Monday, March 2, 2015

የዘመን ምስክር

በዚህ ዐምድ ለቤተ ክርስቲያን መሻሻልና መለወጥ የተጋደሉ፥ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም መልካም ሥራን የሠሩ አበውን ሕይወትና የተጋድሎ ታሪክ አሁን ላለውና ለቀጣዩ ትውልድ አርኣያ እንዲሆን እናስተዋውቃለን፡፡

ነጋድረስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ
መግቢያ
ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ በኻያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አካባቢ የነበሩ ኢትዮጵያዊ ምሁርና ተራማጅ አስተሳሰብ የነበራቸው ግለ ሰብ ነበሩ፡፡ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ የተወለደው በ1878 ዓ.ም. በአድዋ አቅራቢያ በምትገኝ ማይሚሸም በምትባል መንደር ነው፡፡ የገብረ ሕይወት ባይከዳኝ  አባት ገብረ ሕይወት በተወለደ በዐጭር ጊዜ  ውስጥ ነው የሞቱት፡፡
ገብረ ሕይወት ኤርትራ ውስጥ ምጽዋ አጠገብ ምንኩሉ በተባለ ቦታ በሚገኘው የሲውዲን ሚስዮን (Swedish Mission) ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ጀረጃ ትምህርትን አግኝቶአል፡፡ ምንኩሉ በነበረበት ጊዜ አለቆቹ ከነበሩት መካከል አንዱ ስመ ጥሩ ምሁር አለቃ ታየ ነበሩ፡፡ ከዚህም በመነሣት ይመስላል በኋላ ላይ አለቃ ታየ እና ከንቲባ ገብሩን በተመለከተ የሚከተለውን አስተያየት የሰጠው፡- “ሦስት ዓመት ምሉ አዲስ አበባ ላይ ስቀመጥ እንደነዚህ ሁለት ሰዎች አርጎ መንግሥቱን የሚወድ ሰው አላየሁም፡፡ ይህ ደግነታቸው ግን እስከ ዛሬ ድረስ አልታወቀላቸውም ይመስለኛል፡፡ እጅግ ያሳዝናል፡፡ የነሱን ዕድል ያየ ሰው የኢትዮጽያ መንግሥት ለወዳጁ አይጠቅምም ብሎ ተስፋ ይቈርጣልና።” (ገጽ 15)

አለቃ ታየ እና ከንቲባ ገብሩ ልክ እንደ ገብረ ሕይወት ሁሉ ተራማጅ አስተሳሰብ የነበራቸውና ኢትዮጵያን በዘመናዊነት ጐዳና ስትጓዝ ማየት የሚፈልጉ ነበሩ፡፡ ሆኖም ግን ይህ ምኞታቸው በጊዜው ከደረሰባቸው ተቃውሞና ማኅበረሰቡ ለለውጥ ከነበረው ዝቅተኛ አመለካከት የተነሣ ተዳፍኖ ቀርቷል፡፡
 
በሚስዮን ትምህርት ቤት ትምህርቱ ይሰጥ የነበረው በዐማርኛ ቋንቋ ስለ ነበረ፥ በዚያ ገብረ ሕይወት ዐማርኛ ቋንቋን ሊማር ችሏል፡፡ ሰባት ዓመት ሲሞላው ገብረ ሕይወት በመርከብ ወደ ጀርመን እና ኦስትሪያ ሄዷል፡፡ አንዳንድ ሰነዶች ገብረ ሕይወት በወደብ ቆማ የነበረች የጀርመን መርከብን ሊጐበኝ ወደ መርከቧ እንደ ገባና መርከቧም እንደ ተንቀሳቀሰች ይገልጻሉ፡፡ የመርከቡ ካፒቴን ገብረ ሕይወትን ለኦስትሪያዊቷ ሶሪኔ ያስረከቡት ሲሆን፥ ሶሪኔም እንደ እናት በመሆን ገብረ ሕይወትን አስተምረውታል፡፡ በኦስትሪያ ከሕክምና ጋር የተገናኘ ትምህርት ተከታትሎ በዐሥራ ስምንት ዓመቱ ትምህርቱን ጨርሷል፡፡ በኦስትሪያና በጀርመን በነበረው ቈይታ ከሕክምና ትምህርት በተጨማሪ ለምዕራቡ ዓለም እድገት አስተዋፅኦ ያበረከተውን የምዕራቡን ዓለም የፖለቲካ ኢኮኖሚ ዕውቀት እንዲገበይ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ይታመናል፡፡

