Monday, March 30, 2015

ፍካሬ መጻሕፍት

የእግዚአብሔር ቃል ሳይዛባ በተነገረበት መንፈስ ሊተረጐም ይገባል፡፡ በዚህ ዐምድ ቃሉ በዐውዱ መሠረት ሊተረጐም እንደሚገባ በማስረዳት፥ የተሳሳተ ትርጕም እየተሰጣቸው ያሉ ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ለአብነት በማንሣት የቃሉን ትክክለኛ መልእክት ለማስተላለፍ ጥረት ይደረጋል፡፡

“ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል$ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል፡፡ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም፡፡” (ማቴ 10$41-42)

የእግዚአብሔር ቃል በተጻፈበት ዐውድ መሠረት ሊተረጐም ይገባል፡፡ ቃሉን የሚያነብ ሁሉ በቃሉ ላይ ሳይጨምር፣ ከቃሉም ላይ ሳይቀንስ፣ ወይም ቃሉን በተነገረበት መንፈስ ሳይሆን ለባህሉና ለልማዱ በሚስማማ ስልት እንዳይተረጕመውና በተሳሳተ መንገድ እንዳይረዳው ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ይሁን እንጂ በብዙዎች ዘንድ የእግዚአብሔር ቃል በዐውዱ መሠረት እየተተረጐመና እየተኖረበት ነው ማለት አያስደፍርም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ሊተረጐም እንደሚገባ በጮራ ቊጥር 38 በጥያቄዎችና መልሶቻቸው ዐምድ ገጽ 15 ላይ “መጽሐፍ ቅዱስና አተረጓጐሙ” በሚለው ንኡስ ርእስ ሥር አንዳንድ ነጥቦችን ለማሳየት መሞከራችን ይታወሳል፡፡ በዚሁ መሠረት በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ቊጥር 41-42 ያለው ቃል የሚያስተምረንን ለመረዳት ጥረት እናደርጋለን፡፡

በአንዳንዶች ዘንድ ይህ ጥቅስ ስለ ቅዱሳን አማላጅነት ወይም በእነርሱ ስም ዝክር መዘከር ስለሚያስገኘው ዋጋ እንደ ተነገረ ተደርጎ ነው የሚጠቀሰው፡፡ ቃሉ ምን ይላል? ይህ ቃል ስለ ምን እንደ ተነገረ ለማወቅ፥ ብዙዎች እንደሚያደርጉት ከምዕራፉ የመጨረሻ አንቀጽ ወይም ከቊጥር 40 መጀመር በቂ ሊሆን ቢችልም፥ የምዕራፉ መደምደሚያ የሆነውን ይህን አንቀጽ በሚገባ ለመረዳት ምዕራፉን ከመጀመሪያው አንሥቶ ማንበብና ማስተዋል አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ጌታችን ለላካቸው ደቀ መዛሙርት (ቊጥር 5-39) እና የተላኩትን ደቀ መዛሙርት ተቀብለው ለሚያስተናግዷቸው ሰዎች (ቊጥር 40-42) ነው የተናገረው፡፡

በምዕራፍ 10 ላይ የሰፈረው ታሪክ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ጠፉት በጎች ስለ መላካቸው ይናገራል፡፡ ለዚህ ተልእኮ መነሻ የሆነው ጕዳይ የተከሠተው በምዕራፍ 9 ከቊጥር 35-38 ውስጥ እንደ ሆነ እንመለከታለን፡፡ በዚህ ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ ምኵራቦች በማስተማርና የመንግሥትን ወንጌል በመስበክ፥ በከተማዎችና በመንደሮችም እየተዘዋወረ በሕዝቡ ውስጥ ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ በመፈወስ፥ ሕዝቡ በመንፈሱም በሥጋውም ሰላም፣ ዕረፍትና ጤና እንዲያገኝ አደረገ፡፡ በተለይም በከተማዎችና በመንደሮች ሲዘዋወር የተመለከተው ብዙ ሕዝብ፥ እረኛ እያላቸው እንደሌላቸው ሆነው፣ ተጥለውና ተጨንቀው ስለ ነበረ ዐዘነላቸው፡፡ ዐዝኖ ብቻ አልቀረም፤ ለደቀ መዛሙርቱ “መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” ሲል ታላቅ የሆነ የጸሎት ርእስ ሰጣቸው (9$37-38)፡፡

ጸሎታቸው እስኪመለስና ብዙ ሠራተኞች ወደ መከሩ እስኪላኩ ድረስም ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ጠርቶ$ ርኵሳን መናፍስትን የሚያወጡበትንና ደዌንና ሕማምን የሚፈውሱበትን ሥልጣን ሰጥቶ ላካቸው (10$1-4)፡፡ ሲልካቸውም ተልከው ወደሚሄዱባቸው ሰዎች እንዴት ባለ ሁኔታ እንደሚቀርቡ ልዩ ልዩ ትእዛዛትን፣ መመሪያዎችንና ማሳሰቢያዎችን ነግሯቸው ነበር፡፡

ወደ እስራኤል ልጆች ብቻ እንዲሄዱ፣ በተሰጣቸው ሥልጣን ያለ ዋጋ (በነጻ) ድዉያንን እንዲፈውሱ፣ ሙታንን እንዲያስነሡ፣ ለምጻሞችን እንዲያነጹ፣ አጋንንትን እንዲያወጡ$  ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና ምንም ዐይነት ገንዘብ፣ ወይም ትርፍ ልብስ እንዳይዙና በገቡበት ከተማ ወይም መንደር በሚቀበላቸው ሰው ቤት እንዲቀመጡ  አዘዛቸው፡፡

የሚላኩት እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል ስለ ሆነ$ ልዩ ልዩ ስደትና መከራ ይነሣባቸዋልና$ በዚያ ውስጥ በየዋኅነትም በጥበብም እንዲመላለሱ$ ተከሰው በቀረቡ ጊዜ ስለሚናገሩትና ስለሚመልሱት እንዳይጨነቁና የሚናገሩትን መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጣቸው$ ቤተ ሰቦች ጠላቶች ሆነው እንደሚነሡ$ ከአንዱ ከተማ ቢያሳድዷቸው ወደ ሌላው እንዲሸሹ የተለያዩ መመሪያዎችን ሰጣቸው፡፡

ከስድብ ጀምሮ ልዩ ልዩ መከራዎችን እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት ድረስ እንደሚቀበሉ$ ሥጋን ብቻ የሚገድሉትን እንዳይፈሩ$ ነገር ግን ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን እንዲፈሩ$ በሰው ፊት ስለ እርሱ ለመመስከር እንዳያፍሩና እስከ መጨረሻውም እርሱን ለመከተል እንዲጨክኑ አሳስቧቸዋል፡፡        

ለደቀ መዛሙርቱ የሚናገረውን ከፈጸመ በኋላ$ ደቀ መዛሙርቱን ተቀብለው የሚያስተናግዱ ሰዎች ሊያደርጉ ስለሚገባቸው ነገር እንዲህ በማለት ተናገረ፡፡ “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢዩን ዋጋ ይወስዳል$ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል፡፡ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውሃ የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም” (ማቴ 10$41-42)፡፡

ይህ ጥቅስ ጌታ የላካቸውን አገልጋዮች ተቀብሎ ስለ ማስተናገድና እነርሱን ተቀብሎ በማስተናገድ ስለሚገኘው ዋጋ ነው የሚናገረው፡፡ ጕዳዩ ደቀ መዛሙርቱን የማስተናገድ ነገር መሆኑን ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ በሰጠው ትእዛዝና መመሪያ ውስጥ በግልጽ እንረዳለን፡፡ “በምትገቡበትም በማናቸይቱም ከተማ ወይም መንደር$ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያ ተቀመጡ፡፡ ወደ ቤትም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፡፡ ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይድረስለት፡፡ ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ፡፡ ከማይቀበላችሁም ቃላችሁን ከማይሰሙ ሁሉ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ” (ቊጥር 11-14)፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ሥልጣንን ሰጥቶ የላከበት አንዱ ምክንያት እንዲሰብኩ ነው፡፡ በምዕራፉ ውስጥ “ሄዳችሁም፡- መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ” (ቊጥር 7) የሚለው አረፍተ ነገርና “ከማይቀበላችሁም ቃላችሁን ከማይሰሙ ሁሉ” የሚለው ሐረግ ይህን ያመለክታሉ፡፡

