የእግዚአብሔር ቃል ሳይዛባ በተነገረበት መንፈስ ሊተረጐም ይገባል፡፡ በዚህ ዐምድ ቃሉ
በዐውዱ መሠረት ሊተረጐም እንደሚገባ በማስረዳት፥ የተሳሳተ ትርጕም እየተሰጣቸው ያሉ ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ለአብነት
በማንሣት የቃሉን ትክክለኛ መልእክት ለማስተላለፍ ጥረት ይደረጋል፡፡
“ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል$ ጻድቅንም በጻድቅ ስም
የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል፡፡ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ
እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም፡፡” (ማቴ 10$41-42)
የእግዚአብሔር ቃል በተጻፈበት ዐውድ መሠረት ሊተረጐም ይገባል፡፡ ቃሉን የሚያነብ ሁሉ
በቃሉ ላይ ሳይጨምር፣ ከቃሉም ላይ ሳይቀንስ፣ ወይም ቃሉን በተነገረበት መንፈስ ሳይሆን ለባህሉና ለልማዱ በሚስማማ ስልት እንዳይተረጕመውና
በተሳሳተ መንገድ እንዳይረዳው ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ይሁን እንጂ በብዙዎች ዘንድ የእግዚአብሔር ቃል በዐውዱ መሠረት እየተተረጐመና
እየተኖረበት ነው ማለት አያስደፍርም፡፡