ዐጤ ምኒልክ ሐኪም እንዲላክላቸው የጀርመን መንግሥትን በጠየቁ ጊዜ ገብረ ሕይወት ከዶ/ር ስንቲግራፍና ካልስ ጋር ዐሥራ ሁለት ዓመታት ከቈዩበት ኦስትርያ እና ጀርመን የጀርመን ሚስዮን አስተርጓሚ በመሆን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያም ከተመለሱ በኋላ ወደ አንኮበር በመሄድ ሰባት ወራትን በዚያ ያሳለፋ ሲሆን፥ የዐማርኛ ቋንቋ ችሎታቸውንም የበለጠ ማሻሻል ችለዋል፡፡ በአንኮበርም በነበራቸው ቈይታ በጊዜው የዚያ አውራጃ ገዥ ከነበሩት ወኅኒ አዛዥ ይገዙ በሀብቴ ጋር ጥሩ ወዳጅነትን እንዲመሠርቱ አስችሏቸዋል፡፡ ከአንኮበር በኋላ ያቀኑት ወደ ኤርትራ ሲሆን፥ ወደ ዐዲስ አበባም በመመለስ ሦስት ዓመታትን ቈይተዋል፡፡

ዐዲስ አበባ በነበራቸው ቈይታ የዐጤ ምኒልክ አስተርጓሚ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፥ የጀርመን፥ የፈረንሳይና የእንግሊዝኛ ቋንቋዎችን  ይናገሩ ስለ ነበረ፥ ለንጉሡ እጅግ ጠቀሜታ ነበራቸው፡፡  ሆኖም ግን ከእተጌ ጣይቱ ጋር መስማማት ባለመቻላቸው ወደ ሱዳን ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ በሱዳንም የአራት ዓመታት ቈይታ አድርገዋል፡፡

በእንግሊዞች ቅኝ ግዛት በነበረችው ሱዳን ያደረጉት ቈይታ፥ የተለያዩ አመለካከቶችን እንዲያዳብሩና የኢትዮጵያን ሁኔታ ከሱዳን ጋር እንዲያነጻጽሩ እንዳደረጋቸው በገብረ ሕይወት ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ በሱዳን በነበራቸው ቈይታ የኢትዮጵያን ኋላ ቀርነት በተመለከተ በስፋት እንዲያስቡ ሆነዋል፡፡ ሱዳን ቅኝ ግዛት ሆና ብትቈይም ከኢትዮጵያ በተሻለ ሁኔታ የምትተዳደር ነበረች፡፡ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኘው መጽሐፋቸው የሚከተለውን ብለዋል፡-
ከዘመኑ ምሁራን ሁሉ ልቆ የሚታየው ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ውጪ አገር ሄዶ ዘመናዊ ትምህርት ሊቀሥም የቻለው በግል ጥረቱ ነው፡፡ ገና በጮርቃነቱ በመርከብ ተደብቆ ኦስትሪያ በመሄድ የሕክምና ትምህርት አጥንቶ ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡ ተመልሶ ዓለምን ያስደነቀው ግን በሕክምና ጥበቡ ሳይሆን የፖለቲካ ኢኮኖሚን አበጥሮ በማወቁና በተለይም ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ለማዛመድ በመቻሉ ነው፡፡ እንግሊዞች ያስተዳድሯት በነበረችው በሱዳንም የዐጭር ጊዜ ቈይታው ነጻዪቱ ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ከሆነችው ሱዳን ምን ያህል ወደ ኋላ እንደ ቀረች በመገንዘቡ ክፉኛ ታውኮ መጥቷል፡፡

ገብረ ሕይወት ሱዳን እያሉ በኢትዮጵያ ውስጥ የሥልጣን ለውጥ ተከሠተ፡፡ ልጅ ኢያሱ ምኒልክን ተክተው በትረ ሥልጣኑን ያዙ፡፡ ገብረ ሕይወት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈለገው ለውጥ ይመጣል ብለው በማሰብ የመጀመሪያ ጽሑፋቸውን አሳትመዋል፡፡ በጽሑፋቸውም በኢትዮጵያ ውስጥ የማኅበረ-ፖለቲካ ሥርዐት (Socio-political order) ድክመትን በማሳየት በኢያሱ ሊተገበሩ የሚችሉ ለውጦችን አመላክተዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ የበጅሮንድነት ማዕርግን ተቀብለው በቤተ መንግሥት በድጋሚ ማገልገል ጀመሩ፡፡

ሥልጣን በራስ ተፈሪ እጅ ሲወድቅ፥ ገብረ ሕይወት የባቡር ሐዲድ ግንባታን እንዲቈጣጠሩ (የምድር ባቡር ኢንስፔክተር) ኀላፊነትን ተቀብለዋል፡፡ በመቀጠልም የድሬዳዋ ነጋድራስ በመሆን እንዲያገለግሉ ተሾመዋል፡፡ ገብረ ሕይወት ከመሞታቸው በፊት አነስተኛ መጽሐፍ ጽፈው ነበር፡፡ ይህን ጽሑፍ ጳውሎስ መናመኖ የተባለ ወዳጃቸው የአርትዖት ሥራ ከሠራ በኋላ ተፈሪ መኰንን “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” በሚል ርእስ አሳትመዉታል፡፡ ሆኖም ግን ገብረ ሕይወት ብዙም ዕውቅናን ሳያገኙና ሐሳባቸውም በተግባር ሳይውል 33 ዓመት ዕድሜያቸው 1911 ዓ.ም. ዐርፈዋል፡፡ ልዑል ራስ እምሩ “ያን ጊዜ በመላው ኢትዮጵያ እንደርሱ ያለ ዐሥር የሚሞላ ሰው አልነበራትም፡፡” በማለት ገብረ ሕይወትን አድንቀው ጽፈዋል፡፡

የገብረ ሕይወት ሥራዎች
ነጋድራስ ገብረ ሕይወት በሕይወት በኖሩበት ዘመን በተለያዩ ኀላፊነቶች ሀገርን ከማገልገላቸው በተጨማሪ፥ ሀገር ይለውጣሉ ብለው ያሰቧቸውን ሁለት ሥራዎች አበርክተዋል፡፡ የመጀመሪያው ሥራቸው “ዐጤ ምኒልክ እና ኢትዮጵያ” የታተመው 1905 ዓ.ም. አካባቢ ነበር፡፡መንግሥት እና የሕዝብ አስተዳደር” የሚለው መጽሐፋቸው ደግሞ እርሳቸው ከሞቱ በኋላ መጀመሪያ 1916 ዓ.ም.፥ በኋላም በድጋሚ 1953 ዓ.ም. ታትሞ ነበር፡፡ እነዚህ ሁለት ሥራዎች አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ በአንድ ጥራዝ፥ ከኅዳግ ማስታወሻና ከባለሞያዎች ትንተና ጋር በድጋሚ ታትመዋል፡፡ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት በእነዚህ ሁለት ሥራዎቻቸው በነበረው ሥርዐት ላይ ቀጥተኛ እና ጠንካራ ሂስ ሠንዝረዋል፡፡ ጽሑፋቸውን ጠለቅ ብለን ስናነበው በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም አቅጣጫ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ባህላችንን ዘለቅ ብለን በመመልከት መለወጥ ያለባቸው ነገሮች ላይ ሂስን ስንሰነዝርና ከሌሎች በመማር እንደ ሆነ ይጠቊማሉ፡፡ ለምሳሌ፥ ንጉሥን በተመለከተ ያሰፈሩትን እንመልከት፡- “ትምህርት በሌለው ሕዝብ ዘንድ ንጉሥ ማለትና መንግሥት ማለት ትርጉሙ አንድ ነው፡፡ ንጉሣቸው የፈቀደውን ያደርጋል፤ በመላው ሕዝቡ ባሮቹ ናቸው፡፡ … አእምሮ ባላቸው ሕዝቦች ዘንድ ግን መንግሥት ማለት ማኅበር ማለት ነው፡፡ ንጉሣቸውም የማኅበራቸው አለቃ ማለት ነው፡፡” (ገጽ 9-10) ይህ በጊዜው ለኢትዮጵያውያን እንግዳ ሐሳብ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይህ ተራማጅ የሆነ አስተሳሰብ ገብረ ሕይወትን በጊዜው እንዲወቀሡ አድርጎአቸዋል፡፡

“ዐጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ” የተሰኘው መጽሐፉቸው ልጅ እያሱ ሊከተሉት ስለሚገቡ ነገሮች ምክር የሚለግስ ነው፡፡ በልጅ ኢያሱ ባለመርካት በኋላ ላይ እንደ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ድጋፋቸውን ለተፈሪ መኰንን ቸረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኋላ ቀርነት ስላንገበገባቸው፥ በድንቊርናው የሚኖር ሕዝብ ውሎ ዐድሮ ይደመሰሳል ብለው ጽፈዋል፡፡ ይህም እንዳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ሊለወጡ የሚገባቸውን ነገሮች ሁሉ ነቅሰው በማውጣት የማሻሻያ ሐሳቦችን ጠቊመዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል፥ ግብርን፥ ሹሞችን፥ የገንዘብ አስተዳደርን፥ ቋንቋን፥ ወታደርን፥ ሥራን፥ ወዘተ. የተመለከቱ ርእሰ ጒዳዮች ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ጒዳዮች ካልተለወጡና ትኲረት ካልተሰጣቸው አገር እንደማያድግ ተናግረዋል፡፡

አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ በጻፉት የዐፄ ምኒልክ ታሪክ ላይ ፈጸሙ ያሉትን ስሕተት ለማሳየትና ሂስ ለማቅረብ እንደ ጻፉት በሚታመነው “ዐጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ” በተሰኘው መጽሐፍ ስለ ታሪክ አጻጻፍ ያለብንን ጒድለት የሚያሳይና ዛሬ ድረስ እንደ ማእዘን ደንጊያ የሚታይ መርሕ አቅርበዋል፡፡
ታሪክን መማር ለሁሉ ሰው ይበጃል፤ ለቤተ መንግሥት መኰንን ግን የግድ ያስፈልጋል፡፡ የዱሮ ሰዎች ስሕተትንና በጎነትን አይቶ ለመንግሥቱና ላገሩ የሚበጀውን ነገር ያውቅ ዘንድ፡፡ የታሪክ ትምህርት ግን የሚጠቅም የውነተኛ ታሪክ ትምህርት ሲሆን ነው፡፡ እውነተኛንም ታሪክ ለመጻፍ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ የሚከተሉትን ሦስት የእግዚአብሔር ስጥወታዎች ያስፈልጋልና፡፡ መጀመሪያ ተመልካች ልቦና የተደረገውን ለማስተዋል፤ ሁለተኛ የማያደላ አእምሮ በተደረገው ለመፍረድ፤ ሦስተኛ የጠራ የቋንቋ አገባብ የተመለከቱትንና የፈረዱትን ለማስታወቅ፡፡ ያገራችን የታሪክ ጻፎች ግን በነዚህ ነገሮች ላይ ኀጢአት ይሠራሉ፡፡ በትልቁ ፈንታ ትንሹን ይመለከታሉ፡፡ ለእውነት መፍረድንም ትተው በአድልዎ ልባቸውን ያጠባሉ፡፡ አጻጻፋቸውም ድብልቅልቅ እየሆነ ላንባቢው አይገባም፡፡ (ገጽ 1)፡፡

ሁለተኛው የገብረ ሕይወት ሥራ “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” ሲሆን፣ ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ የሚያትት ነው፡፡ ገብረ ሕይወት ነጻነት ያለ ኢኮኖሚ እድገት ዘላቂ ሊሆን እንደማይችል በዚህ መጽሐፋቸው ግልጽ አድርገው አስቀምጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ ዘመናት በነጻነት ብትኖርም፥ በአድዋ ጦርነት ጣሊያንን ማሸነፍ ብትችልም፥ የኢኮኖሚ እድገቷ ግን ኋላ ቀር ነበር፡፡ ይህንም በመረዳት ነው በኻያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያለ ኢኮኖሚ ድገት ነጻነትን ጠብቆ መሄድ አስቸጋሪ መሆኑን ያብራሩት፡፡ እውነተኛ ነጻነት የሚገኘው የራስን መንግሥት በማቋቋም ብቻ ሳይሆን፥ ራስንም በመቻል ጭምር ነው፡፡ ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻ ቢሆንም ራሱን የቻለ አልነበረም፡፡ ይህ ካልተለወጠ እውነተኛ ነጻነት እውን እንደማይሆንና የተገኘውም ነጻነት ዘላቂነት እንደማይኖረው አሳስበዋል፡፡ ሕዝቡ እንዲያድግ የሚፈልግ መንግሥት ትምህርትን ማበረታታት እንዳለበትም ጠቊመዋል፡፡

በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ ገብረ ሕይወት የአውሮፓን እና የጃፓንን ሁኔታ እንደ ምሳሌ በማንሣት ለኢትዮጵያ ምክርን ለግሰዋል፡፡ መጽሐፉ ሰው በሥራ ከተፈጥሮ ጥገኛነት ተላቅቆ ከኋላ ቀር አኗኗር ወደ ተሻለ ሕይወት እንደሚለወጥ ከማስረዳቱም በተጨማሪ፣ ጦርነት የእድገት ፀር መሆኑን ግልጽ በሆነ ሁኔታ ያብራራል፡፡

ሃይማኖት፥ የሃይማኖት ዐርነትና መቻቻል
ገብረ ሕይወት ይኖሩ በነረበት ዘመን የሃይማኖት መቻቻል የሚባለው ዕሳቤ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደ አልነበረም፡፡ የተለየ አመለካከትና ትውፊት የነበራቸው ክርስቲያኖች መናፍቃን ተደርገው ይቈጠሩ ነበር፡፡ ገብረ ሕይወት ግን ከዚህ የተለየ አመለካከት ነበራቸው፡፡ “ዐጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ የሚከተለውን አስፍረዋል፡-
የሃይማኖት ዐርነት ይታወጅ። የሃይማኖት ዐርነት ጥቅም መሆኑ የማያውቅ ብዙ ሰው ይኖራል፡፡ ስለዚህ የሚከተለውን ብናስተውል ደግ ነው፡፡ የአገራችን ሰው የተዋሕዶ ሃይማኖት ከሁሉ ሃይማኖት ይበልጣል ብሎ ያምናል፡፡ በልጦ ግን ምን ረባን? ማንስ ዐወቀው? የአገራችን ካህናት መንግሥት ጠበቃቸው ሁኖ ሌላ ሃይማኖት ሊገባ እንዳይፈቅድ ዐውቀው ሃይማኖታቸውን ለሕዝቡ ሊገልጹለት ዐሳብ የላቸውም፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ እንኳን ተዋሕዶ ማለት ምንድር እንደ ሆነ አይለይ፤ የክርስቲያን ሃይማኖትን አውራ መሠረት የወንጌልን ቃል አያቅም፡፡ ስለዚህ ዐጒል ቀረ፤ የሃይማኖት ዐርነት እስኪታወጅ ድረስም ዐጓጒል ይቀራል፡፡ ለዚህም ነገር ምስክር በሐማሴን እናገኛለን፡፡ በድሮ ዘመን ለዚያች አገር መሃይምንስ ይቅርና ብዙ ቄሶች ሃይማኖታቸውን ሳያውቁ ይኖሩ ነበር፡፡ ጵሮተስታንቶችና ካቶሊኮች ከመጡ ወዲህ ግን ትልቁም ትንሹም የወንጌልን ቃል ዐውቆ በትርጒሙ ይከራከራል፡፡ ካህናትም በላምጣ ቢበዛባቸው ያስተምሩ ጀመር፡፡ በዚህ ምክንያት የሃይማኖት ዐርነት ቢታወጅ ሃይማኖት ይታወቃል እንጂ አያጠፋም፡፡ ደግሞም ባገራችን አንድ የድንቊርና ነገር አለ፡፡ ሃይማኖቱ ተዋሕዶ ያልሆነ ሰው ሁሉ እንደ ርኩስ ይቈጠራል፡፡ ይህም እጅግ ያሥቃል፡፡ አእምሮ የሌለው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ሳያውቅ የእግዚአብሔር ጠበቃ ሊሆን ይወዳል (ገጽ 27፡28)፡፡

በጊዜው ሃይማኖት የሁሉ ነገር መለኪያ ነበር፡፡ ሃይማኖትን ተገን በማድረግ ኢትዮጵያ በለውጥ ጐዳና እንዳትጓዝ ብዙዎች ይጥሩ ነበር፡፡

በዐዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት ትምህርት ቤቶች ስም በጥቅምት 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ቀረበ በተባለው አቤቱታ ላይ እንዲወገዙ ጥያቄ ከቀረበባቸው ታላላቅ ሰዎች ስም ዝርዝር መካከል የነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ስም ይገኛል፡፡ ይህ የሚያመላክተን ገብረ ሕይወት ከሞቱ ከአንድ ምእት ዓመት በኋላም እንኳ የርሳቸው ተራማጅ አስተሳሰብ የሚጐረብጣቸው ቡድኖችና ግለሰቦች እንዳሉ ነው፡፡

ገብረ ሕይወት አንዳንድ ጊዜ ሃይማኖታዊ አመለካከቶቻችንን ያለ አግባብ በመለጠጥ ሁሉም ነገር ከእኛ ቊጥጥር ውጪ አድርገን መመልከታችንንም ነቅፈዋል፡-
ዕውቀት የሌለው ሰው የዝኆንን ቁመትና መብረቅ ሲያይ፥ የትልቅም ነጐድጓድ ጩኸት ሲሰማ የፈጣሪውን ሥራ ያደንቀዋል፤ አስተዋይ የሆነ ሃይማኖተኛው ግን የንብንና የጒንዳንን ትጋት፥ የሥራቸውንም ትክክልነት፥ የሥርዐታቸውን ማማር አይቶ በዚህ ዓለም ፍጥረት ይገረማል፤ ከመብረቅና ከነጐድጓድ ኀይልም ይልቅ የንብንና የጒንዳንን ተኣምር ለፈጣሪው የበለጠ ምስጋና ሁኖ ይታየዋል፡፡ እነዚህንም ሰሎሞን መጽሐፈ ምሳሌ 6፥6፤ 30፥25 ላይ አብራርቶአቸዋል … የአንድ አገር ሕዝብም ይበለጽግ ዘንድ እንዲህ ይሆን ዘንድ ይገባዋል (መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር ገጽ 170)፡፡

ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ወደ ጅቡቲ ተጒዘው ሳለ ሕመም ይጠናባቸውና ሥጋወ ደሙን መውሰድ ይፈልጋሉ፡፡ በዚያ ከሚገኝ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ይቈርባሉ፡፡ ወደ ድሬዳዋ ከተመለሱም በኋላ በድጋሚ ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ይቈርባሉ፡፡ ይህን የተመለከተ አስታማሚ ወዳጃቸው ምን ነው ወዳጄ ብሎ ቢጠይቃቸው፥ ገብረ ሕይወት የሚከተለውን ምላሽ እንደ ሰጡ “ካየሁት ከሰማሁት” የሚለው መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ተጠቅሷል፡-
እኔ ሃይማኖቴ ኦርቶዶክስ ነው፤ ጅቡቲ የወረድኩ ጊዜ በሽታዬ ስለ በረታ ምናልባት የሞትኩ እንደ ሆነ ቈርቤ ልሙት በማለት የኦርቶዶክስም ቤተ ክርስቲያን ጅቡቲ ስላልነበረ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቊርባን የተቀበልኩት ስለዚህ ነው፡፡ ጥቂት ተሸሎኝም ድሬዳዋ ከመጣሁም ከዚያው ከኛው ቤተ ክርስቲያን አስመጥቼ ተቀበልኩ፡፡ ከማናቸውስ ብቀበል ምን የሚያስደንቅህ ነገር አለ፡፡ እኔ የምሻው ያድነኛል ብዬ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ ብቻ ነው፡፡ ሥጋ ቤቶቹ ቢለያዩ ሥጋው ያው የክርስቶስ ነውና የምሻውን አግኝቻለሁ፤ ሌላውን ከትልቅ ነገር አልቈጥረውም፡፡

ይህ የገብረ ሕይወት ምላሽ እኒህ ታላቅ ሰው ለሃይማኖት መቻቻል የነበራቸውን የላቀ ግንዛቤና የተለያዩ የክርስቲያን ቤተ እምነቶች ልዩነቶች ቢኖራቸውም በክርስቶስ አንድ መሆናቸውን የሚያመላክት ነው፡፡

ሥራ
ገብረ ሕይወት አገር የሚለወጠው በሥራ እንደ ሆነ አበክረው ጠቅሰዋል፡፡ በጊዜው የነበረው ማኅበረሰብ በተለይ ታሪክ ጸሓፍያን ታሪክን በሚጽፉበት ጊዜ የሚፈጥሯቸውን ስሕተቶች ከሥራ አንጻር እንዲህ በማለት ነቅፈዋል፡-
የልባቸውን የሚፈጽምላቸው[ን] ንጉሥ ቅዱስ ቅዱስ ይሉታል፡፡ ከድንቊርናቸው ወጥቶ ከፍ ባለ ኅሊና ተመርቶ ስለ ዜጎቹ ልማት የሚጥር ግን ርኩስ፡፡ አሁን ጐዳናንና ድልድዮችን ከሚያስበጅ፥ የጥበብን የማስተማሪያ ቤቶች ከሚከፍት ንጉሥ ይልቅ የመንግሥቱን ጒዳይ ሁሉ ረስቶ ከናዝራዊ ከሌላም ዐይነት መነኩሴ የሚውል ሥራ ፈትተው ለሚኖሩት መነኮሳትም ምግብ ብሎ ብዙ አገሮች የሚጐልት ንጉሥ በነርሱ ዘንድ ይመሰገናል፡፡ (ገጽ 3፡4)

ከላይ እንደ ተመለከትነው ታሪክ ጸሐፍያን፣ ሥራን የሚያበረታታን ንጉሥ በመንቀፍ በተቃራኒው የማይሠራውን ይደግፉ ነበረ፡፡ ገብረ ሕይወት ይህን በግልጽ ተቃውመዋል፡፡ “የሰውም ክብረቱ ሥራና አእምሮ መሆኑን ገና አላወቅንም፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ የሚያውቀውን ወንድማችንን አስማተኛ፥ ደብተራ፤ የጅ ሥራ የሚያውቀውን ቡዳ፥ ፋቂም፥ ሸማኔም እያልን እናዋርደዋለን” (ገጽ 20)፡፡ ከዚህ በተቃረኒ ሀብት ማለት የተከማቸ ሥራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለውጥና ውግዘት
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተለየ ሐሳብ ይዘው ብቅ የሚሉ ሰዎችን ማውገዝ ወይም እንዲወገዙ ማድረግ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ይህ ክሥተት በገብረ ሕይወት ዘመንም የተለመደ ነበር፡፡ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ የሚሆነንን እንጥቀስ፡-
... አንድ ልበ ብሩህ ያበሻ ሰው መሬት ትዞራለች ብሎ ቢያስተምር አሁን በቅርቡ በሐረርጌ በዳኛ ተይዞ አልነበረምን? …  አሁን በ19ኛው መቶ ዓመታት ከክርስቶስ ልደት በኋላ ዐልፈን ኻያኛውን መቶ ዓመት ስንጀምር አንድ ሰው የተዋሕዶን ሃይማኖት ቢነቅፍ ካዲስ አበባ ገበያ ላይ በድንጋይ አልተወገረምን? እስከ ዛሬ ድረስሳ ወደ ሩቅ ሀገር ተሰደው ወደ አበሻችን ከሚመጡት ፈረንጆች ጥቂት ጥበብ ተምረው ያገራቸውን መንግሥት ሊጠቅሙ የሚፈልጉ ወንድሞቻችን ጵሮተስታንት፥ ካቶሊክም፥ መናፍቃን የሌላ መንግሥት ሰላዮች እየተባሉ ሲራቡ ሲከሰሱም እናይ የለምን? የእነዚያንም መከረኞች ስም ስንት ብለን እንቊጠር . . . ፡፡ (ገጽ 14)

ይህ ሐሳብ በጊዜው የነበረው ማኅበረሰብ ለለውጥ ምን ያህል ዝግ እንደ ነበረ የሚያመላክተን ነው፡፡ እጅግ የሚገርመው ነገር ግን ተመሳሳይ ድርጊትን የሚያራምዱ ቡድኖች አሁንም ድረስ መገኘታቸው ነው፡፡

ደግሞም እንደ አገራችን ሰው ትምህርት የሌለው ሕዝብ እውነቱን ሲሰማ አይወድም፤ ቢሰማም አይገባውም፡፡ አንድ ንጉሥ እንዴህ አርጎ ጥሮ ነገሠ፤ ከነገሠም በኋላ በእንዲህ ያለ ምክንያት ይህን ፈጸመ ይህን ተወ፤ በንዴህ ያለም ነገር ወደቀ፤ ወይም ለማ ከሚልዋቸው ይልቅ እገሌ ከሰማይ ወይም ከጠንቋይ እንደዚህ ያለ ትንቢት መጥቶለት ለመንግሥት የተወለደ ሰው መሆኑን ዐውቆ ታውቆ፥ እገሌ ከሰማይ ወይም ከጠንቋይ እንደዚህ ያለ ትንቢት መጥቶለት ለመንግሥት የተወለደ ሰው መሆኑን ዐውቆ ታውቆ እገሌና እገሌ ታጠቁለት፡፡ እገሌና እገሌም ሰይጣን አስቶዋቸው ተዋግተው አሸነፋቸው፤ ነገሠም፤ ከነገሠም በኋላ እገሌ ቅዱስ ወይም ናዝራዊ መክሮት ይህን አደረገ፡፡ (ገጽ 5)
ይባል እንደ ነበረ ጽፈዋል፡፡

ማጠቃለያ
ገብረ ሕይወት ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ ለመለወጥ የጣሩ የኻያኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ ልሂቅ ነበሩ፡፡ ለውጥ ፈላጊ ስለ ነበሩ አንዳንዶች ለኢትዮጵያ ሃይማኖትና ባህል አሥጊ አደርገው ይመለከቷቸው ነበር፡፡ ታሪካችን ለለውጥ የሚነሡትንና ተራማጆችን ጐትቶ በማስቀረት ይታወቃል፡፡ ብዙ የውጪ አገር ታሪክ ሠሪዎችን ታሪክ ስንማር በሥርዐተ ትምህርታችን ውስጥ እንደ ገብረ ሕይወት ያሉ ድንቅ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ መማር አለመቻላችን እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ ይህን ጽሑፍ ደማቆቹ ከተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ ለገብረ ሕይወት የቀረበን መወድስ በመጥቀስ እናጠቃልል፤
ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ምንኛ ተማረ
እሩቅ እያሰበ እርሱ ቅርብ ዐደረ
ያልታደሉ ሰዎች ቀድመው እየመጡ
የደነደነ አንጎል መክረው ሳይለውጡ
ድንቁርናን ታግለው ሳያንደባልሉት
እንደ ተቃጠሉ እንዴት ይግቡ መሬት

ዋቢ መጸሕፍት
ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ፤ ካየሁት ከማስታውሰው፤ አዲስ አበባ፣ አዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ፣ 2001፡፡
ሰሎሞን ጥላሁን እና ሥምረት ገብረ ማሪያም፤ ደማቆቹ ፡-ጸሓያተ ሌሊት፤ አዲስ አበባ፤ 2000፡፡
ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ሥራዎች፤ አዲስ አባባ፤ አዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ፣ 2002
Bahru Zewde, Pioneers of Change in Ethiopia: The Reformist Intellectuals of the Early Twenty      Century. Addis Ababa: Addis Ababa University, 2002.

በጮራ ቍጥር 44 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment