሥራ በነገሰባት አለም በተለይ በኦ/ቤ/ክ እውነትን እንድትመሰክሩልን እናንተን የሰጠን እግዚአብሔር ይመስን አሜን!!!
ReplyDelete