ከአረፍተ ነገሩ የምንረዳው ደቀ መዛሙርቱ ወደ ሰዎች ይዘው የሚሄዱት በክርስቶስ የአዳኝነት ሥራ በማመን መንግሥተ ሰማያት የምትሰጥ መሆኗን የሚያበሥረውን ወንጌል ነው፡፡ ሰዎች ይህን ወንጌል መስማት የሚችሉት በመጀመሪያ ደቀ መዛሙርቱን እንደ ጌታ መልእክተኞች መቀበል ሲችሉ ነው፡፡ እነርሱን መቀበል ካልቻሉ ግን ይዘውላቸው የመጡትን ጌታን ሊቀበሉት አይችሉም፡፡ ጌታንም ካልተቀበሉት እግዚአብሔርን ሊቀበሉት አይችሉም፡፡ ለዚህ ነው መድኀኒታችን ኢየሱስ “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል” ሲል የተናገረው (ቊጥር 40)፡፡ ይህ የጌታን ደቀ መዛሙርት ለመስማት ፈቃደኛ ሆኖ ቃላቸውን በመቀበልና በማመን የሚገኘው ትልቁና ዋናው በረከት ነው፡፡

ጌታ የላከውን ነቢይ፣ ወይም ጻድቅ፣ ወይም ደቀ መዝሙር÷ የጌታ ነቢይ ነው፤ ጻድቅ ነው፤ ደቀ መዝሙር ነው ብሎ÷ በነቢይ ስም፣ በጻድቅ ስም በደቀ መዝሙር ስም ወይም እንደ ነቢይ፣ እንደ ጻድቅና እንደ ደቀ መዝሙር ቈጥሮ የሚቀበልና የሚያስተናግድ÷ የነቢይን፣ የጻድቅንና የደቀ መዝሙርን ዋጋ ያገኛል የሚል ሌላ በረከት ደግሞ አለ፡፡ ጌታችን ሥልጣንን ሰጥቶ የላካቸው አገልጋዮች÷ በተሰጣቸው ጸጋ አገልግለው ዋጋ ያገኛሉ ወይም እንደ ሥራቸው መጠን ይከፈላቸዋል፡፡ ዋጋው እነርሱ ብቻ የሚያኙት አይደለም፡፡ እነርሱን ተቀብለው የሚያስተናግዷቸውም ይካፈሉታል፡፡

በማቴዎስ 10÷41-42 ለተጻፈው ቃል በአንድምታ ወንጌል ላይ የተሰጠው ትርጕም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ “መምሩን መምር ብሎ የተቀበለ መምሩ የሚያገኘውን እኔ የምሰጠውን ዋጋ ያገኛል” ተብሎ ነው የተተረጐመው፡፡ ነገር የሚበላሸው “አንድም” ተብሎ ከዐውዱ ውጪ ሌላ ትርጕም ለመስጠት ሲሞከር ነው፡፡ የሚገርመው ብዙዎች ይህን የመጀመሪያውንና ዐውዱን የጠበቀውን ትርጕም ቦታ አይሰጡትም፡፡ “አንድም ...  ስለ አምላከ ኢሳይያስ ስለ አምላከ ኤርምያስ ብሎ ድኻውን የተቀበለ እኔ የምሰጠውን ነቢይ የሚያገኘውን ዋጋ ያገኛል ...” ተብሎ አለንባቡ ለተተረጐመው መልእክት ግን ከፍ ያለ ግምት ነው ያላቸው፡፡

መቼም ይህ ክፍል የጌታን መልእክተኞች ተቀብሎ ስለ ማስተናገድ እንጂ ድኾችን ስለ መርዳት እንዳልተነገረ ይታወቃል፡፡ የወንጌላዊ ማርቆስ ዘገባ ይህን በግልጽ ያስረዳል፡፡ “የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ በስሜ ጽዋ ውሃ የሚያጠጣችሁ ሁሉ÷ ዋጋው እንዳይጠፋበት እውነት እላችኋለሁ” (ማር. 9÷41)፡፡ ቃሉ ራሳቸውን ደቀ መዛሙርቱን በጌታ ስም ስለ ማጠጣት እንጂ÷ በደቀ መዛሙርቱ ስም ድኾችን ስለ ማጠጣት አልተነገረም ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ “የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል” (መዝ. 111(112)÷6) የሚለውን እየጠቀሱ÷ መታሰቢያ የሚለውን የቅዱሳንን ስም ድግስ ደግሶ ከመዘከር ጋር ሊያገናኙት ይሞክራሉ፡፡ ይህ ቃል የሚይዘው ፍቺ ግን ጻድቅ ሰው በሠራው መልካም ሥራ በእግዚአብሔርም በሰውም ዘንድ ሲታወስ ይኖራል ማለት ነው፡፡ በመዝሙረ ዳዊት የአንድምታ ትርጓሜ ላይ የተሰጠው ፍቺም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ “የጻድቅ ሁሉ ሥራ ለዘላለም ሲነገር ይኖራል” ተብሏል፡፡

በማቴዎስ ምዕራፍ 10 ውስጥ ባይሆንም÷ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ድኾችን ስለ መርዳት ተጽፏል፡፡ ለምሳሌ የሚከተለውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ “ምሳ ወይም እራት ባደረግህ ጊዜ÷ እነርሱ ደግሞ በተራቸው ምናልባት እንዳይጠሩህ ብድራትም እንዳይመልሱልህ÷ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን ዘመዶችህንም ባለጠጎች ጎረ ቤቶችህንም አትጥራ፡፡ ነገር ግን ግብዣ ባደረግህ ጊዜ ድኾችንና ጕንድሾችን ዐንካሶችንም ዕውሮችንም ጥራ፤ የሚመልሱት ብድራት የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ፤ በጻድቃን ትንሣኤ ይመለስልሃልና፡፡” (ሉቃ. 14÷12-14)፡፡ እንዲህ ቢደረግም÷ የሚደረገው ሁሉ ግን በጌታ ስም እንጂ በፍጡራን ስም አይደለም፡፡ “በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት” ተብሎ ታዟልና (ቈላ. 3÷17)፡፡

በማቴዎስ 10÷41-42 ላይ ያለውን ቃል በዚህ መንገድ አለንባቡ መተርጐም ለምን አስፈለገ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ቃሉ በነቢያት፣ በጻድቃንና በሐዋርያት ስም ድኾችን ስለ ማብላትና ስለ ማጠጣትም ይናገራል ብሎ ለማሰብ መነሻ የሚሆነው መጽሐፍ ቅዱሳዊው ትምህርት ሳይሆን ሃይማኖታዊው ልማድ ነው፡፡ ልማዳችንን በቃሉ መሠረት መፈተሸና ሊስተካከል የሚገባውን ማስተካከል ሲገባ÷ ቃሉን ለልማዳችን መሸፈኛ አድርጎ ማቅረብ ወደ ስሕተት ይመራል፡፡

ቃሉን በለመዱትና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት በሌለው በዚህ መንገድ አለ መተርጐም÷ ቅዱሳንን አለ ማክበር የሚመስላቸው ሰዎች ይኖራሉ፡፡ በቅድሚያ መታወቅ ያለበት÷ ክርስቲያን ነን ካልን ለምናምነውም ሆነ ለምደርገው ነገር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ ሊኖረን ይገባል፡፡ ቅዱሳንን ማክበር እንዴት ይገለጻል? ቅዱሳንን ስለ ማክበር መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ቅዱሳንን ስለ ማክበር ምን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተመክሮ አለ? የሚሉት ጥያቄዎች መነሣትና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሽ ማግኘት አለባቸው፡፡

ቅዱሳንን ማክበር የሚገለጸው በልማዳዊ ድርጊት ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረው መንገድ ነው፡፡ በአገራችን ቅዱሳንን ማክበር ማለት በስማቸው ዝክር መዘከር፣ በስማቸው የተደረሱ አዋልድ መጻሕፍትን በማንበብና በመስማት እነርሱን መማጸን፣ በስማቸው ወደ ተሰየሙ ገዳማት መጓዝና የመሳሰሉትን ተግባራት መፈጸም እንደ ሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ መንገድ ቅዱሳንን እንድናከብር ወይም እነዚህ ድርጊቶች ቅዱሳንን ማክበር ተብለው እንደሚወሰዱ መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምርም፡፡ ይልቁንም በማክበር ስም የሚደረጉት እነዚህ ተግባራት አምልኮ ባዕድ ነው የሚሆኑት፡፡ ለመሆኑ በዚህ መንገድ ቅዱሳንን ያከበረ በመጽሐፍ ቅዱስ ይገኛልን? የብሉይ ኪዳንን ቅዱሳን የዐዲስ ኪዳን ቅዱሳን እንዴት አከበሯቸው?

ከብሉይ ኪዳን ቅዱሳን አንዱ አብርሃም ነው፡፡ አብርሃም ካንቀላፋ በኋላ ቀጣዩ ትውልድ አብርሃምን እንዴት አከበረው? በስሙስ ምን አደረገ? አብርሃም ለእግዚአብሔር ሕዝብ አባት እንዲሆን የተጠራና የተመረጠ እንደ መሆኑ አብርሃምን “አባታችን” ከማለትና ስለሚታወቅበት ስለ እምነቱ ከመመስከር በቀር÷ በአብርሃም ስም ያደረገው አንዳች ነገር የለም፡፡ ቢያደርግ ኖሮ ግን ስሕተተኛ ስለሚሆን አርኣያውን አንከተልም፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትእዛዝም ሆነ ተመክሮ በሌለውና ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ በራሳችን ልማድ ተመርተን ቅዱሳንን ማክበር እንዲህ ነው ብንል ስሕተት እንጂ ትክክል አይሆንም፡፡

መጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት ይህ ቢሆንም÷ ልማዳችን ሊሻሻል አይገባውም በሚል÷ ግትር ዐቋም የሚያራምዱ ወገኖች እውነቱን ማስተባበል ሲያቅታቸው÷ ጕዳዩን ቅዱሳንን ከመጥላት ጋር ለማያያዝ ይሞክራሉ፡፡ “ጻድቃንን የሚጠሉ ይጸጸታሉ” (መዝ. 33(34)÷21) የሚለውን በመጥቀስም÷ ራሳቸውን የቅዱሳን ወዳጅ ሌላውን ደግሞ የቅዱሳን ጠላት አድርገውም ይቈጥራሉ፡፡ ቅዱሳንን መውደድና ማክበር ግን በዚህ መንገድ አይገለጽም፡፡ ቅዱሳንን በዚህ መንገድ አናክብር ብንልም በመጀመሪያ ቃሉ አይደግፈንም፡፡ ቅዱሳንም ቢሆኑ እንዲህ ያለውን አምልኮኣዊ ክብር አይቀበሉንም፡፡

ከሐዲስ ኪዳን ቅዱሳን መካከል ጳውሎስና በርናባስ ልስጥራን በተባለ ስፍራ ዐንካሳ የነበረውን ሰው በፈወሱት ጊዜ÷ ሕዝቡ እንደ አማልክት ቈጥረው ሊሠዉላቸው በፈለጉ ጊዜ÷ “የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል” ስለ ተባለ÷ ይህ ክብር ይገባናል ብለው አልተቀበሉትም፡፡ “ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ÷ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል ሮጡ÷ እንዲህም አሉ፡- እናንተ ሰዎች ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን፡፡ እርሱ ባለፉት ትውልዶች አሕዛብን ሁሉ በገዛ ራሳቸው ጐዳና ይሄዱ ዘንድ ተዋቸው፡፡ ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትን ወራት ሲሰጠን÷ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም፡፡ ይህንም ብለው እንዳይሠዉላቸው ሕዝቡን በጭንቅ አስተዉአቸው” የሐዋ. 14÷14-17)፡፡

ቅዱሳን በሕይወተ ሥጋ እያሉ የሸሹትንና “ከንቱ ነገር” ሲሉ የጠሩትን አምልኮ ባዕድ÷ ስሙን ለውጠን “ቅዱሳንን ማክበር” ብንለው ያካሄድነው የስም ለውጥ ነው፤ ድርጊቱ ግን አልተለወጠምና ሥራችን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የለውም፡፡ የእግዚአብሔር ቅዱሳን ግን በጸና እምነታቸውና በቀና ምግባራቸው ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡

በጮራ ቍጥር 40 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment